Monday, June 29, 2015

የኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝትን የሚቃወም ሰልፍ ተጠራ

ኢሳት ዜና (ሰኔ 22 2007 ዓም)
በሚቀጥለው ወር በኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉት የአሜሪካ ፕሬዘዳንትን ጉዞን በመቃወም የፊታችን አርብ በዚህ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ከተማ በሚገኘው “ ሁዋይት ሀውስ ‘’ የተቃውሞ ሰልፍ መጠራቱን አዘጋጆቹ ገለጹ ።
በዋሺንግተን ከተማ ዙሪያ በሚገኘው የወጣቶች ግብረ ሀይል የተዘጋጀው የተቃውሞ ሰልፍ ፕሬዘዳንት ኦባማ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲያስቡበትና እንዲሰርዙት የሚጠይቅ መሆኑ ታውቋል።
ፕሬዘዳንቱ በቀጣዩ ወር በኢትዮጽያ የሚያደርጉት ጉብኝት ይፋ መደረግን ተከትሎ የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተቃውሞ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ የሚኖራቸው ቆይታ የተሳሳተ መልክት እንዲኖር ያደርጋል በማለት ድርጅቶቹ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ከሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶቹ በተጨማሪም የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ አቋሙን በሚገልጽበት ርዕሰ-አንቀጽ ፕሬዘዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ ተችቷል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሬዘዳንት አባማ በምስራቅ አፍሪካ በሚያደርጉት ጉዞ በአለም አቀፍ የጸጥታና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚያድርጉ ገልጸዋል።
ይሁንና በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት ፕሬዘዳንቱ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ቆይታ የተሳሳተ መልክትን ያስተላልፋል በሚል ተቃውሞአቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።
የፊታችን አርብ የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍም እነዚህን ጉዳዮች በስፋት እንደሚያንጸባርቅ የሰልፉ አዘጋጆች አስረድተዋል።
ነዋሪነታቸው በዚሁ በዋሺንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ የሆኑ ኢትዮጵያውያንም በእለቱ በነቂስ በመውጣት በሰልፉ እንዲገኙ አዘጋጆች ጠይቀዋል።
ምንጭ ኢሳት ዜና 

Tuesday, June 23, 2015

የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የታፈኑበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከዓርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በወያኔ ከሰነዓ አለም አቀፍ አውሮፓላን ጣቢያ ታፍነው ከተወሰዱ በዛሬው ዕለት ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ. ም፣ አንድ ዓመት ይሞላቸዋል። የወያኔ አረመኔዎች ይህን ዓይነት የውንብድና ተግባር ሲፈጽሙ በከፍተኛ ደረጃ ያሰሉት፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማፈን፣ ንቅናቄው ብሎም ሕዝቡ፣ ለዕኩልነት፣ ለፍትህና ለነጻነት፣ የሚያደርገውን ትግል ለማዳከምና ከተቻለም ደግሞ ለማጥፋት እንደሆነ፣ ምንም የማያጠራጥር ጉዳይ ነው።
ለመሆኑ የወያኔዎች ስሌት በምን ያህል ትክክል ነበር ?
