Sunday, August 27, 2017

በሳዑዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን በግዳጅ እንዳይባረሩ ጥሪ ቀረበ

BBN news August 26, 2017
በሳዑዲ አረቢያ ያለ መኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሀገሪቱ እንዳይባረሩ ጥሪ ቀረበ፡፡ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ስደተኞቹን ለማባረር መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ድምጹን ያሰማው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ መንግስት በስደተኞቹ ላይ የማባረር እርምጃ እንዳይወስድ ጠይቋል፡፡ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በሀገሪቱ ያለ ህጋዊ ወረቀት የሚኖሩ ስደተኞች እንዲወጡ የሶስት፣ ቀጥሎም ሁለት ጊዜ የአንድ ወር ቀነ ገደብ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ መንግስት ከትላንት በስቲያ እንዳስታወቀው፣ ስደተኞችን በኃይል የማስወጣት እርምጃ ሊወሰድ ነው፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ ሳዑዲ ይፋ ያደረገችውን ቀጣይ እርምጃ የምትፈጽም ከሆነ፣ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ ወረቀት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የእርምጃው ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በኃይል ሊወሰድ የሚችለውን እርምጃ ተከትሎ በርካቶች ሊጎዱ እንደሚችሉ ያስገነዘበው የሰብዓዊ መብት ተሟጋጅ ድርጅቱ፣ በተለይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የፖለቲካ ጠብ ያላቸው ስደተኞች ይበልጥ ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉም አስጠንቅቋል፡፡ በሳዑዲ አረቢያ የኢኮኖሚ ስደተኞች የመኖራቸውን ያህል የኢትዮጵያ መንግስትን ሽሽት ወደ ሳዑዲ የተሻገሩ መኖራቸውን ያወሳው ድርጅቱ፣ ሳዑዲ ያለችውን እርምጃ የምትወስድ ከሆነ፣ የእነዚህ ስደተኞች ዕጣ ፈንታ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል፡፡
ስደተኞቹ በኃይል ተገድደው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚደረግ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ለህይወታቸው አስጊ የሆነ ነገር እንደሚጠብቃቸው የገለጸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፣ ምናልባትም የኢትዮጵያ መንግስት ግድያን ጨምሮ መሰል እርምጃዎችን ሊወስድባቸው እንደሚችል ከወዲሁ ስጋቱን ገልጿል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሳዑዲ አረቢያ በኃይል ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ከተደረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል በመንግስት ግድያ የተፈጸመባቸው መኖራቸውንም ሂውማን ራይትስ ዎች በመግለጫው አትቷል፡፡ ስለ ስደተኞች ብሎ የሳዑዲ አረቢያን መንግስት የሚማጸነው የድርጅቱ መግለጫ፣ ከሳዑዲ ባለስልጣናት በኩል እስካሁን ምላሽ አላገኘም፡፡ ሳዑዲ ያወጣችውን የምህረት ቀነ ገደብ ተከትሎ፣ ከ50 ሺህ የማይበልጡ ወረቀት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መግባታቸው በመንግስት በኩል ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

source BBN news August 26,2017