Friday, July 31, 2015

ሁሉም በያለበት የነፃነት ትግሉን ይቀላቀል!!!

እኛ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የሰውነት መብታችን ተገፎ የዜግነት ነፃነታችን ተረግጦና ተዋርደን የምንገኝበት ጊዜ ቢኖር ዛሬ ነው፡፡ የጅምላ ግድያ፤ የጅምላ እስርና የጅምላ ስደት እንደ ዘመነ ወያኔ የታየበት ዘመን የለም፡፡ ህፃናት በረሀብ ከሚማሩበት ክፍል ውስጥ የሚወድቁበት ፤ ወንድ ልጅ በደህንነት ሀይሎች ታፍኖ የሚደፈርበት፤ ሴት ልጅ በገመድ የታሰረ የባልዋነወ ብልት መንገድ ለመንገድ እንድትጎትት የተደረገበት ዘመን ቢኖር ያሳለፍነው የወያኔ ዘመናት ብቻ ነው፡፡ ባጠቃላይ የሰው ልጅ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ መከራና ሰቆቃ እንድንሸከም የተገደድንበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡
በአንፃሩም ስለ ለፃነት ስለ ፍትህና እኩልነት ሲሉ የተሰዉ ዋጋም የከፈሉ፤ አሁንም እየከፈሉ የሚገኙ ጥቂት አይደ ሉ ም፡፡ ከነዚህም አንዱ አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ለነፃነት ለፍትህና ለ ዲሞክራሲ የሚደረገው ተጋድሎ ውሎ አድሮ ዛሬ ከዋናውና ወሳኝ ከሆነው ምእራፍ ላይ መድረሱ ደግሞ የሁላችንንም ተስ ፋ ያለመለመና የተደፋው አንገታችን ቀና ያደረገ መሆኑና በተቃራኒው የወያኔን ካንፕ ያሸበረ መሆኑ በገሀድ እየታየ የሚገኝ እውነት ነው፡፡
እንግዲህ ይህን ወራዳ ስርአት አስወግዶ በምትኩ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመተካት የሚደረገው ትግል ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ የተደረገው ርብርብ ቀላል ባይሆንም ቀሪውን አጠናቆ ከዳር ለመድረስ ከመቼውም ጊዜ በላይ የእያንዳዱን ኢትዮጵያዊ የተግባር ተሳትፎ የሚጠይቅ፤ ሁሉም ከያለበት ስለ ነፃነት የሚደረገውን የአርነኝነት ትግል በመቀላቀል የድርሻ ውን ሀላፊነት መወጣት ከሚጠይቅበት ወሳኝ ምእራፍ ላይ መድረሳችንን መረዳት ግድ ይላል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ያለ ማንም እርዳታና ድጋፍ ዋጋ ከፍሎ ለፃነትን የማሰከበር እንግዳ ሳንሆን በታሪክ የምንታወቅበት መለያችን መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ እንኳን ዛሬ አለም አለም በጠበበችበት ዘመን ቀርቶ ትናንት በጨለማው ዘመን እንኳ እነ ዶ/ር መላኩ በያን ከአኛ አልፎ ለአፍሪካ ነፃነት ፈር ቀዳጅ ሆነው የተገኙበትን ታሪክ ማስታወስ ይገባል፡፡
እናም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኟውም ስፍራ የሚገኝ ሁሉ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል እውቀት ያለው በእውቀቱ፤ ጉልበት  ያለው በጉልበቱ፤ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ለመደገፍ ዛሬ ነገ ሳይል አሁኑኑ ከአርበኝነቱ ትግል መቀላቀል ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያዊነታችንን ብቻ ሳይሆን ሰው መሆናችን የሚረጋገጠው ነፃነታችንን አስጠብቀን በነፃነት መኖር ስንችል ብቻ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡
ስለዚህ ዛሬ አርበኞች ግንቦት ሰባት የለኮሰው የነፃነት ቀንዲል ከነጻነት አደባባይ ለመትከል የጀመረውን ጉዞ በሰው ሀይል፤ በገንዘብና በቁሳቁስ በማገዝ ሁላችንም የድርሻችንን እንድንወጣ ጥሪ ስናደርግ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ከእኛ ኢትዮጵ ያውያን ውጭ ማንም እንደሌለ በማስገንዘብ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
Source www.patriotg7.org

Saturday, July 25, 2015

ኦባማ፡ “በንግግር (ወሬ) A፣ በተግባር D” ኦባንግ ሜቶ

“በነጻነት መንገዳችን ላይ ዕንቅፋት አትሁኑብን”
ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ውጤት ቢሰጥ በእስካሁኑ የአፍሪካ ፖሊሲያቸው በንግግር (በወሬ) ደረጃ A በተግባር ግን D እንደሚሰጧቸው ኦባንግ ሜቶ አስታወቁ፡፡ አፍሪካውያንም ሆኑ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት በሚያደርጉት ትግል ምዕራባውያን ዕንቅፋት ከመሆን እንዲቆጠቡ አስረዱ፡፡
በአሜሪካ ድምጽ የStraight Talk Africa አዘጋጅ ሻካ ሳሊ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን የአፍሪካ ጉብኝት በተመለከተ ከሁለት ቀናት በፊት ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ሦስት አፍሪካውያንን ተጋብዘው ነበር፡፡ ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ የሴራሊዮኑ ፕሮፌሰር አብዱል ካሪም ባንጉራ፣ የአፍሪካ ስደተኞች ስብስብ ኃላፊ ጋናዊው ኒ አኩቴ እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊው ኦባንግ ሜቶ ነበሩ፡፡
በእስካሁኑ የአፍሪካ ፖሊሲያቸው ለፕሬዚዳንቱ ምን ውጤት ትሰጣላችሁ በማለት ሻካ ላቀረበው ጥያቄ ዶ/ር አብዱል D እሰጣቸዋለሁ፡፡ ይህም በተለይ ከአፍሪካ ጋር ስላለላቸው ግንኙነትና እንዴት የአፍሪካ ፖሊሲያቸው ውጤት አልባ እንደሆነ በመመልከት ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ያሉበትም ምክንያት በርካታ ሰዎችን በመጠየቅ ባደረጉት ጥናትና ምርምር እንደሆነ ሆኖም አሜሪካ ከኩባ ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት በማለዘብደረጃ የተጫወቱ ሚና ከዚህ የወረደ ነጥብ እንዳያገኙ እንደረዳቸው ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡
ጋናዊው  አኩቴ ግን ለኦባማ A እንደማይሰጡ ከተናገሩ በኋላ በዝርዝር ሳይጠቅሱ ፕሬዚዳንቱ ላከናወኑት ተግባራት ግን ተመጣጣኝ ነጥብ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በላይ ግን የትኛውም ነጥብ ይህ ነጥብ ወይም ደረጃ ለምንድነው የሚሰጣቸው ብሎ መጠየቅ ተገቢና አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡obang voa2
ኢትዮጵያዊው ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ውጤት ስጡ ቢባሉ “በንግግር (በወሬ) A በተግባር ግን D” እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ ከዓመታት በፊት ጋናን በጎበኙ ወቅት “አፍሪካ የሚያስፈልጋት ጠንካራ መሪዎች ሳይሆን ጠንካራ ተቋማት” ነው ማለታቸውን ከጠቀሱ በኋላ “በአሁኑ ወቅት በአገሬ ያለው አገዛዝ በምርጫ መቶ በመቶ አሸንፌአለሁ” የሚል መሆኑን አውስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተቋማት መቀጨጭ ወይም መምከን ምን ደረጃ እንደደረሰ ሲያስረዱም “በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት፣ ለሴቶች መብት፣ ለህጻናት መብት፣ ለዕርቅ፣  መሥራት ሕግን እንደ መጣስ ተቆጥሮ” ለእስር እንደሚዳርግ አስረድተዋል፡፡ አሜሪካ የተመሠረተችባቸው እነዚህ እሴቶች በኢትዮጵያ ዋጋ የሌላቸው መሆኑን ሲገልጹ ዋንኛው ምክንያት ጠንካራ ተቋማት በኢትዮጵያ እንዳይኖሩ አገዛዙ የመያዶች ሕግ በመባል የሚታወቀውን በማወጅ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖርና ሊቃወሙት የሚችሉትን ሁሉ በሕገወጥነት በመፈረጁ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ከዚህ ሌላ በአገራቸው ጠንካራ ተቋም እንዳይመሠረት ዕንቅፋት የሚሆን የጸረ አሸባሪነት ሕግ በሥራ ላይ መዋሉን “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት በተመለከተ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደተናገሩት ዋናው ዓላማ የአሸባሪነት ጉዳይ ተብሎ መጠቀሱ ኦባማ ለአፍሪካ ያላቸውን አመለካከት ያሳያል ብለዋል፡፡ ይህም ማለት ማንኛውም የአፍሪካ መሪ ሕዝቡን እያሸበረ የአሜሪካንን ጥቅም እስካስከበረ ድረስ የዜጎች መብት መረገጥ ነገር ለአሜሪካም ሆነ ለምዕራባውያን ከጉዳይ እንደማይቆጥሩት የጋራ ንቅናቄው መሪ ኦባንግ አስረድተዋል፡፡ “ለዚህም ነው በአሁኑ ጊዜ ጠንካራ ተቋማት መመሥረት የሚችሉ ብሩህ ኅሊና ያላቸው ጦማሪያንና ጋዜጠኞችና የነጻነት ድምጾች በአሸባሪነት ተፈርጀው በእስር የሚማቅቁት” በማለት ኦባማ በንግግር ደረጃ ለጠንካራ “ተቋማት መመሥረት ቢያወሩም በተግባር ግን የከሰሩ ናቸው፤ (የአፍሪካ ኅብረትን ሰብስበው ሲያናግሩም) የሚናገሩት ከጠንካራ መሪዎች ጋር ነው” ብለዋል፡፡
ኦባንግ ቀጠሉ “ዛሬ ኢትዮጵያ የምትተዳደረው በአፓርታይድ ዓይነት ዘረኛ አገዛዝ ነው፤ (ወደ አዘጋጁ ሻካ ሳሊ በመጠቆም) ለምሳሌ እኔና አንተ እዚህ አሜሪካ አገር በመጀመሪያ ሰዎች ነን፤ ወንድማማች ነን እንጂ ኢትዮጵያዊ ወይም ዑጋንዳዊ ተባብለን በዘርና በአካባቢ የተለያየን አይደለም፤ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን ይህ አይደለም፤ አንዲያውም በቅርቡ ከአሜሪካ የኔብራስካ ጠቅላይ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የሄደች አንዲት እህት መታወቂያ ካርድ ለማውጣት ስታመለክት ዘርሽ (ብሔርሽ) ምንድነው ተብላ ስትጠየቅ የሁለት ቅልቅል በመሆኗ ይህ ነው ብላ መናገር እንደማትችል፤ ኢትዮጵያዊ መሆኗን ብታስረዳም የግድ እንደሆነ ከኃላፊዎች ሲነገራት በማመልከቻው ቅጽ ላይ አማራ + ኦሮሞ = ______ በማለት እናንተው ሙሉት በሚል ክፍት አድርጋ ትታዋለች፤ (በኢትዮጵያ ሰው ከመሆንህ በፊት ዘርህ ይቀድማል) የትግራይ ነጻ አውጪ ግምባር – ህወሃት የሚባለው ከደርግ ለመታገል በረሃ ወረደ፤ ደርግ ከተወገደ በኋላ ኢህአዴግ በማለት ራሱን የቀየረ በመምሰል አሁንም (ኢትዮጵያን በነጻ አውጪ ስም) እየገዛ ይገኛል፤ ዛሬ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት በህወሃት ቁጥጥር ሥር ውሎ ዜጎች ይበረበራሉ፤ ሚሊታሪው፣ ኢኮኖሚው፣ ደኅንነቱ፣ በሙሉ በህወሃት ቁጥጥር ሥር ነው፤ በመሆኑም ኦማባ እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ የተከተሉት ፖሊሲ ይህንኑ የሚደግፍና ከሕዝቡ ያልወገነ ነው” በማለት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር አስረድተዋል፡፡
