Thursday, August 22, 2013

ለእምነት ነፃነት የምናደርገውን ትግል ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለዜግነት ክብር እና ለሀገር ነፃነት ከምናደርገው ትግል ጋር እናቀናጅ!!!

ትንሽነቱ በፈጠረበት ስጋት ምክንያት ሁሉንም ነገር ካልተቆጣጠረ በጉልበት የያዘውን ሥልጣን የሚያጣ የሚመስለው እና በዚህም ሳቢያ ሁሉም ነገር ውስጥ እጁን የሚነክረው ወያኔ ራሱን በገዢነት ከሾመበት እለት ጀምሮ የሃይማኖት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እንደተጋ ነው። በእኛ በኢትዮጵያዊነት ዳተኝነት ታግዞም ትጋቱ ውጤት እያስገኘለት ነው።
ወያኔ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክህነትን ከፓትሪያርክ ጀምሮ እስከ ደብር አለቆች ድረስ ያለው መንፈሳዊ ሹመት ተቆጣጥሯል። አሁን የቀየረው የቤተክርስቲያኒቷን ሃይማኖታዊ ቀኖናን መቀየር ነው። ወያኔ በሥልጣን ላይ ከቆየ ይህንንም ከማድረግ የማይመለስ መሆኑን በእስልምና እምነት ላይ ተግባራዊ እያደረገ ካለው መገንዘብ ይቻላል።
ልክ እንደ ክርስትናው ሁሉ ወያኔ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን (መጅሊስ) በራሱ ካድሬዎች ሞልቶት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮታል። እስልምና ላይ ግን የሃይማኖት ተቋማትን ከመቆጣጠር አልፎ በቀኖና ጉዳይ በመግባት የራሱን “ምርጥ እስልምና” እያስተዋወቀ ነው። ዛሬ በሙስሊሞች ላይ የመጣው ነገ በክርስቲያኖችም ላይ የሚመጣውን አመላካች ነው።
እርግጥ ነው ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች የወያኔን ጥቃት በፀጋ አልተቀበሉትም። ሁሉም በየራሳቸው መንገድ የወያኔን ሁሉን-ጠቅላይ አገዛዝ እየተቃወሙትና እየታገሉት ነው። ዛሬ የወያኔ ጥቃት የደረሰበት ደረጃ ግን የሁለቱን ሃይማኖቶች አማኖችን ኅብረት የሚጠይቅ ሆኗል። ወያኔ ደግሞ በበኩሉ ይህ መከባበርና መተባበር እንዳይኖር ጥረት እያደረገ ነው።
የሁለቱም ትላልቅ ሃይማኖቶች ምዕመናን ለእምነታቸውና ለእምነት ተቋሞቻቸው ነፃነት በሚታገሉበት በአሁኑ ሰዓት “ጅራፍ እራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ” እንዲሉ ወያኔ ድምፃቸውን ቀምቶ በደሉን ለማጠናከር እየተጠቀመበት ነው። እፍረት ያልፈጠረባቸው የወያኔ ሹማምንት “መንግሥት በእምነታችን ጉዳይ ጣልቃ አይግባብን” እያሉ አቤት የሚሉትን ምዕመናንን “በፓለቲካ ጉዳይ ጣልቃ ገባችሁ፤ ይህ ደግሞ በኛ ሕግ ክልክል ነው” እያለ ይከሳቸዋል።
“ሃይማኖት በመንግሥት፤ መንግሥትም በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ አይገቡም” የሚለውን ሰፊ ተቀባይነት ያለው መርህ ወያኔ መሠሪ በሆነ ተንኮሉ “ሃይማኖት በፓለቲካ፤ ፓለቲካም በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም” ወደሚል እጅግ አደገኛ መርህ እየቀየረው ነው።
“በሃይማኖትና መንግሥት” እና “በሃይማኖትና ፓለቲካ” መካከል ያለው ግዙፍ ልዩነት ለአብዛኛው ምዕመን ግልጽ አይደለም በሚል ግብዝነት ነገሮችን በማጣመም ምዕመናንን በማደናገር ለፍረጃ ያመቻቻቸዋል።
አዎ ሃይማኖትና መንግሥት መለያየት አለባቸው። ኢትዮጵያዊ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች እየጠየቁ ያለውም ወያኔ ይህንን መርህ እንዲያከብር ነው። “ወያኔ ሆይ!!! በሃይማኖታችን ጉዳይ ጣልቃ አትግባብን!” እያሉት ነው።
ሃይማኖትና ፓለቲካ ግን በብዙ ክሮች የተቆላለፉ ነገሮች ናቸው። ለሃይማኖት ነፃነት መከራከር ራሱ ፓለቲካ ነው። ለሰብዓዊ መብቶች መከበር መከራከርም ትልቅ ፓለቲካ ነው። የሁለቱ ሃይማኖቶች አማኞች ይከባበሩ፤ ይተባበሩ ማለትም ፓለቲካ ነው። ይህ እንዳይፈጠር ነው ወያኔ ሃይማኖትና ፓለቲካ እሳትና ጭድ አድርጎ ሊስላቸው የሚዳዳው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ኢትዮጵያዊያን ምዕመናን በሃይማኖትና ፓለቲካ አንድነትና ልዩነት ላይ የጠራ አቋም መያዛቸው ትግላችን ያግዛል ብሎ ያምናል።
ሃይማኖትና መንግሥት መለያየታቸው ተገቢ ነው። ሃይማኖትና ፓለቲካ ግን አንድ ባይሆኑም በብዙ መንገዶች የሚደጋገፉ ናቸው። ሃይማኖቶች ለእምነት ነፃነት፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለዜግነት ክብር፣ ለሀገር ነፃነት እና መሰል ጉዳዮች በግንባር ቀደም መታገል ይኖርባቸዋል። በታሪካችን ውስጥ ታቦቶች ጦር ሜዳዎች ዘምተው አርበኞችን አበረታተዋል። ይህ ዛሬም ሊደረግ የሚገባው የተቀደሰ ተግባር ነው።
በዛሬ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሃይማኖትና የሃይማኖት ተቋማትን ከወያኔ መዳፍ ማውጣት ሀገርን ከወያኔ መዳፍ ከማዳን ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ጉዳይ ሆኗል። ስለሆነም ለሃይማኖት ነፃነት የምናደርገው ትግል ለሀገራችንም የምናደርገው ትግል አካል ነው።
ወያኔ በሃይማኖቶቻችን፣ በሀገራችን ብሎ በራሳችን ላይ የመጣ እኩይ ኃይል ነው።
ስለሆነም፣ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለሃይማኖት ነፃነት የምናደርገውን ትግል ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለዜግነት ክብር እና ለሀገር ነፃነት ከምናደርገው ትግል ጋር እንድናቀናጅ ወገናዊ ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!



    No comments:

    Post a Comment