Tuesday, October 1, 2013

ከዝዋይ እስረኞች የተላከ የትግል ጥሪ!!!!

በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በገጠርና በከተማ የምትገኙ የአገራችን ህዝቦች እንዲሁም እዚህ ላይ የተገኛችሁ ዜጎች
---------------------------------------------------------------------------
በአካል ተገኝተን ከእናንተ ጋር በአገራችን እየተካሄደ ስላለው ግፍና ጭቆና ሃሳባችንን መግለጽ ባንችልም ከእናንተና የኛን ድጋፍ ከሚሹ ልጆቻችን ፣ የትዳር አጋሮቻችን ፣ ወንድምና እህቶቻችን ፣ እናትና አባቶቻችን ተለይተን የሰብአዊ መብት ድርጅቶቻችን እንደሚሉት በተደላደለ ሥፍራ ሳይሆን ቅስም ሰባሪ በሆነ አያያዝ ዓመታት ካስቆጠርንባቸው እስር ቤቶች ሆነን ለናንተ ያለንን ታማኝነትና የትግል አጋርነታችንን እንገልጻለን፡፡

ለሰው ልጆች ክብር፣ነጻነት ፣እኩልነት፣ለዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች መከበር ያለን እምነት ዛሬም እንደ ትናንቱ ጽኑ ነው፡፡

ወደ እስር ቤት የተላክነው እናንተ ዛሬ የምታነሱትን ጥያቄ በማንሳታችን ነው፡፡ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች የገነቧቸው ትላልቅ ህንፃዎች የጋረዱት አስከፊ ድህነት ስለሚያሳስበን ነው፡፡ እኛ ባገራችን ነፃነት አጥተን ተዋርደን ስንኖር ባህር ማዶ ተሻግረው የመጡ ባዕዳን እንኳን በነፃነት ከመኖር አልፈው አገራችንን ዘርፈው ወዳገራቸው ሲያግዙ መታገስ አቅቶን ነው፡፡ ገዢዎቻችን ሥልጣንን በህዝብ ይሁንታ ሳይሆን በጉልበት ቀምተው ያንን በመጠቀም ሚሊዮኖችን እያስራቡ ያገርን ሀብት አሟጠው ካገር በማስወጣት የበይ ተመልካች ሲያደርጉን ዝም ማለት ባለመቻላችን ነው፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ስለመብትና እኩልነት እየለፈፉ በተግባር ግን በዜጎች መካከል በዘር ፣ በሃይማኖትና በአመለካከት ዓይን ያወጣ አድልኦ እያደረጉ በህዝቦች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ጠፍቶ ወደርስ በርስ ጦርነት ጥርጊያ መንገድ ሲከፈት አይተን እንዳላየ ማለፍ ባለመፈለጋችን ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በሥልጣን ላይ በቆየ ቁጥር ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን በአደባባይ ረግጦ ወደለየለት አምባገነንነት ሲለወጥ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አላስችል ብሎን ነው፡፡

ይህ የአብዛኛው የአገራችን ህዝብ ፍላጎትና ስሜት ነው፡፡ ነገር ግን ገዥዎቻችን ሺዎችን በማሠር ሚሊዮኖች ፈርተው ዝም እንዲሉ የወጠኑትን ውጥን ሰብራችሁ ዓላማውን አክሽፋችሁ አይበገሬነታችሁን ለመግለጽ አደባባይ በመውጣታችሁ ኮርተንባችኋል፡፡
ውድ የአገራችን ህዝቦች!በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ልናስታውሳችሁ እንወዳለን፡፡ ለነፃነታችን የምናደርገው ትግል በሠላምና በሠላማዊ መንገድ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ክፋትን በደግነት፣ጭካኔን በርህራሄ፣ራስ ወዳድነትና ሙስናን ለወገን በማሰብና በመቆም፣ትንኮሳን በትዕግስት በመተካት በታላቅ ኢትዮጵያዊ ዲሲፕሊንና ጨዋነት ትግሉን እንድትቀጥሉ እናሳስባችኋለን፡፡ የነገይቱ ምቹ አገር፣መልካም ዜጋና የዳበረ ሥልጣኔ ባለቤት ለመሆን የሁላችን ሰላማዊ ትግል ወሳኝ ነው፡፡ በቀልና አመጽን በማስወገድ የነፃነት የነፃነት ጉዞአችንን በአንድነት እንቀጥል፣ከድቅድቁ ጨለማ ጀርባ ለልጆቻችን የምናወርሰው ብሩህ ዓለም አለና፡፡
የተባበረ ሠላማዊ የነፃነት ትግሉ አምባገነንነትን አስወግዶ ሰብአዊ ክብርን በሚያስጠብቅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስኪተካ ድረስ ይቀጥላል የሚል የፀና እምነት አለን፡፡ እኛም ከናንተ ጋር ነን፡፡

መስከረም 12,2006 ዓ.ም

ዝዋይ ከሚገኙ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች
1. በቀለ ገርባ
2. ኦልባና ሌሊሳ
3. ዘሪሁን ገ/እግዚአብሄር
4. ናትናኤል መኮንን
5. ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)
6. አንዱአለም አያሌው

(ምንጭ አንድንት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት)

No comments:

Post a Comment