ጠያቂው ሻካ ሳሊ “እርስዎ ከበርካታ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎችና ከፍተኛ የፖለቲካ ኃላፊዎች ጋር በየጊዜው ይገናኛሉ፤ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በሚያደርጉት ንግግር ወቅት እነዚህ ባለሥልጣናት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ስላላት አቋም በተመለከተ ምንድነው የሚሉት” በማለት ለኦባንግ ላቀረቡላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በየጊዜው የሚሉት በኢትዮጵያ ጠንካራ ተቃዋሚ የለም ነው፤ እኔ የማስረዳቸው ደግሞ አገዛዙ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር በስልት እንዴት እንዳደረገ ነው፤ ኢንተርኔቱን ተቆጣጥረውታል፤ ከሃያ ዓመታት በላይ መንግሥት የሌላት ሶማሊያ በኢትንተርኔት አጠቃቀም ኢትዮጵያን ትበልጣለች፤ በየጊዜው የሚነሱ የነጻነት ድምጾች ታፍነዋል፤ ታስረዋል፤ ኢትዮጵያውያን በውጪ መደራጀት ይችላሉ ሆኖም በአገር ውስጥ (ህወሃት) ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር አድርጓል” በማለት በየጊዜው ለሚያገኟቸው የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንደሚያስረዱ ጠቁመዋል፡፡
ፕ/ር አብዱል በተራቸው በሙያቸው ባደረጉት ጥናት ኦባማ ለአፍሪካ እጅግም የበጀ ወይም በዋንኘነት የሚጠቀስ ተግባር አለመፈጸማቸው ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር አብዱል ማመጣጠን እንዳለባቸው አዘጋጁ ሻካ ሳሊ በመጥቀስ ለአብነት ያህል በራሳቸው በፕ/ሩ የትውልድ አገር ሴራሊዮን የተከሰተውን የኢቦላ ቫይረስ በመከላከል ኦባማ ያደረጉት አስተዋጽዖ ታላቅ እንደሆነ የሴራሊዮኑ ፕሬዚዳንት መናገራቸውን፣ እንዲሁም በላይቤሪያ ኦባማ የፈጸሙት ተግባር ተጠቃሽ እንደሆነ ፕሬዚዳንት ሰርሊፍ የመሰከሩ መሆኑን ከዚህም ባሻገር ወጣት አፍሪካውያንን ወደ አሜሪካ እየመጡ እንዲማሩ በማድረግ ለአህጉሪቱ የወደፊት ራዕይ የሚበጅ Young Africans Leadership Initiative (YALI) ፕሮግራም መመሥረታቸው ሊጠቀስ እንደሚገባው በቃለምልልሱ ወቅት አውስቷል፡፡
ፕ/ር አብዱል ከበፊቱ ጠንከር ባለ ሁኔታ እንዲያውም ፕሬዚዳንት ኦባማ በኬኒያም ሆነ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት የደመቀ አከባበርም ሆነ ዳንስና ጭፈራ እንደማያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንቱ ለሥራ የመጡ ከሆነ ያላቸውን ጊዜ ሁሉ ምን መደረግ እንዳለበት በዝርዝርና ነጥብ በነጥብ ከአፍሪካውያን ጋር ጊዜያቸውን በሙሉ ማዋል ይገባቸዋል፡፡ ጊዜው የጭፈራና የዳንስ ሳይሆን የሥራና ተግባራዊ ለውጥ የሚታቀድበት ሊሆን እንደሚገባ ፕ/ር አብዱል አስረድተዋል፡፡
obang voa5“ፕሬዚዳንት ኦባማ ይህንን ፕሮግራም ቢመለከቱ ለእርሳቸው የሚነግሩት መልዕክት ምንድነው? ካሜራውን እየተመለከቱ መልዕክት አስተላልፉ” በማለት ሻካ ለኦባንግ ሜቶ ላቀረበላቸው ጥያቄ ጥቁሩ ሰው “ከሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ስለሚቀጥለው ሌጋሲዎ የሚያስቡ ከሆነ እና መታወስ፣ መታሰብ የሚፈልጉ ከሆነ ሲታወሱ ሊኖሩበት የሚችልበት አንዱ መንገድ ለአምባገነኖች በሠሩት ተግባር ሳይሆን ለሕዝብ በሚያከናውኑት ሥራ ነው፤ የአፍሪካ ኀብረት 50ዓመታት እለፎታል በአኅጉሪቷ (ፖለቲካ) ላይ ያመጣው ይህ ነው የሚባል ለውጥ የለም፤ ስለዚህ በሕዝብ ላይ ኢንቨስት ያድርጉ፤ (ከሕዝብ ጋር ይቁሙ)፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማነቆ የሆኑት የጸረ አሸባሪነት ሕግ እና የመያዶች ሕግ እንዲሻሻሉ ወይም እንዲሻሩ ማድረግ ይችላሉና በዚህ ላይ ይሥሩ፤ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አሜሪካ እንዳደረገችው በኢትዮጵያም የሲቪክ ማኅበረሰቦች (መያዶች) በነጻነት እንዲንቀሳቀሱና ሕዝብን በማንቃት ረገድ ተግባራቸውን እንዲወጡ እርስዎም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ይቁሙ” በማለት በቀጥታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሲቀጥሉም “የኢኮኖሚ ዕድገት አለ ይባላል፤ የሚታይ እንቅስቃሴ አለ፤ መንገድ ይሠራል፤ ፎቅም ይገነባል፤ ሆኖም የኢኮኖሚን ዕድገት በፎቅና መንገድ ሥራ መለካት አይቻልም፤ ኢኮኖሚው በእርግጥ እያደገ እየተመደገ የሄደ ከሆነ ለምንድነው ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ቀይባህርን አቋርጠው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሚሰደዱት፤ ከአጠቃላዩ ሕዝብ 6 በመቶ በማይበልጥ አናሳ ብሔረተኞች ቁጥጥር ስር ስለሆነ አድጓል የሚባለው ኦኮኖሚ ይህ ነው የሚባል ለውጥ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ሊያመጣ አልቻለም” በማለት ኦባንግ ሜቶ በመላው ዓለም ፕሮግራሙን ለሚከታተሉ የአገራቸውን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም የጋራ ንቅናቄው ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ “አፍሪካውያንም ሆነ ኢትዮጵያውያን ኦባማን ወይም አሜሪካንን ወይም ምዕራባውያንን ነጻ እንዲያወጡን እየለመንን አይደለም፤ ራሳችንን እንዴት ነጻ እንደምናወጣ እናውቃለን፤ ነገር ግን (ከአምባገነኖች ጋር በማበር) በነጻነት መንገዳችን ላይ ዕንቅፋት አትሁኑብን” በማለት ግልጽ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
Source (http://www.goolgule.com/)

