Friday, August 21, 2015

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዋናው ጸሀፊ ቢሮ አፈትልኮ የወጣው ጥብቅ መረጃ (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

ዛሬ ለኢሳት የደረሰው ጥብቅ መረጃ 11ዓመታትን ወደ ኋላ በትዝታ ወሰደኝ:: ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዋናው ጸሀፊ ቢሮ አፈትልኮ የወጣው መረጃ እንደሚያጋልጠው ለሰላም አስከባሪ 11 ሺህ የኢትዮጵያ ሰራዊት የሚከፈለው ደምወዝ ከ90 በመቶ በላይ የህወሀት ካዝና ውስጥ የሚገባ ነው:: በወር 13 ሚሊዮን ዶላር(500 ሚሊዮን ብር ገደማ) የወታደሩን ገንዘብ ህወሀቶች ይቀራመቱታል:: ይህን ጉዳይ የመንግስታቱ ድርጅት የሚያውቀው ይመስለኛል:: ለዚህም እኔ የተሳተፍኩበትን የሰላም አስከባሪ ዘመቻ አጋጣሚ በአስረጂነት ማሳየት እችላለሁ:: 
እኤአ በ2003-2004 በመንግስታቱ ድርጅት የበላይነት: በአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚነት ከተላከው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ጋር ወደ ቡሩንዲ ሄጄ ነበር:: ወደ 18 የምንሆን አስተርጓሚዎች ከ8 ወር እስከ 1 ዓመት ቆይተናል:: ዝርዝሩን ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ:: ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የተፈጸመውን የህወሀቶችን ለከት ያጣ ስግብግብነትን ላጫውታችሁ::
በዘመቻው በUN ደረጃ ወርሃዊ ደምወዝ ከ1000 ዶላር ያላነሰ: የመስክ ክፍያ በቀን 60 ዶላር: የበዓል ክፍያ በአንድ በዓል 1000 ዶላር: የላብ መተኪያ: .....በጣም ብዙ ዓይነት ክፍያዎች ነበሩት:: አብዛኛው የሰላም አስከባሪ ሰራዊት አባላት በተስፋ ነበር ወደ ቡሩንዲ የተጓዘው:: እዚያ እንደደረስን ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኑ:: ቃል የተገባው: በውል የታሰረው( የሚገርመው የውሉን 3 ኮፒዎች አንሰጥም ብለው እዚያው መከላከያ ግቢ ቀርቷል:: መንግስትን አምነን ነው የተጓዝነው) ክፍያ የለም:: በወር 40 ዶላር ለኪስ እየተሰጠን: ምግብና መጠጥ በአላሙዲን እየቀረበልን: እየበላንና እየጠጣን መኖር ብቻ ሆነ:: ከኢትዮጵያ ሌላ የደቡብ አፍሪካና ሞዛምቢክ የሰላም አስከባሪ ሃይሎችም ለተመሳሳይ ዘመቻ ቡሩንዲ ገብተዋል:: ለእነሱ የሚገባቸው ክፍያና ጥቅማጥቅም ሀገራቸው በባንክ አካውንታቸው የሚገባላቸው ይህንንም የሚያረጋግጥ ደረሰኝ በየወሩ እንደሚደርሳቸው በነበረን ቅርበት ተረዳን:: እኛ ግን ምንም የለም:: ስንጠይቅ ኢትዮጵያ ይጠራቀምላችኋል የሚል መልስ ከማስፈራሪያ ጋር ይሰጠናል:: በእኛና በሌሎቹ ለተመሳሳይ ዘመቻ በመጡ ሀገራት የሰላም አስከባሪው ዘመቻ አባላት መሃል ያለው የኑሮ ሁኔታ የሰማይና የምድርን ያህል የሚራራቅ ነበር:: በህወሀት ስግብግብነት የተነሳ በጣም በሚያሳፍር የኑሮ ገጽታ መቀለጂያ ሆንን:: በሰራዊቱ ውስጥ ቅሬታው ስር ሰደደ:: ተስፋው ጨለመ:: በወር 40 ዶላር እየወረወሩ እዚያ ይጠራቀምላችኋል በምትል ከቃል ያለፈ በደረሰኝ ያልተረጋገጠች ተስፋ ብቻ ይዘን በብስጭት ገፋን:: በመሃል ሲብስብን አስተርጓሚዎች ተነጋግረን ቡጁምቡራ በሚገኝ የUN ጽ/ቤት አቤቱታ ልናቀርብ ሄድን:: የተሰጠን ምላሽ ተስፋችንን ይበልጥ ገደለው:: "ስለ እናንተ የተፈራረምነው ከመንግስታችሁ ጋር በመሆኑ አይመለከተንም:: መንግስታችሁን ጠይቁ::" የሚል ወሽመጥ የሚቆርጥ ምላች ተሰጠን::
በመሃሉ መለስ ዜናዊና ሳሞራ የኑስ ሊጎበኙን ቡጁምቡራ መጡ:: ሳሞራ ሰብስቦን ችግር ካለ ንገሩኝ አለ:: ሰራዊቱ የክፍያው ነገር ሲያንገበግበው ስለከረመ ሳሞራን ሲያገኝው በየተራ እየተነሳ ጠየቀው:: ሳሞራ ጀት ሆነ:: ባለጌ አፍ እንዳለው ያረጋገጥኩት የዚያን ዕለት ነው:: የኢትዮጵያን የችግር መዓት ሲዘረዝር: መዓት ሲያወራ ቆየና " ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም:: የሌሎችን እያያችሁ እንደነሱ እንሁን ማለት አደጋ አለው:: እዚህ ገንዘብ ምንም አያደርግላችሁም:: በብር ኢትዮጵያ እየተጠራቀመላችሁ ነው:: ለሸርሙጣ ፈልጋችሁ ከሆነ ኢትዮጵያ ስትመለሱ ትደርሱበታላችሁ....." እያለ ወረደብን:: ሰራዊቱ ቅስሙ ተሰበረ:: ብዙ የምንሰራው ስራ አለ:: ትምህርት ቤት እንገነባለን:: ....እያለ ተንዘባዘበ:: የዚያን ዕለት ሌሊት ከአምቦ የመጣ የሰራዊቱ አባል በታጠቀው መሳሪያ ራሱን አጠፋ:: ባርቆበት ነው የሚል ሪፖርት እንድናዘጋጅ በህወሀት የጦር አዛዦች መመሪያ ተሰጥቶን የውሸት ሪፖርት አዘጋጅተን ለUN ተላከ:: ይህ የሆነበትም ራሱን ካጠፋ UN ካሳ አይከፍልም:: እርግጠኛ ነኝ በዚህ የተገኘውን በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ዶላር ህወሀቶች ኪስ ገብቷል::
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ እየተጠራቀመላችሁ ነው እየተባለ ስንሸነገል የከረምንበትን ገንዘብ ሊሰጡን ተዘጋጁ:: ለአንድ የሰላም አስከባሪ ሰራዊቱ አባል በትንሹ ከ250ሺህ ብር በላይ ወይም በወቅቱ ምንዛሪ 10ሺህ ዶላር መከፈል ነበረበት:: በጣም የሚያሳፍር የሚያስደነግጥ ነገር ነበር የጠበቀን:: እንደ ቆይታ ጊዜ ከ15ሺህ እስከ 25ሺህ የኢትዮጵያ ብር ሰጥተው አሰናበቱን:: ከእያንዳንዳችን ከ200ሺህ ብር በላይ ህወሀቶች ተቀራመቱት:: ...በሌላ ጊዜ በስፋት እመለስበታለሁ::

Source Mesay Mekonnen Facebook status 

Thursday, August 13, 2015

የኤልያስ ገብሩ ቆይታ ከጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋር (ዝዋይ እስር ቤት)

በኤልያስ ገብሩ
  • ታገሉ! ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ከዝዋይ እስር ቤት)
  • ተመስገን ደሳለኝ ስለሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ፍርድም ሀሳቡን ሰንዝሯል
Temesgen Desalegn Fteh newspaper editor
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
ቦሌ አካባቢ ብርዱ ጠንከር ያለ ነበር፡፡ ከቦሌ ብራስ ወደሚሊኒየም አዳራሽ በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ ወንዱም ሴቱም በፍጥነት ይራመዳል፡፡ ከታክሲ በሁለቱም አቅጣጫዎች የወረዱ ሰዎች ወደመደበኛ ሥራቸው ለመግባት ብሎም የግል ጉዳያቸውን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር – ከትናንት በስትያ ሰኞ (ነሐሴ 04 ቀን 2007 ዓ.ም) ጥዋት 1፡45 ሰዓት፡፡
እኔ እና ወዳጄ አቤል ዓለማየሁ ወደከአዲስ አበባ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደሚገኘው ዝዋይ እስር ቤት አምርተን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን እና ተመስገን ደሳለኝን ለመጠየቅ በዚህ ቀን ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡ አቤል ከቀጠሯችን 20 ደቂቃ ዘግይቶ፣ ቦሌ ጫፍ ደረሰና ወደቃሊቲ መናሃሪያ ሁለት ታክሲዎችን በመጠቀም ደረስን፡፡ ወደዝዋይ የሚጭኑ ሚኒባስ ታክሲዎች እና ‹‹አባዱላ/ዶልፊን›› የሚል መጠሪያ የተቸራቸው የህዝብ ማመላለሻ መኪኖች ቢኖሩም በተለምዶ ‹‹ቅጥቅጥ›› የሚባለውን መካከለኛ አውቶቡስ ምርጫችን አደረግን – የትራፊክ አደጋን በመስጋት፡፡
የተሳፈርንበት አውቶቡስ፣ ከቃሊቲ ትንሽ ወጣ ካለ በኋላ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ በእስር ላይ የሚገኙትን የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “ልማቱን አሳዩኝ” ሲለን ከከተማ ወጣ እያደረግን የምነሳየው… [እውነት ግን፣ በከባድ እስር ላይ መሆናቸው የሚገመተው አቶ አንዳርጋቸው ‹ልማቱን አሳዩኝ› ይሏቸዋልን?!]›› ሲሉ ለቪኦኤዋ ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው የገለጹትን፣ የአዲስ አበባ አዳማ አዲሱ የፍጥነት መንገድ (Express way)ን ተቀላቀለ፡፡ በዚህ መንገድ ሁለታችንም ሄደን አናውቅም ነበር፡፡ ሆኖም እስከዛሬ ካየኋቸው የመኪና መንገዶች በደረጃው ከፍ ያለ ይመስላል፡፡ [በሀገራችን አምረው የተሰሩ የመኪና መንገዶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የመቦርቦር፣ የመፈረካከስ፣ ውሃ የማቆር ችግሮች ገጥሟቸው እንዲሁም ከመንገዱ ዳር እና ዳር የሚገኙ የብረት አጥሮች ተሰርቀው፣ ተገጭተው፣ ተጨረማምተው፣ ተነቃቅለው … አደጋ ሲያደርሱና የተለመደ የሬንጅ የመለጠፍ ሥራ ሲሰራላቸው በገሃድ የምናየው ሀቅ መሆኑን ማስታወስ ግን የግድ ይላል] ይሄኛው መንገድ ከጠቀስኳቸውና ካልጠቀስኳቸው ችግሮች ምን ያህለ ነጻ ነው? ለሚለው ትክክለኛ መስክርነት መስጠት ያለበት ለእውነት የቆመ የዘርፉ ባለሙያ ቢሆንም በኢህአዴግ ‹ልማት› ላይ የጥራት መተማመኛ ማግኘት እጅግ ከባድ መሆኑን ግን አምናለሁ፡፡ አስፋልቱ ለፍጥነት አመቺ መሆኑን ግን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
በሶስት ሰዓታት ጉዞ ዝዋይ በመድረስ ምሳ ከበላን በኋላ ወደእስር ቤቱ የፈረስ ጋሪ መጠቀም ግዴታችን ነበር፡፡ አቧራማው አስቸጋሪ መንገድ፣ ከፊሉ ደቃቅ አሸዋ መልበስ ጀምሯል፡፡ የእስር ቤቱ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ፣ በፊት ውብሸትን ለመየጠቅ ስመጣ ከማውቀው ተፋጥኗል፡፡ አንዱ የሥርዓቱ “የልማት ውጤት” እስረኛ ማብዛት አይደለ ታዲያ?!
