Friday, October 25, 2013

የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ተሰደዱ

ሲኖዶሱ ያሳለፈውን ውሳኔ ፓትርያርኩ ቀለበሱት 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አመታዊ ስብሰባውን እያከናወነ በሚገኝበት ሰዓት በተለያዩ አነጋጋሪ ክስተቶች መታጀቡን የፍኖተ ነጻነት ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የሲኖዶሱ ስብሰባ ከመጀመሩ አስቀድሞ የፌደራል መንግስት ጉዳዩች ሚኒስትር ተወካዩች በተገኙበት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰዎች፣የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ጳጳሳት በተገኙበት በተካሄደ ውይይት ጳጳሳቱ የመንግስት ተወካዩች ላቀረቡት ሐሳብ ያላቸውን ልዩነት በመግለጽ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ እጁን እንዲሰበስብና ለህገ መንግስቱ ተገዢ እንዲሆን መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡በዚህ ስብሰባ ወቅት የሚመሩትን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት በመወከል ተሳታፊ የነበሩት ሃላፊው ያለ ቤተ ክህነቱና ሃገረ ስብከቱ እውቅና ውጪ ወደ አሜሪካ ማቅናታቸው ተረጋግጧል፡፡
የአዲስ አበባው ሃገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መጋቤ አዲስ ይልማ ቸርነት ለስደት ሲዳረጉ ምክትላቸው የነበሩት አቶ ዩናስ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል፡፡መጋቤ አዲስ አገራቸውን በመልቀቅ ለስደት የተዳረጉበትን ምክንያት ከወቅቱ ፓትርያርክና አመራራቸው ጋር ስምምነት በማጣታቸው የተነሳ መሆኑን ምንጮቻችን ግምታቸውን አኑረዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በትናንትናው የስብሰባ ውሎው ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ በአብላጫ ድምጽ ወስኖባቸው የነበሩት የአዲስ አበባው ሊቀ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ በዛሬው ዕለት ፓትርያርኩ አቡነ ማቲያስ ‹‹አዲስ አበባ የእኔ ልዩ ሐገረ ስብከት በመሆኑና ማንም ሊያዝበት ስለማይችል ሊቀ ጳጳሱ በቦታቸው እንዲቀጥሉ በመወሰን የትናንቱን ውሳኔ ሽሪያለሁ››ማለታቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡
ሲኖዶሱ በማድረግ ላይ የሚገኘውን አመታዊ ስብሰባ ነገ የሚያጠናቅቅ ቢሆንም ሂደቱን በመከታተል ጋዜጠኞች እንዳይዘግቡ ሲኖዶሱ ለጋዜጠኞች ወደ ስብሰባው የመግቢያ ፈቃድ ከልክሏል፡፡

ምንጭ UDJ

No comments:

Post a Comment