Friday, July 24, 2015

ዝዋይ እስር ቤት (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ-ማርያም)


ሐምሌ 16/2007 ዓ.ም. ለአሥር ወራት በእስር ላይ የቆየውን ጋዜጠኛ፣ ተመስገን ደሳለኝን (ከኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ዝምድና የለውም፤) ለመጠየቅ ወደዝዋይ ወህኔ ቤት ሄጄ ነበር፤ የወሕኒ ቤቱ ባለቤቶች ማረሚያ ቤት ይሉታል፤ ማረሚያ ቤት ማለት ሀሳቡን በነጻነት የሚገልጽና በሀሳቡም ከወያኔ ጋር በሎሌነት ለመተዳደር የማያመች ሲሆን የቀናውን በጉልበት የሚያጎብጡበት ማለታቸው ነው፤ ማረም ማለት ቀጥታውን ማጉበጥ ነው፤ እንዴት እንደሚያጎብጡት ላሳያችሁ፤–
1. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ እስረኞች ሰዎች በመሆናቸው ሰብአዊ ደኅንነታቸውና ክብራቸው ሁልጊዜም እንዲጠበቅላቸው ያስፈልጋል፡፡
2. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ እስረኞች ሁሉ ከመሰቃየትና ከመጉላላት በጸዳ አያያዝ እንዲጠበቁ ይደነግጋል፤
3. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ አንድ እስረኛ ዘመዶቹና ወዳጆቹ ከሚኖሩበት በጣም ርቆ አይታሰርም፤
4. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ የታመመ እስረኛ ሙሉ ህክምናና አስፈላጊውን መድኃኒት ሁሉ ማግኘት አለበት፤
5. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ እስረኞች በአእምሮና በመንፈስ የሚያድጉበት ትምህርትን የማግኘት፣ መጻሕፍትን የማግኘት መብቶች አሏቸው፤
6. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ማንኛውም እስረኛ በእምነቱ መሠረት አምልኮቱን የመፈጸምና የሃይማኖቱን መጻሕፍት የማንበብ መብት አለው፤
7. የኛን እንተወውና በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ማንኛውም እስረኛ ዘመዶቹና ወዳጆቹ እንዲጎበኙት መብት አለው፤
8. እስረኞች የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ከወህኒ ቤት ሲወጡ ትክክለኛ የማኅበረሰቡ አባሎች ሆነው እየሠሩ ለማኅበረሰቡ እድገት ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ማሰናዳት ያስፈልጋል፤
በዝዋይ እንዳየነውና እንደተነገርነው የእስረኞች ሁኔታ በጣም የሚያሳዝንና ከላይ የተዘረዘሩትን የሰብአዊ መብቶች የሚጥስ ነው፤ ጤንነት ዋና ነገር ነውና በሱ እንጀምር፤ ተመስገን ደሳለኝ ወንጀል የተባለበት የፖሊቲካም ሆነ የማኅበረሰብ እምነቱን እያፍረጠረጠ በመጻፉ ነው፤ (በ1992 ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባደረግሁት ንግግር ‹‹አትፍሩ›› ብለሃል ተብዬ ተከስሼ ነበር!) እንዲያውም ክሱን አስቂኝ የሚያደርገው መንግሥትን ነቅፈሃል የሚል መሆኑ ነው፤ ሦስት ዓመት እስራት ተፈረደበት፤ ይግባኝ ተከለከለ፤ አሁን ከታሰረ አሥር ወራት ሆኑት፤ ተመስገን በጣም ከታመመ ጥቂት ቆየ፤ አንደኛ አንዱ ጆሮው በጭራሽ አይሰማም፤ ሁለተኛ ከባድ የወገብ ሕመም ስላለበት መተኛትና መቀጥም በጭንቅ ሆኖበታል፤ ሆኖም አሳሪዎቹ ወደሀኪም ቤት ሊወስዱት ፈቃደኛ አይደሉም፤ ከዚያም በላይ መድኃኒት ከውጭ ሲመጣለት ይከለክላሉ፤ እኔም የወገብ ሕመም ስላለብኝ የወገብ ሕመሙን የሚያቀልለትን መድኃኒት ወስጄለት ነበር፤ አንድ አሥር አለቃ መድኃኒቱን አየና ከለከለ፤ መልሼ ይዤው መጣሁ፤ እንዲህ ያለውን ውሳኔ የሚያደርጉ ሁሉ ወያኔዎች ናቸው፡፡
ከተመስገን ጋር ትንሽ ጊዜ ቆይተን በዚያው በዝዋይ የታሰሩ ሌሎች ጋዜጠኞችን ለመጠየቅ መጀመሪያ ተፈቅዶልን ስለነበረ ወደዚያ ስናመራ አንድ ሹም መሳይ መጥቶ ወታደሮቹን ለብቻ ለብቻ በስም እየጠራ በመንሾካሾክ ትእዛዝ ይሰጣል፤ እየተንሾካሾከ ለአንዱ ትእዛዝ ሰጥቶ ሌሎቹን እንዳናይ ከለከለንና ተመለስን፤ ምክንያቱን ብንጠይቅ በአንድ ጊዜ መጠየቅ የሚቻለው አንድ እስረኛ ብቻ ነው ተባልን፤ ቅን መንፈስ ለጎደለውና ለሙስና ለተጋለጠ አሠራር ጥሩ ምሳሌ ነው፤ በመንሾካሾክ የሚሰጠውም ትእዛዝ ዓላማው ያው ይመስላል፤ ወያኔ በሰዎች ላይ እንዲህ ያለ ጭካኔ ማሳየት የሚፈልገው ለምንድን ነው?
በዝዋይ እስር ቤት ትምህርትም እንደመድኃኒት የተጠላ ነገር ነው፤ ለተመስገንም ሆነ ለሌሎች መጻሕፍት አይገቡላቸውም፤ ለምን? ብዬ ስጠይቅ አንዱ ጠባቂ ‹‹ለእውቀት የሚሆን መጽሐፍ ይገባል፤›› አለኝ፤ የእውቀትን ፍቺ ለመጠየቅ ስሞክር ቶሎ ግራ መጋባቱን አየሁና ተውሁት፤ እሱም እንዳያውቅ ስለሚፈልጉ፣ አለቆቹ የእውቀትን ፍቺ ጠበብና ቀለል አድርገው አስተምረውታል፤ ሎሌ ትእዛዝን በሹክሹክታ እየተቀበለ ማስፈጸም እንጂ፣ እውቀት አያስፈልገውም፤ እዚህ ላይ ምናልባት በደርግ ጊዜ በእስር ቤቶች የነበረውን የትምህርት መስፋፋት ማንሣት ይጠቅም ይሆናል፤ በደርግ ዘመን ብዙ የተማሩ ሰዎች ታስረው ስለነበረ እረስበርሳቸው እየተማማሩ አንዳንድ ሰዎች ጀርመንኛና ፈረንሳይና ቋንቋዎች፣ ግእዝና ታሪክ እየተማሩ ወጥተዋል፤ በተለይ በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወህኒ ቤቶች አንደኛ ሲወጡ እንደነበረ አስታውሳለሁ፤ ዛሬ በወህኒ ቤቶች ትምህርት ክልክል ነው፤ በቃሊቲ ሁለት የትምህርት ሙከራዎች ከሽፈውብናል፤ አንድ ጊዜ ኦሮምኛ ለመማር የፈለግን ሰዎች ተሰባስበን ተከልክለናል፤ ሕግ ለመማርም ጀምረን ታግደናል፤ እንዲሁም ጂምናስቲክ በቡድን መሥራት ክልክል ነበር፤ ማናቸውም እውቀት አደገኛ ነው! ታዲያ ማረሚያ ቤት የሚሉት ማንን ለማታለል ነው? ማረሚያ ቤት እንዲሆን በመጀመሪያ አሳሪዎቹ መታረም አለባቸው!
እንደተመስገን ደሳለኝ፣ እንደአብርሃ ደስታ፣ እንደእስክንድር ነጋ፣ ከዞን ዘጠኝም በፈቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አቤል ወበላ፣ አጥናፉ ብርሃኔ ገና አልተለቀቁም፤ በተጨማሪም ከእስልምና በኩል የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባሎች ዛሬም እንደታሰሩ ነው፤ የመፍትሔ አፈላላጊዎችን ማሰር ነገሩም ግራ ነው፡፡
በመጨረሻም መነሣት ያለበት አንድ አደገኛ አዝማሚያ አለ፤ ፖሊስ የሚባለው ፍርድ ቤት ከሚባለው ጋር ያለው ግንኙነት ሕግ የሚባለውን ከጨዋታ ውጭ አድርጎታል፤ ፍርድ ቤት የሚባለው እስረኛ እንዲፈታ ፖሊስ የሚባለውን ሲያዝ እንደማይፈጸም በተደጋጋሚ ታየ፤ ይህ የመጨረሻው የውድቀት ምልክትይመስለኛል፤ቆም ብሎ ማሰብና አስፈላጊውን የለውጥ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልገው አሁን ነው፡፡
ሐምሌ 17/2007
ምንጭ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Wednesday, July 22, 2015

የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር የትግሉን ሜዳ ተቀላቀለ

ኢሳት ዜና (ሃምሌ 13 2007 አም) የበክኔል ዩኒቭርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑትና በቅርቡ ከዚሁ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማእረግ የተቀበሉት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በሳምንቱ መጨረሻ ኤርትራ መግባታቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ አብይ መነጋገሪያ ሆኖ ወጥቷል ፤ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የመሪውን ትግል ቦታ መሄድ ይፋ በማድረግ ኢትዮጵያውያን በአቅማቸው መጠን በትግሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል። “እነሆ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ድ/ር ብርሀኑ ነጋ በአካል ትግል ሜዳ ውስጥ ይገኛል የሚችል ሁሉ እንዲከተል ፤ መከተል የማይችል በያለበት ሆኖ ትግሉን እንዲያጧጡፍ አርበኞች ግንቦት ሰባት ጥሪ ያደርጋል’’ ሲል ንቅናቄው ለኢትዮጵያ ህዝብ ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል። አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ “ሊቀመንበራችን ትግል ሜዳ ውስጥ ነው” በሚል ርእስ ሐምሌ 12/2007 ባወጣው መግለጫ “ አሁን ትግሉ በደረሰበት ደረጃ የአመራሩ በትግሉ ሜዳ ውስጥ መገኘት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ሊቀመንበሩን ጨምሮ አመራሩን ወደ ትግል ቦታ አንቀሳቅሷል፤ በዚህ መሰረት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ወደ ትግል ሜዳ ወርደዋል’’ ያለው የንቅናቄው መግለጫ ሲቀጥልም “ወሳኝ የሆነ ትግል ውስጥ ገብተናል የትግሉ መሪዎችም የህይወት መስዋትነት የሚከፈልበት ቦታ ላይ ይገኛሉ’’ ካለ በኋላ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ዘረኛውን የህወሀት አገዛዝ ለማስወገድ በጋራ እንስራ ሲል ጥሪ አቅርቧል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በትግል ሜዳ ላይ የሚገኙ የድርጅታቸውን አባላት ለመቀላቀልና በቅርብ አመራር ለመስጠት ወደ ኤርትራ መጓዛቸው በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ የደስታ ስሜት የፈጠረ ሲሆን ትግሉ የምርና ወሳኝ ደረጃ ላይ ለመድረሱ አመላካች ነው ተብሏል። የስራቱ ደጋፊዎችም በተቃውሞ አስተያየት እየሰጡ ይገኛሉ።
ምንጭ ኢሳት ዜና

