የሙስና ነገር (ክፍል ሁለት)
በዳዊት ከበደ ወየሳ
እውነት የማይመስሉ ግን እውነት የሆኑ የሙስና ታሪኮች - በኢትዮጵያ።
አሁን በኢትዮጵያ አቆጣጠር ወደ 2006 ተሻግረናል። ከአመት ወደ አመት ስንሸጋገር ደግሞ ያለፈውን አመት
የሙስና ነገር በገደምዳሜ ዳሰስ አድርገን ብናልፍ ክፋት የለውም። በመሆኑም የስራ ባልደረባዬ ክንፉ አሰፋ “ክፍል አንድ”
ብሎ በጀመረው የሙስና ጉዳይ… “ክፍል ሁለት” ብዬ እኔ ቀጠልኩበት፤ አንብቡት።
የጉምሩክ ከፍተኛ ሃላፊዎች ሲታሰሩ፤ በየፊናው የነበሩ ጉምቱ ባለስልጣናት መደንገጣቸው አልቀረም። “እገሌስ
መቼ ነው የሚታሰረው ወይም የምትታሰረው?” የሚለው ሹክሹክታም ከቢሮ አልፎ በአደባባይ የህዝቡ መነጋገሪያ ሆኖ
ሰንብቷል። በዚያኑ ሰሞን ከኢትዮጵያ የመጣ አንድ ዘመዴ ጋር ቁጭ ብለውን ስናወራ፤ “ገብረዋህድ የሚባለውንስ እንኳንም
አሰሩት።” አለኝ።
“ምነው?” አልኩት።
“በጣም መጥፎ ሰው ነው” ብሎ ጀመረልኝ - ፊቱን አጨፍግጎ። “መጥፎ ሰው ነው። አንዳንዴ እንደተራ ሰው ሻይ
ቤት እና ቡና ቤት ገብቶ፤ የሆነ ነገር አዝዞ ይቀመጣል። ከዚያም አንዱ ተስተናጋጅ፤ ሂሳቡን ከፍሎ ሲወጣ፤ ድንገት ደረሰኝ
ይዞ ካልወጣ… ከመቀመጫው ተነስቶ፤ ‘ሌቦች አጭበርባሪዎች’ ብሎ ይሳደብና ፖሊስ ወዲያው ጠርቶ የንግድ ቤቱን
ያሳሽጋል።” (ደረሰኝ ለደንበኛ አለመስጠት ሙስና መሆኑን እዚህ ላይ ጠቅሰን እንለፍ)… እናም ይህ የጉምሩኩ ምክትል
ሰውዬ ያላስለቀሰው ነጋዴ የለም።
ደግሞም በነጋዴዎቹ ቢበቃው ጥሩ ነበር። የመስሪያ ቤቱን ሰራተኞች በሙስና እየወነጀለ ያላሳሰረው ሰራተኛ
እንዳልነበር፤ የቅርብ ሰዎች ያወራሉ። እዚህ ላይ አንድ አስቂኝ ነገር አለ። ይሄ ለሰማይና ለመሬት ከብዶ ህዝቡን ሲያስለቅስ
የነበረ ሰውዬ በመጨረሻ የሱም ቀን ደረሰና ሊታሰር ሆነ። እናም በቁጥጥር ስር በዋለበት ቀን፤ ሁለት የፌዴራል ፖሊስ
አባላት ወደ ቢሮው ገብተው በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ሲሉ ይደነፋል።
“ማን እንደሆንኩ ታውቃለህ?” ይላል።
“አዎ እናውቃለን!” አሉት። አንድ ሁለት ቃል ከተለዋወጡ በኋላ፤ ልክ እንደ ነጋ ገብረእግዚአብሄር - አንቱ
ወደተባሉ ከፍተኛ የህወሃት አባላት ስልክ መደወል ይጀምራል። ከባለስልጣናቱ የሚሰማው ነገር ያልጠበቀው ነበር። በመሃል
ፌዴራል ፖሊሶቹ ከቢሮው እንዲወጡ ያደርግና ከውስጥ በኩል የቢሮውን በር ይቆልፈዋል። ፖሊሶቹ ቢያንኳኩ -
ቢያንኳኩ የሚከፍት ሰው ጠፋ። የጉምሩክ መስሪያ ቤት ተጨነቀ። በቢሮ አካባቢ ያሉት “በቃ ይሄ ሰውዬ እንደ አጼ
ቴዎድሮስ የራሱን ህይወት ሊያጠፋ ነው” ብለው በመስጋት፤ ከአሁን አሁን የተኩስ ድምጽ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ሌሎች
የግቢው ጥበቃ ሰራተኞች ደግሞ፤ ‘ከፎቅ ላይ ራሱን ወርውሮ ይገድላል’ በሚል ስጋት አንገታቸውን ወደ ፎቁ አንጋጠው፤
ድንገት ከፎቅ ላይ ሲወድቅ ሮጠው እንደኳስ ሊቀልቡት ተዘጋጅተዋል። ይሄ ሁሉ ሲሆን፤ ሰውየው ቢሮውን ቆልፎ
ከህወሃት ባለስልጣናት እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ድረስ ስልክ እየደወለ ነበር።
የደወለላቸው ባለስልጣናት በሙሉ ለራሳቸው በመስጋት የተለያየ ምክንያት እየሰጡ ስልኩን ጆሮው ላይ ዘጉበት።
በዚህች ቀውጢ ወቅት በመከላከያ ውስጥ የኮሎኔል ማዕረግ የተሰጣት፤ እጩ ጄነራል ሚስቱም ልታድነው አልቻለችም።
ፌዴራሎቹ ጉዳዩን አስመልክተው ወደ አለቆቻቸው ደወሉ። “ሰውየው እራሱን እንዳያጠፋ ስለሰጋን ነው” አሉ።
ከአለቆቻቸው የተሰጣቸው መልስ አጭር ነበር። “እራሱን አያጠፋም። ተጨማሪ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ እዚያው ቆዩ”።
የሙስና ነገር (ክፍል ሁለት) በዳዊት ከበደ ወየሳ ገጽ1“ሰራተኛ ሲወጣ፤ እሱ ከቢሮ ካልወጣ ሰብራችሁ ትገባላችሁ” ተባሉ። ፖሊሶቹም ሰራተኛው ከስራ እስኪወጣ
መጠባበቅ ጀመሩ። ሰራተኛው ከወጣ በኋላ፤ ፌዴራሎቹ በር የሚሰብሩበትን መሳሪያ እያፈላለጉ ሳለ ገብረዋህድ
ከተደበቀበት ቢሮ ሹክክ ብሎ ወጣ።
“ምነው ብዙ የምታስጠብቀን?” ብለው ጠየቁት ፌዴራሎቹ።
“በሰራተኛው ፊት ታስሬ መሄድ ስላልፈለኩ ነው” አላቸው።
ገብረዋህድ በማግስቱ የፈራው ደረሰበት። ለፖሊስ ቃሉን ከሰጠ በኋላ፤ በሚቀጥለው ቀን የመንግስት ንብረት
እንዲያስረክብ ወደ ጉምሩክ ሲወሰድ፤ በሰራተኞቹ ፊት ሁለት እጁን ተጠንጎና በፌዴራል ፖሊሶች እየተጎነተለ መጣ። “ከዚህ
በላይ ውርደት?” ብለን ቃሉን አለመጨረሹ ይሻለናል።
ሌላም የሚገርም ነገር አለ። ይሄ ሰው ከመታሰሩ አንድ ወር በፊት በመላው አገሪቱ የሚገኙ የጉምሩክ
ባለስልጣናትን በኮንፈረንስ ስብሰባ አድርጎ ነበር። የፈረደበትን የሟቹን ጠቅላይ ሚንስትር ፎቶ በመለጠፍም “በሙስና
ለምትጨማለቁት እንደደርግ ጥይት አናጎርሳችሁም፤ እናስራችኋለን።” እያለ ስለመለስ ራዕይ ሲያወራ ነበር። በንግግሩም
መጨረሻ፤ (ያን ሰሞን የመለስ ሚስት የምኒልክን ቤተ መንግስት ለቅቃ ነበርና…) “በአሁኗ ደቂቃ የመለስ ዜናዊ ልጆች
