Sunday, September 22, 2013

ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማን ሊሆን ይችላል?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ርዕሰ ብሔር በመሆን በሁለት ዙር ለ12 ዓመታት ያገለገሉት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ የስልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ የቀራቸው ጥቂት ቀናት ብቻ ነው። ይሄም ሆኖ ግን ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማን ሊሆን እንደሚችል አሁንም ድረስ ፍንጭ አልተገኘም። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የስልጣን ዘመን የስራ ክንውኖች ዙሪያ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ባለስልጣናትንና ምሁራንን አስተያየቶች አሰባስባለች፡፡ የ90 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ፕሬዚዳንት ግርማ ምን ተሳካላቸው፣ ምንስ ከሸፈባቸው? እሳቸውን የሚተካው አዲሱ ፕሬዚዳንትስ ማን ይሆን? አስተያየቶቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
=============
“የመምረጥ እድል ቢሰጠኝ ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞንን እመርጣለሁ” ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም ፕሬዚዳንት ግርማ እስካሁን በስልጣን ላይ ሲቆዩ ይህን ሰሩ፣ ይህን አደረጉ የምለው አንድም ወደ አዕምሮዬ የሚመጣ ነገር የለም። አንድም ጊዜ አቋም ወስደው በአገር ፖሊሲ ላይ ጫና ሲፈጥሩ አይቼም ሰምቼም አላውቅም። እንደውም እውነቱን ለመናገር ከነመኖራቸውም ትዝ አይሉኝም፡፡ አንድ ጊዜ እንደውም “አሰብ የኤርትራ አንጡራ ሀብትና ግዛት ናት” ሲሉ በጆሮዬ ሰምቼ እጅግ አዝኜባቸዋለሁ፡፡ ይህን በቴሌቪዥን ነው የተናገሩት፡፡ ቦታው ለምልክትነት ካልሆነ ብዙ የሚሰራበት አይደለም በሚለውም አልስማማም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሊያከናውኗቸው የሚችሏቸው የተለያዩ ተግባራት አሉ፡፡ በግልፅ የተቀመጡትን እንግዳ መቀበል፣ ፓርላማ መክፈት እና የመሳሰሉትን ትተን፣ በርካታ ስራዎችን መከወን ይችሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የበጐ አድራጐት ስራዎችን መምራት፣ የተለያዩ ማህበራትን ማጠናከር፣ ህዝቡን ለስራ ማደፋፈር፣እስረኞችንና ህሙማንንን መጐብኘትና ያሉበትን ሁኔታ መከታተልና የመሳሰሉትን ሊሰሩ ይችሉ ነበር፡፡
ከዚህም ባለፈ የውጭ ግንኙነት ላይ የዲፕሎማሲ ስራዎች ሞልተዋል፡፡ ነገር ግን እኔ አንዱም ላይ ሲንቀሳቀሱ አላየሁም፡፡ ስለዚህ በዚህች አገር ፕሬዚዳንትነት ላይ ብዙም የሚታወሱ አይደሉም ማለት እችላለሁ፡፡ የተለያዩ የአለምና የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች በርካታ ስራዎችን ይሰራሉ፣ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግን እንቅስቃሴያቸው በጣም ደካማ ነው፡፡ በቀጣይ ማን ፕሬዚዳንት ይሁን በሚለው ላይ የመምረጥ እድል