Saturday, August 31, 2013

ከስልጣን የተነሳው የደህንነት ሹም፣ እስር ቤት ተወረወረ!!

በዳዊት ከበደ ወየሳ
(ኢ.ኤም.ኤፍ) የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በህይወት
በነበረበት ወቅት፤ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል ምክትል የደህንነት ሹም ሆኖ
ይሰራ ነበር። ወልደስላሴ የህወሃት ታጋይ የነበረ ሲሆን፤ በትግላቸው
ወቅት... ወንድ እና ሴት ታጋዮችን “ፍቅር ስትሰሩ ተገኝታችኋል” በማለት
ብዙዎችን በመረሸን ይታወቃል። ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ
በኋላ፤ የመለስ ዜናዊ ክርስትና እናት ልጅ የሆነው፤ ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ
የቤተ መንግስቱ ዋና ኃላፊ፣ ወልደስላሴ ደግሞ የቀድሞው ደህንነት ሃላፊ
ክንፈ ገብረመድህን ረዳት ሆኖ እንዲሰራ ተደርጎ ነበር።
እ.ኢ.አ የ1994ቱ ክንፈ ገብረመድህን ድንገተኛ ሞት ያስደነገጠው
የህወሃት ቡድን፤ የደህንነት ምክትሉን ወልደስላሴን ዋና የደህንነት ሃላፊ
አድርጎ ቦታው ላይ አላስቀመጠውም። ለዚህ ዋናው ምክንያት ወልደስላሴ
ችኩል፣ ያልተማረና ብቃት የሌለው ሰው መሆኑ ነበር። በርግጥ ሌላ
የተማረ ኢትዮጵያዊ ጠፍቶ ሳይሆን፤ ይህንን ቦታ መያዝ የሚገባው ከሌላ
ድርጅት ወይም ብሄር የተገኘ ሰው ሳይሆን፤ የህወሃት ወይም የትግራይ
ተወላጅ እንዲሆን ስለተፈለገ፤ ጌታቸው አሰፋ ለትምህርት ከተላከበት
አሜሪካ፣ ቴክሳስ ግዛት በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ታዘዘ።
ያልጠበቀው ሹመትም ተሰጠው።
ጌታቸው አሰፋ የደህንነት ሃላፊ ይሁን እንጂ፤ የቤተ መንግስቱን
ወይም የመለስ ዜናዊን ጥበቃ በተመለከተ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁለቱ
ሹሞች ወልደስላሴ እና ኢሳያስ ሆኑ። ለምሳሌ መለስ ዜናዊ ወደ ውጭ አገር
በሚሄድበት ጊዜ መንገዱ እንዲዘጋና ጥበቃ እንዲደረግ፤ የቤተ መንግስቱ
ጥበቃ ሃላፊ ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ ቀጥታ ግንኙነት የሚያደርገው
ከወልደስላሴ ጋር እንጂ፤ ከዋናው ሃላፊ ጌታቸው አሰፋ ጋር አልነበረም።
በአጭር አነጋገር “መለስ መጣ” ሲባል የቦሌን መንገድ አዘግተው፤ ህዝቡን
እያስደበደቡ ከመንገድ የሚያስባርሩ አንጋች እና አጎንባሽ ሆኑ። የሁለቱ
ሹሞች የርስ በርስ መቀራረብ ብቻ ሳይሆን፤ ለመለስ ዜናዊም ቅርበት
አላቸው ስለሚባል፤ በደህንነት ሃላፊዎች ጭምር የሚፈሩ ሰዎች ነበሩ።
በዚህም ምክንያት ከታች ወደላይ ለጌታቸው አሰፋም ትዕዛዝ የሚሰጡ
ሆነው ቆይተዋል።
ያለፈው አመት የመለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሞት ግን ይህንን ሁሉ
ምስቅልቅል እያጠራው መጣ። ጌታቸው እና ምክትሉ ወልደስላሴ
እንደተፋጠጡ የህወሃትን ጉባዔ ይጠባበቁ ጀመር። በዚህ መሃል
የወልደስላሴ ስልጣን እየኮሰመነ መጣ። ኢሳያስም ሆነ ወልደስላሴ