ባለፈው አንድ አመት ውስጥ፣ ወያኔ በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የፈጸመው የውንብድና አፈና ተግባር፣ ንቅናቄያችን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሐገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባለው ሕዝብ ልብ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ሌላው ቀርቶ ከአፈናው በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ንቅናቄያችንን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ወገኖች በአደባባይ ወጥተው፣ ” እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ” በማለት አቶ አንዳርጋቸውና ንቅናቄው ለሚታገሉለት ሕዝባዊና ሐገራዊ ዓላማ መቆማቸውን በግልጽ አሳይተዋል። እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በሐገር ውስጥ፣ በምድር ላይና በውጭ ሐገር የሚገኘውን የንቅናቄያችንን አካላት ተቀላቅለዋል። ቀደም ሲል በንቅናቄያችን በተለያዩ ደረጃዎች ይሰሩ የነበሩ ዓባላቶች ከአፈናው በኋላ ለትግሉ ያላቸውን ቁርጠኝነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምረዋል።
የአቶ አንዳርጋቸውን አፈና ተከትሎ፣ የንቅናቄው አመራር መሰረታዊ የትግል እንቅስቃሴዎቹን በስፋትና በጥልቀት በመፈተሽ አስፈላጊውን ማሻሻያዎችና ማስተካካያዎችን አድርጓል። ንቅናቄያችን አቶ አንዳርጋቸው ለረጅም ጊዜ የደከሙለትን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ የመታገለን ጥረት አሳክቶ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዓርበኞች ግንባር ጋር ሙሉ ለሙሉ ተዋህዷል። ከዚህም በተጨማሪ የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን ጨምሮ፣ ከሌሎች አምስት በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋራ በጥምረት ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሷል።
በሌላ በኩል ያለፈው አንድ አመት የወያኔ የዘረኛ ዓምባገነን ቡድን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን የአፈና፣ የግድያ፣ የዕስርና የድብደባ ውንብድና ተግባር አጠናክሮ የቀጠለበት ዓመት ነበር ። ለዚህም ጸረ ሕዝብ ተግባሩ፣ በባህርዳር ከተማ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሰውን ግድያ፣ በሰላም እንታገላለን ብለው ይንቀሳቀሱ የነበሩትን የአንድነትና የመኢሀድ ድርጅቶች ማፍረስ ብቻ ሳይሆን፣ ዓባሎቻቸው ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ የድብደባና የዕስር ወንጀል መጥቀስ ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በኦሮምያ፤ በአፋር፤ በጋምቤላ፤ በኦጋዴን፤ በትግራይና በደቡብ ክልሎች ይህ ነው የማይባል አፈና፤ ግድያና የሕዝብ መፈናቀል በሰፊው አከናውኗል:: ከምርጫው ጋር ተያይዞም በአደረበት ስጋት የተነሳ በርካታ፣ በተለይ ወጣቶች ላይ፣ የመደብደብ፣የማዋከብ የዕስርና የግድያ ተግባር የፈጸመው በዚሁ አቶ አንዳርጋቸውን ከአፈነበት ቀን ጀምሮ በተቆጠረው የአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነበር። በጣም የሚገርመው ለራሱ አመቻችቶ ያዘጋጅውን ምርጫ እንኳን ሙሉ በሙሉ አሸነፍኩ ብሎ ከአወጀም በኋላም፣ ከምርጫው በፊት በሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ወንጀል አጠናክሮ መቀጠሉ ያለበትን የስጋትና ጭንቀት ደረጃ የሚያሳይ መረጃ ነው ።
የወያኔ በራስ የመተማመን ደረጃ ከመቼውም ወቅት ይልቅ እጅግ አሽቆልቁሎ የታየውም ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነበር። በሐገር ውስጥ ይነሳብኛል ብሎ በሚያስበው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ስጋት ምክንያት ይህን ስጋት ለመቀነስ በአንድ መንገድም ይሁን በሌላ ይረዱኛል ብሎ ያሰባቸውን በአካባቢው የራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ያላቸውን ቀደም ሲል ወቀሳ ቢጤ እንደመሰንዘርም ዕልህም እንደመጋባትም ይዳዳቸው የነበሩትን መንግስታት ባለሥልጣኖች በመማጸንና ሐገር ውስጥ በመጋበዝ ማንነቱን አበጥሮ ለሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአደባባይ ወጥተው ወያኔ ያልሆነውን ነው ብለው ምስክርነት እንዲሰጡለት ማድረጉ የወያኔ ስጋት የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ ሌላው መረጃ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ንቅናቄያችን አቶ አንዳርጋቸውን አፍነው ለወያኔ የሸጡትን የየመን ባለሥልጣኖች ድርጊት በሚመለከት በጊዜው በሰጠው መግለጫ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ “ጊዚያዊ ጥቅምን በማየት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዕኩልነት፣ ለፍትህና ለነጻነት የሚያደርገውን ትግል ከወያኔ ጋር በቀጥታም ሆን በተዘዋዋሪ በመተባበር ለማፋን መሞከር፣ ታሪካዊ ስህተት መስራት ነው!” እንዳለው ሁሉ፣ ዛሬም የሌሎች መንግስታት ባለ ሥልጣኖች እንደ ትላንትናዎቹ የየመን ባለሥልጣኖች ጊዚያዊ ጥቅምን ብቻ በማየት ሌላ ታሪካዊ ስህተት እንዳይደግሙ ከወዲሁ ለማሳሰብ ይወዳል።
በንቅናቂያችን እምነት ከዚህ በላይ በጥቂቱም ቢሆን ለማሳየት እንደተሞከረው ያለፈው አንድ ዓመት ያሉት መረጃዎች በሙሉ የሚያሳዩት ወያኔ አቶ አንዳርጋቸውን በማፈን ለማዳከም ያሰበው ትግል ይበልጥ ተጠናክሮና ተቀጣጥሎ በርካታ አንዳርጋቸውዎችን ከማፍራቱም በላይ ብዙዎች ለነጻነታቸው መተኪያ የሌላትን ህይወታቸውን እስከመስጠት የሚያደርስ ዕልህ ውስጥ ገብተዋል። ወያኔ እንዳሰበውና እንዳሰላው ትግሉ መዳከም ሳይሆን መሬት እያያዘና እየተጠናከረ በመምጣቱ የወያኔ ስጋት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየጨመረ ሄዷል። ይህም ሁኔታ የዛሬ አንድ ዓመት በፊት ወያኔ አቶ አንዳርጋቸውን ሲያፍን ያሰላው ስሌት እጅጉኑ የተሳሳተ እንደነበረ በግልጽ አረጋግጧል። የወያኔ የአፈና ተስፋ ገና በአፈናው ማግስት እንደ ጧዋት ጤዛ ተኗል። ከአለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በመላው ሀገሪቷ ተጠናክሮ የምናያቸው የወያኔ የጭካኔ እርምጃዎች የሚያመለክቱት ይህንኑ ስጋትና ጭንቀት ነው። የወያኔ የቅዥትና የስጋት የዛፍ ላይ እንቅልፍ፣ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ተሸጋግሮና ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ንቅናቄያችን፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ ለዕኩልነት ለፍትህና ነጻነት የሚደረግ ትግል፣ በተለይ እንደወያኔ ባለ ዘረኛ አምባገነን ቡድን በበላይነት በሚዘወር ሐገራዊ ሁኔታ ውስጥ፣ ምን ያህል ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን አስቀድሞ ጠንቅቆ ያውቃል። ይህም ሆኖ ግን ባለፈው አንድ ዓመት፣ የትግል ጓዳችን የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው በወያኔ እጅ ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ እየደረሰባቸው ያለውን መከራና ስቃይ እንዲሁም ይህ ሁኔታ በቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ ያስጀመረውን የጭንቀት ዘመን፣ ለአንድ ሴኮንድም ቢሆን መዘንጋት አይችልም።
ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 በአቶ አንዳርጋቸው ላይ በአፈናው የተነሳ የደረሰው መከራና ስቃይ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ለፍትህ ለዕኩልነትና ለነጻነት በመቆማቸው በወያኔ አረመኔዎች ቁም ስቅላቸውን የሚያዩት በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ሰቆቃ የሚያበቃው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ በሚያደርገው ሁለ ገብ ትግል በመሆኑ ማንኛችንም በአቶ አንዳርጋቸውም ሆነ በሌሎች ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እንደራሳችን ጥቃት አድርገን የሚሰማን ወገኖች በሙሉ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከታፈኑበት አንድ አመት ወዲህ የተጀመረውን ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ አጠናክረን ወደ ውጤት ደረጃ በማድረስ መጭው ዘመን የሕዝብ የፍትህ የእኩልነትና የነጻነት ተስፋ የሚለመልምበት ፣ የወያኔ አምባገነን ሥርዓት እድሜ የሚያጥርበት ዘመን እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ንቅናቄያን ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ክብር ለፍትህ ለእኩልነትና ነጻነት መስዋትዕነት ለከፈሉና እየከፈሉ ላሉ ታጋዮች!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
አርበኞች ግንቦት7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ
ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም.