ከቀኑ 7፡30 ሰዓት ላይ የምንጠይቀውን እስረኛ በማስመዝገብ ተፈትሸን ገባን፡፡ ሁለት እስረኛ በአንዴ መጠየቅ ስለማንችል እኔ ተመስገን ጋር፣ አቤል ደግሞ ውብሸትን ለመጠየቅ ተስማምተን ነበር፡፡ አቤል ውብሸትን ከጠየቀ በኋላ እንደምንም ብሎ ተመስገንን ለመጠየቅ ጥረት እንደሚያደርግ ግን ቀድሞ ነገረኝ፡፡
ተመስገን እና ውብሸት የታሰሩበት ዞን ስለሚለያይ እኔ እና አቤል ሌላ የውስጥ ፍተሻ ካደረግን በኋላ መለያየታችን ግድ ነበር፡፡ የእስር ቤቱ ፖሊሶች የሚኖሩበትን ጉስቁልና ያጠቃቸው፣ መኖሪያ ቤቶችን አልፌ መጠየቂያው ጋር ደርሼ የታሳሪው ስም ያለባትንና በፖሊሶች የምትጻፈዋን ቁራጭ ወረቀት እስረኛን ለሚጠራው ፖሊስ ሰጠሁትና በአጣና እንጨት ርብራብ በተሰራው መጠየቂያው አግዳሚ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ከቅርብ ርቀት የፖሊሶች ማማ ይታያል፡፡ መሳሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ማማው ላይና ከማማው ሥር በዛ ብለው ተቀምጠው ያወጋሉ፡፡ አብዛኞቹ ፖሊሶች ከላይ የለበሷት እና “Federal prison” የሚል የታተመባት አረንጓዴ ዩኒፎርምም በፀሃይ ብዛት ነጣ ወደማለት ደርሳለች፡፡ አንዱ ፖሊስ መጣና ከእኔ በትንሽ ሜትር ራቅ ብሎ ተቀመጠ፡፡ ‹‹አዳማጭ ነው›› አልኩ በልቤ፡፡ ወደፊት ለፊቴ ወደሚታየኝ የእስር ቤት ግቢ አማተርኩ፡፡ ለእይታ የሚጋብዝ አንዳች ነገር አጣሁ፡፡ የተበታተኑ ዛፎች፣ ቅርጽ አልባ ሳሮች፣ አስታዋሽ ያጡ አረሞች፣ ግድግዳ እና ጣራቸው በቆርቆሮ የተሰሩ የእስረኛ መኖሪያዎች፣ …ብቻ ጭርታ እና ድብታ የወረረው የግዞት መንደር ይመስላል፡፡
ከአንደኛው የእስረኛ ቆርቆሮ ቤት ጣሪያ ላይ ሁለት ተለቅ ተለቅ ያሉ ሙቀት ማቀዝቀዣዎች ይሽከረከራሉ፡፡ ወደፖሊሱ ዞሬ ‹‹ለሙቀት ነው?›› አልኩት ወደ ጣራው በመጠቀም፡፡ ‹‹አዎ፣ ወባ አደገኛ ነው›› አለኝ፡፡ ‹‹እስረኞች ሲታመሙ እንዴት ይሆናሉ?›› ስል ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡ ‹‹ያው እዚሁ ይታከማሉ›› አለኝ ድምጹን ቀሰስ አድርጎ፡፡ የእኔም ሆነ የእሱ ልብ፣ በማረሚያ ቤቱ (በእነሱ አጠራር) በቂ ህክምና እንደማይሰጥ ግን ያውቃል ብዬ አሰብኩ፡፡ ቀጭኑ ፖሊስ፣ ‹‹ለወባ ህመም ምግብ ወሳኝ ነው›› አለኝ አስከትሎ፡፡ ‹‹በቂ ምግብ የለም ማለት ነው?›› ስል ድጋሚ ጠየኩት፡፡ ‹‹በፊት በፊት አቀራረቡ ዝም ብሎ ነበር፤ ሙያ ባሌላቸው ሴቶች ነበር የሚሰራው፡፡ አሁን ግን ለውጥ አለ›› አለኝ፡፡ ‹‹ምን አይነት ለውጥ? ጥቂትም ቢሆን ታስሬ፣ ለእስረኞች የሚቀርበውን በጣም ደረጃውን ያልጠበቀ ምግብ አይቻለሁ›› አልኩት፡፡ ‹‹በፊት ጥቁር ጤፍ ነበር የሚቀርበው፤ አሁን የነጭ ጤፍ እንጀራ ነው የሚበሉት፤ እስረኞች ችግር የለባቸውም፤ ባለሙያ ሴቶችም ናቸው የተቀጠሩት …›› ‹‹(ውስጤ አላመነምና) ለእስረኛ የነጭ ጤፍ እንጀራ እያቀረባችሁ ነው?!›› …‹‹አዎ›› ብሎ ሊያብራራልኝ እያለ ከታች ከርቀት ‹‹አረንጓዴ ኮፊያ፣ ቲ-ሸርትና ስካርፍ ያደረገ ሰው አየሁ፡፡ ትኩረቴን ከፖሊሱ አዙሬ ቁልቁል ተመለከትኩ – ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነበር፡፡ ተሜም፣ ረጋ ብሎ በራስ በመተማመን መንፈስ ወደመጠየቂያው ሥፍራ ቀረብ ብሎ ጠያቂውን ለማወቅ ጥረት አደረገ፡፡ ሳየው አንዳች የሀዘን ስሜት ውስጤ ገባ፡፡ ቆሜ ጠበኩት፡፡ ፈገግ እያለ መጣና ተጨባብጠን አራት አምስቴ ያህል ተቃቀፍን፡፡ ‹‹በዚህ በጸሐይ ለምን መጣህ?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡ ከአቤል ጋር መምጣታችንን፣ እሱ ውብሸትን ሊጠይቀው መሄዱን ነገር ግን ከቂሊንጦ በኋላ እስከአሁን ዝዋይ ድረስ መጥቼ ባለመጠየቄ የጸጸት ስሜት ውስጤ እንዳለ ገለጽኩለት፡፡ ‹‹መንገዱ ረዥም ነው፣ ባትመጡም እረዳለሁ›› ካለ በኋላ፤ ‹‹ምን አዲስ ነገር አለ?›› በማለት ፊት ለፊት በእንጨት አጥር ተከልለን በመቀመጥ ጨዋታችንን ቀጠልን፡፡
‹‹አሁን ምን እየሰራችሁ ነው?››፣ ‹‹ክስህስ እንዴት ሆነ?››፣ ‹‹አዲስ ጋዜጣ ለማቋቋም ለምን ጥረት አታደርጉም?›› ከተመስገን በተከታታይ የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ አጠር አጠር አድርጌ መለስኩለት፡፡ የጋዜጣ /የመጽሔት ህትመትን ድጋሚ መጀመር የግድ አስፈላጊ መሆኑን ግን ተመስገን አጽንኦት የሰጠበት ጉዳይ ነበር፡፡ …ስለተወሰኑ ጋዜጠኞችና የዞን 9 ጦማሪያን ከእስር መፈታት፣ ስለኦባማ የአዲስ አበባ ጎብኝት፣ በቂሊንጦ ዞን አንድ ከእነአብበከር አህመድ፣ ጦማሪ አቤል ዋበላና ዘላለም ክብርት ጋር ስለነበረው ቆይታ፣ እሱ ወደዝዋይ ከወረደ በኋላ እኔም በዚያ ዞን ገብቼ በነበረበት ጊዜ እነአቡበከር፣ አቤልና ዘላለም እሱን በተመለከተ ስለነገሩኝ ነገሮች ሳቅ እያልን አወጋን፡፡