የሚያጅቡት መለስ ስለሌለ፤ በአዜብ መስፍን ዙሪያ ተሰበሰቡ። እናም አዜብ
መስፍን ቤተ መንግስቱን ለቅቃ እስከምትወጣ ድረስ፤ አልቃሽ እና አስለቃሽ
ሆነው ሰነበቱ። ጌታቸው አሰፋ ግን ለቅሶውን ትቶ፤ የነበረከት ስምኦንን
ቡድን ጨምሮ፤ አዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና
ሌሎችንም እያስተባበረ የራሱን ኃይል ማደራጀት ጀመረ።
የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ለቅሶ ሲያበቃ፤ ህወሃት/ኢህአዴግ
በሞተው እና በደከመው ምትክ አዳዲስ ሰዎችን ለመተካት እላይ እታች
ማለት ጀመረ። በዚህ መሃል ወልደስላሴ ወልደሚካኤል አጋጣሚውን
ተጠቅሞ በህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ለመመረጥ የራሱን ጥረት
ማድረጉን ቀጠለ። የደህንነት ሃላፊው ጌታቸው አሰፋም — የወልደስላሴ
የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ጠላቱ መሆኑን በዚህ ስብሰባ ላይ ግልጽ ሆኖ
ወጣ።
“ህወሃት አድርጎት በነበረው ስብሰባ ላይ ወልደስላሴ እንዲመረጥ
እጩ ሆኖ ሲቀርብ፤ የመጀመሪያ ተቃዋሚ ጌታቸው አሰፋ ነበር። ይህ
የጌታቸው አሰፋ ተቃውሞ ተሳክቶ፤ ወልደስላሴ ምርጫ ውስጥም
እንዳይገባ ተደርጎ ተሰረዘ፤ ሳይመረጥም ቀረ። የወልደስላሴ ጓደኛ እና
የመለስ ዜናው የክርስትና እናት ልጅ የሆነው ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ ግን
በጠባብ ሁኔታ እንደገና ተመርጦ የማዕከላዊ ኮሚቴው አባል ሆነ።
የህወሃት ስብሰባ ላይ ይደረግ የነበረው ድራማ አላበቃም። በመቀጠል
ደግሞ ጌታቸው አሰፋ ተጠቆመ። ይሄን ጊዜ ወልደስላሴ ለመናገር እጁን
አወጣና እድል ተሰጠው። እንዲህም በማለት ጌታቸው አሰፋን ኮነነው።
“ጌታቸው አሰፋ በህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እንደገና መቀጠል
የለበትም። ጌታቸው ህወሃትን እያገለገለ አይደለም። ስራውንም በአግባቡ
አይወጣም። ይሄ ሰው የአላሙዲን ተላላኪ እና አሽከር ሆኗል።” በማለት
ወቀሳውን ቀጠለ። ሆኖም ይህ የወልደስላሴ ወቀሳ ተቀባይነት ሳያገኝ
ቀርቶ ጌታቸው አሰፋ ብቻ ሳይሆን፤ ወንድሙ ዳንኤል አሰፋም ጭምር
በህወሃት ማእከላዊ አባልነቱ እንዲቀጥል ተደረገ። ከዚህ የህወሃት ስብሰባ
በኋላ እነዚህ ሁለት የህወሃት ደህንነት ሃላፊዎች አብረው ሊሰሩ
የሚችሉበት ሁኔታ እየጠበበ መጣ።
ወልደስላሴ በትግራይ የሚገኙ የቀድሞ የህወሃት አባላትን
በማስተባበር፤ በጌታቸው አሰፋ ላይ ሰፊ የጥላቻ ዘመቻ ማድረጉን ቀጠለ።
ይህ ዘመቻው ግን የቆየው እስከ ሰኔ ወር አጋማሽ ነበር። ከሁለት ወራት
በፊት ወልደስላሴ ወልደሚካኤል ከሃላፊነቱ ተነስቶ፤ ከስራ ተሰናብቶ
የህወሃት አባላትን ደጅ ሲጠና ሰነበተ። አዜብ መስፍንን፣ ስብሃት ነጋን እና
ሌሎችንም በመቅረብ እጅ መንሳት ጀመረ። ሃምሌ አልፎ ነሃሴ ተተካ።
ከዚያም የአቶ መለስ ዜናዊ ሙት አመት ተከብሮ ሳያበቃ፤ አዜብ
መስፍንም ጥቁር ልብሷን ሳትቀይር ሌላ ሃዘን መጣ - ወልደስላሴ
