Friday, July 26, 2013

በቅርቡ በኦሮሞ ወንድሞቻችን ላይ የተፈጸመዉ ሰቆቃ ሊቆጨን፤ ሊያንገበግበንና ሊያስተባብረን ይገባል

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለምአቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ ዘጠኝ፤ አንቀጽ አስርና አንቀጽ አስራ አንድ የማንኛዉም አገር ዜጋ ያለ አግባብ መታሰር እንደሌለበት፤ በወንጀል ተጠርጥሮ የሚታሰር የማንም አገር ዜጋ በአስቸኳይ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበትና የፍርድ ቤቱ ሂደት አስከተፈጸመ ድርስ ደግሞ የተጠርጣሪዉ ዜጋ ንጽህና የተረጋገጠ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል። በዚሁ የተመድ አለምአቀፋዊ ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ድንጋጌ ሰነድ ላይ ተመስርቶ የተጻፈዉ የ1994ቱ የኢትዮጵያ ህገመንግሰት አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ ማንም ዜጋ ያለ አግባብ መታሰር እንደሌለበት፤ ማንም ዜጋ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ዉጭ መታሰር እንደሌለበትና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታሰረ ዜጋም ቢሆን በአስቸኳይ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት በግልጽ ይደነግጋል። ኢትዮጵያ ደግሞ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ያረቀቀችና ያጸደቀች አገር ብቻ ሳትሆን ከሃምሳ አንዱ የተመድ መስራች አገሮች ዉስጥ አንዷ ናት።
የ17 አመት የጫካ ዉስጥ ትግል ያካሄደዉና በ1983 ዓም አዲስ አበባ ገብቶ ላለፉት ሃያ ሁለት አመታት የኢትዮጵያን በትረ ስልጣን ጨብጦ የያዘዉ ህወሃት ኢትዮጵያ በፊርማዋ ያፀደቀችዉን የተመድን አለምአቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌም ሆነ እሱ እራሱ አርቅቆ የጻፈዉን የኢትዮጵያ ህገመንግስት ማክበር ቀርቶ የሰነዶቹ ምንነት በዉል የጋባዉ ድርጅት አይደለም። ህወሀት የተወለደዉና ጥርሱን ነቅሎ ያደገዉ ጫካ ዉስጥ ሲሆን ዛሬም ከ22 አመታት የከተማ ዉስጥ ቆይታዉ በኋላ ኢትዮጵያን ያክል ትልቅ አገር የሚያስተዳድረዉ በዚያዉ ተወልዶ ባደገበትና በተካነዉ የጫካ ዉስጥ ህግ ነዉ። ህወሀትን ይዞት ካደገዉ ባህሉና ከዋና መገለጫ በህሪይዉ ተላቀቅ ማለት ዉኃ መዉቀጥ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም የጥቁር ህዝብ የነጻነት ምልክት የሆነዉን የኢትዮጵያን ህዝብ በጫካ ዉስጥ ህግ መዳኘትና ማስተዳደር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ በፍጹም ሊቀበለዉ፤ አለም አቀፉ ህብረተሰብ ደግሞ አፉን ዘግቶ ሊመለከተዉ የማይገባ በህዝብና በአገር ላይ የሚፈጸም ከባድ ወንጀል ነዉ።
ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የተቃወመዉን ማሰር፤ ሀሳቡን በንግግር ወይም በጽሁፍ የገለጸዉን ማሰቃየትና የዘረኝነት ፖሊሲዉንና ኢትዮጵያን የማፍረስ አላማዉን ያወገዘን ዜጋ ሁሉ አስሮ ሰቆቃ መፈጸም ወይም ከአገር እንዲሰደድ ማድረግ ከመደበኛ አገር የመምራት ፖሊሲዎቹ ዉስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ። በወያኔዋ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወንጀል ተብለዉ ዜጎችን ከሞት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ድረስ የሚያስቀጡት የፈጠራ ክሶች አፍሪካን ጨምሮ በብዙዎቹ የአለማችን አገሮች ዉስጥ የማይገሰሱ የዜጎች መብቶች ናቸዉ። የሚገርመዉ ወረቀት ላይ የሰፈረዉ የወያኔ ህገመንግስትም ይህንኑ ይደነግጋል፤ ሆኖም ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁለት አይነት ዜጎች ያሉ ይመስል በአንድ በኩል ህገመንግስቱ የሚቆምላቸዉ ዜጎች አሉ በሌላ በኩል ደግሞ ህገመንግስቱ የሚቆምባቸዉ ዜጎች አሉ። ዜጎችን በግልሰብ ደረጃ በባህሪያቸዉና በችሎታቸዉ ሳይሆን በቡድን ለይቶ በዘር ማንነታቸዉ የሚመለከተዉ ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ ስልጣኔን ይቀናቀኑኛል ብሎ ካሰባቸዉ ከሁለቱ ግዙፍ የአገራችን ብሄረሰቦች ማለትም ከአማራዉና ከኦሮሞዉ ብሔረሰቦች ጋር ለብዙ ግዜ ጥርስ ተናክሶ ቆይቷል። ባለፉት ሁለት አመታት አማራዉን በአማራነቱ ብቻ እያሳደደ መድረሻ ያሳጣዉ ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ በቅርቡ በግፍ ታስረዉ በቁጥጥሩ ስር በሚገኙ 69 የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ይህ ነዉ ተብሎ በሰዉ አንደበት ሲነገር አጅግ በጣም የሚዘገንን ወንጀል ፈጽሞባቸዋል።
መለስ ዜናዊ ከመሞቱ ከአንድ አመት በፊት ከፍርድ ቤት ፈቃድ ዉጭ በግፍ ሰብስቦ ያሰራቸዉና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡና ለምን እንደታሰሩ እንኳን ሳያዉቁ ለሁለት አመታት እስር ቤት ዉስጥ የከረሙት 69 የኦሮሞ ተወላጆች ባለፈዉ ሳምንት እስር ቤት ዉስጥ እንዳሉ እጅግ በጣም የሚዘገንን ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። ባለፈዉ ሀምሌ 6 ቀን ፍርድ ቤት ለመቅረብ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ቀጠሯቸዉ በአራት ወር የተራዘመባቸዉ ስልሳ ዘጠኙ የኦሮሞ ተወላጆች የቀጠሮዉን መራዘም በመቃወም አቤቱታቸዉን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ለማቅረብ ሲሞክሩ የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪዎች እንዴት እንዲህ ይታሰባል በሚል በቂም በቀል በመነሳት እስረኞቹን በቡድን በቡድን በመከፋፈልና እጅና እግራቸዉን በማሰር ከፍተኛ ድብደባ መፈጸማቸዉን ከሆስፒታል ምንጮች የተገኘዉ መረጃ ያመለክታል። በዕለቱ ድብደባ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸዉ እስረኞች ዉስጥ ስምንቱ በድብደባ ብዛት እራሳቸዉን በመሳታቸዉ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ስልሳ ዘጠኙ አስረኞች በሶስት ቡድን ተከፍለዉ ድብደባዉ የተፈጸመባቸዉን ክፍሎች በአይናቸዉ ከተመለከቱ ሰዎች በተገኘዉ መረጃ መሰረት እስረኞቹ የተደበደቡባቸዉ ክፍሎች በደም በመጨቅየታቸዉ አርብ ቀኑን ሙሉ በውሀ ሲታጠቡ አንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ይህ ወያኔ ቀድሞዉኑም ቢሆን ያለ አግባብ ባሰራቸዉ ንጹህ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የፈጸመዉ ወንጀል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በየቀኑ የሚፈጽመዉ በደልና ወንጀል አካል በመሆኑ ግንቦት ሰባት የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የህንን ዘግናኝ ወንጀል በራሱ ላይ እንደተፈጸመ አገራዊ ወንጀል በመቁጠር ከወያኔና ከዘረኛ ስርዐቱ ለመገላገል የሚያደርገዉን ትግል በያለበት እንዲያፋፍም ወገናዊ ጥሪዉን ያስተላልፋል። ኦሮሞዉ ሲጠቃ አማራዉ ካልደረሰለት አማራዉ ሲረገጥ ሶማሌዉ ፤ አፋሩ፤ ሲዳማዉና ወላይታዉ ወዘተ ካልደረሱለት ከፋፋዩ የወያኔ ስርዐት እያንዳንዳችንን ተራ በተራ ማሰቃየቱንና መርገጡን መቀጠሉ የማይቀር ነዉ። ስለዚህ ከወያኔ ጋር በምናደርገዉ የሞት የሽረት ትግል የኛ ኃይል አንድነት የወያኔ ኃይል ደግሞ መነጣጠላችን መሆኑን አዉቀን ይህንን ዘረኛ ስርዐት በቃ ብለን ከጀርባችን ላይ አሽቀንጥረን ለመጣል በህብረት እንነሳ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!



    No comments:

    Post a Comment