ሐምሌ 28 2005 ዓ.ም.
ወያኔ ወገኖቻችንን እየገደለ፤ አገራችንን እና ሕዝቧን በሽብር እያመሰ ነው። ከአርብ ሐምሌ 26 ቀን 2005 ዓም ጀምሮ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች የወያኔ ሠራዊት ባልታጠቁና ባልተዘጋጁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥይት እያዘነበ ይገኛል። እስካሁን የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ማወቅ ቀርቶ መገመት እንኳን አዳጋች ነው። ሞስሊም ወገኖቻችን፣ በሕጋዊ መንገድ ለውጥ እናመጣለን ብለው የሚያምኑ ሰላማዊ ታጋዮች፣ ሕፃናትና አዛውንት የጥቃቱ ሰለባ ናቸው።
የወያኔ ግንባር ቀደም የጥቃት ሰለባዎች ሰላማዊነታቸው ለማሳየት እጆቻቸውን አስረው ፍትህ ሲማፀኑ የነበሩ ዜጎች ናቸው። ሕግ የማያውቀው ወያኔን በሕጋዊ መንገድ ታግለን መሠረታዊ መብቶቻችንን እናስከብራለን ያሉ ወገኖቻችን በግፍ ተግደዋል፤ ተደብድበዋል፤ ተግዘዋል። የምዕራብ አርሲ ከተሞችና መንደሮች በአጋዚ ጦር ተወረዋል። አዲስ አበባም ውስጥ ዋይታ በርክቷል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በወያኔ ፋሽስታዊ እርምጃ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ቤተሰቦች ሁሉ የተሰማው መሪር ሀዘን ይገልፃል። እንደዚሁም ለአካል ጉዳት ለተዳረጉ፣ ለተዋከቡ፣ ለተረገጡ፣ ለጅምላ እስር ለተዳረጉ ወገኖቻችን ሁሉ በደረሰባቸው በደል መቆጨቱን ይገልፃል።
ወያኔ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ የእምነትም ሆነ ሌላ ማናቸውን ነፃነት ሊኖር እንደማይችል የትናትናና የዛሬው ድርጊት አንድ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ወያኔ በሥልጣን መንበር ላይ ውሎ ባደረ መጠን እንዲህ ዓይነቱ መርዶ መስማታችን የማይቀር ነው ብሎ ግንቦት 7 ያምናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ እንዲያበቃ ወያኔ ከሥልጣን መወደግ አለበት፤ ገዳዮች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የሰላማችን ዋስትና የወያኔ መወገድና በምትኩ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት መተካት ነው ብሎ ያምናል። ስለሆነም በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን እና መሠረታዊ መብቶቻችን ተከብረውልን መኖር እንድንችል ወያኔን ለማስወገድ ቆርጠን እንነሳ።
መጽናናት ለተገዱ ወገኖቻችን ቤተሰቦች!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
No comments:
Post a Comment