Monday, November 11, 2013

ኢህአዴግና የሃይማኖት ነፃነት (ተመስገን ደሳለኝ)

ኢህአዴግና የሃይማኖት ነፃነት

…ኢሠፓ መራሹ መንግስት በኢህአዴግ ከተተካ ጥቂት ወራት ቢያልፈውም፣ የተራዘመው የእርስ በእርስ ጦርነት
ያልደረሰባቸው በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞችን ገና በቅጡ አልተቆጣጠራቸውም፤ በአናቱም
በኢሠፓ መንግስት ሽንፈት ሳቢያ እንዲበተን ከተገደደው የሀገሪቱ መደበኛ ወታደር፣ አብዛኛው ከእነ ትጥቁ
የትውልድ መንደሩንና ቤተሰቡን መቀላቀሉ በሀገሪቱ ላይ ከባድ ፍርሃት አንብሯል፤ በሰላም ወጥቶ ለመመለስ
እርግጠኛ መሆን የማይቻልበት ከበባዊ አየርም አስፍኗል፡፡ በበርካታ ቦታዎች ተጠንተውና ታቅደው የሚፈፀሙ
ወንጀሎችም፣ ከአምስት እስከ አስራ አምስት በሚደርሱ ወታደሮች የተደራጁ ልዩ ልዩ ህገ-ወጥ ቡድኖች
በየማዕዘኑ እያቆጠቆጡ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ቆዳ ስፋትና የነዋሪዎቿ የአኗኗር ዘይቤን በቀላሉ ለመልመድ የተቸገሩት
‹ተጋዳላዮች›፣ ለትንሽ ትልቁ ግርግር ጠብ-መንጃን እንደ መፍትሄ መምረጣቸው ችግሩን አባብሶታል፤ ጉዳዩ እያሳሰባቸው የሄደው
የኢህአዴግ ዋነኛ መሪዎችም እንዲህ አይነት አለመረጋጋቶችንና ስርዓት አልበኝነቶችን ለመቆጣጠር የመንፈሳዊ መሪዎች አስተዋፅኦ ወሳኝ
መሆኑን ከስምምነት ላይ ደርሰዋል (እንደቀድሞው ስርዓቶች ሁሉ ‹ለቅብሉነት› ከሚጠቀሙበት በተጨማሪ ማለት ነው)፤ ይሁንና
በመንበሩ ላይ የነበሩት አቡነ መርቆርዮስ ሀገር ለቀው እንዲወጡ በመደረጉ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡

ይህን ጊዜም ነው ከ1973 ዓ.ም. ጀምሮ መኖሪያቸውን አሜሪካን ሀገር ያደረጉ አንድ መንፈሳዊ አባት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ
የተወሰነው፤ በጥሪው መሰረትም ወደ ሀገራቸው ሲገቡ መንግስት የክብር አቀባበል አደረገላቸው፤ እኚህ ሰው ዛሬ በፓትርያርኩ መንበር
የተቀመጡት አቡነ ማቲያስ ነበሩ፡፡ ሆኖም ከሳምንት ሽር-ጉድ በኋላ አቡኑ የኢዲዩ አባል እንደነበሩ በአመራሩ አካባቢ ወሬው በስፋት
መሰራጨቱ ያልተጠበቀ ዱብ-ዕዳ አስከተለ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢህአዴግ እና ኢዲዩ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ትግራይና ጎንደር ውስጥ
በርካታ መስዋዕትነት ያስከፈለ ውጊያ ማድረጋቸው ብቻ አይደለም፤ የመጀመሪያዎቹ ሊቀ-መንበሮች ስሁል ገሰሰና መሀሪ ተክሌ (ሙሴ)
‹‹የተገደሉት በኢዲዩ ነው›› የሚለው ወሬ በድርጅቱ ውስጥ ከጫፍ ጫፍ የተናኘና የታመነበት ጉዳይ መሆኑ ነበር፤ በዚህም ላይ የህወሓት
መሪዎች ግራ ዘመምነት ተደማምሮ አቡነ ማቲያስ በወቅቱ ወደ ታሪክነት ከተቀየረ ዓመታትን ባስቆጠረው ‹‹ኢዲዩ›› ተፈርጀው፣
ከታጩበት የ‹ፕትርክና መንበር› ተገፈተሩ፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር አብላጫውን የትጥቅ ትግል ዘመን በአሜሪካ ያሳለፉት አሰፋ ማሞ እና ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ‹ውድብ› የሰጠቻቸውን
ተልዕኮ ተቀብለው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ያመሩት፤ እናም ቀድሞም ትውውቅ ወደ ነበራቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘንድ ሄደው
ለ‹ፕትርክና ወንበር› መታጨታቸውን አበሰሯቸው፡፡ በእንዲህ ያለ መንገድ መንግስት የቀባቸው ታጋዩ አባ ጳውሎስም እስከ ህልፈታቸው
ድረስ አወዛጋቢ መሪ ሆነው ዘልቀዋል (በነገራችን ላይ በአሜሪካን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ ከሲኖዶሱ ተነጥሎ የቆመ ቤተ-ክርስቲያን
የመሰረቱት አቡነ ጳውሎስ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ አቡኑ ደርግ ለጥቂት አመት አስሮ ከለቀቃቸው በኋላ ወደ አሜሪካ ሄደው የፈጣሪያቸውን
ሰማያዊ መንግስት ሲሰብኩ ቆይተው፣ የህወሓት ሠራዊት ክንዱ እየበረታ በቁጥጥሩ ስር ያዋላቸው ከተሞችም እየበዙ ሲሄዱ፣ እርሳቸውም
ስብከታቸውን ወደ ትግርኛ ቋንቋ ከመቀየራቸውም በላይ፣ ለ‹ነፃ አውጪ›ው ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ያሰባስቡ ጀመር፡፡ የስርዓት ለውጥ
መደረጉን ተከትሎም በፖለቲከኞች በተቀነባበረ ሴራ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ቦታ የተለዋወጡት አቡነ መርቆርዮስም፣ እዛው አሜሪካን ሀገር
‹ተተኪ›ያቸው የጀመሩትን ብሔር ተኮርና ከሲኖዶሱ የተገነጠለ ቤተ-ክርስቲያን አስፋፍተው ዛሬ ለደረሰበት ‹የጎንደሬ ማሪያም›፣ ‹የትግሬ
ገብርኤል›… ለተሰኘ አሳፋሪ ክፍፍል ዳርገውታል፡፡ በርግጥ ለአቡኑ ከሀገር መባረር የኢህአዴግ እጅ እንዳለበት እንድናምን የሚያስገድደን
በቅርቡ ታምራት ላይኔ ‹‹በእኔ ፊርማ ነው ያባረርናቸው›› ማለቱን ዊክሊክስ ካደረሰን መረጃ በተጨማሪ፣ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ህወሓት
በተቆጣጠራቸው በትግራይና ወሎ ነፃ መሬቶች በሚገኙ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎችን ቀስቅሶና አደራጅቶ ፓትርያርኩ ላይ ‹‹ሽጉጥ ታጣቂ
ጳጳስ››፣ ‹‹ቀይ ደብተር ያለው /ለኢሠፓ አባላት የሚሰጥ ነው/ የሸንጎ ተወካይ››… የመሳሰሉትን መፈክሮች እያሰሙ በተቃውሞ ሰልፍ
እንዲያወግዟቸው ማስተባበሩን ስናስታውስ ነው)

 ዛሬስ የሃይማኖት ነፃነት የት ድረስ ነው?
ከላይ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብዬ በደምሳሳው ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት፣ ኢህአዴግ በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ጣልቃ ማስገባት
የጀመረው ክንዱ ሳይፈረጥም፣ ገና በርሃ ሳለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ጣልቃ-ገብነት ዛሬም ድረስ ተባብሶ ቀጥሏል፤ ምንም እንኳን
በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባ በደፈናው ከህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 11ን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ለማስተባበል ቢሞክርም፣
ያለፉት ዓመታት ተጨባጭ ተግባሮቹ የሚመሰክሩት ግልባጩን ነው፡፡ ድርጅቱ ራሱም ቢሆን ጥያቄው በተነሳ ቁጥር ከህገ-መንግሥቱ
አንቀፅ 11ን የሚጠቅሰው ለማጭበርበሪያነት እንጂ ህጉ ገቢር አለመሆኑን ሳይረዳ ቀርቶ አይደለም፡፡ ተፈራ ዋልዋም በ1998 ዓ.ም
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ህዳር/ታኀሣሥ ወር ከታተመችው ‹ሐመር› መፅሄት ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ ጉዳዩን አስመልክቶ የሰጠው አስተያየት የኢህአዴግን
አጭበርባሪነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡-

