እስር ቤት የምትገኘው ጋዜጠኛ ሒሩት ክፍሌ
በእነ ኤልያስ ክፍሌ መዝገብ በሽብርተኝነት ክስ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት ከሚገኙት አራቱ ኢትዮጵያውያን መሀከል ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌና አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሄር በ2004 ዓ.ም ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን ምላሽ ሳያገኙ ለረዥም ጊዜ መቆየታቸው ሲያነጋግር ሰንብቷል፡፡ በተለይ ሲውዲናውያኑ ጋዜጠኞች ከኢትዮጵያውያኑ ጋር በተመሳሳይ ወቅት ይቅርታ ጠይቀው አፋጣኝ ምላሽ ማግኘታቸውና በአንጻሩ የእነውብሸት ይቅርታ ከአመት በላይ መዘግየቱ ተገቢ አለመሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ከአንድ አመት በላይ ቆይታ በኋላ ሐምሌ 25 2005 ዓ.ም የይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት ማህተም አርፎበት ለወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ በተላከ ደብዳቤ የይቅርታ ጥያቄያቸው ለፕሬዝዳንቱ ቀርቦ ውድቅ መደረጉ ተገልጾላቸዋል፡፡ ወ/ሮ ሂሩት ከእነ ውብሸት ጋር ባንድ መዝገብ ተከሰው 19 አመት የተፈረደባቸው ሲሆን የይቅርታ ጥያቄውንም ያቀረቡት በተመሳሳይ ወቅት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ህትመት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ለጋዜጠኛ ውብሸት ታዬና ለአቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር የደረሳቸው ደብዳቤ አለመኖሩን አረጋግጠናል፡፡
የወ/ሮ ሂሩት ይቅርታ በፕሬዝዳንቱ ውድቅ መደረጉን አስመልክቶ ልጃቸው ፍጹም መሰለ እናቱ ከተፈረደባቸው በኋላ ይግባኝ ከማለት ይልቅ ይቅርታ መጠየቅ የወሰኑበት ምክኒያት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ቀርበው “እንኳን ሀገር ውስጥ ያሉት ውጪ ያሉትም ቢሆኑ ዛሬ ይቅርታ ከጠየቁ ከነገ ጀምሮ ነጻ ናቸው” የሚል ቃል መግባታቸው እንደሆነ ገልጾ ይግባኝ የምንልበት አማራጭም አልፎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከገቡት ቃል በተቃራኒ ይቅርታው ውድቅ ተደርጓል መባሉ እንዳሳዘነው ተናግሯል፡፡ ፍጹም አክሎም “ለሲውዲናውያን የተሰጠው ዕድል ለኢትዮጵያውያን ጨርሶ ይከለከላል የሚል ዕምነት ስለሌለን የይቅርታ ጥያቄውን በድጋሚ በሽማግሌዎች በኩል እናቀርባለን” ብሏል፡፡
የአቶ መለስ ዜናዊን ሙታመት አስመልክቶ በርካታ እስረኞችን ለመፍታት መንግስት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ያረጋገጡት ምንጮቻችን ጋዜጠኛ ውብሸትና አቶ ዘሪሁን ደብዳቤ ያልደረሳቸው ከሚፈተቱት እስረኞች ዝርዝር ውስጥ ገብተው ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=6471
No comments:
Post a Comment