Sunday, July 19, 2015

ሊቀመንበራችን ትግል ሜዳ ውስጥ ነው!- መግለጫ

ሐምሌ 12 2007 ዓ.ም.
ህወሓት በኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያ ላይ ያሰፈነው ዘረኛና ፋሽስታዊ አገዛዝ እንዲያበቃ፤ በምትኩም ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈኑበት የፓለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲመሠረት እና የሀገራችን አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ ለማኖር አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ተገዶ የገባበት የመረረ የአመጽ ትግል መጀመሩን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያዊያን የነፃነት አርበኞች በጀግነትና በጽናት እየታገሉ ነው።
ይህ ትግል በባርነትና በነፃነት መካከል የሚደረግ ወሳኝ ትግል ነው። የዚህ ትግል ውጤት የእኛ የዚህ ዘመን ትውልድ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የአገራችንን የወደፊት ታሪክ፤ የልጅ ልጆቻችንን ሕይወት ይወስናል። በዚህም ምክንያት ይህንን ትግል በድል መወጣት ግዴታችን ነው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ለነፃነት ግድ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጎናችን ሊቆም ይገባል።
አርበኞች ግንቦት 7 አመራሩን ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠን እና ትግሉ በሚጠይቀው ቦታ እንዲገኙ የሚያደርግ መሆኑ ሲገልጽ ቆይቷል። አሁን ትግሉ በደረሰበት ደረጃ የአመራሩ በትግሉ ሜዳ ውስጥ መገኘት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ሊቀመንበሩን ጨምሮ አመራሩን ወደ ትግሉ ሜዳ አንቀሳቅሷል። በዚህም መሠረት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ ትግል ሜዳ ወርዷል።
ትግሉ መሯል። ወሳኝ የሆነ ትግል ውስጥ ገብተናል። የትግሉ መሪዎች የሕይወት መስዋዕትነት እሚከፈልበት ቦታ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት የንቅናቄው አመራር በተሟላ ሁኔታ በትግሉ ሜዳ ውስጥ እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል። ኢትዮጵያዊያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ዘረኛው የህወሓት አገዛዝን ከጫንቃችን ለማስወገድ ቆርጠን እንድንነሳ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
ኢትዮጵያን ከህወሓት አገዛዝ ነፃ የሚያወጣው አርበኞች ግንቦት 7 ብቻ አይደለም። ስለሆነም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚደረገው ትብብር ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች አንዱ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ለድል እንዲበቃ ይታገላል። ኢትዮጵያዊያንም በያሉበትም በተመሳሳይ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በህወሓት ፋሽስታዊ አገዛዝ ላይ ክንዳቸውን እንዲያነሱ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
እነሆ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በአካል ትግል ሜዳ ውስጥ ይገኛል። የሚችል ሁሉ እንዲከተል፤ መከተል የማይችል በያለበት ሁኖ ሁለገብ ትግሉን እንዲያጧጥፍ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ
source www.patriotg7.org

Saturday, July 11, 2015

የግፍ ሠንደቅ ወረደ!

“የዘረኝነት ምልክት መፍረስ ይገባዋል”
በአሜሪካ የደቡብ ካሮላይና ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ የሸንጎ ሕንጻ ላይ ከ50 በላይ ሲውለበለብ የነበረው ሠንደቅ አርብ ወረደ፡፡ “ውሸት ለዘላለም መቆየት አይችልም፤ የዘረኝነት ምልክት እና ዘረኝነት መፍረስ ይገባቸዋል” በማለት የሠንደቁን መውረድ የደገፉ ተናገሩ፡፡
በእንግሊዝኛው አጠራር “የኮንፌዴሬት” ሠንደቅ የሚባለው በአሜሪካ የእርስበርስ ጦርነት ወቅት ከኅብረቱ ለመለየት የፈለጉ ግዛቶች የራሳቸውን ፕሬዚዳንት መርጠው ከኅብረቱ ደጋፊዎችና አብርሃም ሊንከን ጋር ጦር በገጠሙበት የተጠቀሙበት ሠንደቅ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት አብርሃም በአሜሪካ ውስጥ የተንሰራፋውን በዘር ላይ የተመሠረተውን ባርነት ለመደምሰስ ህግጋትን እያወጡ በነበሩበት ወቅት በባሪያ ፈንጋይነት የሚታወቁት የደቡብ ጠቅላይ ግዛቶች የባርነትን መወገድ በመቃወም ከኅብረቱ ለመገንጠል በመፈለጋቸው በአሜሪካ የእርስበርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡
ጥቁሮችን እጅግ አሠቃቂና ፍጹም ኢሰብዓዊ በሆነ መልኩ ሲያሰቃዩ፤ በግፍ ሲገድሉ፤ ከነህይወታቸው በእሣት ሲያቃጥሉ፤ ሴቶቻቸውን ቀን በጥጥ ለቀማና በመሳሰለው ሥራ በሃሩር በግፍ ሲያሰሩ ቆይተው ማታ ደግመው ይደፍሩ የነበሩ፤ የተወሰነላቸውን ጥጥ በቀኑ መልቀም ያልቻሉ ሌሊቱን ጀርባቸው እስኪተለተል ሲገርፉ የነበሩ፤ በነጋታው ልብሳቸው በደም ርሶ ከቆዳቸው እንደተጣበቀ በጥጥ ለቀማ እንደገና እንዲሰማሩ ግፍ ሲፈጽሙ የነበሩ፤ በነጮች ሰፈር መንገድ ላይ ሲሄዱ በመገኘታቸው ብቻ ከነህይወታቸው በእንጨት አስረው በእሣት እያቃጠሉ የደስታ መጠጥ ሲጠጡ እና የፍም ጥብስ እየበሉ በሰው ስቃይ ሲዝናኑ የነበሩ፤ … ጥቁሮች ነጻ መውጣት የለባቸውም በማለት ለጦርነት ሲሄዱ የተጠቀሙት ሠንደቅ ነበር ይህ “የኮንፌዴሬት” ሠንደቅ የተባለው፡፡
በደቡብ ካሮላይና ግዛት በቅርቡ በቤተክርስቲያን በጸሎትና መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ የነበሩ ጥቁሮችን የገደለው ነጭ ወጣት ይህንን የግፍ ሠንደቅ ይዞ የበላይነቱን ማሳያ አድርጎ የተነሳበት ፎቶ ከተለቀቀ ወዲህ ይህ ሠንደቅ ከመንግሥት ሕንጻ ላይ እንዲነሳ የቀረበው ሃሳብ ከፍተኛ ክርክር አስነስቶ ነበር፡፡ የጠቅላይ ግዛቱ ገዥ በውሳኔው ላይ ፊርማቸውን በማስቀመጥ ካጸደቁት በኋላ የግፍና የደም እንዲሁም የሰቆቃ መለያ የሆነው ሠንደቅ አርብ በይፋ ወርዷል፡፡
በሥነሥርዓቱ ላይ የነበሩ የግፉ ሰለባዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ይህ ሠንደቅ የክፍፍል፣ የዘር፣ የወገንተኝነት፣ አንዱ ከሌላው የበለጠ ወርቅ ዘር ስለሆነ ገዢ መሆኑን የሚያሳይበት፣ የርኩሰት መለያ ነው፤ መውረዱ ተገቢ ነው ብለዋል የጥቁር ሰብዓዊ መብት ተከራካሪ፡፡
“አሜሪካ የተገነባችው በዘር ላይ ነው፤ የዘረኝነት ሥርዓት እና ምልክቱ ሁሉ ደግሞ መፍረስ አለበት” በማለት የጥቁር ወጣቶች ኅብረት ሃላፊ ተናግሯል፡፡ “ውሸት ለዘላለም መኖር አይችልም፤ ይህ ሠንደቅ የውሸት መለያ ነው” በማለት ለጥቁሮች መብት የሚከራከረው ድርጅት ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
“ግፍ፣ ሰቆቃ፣ ሃዘን፣ ስቃይ፣ መታሰር፣ መገደል፣ አምባገነንነት፣ ዘረኝነት፣ ከፋፋይነት፣ እና እነዚህን የሚወክሉ መለያዎችና ምልክቶች ሁሉ የፈለገ ቢያደርጓቸው ቀናቸውን ጠብቀው ከተሰቀሉበት ከነሰቃዮቹ መውረዳቸው አይቀርም” በማለት የሠንደቁን መውረድ አስመልክቶ አንድ አዛውንት ጥቁር የተናገሩት አሁንም በተመሳሳይ ሠንደቅ ዓላማ ምልክትነት እየተጨቆኑ ለሚገኙ ሁሉ ተስፋን የሚፈነጥቅ ሆኗል፡፡
ይህንን ሠንደቅ ዓላማ ከሌሎች የአሜሪካ ደቡባዊ ጠቅላይ ግዛቶች የማውረድ እንቅስቃሴ በሰፊው ተጀምሯል፡፡
ምንጭ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Wednesday, July 8, 2015

ይድረስ ለገራፊዎቻችን – እኛ የፀናነው እናንተንም ነፃ ለማውጣት ነው!