ሰፊ ውይይት ያደረግነው በሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ በቅርቡ ከ7 እስከ 22 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ፍርድን በተመለከተ ነበር፡፡ ‹‹እኛ ከሙያ ጋር በተያያዘ ነው የታሰርነው፡፡ ታስረንም እንወጣለን፡፡ ከባዱ የሙስሊሞቹ እስር ነው፡፡ ኢህአዴግ እውነተኛ ሰላም ከፈለገ እነአቡበከርን በነጻ መፍታት አለበት፡፡ እኔ የእነሱ መከላከያ ምስክር ሆኜ ምስክርነቴን ሰጥቻለሁ፡፡ በወቅቱ ዘንግቼው ያልተናገርኩት አንድ ነገር ነበር፤ አሁን ሳስበው ትንሽ ይቆጨኛል – በተናገርኩ ብዬ፡፡ ያኔ (በምስክርነት ጊዜ)፣ ‹የኮሚቴዎቹ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ነበር ወይስ አልነበረም?› የሚለው ጥያቄ በራሱ መነሳት አልነበረበትም፡፡ እንቅስቃሴያቸው፣ ሰላማዊ ባይሆን ኖሮ እንዴት ሶስት ዓመት ሙሉ በክስ ሂደት ይቀጥላል?! ሰላማዊ ስለሆኑ እኮ ነው፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት ምንም ያልተፈጠረው፡፡ እስኪ በእነሱ አንድ የተሰበረ መስታወት አለ?! ቅንጣት የወደመ ንብረት አለ?! የማንንስ ሕይወት አጠፉ?! በእነሱ የተፈጠረ አንድም ነገር የለም፡፡ ጥያቄያቸው ኃይማኖታዊ እንጂ ፖለቲካዊ አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ ቢሆን ኖሮ ትግሉ አቅጣጫውን ይቀይር ነበር፡፡ ‹የመጅሊስ አመራሮችን ካለመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንምረጥ!› ነው አንዱ ሰላማዊ ጥያቄያቸው፡፡ ያው ምስክር ስትሆን ከዚህም ከዚያ ጥያቄ ሲነሳ ስለምትዘናጋ መመስከር ያሰብከውን ነው ቅድሚያ የምትሰጠው እንጂ አሁን የምልህን ያኔ ብገልጸው በጣም ደስ ይለኝ ነበር …›› በማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ከታሪክ አኳያ፣ በሁለቱ ትልልቅ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ስለነበረው ግንኙነት በዝርዝር የራሱን ምልከታ እና ሀሳብ ደጋግሞ አወጋኝ፡፡ ኃይማኖታዊ መቻቻል ነበር ወይስ አልነበረም? የሁለቱም እምነት ተከታዮች ጉርብትና ነበራቸው ወይስ አልነበረባቸውም በሚሉት አንኳር ጉዳዮችም የራሱን አቋም አንጸባረቀልኝ፡፡
ኡስታዝ አቡበከር አሕመድን አስመልክቶም አንድ ጥሩ ምሳሌም አንስቶልኝ ነበር ተመስገን፡፡
‹‹አሁን ባለሁበት ዞን፣ በአንድ የወንጀል ክስ ግብረ-አበር ተብለው አምስት ዓመት የተፈረደባቸው አንድ ቄስ አሉ፡፡ እኚህ ቄስ ለጠበቃ የሚከፍሉት አጥተው የጠበቃ ክፍያ የፈጸመላቸው አቡበከር እንደሆነ ነግረውኛል››
እኔም ፣ በህዳር ወር ቂሊንጦ ዞን አንድ በነበርኩበት ጊዜ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር፣ ስለአቡበከር ሰምቼ ነበር፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡- አንዱ እነአቡበከር ይገኙ በነበረበት ዞን 1 8ኛ ቤት ውስጥ የቀጠሮ እስረኛ ነበር፡፡ ዋስትና ይጠየቅና በዚህ ክፍል ውስጥ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ አንድ የናጠጡ ሀብታም (ልጃቸው 22 አካባቢ እጅግ ዘመናዊ ሆቴል አለው) ጋር ጠጋ ብሎ ለዋስትና የሚሆን ብር ተጨንቆ በአክብሮት ይጠይቃቸዋል፡፡ እሳቸውም ‹‹እኔም እንደአንተው እስረኛ እኮ ነኝ!›› በማለት ይመልሱለታል፤፡፡ ልጁም ያዝናል፡፡ ይህ ጉዳይ አቡበከር ጆሮ ይገባና ለልጁ የሚስፈልገውን የዋስትና ብር ከፍሎ ልጁን ከእስር እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ እንግዲህ፣ ከሁለቱ እውነተኛ ምሳሌዎች በመነሳት፣ አቡበከር ለወገኖቹ ሃይማኖትን መሰረት ሳያደርግ፣ በሰብዓዊነት ደግ መሆኑን እንማራለን፡፡
ከተመስገን ጋር በነበረን ሰፋ ባለ የጨዋታ ጊዜ፣ ከጎኔ የነበረው ፖሊስ በተመስጦ ቢያዳምጥም፣ አንዴም አላቋረጠንም ነበር፡፡ …ስለ 100% ቱ የዘንድሮ ምርጫ ፍጻሜ፣ በሰሞኑ በአፋር ክልል ስለደረሰው የድርቅ አደጋ፣ በአይ ኤስ አሸባሪ ቡድን ስለተቀሉና ስለተገደሉት ኢትዮጵያኖች፣ ድርጊቱን በማውገዝ በመስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ ስለተፈጠረው ረብሻ፣ ጉዳትና እስር ተመስገን የራሱን አተያይ በስሜት ተውጦ የግሉን ሀሳብ አብራራልኝ፡፡ በተጨማሪም፣ አይ ኤስ ያንን ድርጊት፣ ያንን ጊዜ መርጦ አደረገ ያለበትን የራሱን የተለየ (ከማንም ያላደመጥኩትን፣ ተጽፎም ያላነበብኩትን) ሀሳብ አጋራኝ፡፡ የተለየ ሃሳብ በመሆኑም ‹‹አሃ!›› ብያለሁ፡፡
