Tuesday, September 17, 2013

አሁንስ በዛ …. ገለማኝም! ከሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ ሥላሴ
በጣም ብዙ ታገስኩኝ። በጣም ብዙ ብእሬን ኮረኮምኳት። የሚባለውን አነባለሁ። እያደንኩ አያለሁ። ዝም ያልኩት ግን
መማር ይቻል እንደሆን ብዬ ነበር። ከዚህም ሌላ በድርጀቱ በአባልነት ሆነ በአካልነት ያሉ ወንድምና እህቶቼም
ብዕራቸውን ሊያነሱ ይችላሉ ብዬም ጠበቅሁ። አሁን ግን እኔ ነፃ ሴት ስለሆንኩ ውስጤ የቆሰለበትን ነፃ አስተሳሰቤን
ላጋራችሁ ወደድኩ።
ለማን እንደሚጠቅም አላውቅም። ለማን ይመቸው ተብሎ እንደሚደረግም አይገባኝም። ለነገሩ እንዲገባኝም
አልፈልግም። ጠናና ዕይታና ቅንነት የነጠፈበት የምቀኝነት ቋሳ ----፤ ሽፍታው ድርጅት ወያኔ የሚፈጥረው መጠራቅቅ
አልበቃ ብሎ የነፃነት ትግሉ ቤተሰቦች ከሆኑት ስህተቶች እዬተፈለጉ፤ ስንጥርና ስንጥቅ እዬተፈተሽ በግንቦት ሰባት ላይ
ጦር የሚመዘዝበት ነገር አይገባኝም።
ድርጅት የሰዎች ስብስብ ነው። ስብስቡ ደግሞ እንደ ሰው ሊፈጽመው የሚችል ስህተት ሊኖር ይችላል። በግንቦት ሰባት
ግን ሁሉ ነገር ብርቅና ድንቅ ነው። አሉ የሚባሉትን ስህተቶች ለድርጅቱ መላክ ይቻላል። ቀጠሮ ይዞም ቁጭ ብሎ ፊት
ለፊት ቀርቦ ለመነጋጋርም መሪዎቹ ዕድሉን የሚነፍጉ አይመስለኝም፤ - ከቅንነት የመነጨ ከሆነ። ወያኔ የሚፈራውን፤
የሚርበደበትን ነገር የበለጠ ጥንካሬ መስጠት ሲጋባ ከጠላት ያልተለዬ ዱላ ይመዘዝበታል ግንቦት ሰባት። ይቀጠቀጣል
በመዶሻ፤ ከዚህም ባላፈ እንዘምትበታለን የሚል ጹሑፍም አንብቤያለሁ። ለመሆኑ ማንን እያገዝን ነው? ማንንስ
ይድላው ብለን ነው ይህን መሰል እርምጃ የምንወስደው? እስኪ ህሊናችሁን መርምሩት የነፃነት ትግሉ ቤተኞች።
በሌላ በኩል መወጮ ሰበሰበ ተብሎ ግንቦት ይተቻል። የድርጅት ህግ እኮ ነው። ፈቅደው አባል ከሚሆኑ አባሎቹ ገንዘብ
ንቅናቄው መሰብሰቡ። ደርግ እንደ መንግሰት ተደራጅቶ ኢሰፓ ከሚባል ፓርቲው ከአባላቱ በዬወሩ እንደ ገቢያቸው
መጠን መዋጮ ይሰበስብ ነበር። ይህ ደግሞ አንድ ድርጅት ሲፈጠር በሚያጸድቀው ደንቡ ላይ የአባላት መብትና ግዴታ
ላይ የሚደነገግና በአባላት ጉባኤ የሚጸድቅ መርህ ነው። አባላቱ ድርጅታችን ነው ሲሉ አይደለም ገንዘባቸውን ደንቡን
የህይወታችን መመሪያ ብለው ፈቅደውና ወደው ነው የሚቀበሉት። እስኪ እባካችሁ ወገኖቼ ስለ ፓርቲ አደረጃጃትና
አመራር ቀደምት ልምድ ያካበቱ ሀገሮችን ተመክሮ እስኪ አንብቡት። ውጪ ሀገር ደግሞ ግዴታ የለበትም ሰው ወዶና
ፈቅዶ አምኖበትም ነው አባል የሚሆነው። ስለሆነም ለወሰነው ውሳኔ እራሱን በነፃነት ማስገዛቱ የተገባ ነው።
ሌላው ጎልቶ ሲነገር የምሰማው ግንቦት 7 አልሰራም የሚለው ነው። ለድልም ተሎ በፍጥነት አልበቃም የሚሉም አሉ።
ድል ገቢያ ተሂዶ የሚገዛ ሸቀጥ ይመስል? ነባራዊ ሁኔታ እንደ ፍሬቻ በሰው እጅ የሚገራ እንደሆነ … አዬ! ለማንኛውም
ንቅናቄው ሲወጠን ከነበሩት ሁኔታዎች ተነስቼ ለምን እንዳሰበው አልተጓዘም ለሚለው … የግል ዕይታና የደረስኩበትን
መደምደሚያ ለመነሻ እንደሚከተለው አቀርባለሁ ….