መኖሪያ ቤት እንኳን የላቸውም። ሜዳ ላይ ነው የቀሩት።” ሲል የዋሆቹ ሲያለቅሱ፤ ነገሩን የሚያውቁ ግን ስቅስቅ ብለው
ይስቁ ነበር።
ገብረዋህድ ከታሰረ በኋላ በስሙ የአርሲን ቆዳ ስፋት የሚያህሉ የቤት ካርታዎች ሲገኙ፤ “ምናለበት አንዱን ቤት
ሜዳ ላይ ለወደቁት ለመለስ ዜናዊ ልጆች ቢሰጣቸው ኖሮ?” መባሉ አልቀረም።
ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲገቡ፤ ቦሌ መንገድ ላይ ያሉትን ህንጻዎች ከተመለከቱ፤ ህዝቡ ራሱ እንደጎበዝ አስጎብኚ
ይነግርዎታል። “ይሄ ህንጻ የጄነራል ጻድቃን ነው። ይሄኛው የጄነራል እገሌ ነው እያሉ፤ መድሃኔአለም ቤተ ክርስቲያን ፊት
ለፊት ከሚገኘው ኤድናሞል ህንጻ ጋ ሲደርሱ ደግሞ “ከጎኑ ያለው የሚያምር ህንጻ የጄነራል አባ ዱላ ነበር።” ይሏችኋል።
“አሁንስ የማነው?” ካሉ አስጎብኚዎ የሙስናን ነገር እያጣቀሰ ወሬውን ሊቀጥል ይችላል። እኛም እንንገርዎ - የነ አባ
ዱላን ነገር። አባ ዱላ ገመዳ አሁን የፓርላማው አፈ ጉባዔ ነው። ከዚያ በፊት የኦሮሚያ ፕሬዘዳንት፡ ከዚያም በፊት
የመከላከያ ሚንስትር፡ ከዚያ በፊት በሻዕቢያ የተማረከ የደርግ ወታደር ነበር… መቼም አንድ ወታደር ለሻዕቢያ እጅ ሰጥቶ
ከተማረከ ከዚያ በፊት ምን ነበር? ተብሎ አይጠየቅም። እናም አባዱላ እና በሙስና ስለተሰራው ትልቅ ቤተ መንግስት
የመሰለ ቤታቸው ከማውራታችን በፊት፤ ሰውየው ሌሎቹን ጄነራሎች ጭምር እንዴት በሙስና እንዳነካኩ ላጫውታችሁ።
በአንድ ወቅት ለጄነራሎቹ (ያው ከአባ ዱላ በቀር ብዙዎቹ ህወሃቶች ናቸው) አዲስ አበባ ውስጥ መኖሪያ እንዲሰሩ
መሬት ተሰጣቸው። የሲሚንቶ እና የሌላ ሌላው ነገር ዋጋ መጨመርን ተከትሎ የብዙዎቹ አቅም የሚችለው አልሆነም።
እናም የኦሮሚያ ፕሬዘዳንት የነበሩት አባ ዱላ ገመዳ ከሌሎቹ ጄነራሎች ጋር በመመሳጠር በኦሮሚያ የሚገኙ መሬቶች፤
እየተሸነሸኑ ለጄነራሎቹ በስጦታ መልክ እንዲሰጣቸው አደረጉ። ይህ የተደረገው ያለ ምክንያት አይደለም። በኋላ ላይ
ጄነራሎቹ በኦሮሚያ ባለስልጣናት የተሰጣቸውን መሬት እየሸጡ፤ አዲስ አበባ ላይ በተሰጣቸው መሬት ላይ ህንጻ
ከቢሾፍቱ እስከ አዳማ፤ አልፎም እስከ ሻሸመኔ ድረስ ያሉ መሬቶች በዚህ አይነት የሙስና ቅብብሎሽ ለጄነራሎቹ
ታደሉ። አባ ዱላ ገመዳ ይሄንን ሁሉ ሲያደርግ፤ ለሱም ትንሽ ጉርሻ ይሰጠው ነበር። ያቺ በጉቦም በ እጅ መንሻም ያገኛትን
ገንዘብ ሰብስቦ ቦሌ መድሃኔአለም ፊት ለፊት የተንጣለለ ህንጻ መገንባት ጀመረ።