ከተመስገን በጣም የገረመኝ፣ የማስታወስ ችሎታው ነበር፡፡ በጥቅምት ወር፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ‹‹ጥፋተኛ›› በተባለበት ማግስት ጥዋት አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ልጠይወቅ ሄጄ በማያመች ሁኔታ ውስጥ ሆነን አብዮትን አስመልክቶ የተለዋወጥናቸውን ሃሳቦችን፣ እንዲሁም ከአቤል ጋር ቂሊንጦ ስንጠይቀው ያነሳናቸውን ሀሳቦች ድጋሚ በማስታወስ በዚህ ቀን ለተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች የውይይት ማጠናከሪያ ሀሳብ ሲያደርጋቸው አስተውያለሁ፡፡
ለተመስገን አሁን ስለሚገኝበት ዞን ሁኔታ ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ቀደም ሲል ከእነውብሸት ጋር አብሮ እንደነበረ ጠቅሶ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ገመና›› በሚል ርዕስ በእስር ቤት ውስጥ ስላወቀው ነገር ሁለት ተከታታይ ጽሑፎችን ካወጣ በኋላ ወደዚህ ዞን መዘዋወሩን ይገልጻል፡፡ አሁን ባለበት ክፍል 80 የሚሆኑ እስረኞች አብረውት አሉ፡፡ ብዙዎቹ ከደቡብ ክልል የመጡ ናቸው፡፡ ከእሱ ጋር አንድም የፖለቲካ እስረኛም ሆነ ጋዜጠኛ አብሮት የለም፡፡ [አቶ በቀለ ገርባ ከወራቶች በፊት የ3 ዓመት ከ7 ወር የእስር ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ከዝዋይ እስር ቤት በተፈቱ ማግስት ተመስገን ከባድ ወደሆነው ወደዚህ ዞን መሸጋገሩን ነግረውኝ ነበር] አሁን ባለበት ዞንም ከእሱ ጋር እስረኞች እንዳያወሩ እና እንዲያገልሉት በዘዴ ተደርጓል፡፡ ከእሱ ጋር በቅርበት ሆነው የሚያወሩ ካሉ፣ እንደትልቅ ተስፋ በሚጠብቁት አመክሯቸው ላይ እንደመፍረድ ይቆጠራል እንደተመስገን አባባል፡፡ ‹‹በዚህ ጉዳይ ማናቸውም ላይ አልፈርድም፤ ከእኔ ጋር አውርተው የአመክሮ ጊዜያቸውን እንዲያጡ አልሻም፡፡ ግን እንዲህ ያደረጉት ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ቢሆኑ ኖሮ ይሰማኝ ነበር፡፡›› ሲል ያለበትን ከባድ ሁኔታ ያስረዳል፡፡
‹‹ማንበብ፣ ማጸፍስ ትችላለህ?›› ሌላኛው ጥያቄዬ ነበር፡፡ ‹‹መጽሐፍ አይገባም ተልክሏል፤ ያነበብኳቸው ጥቂት ልብወለድ መጽሐፍቶች አሉ፡፡ መጻፍ ትንሽ ጀምሬ በእስረኞች በኩል ተጠቁሞ የጻፍኩት ተወሰደ፡፡ ሁለት ሶስቴ ለመጻፍ ሞክሬ ነበር፡፡ ግን ተመሳሳይ እርምጃ በመወሰዱ ተውኩት፡፡›› ይላል ተመስገን፡፡ ‹‹ቀኑን እንዴት ነው የምታልፈው?›› የሚለው የመጨረሻ ጥያቄዬ ነበር፡፡ ‹‹ሁለት የማውቃቸው የአዲስ አበባ ልጆች አሉ፤ ጫናውን ችለው ያናግሩኛል፡፡ ከእነሱ ጋር ቼዝ እጫወታለሁ፡፡ የእግር ኳስ ፕሮግራም የሚተላለፍባቸው ቻናሎች ቢኖሩም መገለሉን አስበውና ደስ ስለማይለኝ ወደክፍሌ እገባለሁ›› የሚለው የተመስገን መልስ ነበር፡፡
ተመስገን አቤልን ከርቀት አይቶት ‹‹ያ አቤል ነው አይደለ?›› አለኝ፡፡ ዞሬ አየሁት፣ አቤል ውብሸትን ጠይቆት ከርቀት ወደመውጪያው በር እየሄደ ነበር፡፡ ‹‹ግን እንዴት አስገቧችሁ?፤ ይመልሱ ነበር እኮ›› አለኝ፡፡ አቤልም ተመስገንን ተመስገንም አቤልን ማግኘት ፈልገው ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ አቤል አንዱን ፖሊስ እንደምንም አናግሮ ተመስገንን ሊጠይቅ መጣ፡፡ ተቃቅፈው ተሳሳሙ፡፡ የሶስትዮሽ ጨዋታችንን ለግማሽ ሰዓት ያህል አደራነው፡፡ ተመስገን ከታሰረ በኋላ የግራ ጆሮው እንደማይሰማለት እና ወገቡም ሕክምና በማጣቱ አሁንም ድረስ እንደሚያመው አልሸሸገንም – ‹‹እዚህ ያለው መድኃኒት ፓናዶል ብቻ ነው›› በማለት፡፡ አያይዞም ‹‹ሰው መጥቶ ሲጠይቅህ ደስ ይላል፤ ጥሩ እንቅልፍ ትተኛለህ፤ግን የመንገዱን ርቀት ሳስበው ሰው ባይመጣ እላለሁ›› አለን በድጋሚ፡፡
የእስረኛ መጠየቂያ ጊዜ መጠናቀቁን ፖሊሶች ነገሩንና ተቃቅፎ መለያት ግድ ሆነ፡፡ ‹‹አይዞህ የምትባል አይደለህምና ሰላም ሁን›› አልኩት፡፡ ‹‹ምን መልዕክት አለህ?›› ስል የመጨረሻ ጥያቄዬን ሰነዘርኩለት፡፡ ተመስገንም ‹‹ታገሉ!›› ሲል መለሰና በመጣበት መንገድ ቻው ብሎን እርምጃውን ቀጠለ፡፡ ሲሄድ አራት እና አምስት ጊዜ ያህል ዞረን አየነው፡፡ ስለገኘነው ደስ ቢለንም በሳሮች መካከል ባለው መንገድ ወደታሰረበት ክፍል ሲያመራ ማየት ዳግመኛ የመረበሽ እና የማዘን ስሜት በውስጤ ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ስሜቱ በጣም የሚገባው በቦታው ላይ ሲገኙ ነው!
ተመስገን፣ ያመነበትን ሀሳብ በድፍረት ስለጻፈ ነበር በኢ-ፍትሃዊነት ሶስት ዓመት እስር የተፈረደበት፡፡ ሰው መታሰሩ ሳያንስ፤ ከቤተሰቡ፣ ከወዳጁ፣ ከዘመዱ፣ ከጓዳኞቹ እርቆ እንዲታሰር ማድረግ ሌላ ቅጣት ነው! ሰው መታሰሩ ሳያንስ፣ ህክምና መከልከሉ፣ በሌሎች እስረኞች እንዲገለል መደረጉ፣ መጽሐፍ ማንበብ እና የግል ማስታወሻዎቹን እንዳይጽፍ መከልከሉ ይሄም ሌላ ቅጣት ነው! ሰው ግን በስንቱ ይቀጣል?! እንዲህም ሆኖ፣ ትናንት የምናውቀው ጋዜጠኛ ተመስገን፣ አሁንም ድረስ ያ ያመነበትን የመናገር ድፍረቱ፣ መንፈሳዊ ብርታትና ጥንካሬው አብሮት አለ!!! አካል ቢታሰር ህሊና መቼም አይታሰር!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
Source ecadforum.com

Wednesday, August 12, 2015

አለቃዎ ሳይሆን ቅን ህሊናዎ የሚያዝዎትን በመፈፀም መልካም ዜጋ ይሁኑ!

መልካም ዜጋ ማለት ምን ማለት ነው?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ በርካታ መጻሕፍት መፃፍ ይቻላል፤ መሠረተ ሀሳቡን ግን በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ማቅረብ ይቻላል።
መልካም ዜጋ ኢፍትሃዊ ተግባር ሲፈፀም “እኔ ምናገባኝ?” አይልም። መልካም ዜጋ “ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ”፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶም አይብቀል”፤ “እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም” እና በርካታ መሰል ምሳሌዎችን አይሰማም። መልካም ዜጋ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ከነፃና ቅን ህሊናው ጋር ታርቆ ይኖራል።
የህወሓት አገዛዝ፣ መልካም ዜጋ ማለት የመንግሥት ሥልጣን የያዘን ማንኛውም አካል ማክበርና በታማኝነት ማገልገል ተደርጎ እንዲተረጎምለት ይሻል። ፍትህ የሚያዛባ መንግሥትን መቃወም የመልካም ዜጋ አቢይ ተግባር መሆኑ የዘመናችን ወጣት እንዳይገነዘብ ያደርጋል። በተለይ ባለሙያዎች የሚያገለግሉትን አገዛዝ ባህርይ እግምት ውስጥ ሳያስገቡ የተቀጠሩበትን ሥርዓት በታማኝነት ማገልገል የዜግነት ግዴታቸው አድርገው እንዲወስዱት ይወተውታል።
ኦስካር ግሮኒንግ ( Oskar Groening)የዘጠና አራት ዓመት ሽማግሌ ጀርመናዊ ነው። በጀርመን የሂትለር አገዛዝ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁሃን የተፈጁበት አሽዊትስ ካምፕ ውስጥ የሂሳብና ጽህፈት ሠራተኛ ነበር። ኦስካር ግሮኒንግ አንድም ሰው አልገደለም፤ አንድም ሰው አልገረፈም። እሱ ሂሳብ ነው የሠራው። ሆኖም በደል ሲፈፀም አይቶ “ምናገባኝ” ብሎ አልፏልና ከብዙ ዓመታት በኋላ ተከሶ በቅርቡ የ4 ዓመታት እስር ተፈርዶበት በሁለት እግሮቹ መቆም በማይችልበት በ 94 ዓመቱ በእርጅናውና በመጦሪያው ዘመን ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ፊት ተዋርዶ እስር ቤት ወርዷል።
በአንፃሩ ኦስካር ሽንድለር (Oskar Schindler) በጀርመን ናዚ ወቅት ሂትለር ይመራው የነበረው የናዚ ፓርቲ አባልና ሰላይ ነበር። ሆኖም ግን የሥርዓቱን ኢሰብዓዊነት ሲረዳ እዚያው የናዚ ፓርቲ ውስጥ ሆኖ አለቆቹ ያዘዙትን ሳይሆን ቅን ህሊናው ያዘዘውን በምስጢር መሥራት ጀመረ፤ በዚህም የ 1200 ሰዎችን ሕይወት ታደገ። ከጦርነቱ በኋላ ኦስካር ተከብሮ የኖረ በርካታ የክብር ስሞችና ሽልማቶች የተሰጠው በመልካም አርዓያነቱ የሚጠቀስ ሰው ሆነ።
በአገራችንም በአምስት ዓመታቱ የፋሽስት ወረራ ወቅት ስመ ጥር የውስጥ አርበኞች ነበሩ። ከነፃነት በኋላ ባንዶች እንኳን በውስጥ አርበኝነት ለመጠራት ያደርጉት የነበረውን እሽቅድድም ልብ በሉ።
በህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴግ፣ ደህዴግ እንዲሁም አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ ያላችሁ ወገኞች ኦስካር ግሮኒንግን ወይንስ ኦስካር ሽንድለርን መምሰል ትፈልጋላችሁ? በህወሓት ፋሽስታዊ አገዛዝ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ውስጥ ያላችሁ ወገኖቻችን ነገ የምትዋረዱበትን ሥራ መሥራት ነው የሚበጃችሁ ወይስ ዛሬ ከህሊናችሁ ጋር ታርቃችሁ እየኖራችሁ ነገ ደግሞ ልጆቻችሁና የልጅ ልጆቻችሁ የሚኮሩበትን ተግባር መፈፀም ትፈልጋላችሁ? በአገዛዙ የስለላ ድርጅቶች ውስጥ ያላችሁ ወገኖች ስማችሁን በመልካም ማስጠራት አትሹምን?