‹‹ኢህአዴግ እኮ የሚመራው መንግስት፣ በደርግም ጊዜ፣ በኃይለ ሥላሴም ጊዜ እንደ ሚታወቀው ‹የቤተ-ክርስቲያን ሥራ አስኪያጅ
ሹምልን› ተብሎ ተጠይቆ ‹የለም ራስዋ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ትሾማለች እንጂ እንደ ቀድሞው መንግስት አይሾምላችሁም› የሚል መልስ የሰጠ
መንግሥት ነው፡፡››

 በህዝበ ሙስሊሙ ተመርጦ ለእስር የተዳረገው የኮሚቴ አባላትም በአንድ ወቅት ለሚመለከተው የመንግስት ባለስልጣን የፃፈው ደብዳቤ
ጣልቃ ገብነቱን በግልፅ ያሳያል፡-

‹‹መንግስት እንደ መንግስት ህዝቡ ተበድያለሁ፣ ምርጫ ይካሄድ፣ የመጅሊሱን አመራር አላመንኩበትም፣ አልመረጥኩትም፣ ውክልና
የለውም እና ህገ ወጥ ነው ያለውን አካል ህገ ወጥነቱ እንዲረዝም ምርጫውን እሱው እንዲያካሄድ መወሰን ህዝብን ግራ አጋቢ ነው››

ስርዓቱ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ለማሳመን ይህን ያህል ቢዳክርም፣ በቅርቡ ‹‹የፀረ-አክራሪነት ትግል፣ የወቅቱ ሁኔታና
ቀጣይ አቅጣጫዎች›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ባለ 44 ገፅ ሰነድ፣ መንግስት በዘወርዋራ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ሙሉ
በሙሉ የሚያምን ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡-

‹‹የመንግስት መዋቅራትን ሴኩላር መንግስት መሆናችንን አውቆ የመንግስትን መዋቅር ተጠቅሞ የራሱን ሃይማኖት መሰረት ያደረገ
አገልግሎት ከመስጠት ሙሉ በሙሉ ያልፀዳ መሆኑን የተለያዩ ጥቂት የማይባሉ ገሐድ የወጡ መገለጫዎች አሉ፡፡ እንዲያውም የትኛውም
አክራሪ ኃይል ከመዋቅር (ከመንግስት) አካል ‹በርታ› ሳይባልና ‹ሽፋን› ሳይሰጠው የሚንቀሳቀስ እንደሌለ በገሐድ አማኞቹ ይገልጻሉ፡፡››

መቼም ይህንን ያነበበ ዜጋ መረጃው የተገኘው በመንግስት ከተዘጋጀ ሰነድ ሳይሆን በ‹ኒዮ ሌብራሊስት›ነት ከተፈረጁት እነ‹ሂዩማን ራይት
ወች› እና ‹አምኒስቲ ኢንተርናሽናል› ቢመስለው አይደንቅም፤ ሀቁ ግን ይኸው ነው፡፡ አገዛዙ ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ‹መንግስትና
ሃይማኖት› እንዲለያዩ ማድረጉን ሲደሰኩር ከመቆየቱም በላይ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን የዘገቡ ጋዜጠኞችን ከስሶ ዛሬም ድረስ
ፍርድ ቤት እያመላለሳቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ይመስለኛል አለም አቀፍ ማህበረሰብን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን
በእስር ላይ የሚገኙት የእነ አቡበከር መሀመድ ክስ፣ የሼህ ሁሴን ኑር ግድያ፣ በማህበረ ቅዱሳን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ውንጀላዎችና መሰል
ፍረጃዎችን አምኖ ለመቀበል የተቸገሩት፡፡

 ያም ሆነ ይህ ሃይማኖትን ብቻ ሳይሆን እድርና ዕቁብንም ሳይቀር ‹ካልተቆጣጠርኩ ሞቼ እገኛለሁ› በሚል የቁጥጥር ልክፍት የተያዘው
ኢህአዴግ፣ በተለይም ‹‹99.6 ድምፅ አግኝቼ አሸንፌያለሁ›› ብሎ ካወጀበት ከምርጫ 2002 ማግስት ጀምሮ ‹‹አናት ላይ ከተቀመጡ
መሪዎቻቸው በቀር ሙሉ በሙሉ አልተቆጣጠርናቸውም›› የሚላቸውን የእስልምናና የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነትን ዋነኛ አጀንዳው
አድርጎ እየሰራ ለመሆኑ በርካታ መረጃዎች አሉ፡፡ በ2003 ዓ.ም. ህዳር ወር ‹‹የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና
የኢትዮጵያ ህዳሴ›› በሚል ርዕስ በአቶ መለስ ዜናዊ ተሰናድቶ የተሰራጨው ጥራዝ፣ የስርዓቱን ቀጣይ አካሄድና ይህንን ሁናቴ የሚያሳይ
ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ዛሬም ድረስ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ መንግስት የሚያዘጋጃቸው ስልጠናዎችም ሆኑ ጥናታዊ ፅሁፎች መነሻ
ሃሳባቸው ይኸው ዳጐስ ያለ ጥራዝ እንደሆነ ይነገራል፡፡