እንግዲህ ልብ በሉ። በቦሌ መንገድ እርስዎ ብቻ አይደሉም የሚሄዱት- ሟቹ ጠቅላይ ሚንትርም በዚያ መንገድ
ብዙ ጊዜ ተመላልሰው ነበር - ያውም መንገድ እየተዘጋ። እናም አስጎብኚው ለርስዎ እንደሚነግርዎ ለመለስ ዜናዊም፤ “ይሄ
የእገሌ ነው። ይሄኛው የጓደኛችን እገሌ ነው።” መባሉ አልቀረም። ነገር ግን ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትርም ቢሆኑ፤ የስርአቱ
ዋነኛ መገለጫ የሆነውን የሙስና አደጋ በዝምታ ሲያልፉት ነበር። የኢህአዴግ ሰዎች ሙስናን እንደጥፋት የሚያዩት ከዚያ
ሰውዬ ጋር እስከሚጣሉ ድረስ ነው። እናም ከአባ ዱላ ጋር እስከሚጣሉና የጄነራልነት ማዕረጉን እስከሚገፈፍ ድረስ ምንም
አላሉም። በኋላ ላይ ግን… አባ ዱላ ከህወሃት ሰዎች ጋር ሳይሆን ከራሱ ሰዎች ጋር መጋጨት ጀመረ። በተለይም በኦህዴድ
የሙስና ነገር (ክፍል ሁለት) በዳዊት ከበደ ወየሳ ገጽ2ውስጥ ካለው ከነ ግርማ ብሩ ቡድን ጋር ክፉኛ ተጋጨ - የቁርጡ ቀን ሲመጣም በመታሰር፣ ክብርን በማጣት እና ንብረቱን
በመስጠት መካከል ዋዠቀ።
በመጨረሻ አባ ዱላ ገመዳ ያሰራውን እና ሊኖርበት የነበረው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የወጣበት ባለ
ትልቅ ግቢ ቪላ ጥያቄ ውስጥ ገባ። ጸቡ እየከረረ ሲመጣ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ያሰራው ትልቅ ህንጻ በሙስና መሆኑን ነገሩት።
መጀመሪያ ሊከራከር ፈለገ። በኋላ ላይ ግን ደሞዙና የወጣው ወጪ እንደማይመጣጠን ሂሳቡን ሰርተው ሲያሳዩት፤ “አይ እኔ
እንኳን Surprise ላደርጋችሁ ብዬ ነው” አለ።
ኦህዴዶቹም በመገረም፤ “ምንድነው Surprise የምታደርገን?” ሲሉ ጠየቁት።
“ይሄንን ቤተመንግስት የመሰለ ቪላ የሰራሁት ለኔ ሳይሆን፤ ለድርጅታችን ነው።” ብሎ የቤቱን ቁልፍ ሲያስረክብ፤
አጨብጭበው ዝም አሉት። አሁን በቦሌ በኩል ስታልፉ፤ “ይሄኛው የጄነራል አባ ዱላ ነበር” ይሏችኋል። ከርክክቡ በኋላ
ግን የኦህዴድ ዋና ጽህፈት ቤት ሆኗል - እውነት የማይመስል የአገራችንን ታሪክ ነው እያወጋናችሁ ያለነው።
ባለስልጣናቱ “Surprise” ከመባላቸው በፊት፤ እዚያው ቤት ምሳም እራት ተጋብዘው በልተዋል። የቤት ምርቃቱ
ጊዜ፤ ስጦታ ይዘው መጥተዋል። ጸቡ ሲመጣ ዝምድናው ወደ ሙስና ተቀይሮ፤ አባ ዱላ ገመዳ ቪላ ቤቱን ከነ ሙሉ እቃው
የኦሮሚያ ቤተ መንግስት እንዲሆን ሰጥቶ ከመታሰር አመለጠ። የጄነራልነት ማዕረጉን ከመቀማት ግን አልዳነም። ከመከላከያ
ሚንስትርነትም ሆነ ከኦሮሚያ ፕሬዘዳንትነት በጥፋት ተወንጅሎ ከተነሳ በኋላ ይህንን ታማኝ ሰው ሙስና የሌለበት ቦታ
ሊመድቡት ፈልገው ክፍት የስራ ቦታ ፓርላማ ውስጥ ተገኘ። እናም የፓርላማው አፈ ጉባኤ በመሆን፤ ኢህአዴግን
በማገልገል ላይ ይገኛል - አባ ዱላ (ምናሴ ገብረማርያም )።
እንግዲህ ይህ ሙስና የምንለው ነገር… ዋናዎቹን ሰዎች እስካላስከፋ ድረስ፤ በኢህአዴጎች ዘንድ እንደባህል
የሚቆጠር ነውር ያልሆነ ተግባር ነው። የሙስና ነገር አውርተን… የኢህአዴግ ሙስና እመቤት ስለሆነችው ወ/ሮ አዜብ
መስፍን ሳንጨዋወት ብንቀር እሳቸውም ቅር ይላቸዋልና ስለ ወይዘሮዋ ትንሽ እንዙር።
በአንድ ወቅት ለጄነራሎቹ መሬት ሲታደል ወይዘሮዋ ቦታ አምልጧቸው ኖሮ ተናደዋል። ወደ አዳማም ሆነ
ቢሾፍቱ ደውለው ቢጠይቁ፤ “መሬት ተወዲ’ዩ” አሏቸው። ቆይተው ግን በኦሮሚያ ሰበታ ከተማ መሬት መሰጠት መጀመሩን
ሰምተው፤ እንዲሰጣቸው ጠየቁና ተሰጣቸው። ከዚያም የሚያውቋቸውን ሰዎች እየላኩ መሬት ያሳድሉ ጀመር። በኋላ ላይ…
የሰበታ ከተማ አስተዳዳሪዎች ሁኔታው ሲበዛባቸው፤ በወ/ሮ አዜብ አማካኝነት የሚላኩትን ሰዎች መሬት ከለከሏቸው።
በዚህን ጊዜ ወ/ሮ አዜብ መስፍን እሳት ለብሰው፣ እሳት ጎርሰው ለከተማው አስተዳዳሪ ደወሉና ከፍ ዝቅ አድርገው
ተናገሩት። በመጨረሻ የሆነው ነገር ነው የሚገርመው… ወይዘሮዋ ዛቻ ቢጤ አሰሙ። እንዲህ ሲሉ።
“እንዲያውም በሰበታ አካባቢ ሙስና አብዝታችኋል ማለት ነው! ሙስና ስላበዛችሁ ግምገማ መደረግ አለበት።”
ወ/ሮ አዜብ እንዳሉትም በህወሃት ሰዎች ታጅበው ሰበታ ከተማ በመገኘት የመንግስት ሃላፊዎችን ከላይ እስከታች
አተረማመሷቸው። ለሳቸው መሬት የሰጧቸው ሰዎች ሳይቀር፤ በሙስና ተወንጅለው እየተለቀሙ ታሰሩ። መሃንዲሱ እና
መሬት ፈቃጆቹ ሁሉ ተቀፈደዱ። ከዚያም የራሳቸውን ታማኞች ሹመው ሰበታ ከተማን ለቀው ተመለሱ። ባለፈው አመት
ኢቲቪ ስመለከት እነዚያ በሰበታ ከተማ “ሙስና ውስጥ አላችሁበት” የተባሉ ሰዎች እያንዳንዳቸው ከአስር አመት በላይ
እንደተፈረደባቸው ሰማሁ። በርግጥ ሰዎቹ ሙስና ውስጥ ነበሩበት። ቢሆንም ግን ለወ/ሮ አዜብ መስፍን እና ለሌሎች መሬት
ሲሰጡ፤ ሙስና አልተባለም… የአዜብን “ትዕዛዝ አንቀበልም” ሲሉ ግን የጨዋታው ህግ ተቀይሮ፤ ሰዎቹ በሙስና ወንጀል
እየተለቀሙ ወህኒ ወረዱ።
መቼም የወ/ሮ አዜብ መስፍን ታሪክ ማለቂያ የለውም። ባለፈው ሰሞን ደሞ፤ አቶ አያሌው የተባሉ ትልቅ ባለሃብት
ፍርድ ቤት ቀርበው ሲናገሩ፤ “ክቡር ፍርድ ቤት እኔ ምንም ጥፋት እንደሌለብኝ አቃቤ ህጉም ያውቀዋል። የኔ ጥፋት ከወ/ሮ
አዜብ መስፍን ጋር በሽርካነት እንድሰራ ተጠይቄ እምቢ ማለቴ ነው።” ብለው ነበር። አቶ አያሌው በተከበሩበት አገር አስራ
ስድስት አመት ተፈርዶባቸው ወደ እስር ቤት መወርወራቸውን ከጥቂት ወራት በፊት ስንሰማ ማዘናችን አልቀረም። እንግዲህ
አቶ አያሌው በደርግ የሶሻሊዝም ዘመን ሳይቀር በንግድ ሙያ ውስጥ የቆዩ ናቸው። የደርግ ዘመን አልፎ በዘመነ - ነጻ ገበያ
ሲታሰሩ ያልገረመው ሰው የለም።
የሙስና ነገር (ክፍል ሁለት) በዳዊት ከበደ ወየሳ ገጽ3እዚህ ላይ የምናወራው ላይ ላዩን የምናውቀውን… እውነት የማይመስል፤ ነገር ግን እውነት የሆኑ የሙስና ታሪኮችን
ነው። ውስጥ ውስጡን የማናውቀው ብዙ ነገር ሊኖር እንደሚችል ምንም አያጠያይቅም። ሌላ ነገር ትውስ አለኝ። የዛሬ 12
አመት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ወደ አሜሪካ ሲመላለሱ፤ ብዙም አይን የሚገቡ ሰው አልነበሩም። ሃብታቸውም ሰማይ
አልደረሰም ነበርና ብዙዎች ትኩረት አንሰጣቸውም ኖሯል። ሆኖም እዚሁ አሜሪካ ኮሎምበስ ኦሃዮ ለምትገኘው እህታቸው፤
250 ሺህ ዶላር ካሽ ከፍለው ቪላ ቤት ሲገዙ ብዙዎቻችን ማመን አቃተን። እናም ‘አዜብ ሙስና ውስጥ የለችበትም’ እያለ
ለሚጨቀጭቀኝ ዘመዷ ስልክ ደወልኩና ጠየኩት።
“የምንሰማው እውነት ነወይ?” አልኩት።
“ምኑ?” አለኝ።
“ዘመድህ ካሽ ከፍላ ለእህቷ ቪላ ቤት የመግዛቷ ነገር…” ብዬ ሳልጨርስ፤ የነገሩን እውነተኛነት አረጋግጦ በትህትና
ሊያስረዳኝ ሞከረ።
“እሷም ሆኑ ልጆቿ ሲመጡ የሚያርፉበት ቤት ያስፈልጋቸዋል። ... ታዲያ ይህን ማድረጓ ምን ያስደንቃል?" የሚል
አይነት ምላሽ ሰጠኝ። ለነገሩ ከደጃዝማች ጎላ የሚወለዱ፤ የነአዜብ መስፍን የቅርብ ዘመዶች ብዙ ናቸው። ድርጊቷን
የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ፤ በግልጽ የሚቃወሟትም አሉ። ለገንዘብ ሳይሆን ለህሊናቸው ላደሩ ዘመዶቿ አክብሮት እንዳለኝ
በዚህ አጋጣሚ ጠቅሼ የውጪ ሃብት ግዢውን ነገር እዚህ ላይ ገታ ላድርገው።
የ"ደቡብ ክልል" ፕሬዚዳንት የነበሩት የአቶ አባተ ኪሾ ጉዳይም አለ። አባተ ኪሾ ከወያኔ ሳይጣሉ ከደቡብ በጀት
ተመላሽ የሆነ ሰባ ሚሊዮን ብር (70.000.000) ለመንግስት ተመላሽ ሊያደርጉ ሲሉ "ወዲህ በል!የምን መንግስት ነው?"
በማለት ወ/ሮ አዜብ ተቀብለው ወስደዋል። ብሩ ወደ አዜብ ካዝና ይግባ እንጂ የፖለቲካ ቂም የተቋጠረባቸው አቶ አባተ
ወደ ወህኒ ከመወርወር አልዳኑም። አቶ አባተ ኪሾ ይህንን ጉዳይ በፍ/ቤትም ጭምር ምስክር ሰጥተውበት ነበር።
የወ/ሮ አዜብን ጉዳይ ጨርሼ ወደሌሎቹ መሄድ ብፈልግም። ብዙ እውነት የማይመስሉ፤ ነገር ግን እውነት የሆኑ
አስገራሚ ነገሮች ታወሱኝ። ስለሁሉም ነገር ምንም ማለት ስለማልችል ጥቂት ነገር ብዬ የሴትዮዋን ነገር ልቋጭ። በኢትዮጵያ
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲቋቋም በዋናነት እንዲሰራ ከታዘዙት ነገሮች አንዱ፤ የመንግስት ባለስልጣናት ሃብታቸውን
እንዲያስመዘግቡ ማስደረግ ነው። ይህ ስራ እንደተጀመረ… “አሻፈረኝ አላስመዘግብም” ካሉት ውስጥ ወ/ሮ አዜብ እና
የህወሃት ጄነራሎች መሆናቸውን ከዚህ በፊት በሌላ ጉዳይ ላይ ጠቅሼው ነበር። አሁንም ልድገመው። እናም የወ/ሮ አዜብ
መስፍን የሃብት መጠንም ሆነ ምንጭ እስካሁን ድረስ በመንግስት ደረጃ አልተመዘገበም። አሁንማ ሴትዮዋ ጥቁር ሲለብሱ፤
ጥቁር ለብሰው የሚያጅቧቸው፤ ሲያስነጥሳቸው መሀረብ የሚያቀብሉ አሽከሮች አላቸው። ሴትዮዋ ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ
እንደጎማ ተንፈስ ብለዋል። ሜጋ ሚሊዮን ዶላር ከሚያንቀሳቅሰው የህወሃት ኤፈርት ሊቀመንበርነት ተነስተው፤ የመለስ
ዜናዊ ፋውንዴሽን ዛፍ አስተካይ ከመሆን ያለፈ ስልጣን እንደሌላቸው እየስማን ነው።
በሌሎች ላይ የሚደረገውን የሙስና ክስ አመሰራረት እያየን… “የሙስና እመቤቷ ወ/ሮ አዜብ እና ሌሎች
የኢህአዴግ ሰዎችስ ተራ መቼ ይሆን?” ማለታችን አልቀረም። ደግሞም “የጉምሩክ ባለስልጣናት ሲታሰሩ ዋነኛውን ሃላፊ አቶ
መላኩ ፈንታን ወንጀል አግኝተውበት ይመስላችኋል?” አይደለም። ነገሩ የህወሃቱን ገብረዋህድ ብቻውን ቢያስሩት በህወሃት
አካባቢ ከፍተኛ ጫጫታ መምጣቱ አይቀርም። ስለዚህ ከብአዴንም “የአማራ ድርጅት አባል አስረናል” በማለት ነገሩን
ለማብረድ የተጠቀሙበት ነው የሚመስለው።
ባለፈው አመት ብቻ ምን ያህል ሙስና እንደተፈጸመ እናውጋ እና እንለያይ። ባለፈው አመት (እ.ኢ.አ 2005) ከ1
ሺህ 500 በላይ ጥቆማዎች ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ደርሰው በ200 ያህሉ ላይ ክትትል አድርጓል። የሚገርመው ግን ከሁለት
ሺህ በላይ ጥቆማዎች ደግሞ፤ ከስልጣኔ በላይ ነው በማለት ባሉበት ትቷቸዋል። (ይህንን መረጃ ያገኘነው ከራሱ ከፀረ ሙስና
መስሪያ ቤት ነው።) እነዚህ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን አቅም በላይ የሆኑት እንግዲህ፤ የጄነራሎቹ፣ የነአዜብ እና የህወሃት
ከፍተኛ ንብረት እና የመከላከያ ጉዳይ መሆኑ ነው።
የሙስና ነገር (ክፍል ሁለት) በዳዊት ከበደ ወየሳ ገጽ4ለመሆኑ መከላከያ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በሙስና ተወዳዳሪ ያልተገኘለት፤ ከፌዴራል መንግስት ውጪ የራሱ ባለ
አምስት ሆቴል እና ሌሎች የንግድ ስራዎችና ገቢዎች እንዳለው ያውቃሉ? የምናወራው እውነት ስለማይመስሎት፤ የሙስና
ታሪካችን ስለሆነ አብረውን ይቆዩ።
ፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ከስልጣኑ ውጪ ያሉትን ሙስናዎች አይከታተልም። እናም ከዚህ በታች ያሉት ኮሚሽኑ
እርምጃ ስለወሰደባቸው ጉዳዮች ነው።
ባለፉት ሁለት አመታት ከአንድ ሺህ በላይ የሙስና ክሶች ተከፍተው፤ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ታይቷል ወይም