ልቦና ያላችሁ ወገኖቻችን ሆይ! መልካም ዜግነት ሎሌነት አይደለም። መልካም ዜግነት ለቅን ህሊና ታማኝ መሆን ነው። መልካም ዜግነት ሲመች በገሀድ፤ ሳይመች በምስጢር ኢፍትሃዊነትን መዋጋት ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በማናቸውም መንገድ በአገዛዙ የፓለቲካ፣ የጦርና የፓሊስ ተቋማት፤ በስለላም ይሁን በሌላ የሲቪል ሙያ የተሰማራችሁ ወገኖቻችን የታዘዛችሁትን ሳይሆን ቅን ህሊናችሁ የሚጠይቃችሁን በመሥራት ኢፍትሃዊ፣ ፋሽስታዊና ዘረኛ የሆነውን የህወሓት አገዛዝን እንድታዳክሙ ጥሪ ያቀርብላችኋል። በአገዛዙ ውስጥ ሆናችሁ እያለም የምትሠሩት ለሀገርና ለትውልድ የሚጠቅም በርካታ ሥራ አለ። የአገዛዙን ምስጢራዊ ሰነዶች ለአርበኞች ግንቦት 7 እንዲደርስ ማድረግ፤ አሊያም በማኅበራዊ ሚዲያዎች (ለምሳሌ ፌስ ቡክና ቱተር) ማሰራጨት ትልቅ ዋጋ ያለ ሥራ ነው። የህወሓት ፀረ-አገር እና ፀረ-ሕዝብ ፕሮጀክቶችን ማሰናከል ሌላ ትልቅ ሥራ ነው። በነፃነት ታጋዮች ላይ የሚደረጉ ዱለታዎችን ማክሸፍ ሕይወት አድን ሥራ ነው። ድርጅቶቹ ውስጥ ሆኖ ድርጅቶቹን ማዳከም የመልካም ዜግነት ግዴታ መወጣት ነው።
በሥርዓቱ ውስጥ ሆነው ኢፍትሃዊነትን ለማጋለጥ እና ሥርዓቱን ለማዳከም ለሚጥሩ ወገኞች አርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ ክብር አለው፤ ደህንነታቸው እንዲጠበቅም የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ፀረ ኢትዮጵያ እና ፀረ ሰው የሆነውን የህወሓትን ሥርዓት ለመጣል እና በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና የሀገር አንድነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለማጽናት ከሥርዓቱ ውስጥም ውጭም የሚደረገውን ትግል እናፋፍም።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
source www. patriotg7.org

Tuesday, August 4, 2015

ቴድሮስ አድሃኖም “ኢህአዴግ ቂመኛ አይደለም” አሉ

አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ በቂም ስለሚፈጸው ወንጀል አልተጠየቁም
የኢህአዴግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም “ኢህአዴግ ቂመኛ አይደለም” ሲሉ ከቪኦኤ አማርኛው ክፍል ባልደረባ ትዝታ በላቸው ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታወቁ። ሚኒስትሩ ድርጅታቸውን ከደርግ ጋር በማነጻጸር ከቂም የጸዳ እንደሆነ ሲያስረዱ ጋዜጠኛዋ አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ በቂም በቀል ስለተፈጸመውና እየተፈጸመ ስላለው ግፍ ጥያቄ አላቀረበችም። ሚኒስትሩ ኢህአዴግ በህግ የበላይነት ስለማመኑ በመረጃ አልተሞገቱም
በዘር፣ በብሄርና በጎሳ ላይ ተንጠልጥሎ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆየው ኢህአዴግ፣ በ፩፱፰፫ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በገሃድ አማርኛ ተናጋሪዎችን ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በማናከስ፣ ቂም በማቋጠር፣ የስርአተ ማህበሮችን ችግሮች ከነፍጥ ጋር በማያያዝ እያላከከባቸው፣ “ነፍጠኛ” የሚል ስም በመስጠት የህዝብ ንብረት በሆነው መገናኛ የጥላቻ ዘመቻ በማራገብ የደረሰው ጥፋት ሰፊ ነው። የኢህአዴግ የቀድሞ አመራሮች በተለያዩ አጋጣሚዎቸ ይፋ እንዳደረጉት ይህንኑ አማርኛ ተናጋሪ የህብረተሰብ ክፍል ለይቶ የማጥፋትና የማጥቃት እቅድ በፕሮግራም ደረጃ የተቀመጠ ነው።
ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ለኅልፈት የተዳረጉት “አማራው ተሟጋች አጣ” በሚል ስለ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። በቂም ተወልዶ፣ በቂም እዚህ የደረሰው ኢህአዴግ ከዚህ ከማይደበቀው ታሪኩ ፊት ለፊት ቆሞ “እንዴት ቂመኛ አይደለሁም ሊል ይቻለዋል” የሚሉ ወገኖች ቴድሮስ አድሃኖምን ለመታዘብ ጊዜ አልወሰዱም።