Source www.patriotg7.org

Tuesday, June 9, 2015

ምርጫ ሲባል፣ መሳይና አስመሳይ (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

ምርጫ ሲባል የነጻነት ዓየር አለ፤ ምርጫ ሲባል ተፎካካሪዎች አሉ፤ ምርጫ ሲባል ተፎካካሪዎች በእኩልነትና በነጻነት የቆሙበት መድረክ አለ፤ ምርጫ ሲባል የራሱን ፍላጎት በትክክል የሚያውቅና ከፍርሃት ነጻ የሆነ መራጭ አለ፤ ምርጫ ሲባል የተፎካካሪዎቹን እኩልነትና ነጻነት፣ የመራጮቹን እኩልነትና ነጻነት የሚያከብሩና የሚያስከብሩ ዳኞች አሉ፤ ምርጫ ሲባል የመራጮቹን ፍላጎት በትክክልና ያለአድልዎ የሚያሳይ ሰነድ የሚያዘጋጁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ሕግን የሚያከብሩ፣ ለሕዝብና ለአገር የሚቆረቆሩ ሰዎች አሉ፤ ምርጫ ሲባል ይኸኛው ከዚህኛው ይሻለኛል ብለው የመወሰን ችሎታ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ ምርጫ ሲባል መራጮቹ ተመራጮቹን ማገላበጥ አለ።
ታዲያ እኛ ምርጫ የምንለው ይህንን ሁሉ የያዘ ነው? ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱም እንኳን ቢጎድል፣ ምርጫ አንለውም፤ ምርጫ-መሳይ ልንለው እንችል ይሆናል፤ አንድ የሁለት ጓደኞች የቆየ ቀልድ ትዝ አለኝ፤ አንዱ ስሙ መሳይ ነው፤ ፊታውራሪ ነው፤ ሌላው ስሙ በፈቃዱ ነው፤ ሀኪም ነው፤ አንድ ቀን በፈቃዱ መሳይን ሲያገኘው በፊታውራሪነቱ ለማሾፍ ፊታውራሪ መሳይ አለ፤ መሳይን ጫን ብሎ፤ መሳይም ሲመልስ በዶክተርነቱ እያሾፈ ዶክተር በፈቃዱ ብሎ ዶክተርን ጫን ብሎ መለሰለት! የኛን ምርጫ-መሳይ ምን ብለን፣ እንዴት ብለን እናሹፍበት? ያውም ማሾፍ ከተፈቀደ! በባህላችን በጣም የተወደደ ምግብ አለ፤ ያንን ምግብ አቅርበው መሣሪያው ሲነፍጉ ሥጋውን ሰጥቶ ቢላዋውን መንሣት ይባላል፤ ንፉግነት ብቻ አይመስለኝም፤ ክፋትም አለበት፤ የደርግና የወያኔ ምርጫ-መሳዮች በአለማወቅና በንፉግነታቸው ይመሳሰላሉ፤ በክፋት ግን አይመሳሰሉም።
ደርግም ሆነ ወያኔ ከሌኒን ለመማር አልቻሉም እንጂ አስመስለዋል፤ ምርጫ-መሳዩንም ያገኙት ከዚያው ነው፤ ሌኒን ጉሮሮን ግጥም አድርጎ በብረት ሰንሰለት አስሮ ነጻ ነህ ይላል! መገንጠል ትችላለህ! ይላል፤ ወያኔም ሲሉ ሰምቶ መገንጠል-መሳይ ሕግ-መሳይ አወጣ!