ወልደሚካኤል ተይዞ ታሰረ።
አሁን ጌታቸው አሰፋ በፌዴራል መንግስት ደረጃ ያለውን ስልጣን
እያደራጀ የመጣ ይመስላል። ከስር ሆኖ የሚያዘው ወልደስላሴ እስር ቤት
ገብቷል። ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ ከቤተ መንግስት እየደወለ ትእዛዝ እና
መመሪያ አይሰጠውም። ጌታቸው አሰፋ አሁን ነጻ ሰው ነው። ይህ ነጻነቱ
የሚቆየው ግን ቀጣዩ የህወሃት/ኢህአዴግ ስብሰባ እስከሚደርስ ይሆናል።
እስከዚያው ድረስ ግን እነ ኢሳያስን በአይነ ቁራኛ መጠበቅ አለበት። አዜብ
መስፍን ከኢፈርት ስልጣንዋ ወርዳ፤ ስለመለስ ፋውንዴሽን ብቻ እያወራች
እንድትኖር እድል ሰጥቷታል። ቢሆንም ግን ህወሃት ውስጥ ሌሎች
የጌታቸው አሰፋ ጠላቶች አሉ። እስከሚቀጥለው የህወሃት ስብሰባ እና ሌላ
ውጥንቅጥ ድረስ፤ ድራማውን ከዳር ሆነን እናያለን።
ከስልጣን ተነስቶ ለሁለት ወራት ከቆየ በኋላ የታሰረው፤ ወ/ስላሌ
ከበረሃ ጀምሮ በርካታ የድርጅቱን ታጋዮች በመረሸን ይታወቃል። « ፆታዊ
ግንኙነት ስታደርጉ ተገኝታችኋል…» በሚሉና ሌሎች ተልካሻ ምክንያቶች
እንዲረሸኑ በበላይ አመራር ውሳኔ የተላለፈባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ
የፓርቲው አባላት (ታጋዮች) ለመግደል ይጣደፉ ከነበሩት መካከል
ኢሳያስና ወ/ስላሴ ዋናዎቹ ነበሩ ሲሉ ያስረዳሉ። አቶ መለስ ሁለቱን
አባላት ወሳኝ በሆነው የደህንነት ቢሮ ቁልፍ ስልጣን የሰጧቸው
«አድርጉ» የተባሉትን ያለማመንታት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ጠንቅቀው
ስለሚያውቁ ነበር። ወ/ስላሴ ስልጣን በጨበጠ ማግስት በአንድ ቀን አርባ
የቢሮው አባላትን (መኮንኖች ተብለው ነው የሚጠሩት) ከስራ አባሯል።
በየጊዜው በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላትን «ተሃድሶውን አልተቀበላችሁም፣
የቅንጅት ደጋፊዎች ናችሁ..» በሚሉና ሌሎች ምክንያቶች ከማባረር -
እስር ቤት እስከመወርወር የደረሰ እርምጃ ሲወስድ ቆይቷል። ከመለስ ጋር
በሃሳብ ያለተስማሙ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናትን በገዛ መኖሪያ ቤታቸው
በገመድ በማነቅና በስለት በማረድ የጭካኔ ተግባር ያስፈፀሙት ወ/ስላሴ
እና ኢሳያስ መሆናቸው በሰፊው ይወራል። በግፍ የተገደሉት የመገናኛ ሚ/
ሩ አቶ አየነውና የቤተመንግስት የደህንነት ሹም አቶ ዘርኡ መሆናቸውን
ጠቁመዋል።
አሁን ለጊዜው ከደህንነቱ ዋና ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ፊት
እንዲርቅ የተፈለገው ግን ወልደስላሴ ወልደሚካኤል በመሆኑ፤ “ሃብት
በማጋበስ ወንጀል” ተብሎ በሙስና ወህኒ ተወርውሯል። የ እስሩን ዜና
የኢህአዴጉ ፋና ሬዲዮ ሲያቀርበው፤ ሌሎች የመንግስት ሚዲያዎች ግን
በደረሰባቸው ድንጋጤ ምክንያል ይመስላል - ዝምታን መርጠዋል።
ምንጭ (የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ)

No comments:

Post a Comment