Saturday, October 4, 2014

የኢድ አል አድሀ አረፋ በዓልን በማስመልከት ከድምፃችን ይሰማ የተላለፉ 4 ነጥቦች

ዒዳችንን ‹‹የአንድነት ዒድ›› ስንል ሰይመነዋል!
አርብ መስከረም 23/2007
ዒዳችንን ‹‹የአንድነት ዒድ›› ስንል ሰይመነዋል! ላለፉት ሶስት ዓመታት አላህን በብቸኝነት በማምለክ ገመድ ተሳስረን፣ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ለአንድነታችን ትኩረት ሰጥተን የተቃጣብንን ሃይማኖታዊ የመብት ጥሰት በመቃወም ቆይተናል፡፡ የዛሬዋ የዒድ ዕለት ተፈጥሯዊ ባህሪዋ ኾኖ በልዩ መልኩ ከምትዘከርባቸው ክስተቶች አንዱ አላህን በብቸኝነት በማምለክ በአንድነት መተሳሰር፣ ይህንኑም በተግባር ማሳየት ነው፡፡ በተጨባጭ በዓለም እየሆነ ያለውም ይኸው ነውና እኛም ይህንኑ ወርቃማ አጋጣሚ ተጠቅመን አንድነታችንን በአንድያው ጌታችን ይበልጥ ለማጠንከር ተነስተናል፤ አንድነታችን የድላችን መሰረት ነውና!
muslim 1
በዘንድሮው ዒድ አል-አድሃ ለዲናችን መከበር ያለንን ፅናት የምናጎለብትበት፣ አንድ ሆነን በአንድነት የምንታይበት፣ አንድነታችን እንዲሳሳ ለሚፈልጉ ሁሉ እንደማይሳካላቸው የምናሳይበት ይሆናል፡፡ ሁላችንም በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት በክልሎች ደግሞ በተለመዱት የስግደት ቦታዎች በመገኘት ስግደታችንን አንፈፅማለን፡፡ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ባለማሰማት ተቃውሞ በድምፅ ብቻ ሳይሆን በልቦና ውስጥ በሚኖር ፍፁም አንድነት እንደሚፀባረቅም ጭምር የምናሳይበት ዒድ ይሆናል፡፡ ህገ ወጥ መንገድ መከተልን ምርጫው ላደረገው መንግስትም ለሚከተለው ህገ ወጥ መንገድ የማንመች፤ በሰላማውያን ላይ ግፍ መፈፀምን ለሚሻው አካል በጅ የማንል መሆኑን፣ በተመሳሳይ ህዝብን የሚንቁ አካላት በምንከተለው የሰከነ መንገድ አላማቸው እንዲከሽፍና ነገም ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሰላማዊነታችንን ጠብቀብ ሚዛናችንን የማንስት መሆኑን በተግባር የምናሳይበትም ነው፡፡
በመጨረሻም
1. ባለፉት ረጅም አመታት እናደርገው እንደነበረው ሁሉ በበዓላችን ሁላችንም በአንድ ላይ በአዲስ አበባ በስታዲየም፣ በክልሎች ደግሞ በተለመዱት የስግደት ቦታዎች በመሰባሰብ በጋራ ሃይማኖታዊ ሥነ- ስርዓታችንን በአላህ ፈቃድ እንፈፅማለን፡፡ በነገው የዒድ አል-አድሃ በዓል ባለፈው የዒድ አል-ፈጥር በዓል ላይ በከፊል እንደተስተዋለው በየቦታው ተበታትኖ ከመስገድ ተቆጥበን ሁላችንም ለዒድ ሰላት ወደ ስታዲየም በአንድ ላይ ሆነን እንድንጎርፍ፣ መንገዶች ሁሉ ወደ ስታዲየም እንዲያመሩ ጥሪው ተላልፏል፡፡
2. በዒድ ቀን ከሰላት በፊትም ሆነ ከሰላት በኋላ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አይኖርም፡፡ በመሆኑም ምንም ዓይነት ተቃውሞ ከሰላት በፊትም ሆነ በኋላ ባለማሰማት ተቃውሞ በድምፅ ብቻ ሳይሆን በልቦና ውስጥ በሚኖር ፍፁም አንድነት እና የአምልኮ መንፈሳዊነት እንደሚፀባረቅም ጭምር እናሳያለን፡፡
3. ይሁንና በማይወክሉን ሹመኛ የመጅሊስ አካላት እና ግፍና በደል እየፈፀሙብን በሚገኙት የመንግስት አካላት ንግግር ከተደረገ ፈፅሞ የሀሰት ፐሮፓጋንዳ የምንሰማበት ጆሮ እንደሌለን ለማሳየት ጆሯችንን በእጃችን በመያዝ ለመስማት ፈቃደኞች እንዳልሆንን ተምሳሌታዊ በሆነ ስርዓት እንገልፃለን እንይዛለን፡፡
4. ከዒድ ሰላት መልስ የ ‹‹ኡድሂያ›› እርድ ላይ በትግሉ ተጎጂ የሆኑ ቤተሰቦችን፣ ደካሞችን እና የተቸገሩ ወገኖቻችንን በጠንካራ ወንድማዊነት እንድናስታውስም አደራ እንላለን፡፡
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

No comments:

Post a Comment