-በ29 ሺሕ ካሬ ሜትር ውስጥ ወርቅ ለማምረት ማስጠናት ጀምሯል
ታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በሚጠይቀው የማዕድን ዘርፍ ውስጥ በመግባት፣ በደቡብ ክልል ለወርቅ ማምረቻ በተረከበው ቦታ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ማጠናቀቁ ታወቀ፡፡
ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በሽርክና ወርቅ ለማምረት የተቋቋመው አዲሱ ኩባንያ ላጋሉላ የሚል ስያሜ አለው፡፡ የኩባንያው ስያሜ የተወሰደው ለወርቅ ማምረቻ ከተመረጠው አካባቢ መጠሪያ ነው፡፡ አዲሱ ኩባንያ ለመጀመሪያ ደረጃ ጥናቱ የተረከበው መሬት 29 ሺሕ ካሬ ሜትር መሆኑን፣ በቅርቡም ተጨማሪ ቦታ ለመጨመር ዕቅድ እንዳለው ኃይሌ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ወርቅ በማምረት ታዋቂ ከሆነ አንድ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ጋር ድርድር እያደረገ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናቱ የተጠናቀቀ በመሆኑ፣ ቀሪ ሁለት ጥናቶች ከተካሄዱ በኋላ ወደ ምርት ይገባል፡፡ ወርቅ ማምረት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ መሆኑን የገለጸው ኃይሌ፣ የፈለገውን ያህል ወጪ ቢጠይቅ በዚህ ዘርፍ በመሰማራት የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለማሳደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት መቁረጡን አስረድቷል፡፡
የአገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ በወጪ ንግድ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት የሚል እምነት እንዳለው የሚገልጸው ኃይሌ፣ ወደ ወርቅ ምርት ኢንቨስትመንት ለመግባት ባደረገው ጥናት አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የወርቅ ሀብት እንዳላትና አዋጭ የሆነ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደሆነ መመልከቱን አስታውቋል፡፡
አትሌቱ በዘርፉ በማድረግ ያለውን እንቅስቃሴ የጀመረው ላጋሉላ የወርቅ ማምረቻ ኩባንያ ከመቋቋሙ ቀደም ብሎ የቡናና የቅመማ ቅመም እርሻ ሲጀምር መሆኑን ገልጿል፡፡ ለዚሁ የእርሻ ኢንቨስትመንቱም በደቡብ ክልል ማሻ ወረዳ ከ1,500 ሔክታር መሬት በላይ መረከቡ ይታወሳል፡፡ እስካሁንም ለእርሻ ሥራው ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንና ከ400 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን መቅጠሩን ይናገራል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በ200 ሔክታር መሬት ላይ የቡና ተከላ መጀመሩ ተገልጿል፡፡ አትሌት ኃይሌ አዲሱን ኩባንያ ሳይጨምር አሁን በተሰማራባቸው የሆቴል፣ የሪል ስቴትና ሌሎች የተለያዩ መስኮች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት እንደሚያንቀሳቅስ ይነገራል፡፡
ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment