Thursday, August 15, 2013

ነግ በኔ አለማለት በወረፋ ለመጠቃት መዘጋጀት ነው!

የወያኔ ጉጅሌ የህዝባችንን መሰረታዊ መብቶች ነጥቆና ረግጦ ለመግዛት ከወሰነ የቆየ ቢሆንም ዛሬ ህዝቡ ብሶቱ እየገነፈለ አደባባይ መውጣቱ አርበትብቶታል። ወያኔ የህዝብን ጥያቄና ኮሽታ በሰማ ቁጥር የህዝብን ደም በግፍ የሚያፈሰውም ከዚህ መርበትበትና ብረገጋው ጋር በተያያዘ ነው።
ከአላንዳች ህዘባዊ መሰረት በጠመንጃ እና በፖሊስ ሃይል ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ቁም ስቅላችንን የሚያሳየን ወያኔ ከህዝብ የበለጠ ሃይል ኖሮት አይደለም። የወያኔ ጉልበትና ግፍ የፀናብን ተከፋፍለን በየተራ ለመቀጥቀጥ ስለፈቀድንለት ብቻ ነው። ወያኔን ያጎለበተው በአንዱ የህብረተሰብ ክፍል ላይ መዐት ሲወርድ ሌሎቻችን ወረፋችን እስኪደርስ ቆመን በመመልከታችን ነው ። ባለፈው ሳምንት የእስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን የ ክቡር በዓላቸውን በሚያከብሩበት ቅዱስ ቀን በደም ያጠመቃቸው ክርስቲያኑና ሌላው ተመልካች ይሆናል ብሎ ስላመነ ነው። የኦሮሞው ጥቃት ለአማራው ምንም እንዳልሆነ፣ የአማራው ጥቃት ለኦሮሞው፣ ለደቡቡና ለትግሬው ምኑም እንዳልሆነ፣ የደቡቡ ጥቃት ሌሎችን የማያገባና የማይመለከት ነዉ ብለን ስለምናምን ለወያኔ ጥቃት ተመችተነዋል። በአጠቃላይ “ነግ በኔ” ማለት ትተናል። በወረፋ ለማጥቃት ወያኔ አመቻችቶናል። እኛም ተመቻችተናል። የኢድ አልፈጥር እለት እናቶችን፣ ሽማግሌዎችንና ህጻነትን ሳይመርጥ እንደእባብ በዱላ ሲቀጠቅጥ የዋለው የወያኔ ልዩ ሃይል የተማመነው “ነገ በኔ” የሚል ህዝብ ይኖራል ብሎ አለማሰቡና፣ የመከፋፈያ ሴራዪ ሰርቶልኛል ብሎ በማመኑ ነው። ነገሩ ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ነው። ሁላችንንም ባይንቀን ኖሮ ጥቂቶቻችንን አይደፍረንም ነበር።
ዛሬ የወያኔ ጥቃት ሰለባ ያልሆነ፣ በወረፋው ያልተመታ፣ ያልተገደለ፣ ያልታሰረ፣ ያልተሰደደ፣ ከመኖሪያው ያልተፈናቀለ፣ ከስራው ያልተባረረ የህብረተሰብ ክፍል የለም። ሰራተኛ፣ ምሁራን፣ ገበሬዎች፣ የብሄር ብሄረሰብ ስብስብ፣ ተማሪ፣ መመህር ወዘተ የጥቃት ወረፋ ያልደረሰው የለም።
ጥያቄው ለምን በወረፋ እንደበደባለን? እስከመቼስ ነው ወያኔ የአንዳንዶቻችንን ጥየቄ የሌሎቻችን ማስፈራሪያ እንዲያደርገውና የጥቃት እርምጃውን በየተራ እንዲያፈራረቅብን የምንፈቅድለት? የሚለው ነው ።
ግንቦት 7 ለፍትህ፣ ለነጻነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ዛሬ ወያኔ በሙስሊሙ ወገኖቻችን ላይ የከፈተው የጥቃት ዘመቻ በጋራ መመከት ካልተቻለ ነገ በክርስቲያኑ ወይም በሌላው እምነት ተከታይ ላይ ላለመደገሙ ማረጋገጫ የለም ብሎ ያምናል::
የኢትዮጵያ ህዝብ ከቀን ወደቀን ለነጻነቱና ለማንነቱ ሲል የሚያደርገው ትግልና እንቅስቃሴ እንቅልፍ የነሳቸው እና የእግር ዉስጥ እሳት የሆነባቸው ህወሃቶች፤ የሀገራችንን አንድነት ህልውና እና ማንነት ለማጥፋት፣ ዜጎች ስለመብታቸው እንዳይጠይቁ እየነጣጠሉ እና እየከፋፈሉ በደም የተጨማለቀ እጃቸውን እንደገና በደም እያለቀለቁ ስለሃይማኖታቸው ነጻነት፣ ስለፍትህ እጦት፣ ስለዲሞክራሲ መስፈን በጮኹ አንደበቶች፤ አንደበታቸውን በጥይት ሲዘጉ ማየት በወያኔ ጎራ በእነ ኢቲቪ መንደር የእነ አስረሽ ምችው ድለቃ የተለመደ ነው። ስለዚህ የማንኛውም ዜጋ የእኩልነት፣ የፍትህ፣ የነጻነት ጥያቄ ምላሹ ሞትና መታሰር ከሆነ እስከ መቼ ተራ እንጠብቃለን?
ተቻችለንና ተከባብረን የኖርን ኢትዮጵያውያን ለወያኔ ከፋፍለህ ግዛ እና አጥቃ ፖሊሲ መመቸት የለብንም። በደስታና በሀዘን ሳንለያይ የዘለቀውን አንድነታችን አሁን በዚህ አስከፊና ጨካኝ ወያኔያዊ ድርጊት አዝነን ከንፈራችንን ለሞቱት እና ለታሰሩት በመምጠጥ አይደለም ቁጭታችንና ሀዘናችን መግለጽ ያለብን። ለተጠቁ ወገኖቻችን መከታ ጋሻ ሆነናቸው ቁስላቸው ቁስላችን፣ ደማቸው ደማችን፣ ሀዘናቸው ሀዘናችን፣ ሆኖ ነገ በኔ በሚል ዛሬ ሁሉንም የትግል ስልቶች ተጠቅመን አለንላችሁ በሚል አንድ ላይ ሆነን ስንታገል ብቻ ነው።ቋንቋና ሃይማኖት ቢለያየንም በወያኔ ግፍ ግን ሁላችንም አንድ መሆናችንን ለአፍታ እንኳን መዘንጋት በወረፋ ለመቀጥቀጥ መዘጋጀት ነውና በወያኔ ላይ በአንድነት እንነሳ!!
ግንቦት 7 ንቅናቄ የሀገራችን ህልውናን ለማዳን፣ የሁሉም ዜጋ የእምነት ነጻነት፣ እኩልነት፣ የሰው ልጆች መሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ዛሬም በቆራጥ ልጆቹ መሰዋእትነት የወያኔን ዘረኛ አክራሪነት ለመታገል ቃል ኪዳኑን ያድሳል። መላው የሀገራችን ህዝብ ሆይ፡ የነጻነት ጥያቄ ድምፃችሁ፣ ድምጻችን ነው። የጥቃት ወላፈኑ አቃጥሎ ሳይጨርሰን፣ ዳር ሆነን ላንመለከት ወያኔን በማናቸውም መንገድ ታግለን ልንጥለው፣ ልናስወግደው ትግሉን ጀምረናል፡፡ ያለውን ሰቆቃ በማስቆም በወያኔ ከርሰ መቃብር ላይ ኢትዮጵያችን የሁሉም እምነት ተከታዮች ተከባብረውና ተፋቅረው በነጻነት የሚኖሩበት አገር ትሆን ዘንድ እንታገል:: ኑ ተቀላቀሉን! ዳር ሆኖ መመልከቱ ይብቃ! በቃ!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

No comments:

Post a Comment