ቢሰጠኝ አንድ ዕጩ አለኝ በውስጤ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ይህ በተለይ ለኢትዮጵያ ሴቶች ትልቅ አቅም ይፈጥራል። አሁን ባሉበትም ብዙ እየሰሩ ነው፣ ወደፊትም ብዙ ለመስራት አቅም እንዳላቸው ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም እጩ ምረጥ ብባል ለወ/ሮ ሙሉ ሰላምን ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡ “ፕሬዚዳንቱ ለሁለተኛ ጊዜ መመረጣቸው ፈፅሞ ስህተት ነበር” አቶ ሙሼ ሰሙ (የኢዴፓ ሊቀመንበር) እኔ እስካሁን በኖሩበት የፕሬዚዳንት ዘመናቸው አንድም የማስታውሰው ስኬት የላቸውም፡፡
ይህን የምልበት ምክንያት አንደኛ፣ ጤነኛ ሆነው አመቱን ሙሉ የሰሩበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ሁለተኛ፣ የሰውነት አቋማቸው በንቃት እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርጋቸው አልነበረም፡፡ በሶስተኛ ደረጃ፣ ባሉበትም ሁኔታ ይህን ሰሩ ብዬ በግልፅ የምጠቅሰው ነገር የለኝም፡፡ በዚህች አገር ጉዳይ ላይ፣ ይህችን አገር ወደፊት ያራመደ ጠንካራም ሆነ ደካማ የማስታውሰውም የማውቀውም ነገር የለም። እኔ ፕሬዚዳንት ግርማን የማውቃቸው በአገር ምልክትነታቸውና መገለጫነታቸው ብቻ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ህገ-መንግስቱ ሰፍሮ ከሰጣቸው ስልጣን ባለፈ በፕሬዚዳንትነታቸው ሊሰሯቸው የሚችሏቸው ሥራዎች ሞልተዋል፡፡ ለምሳሌ የፕሬዚዳንቱ ቦታ የዲፕሎማቲክ ስራዎችን እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ብዙ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችም አሉ፡፡ ምናልባት አንድ ወቅት ላይ በእርሳቸው ተጀምሮ የከሸፈ ወይም የት እንደደረሰ የማላውቀው የአገሪቷ የደንና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ነበር።
አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሊሰራባቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከጤና፣ ከአረጋዊያን፣ ከህፃናትና ከሴቶች፣ ከህፃናት ጥቃትና መሰል ጉዳዮች ጋር የተገናኙ ሥራዎች ሞልተዋል፡፡ በፖለቲካውም ማህበራትን በማቋቋምና በማጠናከር፣ እንዲሁም በት/ቤቶች ዙሪያ ሊሰሩ የሚችሉ እጅግ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ይህቺ አገር የሚያስፈልጓት ስራዎች ማለቴ ነው፡፡ እናም እርሳቸው የሀገሪቱ ምልክት እንደመሆናቸው ከተለያዩ አገራት መንግስታት ጋር እየተገናኙ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ፋውንዴሽኖችን ማቋቋምና ማጠናከር ይችሉ ነበር፡፡ የሌሎች አገሮች ፕሬዚዳንቶች ይህንን ያደርጋሉ። በሴቶችና በህፃናት ጥቃት ጉዳይ፣ በህፃናት የትምህርት ጉዳይ፣ በጤናና በበርካታ ሚሊዮን ጉዳዮች ዙሪያ ሊንቀሳቀሱና ሊሰሩ ይችሉ ነበር፡፡ ይህቺ አገር ያለባት ማህበራዊ ችግር ሠፊና ጥልቅ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ይህ ከማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በፖለቲካው ረገድ ብትወስጂው እዚህ አገር እጅግ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በፖለቲካ፣ በወንጀል እና በተያያዥ ጉዳዮች ወህኒ ቤት የሚገኙ እስረኞች አሉ፡፡ የእነዚህ እስረኞች ጉዳይ መፍትሄ አግኝቶ በቀላሉ የሚፈቱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በሠፊው መስራት ነበረባቸው፡፡ አንዳንዱ ሰው እኮ እስር ቤት የቆየበትን ምክንያት እንኳን አያውቀውም፡፡ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ከኦነግ ጋር፣ ከኦብነግ ጋርና ከተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ እስር ቤት ገብተው እስካሁን ያልተፈቱ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ጉዳይ አንድ ማህበራዊ ተቋም ተመስርቶ፣ ተጣርቶና መፍትሄ አግኝቶ መስተካከል ነበረበት፡፡ ይህን መስራት ያልቻሉት በጤናና በአቅም ሁኔታ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው መንግስት በርካታ ተጠቃሽ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ ቀላል የማይባሉ ተቋማትን በማጠናከር ረገድም ብዙ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡ ሰውየው የብቃት ችግር አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ አሁን ግን የእድሜ፣ የጤናና የሰውነት አቋም ችግሮች ተደማምረው በፕሬዚዳንትነታቸው መስራት የሚገባቸውን እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ መቼም ግልፅና ብዙም የማያወዛግብ ጉዳይ ነው፡፡
በተለይ ሁለተኛው ተርማቸው ፈፅሞ መደረግ ያልነበረበት ነው። አሁን ኢትዮጵያ ወደፊት ለመራመድ ከምትፈልገው አቅጣጫ አኳያ ጠቃሚ ያልሆነ ውሳኔ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ልማት፣ እድገትና ብልፅግና ማምጣት የምትፈልግ አገር ነች፡፡ የዚያ መገለጫ የሚሆን ፕሬዚዳንት ነው የሚያስፈልጋት፡፡ ለእኔ ያንን መገለጫ የሚያሳዩ ፕሬዚዳንት አልነበሩም፡፡ እንዳልኩሽ ኢትዮጵያ ራዕይ አላት፡፡ ራዕይ ስልሽ የኢህአዴግ ራዕይ አይደለም፣ የዜጐች ራዕይ ማለቴ ነው፡፡ ያ ራዕይ ደግሞ ዜጐች ከድህነት ወጥተው፣ የተረጋጋ የኢኮኖሚና በተረጋጋ አገር ውስጥ የመኖር ራዕይ አላቸው፡፡ ይህንን ለማምጣት ደግሞ አቅምና ብቃት ያለው ገለልተኛ ፕሬዚዳንት ያስፈልጋል፡፡ ገለልተኛ ሲሆን የፖለቲካ ተቃርኖዎችን በማስታረቅና መፍትሄ በመስጠት እንዲሁም አቅጣጫ በማሳየት፣ እነዚህን ሁሉ ስራዎች ወደ ውጤት መቀየር የሚችል መሪ ይሆናል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን የዜጐች ራዕይ ማን ያሳካል ለሚለው፣ እከሌ ማለት ምኞት ብቻ ነው የሚሆነው። አንደኛ፣ ኢህአዴግ ይህን እድል ለማንም አይሰጥም። ሁለተኛ የራሱን ሰው መርጧል፡፡ ሲመርጥ ደግሞ በራሱ መስፈርት ነው፡፡ ከብሄር፣ ከሀይማኖትና ከመሰል ጉዳዮች አኳያ እንደሚመርጥ ነው የሚገመተው፡፡ ከዚህ በፊት በውስጤ ያሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ከኢህአዴግ አኳያ አቅጣጫውን ሳየው፣ እከሌ ወይም እንትና ማለት ጥቅም የለውም፡፡
ስለዚህ አስፈላጊ አይደለም። ምክንያቱም ኢህአዴግ እንዲህ አይነት እድል የሚሰጥ ባህሪ የለውም፡፡ የሰዎችን ባህሪና ስነ-ልቦና አዳምጦ፣ ጠቃሚ የሆነን ሰው ወደዚያ ቦታ ለማምጣት ተነሳሽነት ያለው ድርጅት አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን አስተያየት መስጠት ዝም ብሎ ምኞት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ እኔ ደግሞ የምኞት ሰው ሳልሆን የተግባር ሰው ነኝ፡፡ “እንኳን አቶ ግርማ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳስ ምን ሰራና ነው” ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም ለመሆኑ አቶ ግርማ ምን ሰርቶ ነው ስኬት ነበረው ውድቀት ነበረው የምትይው? አሁን ይሄን ጥያቄ ብለሽ ነው የምትጠይቂው ወይስ ጠፍቶሽ ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ምን ሀላፊነት ተሰጠውና ነው ስኬት ውድቀት የምትለኪበት? የፕሬዚዳንቱ ስራ ዝም ብሎ ቁጭ ማለት ነው፡፡ ወደ 12 ዓመት ገደማ ቁጭ ብሏል ይወጣል፣ በቃ አለቀ፡፡ የምን ስኬት ነው? ምንስ ስራ ተብሎ ነው ስኬቱ የሚለካው? በመሰረቱ ህጉ ራሱ ምንም ሀላፊነት እና ሥራ አይሰጠውም፡፡ በህጉ ላይ የተወሰኑ ነገሮች አሉ፡፡ ሰዎችን መቀበል፣ እንግዶችን ማስተናገድ፣ አምባሳደሮችን መቀበልና መሸኘት፣ ይቅርታ መስጠት፣ “ይሙት በቃ” የተፈረደባቸውን ሰዎች ፈርሞ ማፅደቅ የመሳሰሉትን ያከናውናል፡፡ ይህንንም ቢሆን የሚፈፅመው ግን ከላይ ያሉት ሲፈቅዱለት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ እናንተ ጋዜጠኞቹም ታውቁታላችሁ፣ ዝም ብላችሁ ነው የምታደርቁን፡፡
እኔ የምለው--- ከእርሱ በፊት የነበረው ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳስ ምን ሰራ? እንኳን አቶ ግርማ? ዝም ብሎ ተቀምጦ ኖሮ ጊዜው ሲደርስ ወጣ፣ በቃ ይሄው ነው፡፡ አንድ ሰው ስኬቱና ውድቀቱ የሚለካው ይህን ይህን ይሰራል ተብሎ በጉልህ የተቀመጠ እና ሊያሰራ የሚችል ሁኔታ ላይ ሲሆን ነው፡፡ ይሄ በሌለበት ስኬት ውድቀት የሚባለው ነገር አይገባኝም፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ማን ይሁን? ምን ይስራ? ለሚባለው የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ እኔን ተይኝማ ጐሽ! “ፕሬዚዳንት የሚሆኑ ሰዎች ጤናማና ቀልጣፋ ቢሆኑ እመርጣለሁ” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር) ፕሬዚዳንቱ ስኬታቸው ውድቀታቸው ምንድነው የሚለው ጥያቄ ከባድና የሚገርም ጥያቄ ነው፡፡ እኔ እንደውም ባልናገር ይሻለኛል፡፡ እንዴ! እርሳቸው ቤተ-መንግስት ገብተው ሲጦሩና ሲታከሙ ኖሩ እንጂ ምን የሰሩት ስራ አለና ነው እንደ ጥያቄ የሚነሳውስ፡፡ እናንተም ቢሆን እንዴት አንድ ነገር ሳንፅፍ ይሰናበታሉ በሚል ለወጉ ነው እንጂ ያነሳችሁት ምንም አለመስራታቸውን ሳታውቁት ቀርታችሁ አይደለም፡፡ በግላቸው በተፈጥሮ ሳይንሱና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ፍላጐት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ እሰማለሁ፡፡ ነገር ግን ያ ጉዳይ ወደ ተግባር ተለውጦ ማየት ነበረብን፡፡
እኔ በበኩሌ ይሄ ነው የሚባል ነገር አላየሁም፡፡ እርሳቸው ርዕሰ መንግስት ሳይሆኑ ርዕሰ ብሄር ናቸው፣ ስለዚህ እሳቸው ሊሰሩ ይገባ የነበረው ይቅርታን የመስበክ፣ ሁሉንም ፓርቲዎች እኩል የማየት፣ በሀይማኖት ጉዳይ ችግር ሲከሰት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ነበር፡፡ ነገር ግን እርሳቸው ጤናቸውም፣ እድሜያቸውም ምክንያት ሆኖ የስራ እንቅስቃሴያቸው ትክክለኛ ፕሬዚዳንት ሊያደርገው የሚችለው አይነት አልነበረም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፣ እርሳቸው ኢህአዴግን ከማመን ውጭ በራሳቸው ተንቀሳቅሰው ይህን አደረጉ የሚባልላቸው ነገር የለም፡፡ በሶስተኛ ደረጃ፣ ቦታውም ሆን ተብሎ በህገ-መንግስቱ ሲፀድቅ ባዶ ከመሆን የማይሻል ተደርጐ ስለሆነ እኔ እንደ አንድ የፖለቲካ ቁምነገር ለማየት እቸገራለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ህገ-መንግስቱ ላይ ባይቀመጥም ፕሬዚዳንቱ ብዙ ሊሰሯቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ እርሳቸው ግን ምንም አላደረጉም፡፡ ለምሳሌ በሀይማኖቶች አካባቢ ያለውን እንመልከት፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ለሁለት ተከፍሎ ችግር ላይ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት እነዛም ከውጭ ይምጡና ይወዳደሩ የሚል ሀሳብ ካቀረቡ በኋላ፣ ፖለቲከኞቹ ሲቆጧቸው ሀሳቡን አንስቻለሁ አሉ። በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ይህ ሁሉ ችግር ሲፈጠር፣ እንደ ርዕሰ-ብሄርነታቸው መንግስት ከዚህ ጨዋታ እንዲወጣና ችግሮቹ መልክ እንዲይዙ ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ በምርጫው ጊዜ በፓርቲዎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ወደ እርቅ፣ ወደ መቻቻልና ወደ ሰላም እንዲመጡ የራሳቸውን አስተያየትና ሀሳብ መስጠት ይችላሉ፡፡
እንደርዕሰ ብሄርነታቸው ጐላ ባለ መልኩ ሊሰሯቸው የሚችሏቸው በርካታ ነገሮች ነበሩ፣ ነገር ግን እንደነገርኩሽ ዕድሜያቸውም ሆነ ጤናቸው እንዲሁም አጠቃላይ ሁኔታቸው ያንን እንዲከውኑ አላደረጋቸውም። በዘመኑ ቋንቋ “ከደረጃ በታች ተጫውተዋል” ነው የእኔ አስተያየት፡፡ በትምህርት ዝግጅት፣ በዲፕሎማሲ በአጠቃላይ ሁኔታዎች እከሌ ቢመረጥ የምትለው አለ ወይ ለተባልኩት እኔ በእውነቱ ምንም እከሌ የምለው ሰው የለኝም፡፡ አንደኛ የሚመረጠው ሰው በኢህአዴግ ኮረጆ ውስጥ ገብቶ ነው የሚሰራው፡፡ ሁለተኛ ቦታውም እዚህ ግባ የሚባል ስልጣን በህገ-መንግስቱ አልተሰጠውም፡፡ የሚወዳደሩትም ሰዎች በብዛት እዚያ ሲስተም ውስጥ የሚገቡት በዚህ ታሪክ ውስጥ ስማችን ተመዝግቦ እናልፋለን ብለው እንጂ ቦታውን አሁን ባለው ሁኔታ ቁም ነገር እንሰራበታለን ብለው አይደለም፡፡ ስለዚህ ለእኔ ማንም ተመረጠ ማን ለውጥ አያመጣም፡፡ ነገር ግን ጨቋኞች ቢሆኑም የአገር ምልክት ናቸውና ጤነኛ፣ የተማረ፣ ተነጋግሮ በቋንቋ የሚግባባ ሰው፣ በተቀላጠፈ ሁኔታ የሚንቀሳቀስና ያሉትንም ውስን ስራዎች የሚያከናውን ቢሆንና አገር ባይዋረድ እመርጣለሁ፡፡