 ጥራዙ የእምነት ተቋማትን በተመለከተ ከገጽ 128-132 ያካተተው ሃሳብ፣ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ምክንያት ‹‹የሃይማኖት
አክራሪነት›› መሆኑን ከጠቃቀሰ በኋላ፣ ችግሩን ‹‹ተኪ የሆነ ልማታዊ አስተሳሰብ›› በማምጣት ማስወገድ እንደሚቻል ይመክራል፡፡
ይህንን ከግብ ለማድረስ ደግሞ ሚዲያዎችንና ተያያዥነት ያላቸውን ማህበራት መጠቀሙ አዋጭ እንደሆነ ይተነትናል፡፡ የኢህአዴግ አባላት
በየእምነት ተቋሞቻቸው ያሉ ማህበራትን በአይነ ቁራኛ መከታተል እንዳለባቸውም ያሳስባል፡- ‹‹(አባላት) ከእምነት ተቋማት ውጭ
ባላቸው አደረጃጀት አማካይነት በሰፊው መስራት አለብን››፡፡ በርግጥም የእስልምና እምነት ተከታዮች ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ይከበር››
የሚል ተቃውሟቸውን ባጠናከሩበት ሰሞን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ሙስሊም አባላቱን ለብቻ እየሰበሰበ
እንቅስቃሴውን የማክሸፍ ስራ መስራት ግዴታቸው መሆኑን የሰበከው ከዚሁ መለስ ዜናዊ አዘጋጅቶት ከነበረው ጥራዝ ነው ብሎ
መከራከር ይቻላል፡፡

ከጣልቃ ገብነት ወደ ጠቅላይ ተቆጣጣሪነት

 በዘወርዋራም ቢሆን በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መገባቱን ሙሉ በሙሉ የሚያምነው ከላይ የተጠቀሰው ሰነድ በሀገሪቱ ‹‹የሃይማኖት
አክራሪነት›› መከሰቱን ካተተ በኋላ፣ ዋነኛ ተጠያቂዎች አድርጎ ያቀረበው እንደወትሮው ሁሉ ለተደጋጋሚ መሸማቀቅ የተዳረጉትን
መንፈሳዊ መሪዎችንና ማህበራትን ሳይሆን መንግስትን ነው፡-
‹‹የመንግስት መዋቅራችን አካል ሆነው አክራሪነቱን በድብቅም/በገሐድም የሚደግፍ አካል በፌዴራልም በክልልም ከሞላ ጎደል የሚታወቁ
ናቸው፡፡ እነዚሁ አካላት በተቻላቸው ሁሉ በመድረክ ጤናማ እየመሰሉ የሚኖሩ ናቸው፡፡ የፀረ-አክራሪነቱን ትግል ማጧጧፍ
የሚፈልገውን የመዋቅር አካልም ይሁን የህዝብ አካል በተደራጀና በመረባቸው አማካኝነት ከፍተኛ ጫና የሚያሳድሩ፤ የተቋማቸውን ምቹ
ሁኔታ ተጠቅመው በፀረ-አክራሪነት የሚንቀሳቀሱትን አካል የሚቀጡ፣ አሉባልታ እየፈጠሩ የሚያሸማቅቁ፣ ሆን ብለው ድጋፍ የሚነፍጉና
በሐሰት ምስክርም ጭምር ዜጐችን የሚያሳስሩ ናቸው፡፡ የመንግስትን አቅሞች ተጠቅመው አክራሪነትን የሚያስፋፉና ከአክራሪነት
እንቅስቃሴ ጋር በተለያዩ ጥቅሞች የተሳሰሩ ናቸው፡፡››

