ሼክ መሐመድ አል አሙዲ 80 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ በመያዝ ለግብርና ኢንቨስትመንት የመሠረቱት ሆራይዘን ፕላንቴሽን የተባለ ኩባንያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለለውዝ እርሻ የተረከበውን 20 ሺሕ ሔክታር መሬት ባለማልማቱ ሊነጠቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስወጣትን የምግብ ዘይት ግዢ በአገር ውስጥ አምርቶ ለማስቀረት ዕቅድ ይዞ ነበር የተባለው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ኩባንያ፣ እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2012 ለምግብ ዘይት የሚሆነውን ለውዝ ለማምረት 20 ሺሕ ሔክታር መሬት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሊዝ ተረክቧል፡፡
በኩባንያው ዕቅድ መሠረት 20 ሺሕ ሔክታር መሬቱ ለለውዝ እርሻ የሚውል ሲሆን፣ በአማራ ክልል ባህር ዳር ላይ ደግሞ በ600 ሚሊዮን ዶላር የዘይት ፋብሪካውን ለመገንባት ታስቧል፡፡
ይሁን እንጂ ኩባንያው መሬቱን ከወሰደበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ ባለማድረጉ፣ በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ጉዳዩን እንዲመለከተው አስገድዷል፡፡
‹‹ኩባንያው መሬቱን ከወሰደበት ጊዜ አንስቶ ወደ ልማት መግባት ባለመቻሉ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰው አድርገናል፤›› ሲሉ የዳይሬክቶሬቱ አስተባባሪ አቶ ብዙዓለም በቀለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ለተጻፈለት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ምክንያቶቹ በመዘርዘር ኩባንያው ምላሽ እንደሰጠ፣ ለዚህም ምላሽ ተጨማሪ ደብዳቤ ማስጠንቀቂያውን በማፅናት እንደተጻፈለት አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የተለወጠ ነገር ባለመኖሩ የመሬቱ ውል እንዲቋረጥና መሬቱ እንዲመለስ ሐሳብ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው መሬቱን ከወሰደ አንስቶ ልማት ካለመጀመሩም በላይ፣ አንድም ቀን ከግብርና ኢንቨስትመንት ዳይሬክቶሬቱ ጋር ኢንቨስትመንቱን በተመለከተ ግንኙነት እንዳልነበረው አቶ ብዙዓለም አስረድተዋል፡፡
ሆራይዘን ኩባንያ ለለውዝ ልማት የጠየቀው መሬት ምቹ ይሁን አይሁን ጥናት ሳያደርግ መረከቡን፣ በተረከበበትም ወቅት የተሰጠው መሬት በጣም ምቹ እንደሆነ መግለጹን የሚያስታውሱት አስተባባሪው፣ ለዓመት ከዘገየ በኋላ የሚሰጠው ምክንያት መሬቱ ምቹ እንዳልሆነለት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ይህ ኩባንያውን የሚያቀርበው ሰበብ ‹‹የበርካታ ኩባንያዎች ችግር ነው›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡
የሆራይዘን ኩባንያ ኃላፊዎች ሊወሰድ የታሰበው ዕርምጃ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ከግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ሼክ መሐመድ አል አሙዲ በ2005 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት በኮምቦልቻ ሊገነቡት ያቀዱትን ጦሳ የብረታ ብረት ኩባንያ እንዲገነባ ከመረጡት የጣሊያን ኩባንያ ጋር ሲፈራረሙ፣ የዘይት ፋብሪካውንም ግንባታ ለመጀመር በአሥር ቀናት ጊዜ ውስጥ ከአንድ የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር እንደሚፈራረሙ በወቅቱ ተገኝተው ለነበሩት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጭምር ገልጸው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የዘይት ፋብሪካ ግንባታ ስምምነት እስካሁን አልተፈረመም፡፡ ሼክ አል አሙዲ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በግብርና ኢንቨስትመንት በስፋት ለመሰማራት እየሠሩ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ግዙፍ የመንግሥት የእርሻ ልማቶችንም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከፕራይቬታይዜሽንና ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ መግዛታቸው ይታወሳል፡፡ ሼኩ በጨረታ ያሸነፉዋቸውን የእርሻ ልማት ድርጅቶች ለመግዛት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ወጪ ሲያወጡ፣ ከመንግሥት የገዟቸውን ድርጅቶች 35 በመቶ ክፍያ ለመፈጸም ከዓመት በላይ እንደፈጀባቸው ያስረዳሉ፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ መረጃ እንዲሰጡ የሆራይዘን ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment