ሥርጉተ ሥላሴ 10.09.2013
መቼም እኛ መላ ያጣን፤ ስንፈጠር ያዬነውን ነገር ለማድነቅ ያልተደልን ፤ በእጃችን ያለውን ኃብታችን ለማመሰገን
ያልተባረክን መሆናችን፤ አንጀት
የሚቆርጥ መቀስ ነው። ከብክበን
ያሳደገነው አብሮ አደግ ኮሳሳ
ባህሪያችን ቅናት ነው። እኛ የሌላ
ሀገር ጀግኖችን በትውስት
ስናሞጋግስ ይመቸናል። የተገለበጠ
ጉድ። በዚህ ዕድሜ የተመቸና
ሰላም የሰፈነው የለንደን ኑሯቸውን
ረስተው፤ ቤተሰቦቸውንም
ትተው፤ ልጆቻቸውንም አባት
አልባ አድርገው እንደ ገና ጫካ
ለጫካ ለነፃነት የሚተጉትን ክቡር
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለእኔ
ጀግናዬ ናቸው። ለሰማዕትነት
እራስን ፈቅዶ ከመስጠት ባላይ
ምን ትርጉም ያለው ጀግነንነት
አለና!
አቶ አንዳርጋቸው ጥሩ ተናጋሪ - አንደበተ ርዕቱ፤ ብቁ አስተማሪ፤ ጥሩ አደራጅ ከመሆናቸውም በላይ ጥሩ አድማጭም
ናቸው። እኔ በሁለት አጋጣሚ ከእሳቸው ጋር ተገናኝቼ በነበረበት ወቅት ውስጣቸውን ያዬሁት፤ በጥልቀት የመረመርኩት
ጉዳይ እራሳቸው የድርጅት ተቋም መሆናቸውን ነበር። አንዳንድ ተፈጥሮዎች አሉ እንዲዚህ ልዩ ጸጋና በረከት
የተመረቀለት። ያጌጠ መክሊት! እኔ ከፖለቲካ ተግባራት ጋር በጽኑ በተቆራኜው የህይወት ዘመኔ ሁሉ በታሪክ ታድዬ
ከሁለት ተፈጥሯቸውን እግዚአብሄር አምላኬ ለድርጅት ከመረጠው ወገኖቼ ጋር ተገናኝቻለሁ።
በአንድ ወቅት አብሬው እሰራው የነበረውና በአግባቡ ሰብዕናዬን የቀረጸው የድርጅት የተግባር መምህሬና አሁን ደግሞ
ለሁለተኛ ጊዜ የገጠሙኝ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ናቸው። ስለሆነም ይህን ተፈጥሮን እንዳከብረው፤ እንዳደንቀውና
እንድምሰክርለት ግድ አለኝና ብዕሬን እነሆ አነሳሁ።
አንድ የፖለቲካ ድርጅት የህይወቱ አናት ለድርጅት ጉዳይ ልዩ ተፈጥሮ ያላቸው፤ ሰብዕናቸው ለዚህ የተመረጠ፤ የተረጋጋ
የመንፈስ ቅምጥ ሃብት ያላቸው፤ የህዝብን ውስጣዊ ስሜት እዬረመሩ የሚፈውሱ ወገኖችን ማግኘት እጅግ አስቸጋሪና
መንገዱም አድካሚ ነው። ዘርፉ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውድቀትም ሆነ እድገት መሰረታዊ ሩህ ጉዳይ ነውና። የአንድ
የፖለቲካ ድርጅት አካላዊ አቋሙ፤ ህልውና፤ የአፈጣጠሩን ሥነ ምግባር አሟልቶ ኃይል ሊሆን የሚችለው ለድርጅት
ተፈጥሮው ሥነ ምግባሩን ያሟሉ፣ ትክክሉና ግጣሙን ያሟሉ ዜጎችን ሲያገኝ ብቻ ነው። በዚህ ስሌት ስንሄድ ለአንድ
የፖለቲካ ድርጅት ወይንም ግንባር ወይንም ንቅናቄ ምንም ዓይነት የመዋቅር ጋጋታ፤ የማንፌስቶ መሽሞንሞን፤ የፖሊሲ
ጥራት አስተዋጾ እንጂ ወሳኝ ሚና የላቸውም።
አንድ የፖለቲካ ድርጅት የወሳኝነት ሚና የሚጫወተው የድርጅት ብቃቱ ምንጭ የሆነ፤ አቅምን ፈጥሮ አቅምን
በአግባቡ ተግባር ላይ ሊያውል የሚችል ብቁ ተፈጥሮ ያለው ሰው ዘርፉን የመምራት አጋጣሚ ከተገኘ ልዩ ሽልማት
ነው። „ሽልማታችን“ በሚልም በዬካቲት ወር መጨረሻ በ2009 የጻፍኩት መጣጥፍ ይህን የብቃት መሰረት መነሻ ያደረገ
ነበር።
ሰው እንደ ሰው የሚያድርጉት አካላቱና የነቃው ህሊናው ሙሉዕነት ነው። ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት የሰው ሰውነቱ
ደግሞ የድርጅት ጉዳይ ነው። ይህ ከተገኘ መሰረቱ ሆነ መድረሻ እርካቡ ሙሉዕ ይሆናል። የዛ ድርጀት …. የጉዞ
እርግጠኝነት ይለፍም ይኖረዋል ። እርግጥ ነው ብዙ የፖለቲካ ድርጀቶች በዚህ ተፈጥሮ የታደሉ ሰዎችን በመምረጥና