1. በወቅቱ ፈርታይል ወይንም የለሙ ሁኔታዎች ነበሩ። እንቅስቃሴው ይፋ ተግባሩን ሲጀምር፤ ነገር ግን ጦርነቱ
የእርስ በርስ ነውና በቀንበጡ ተስፋ ላይ ጫና ገጠመው። ሚስጢር ማሸነፍ ነውና። ሚስጢር ከፈሰሰ ጠላት
እጅ ከገባ ብዙ ነገሮችን ይበክላል። ለቀጠይ እርምጃ ደግሞ እንደ ገና ከ“ሀ“ ይጀመራል። አዲስ ስልት ቅዬሳ
ሽርሽር አይደለምና ….
2. የሽፍታው አስተዳደር ያወጣው የሽብር ህግም ሌላው በንቅናቄው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው ጉዳይ ነው።
3. የከፍተኛ አመራሩ የአኗኗር ዘይቤ በተለያዩ አኽጉሮች መሆን፤ ለተግባሩ ፍጥነት እንቅፋት እንደሆንበት
አስባለሁ።
4. ዓለምዓቀፋዊ፤ አህጉራዊና ሀገራዊ ሁኔታዎችም የራሳቸው አሉታዊ ጫና አድርገውበታል፤
5. በመሪ አካላቱ ላይ ሽፍታው አስተዳደር የወሰደው ከዕድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት ድረስ ህገ ወጥ ዳኝነት
ሌሎችን እንዲሸማቀቁ አድርጓቸዋል፤
6. የፋይናንስ አቅሙ ራሱን ያልቻለ፤ በአባላቱ ጥገኛ መሆኑ እንደ ፍላጎቱ እንዳይራመድ እንቅፋት ሆኖታል።
7. ሁሎችም ማለት ይቻላል አመራሩ በቋሚነት ሳይሆን በትርፍ ጊዜያቸው ብቻ እንዲሰሩ መገደዳቸው። ይህም
የእንቅስቃሴው የኢኮኖሚ አቋም፤ አቅም ከድርጅቱ ትውልዳዊ ራዕይ ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ ለተልእኮው
መጠራቅቅ እንደፈጠረበት እገምታለሁ።
8. ድጋፍ በመስጠት እረግድ ምቀኝቱ በገፍ፤ ቅንነቱ ደግሞ በመቁንን የትውልዱ ዕጣ ፋንታ መሆኑ፤ ፈቃድ
የሰጠነው መሰናክል …. ነው፤
9. የትጥቅ ትግሉን ለመምራት አስተማማኝ፤ እርግጠኛ ቦታ፤ ወይንም መቀመጫ፤ ወይንም ኮማንድ ፖስት ሀገር
ለማግኘት የነበረው አቀበታማ ጉዞ፤ የተገኘው ቦታም ራሱን የቻለ የዲፕሎማሲዊ ጥረትና ተግባር፤ ሰፊ ጊዜና
ትእግስትን ይጠይቅ ስለነበር ….
