Wednesday, July 8, 2015

ይድረስ ለገራፊዎቻችን – እኛ የፀናነው እናንተንም ነፃ ለማውጣት ነው!

"ለራሳችሁ ስትሉ ጉድጓዱን አርቃችሁ አትቆፍሩት"
“በምርመራው ወቅት የነበረው ድብደባ እና ክብረ ነክ ስድብ ወደ ምድር የመጣሁበትን ቀን እንድረግም አደረጉኝ፡፡ በተለይ ከአሁን በኋላ ልጅ መውለድ እንደማልችል እየዛቱ የውስጥ እግሬን ክፉኛ ገረፉኝ፡፡ . . . እኔም ልብሴን እንደማላወልቅ ነገርኳቸው፡፡ በዚህም ከአሁን ቀደሙ ለየት ያለ ከባድ ድብደባ አስተናገድኩ፡፡ ድብደባው ከአቅሜ በላይ ሲሆን ግን ከውስጥ ሱሪዬ ውጭ ያለውን ልብሴን ለማውለቅ ተገደድኩ፡፡ የውስጥ ሱሪዬንም እንዳወልቅ አዘዙኝ፡፡. . . “
ሐምሌ 5/2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ የክረምት መግቢያ መባቻ፣ ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ደግሞ የፆም ሐዋሪያት መፍቻ ነው፡፡ በዚች እለት እኔም እንደወትሮዬ በአካባቢዬ በምትገኝ አንዲት ካፌ ውስጥ ቁጭ ብዬ ከስርዓቱ አፈና የተረፉትን ጥቂት መጽሔቶች እና ጋዜጦች ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜናዎችን ማንበብ ተያያዝኩት፡፡ በዕለቱ ከታተሙት ጋዜጦችና መፅሄቶች መካከል ከፍተኛ ሽፋን ተሰጥቶት ይዘገብ የነበረው በዚች ምስኪን ሀገር በስስት የሚታዩ አራት ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በግፍ ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት መወርወራቸውን የሚያትት ነበር፡፡ ከዛ በፊት ደግሞ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ሲዘገብ የነበረው በኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ የሆኑት ጋዜጠኞችና ጦማሪያና በማዕከላዊ እስር ቤት እየደረሰባቸው ያለው ስቃይና የፍርድ ሂደት ነበር፡፡
ማንበቤን አቋርጬ ለጥቂት ደቂቃዎች ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ይህ ነገር የስርዓቱ የተለመደ የስልጣን ማራዘሚያ ዘዴ ቢሆንም ቅሉ እስከ መቼ እንዲህ ይቀጥላል? ይህ ስርዓት በኢትዮጵያውያን ላይ እስከመቼ ነው የሚቀልደው? የኢትዮጵያ ህዝብ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የነፃነት፣ የዴሞክራሲ አየር የሚተነፍሰውስ መቼ ነው? ከዘመናዊ ባርነት ተላቅቆ በነፃነት የሚኖርበት ጊዜስ ምን ያህል ሩቅ ይሆን? ነፃ ተቋማት የምንገነባውስ መቼ ይሆን? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እያሰላሰልኩ በአካባቢው የስርዓቱ ጠባቂ የሆኑት የፌደራል ፖሊሶችና የደህንነት አባላት ከሁለት መኪና ወርደው የአካባቢውን የትራፊክ እንቅስቃሴ አስቆሙት፡፡ የነበርኩበት ካፌ ተከበበ፡፡ አንድ የመገናኛ ሬድዮ የያዘ የፌደራል ፖሊስና ሁለት ሳምሶናይት የያዙ ደህንነቶች በቀጥታ ወደ እኔ መጡና የፌደራል ፖሊሱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አሳየኝ፡፡ በቁጣ “ተነስ! ፖሊስ ጣቢያ ቃልህን ትሰጣለህ!” የሚል ትዕዛዝ አከለበት፡፡ የተጠቀምኩትን ሻይ፣ ያነበብኳቸውን ጋዜጣና መፅሄት ሂሳብ ከፍዬ ከካፌው ወጣን፡፡
ካፌውን ለቀን ከወጣን በኋላ በተዘጋጀው የደህንነት መኪና ውስጥ ገባንና በፖሊስ ታጅቤ ወደ መኖሪያ ቤቴ አቀናን፡፡ ስንደርስ የመኖሪያ አካባቢዬ፣ መውጫ፣ መግቢያው በፌደራል ፖሊስ ተከብቧል፡፡ የደህንነት ሰዎች ካሜራቸውን እስኪያስተካክሉ ድረስ እኔ መኪናው ውስጥ ቆይ ተብያለሁ፡፡
ከደቂቃዎች በኋላ ደህንነቶችም ካሜራቸውን አስተካከሉና እኔም እየተቀረፅኩ ወደ ቤቴ እንድገባ ተደረገ፡፡ ከነበሩት የደህንነትና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ከታጠቁት መሳሪያ አንፃር አንድ ግለሰብን የሚይዙ ሳይሆን አካባቢው ትልቅ የጦር ቀጠና ይመስል ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ የሚያሳየው ስርዓቱ ያጋጠመውን የፍርሃት ደረጃ ነው፡፡ በመኖሪያ ቤቴ ከጠዋቱ 3፡00 እስከ 4፡30 እያንዳንዱ ነገር ተፈተሸ፡፡ ያለምንም ማስረጃ ፍተሻው ተጠናቀቀ፡፡ በፍተሻው ወቅት ፖሊስና ደህንነቶች ያሳዩት የነበረው ብልሹ ስነምግባር የስርዓቱ አንድ አካል ስለሆነ ብዙም አልገረመኝም፡፡ ፍተሻው ከጠናቀቀ በኋላ ጉዞው ገዥዎች ኢትዮጵያውያንን በገዛ ሀገራቸው፣ በግፍ፣ አሰቃቂና ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንገድ የሚያሰቃዩበትና በስውር የሚገድሉበት ማዕከላዊ እስር ቤት ሆነ፡፡ ማዕከላዊ ስንደርስ በተለምዶ ሳይቤሪያ ተብሎ የሚጠራው ጠባብ፣ ጨለማ እና ቀዝቃዛ የእስር ቤት ክፍል ተወረወርኩ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ አቶ ዳንኤል ሺበሽ እና ከተለያዩ ክልሎች ለቃቅመው ያሰሯቸው ሌሎች ስድስት ምስኪን ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡
ከሁለት ቀን በኋላ እኔና በእኔ መዝገብ የተከሰሰው መምህር ተስፋዬ ተፈሪ በአራዳ ምድብ ችሎት ቀረብን፡፡ የእለቱ “ዳኛ” ክሱን “እራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራው ፀረ ሰላምና ፀረ ህዝብ አሸባሪ ቡድን አባልና አመራር በመሆን፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍሎች አባላትን በመመልመል፣ በማደራጀት፣ የ2007 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫን ለማደናቀፍ፣ አመፅና ሁከት በመቀስቀስ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ፣ ሆን ብሎ የሽብር ቡድኑን አመራር በመቀበል . . .” ወዘተ የሚል ነበር ያነበበችው፡፡
ከፍርድ ቤት መልስ ወደ ምርመራ ክፍል ተጠርቼ በሀይል የኢሜል ሚስጥር ቁልፎቼን ተቀበሉኝ፡፡ ማታም ከምሽቱ 2፡30 ወደ ምርመራ ክፍል ተጠራሁ፡፡ በምርመራው ወቅት የነበረው ድብደባ እና ክብረ ነክ ስድብ ወደ ምድር የመጣሁበትን ቀን እንድረግም አደረጉኝ፡፡ በተለይ ከአሁን በኋላ ልጅ መውለድ እንደማልችል እየዛቱ የውስጥ እግሬን ክፉኛ ገረፉኝ፡፡ ከምሽቱ 2፡30 የጀመረው ድብደባና “ምርመራ” እስከ ሌሊቱ 8፡00 ድረስ ቆይቶ ወደ ጨለማውና ቀዝቃዛው የማጎሪያ ክፍሌ መለሱኝ፡፡
በማግስቱ ከቀኑ 8፡00 አካባቢ እንደገና ወደ ምርመራ ክፍል ተወሰድኩ፡፡ አንድ እድሜው በግምት በሰላሳዎቹ አጋማሽ የሚገኝ የደህንነት አባል “የኋላ ታሪክህን ከስር ከመሰረቱ አስረዳ!” ብሎ በቁጣ ትዕዛዝ አይሉት ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ የህይወት ታሪኬን በዝርዝር አስረዳሁት፡፡ ከአሁን በኋላ የሚመረምረኝ እሱ መሆኑን ከገለጸልኝ በኋላ “የትናንትናው ሌሊት ምርመራ እንዴት ነበር?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ምርመራው ምን ይመስል እንደነበር ጥያቄውን በጥያቄ ጀመርኩለት፡፡ “የሰው ልጅ፣ ያውም ወገን እንዴት እንዲህ ይደበደባል?”፣ “አልተማራችሁም እንዴ?”፣ “ፎረንሲክ ሰልጣኞቹ የሉም እንዴ?” እና መሰል ጥያቄዎቹን በመጠየቅ የደረሰብኝን ኢ-ሰብአዊና ዘግናኝ ደብደባ እያስረዳሁት እያለ በድንገት “በቃ!” ብሎ ጠረጼዛውን በመደብደብ አስቆመኝ፡፡ እሱም ምርመራው ገና እንዳልተጀመረና በምርመራው ሂደትም አካሌን ብቻ ሳይሆን ህይወቴንም ላጣ እንደምችል የ”መርማሪነቱን” ካስፈራራኝ በኋላ ወደ ክፍሌ መለሰኝ፡፡
በዚህ ቀን ከምሽቱ 2 ሰዓት ገደማ የጀመረው አሰቃቂ ድብደባና “ምርመራ” በግምት ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ ተጠናቀቀ፡፡ ከአንድ ቀን በፊት ከነበረው የባሰና ጭካኔ የተሞላበት ነበር፡፡ በተለይ ለሁለተኛ ጊዜ የተገረፈው የውስጥ እግሬ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ከዚህ “ምርመራ›› በኋላ እንደተረዳሁት በቀኑ ምርመራ ወቅት “ፎረንሲክ ሰልጣኞች የሉም እንዴ?” ብዬ ያቀረብኩት ጥያቄ የዝቅተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ማታ “ለመሆኑ የእኛን የትምህርት ደረጃ የት ታውቃለህ?” እያሉ ነበር ያሰቃዩኝ፡፡
ከሶስት ቀን በኋላ ወደተለመደው የ”ምርመራ” ክፍል ተጠርቼ ተመሳሳይ ጥያቄና ዱላ አስተናገድኩ፡፡ ይህኛው ካለፉት ቀናት የሚለየው በእረፍት ቀን መሆኑ ነው፡፡ በጣም የገረመኝ ነገር ቢኖር ክብሩን የሰው ልጅ ለማሰቃየት ሙሉ የእረፍት ጊዜያቸውንም በመግረፍ የሚያሳልፉ መሆናቸው ነው፡፡ ሰኞ እለት በግምት ከምሽቱ 2፡30 አካባቢ ወደ ምርመራ ክፍል ተወሰድኩ፡፡ ምርመራው በተለመዱ ጥያቄዎችና ዱላ ተጀመረ፡፡ በድብደባው ወቅት ከመርማሪዎች አፍ በሚወጣው የአልኮል ጠረን መርማሪዎቹ ሞቅ እንዳላቸው ተረድቻለሁ፡፡ የተወሰነ ከደበደቡኝ በኋላ ልብሴን እንዳወልቅ ትዕዛዝ ተሰጠኝ፡፡ እኔም ልብሴን እንደማላወልቅ ነገርኳቸው፡፡ በዚህም ከአሁን ቀደሙ ለየት ያለ ከባድ ድብደባ አስተናገድኩ፡፡ ድብደባው ከአቅሜ በላይ ሲሆን ግን ከውስጥ ሱሪዬ ውጭ ያለውን ልብሴን ለማውለቅ ተገደድኩ፡፡ የውስጥ ሱሪዬንም እንዳወልቅ አዘዙኝ፡፡
“አላወልቅም” አልኩ
“ለምን?” አሉኝ፡፡
“ኃይማኖታችን፣ ባህላችን፣ የአባቶቻችን ስርዓት የሰው ልጅ በእንዲህ አይነት ሁኔታ እንዲቀጣ አይፈቅድም” አልኳቸው፡፡ አሁንም አልተሳካልኝም፡፡ ከፍተኛ ድብደባ፣ ከዚህም በላይ በጣም ክብረ ነክ የሆኑ ስድቦችን ሰደቡኝ፡፡ ከዚህ የማሰቃያ ክፍል ስመለስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዮሴፍን ታሪክ በማንበብ ራሴን ለማረጋጋት ሞከርኩ፡፡ ያች ቀን በዚህ መልኩ አለፈች፡፡
አርብ ሐምሌ 18/2006 ዓ.ም የገብርኤል ዋዜማ ከቀጨኔ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አመታዊ ክብረ በዓል በእልልታ ደምቋል፡፡ የዕጣኑ መዓዛ አልደረሰንም እንጅ ዝማሬው በደንብ ይሰማን ነበር፡፡ በዚህ ምሽት ያለ ወትሮው “ምርመራ” የተጀመረው ከሌሊቱ 5፡00 ገደማ ላይ ነበር፡፡ ከገባሁበት ቀን ጀምሮ የምግብ ፍላጎቴ በጣም ወርዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየጊዜው የሚፈፀምብኝ ድብደባና ሞራላዊ በደሎች ተጨምረው የዚህን ቀን ድምደባ መቋቋም አቅቶኝ ራሴን ስቼ እንደወደኩ አስታውሳለሁ፡፡
ቅዳሜንና እሁድን ከማዕከላዊ ምርመራ አንጻር በ”ሰላም” አሳልፌ ሰኞ ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ ወደ ምርመራ ክፍል ተወሰድኩ፡፡ “መርማሪው” ደስታ ይባላል፡፡ ከእሱ በፊት ከፍተኛ አመራርነት ላይ ያሉት የደህንነት አባላት መርምረውኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ለእሱ አሳልፈው የሰጡኝ፡፡ “መርማሪ” ተብዬው ደስታ ማዕከላዊ ከገባሁ ጀምሮ ግቢው ውስጥ አይቼው ከማላውቀው ሌላ የደህንነት አባል ጋር ሆኖ ጠበቀኝ፡፡ ወደ ክፍሉ እንደገባሁ እንግዳው የደህንነት አባል “የሽብር ቡድኑ አላማ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ እኔም “እኔኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ ባህልና ወግ ተኮትኩቼ ያደኩ፡፡ እኔ አሸባሪ ከሆንኩ የሚሸበረው የየት ሀገር ዜጋ ነው?” ብዬ ስመልስለት “መርማሪው” ደስታ ንግግሬን በድብደባ አስቆመኝ፡፡ እንግዳው ደህንነት እንደሚገድለኝ ከዛተብኝ በኋላም ወደ ጨለማና ቀዝቃዛው ክፍሌ ተመለስኩ፡፡ ያም ሆኖ እኔ ላይ የደረሰው በደልና ግፍ በዚህ የማሰቃያ ክፍል ስቃይ ከሚደርስባቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ግን ደግሞ ማዕከላዊ ከሚገኙት ጨካኝ ገራፊዎች መካከል ምን ላርግልህ፣ ምህረት፣ ደስታ፣ … የተባሉና ሌሎችም ስማቸውን የማላውቃቸው በየ ተራ “ጥሩ” ገራፊነታቸውን ሞክረውብኛል፡፡
በማዕከላዊ ቆይታዬ የገረመኝ ነገር ቢኖር መርማሪዎች በሙሉ በትዕዛዝ የተሰፉ እስኪመስሉ ድረስ ተመሳሳይ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአቅምና የብቃት ማነስ ችግር ሁሉንም ያመሳስላቸዋል፡፡ ሁሌም ከአፋቸው የማትጠፋ “ተናገር!” የምትል ቃል አለች፡፡ ምን እንደሚናገር ባያውቀውም በእሱ እጅ የሚገኝ ማንኛውም እስረኛ መናገር አለበት፡፡ ያው በቁጣ “ዝም በል!” የምትል ከመርማሪዎቹ የማትጠፋ ሌላ ቃል እስከሚነገረው ድረስ፡፡ “እንዳያልፉት የለም፣ ያ ሁሉ ታለፈ” እንዳለው ብአዴን ይህ ሁሉ በደልና ግፍ አልፈን ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተዘዋወርን በኋላም ምንም እንኳ የማዕከላዊ ድብደባ ባይኖርም የችሎቱ ድብደባ ከማዕከላዊ ባልተናነሰ መልኩ ሲያሸማቅቀን እና ሲያመላልሰን ይኸው እንደቀልድ ሐምሌ 5/2007 አንድ አመት ሊሆነን ነው፡፡ ዛሬ በቂልንጦ እስር ቤት ሆኜም ብዙ ነገሮች ያሳስቡኛል፡፡ ሀገሬ በአምባገነኖች ስር ሆና፣ ዜጎች በጨካኝና ዘግናኝ ድብደባ እየተሰቃዩ እስከ መቼ እንቀጥላለን? በንፁሃን ዜጎች ላይ “አሸባሪ” የሚል ክስ እየተለጠፈ እስከ መቼ ይሰቃያሉ? በእስር ቤት ከደረሰብኝና እየደረሰብኝ ከሚገኘው ስቃይ ይልቅ ለውጥ! ለውጥ! ለውጥ! ነፃነት! ነፃነት! ነፃነት! የሚል ድምፅ ይሰማኛል፡፡ እውነት ይህን ድምፅ በቅርቡ በኢትዮጵያ ምድር እውን ሆኖ እናየው ይሆን?
ገራፊዎቻችና አሰቃዮቻችን ሆይ!
ያደረጋችሁብን ሁሉ ፅናታቸውንና የሀገር ፍቅራችን ይበልጡን አጠናከረው እንጅ ቅንጣት ታክል አልቀነሰብንም፡፡ ግን ለራሳችሁ ስትሉ ግፍና ሰቆቃውን ባታበዙት ይሻላል፡፡ እደግመዋለሁ! ለራሳችሁ ስትሉ ጉድጓዱን አርቃችሁ አትቆፍሩት፡፡ እኛ መከራውንና ግፍን በፅናት የምንቀበለው እናንተን ወደ ትልቅ ጉድጓድ ገፍትረን ነፃ ለመውጣት ሳይሆን በጋራ፣ እኛም፣ እናንተም አብረን ነፃ እንወጣ ዘንድ ነውና! (ፎቶ: ለማሳያ ከኢንተርኔት የተገኘ)
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
(ከባህሩ ደጉ፤ ቂሊንጦ እስር ቤት ለነገረ ኢትዮጵያ የተላከ)
ምንጭ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment