በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ወደ መንበሩ ሲመጡ ቀላል የማይባሉ የፕሮቴስታን ክርስትና ተከታዮች በደስታ ጮቤ እንደረገጡ ትዝ ይለኛል፡፡ በአንዳንዶቹ የእምነት ተቋማትም የምስጋና ፕሮግራም እንደነበር ሰምተናል፡፡ ሙስሊሞች ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስሊም ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲመጣ ቢመኙ መሻታቸውንም አይቶ ዓምላክ ቢሰጣቸው ክፋቱ አይታየኝም፡፡ በግሌ እኔም በእምነቱ ጠንካራ የሆነ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መንበሩን ቢይዝ ጮቤ ባልረግጥ እንኳን ደስ እንደሚለኝ ይሰማኛል (የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦርቶዶክስ ነበሩ?)፡፡ ነገር ግን እነዚህ ቦታዎች የሚያዙበት መስመር ሰዎች ባላቸው የፖለቲካ አመራር እና ሌሎችን እምነቶች በእኩል ለማስተዳደር ባላቸው ብቃት እና የሁሉንም ይሁንታ ሲያገኝ ነው እንጂ በእምነት ተቋማቱ በኩል ተወክለው ሲመጡ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሲሆኑ የፓርቲ ፕሮግራም ለማስፈፀም ካላቸው ቁርጠኝነት ብቻ ነው እንጂ ፕሮቴስታን መሆናቸውን ያሰበውም የለም፡፡ መሆን ያለበትም እንዲህ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ሌላ ምሳሌ ልስጥ ባራክ ኦባማ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ አብዛኛው ጥቁር ደስ ብሎታል በተለምዶ የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊ የነበሩ አንድ አንዶችን ጨምሮ ኦባማ ግን የጥቁር ብቻ ሳይሆን የሁሉም አሜሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሙስሊም ጠቅላይ ሚኒስትር ለማየት ቢፈልጉ ክፋት የቱ ጋ እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ይህን በጉልበት በተለይም ሌሎች ክርስቲያኖችን በማጥፋት እናድርገው እያሉ ከሆነ መረጃ ይሰጠን እና አብረን እንታገላቸው፡፡ ምክንያቱም ይህ የእልውና ጉዳይ ነው፡፡ እኔ እንደ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው መጥፋት አልፈልግም፡፡ ይህ ነገር ካለ በእውነት ኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነት አለ ብለን ልንስማማ እንችላለን መፍትሔም በጋራ መፈለግ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ መሰመር ያለበት እብድ የለም እያለን እንዳልሆነ ነው፡፡
የዛሬ ፅሁፌ መነሻዬ መግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት በእኛ ቤተክርስቲያ ለእምነት ዘብ ቁሙ በሚል የተቀባ መርዝ እየሸተተኝ ስለሆነ ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ማለት የምፈልገው የአሜሪካዊው የሰብዓዊ መብት መከበር ጀግና የነበረው ማርቲን ሉተር ኪንግ “ዕልም አለኝ” የሚለውን ንግግር ያደረገበት አምሳኛ ዓመት የሚከበርበት ወቅት ጋር በመገጣጠሙ የእኛ ማርቲን ሉተር ኪንግ ማን ነው ማለት ፈለግሁ፡፡ ኪንግ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የወንጌል አስተማሪ (ፓስተር) የነበረ ነው፡፡ አደባባይ ወጥቶ በሊንከን መታሰቢያ ላይ ቆሞ “ዕልም አለኝ” የሚለውን ንግግር ከማድረጉ በፊት ህዝቡን ያስተምርና ለመብቱ እንዲቆም ይሰብክ የነበረው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ መፅሐፍ ቅዱስን እየጠቀስ ስብዓዊ መብት በቀለም፣ በዘር፣ በሀይማኖት ተለክቶ የሚሰጥ ሳይሆን ሰው በመሆ ብቻ የሚገኝ ከፈጣሪ የተሰጠ የተፈጥሮ መሆኑን ነው፡፡ የእኔ ጥያቄ የሚሆነው አሁን ክርስትናን ከጥፋት ለመከላከል ዘብ መቆም ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊ መብቱ እንዲከበርለት የወንጌል መምህራን እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ አውነትን እንዲጋፈጡ እና ከመንግሰት የሚላክላቸውን አጀንዳ ማራመድ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር መስበክ ይኖርባቸዋል፡፡ እውነት ነው የወንጌል ሰባኪዎች በተዘዋዋሪ መንግሰትን ይተቻሉ፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት በግልፅ የኢትዮጵያ ህዝብ ስብዓዊ መብት መከበር ከቁስ ዕድገት መቅደም እንዳለበት ለሀይማኖት መሪዎችና ወንጌል ሰባኪዎች መንገር ድፍረት ነው የሚሆነው፡፡ ስብዓዊ መብቱ ያልተከበረለት ህዝብ መንፈሳዊ ህይወቱ ይጎለብታል ቢሉኝ ለማመን አልችልም፡፡ መንፈሳዊ ህይወት ቦታው ሰው ነው፡፡ ሕንፃ አይደለም፡፡ ቁስዊ ጥቅም ግን የሰብዓዊ መብት መከበር ሳይሆን ይልቁንም እንደዚህ ዓይነት ልዕልናዎችን ማጣት የበለጠ ቅርብ ያደርገዋል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ የልኑርበት፣ ፖለቲካና ኮረንቲ፣ ዓይማኖትና ፖለቲካ፣ ወዘተ የሚባሉ አደንዛዥ ቃላት የተበራከቱት ለዚህ ነው፡፡ ለዚህ ደግሚ በሁሉም መስመር ያሉ ሰባኪዎች ሚና አላቸው፡፡ ሰባኪዎቻችንም እራሳቸው የልኑርበት ልዕልና ላይ ስለሚገኙ ብቻ ሳይሆን በተገኘው አጋጣሚ መንጋውን በትነው በስደት ስለሚኖሩ ጭምር፡፡
ከኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ባለብት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ሰብዓዊ መብቱ እየተደፈረ መሆኑን፤ ማንም ስው ወንጀለኛም ቢሆን (መሳሪያ ይዞ ሲታኮስ ካልሆነ በስተቀር) በመንገድ ላይ ሲገደል ገዳዩን (መንግሰትንም ጭምር) በይፋ ወንጀል መሆኑን፤ ለመናገር ድምፅ የሚያሰማ ማን ይሆን፡፡ ማን ነው የእኛ ማርቲን ሉተር ኪንግ የሚሆነው፡፡ የእኛ ወንጌላዊያን ክርስትና የሚስፋፋው በወንጌል ማስፋፋት ቅድሚያ የሚሰጠው ልጆችን በእምነት ኮትክቶ በማሳደግ መሆኑ እንድንረሳ አድርጎ ሙስሊሞች ሊያጠፉን ነው ወደሚል ሃሳብ እንድንሳብ እና ለዚህም እሰከ ሞት የሚደርስ መስዋዕትነት እንድንከፍል የምንጠየቀው ለምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ እኛ ለእምነታችን ዘብ ስንቆም ሙስሊሞቹም ዘብ እንደማይቆሙ የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል፡፡ ሁለት ቡድኖች በተጠንቀቅ ከሆኑ አንድ እብድ በሚለኩሰው የግል ወይም የሰፈር ፀብ የሁለት ትልልቅ ቡድኖች ጦርነት እንደማያድ ማረጋገጥ አይቻለም፡፡ የዚህም ጦርነት ጦስ ሀገራችን ኢትዮጵያ የእኔ ብቻ ነች ከሚል አስቀያሚ በድነኝነት ወደ የማንም የማትሆን ምድረበዳ ሀገር ማድረግ ነው የሚሆነው፡፡ ወይም አሰታራቂ ነኝ ለሚል ከፋፍሎ ለሚገዛን እራሳችንን ማዘጋጀት፡፡ አንድ መውጫ ነገር ልበል ኢትዮጵያ ሀገራችን በቅዱስ መፅኃፎች የሚገዙ ግለሰቦች እንጂ ሀይማኖታዊ መንግሰት እንደማይስፈልገን፣ የሙስሊም ወይም የክርስቲያን ብራዘርሁድ ፓርቲ እንደማያስፈልገን ማስመር የግድ ነው፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት፡፡ ሀገራዊ ዕርቅ የሚሰፍንበት ከጥላቻ ፖለቲካ የምንገላገልበት ዓመት እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡ የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ፡፡
source Millions of voices for freedom - UDJ
No comments:
Post a Comment