እየታየ ነው። እውነት ከማይመስሉ መካከል አንዳንዶቹን እንጥቀስ። በየሰፈሩ ወጣቶችን ሳያደራጁ፤ ያደራጁ አስመስለው
መሬት የወሰዱ የኢህአዴግ አባላት ብዙ ናቸው። የሃሰት የማህበራት ማደራጃ ሰነድ በማዘጋጀት ግምቱ 25 ሚሊዮን ብር
የሆነ መሬት በነዚህ ሰዎች እንደአባት ውርስ ። ከሰላሳ ሚሊዮን ግምት በላይ ያለው 4ሺህ ካሬ መሬትም በ’ነዚህ የኢህአዴግ
ሰዎች ያለአግባብ ወደ ግል ይዞታነት ተቀይረዋል ወይም ካርታ ወጥቶባቸዋል፤ አልፎ ተርፎም የገንዘብ ብድር
ተወስዶባቸዋል። ግምቱ 842 ሚሊዮን ብር የሆነ መሬትም ያለአግባብ በግለሰቦች እጅ ገብቶ፤ የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ
የሚያደርገው ጠፍቶት፤ ግራ እንደተጋባ 2006 ዓ.ም. ገብቷል።
የኢህአዴግ አባላትና ሹመኞች በመሬት ቅርምት ብቻ አያበቁም። ጉምሩክ መስሪያ ቤት ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው
ነበር። በኮንትርባንድ የተያዘን ለዋስትና የተያዘን ቦንድ ሰነድ በማጥፋት ገንዘቡን ቅርጥፍ አድርገው ይበሉታል። የኢህአዴግ
ወዳጆች ወይም ጉቦ የሚሰጡትን አነስተኛ የታክስ መጠን በማስከፈል ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወደ ግለሰቦች ኪስ ገቢ
ሆኗል።
በመንግስት መስሪያ ቤቶች ትላልቅ ግዥና ሽያጭ ሲደረግ ያለው ማጭበርበር ደግሞ አይን ያወጣ ነው። የአፋር
መስተዳድር ቻይናዎች መንገድ እንዲሰሩ ከተዋዋሉ በኋላ የፌዴራሉ መንግስት የሰጣቸውን 10.7 ሚሊዮን ብር እጃቸው
አስገብተው ከመብላታቸው በፊት ተይዘዋል። እንዲህ አይነት ብዙ ታሪክ መዘርዘር ይቻላል። ባለፈው አመት ብቻ ልዩ ልዩ
የመንግስት መስሪያ ቤቶች ባወጧቸው ጨረታዎች እና የሃራጅ ሽያጮች 3 መቶ ሚሊዮን ብር ተጨበርብሮ የተያዙም
የተፈቱም ሰዎች አሉ።
ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ 75 ሚሊዮን ብር መሰረቁን እንንገርዎና በየመስሪያ ቤቱ እንዲህ ያለው ማጭበርበር ምን
ያህል ሊሆን እንደሚችል እርስዎ ይገምቱ።
“በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል የሚመጡ ተጓዦች ንብረት መጥፋቱንስ ሰምተው ይሆን?” አዎ ባለፈው አመት
ብቻ፤ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ንብረቶች እና ሻንጣዎች ጠፍተዋል።
“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ነው የሚባለው… እንዲህ እንዲህ እያልን፤ የዳኛውንም፣ የጉቦኛውንም ታሪክ
እያወራን ከቀጠልን ጊዜና ምሽቱ ላይበቃን ነው። ስለዚህ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን በማለት ልንለያቹህ ነው። ጊዜ
አግኝተን እንደገና ከተጨዋወትን ከአጼ ምኒልክ ቤተመንግስት ስለተሰረቁት የወርቅ ሹካ እና ማንኪያዎች ጭምር
እናወጋለን። እንደገና ከተገናኘን የአጼ ኃይለስላሴ የወርቅ ቀለበት ስርቆት እንጨዋወታለን። አረ ሌላም አለ። የአጼ ምኒልክን
ሽጉጥ ሰርቆ፤ መጠጥ ቤት ሲፎልል የነበረን አንድ የኢህአዴግ ኮሎኔል ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታተመው ጋዜጣዬ ላይ
አጋልጠነው ነበር። በአገራችን የሚፈጸመው እውነት የማይመስለን የኢህአዴግ ሙስና ማብቂያ ያለው አይመስልም። በዚሁ
እንሰነባበት… መልካም አዲስ አመት።
የሙስና ነገር (ክፍል ሁለት) በዳዊት ከበደ ወየሳ ገጽ5
ምንጭ የኢትዮጵያ ሚዲያ መድረክ
No comments:
Post a Comment