በማሰማራት በአቅም ማነስ፤ ወይንም ጨርሶም ይህ ልዩ ተፍጥሮ ያላቸውን ካለማግኘት፤ ወይንም ለዘርፉ ብቁ ትኩረት
ካለመስጠትም ሊሆን ይችላል የድርጀቱ ሆድ ዕቃ የሆነውን የዘርፉን ጸጋዎች ለባለ ጸጋዎች ስለማያገናኙት ቀጭጨው
ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ካለ ሐሴት እንዲያልፉ ይገደዳሉ። እንዲህ የሰመረ ግንኙነት ሲኖር ግን ፈተናውን በማለፍ
ለውጤት የመብቃቱ አጋጣሚ አብዛኛውን እጁን ይይዛል። ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የድርጅት ዘርፍ ኃላፊው አንጎሉና ማዕከላዊ የደም ማማንጫ እንብርቱ እንዲሁም መተንፈሻ
ቧንቧውም ነው። ከክቡር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተፈጥሮ ስነሳ በዚህ ግንቦት 7 ከሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች
የበለጠውን ዕድል አግኝቷል ብዬ አምናለሁ። ግንቦት ሰባት የዚህ ዕድል ባለድርሻ በመሆኑም ከምንም ነገር በላይ
የመንፈስ ዲታ ነው።
ምክንያቱም የድርጀቱ መዋቅራዊ ነባቢተ ነፍስ መደወሪያ ይህ ዘርፍ ነው። በድርጀት ዘርፍ ተግባር ከሁሉም በላይ ረጅም
ጊዜ ሳይሰለቹ መቀመጥን ይጠይቃል። ፍላጎትን ጠቅልሎ በተገቢው ሰዓት - ለተገቢው ኃይል በአግባቡ ማከፋፈልን
ይሻል። እንደ ገናም ያሰማራቸውን ተግባሮች ሰብስቦና ገምግሞ ለቀጣይ ስምሪት ድክመቶችን በማረም እንዲሁም
ፈተናዎችን በማረቅ ተከታይ የስምሪት ተግባር እዬከወነ ለውጤቱ ድልድይ ያበጅለታል። ለዚህ ደግሞ ለግንቦት 7 ብቻ
አይደለም ለትውልዱ ክቡር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የግንቦት 7 ጸሐፊ ተፈጥረዋል። ስጦታም ናቸው።
እርምጃውን እራሱ ቁጭ ብዬ ሳስተውለው ይህ እርምጃ በዚህ ዘመን ይታሰባልን? ይህ ውሳኔ በዚህ ዘመን ይታለማልን?
ለዛውም ከአውሮፓ ወደ ሳልህ በረኃ … በማለት እኔ እና እኔን ስብሰባ አስቀምጬ ፍርድ ስጥ ብዬ ህሊናዬን ሳፋጠው
መልስ አልነበረው። ህሊናዬ ከበደው። እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ክቡር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፍጹም ሊገለጽ የማይችል
የመስዋዕትነት የተግባር አብነት ሆኖ ነው ያገኘኋቸው። ተግባሩ ሥነ ጸጋ፤ ከሥነ - መስዋዕትነት ጋር ሲጋባ የነፃነት
ስዋሰዋዊ ህግ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
የማይሆነው ሲሆን፤ ያልተሰበው ሲከውን በዓይን ላይ ዕውነት ቁሞ ሲመሰከር ማዬትን ላልታደሉት ስውሮች
መዳህኒዓለም አባቴ ዓይናቸውን በተለይም ህሊናቸውን እንዲበራላቸውና የቀበሩትን ቅንነት ይጠቀሙበት ዘንድ
እንዲረዳቸው እዬተመኘሁ …. የእናታችነን ጥቃት ለማውጣት በዱር በገደሉ ለሚከላተሙት የነፃነት ደቀ መዝሙር
የ2006 ምርጥ ሰው ክቡር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን እግዚአብሄር አምላክ እንዲጠብቃቸው ድንግልም ጥላ ከላላ
ትሆናቸው ዘንድ እማጸናለሁ። ድካማቸውን ለፍሬ ይበቃ ዘንድም ከልብ እመኛላቸዋለሁ። ለአርበኞቻችንም
ከማያልቀው የኤደን ገነት ኃይልና ብርታት ድልና ሰብል ዕለታዊ ስንቃቸው እንዲሆንላቸው ከልቤ እመኛለሁ።
ድል ለአርበኞቻችን!
የትውልዱን ባለውለታዎች የምናከብርበት ንጹህ ልቦና አምላካችን ይፍጠርልን!
አሜን!
source Addis Voice.
No comments:
Post a Comment