ከዚህ ባለፈ በስራ ደረጃ ፕሬዚዳንቱ ይህን ሰርቶ፣ ይህን አድርጐ ለውጥ ያመጣል በሚል የምጠብቀው ምንም ነገር የለም፡፡ “ፕሬዚዳንት በህገ-መንግስቱ የተቀመጠላቸውን ሀላፊነት በአግባቡ ተወጥተዋል” ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ፕሬዚዳንቱ ይህን ሰሩ ወይም አልሰሩም ለማለትም በህገ-መንግስቱ የተቀመጠላቸውን አቅጣጫ ማየት ግድ ይላል፡፡ በህገ-መንግስቱ የተቀመጠና የተሰጣቸው የስራ ሀላፊነት አለ፣ ያንን ከመወጣት አኳያ በተገቢው መንገድ ተወጥተዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ ውጭ በግላቸውም በተለይ አካባቢንና ተፈጥሮን ከመንከባከብ አኳያ የጀመሩት ስራ በጥሩ ሁኔታ ተከናውኗል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የእኛ አገር አካሄድ በአብዛኛው ፓርላሜንታሪ ነው፡፡ በፓላሜንታሪ አገር ደግሞ ብዙውን ስራና ሀላፊነት የሚጥለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ስለሆነ ባልተሰጣቸው ሀላፊነት ስራ አልሰሩም ተብሎ የሚወቀሱበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም። ህገ መንግስቱ የፈቀደላቸውን ግን በአግባቡ ተወጥተዋል ባይ ነኝ፡፡ ይቅርታ በማድረግ፣ አምባሳደሮችን በመሾም እና በመሰል ጉዳዮች ላይ ሰርተዋል ወይ ከተባለ፣ አዎ ሰርተዋል። ሹመቶቹንም ቢሆን ቀጥታ መሾም ሳይሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ነው የሚሾሙት፣ ስለዚህ ስራቸውን ተወጥተዋል፡፡ ስለወደፊቱ ፕሬዚዳንት አመራረጥ መነሻው ህገ-መንግስቱ ነው፡፡
በህገ መንግስቱ መሰረት ለገዢው ፓርቲ የተሰጠ ስልጣን አለ፡፡ ገዢው ፓርቲ ነው ፕሬዚዳንቱን የሚያቀርበው፣ ስለዚህ ስለ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ከዚህ በላይ ማለት አልችልም፡፡ “ፕሬዚዳንት ግርማ ስኬታማም እድለኛም መሪ ናቸው” “የቀጣዩን ፕሬዚዳንት ማንነት መተንበይ አልችልም” አቶ አሰፋ ከሲቶ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ የፕሬዚዳንት ግርማ ዋናው ስኬት ለሁለት ጊዜ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመረጣቸው መሆኑ ነው፡፡ ከዴሞክራሲ ሂደቱ አንፃር ይሄ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በራሳቸው ለህዝብ አርአያ የሚሆን በርካታ ስራዎችን ላለፉት 12 ዓመታት ሲያከናውኑ ነው የቆዩት፡፡ የህዝብ አገልጋይነትን ስሜት ይዘው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ህዝብ ማገልገል መቻላቸው በጣም አስደሳች ነው፡፡ ለምሳሌ የተቸገረ ሰው ወደ እርሳው አቤቱታ ባቀረበ ጊዜ ችግሩ እንዲፈታ ያደርጋሉ፡፡ የቅርብ አማካሪ እንደመሆኔ የእርሳቸውን ውሳኔና ድጋፍ ሊያገኝ የመጣ ሰው የእርሳቸውን ድጋፍና ምክር አግኝቶ የሚሄድበት ሁኔታ እንደነበር አውቃለሁ በአጠቃላይ ዜጐችን የማገልገል እምነታቸውና ፍላጐታቸው ጠንካራ መሆኑን ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ በሌላ በኩል እውቀታቸው ከምንምና ከማንም ጋር ተወዳዳሪነት የሌለው ነው።
ለምሳሌ የቋንቋ ችሎታቸው በጣም ሰፊ በመሆኑ ከማንኛውም አገር መሪና ኤምባሲዎች ጋር በመገናኘት በፈለጉት ቋንቋ ሀሳባቸውን የመግለፅ ብቃታቸው ወደር የለውም፡፡ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳኛ፣ ጣሊያንኛና ሌሎችንም ቋንቋዎች አቀላጥፈው መናገር የሚችሉ በመሆናቸው ስለ አገሪቱ ጠቅላላ ሁኔታ በእድገት ጉዞና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአገርን ገፅታ ግንባታ በመስበክ ስኬታማ መሪ ናቸው፡፡ በጣም አንባቢ ናቸው፡፡ የማስታወስ ችሎታቸው ፍፁም የሚደነቅና ወደር የለሽ ነው፡፡ በዚህ ለሌሎች አርአያ መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡ ሌላው ማረሚያ ቤት ገብተው የታረሙ ሰዎች ይቅርታ አግኝተው እንዲወጡ ከፍተኛ ክትትል ያደርጋሉ። አንድ ሰው ወንጀል ፈፅሞ በፍ/ቤት ፍርድ ተሰጥቶ ማረሚያ ቤት የገባ ሰው መታረሙ ከተረጋገጠ ማረሚያ ቤት እንዲቆይ አይፈልጉም፡፡ ታራሚው ከማረሚያ ከወጣ በኋላ ችግር የማይፈጥር መሆኑን እንደ ይቅርታ መስፈርት ይወስዱታል፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት የነገሩኝን ባነሳ ደስ ይለኛል፡፡ በ1950ዎቹ ኢሉባቡር ጐሬ ውስጥ ለስራ በሄዱ ጊዜ 15 ሰዎች መንገድ ላይ ቆመው ያገኛሉ። ከመኪና ወርደው “ምንድናችሁ?” ብለው ሲጠይቁ፣ እስረኞች እንደሆኑ መለሱላቸው ከመሀላቸው አንዱ ጠብመንጃ ይዟል፡፡
“አንተስ ጠብመንጃ የያዝከው ምንድነህ?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ “ወደ መቱ አጅቦን የሚሄደው ፖሊስ ሊፀዳዳ ወደ ጫካ ገብቶ ጠብመንጃውን ያዝ ብሎኝ ነው” አላቸው፡፡ እርሳቸውም በጣም ተገርመው በወቅቱ መቱ ጠቅላይ ግዛት ሀላፊ ለነበሩት ሰው ደብዳቤ ፅፈው እንዲፈቱ አድርገው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን አጫውተውኛል፡፡ እናም የታረሙ ሰዎች እስር ቤት እንዲቆዩ አይፈልጉም፡፡ እድለኛ ናቸው የምለው ደግሞ በእርሳቸው ዘመን ታላቁ የህዳሴ ግድብ በመጀመሩ ነው፡፡ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድም ውጤታማ በሆነ መንገድ ተፈፃሚ እየሆነ ያለበት ወቅት በመሆኑም ስኬታማም እድለኛም ናቸው እላለሁ፡፡ እስካሁን እንደ ርዕሰ ብሄርነታቸው በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 11 መሰረት የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር ሙሉ ለሙሉ በአግባቡ እንደተወጡ አምናለሁ፡፡ በአስፈፃሚ አካል ስልጣንና ሃላፊነት ጣልቃ አይገቡም፡፡ ጠንካራና ታታሪ ሰራተኛ ናቸው፡፡ ለምሳ የማይወጡበትቅ ጊዜ ይበዛል፡፡ ሀላፊነታቸውንና ተግባራቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል፡፡ እርሳቸውን ተክቶ የሚሰራውን ሰው መገመት አልችልም፡፡ በህገ መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት ቀጣዩ ፕሬዚዳንትም በህዝብ በተወካዮች ም/ቤት እና በፌዴሬሽን ም/ቤት ስብሰባ ተደርጐ በውይይት ተመርጦ ነው የሚቀርበው፡፡ በመሆኑም የቀጣዩን ፕሬዚዳንት ማንነት መተንበይ አልችልም፡፡ የማውቀውም ነገር የለም፡፡
(ምንጭ አዲስ አድማስ)

No comments:

Post a Comment