Wednesday, July 24, 2013

ወ/ሮ አዜብ መስፍን ኢሕአዴግ የአቶ መለስን ሕልፈት ለመቀስቀሻ ተጠቅሞበታል መባሉን አስተባበሉ

  ነሐሴ 14 ቀን የአቶ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ እንዲሆን ተወሰነ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ ኢሕአዴግ ሕዝብን ለማነቃቃትና የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ለማስፋት ተጠቅሞበታል መባሉን፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን አስተባበሉ፡፡
24 JULY 2013 ተጻፈ በ  
ወ/ሮ አዜብ ሐምሌ 13 ቀን 2005 ዓ.ም. ማስተባበያውን የተናገሩት፣ የባለቤታቸውን አቶ መለስ ዜናዊን የሙት ዓመት አከባበር አስመልክቶ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡

‹‹ኢሕአዴግ የአቶ መለስን ሞትና መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽንን ለሕዝብ ማነቃቂያነት እየተጠቀመበት መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ ምላሽዎ ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ወ/ሮ አዜብ፣ መጀመሪያ ‹‹መለስ ማነው?›› የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ አዜብ በምላሻቸው፣ ‹‹መለስ ኢሕአዴግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመለስ ከፍተኛ ፍቅር አለው፡፡ ከኢሕአዴግ በፊት የመለስን ሐሳቦች፣ ጅምሮችና ውጥን ሥራዎች ለማስቀጠል ሕዝቡ ቃል ገብቷል፡፡ ሕዝቡን ፓርቲው ኢሕአዴግ ቀስቅሶት ሳይሆን የራሱ ስሜትና ፍቅር ፈንቅሎት ወጥቷል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የአቶ መለስ ዜናዊ ሥራዎች በኢሕአዴግ ቅስቀሳ ላይ ተመሥርተው ከሕልፈታቸው በኋላ የሰረፁ አለመሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ አዜብ፣ አቶ መለስ በነበሩበት ወቅት ምንም ዓይነት ቅስቀሳም ሆነ ሌላ ነገር ሳይኖር፣ በሕዝቡ ውስጥ ሰርፆ የቆየና ገንፍሎ የወጣ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ሕዝቡ የኢሕአዴግ ቅስቀሳ እንደማያስፈልገው የተናገሩት ወ/ሮ አዜብ፣ በአቶ መለስ የተጀመሩ ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ ግን ኢሕአዴግ የመምራት ግዴታ እንዳለበትና እየመራም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሚመራቸው ሥራዎች በሙሉ የአቶ መለስ ጅምሮች በመሆናቸውና በተሰባሰበ የሰው ኃይል መሠራት ስላለባቸው፣ ኢሕአዴግ የማስፈጸም ሥራውን ሊያከናውን የግድ እንደሚለውም አክለዋል፡፡
24 JULY 2013 ተጻፈ በ  
እንደ ወ/ሮ አዜብ ገለጻ፣ ፓርቲው የአቶ መለስ ክብርና ፍቅር ስላለው እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ስማቸውን መጥራቱና ማንሳቱ ነውር የለውም፡፡ ለመነገጃነት ግን አለመጠቀሙን ሕዝቡ ሊገነዘብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን የቦርድ አመራር ሆነው ከተመረጡት ከወ/ሮ አዜብ በስተቀር፣ ሌሎቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት መሆናቸው ‹‹አቶ መለስና ሥራዎቻቸው የሕዝብ ናቸው›› ከሚለው ጋር እንደሚጋጭና ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ለምን እንዳልተካተቱ እንዲያብራሩ የተጠየቁት ወ/ሮ አዜብ፣ ጥያቄው ትክክል ነው ብለዋል፡፡

‹‹ፋውንዴሽኑ በተቋቋመበት ወቅት ይኼንን ኃላፊነት ተሸክሞ መንቀሳቀስ የሚችለው የቅርብ ኃይል አሁን ቦርድ ሆኖ የተሰየመው ነበር፤›› ካሉ በኋላ፣ ሕዝቡ ግን ፍላጎት እንዳለው እንደሚያውቁ ገልጸዋል፡፡ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ባለቤት የሚሆንበት ማዕከል እንደሚገነባና አሁን ያለው ሁኔታም እንደሚስተካከል አስረድተዋል፡፡

‹‹ዘመቻ መለስ ለአረንጓዴ ልማት›› በሚል መሪ ቃል ተራራዎችን በችግኝ ለማልበስ፣ የፋውንዴሽኑ ቦርድ በችግኝ ማፍላት ዙርያ ሲረባረብ መክረሙን የገለጹት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ሲሆኑ፣ የችግኝ ተከላው ፕሮግራም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

የአቶ መለስ ዜናዊን ሙት ዓመት አስመልክቶ የተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ ካሳ፣ ‹‹አረንጓዴና ዘላቂ ልማት›› የሚለው የአቶ መለስ ፅኑ እምነት በመሆኑ፣ በስማቸው የሚሰየም ቦታን በመከለልና በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የችግኝ ተከላ በወረዳ፣ በክፍለ ከተማና በማዕከል እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንዳንድ የሚያስተካክለውና የሚሠራው በመኖሩ፣ ሙዚየሙና ፓርኩ የሚገነባበት ትክክለኛ ቦታ ለጊዜው ባይታወቅም፣ ዲዛይኑ በመሠራት ላይ መሆኑንና በቅርቡ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ አፈ ጉባዔው አስታውቀዋል፡፡

በሙዚየሙና በፓርኩ መሥሪያ ቦታ ላይ ነሐሴ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ እንደሚቀመጥ የገለጹት አቶ ካሳ፣ ነሐሴ 14 ቀን የአቶ መለስ ሕልፈት የተነገረበትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ድንጋጤና ሐዘን የሰማበት ቀን በመሆኑ፣ ‹‹የአቶ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ ቀን›› እንዲሆን ቦርዱ መወሰኑንም ተናግረዋል፡፡ ኅብረተሰቡ በፍላጎቱ ለሙዚየሙና ለፓርኩ ግንባታ መዋጮ ማድረግ እንደሚፈልግ በተለያየ መንገድ እየገለጸ መሆኑን፣ በፍላጎቱ መሠረትም ማዋጣት እንዲችል በኢትዮ ቴሌኮም አማካይነት በሚሰጡ ቁጥሮች ከሁለት እስከ አንድ መቶ ብር መላክ እንዲያስችለው መመቻቸቱንና በቅርቡ በመገናኛ ብዙኀን እንደሚገለጽ አስታውቀዋል፡፡     
ምንጭ ሪፖርተር.

No comments:

Post a Comment