“ደርግ ያለ ርህራሄ ፷ ሚንስትሮችን ረሸነ፣ የውሻ ያህል እንኳን ክብር አልሰጣቸውም” እያሉ የሰው ልጅ ክቡርነትን በመጥቀስ ቂም ኢህአዴግ ቤት እንደሌለ ለትዝታ በላቸው ያስረዱት የኢህአዴግ ሹመኛ፣ “ኢህአዴግ በመሆኔ ደስ የሚልኝ ቂመኛ ድርጅት ባለመሆኑ ነው” ሲሉ ተመጻድቀዋል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከተማ ሽርሽር እንደሚወጡና የአዳማን ልማት ተመልክተው መደሰታቸውን የጠቆሙት ቴድሮስ ይህ ሁሉ ኢህአዴግ ቂመኛ ድርጅት ላለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ላብቶፕ ተሰጥቷቸው መጽሃፍ ጽፈው ወደማጠናቀቁ መዳረሳቸውን እግረመንገዳቸውን ጠቁመው ያለፉት ቴድሮስ፣ ይህ ሁሉ የፓርቲያቸውን ርኅሩኅነት የሚያሳይ መሆኑን አመላክተዋል። በሌሉበት የሞት ፍርድ የተበየነባቸው አቶ አንዳርጋቸው ይቅርታ የመጠየቅ መብት አላቸው፣ ግን ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቀም ብለዋል። በቤተሰብና በጠበቃ ለመጎብኘት ፈቃድ መከልከሉን አስመልክቶ “ትንሽ የሚጠየቃቸው ጥያቄዎች ሰለነበሩ ነው” ሲሉ አቃልለው መልስ ሰጥተዋል። አሁን ወደ መደበኛ ማረሚያ ቤት በመዘዋወራቸው ሁሉም ነገር እንደሚመቻች ገልጸዋል።
ከሰኔ፩፮ ቀን ፳፩፮ ጀምሮ ባልታወቀ ስፍራ ታስረው የቆዩት አቶ አንዳርጋችው ጽፈውታል የተባለውና በቅርቡ ለንባብ ይበቃል የተባለው መጽሃፍ “ስልጣን ላይ ያለው አካል በአቶ አንዳርጋቸው ስም ያዘጋጀው ነው” ሲል ኢሳት ይፋ ያላደረጋቸውን ምንጮች ጠቅሶ አመልክቷል። ኢሳት እንዳለው በመጽሃፉ ዝግጅት ላይ ህላዊ ዮሴፍ በረከት ስምዖን፣ አባይ ጸሃዬ እንደተሳተፉበት አመላክቷል። የመጽሃፉ ይዘት በኤርትራ ያለውን ትግል የማንኳሰስና የግንቦት ሰባት አመራሮች ስብእና ላይ ያተኮር መሆኑንም አስታውቋል።
እሳቸው ብቻ ተናጋሪ በሆኑበት ቃለ ምልልስ ሚኒስትሩ አስቂኝ ትንተና በመስጠት የቅዳሜውን የቪኦኤ ዝግጅት መዝናኛ አድርገውት ነበር። “እኛ” አሉ አቶ ቴድሮስ፣ “እኛ መቶ በመቶ ምርጫ አላሸነፍንም። ይህ መስተካከል አለበት። ያሸነፍነው በተወዳደርንበት ቦታ ብቻ ነው” ትዝታ ታዳምጣለች ቴድሮስ ቀጠሉ። ኢህአዴግ የአራት ድርጅቶች ጥምረት መሆኑን አስረዱ። የተቀሩት “አጋር” እንኳን ሲሉ ያልጠሯቸውን የጎሳ ድርጅቶች “ተቃዋሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ” አሏቸውና አረፉት።
የጋምቤላ፣ የቤኒሻነጉል፣ የአፋር፣ የሶማሌ ከልል ኢህአዴግ ሰራሽ /እንደራሴ/ ወይም ድቃይ ድርጅቶች “እንደ ሌሎች ተቃዋሚዎች ድምጻቸውን አውጥተው አይቃወሙንም እንጂ የማንግባባቸው ጉዳዮች አሉ” በማለት እነሱ በሚያስተዳደሩት ከልልሎች ውስጥ ኢህአዴግ አለመወዳድሩን በማሰረዳትና በመተንተን ኢህአዴግ መቶ ከመቶ ምርጫውን አሸነፈ ሊባል እንደማይቻል አመላክተዋል።
አዲስ አበባን አስመልክቶ ኢህአዴግ ትንሽ ከስልሳ በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘቱን፣ ተቃዋሚዎች አርባ በመቶ የሚጠጋ ድምጽ አግኝተው እንደነበር፣ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተቃዋሚዎች ያገኙት ድምጽ ሲደመር ኢህአዴግ ካገኘው በላይ ቢሆንም አንድ ባለመሆናችው ሊያሸንፉ አለመቻላቸውን፣ ያመለከቱት የህወሃቱ አባል ቴድሮስ፣ “ተቃዋሚዎች የተበጣጠሱ ናቸው፤ እኛ አንድ ልናደርጋቸው አንችልም። አንድ ቢሆኑ በርግጠኛነት ከሰላሳ በመቶ በላይ መቀመጫ ማግኘት ይችላሉ” ሲሉ የቀጣዩን ምርጫ ውጤት ተንብየዋል።
ሚኒስትሩ ባልተለመደ መልኩ በመቻቻል፣ በመፋቀር፣ በመረዳዳት፣ በህብረት አገር ለማሳደግ ሁሉም ወገኖች ሊሰሩ እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል። “አዲስ የዴሞክራሲ ግንባታ በመሆኑ ብዙ እናበላሻለን” ሲሉ ችግሮች ስለመኖራቸው ያልሸሸጉት አቶ ቴድሮስ፣ ስለመተባበር ጥሪ ቢያቀርቡም የአርበኞች ግንቦት ፯ ሃይል ታጋይና ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋን በስም በመጥራት ወደ ኤርትራ ማቅናታቸውን ጠቁመው “የሚያመጣው ነገር የለም። እርግጠኛ ነኝ የሚፈይደው ነገር የለም። ዜሮ፣ ፕሮፓጋንዳ ከመሆን ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም” ሲሉ አጣጥለዋቸዋል። እሳቸው ይህንን ቢሉም ኤርትራ የመሸገው የአርበኞ ግንቦት ፯ ሃይል በተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘሩን፣ ጉዳት ማድረሱን፣ ቁጥራቸው ከአርባ በላይ የሚሆኑ የአየር ሃይል አባላት ከዱ ስለመባሉ ኢህአዴግ በይፋ ሲያስተባብል አልተደመጠም።
ምንጭ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