Wednesday, August 21, 2013

የአቶ መለስ ዜናዊ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ

21 AUGUST 2013 ተጻፈ በ  
ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ነሐሴ 14 ቀን 2005 ዓ.ም በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ተከናወነ፡፡
“የመለስ ዜናዊ የሕዝብ መናፈሻና ቤተ መጻሕፍት” የመሠረተ ድንጋይ በተቀመጠበት ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የአቶ መለስ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን፣ የአፍሪካ አገሮች መሪዎችና ተወካዮች፣ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ወይዘሮ አዜብ፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ተወካይ፣ የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር፣ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ፣ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ተወካይ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ተወካይ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተወካይ ተሳትፈዋል፡፡
የዛሬ ዓመት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት አቶ መለስ ዜናዊ፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች በስማቸው የመታሰቢያ ፓርኮችን የመሰየምና የችግኝ ተከላ ሥራ ሥርዓቶች ሲካሄዱ ሰንብተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት እሳቸውን የሚዘክሩ ፕሮግራሞች ተካሂደዋል፡፡ የማክሰኞው በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል መታሰቢያ ፕሮግራም በስማቸው ፓርክና ቤተ መጻሕፍት ለመገንባት የሚያስችል ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
በዚህ አንደኛ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ የአቶ መለስ ሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸው የታወሱ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ “በታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የተቀየሱ ፖሊሲዎች በተቀመጠላቸው አቅጣጫ እየተተገበሩ ናቸው፤” ብለዋል፡፡ አቶ መለስ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ አንድ ዓመት በኋላም ይመሩት የነበረው መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ ሲያካሂድ በስትራቴጂያዊ ለውጦች ላይ በማተኮር እየተጓዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 
ባለቤታቸው ወይዘሮ አዜብ፣ “የአዲሲቱ ኢትዮጵያ አናፂና መሪ ነበሩ፤” ያሉዋቸው አቶ መለስ አንደኛ ዓመት እንደዛሬ ዓመቱ በለቅሶ የሚዘከር ሳይሆን፣ ራዕያቸውን ለማስፈጸም በእልህ የሚመራበት ነው ብለዋል፡፡
የአቶ መለስ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ማክሰኞ ማለዳ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በተገኙበት የፀሎት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
 ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment