Saturday, August 24, 2013

ሰማያዊ ፓርቲ በመብራት ሀይል ሊያካሂድ የነበረውን ስብሰባ በጽ/ቤቱ ሊያደርግ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
“አዳራሽ መፍቀድ ያለበት ባለቤቱ እንጂ መስተዳድሩ አይደለም” 
ሰማያዊ ፓርቲ ነገ መብራት ሀይል አዳራሽ ሊያካሂድ የነበረውን ህዝባዊ ስብሰባ በፅህፈት ቤቱ ለማድረግ ወሠነ፡፡ ፓርቲው በአዳራሹ ህዝባዊ ስብሰባ እንዳላካሂድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስብሰባና ሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍል እንቅፋት ሆኖብኛል ብሏል፡፡ 
የመስተዳድሩ የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ሀላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ በበኩላቸው፤ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመፍቀድ መብት የባለ አዳራሹ እንጂ የመስተዳድሩ አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 
ፓርቲው “የግጭት አፈታት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የመነሻ ሀሳብ እንዲያቀርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ፋካልቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑትን ዶ/ር በቃሉ አጥናፉን መጋበዙን ገልፆ፣ አዳራሽ ለመከራየት ሲሄዱ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ለስብሰባ ያስፈቀዳችሁበትን ደብዳቤ ካላመጣችሁ አናከራይም መባላቸውን የፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ተናግረዋል፡፡ ከምኒልክ ት/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽም ተመሳሳይ ምላሽ ማግኘታቸውን ኢ/ሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 
“አዳራሽ ተከለከልን ብለን ፕሮግራማችንን አናስተጓጉልም” ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ህዝባዊ ስብሰባውን በፓርቲው ጽ/ቤት ለማካሄድ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡ 
ከዚህ ቀደም ለሌሎች ፓርቲዎች የመስተዳድሩ ማሳወቂያ ክፍል ደብዳቤ ፅፎላቸው ስብሰባቸውን ማከናቸናቸውን የገለፁት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፤ ለእኛ ጊዜ መስተዳድሩ ደብዳቤ አለመፃፉ ሆን ተብሎ የፓርቲውን እንቅስቃሴ ለመግታት የተደረገ ነው ሲሉ አማረዋል። 
የመስተዳድሩ የስብስብና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ሀላፊ ግን በሰዎች አዳራሽ አያገባንም፤ ለአዳራሽ የከፈላችሁበትን ደረሰኝ አምጡ ማለታችን ትክክለኛ የአሰራር አካሄድ ነው ብለዋል፡፡ 
ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የመብራት ሀይል አዳራሽ የስራ ሀላፊ ግን በእስከዛሬው አሰራራቸው ከመስተዳድሩ ህጋዊ ስብሰባ ማካሄጃ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ አዳራሹን እንደሚያከራዩ ገልፀው፤ ሰማያዊ ፓርቲ ይህን ደብዳቤ ሊያቀርብ ባለመቻሉ አዳራሹን ለማከራየት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ 
በተያያዘ ዜና፤ ሰማያዊ ፓርቲ ነሀሴ 26 የሚያካሂደውን ሁለተኛውን ሰላማዊ ሰልፍ ለመስተዳድሩ የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ማሳወቂያውን ካስገባ በኋላ በምን ዙሪያ፣ የትና እነማን ሰልፉን እንደሚያካሂዱት በደብዳቤ እንዲገልፅ ተጠይቆ በደብዳቤ ምላሽ መስጠቱን ገልጿል፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ

No comments:

Post a Comment