ከዚህም በገዘፉ ፈተናውች ውስጥ የጮርቃ ድርጅት ኃላፊነቱና የልጅነቱ አቅሙ ማገራዊ አጥንት ከሚችለው በላይ
ሸክም ነበረበት። ይህም ሆኖ 1. ለድርጅቱ የተግባር መሰረት የሚሆኑ መመሪያዎችንና ሰነዶችን በማዘጋጀት፤
2. አመራሩን በመምረጥና በመመደብ፤ መደበኛ ጉባኤዎችና አስቸኳይ ስብሰባዎችን በማካሄድ፤
3. በተከታታይ ዓላማውንና ተግባሩን ለማስተዋወቅ የተደረጃ ህዝበዊ ስብሰባዎችን በአውሮፓ፤ በአሜሪካና
በአውስትረልያ በማካሄድ የተበተነው መንፈስ ለመሰብሰብ ያደረገው ጥረት ጉልበታም ነበር፤
4. በምስረታው ወቅት መዋቅራዊ ድርጅቱንም በመዘርጋት የሚመጥን ሰው ከማግኘት ጋር የነበረው ፈተናና
መጠራቅቅ ሰፊ እንደሚሆን እገምታለሁ፤ ግን የገጠመውን ፈተና ተቋቁሞ ተግባረዊ ማድረግ መቻሉ ደግሞ
የጥናካሬው አካል ነው።
5. የራዲዮ ፕሮግራሙ ሌላው የመረጃ ፍሰቱን መሰረት አስጥሏል፤
6. ድህረ ገጹን በመምራት፤ በማስተዳደርና ተልእኮውን እንዲወጣ በማድረግ እረግድ የበሰለ ተግባር ነው
እዬተከወነበት ያለው …
7. የዲፕሎማሲያዊ ተግባራቱ ደግሞ ከሁሉም የገዘፈው ኃላፊነቱ እንደሚሆን እስባለሁ።
8. ለስንት ዘመን ለዜና ለመዘገብ ፈቃደኛ ያልነበረውን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባርን ማንፌስቶ እስከማስቀዬር
የደረስ እጅግ ድንቅ ተግባር ሲሆን፤ የዘመናችን ምርጥ ክንውን ሊባል የሚያስችለውም ይመስለኛል።
9. በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የጥምረት መፈጠርና ለነፃነት ትግሉ የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት መንገድ መከፈቱ፤
10. ሰራዊት ለመመልምል፤ ለማደራጀትና፤ ለማሰልጠን ያደረገው ጥረት ….
11. በህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ያለውን የውክልና ፍላጎት በማሟላት እረግድም ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ የድርጊቱ
አካል እንደ ሆነ ይሰማኛል።
12. ተጨማሪ አባላትን በመልምልና በማሰማራት፤ አዳዲስ ውክል አካላትን በመሰዬምና መዋቅር በመዘርጋትም
ተከታታይ ተግባራትን ከውኗል ብዬ አስባለሁ። ዕለታዊ መተንፈሻ ተግባሩ ነውና ወዘተ … ከዚህ ሌላ ህዝብ
ዳኝነት ለመስጠት የማይችላቸው፤ ማለትም ለሚዲያ ይፋ ያልሆኑ ረቂቅ ስውር ሥራዎችንም እንደ ከወነ
ይገባኛል። ሁለገብ ትግልን የመረጠ ድርጅት ሁሉ ተግባሩን ይፋ እንዲያደርግ የአደረጃጃት ባህሪው
አይፈቅድለትም። ይህ እንግዲህ እኔ ውጭ ሆኜ የማያቸው ተግባራት ከሞላ ጎደል ለናሙና አነሳሰሁ።
እናንተ እንደምትሉት ደግሞ ኢሳት የግንቦት 7 ከሆነ በአፍሪካ የነፃነት ትግል ታሪክ ውስጥ በስደት አዲስ የፈጠራ፤
የብቃት ምዕራፍ ነው። አደረጃጀቱ፣ አመራሩ፣ ተግባሩ፣ ብቃቱ፣ ጥራቱ፤ አስተማሪነቱ ፍጥነቱ፤ መዘከርነቱና
አሸናፊነቱ ከልጅነቱ ጋር ኢሳት ሲመዘን ከባለ ግራጫው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ጋር ሲገመገም እርቀቱን እናንተው
ገምግሙት … ከሁሉ በላይ እርምት ለመቀበል ያለው ዝግጁነትና ቅንነቱ ፍቅርን ካለ ገድብ እንዲሸምት አድርጎታል።
ከዚህ በተረፈ በዬመድረኩ፤ በዬሩሙ፤ የግንቦት ነገር ሲነሳ ጆሯችሁን ቀጥ ለምታደርጉ ስህተት ቆፋሪዎች
የምነግራችሁ ከእላፊ ነገር ተቆጠቡና በሩ ክፍት ነው። አባል ሁኑ፤ ግዴታችሁን እዬተወጣችሁ እንዳሻችሁ
በመብታችሁ እራሳችሁን ተቹት፤ ተግባሩንም ገምግሙት፤ በዕለታዊ ድሉም ታደሙ! የማከብራችሁ ፍጽማናን
ከሰው ልጅ የምትጠብቁ ወገኖቼ ሁሉ የግንቦት አባል ሁኑና ግዴታችሁን እዬተወጣችሁ የመብታችሁን አፄ ለመሆን
ቁረጡ! ወስኑ!። አልመሸም …. መልካም ጉዞ …. ለአዲስ ዓመት ዋዜማ
ደግሞ! እስኪ ይሁን አልሰራም ከተባለም ብለን ጸጥ አለነ። አሁን በቅርቡ ክቡር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ያለውን
ተጨባጭ ሁኔታ ሲገልጹ ደግሞ ወያኔ ካበደው በላነሰ የነፃነት ፈላጊው ቤተሰብ ያሰማው ጩኽት በእውነት
የጆሮዬን ታንቡር ነው የበጠረቀው። ምን ይሁን ነው የምትሉት?!!! ምንድን ነው የምንፈልገው? ለመሆኑ
ከፍላጎታችን ጋር እንተዋወቃለን ….?! የሚፈልግ በሰላም፤ የሚፈልግ በመሳሪያ በቀለኛውን ወንበዴ ለመስወገድ
ወስኖ መታገል መብት አለው።
አሁን ሳዬው ግንቦት የድርጅቱን ነጻነትም እዬተጋፋነው ነው። በስልቱ ላይ ትችት አለን። በስትራቴጁ ላይ ትችት
አለን። ምን ችግር አለው የሚመጥነውን ድርጅት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ነው። ከቶ ማን ያዘን …. ጀምሩት እና ሞክሩት
… ከበሮ በሰው ሲይዙሽ እኮ ነው … ። ልናከብረውም ልናደንቀውም ሲገባ ጅማታችን እስኪገታተር ድረስ
እንወርድበታለን። ምን እንዲሆን ይሆን የምንፈልገው …. ስለተንገላታ በርኃ በበርኃ ስለተከላተመ …
ለምን ኤርትራ ተመረጠች የሚለውም ሌላው የጦርነት ግንባር ነው …. ይህም በሌሎች ድርጅቶች እኮ አይነሳም።
ቁጭ ብዬ ስታዘባችሁ። ከህሊናችሁ ጋር ስለመኖራችሁ እጠራጠራለሁ። የት ይሂድ …. የጁቡቲ መንግስት ማነን ይዛ
እንደሰረከበ ታውቃላችሁ። ሱዳን ሻ/ አጣናው ዋሴን ይዞ ነው የሰጠው። ኬኒያ በቅርቡ እንኳን ኢንጂነር ተስፋዬ
ጨመዳን ይዞ እስረክቧል። ሻ/አጣናው ዋሴና ኢንጂነር ተስፋዬም ነፃነት እንደ ራባቸው አልፈዋል። እኛ
የማናውቃቸው ታፍነው የተገደሉ፤ የታረዱ፤ የታሰሩ ሺ ናቸው። እዬሰሙ በጩቤም የተዘለዘሉም። ሄሮድስ መለስ
እኮ ከራሳቸው ውጪ ለማንም ምህረት የማይሰጡ ሳጥናኤል እኮ ነው የነበሩት። በቀል ነበር አንጎላቸው ገባችሁ!
ለመሆኑ የት ተሂዶ ትግል ይደረግ? ኤርትራ አካላችን ናት፤ ተገነጠለች ስንል አልነበረም? አሁን ጥግ ስትሆነን
ለምንድነው የሚጎረብጠን። አንድ ወገና በወያኔ ጦር ቆስሎ ህክማና ሳያገኝ መሞቱ ነውን ደስታ የሚፈጥርልን ይሆን
ግራዎች እስኪ መልሱልኝ? … እኔ በርቀትም ኡጋንዳ ላይ ኮማንድ ፖስቱን ያደረገ ድርጅት አውቃለሁ። ከተጨባጩ በጣም የራቀ ስለሆነ ፍላጎቱ ሆነ ራዕዩ ባክኖ ነው የቀረው። ስለሆነም ለአርበኞቻችን ጥግና ቤት የሆነውን አካላችነን
የሆነውን የኤርትራ መንግስት ከልብ አመሰግናለሁ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ! ። ለሎጅስቲክስ ሆነ ለትግል ከ ኤርትራ
የተሻለ ለ እኛ የለም። ወዛችን እኮ ናቸው! የሚገርመው „የብሄረሰቦች ነፃነት እሰከ መገንጠል“ እያሉ ስንት ህዝብ
ያስጨረሱ ድርጅቶች አሁን ደግሞ ኮናኞች መሆናቸው ግርንቢጥ ነው …. ጎርባጣ!
እንደ ማሳረጊያ አንድ ነገር ላንሳ እና …. ልሰናበት። ግንቦት ገንዘቡን የት አገኘው? የሚልም እድምታ አለ። ከዬትም
ይሁን። ጥገኛ እንዳይሆን ከተፈለገ ወጪውን ሁሉ የመሸፈን ግዴታ አለብን። እኛ ግን እንኳንስ ወጪውን ሁሉ
የዓመት የስልክ ወጪ የመሸፈን አቅሙ የሌለን በማለት ብቻ የዘለብን የተግባር ድሆች ነን። ለመሆኑ ከልመና ውጪ
የሆነ አቅም ያለው የፈጠርነው ድርጅት ወይንም ተቋም ለናሙና፤ ለምልክት አንድ ነገር አለን?~~~~ አዬ -
ትብትባችን መጠኑ ስፋቱ ቀመቱም ርዝመቱ …. በስንት ጉድ እኮ ነው የምንታመሰው። …. ይደክማል፤
መከረኛው ግንቦት 7 … እንደ ሰው የድርጅቱ አካላት ነፃነትም እንደተነፈገ ይሰማኛል። እኛ በዬቤታችን ስንት
እንላለን? ስንቱን ስናብጠለጥል ውለን እናድራለን? ደግሞ ለዚህም አመራሩ የእኛን ነፃነት የመስጠት ፈቃድ ይጠይቅ
…. አይደል? ስንገርም?! እግዚኦ! እኛ ብንችል አንደበታቸውን በዚፕ እንዘጋው ነበር። …. ሁላችንም የተሰደድነው
ነጻነት ፈልገን ነው። ሞተውም ደምተው ተቃጥለውም ያስጠጉን ሀገሮች ለሰጡን ነፃነቱንም ካልተሰረ ብለን ኡኡታ
እናሰማለን … አዝናለሁ። እራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የቆረጡትን … የግል ህይወታቸው፤ ፖለቲካዊ
ኑራቸውን፤ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸው ሁሉ ስነብጠለጥል መሽቶ ይነጋል። ነግቶ ይመሻል። ይህ ለእኔ ሥራ ፈትነት
ይመስለኛል።
ድል ከተፈለገ የመብታችና የግዴታችን ጣራና ግድግዳ አውቀን እንራመድ!
ማሰተዋል እንደ ተሰጠን እንፈጽመው ዘንድ እግዚአብሄርን በሱባኤ እንጠይቀው!
ቅንነትን ለማዳ እናድርገው!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
source addisvoice.

No comments:

Post a Comment