እነሆም በእንዲህ አይነቱ የውንብድና ተግባር የተሰማሩ ባለስልጣናት የተሰባሰቡበት፣ ውንብድናው መኖሩንም የሚያምን መንግስት
አንድም ተጠያቂዎቹን ለህግ አሳልፎ አለመስጠቱ፣ አሊያም ሥልጣኑን በፍቃዱ አለመልቀቁ በሀገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ
ለመረዳት ነብይነትን አይጠይቅም፡፡ በአናቱም ስርዓቱ ለህግ የበላይነት ተገዥ አለመሆኑን የሚያሳየው በዚህ ደረጃ ‹‹ችግሩን
ተረድቸዋለሁ›› እያለም እንኳ፣ ዛሬም የቅጣት በትሩን ያሳረፈው ከመዋቅሩ ጋር አንዳችም ንክኪ በሌላቸው መንፈሳዊ መሪዎች ላይ መሆኑ
ነው፡፡ በርግጥ ይህ አይነቱ አሰራር ከአምባገነን አስተዳደር መገለጫዎች አንዱ ነው፡፡ ኢህአዴግም ያለፉትን አራት ምርጫዎች ጨምሮ
በተለያየ ጊዜ የዴሞክራሲም ሆነ የሰብዓዊ መብትን በአደባባይ መጣስ፣ የሀሰት ክሶችንና ፍረጃዎችን እንደ ምክንያት መጠቀም ነባር ስልቱ
እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በማህበረ ቅዱሳን ላይ እየዘረዘረ ያለው የፈጠራ ውንጀላ እና ለሙስሊሙ ጥያቄ ‹‹መፍትሄ አፈላላጊ›› ተብለው
በተመረጡት የኮሚቴ አባላት ላይ የወሰደው እመቃ መግፍኤ ይኸው ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ ከዚህ ቀደም በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ለሚፈፅመው የግፍ ግድያዎች ይሰጥ የነበረውን ምክንያት በመንፈሳዊ ሰዎችም
ላይ ያለአንዳች የይዘት ለውጥ ለመጠቀም አላመነታም፡፡ እንደሚታወሰው በድህረ-ምርጫ 97 በአምቦና በኢተያ በታጣቂዎች የተገደሉትን
የኦህኮ አባላት ከተፈጥሮ ህመም ጋር አያይዞት ነበር፡፡ በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጀመሪያ በተካሄደው የሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ ደግሞ
የምዕራብ ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሄኖክ ‹‹ቤጊ›› ወረዳ በመንግስት ባለስልጣናት ተፈፀመ ያሉትን ግድያ ለፌደራል
ጉዳዮች ሚኒስትር ተወካይ፡-

‹‹በቤተ-ክርስቲያን 70 ሜትር ርቀት ላይ የሌላ እምነት ተከታዮች የራሳቸውን ቤተ-ክርስቲያን እንዲሰሩ መፈቀዱን ከተቃወሙት መካከል
አንድ ዲያቆን ተደብድቦ በሶስተኛው ቀን ህይወቱ ሲያልፍ ‘በወባ በሽታ ነው የሞተው’ ተብሎ ለፍርድ ቤቱ የሐሰት ማስረጃ ከዶክተሩ
እንዲቀርብ ታዘዘ፡፡›› ማለታቸውን መጥቀሱ ለጉዳዩ አስረጂነት በቂ ይመስለኛል፡፡

የሆነው ሆኖ አገዛዙ በዘረጋው ግዙፍ መዋቅሩ ውስጥ ያልታቀፉ ማህበራትንም ሆነ የሃይማኖት ተቋማትን የስጋት ምንጭ አድርጎ ማየቱ፣
በእምነት ነፃነት ላይ ጣልቃ ለመግባትም ሆነ ምንም አይነት ገለልተኛ ተቋማት እንዳይኖሩ እንቅልፍ አጥቶ መስራቱን ያሳያል ብዬ
አስባለሁ፤ በሚቆጣጠራቸው የኤሌክትሮኒክስና የህትመት ሚዲያዎች ቀን-ከሌት የፕሮፓጋንዳ ከበሮ የሚመታበት የ‹አክራሪ›ነት ፍረጃም
መነሾው ይህ ይመስለኛል፡፡ ሰነዱን ከዚህ ቀደም ካየናቸው ለየት የሚያደርገው፣ በመንግስት መዋቅር ውስጥ አሉ ከሚላቸው ወንበዴዎች
በተጨማሪ የሚከስሳቸውን ማህበራት በደፈናው ‹‹በክርስትና እምነት ውስጥ ያሉ›› ብሎ አለማለፉ ነው፤ ቃል በቃል እንዲህ ይላልና፡-
‹‹በማሕበረ ቅዱሳን ውስጥ የመሸጉ የትምክህት ኃይሎች፣ ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች አካል በመሆን በጋዜጣና በመጽሔት ህዝባችንን
ለአመፅና ሁከት ለማነሳሳት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ …በራሳችንም ኃይል እንደሌላው ሰልፍ ልንወጣ ይገባል በሚል የአመፅና የሁከት
ቅስቀሳ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡››

ይህ ሁኔታ መንግስት መንፈሳዊ ማህበራትን ጠቅልሎ ለመቆጣጠር በመፈለጉ ለተቃዋሚዎች ያሰመረውን ‹ቀይ መስመር› መጣሱን
ያሳያል፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማትን የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ መጠቀሙ አልበቃ ብሎት፣ ወደ ማህበራቱ መዞሩ
ነው፤ በገሀድ እንደሚታወቀው የክርስትናም ሆነ የእስልምና መንፈሳዊ መሪዎች በተለያየ ጊዜ ከስርዓቱ ጎን ተሰልፈው ‹ናዳን ለመግታት›
ያደረጉት አበርክቶ በቀላሉ የሚገመት አለመሆኑ ነው፡፡ በርግጥም ‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› በሚል አስተምህሮ የሚያድሩ፣ ደሞዛቸው በምድር
ያልሆነ መንፈሳዊ አባቶች በድህረ ምርጫ 97 ህፃናትን ሳይቀር በጥይት የፈጀውን ስርዓት ማውገዝ ቀርቶ መምከር ያለመፈለጋቸው
ምክንያት ፍርሃት ብቻ ሳይሆን፣ የግል ጥቅምን ታሳቢ ያደረገው ግንኙነታቸው ያሳደረው ተፅዕኖ ይመስለኛል፡፡ ከቅዱሳን መጽሐፍት
ይልቅ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ‹አዳኝ› አድርገው የመቀበላቸው መግፍኤ ይኸው ነው፡፡ ኢህአዴግም ‹ነገረ መለኮት›ን ለሲኖዶሱና
ለመጅሊሱ አስከማስተማር ድረስ የደፈረው፣ የእነርሱ ‹ለሁለት ጌታ› መገዛት ነው፤ ለፈጣሪና ለገንዘብ፡፡

 የሲኖዶሱ እና የመንግስት ፍጥጫ
 በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ዶግማ ‹‹ሲኖዶስ›› ከፍተኛውን ስልጣን የሚይዝ ሲሆን፣ ፓትርያርክንም የመሾምና የመሻር ስልጣን
አለው፡፡ ሆኖም ይህ የላዕላይ መዋቅር እስከ አቡነ ጳውሎስ ህልፈት ድረስ ለእርሳቸውም ሆነ ለስርዓቱ ሰጥ-ለጥ ብሎ የሚገዛ ‹ጥርስ
የሌለው አንበሳ› በመሆኑ ለትችት ከመዳረጉም በላይ በአማኞች ዘንድ ለመንፈሳዊ አባቶች የሚሰጠውን ክብርም ነስቶት ቆይቷል፡፡
 ይሁንና በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጀመሪያ በተካሄደው ‹‹የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 32ኛው አመታዊ
ስብሰባ›› ላይ ከመንግስት የተወከሉ ኃላፊዎች ‹‹የብዝኃነት አያያዝ፣ አክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎቹና መፍትሔዎቹ›› በሚል ርዕስ
ያቀረቡትን ጥናት ተከትሎ ከስድስት በላይ ጳጳሳት ቀድሞ ባልታየ መልኩ ጠንካራ ተቃውሞ ማቅረባቸው፣ በብዙዎች ዘንድ የሀይማኖት
መሪዎች ለመንፈስ ልዕልናቸው ሊገዙ ይሆን? ከምድራዊውን ይልቅ ሰማያዊውን ሊመርጡ ይሆን? ‹እመን እንጂ አትፍራ› የሚለውን
አስተምሮአቸውን ሊተገብሩ ይሆን? የሚል ጥያቄ አጭሯል፡፡ በዕለቱ የመጀመሪያው ተናጋሪ የነበሩት የሰሜን ወሎና ዋግ ኹምራ አህጉረ
ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በጥናቱ ላይ መቻቻል መጥፋቱን አስመልክቶ የቀረበውን ድምዳሜ እንዲህ ሲሉ ነበር ያጣጣሉት፡-
‹‹ይኼ አክራሪነት ጽንፈኝነት የሚለውን ቋንቋ እናንተው ናችሁ ያሰማችሁን፤ ከዚህ በፊትም አይታወቅም፤ በደርግም ይሁን በሌላ፡፡
እንደገና ደግሞ ብዙ ጊዜ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት እያላችሁ እድሜ ሰጥታችሁ ያበለጸጋችኋቸው እናንተው ናችሁ፡፡››

በርግጥም አቡኑ የተቹት ስርዓቱ የፕሮፓጋንዳው ፋሽን ያደረገውን ‹‹መቻቻል››ን ብቻ አይደለም፤ ‹‹በመቃብሬ ላይ ነው የሚሻሻለው››
የሚለውን የመሬት ፖሊሲንም ነው፡፡ በተጨማሪም ጥናት አቅራቢዎች በነገስታቶቹ ዘመን ቤተ-ክርስቲያኗ በርካታ መሬት መያዟንና ‹ሁሉ
በእጇ ሁሉ በደጇ› እንደነበር አድርገው ማቅረባቸውንም አልተቀበሉትም፡፡

‹‹በፊት መሬትም ህዝብም የነገስታቱ ነበር፤ አሁንስ የማን ነው? ይልቁንም ከአንድ ቤት ‹ግድግዳው የቤቱ ባለቤት ነው፣ ሳሎኑ የመንግስት
ነው› የሚለው አዋጅ የአሁኑ አይደለም እንዴ? ለኢትዮጵያዊነቱ ዋስትና የለውም፤ ይኼ የእኔ ነው የሚለው ከሌለ ምንድን ነው? ይህች
የእኔ የኢትዮጵያዊነቴ መገለጫ ናት ካላለ፣ ምንድን ነው ኢትዮጵያዊነት? አሁንም መሬቱም ህዝቡም የእናንተው ሁኖ ሳለ ለፊቱ፣ ለነገስታቱ
መስጠታችሁ በምን ተመልክተውት ነው?››

የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እንድርያስም በሚያስተዳድሩት አካባቢ ያለውን የመንግስት ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖን
ከዘረዘሩ በኋላ፣ ለተሰነዘረው ፍረጃና ማሸማቀቂያ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡-
‹‹የተበደለ ሰው ሲናገር ‹ፖለቲካ ተናገረ› እየተባለ የውሸት ውሸት ሲያተራምሱን የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡… እንዴ! የመንግስት ስልጣን
የተረከቡ ወንድሞች የእኛን አፍ፣ የእኛን አንደበት ብቻ ነው እንዴ የሚጠብቁት፣ ለሌሎቹ ሞራል ይሰጣሉ ማለት ነው? …ለምንድን ነው
ግን በሽፋን የምትጠቀሙብን? መንግስት እኛን ሽፋን አድርጎ ነው ሲበዘብዘን የምንኖረው፡፡ ሌባውም ቀጣፊውም ሰርጎ ገቡም
ሲያጭበረብረን ሲያታኩሰን መንግስትን ሽፋን አድርጎ ነው፡፡››

የወላይታ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅም በተመሳሳይ መልኩ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ቤተ-ክርስቲያኗ ስትቃወም
ጉዳዩን ወደ ፖለቲካ እየቀየሩ ማስፈራራቱ እንደተለመደ እና ለቀብር ማስፈፀሚያ የሚሆን መሬት ከመስተዳደሩ በሚጠየቅበት ጊዜ
የሚሰጠው መልስ በሀሰት መወንጀል እንደሆነ ከገለፁ በኋላ፣ ጉዳዩ መፍትሄ ካላገኘ ሊከተል የሚችለውን ስጋታቸውን ተናግረዋል፡-
 ‹‹‘የፖለቲካ ጉዳይ ነው፤ ህዝብን በሃይማኖት ሽፋን ታንቀሳቅሳላችሁ’ እየተባልን እየተሸማቀቅን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህን
እንዴት ታዩታላችሁ? መቻቻልስ የሚመጣው ከምን አኳያ ነው? ዝም ብለን የምንቀመጥ ከሆነ ምናልባት ኃላፊነት ለመውሰድ
ስለሚከብደን ይህን ወርዳችሁ እንድትፈትሹ ለማለት ነው፡፡››

(በነገራችን ላይ የሲኖዶሱ ጉባኤ በተጠናቀቀ ማግስት ከማህበረ ቅዱሳን የአመራር አባላት መካከል ሶስት ሰዎች በፌደራል ጉዳዮች ቢሮ
ተጠርተው ዶ/ር ሽፈራውን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ከመስሪያ ቤቱ ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡
ሚኒስትሩ ከአመራሩ ጋር ለመወያየት የተገደደው ካልተጠበቀው የሲኖዶሱ አባላት ድፍረት ጀርባ ‹የማህበረ ቅዱሳን እጅ አለበት› የሚል
ጥርጣሬ በመያዙ ነው፡፡ በውይይቱም ላይ የተንፀባረቀው የባለስልጣናቱ መለሳለስ፣ ማህበሩን ‹አክራሪ› ብለው እንደማያምኑ እና ከዚህ
ቀደም የተሰራጩት ወንጃይ ሰነዶችን ሳይቀር ‹አናውቃቸውም› እስከማለት የደረሰ እንደነበር አረጋግጫለሁ፡፡ ይሁንና ይህ አይነቱ ‹እሳት
ማጥፊያ› ስልት፣ ከስርዓቱ ጋር የቆየ መሆኑ ይታወቃል፤ የማህበሩ አመራርም ይህ ይጠፋዋል ብዬ ባላስብም፣ ኢህአዴግ መስከረም
22/1998 ዓም ቅንጅትን እንዴት አቂሎ ለታሪካዊ ስህተት መዳረጉን አለመርሳቱ ይጠቅመዋል)

 የሆነ ሆኖ በዕለቱ ከፌደራል ጉዳዮች ተወከለው ከመጡት ሶስት ሰዎች መካከል አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን አብዛኛውን ጥያቄ በተመለከተ
የሰጠው ምላሽ፣ የወከለው መንግስት ዛሬም በተሳሳተ የታሪክ ንባብ እያሸማቀቀ፣ እያስፈራራ፣ ህግን እየጠመዘዘ፣ እስር ቤት እየከተተ…
የፖለቲካ ጥቅሙን ማስከበር ላይ ያተኮረ መሆኑን ያሳያል፤ ኃላፊው ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፈው እንዲህ በማለት ነው፡-
‹‹መጀመሪያ ግንዛቤ ላይ እንስራ በሚል እርምጃ አልወሰድንም፡፡ ኮሽ ባለቁጥር ወደቃሊቲ መፍትሄ አይሆንም፡፡››

 …‹ቃሊቲ›ን ምን አመጣው? መቼም ለጣልቃ ገብነቱ ከዚህ የበለጠ ማሳያ መፈለግ ‹አውቆ የተኛን…› እንደመሆን ነው፡፡ ‹መንግስትና
ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው› ብሎ መከራከሩም ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ ይመስለኛል፡፡ እናም የተሻለው መንገድ ከላይ በጠቀስኩት ሰነድ
‹‹በየማዕከላዊ ኮሚቴው በሚካሄደው የስምሪት ተግባር በፀረ-አክራሪነት ትግል ላይ ያለው የእያንዳንዱ ግለሰብ ቁመና መፈተሽ አለበት›› ተብሎ የተገለፀውን ማሳሰቢያ በፍጥነት በመተግበር፣ በቅድሚያ ራስን ከአክራሪነትና አሸባሪነት ማራቅ ነው፡፡ ማረጋገጫ የማይቀርብበትን
አፈ-ታሪክንም እየለቃቀሙ በአንድ ሃይማኖት ላይ መለጠፉ አስተማሪ አይመስለኝም፡፡

 ከዚህ ባለፈ ‹የሃይማኖት ኮማንድ ፖስት አቋቁመን ለችግሩ እልባት እንሰጣለን› የምትሉት ጉዳይ ቀጥታ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ
እጁን ማስገባቱን በአደባባይ ከማመን ያለፈ የፖለቲካ ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡ ጳጳሳቶቹም ሆኑ ሼኼዎች ኃላፊነትና ግዴታቸው
ሰማያዊውን መንግስት መስበክ እንጂ፣ ከሰላይ አለቆችና ከፖሊስ አዛዦች ጋር ቢሮ ዘግተው የመንፈስ ልጆቻቸውን ‹ትምክተኛ›፣
‹አሸባሪ›፣ ‹አክራሪ›… እያሉ እንዲፈርጁ መፈታተኑ ያልታሰበ ህዝባዊ ቁጣ መቀስቀሱ አይቀርም፡፡






ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
November 10, 2013

No comments:

Post a Comment