ችግር ነው ጌትነት! ዱሮ ተረት ነበር፤ ዛሬ ግን በእውነት ሲቸግር እያየን ይመስለኛል፤ አንድ ሰው ራሱ ባፈራው ሀብትና በደረሰበት የጌትነት ደረጃ ችግር አይሰማውም፤ ሀብቱ ከየት እንደመጣ፣ እንዴት እንደመጣ፣ ምን ያህል ልፋት እንዳስከተለ መገመት ይቻላል፤ በተዘረፈ ሀብት ጌትነት ሲመጣ ግን ችግርን አዝሎ ነው፤ አንድ ሰው አራት ሚልዮን ብር ወድቆ ቢያገኝ አራት መቶ ካሬ ሜትር መሬት ቢገዛበት አያስደንቅም፤ የገንዘብ አያያዝን ስለማያውቅና በስጋት ስለሚከሳ መሬቱ ላይ መቀመጥ አስተማማኝ መስሎ ይታየዋል፤ ከካስትሮ በፊት የነበረውን የኪዩባ ሁኔታ በትንሹም ቢሆን የሚያውቅ በዛሬው ጊዜ በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነቱን ለመረዳት አያዳግትም፤ በኪዩባም ሆነ በኢትዮጵያ በተዘረፈ ሀብት ጌትነትን ያስፋፋው አሜሪካ ነው፤ ሕዝብ የሚደኸየውና የሚከብረው በጉልበትና በዝርፊያ ብቻ በሆነበት አገር ጊዜውን ጠብቆ ከሁለት አንዱን አርግዞ ይወልዳል፤ ወይ ዘራፊዎችን ሁሉ ዘርፎ ሙልጭ የሚያወጣቸው ጉልበተኛ ይመጣል፤ ወይ በሕጋዊ መንገድ ከዘራፊዎች እየገፈፈ ሀብትን ለሕዝብ የሚያደላድል ሕጋዊ ሥርዓት ይመሠረታል፤ ሁለቱንም በማስረገዝ ላይ ያሉት በግፍ ሀብታም የሚሆኑት ናቸው።
ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንደሆነ ለማስመሰል ምርጫ መሳይ አለ፤ ሕዝብ የሀብት ባለቤት እንደሆነ ለማስመሰል ግን ትንሽ ያስቸግራል፤ በኮንዶሚንየም ለማስመሰል ቢሞከርም አልሆነም፤ ለሎሌዎች ሹሞችም አልተዳረሰም!
በምርጫ መሳዩ ማሸነፍ ቀላል ነው፤ እንዲያውም መቶ በመቶ ማሸነፍ ይቻላል፤ ችግሩ የሚመጣው ከዚያ በኋላ ነው፤ ደካሞች የፖሊቲካ ቡድኖችንና ደካማውን ሕዝብ ማሸነፍ እንደሚቻል ጉልበተኛው አስመስክሯል፤ ሌላው ቀርቶ “የኔ” የሚላቸውን ቡድኖችም አፈር ላይ ሊያስተኛቸው ይችላል፤ እንዲያውም አፈሩ ምቹ ፍራሽ ነው ብለው በደስታ እንዲቀበሉ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ አሁን የጉልበተኛው መድረክ እየጠበበ መጣ፤ ችግሩ የሚፈጠረው እዚህ የጠበበው መድረክ ውስጥ ባሉት ጉልበተኞችና ጉልበተኛ መሳዮች ነው፤ በአንድ በኩል በጉልበተኞች መሀከል፣ በሌላ በኩል በጉልበተኛ መሳዮች መሀከል፤ በሌላ በኩል በጉልበተኞችና በጉልበተኛ መሳዮች መሀከል፣ ይህ ትግል ደካማዎች የፖሊቲካ ቡድኖችን እንደማሸነፍ ቀላል አይደለም፤ በአጥር ላይ እየተንጠለጠሉ የጣሉትን ለመልቀም እየተሻሙ ነው፤ በጉልበተኞቹ መሀከል ክፉ የሥልጣን ችጋር ገብቷል ማለት ነው፤ ጦር መማዘዝ ኪስን እንደሚያራቁት ያውቃሉ፤ ያለሥልጣን ኪስ ሙሉ እንደማይሆንም ያውቃሉ፤ ታዲያ ምን ይሻላል?
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
(ምንጭ: Mesfin Wolde-Mariam Blog)እና 

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ (http://www.goolgule.com/)