"ለራሳችሁ ስትሉ ጉድጓዱን አርቃችሁ አትቆፍሩት"
“በምርመራው ወቅት የነበረው ድብደባ እና ክብረ ነክ ስድብ ወደ ምድር የመጣሁበትን ቀን እንድረግም አደረጉኝ፡፡ በተለይ ከአሁን በኋላ ልጅ መውለድ እንደማልችል እየዛቱ የውስጥ እግሬን ክፉኛ ገረፉኝ፡፡ . . . እኔም ልብሴን እንደማላወልቅ ነገርኳቸው፡፡ በዚህም ከአሁን ቀደሙ ለየት ያለ ከባድ ድብደባ አስተናገድኩ፡፡ ድብደባው ከአቅሜ በላይ ሲሆን ግን ከውስጥ ሱሪዬ ውጭ ያለውን ልብሴን ለማውለቅ ተገደድኩ፡፡ የውስጥ ሱሪዬንም እንዳወልቅ አዘዙኝ፡፡. . . “
ሐምሌ 5/2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ የክረምት መግቢያ መባቻ፣ ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ደግሞ የፆም ሐዋሪያት መፍቻ ነው፡፡ በዚች እለት እኔም እንደወትሮዬ በአካባቢዬ በምትገኝ አንዲት ካፌ ውስጥ ቁጭ ብዬ ከስርዓቱ አፈና የተረፉትን ጥቂት መጽሔቶች እና ጋዜጦች ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜናዎችን ማንበብ ተያያዝኩት፡፡ በዕለቱ ከታተሙት ጋዜጦችና መፅሄቶች መካከል ከፍተኛ ሽፋን ተሰጥቶት ይዘገብ የነበረው በዚች ምስኪን ሀገር በስስት የሚታዩ አራት ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በግፍ ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት መወርወራቸውን የሚያትት ነበር፡፡ ከዛ በፊት ደግሞ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ሲዘገብ የነበረው በኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ የሆኑት ጋዜጠኞችና ጦማሪያና በማዕከላዊ እስር ቤት እየደረሰባቸው ያለው ስቃይና የፍርድ ሂደት ነበር፡፡
ማንበቤን አቋርጬ ለጥቂት ደቂቃዎች ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ይህ ነገር የስርዓቱ የተለመደ የስልጣን ማራዘሚያ ዘዴ ቢሆንም ቅሉ እስከ መቼ እንዲህ ይቀጥላል? ይህ ስርዓት በኢትዮጵያውያን ላይ እስከመቼ ነው የሚቀልደው? የኢትዮጵያ ህዝብ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የነፃነት፣ የዴሞክራሲ አየር የሚተነፍሰውስ መቼ ነው? ከዘመናዊ ባርነት ተላቅቆ በነፃነት የሚኖርበት ጊዜስ ምን ያህል ሩቅ ይሆን? ነፃ ተቋማት የምንገነባውስ መቼ ይሆን? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እያሰላሰልኩ በአካባቢው የስርዓቱ ጠባቂ የሆኑት የፌደራል ፖሊሶችና የደህንነት አባላት ከሁለት መኪና ወርደው የአካባቢውን የትራፊክ እንቅስቃሴ አስቆሙት፡፡ የነበርኩበት ካፌ ተከበበ፡፡ አንድ የመገናኛ ሬድዮ የያዘ የፌደራል ፖሊስና ሁለት ሳምሶናይት የያዙ ደህንነቶች በቀጥታ ወደ እኔ መጡና የፌደራል ፖሊሱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አሳየኝ፡፡ በቁጣ “ተነስ! ፖሊስ ጣቢያ ቃልህን ትሰጣለህ!” የሚል ትዕዛዝ አከለበት፡፡ የተጠቀምኩትን ሻይ፣ ያነበብኳቸውን ጋዜጣና መፅሄት ሂሳብ ከፍዬ ከካፌው ወጣን፡፡
ካፌውን ለቀን ከወጣን በኋላ በተዘጋጀው የደህንነት መኪና ውስጥ ገባንና በፖሊስ ታጅቤ ወደ መኖሪያ ቤቴ አቀናን፡፡ ስንደርስ የመኖሪያ አካባቢዬ፣ መውጫ፣ መግቢያው በፌደራል ፖሊስ ተከብቧል፡፡ የደህንነት ሰዎች ካሜራቸውን እስኪያስተካክሉ ድረስ እኔ መኪናው ውስጥ ቆይ ተብያለሁ፡፡
ከደቂቃዎች በኋላ ደህንነቶችም ካሜራቸውን አስተካከሉና እኔም እየተቀረፅኩ ወደ ቤቴ እንድገባ ተደረገ፡፡ ከነበሩት የደህንነትና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ከታጠቁት መሳሪያ አንፃር አንድ ግለሰብን የሚይዙ ሳይሆን አካባቢው ትልቅ የጦር ቀጠና ይመስል ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ የሚያሳየው ስርዓቱ ያጋጠመውን የፍርሃት ደረጃ ነው፡፡ በመኖሪያ ቤቴ ከጠዋቱ 3፡00 እስከ 4፡30 እያንዳንዱ ነገር ተፈተሸ፡፡ ያለምንም ማስረጃ ፍተሻው ተጠናቀቀ፡፡ በፍተሻው ወቅት ፖሊስና ደህንነቶች ያሳዩት የነበረው ብልሹ ስነምግባር የስርዓቱ አንድ አካል ስለሆነ ብዙም አልገረመኝም፡፡ ፍተሻው ከጠናቀቀ በኋላ ጉዞው ገዥዎች ኢትዮጵያውያንን በገዛ ሀገራቸው፣ በግፍ፣ አሰቃቂና ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንገድ የሚያሰቃዩበትና በስውር የሚገድሉበት ማዕከላዊ እስር ቤት ሆነ፡፡ ማዕከላዊ ስንደርስ በተለምዶ ሳይቤሪያ ተብሎ የሚጠራው ጠባብ፣ ጨለማ እና ቀዝቃዛ የእስር ቤት ክፍል ተወረወርኩ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ አቶ ዳንኤል ሺበሽ እና ከተለያዩ ክልሎች ለቃቅመው ያሰሯቸው ሌሎች ስድስት ምስኪን ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡
ከሁለት ቀን በኋላ እኔና በእኔ መዝገብ የተከሰሰው መምህር ተስፋዬ ተፈሪ በአራዳ ምድብ ችሎት ቀረብን፡፡ የእለቱ “ዳኛ” ክሱን “እራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራው ፀረ ሰላምና ፀረ ህዝብ አሸባሪ ቡድን አባልና አመራር በመሆን፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍሎች አባላትን በመመልመል፣ በማደራጀት፣ የ2007 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫን ለማደናቀፍ፣ አመፅና ሁከት በመቀስቀስ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ፣ ሆን ብሎ የሽብር ቡድኑን አመራር በመቀበል . . .” ወዘተ የሚል ነበር ያነበበችው፡፡
ከፍርድ ቤት መልስ ወደ ምርመራ ክፍል ተጠርቼ በሀይል የኢሜል ሚስጥር ቁልፎቼን ተቀበሉኝ፡፡ ማታም ከምሽቱ 2፡30 ወደ ምርመራ ክፍል ተጠራሁ፡፡ በምርመራው ወቅት የነበረው ድብደባ እና ክብረ ነክ ስድብ ወደ ምድር የመጣሁበትን ቀን እንድረግም አደረጉኝ፡፡ በተለይ ከአሁን በኋላ ልጅ መውለድ እንደማልችል እየዛቱ የውስጥ እግሬን ክፉኛ ገረፉኝ፡፡ ከምሽቱ 2፡30 የጀመረው ድብደባና “ምርመራ” እስከ ሌሊቱ 8፡00 ድረስ ቆይቶ ወደ ጨለማውና ቀዝቃዛው የማጎሪያ ክፍሌ መለሱኝ፡፡
በማግስቱ ከቀኑ 8፡00 አካባቢ እንደገና ወደ ምርመራ ክፍል ተወሰድኩ፡፡ አንድ እድሜው በግምት በሰላሳዎቹ አጋማሽ የሚገኝ የደህንነት አባል “የኋላ ታሪክህን ከስር ከመሰረቱ አስረዳ!” ብሎ በቁጣ ትዕዛዝ አይሉት ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ የህይወት ታሪኬን በዝርዝር አስረዳሁት፡፡ ከአሁን በኋላ የሚመረምረኝ እሱ መሆኑን ከገለጸልኝ በኋላ “የትናንትናው ሌሊት ምርመራ እንዴት ነበር?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ምርመራው ምን ይመስል እንደነበር ጥያቄውን በጥያቄ ጀመርኩለት፡፡ “የሰው ልጅ፣ ያውም ወገን እንዴት እንዲህ ይደበደባል?”፣ “አልተማራችሁም እንዴ?”፣ “ፎረንሲክ ሰልጣኞቹ የሉም እንዴ?” እና መሰል ጥያቄዎቹን በመጠየቅ የደረሰብኝን ኢ-ሰብአዊና ዘግናኝ ደብደባ እያስረዳሁት እያለ በድንገት “በቃ!” ብሎ ጠረጼዛውን በመደብደብ አስቆመኝ፡፡ እሱም ምርመራው ገና እንዳልተጀመረና በምርመራው ሂደትም አካሌን ብቻ ሳይሆን ህይወቴንም ላጣ እንደምችል የ”መርማሪነቱን” ካስፈራራኝ በኋላ ወደ ክፍሌ መለሰኝ፡፡
በዚህ ቀን ከምሽቱ 2 ሰዓት ገደማ የጀመረው አሰቃቂ ድብደባና “ምርመራ” በግምት ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ ተጠናቀቀ፡፡ ከአንድ ቀን በፊት ከነበረው የባሰና ጭካኔ የተሞላበት ነበር፡፡ በተለይ ለሁለተኛ ጊዜ የተገረፈው የውስጥ እግሬ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ከዚህ “ምርመራ›› በኋላ እንደተረዳሁት በቀኑ ምርመራ ወቅት “ፎረንሲክ ሰልጣኞች የሉም እንዴ?” ብዬ ያቀረብኩት ጥያቄ የዝቅተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ማታ “ለመሆኑ የእኛን የትምህርት ደረጃ የት ታውቃለህ?” እያሉ ነበር ያሰቃዩኝ፡፡
ከሶስት ቀን በኋላ ወደተለመደው የ”ምርመራ” ክፍል ተጠርቼ ተመሳሳይ ጥያቄና ዱላ አስተናገድኩ፡፡ ይህኛው ካለፉት ቀናት የሚለየው በእረፍት ቀን መሆኑ ነው፡፡ በጣም የገረመኝ ነገር ቢኖር ክብሩን የሰው ልጅ ለማሰቃየት ሙሉ የእረፍት ጊዜያቸውንም በመግረፍ የሚያሳልፉ መሆናቸው ነው፡፡ ሰኞ እለት በግምት ከምሽቱ 2፡30 አካባቢ ወደ ምርመራ ክፍል ተወሰድኩ፡፡ ምርመራው በተለመዱ ጥያቄዎችና ዱላ ተጀመረ፡፡ በድብደባው ወቅት ከመርማሪዎች አፍ በሚወጣው የአልኮል ጠረን መርማሪዎቹ ሞቅ እንዳላቸው ተረድቻለሁ፡፡ የተወሰነ ከደበደቡኝ በኋላ ልብሴን እንዳወልቅ ትዕዛዝ ተሰጠኝ፡፡ እኔም ልብሴን እንደማላወልቅ ነገርኳቸው፡፡ በዚህም ከአሁን ቀደሙ ለየት ያለ ከባድ ድብደባ አስተናገድኩ፡፡ ድብደባው ከአቅሜ በላይ ሲሆን ግን ከውስጥ ሱሪዬ ውጭ ያለውን ልብሴን ለማውለቅ ተገደድኩ፡፡ የውስጥ ሱሪዬንም እንዳወልቅ አዘዙኝ፡፡
“አላወልቅም” አልኩ
“ለምን?” አሉኝ፡፡
“ኃይማኖታችን፣ ባህላችን፣ የአባቶቻችን ስርዓት የሰው ልጅ በእንዲህ አይነት ሁኔታ እንዲቀጣ አይፈቅድም” አልኳቸው፡፡ አሁንም አልተሳካልኝም፡፡ ከፍተኛ ድብደባ፣ ከዚህም በላይ በጣም ክብረ ነክ የሆኑ ስድቦችን ሰደቡኝ፡፡ ከዚህ የማሰቃያ ክፍል ስመለስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዮሴፍን ታሪክ በማንበብ ራሴን ለማረጋጋት ሞከርኩ፡፡ ያች ቀን በዚህ መልኩ አለፈች፡፡
አርብ ሐምሌ 18/2006 ዓ.ም የገብርኤል ዋዜማ ከቀጨኔ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አመታዊ ክብረ በዓል በእልልታ ደምቋል፡፡ የዕጣኑ መዓዛ አልደረሰንም እንጅ ዝማሬው በደንብ ይሰማን ነበር፡፡ በዚህ ምሽት ያለ ወትሮው “ምርመራ” የተጀመረው ከሌሊቱ 5፡00 ገደማ ላይ ነበር፡፡ ከገባሁበት ቀን ጀምሮ የምግብ ፍላጎቴ በጣም ወርዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየጊዜው የሚፈፀምብኝ ድብደባና ሞራላዊ በደሎች ተጨምረው የዚህን ቀን ድምደባ መቋቋም አቅቶኝ ራሴን ስቼ እንደወደኩ አስታውሳለሁ፡፡
ቅዳሜንና እሁድን ከማዕከላዊ ምርመራ አንጻር በ”ሰላም” አሳልፌ ሰኞ ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ ወደ ምርመራ ክፍል ተወሰድኩ፡፡ “መርማሪው” ደስታ ይባላል፡፡ ከእሱ በፊት ከፍተኛ አመራርነት ላይ ያሉት የደህንነት አባላት መርምረውኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ለእሱ አሳልፈው የሰጡኝ፡፡ “መርማሪ” ተብዬው ደስታ ማዕከላዊ ከገባሁ ጀምሮ ግቢው ውስጥ አይቼው ከማላውቀው ሌላ የደህንነት አባል ጋር ሆኖ ጠበቀኝ፡፡ ወደ ክፍሉ እንደገባሁ እንግዳው የደህንነት አባል “የሽብር ቡድኑ አላማ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ እኔም “እኔኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ ባህልና ወግ ተኮትኩቼ ያደኩ፡፡ እኔ አሸባሪ ከሆንኩ የሚሸበረው የየት ሀገር ዜጋ ነው?” ብዬ ስመልስለት “መርማሪው” ደስታ ንግግሬን በድብደባ አስቆመኝ፡፡ እንግዳው ደህንነት እንደሚገድለኝ ከዛተብኝ በኋላም ወደ ጨለማና ቀዝቃዛው ክፍሌ ተመለስኩ፡፡ ያም ሆኖ እኔ ላይ የደረሰው በደልና ግፍ በዚህ የማሰቃያ ክፍል ስቃይ ከሚደርስባቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ግን ደግሞ ማዕከላዊ ከሚገኙት ጨካኝ ገራፊዎች መካከል ምን ላርግልህ፣ ምህረት፣ ደስታ፣ … የተባሉና ሌሎችም ስማቸውን የማላውቃቸው በየ ተራ “ጥሩ” ገራፊነታቸውን ሞክረውብኛል፡፡
በማዕከላዊ ቆይታዬ የገረመኝ ነገር ቢኖር መርማሪዎች በሙሉ በትዕዛዝ የተሰፉ እስኪመስሉ ድረስ ተመሳሳይ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአቅምና የብቃት ማነስ ችግር ሁሉንም ያመሳስላቸዋል፡፡ ሁሌም ከአፋቸው የማትጠፋ “ተናገር!” የምትል ቃል አለች፡፡ ምን እንደሚናገር ባያውቀውም በእሱ እጅ የሚገኝ ማንኛውም እስረኛ መናገር አለበት፡፡ ያው በቁጣ “ዝም በል!” የምትል ከመርማሪዎቹ የማትጠፋ ሌላ ቃል እስከሚነገረው ድረስ፡፡ “እንዳያልፉት የለም፣ ያ ሁሉ ታለፈ” እንዳለው ብአዴን ይህ ሁሉ በደልና ግፍ አልፈን ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተዘዋወርን በኋላም ምንም እንኳ የማዕከላዊ ድብደባ ባይኖርም የችሎቱ ድብደባ ከማዕከላዊ ባልተናነሰ መልኩ ሲያሸማቅቀን እና ሲያመላልሰን ይኸው እንደቀልድ ሐምሌ 5/2007 አንድ አመት ሊሆነን ነው፡፡ ዛሬ በቂልንጦ እስር ቤት ሆኜም ብዙ ነገሮች ያሳስቡኛል፡፡ ሀገሬ በአምባገነኖች ስር ሆና፣ ዜጎች በጨካኝና ዘግናኝ ድብደባ እየተሰቃዩ እስከ መቼ እንቀጥላለን? በንፁሃን ዜጎች ላይ “አሸባሪ” የሚል ክስ እየተለጠፈ እስከ መቼ ይሰቃያሉ? በእስር ቤት ከደረሰብኝና እየደረሰብኝ ከሚገኘው ስቃይ ይልቅ ለውጥ! ለውጥ! ለውጥ! ነፃነት! ነፃነት! ነፃነት! የሚል ድምፅ ይሰማኛል፡፡ እውነት ይህን ድምፅ በቅርቡ በኢትዮጵያ ምድር እውን ሆኖ እናየው ይሆን?
ገራፊዎቻችና አሰቃዮቻችን ሆይ!
ያደረጋችሁብን ሁሉ ፅናታቸውንና የሀገር ፍቅራችን ይበልጡን አጠናከረው እንጅ ቅንጣት ታክል አልቀነሰብንም፡፡ ግን ለራሳችሁ ስትሉ ግፍና ሰቆቃውን ባታበዙት ይሻላል፡፡ እደግመዋለሁ! ለራሳችሁ ስትሉ ጉድጓዱን አርቃችሁ አትቆፍሩት፡፡ እኛ መከራውንና ግፍን በፅናት የምንቀበለው እናንተን ወደ ትልቅ ጉድጓድ ገፍትረን ነፃ ለመውጣት ሳይሆን በጋራ፣ እኛም፣ እናንተም አብረን ነፃ እንወጣ ዘንድ ነውና! (ፎቶ: ለማሳያ ከኢንተርኔት የተገኘ)
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
(ከባህሩ ደጉ፤ ቂሊንጦ እስር ቤት ለነገረ ኢትዮጵያ የተላከ)
ምንጭ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ 

Friday, July 3, 2015

በህወሓት አገዛዝ እየተሰቃዩ ላሉ ወገኖቻችን ደህንነት የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጫና ይቀጥል!

ከሣምንት በፊት የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን የሚመለከት አንድ መግለጫ አውጥቷል። በዚህ መግለጫው፣ አንዳርጋቸው ጽጌ ለአንድ ዓመት ሙሉ መሠረታዊ የሆኑ የታሳሪዎች መብት እንኳን ተነፍጎት ባልታወቀ እስር ቤት የሚገኝ መሆኑ እና በእንግሊዝ ባለሥልጣናትና በቤተሰቦቻቸው እንዲጠየቅ፣ ቋሚ የቆንስላና የህግ ምክር እንዲያገኝ በተደጋጋሚ የቀረበው ጥያቄ በወያኔ አገዛዝ ውድቅ መደረጉ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑ ከወትሮው ጠንከር ባሉ ቃላት ገልጿል። አዲስ አበባ የሚገኘው የብሪታኒያ አምባሳደርም እንደዚሁ ከተለመደው ዲፕሎማሲያዊ ለስላሳነት ወጣ ያለ ያለ መግለጫ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚታተመው ሪፓርተር ጋዜጣ ሰጥቷል። እነዚህ የሰሞኑ የእንግሊዝ መንግሥት መግለጫዎች በቀና የሚታዩ ቢሆንም የብሪታኒያ መንግሥት ማድረግ ይገባው ከነበረው እና ማድረግ ከሚችለው አንፃር ሲታይ ብዙ ይቀረዋል። የአውሮፓ ኅብረት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በተደጋጋሚ አንስቷል። የተባበሩት መንግሥታትም የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝ ጉዳይ ምርመራ እንዲደረግበት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከላይ የተዘረዘሩት ኩነቶች፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ያለሟቋረጥ የሚያደርጉት ውትወታ ውጤት እያመጣ መሆኑ ያሳያል። ይህ ጥረት ለወደፊቱም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስልጥኖ አሰማርቷችኋል” ተብለው እንደተለመደው በሀሰት የተከሰሱ ወገኖቻችን “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ መከላከያ ምስክር እንዲሆኑን ይታዘዝልን“ ብለው ሲጠይቁ ዳኛ ተብየው “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ ሰውን በመከላከያ ምስክርነት ማቅረብ ይከብዳል” ብሎ ሲናገር ተደምጧል። አቶ አንዳርጋቸው ለምስክርነት ይቅረብ አይቅረብ ብይን ሊሰጥበት ቀጠሮ ተይዟል።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የነፃነት አርበኛው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእስር አያያዝ ሁኔታ ዓለም ዓቀፍ የዲፕሎማሲ አጀንዳ በሆነበት በዚህ ወቅት በህወሓት አገዛዝ በተሾመ ዳኛ “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ” መባሉ አሳሳቢ ጉዳይ አድርጎ ይመለከተዋል። አርበኞች ግንቦት 7፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የተከሳሾች፣ የአቃቤ ህጉና የዳኛው ምልልስ ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአውሮፓ ኅብረትና ለእንግሊዝ መንግሥት እንዲደርስ እንዲያደርጉም ያሳስባል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ብቻ ሳይሆን በህወሓት እስርቤቶችና ከእስር ቤቶች ውጭ ባልታውቁ ቦታዎች ታስረው እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖቻችን ሁሉ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ የሚወጣው፣ ኢትዮጵያዊያን በሚያደርጉት ሁለገብ ትግል ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። ስለሆነም ራሳችንን፣ ወገኖቻችንና አገራችን ነፃ ለማውጣት የምናደርገው ትግል ማጠናከር ግዴታችን ነው። እኛ ራሳችን እንጂ ማንም ነፃነታችንን አያጎናጽፈልንም።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የህወሓትን እኩይ ተግባራት በዓለም አደባባዮች ማጋለጥ፤ የህወሓት አገዛዝን ወዳጅ ማሳጣት እና በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ደህነት የሚያሻሽሉ ተጽዕኖዎችን መፍጠር እጅግ አስፈላጊ ተግባር በመሆኑ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ በህወሓት እጅ ለወደቁ ወገኖቻችን ድጋፍ የሚያሰሙትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
source www.patriotg7.org