Wednesday, July 24, 2013

የፓርላማው ውይይት መታፈኑን በይፋ ያጋለጠው የኢቲቪ ጋዜጠኛ ከሥራ ተባረረ

(በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበው)
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናና የአስፈፃሚ ተቋማት ኃላፊነት” በሚል ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ.ም ያደረገውን ውይይት በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በኩል ተቆራርጦና ተዛብቶ እንዲተላለፍ ተደርጓል በሚል አንድ ዜና መዘገቡ ይታወሳል።
ይህን ዜና በሰንደቅ ጋዜጣ የህዳር 5 ቀን 2005 ዓ.ም ዕትም “ኢቲቪ የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ውይይት በማፈን ተወቀሰ” በሚል ርዕስ ከቀረበ በኋላ፤ በዚህ ዘገባ ላይ ተመድቦ የሠራው የቀድሞ የኢቲቪ ባልደረባ ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ ረቡዕ ህዳር 12 ቀን 2005 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ለዝግጅት ክፍላችን ምላሹን ሰጥቷል።
ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ
(ፎቶ ከሰንደቅ ጋዜጣ)
እነዚህ ዘገባዎች ከተስተናገዱ በኋላ፣ ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ ለሰንደቅ ጋዜጣ መረጃ እንደሰጠና ሚስጢር እንዳወጣ ተቆጥሮ የዲስፒሊን ክስ ቀርቦበታል። ኢ.ሬ.ቲ.ድ በዲስፒሊን ክሱ ላይ አራት ከፍተኛ የሥራ አመራሮች በምስክርነት ዘርዝሮ አቅርቧል። የድርጅቱ የዲስፒሊን ኮሚቴ በከሳሽ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና በጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ መካከል የክስ ዝርዝር እና የመልስ መልስ ደብዳቤዎች ሲያዳምጥ ከሰነበተ በኋላ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም በቁጥር ቴ02.1/131-304/02/8/ በተፃፈ ደብዳቤ ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻ ከግንቦት 10 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ከሥራ የሚያሰናብተውን ቅጣት አሳልፏል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባለቤትነት በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ጥቅምት 23 ቀን 2005 ዓ.ም የተካሄደው ስብሰባ በመልካም አስተዳደር፣ በተጠያቂነት፣ በሙስና ችግሮችና በመሳሰሉት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተካሄደ ሲሆን በዚህ ውይይት ላይ የኢፌዲሪ ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ ፀሐዬ፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ የእምባ ጠባቂ ተቋም ዋና እምባ ጠባቂ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣ የአ/አ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አበባው ስጦታው እና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጠራውና የአስፈፃሚ አካላትና የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናን በተመለከተ የተደረገው ውይይት፣ በዕለቱ በሥፍራው ባልነበረ ጋዜጠኛ ተገቢ ባልሆነ መልኩ ተቆራርጦና ተዛብቶ ለሕዝብ መቅረቡ ትክክል እንዳልነበረ በይፋ በመግለፁ ምክንያት ከሥራ የተሰናበተው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ባልደረባ የነበረው ጋዜጠኛ አዲሱ መሸሻን ስለሁኔታው ፋኑኤል ክንፉ አነጋግሮታል።
ሰንደቅ፡- የዚህ ዜና መነሻ አንተን አድርገው ለመውሰድ ያስቻላቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- ይህን ምላሽ መስጠት የሚችሉት እነሱ ናቸው። በሰጡኝ የክስ ዝርዝር ላይ ግን ሌላ ምክንያት ነው ያስቀመጡት። ወይም ደግሞ ላነሳኸው ጥያቄ ማረጋገጫ ማቅረብ የሚችለው የዚህ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ብቻ ነው።
ሰንደቅ፡- እንዴት?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- ምክንያቱም “ኢቲቪ የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ውይይት በማፈን ተወቀሰ” ለሚለው ዜና መነሻ ለሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በእኔ በኩል ያልኩትም አንዳች ነገር የለም። እንደማንም አንባቢ ይህ ዜና በሰንደቅ ጋዜጣ ከወጣ በኋላ ነው የተመለከትኩት። ስለዚህም መረጃ ከእኔ አግኝታችሁ ከሆነ አግኝተናል፤ ካላገኛችሁ አላገኘንም ለሚለው ምላሽ መስጠት የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ይመስለኛል።
ሰንደቅ፡- በርግጥ የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ለዚህ ዜና መነሻ መረጃውን ያገኘው ከሌላ ሶስተኛ ወገን መሆኑን ማረጋገጥ እንችላለን። ሆኖም ግን ይህ ዜና በወጣ በሳምንቱ ህዳር 12 ቀን 2005 ዓ.ም. እርሶ ለሰንደቅ ጋዜጣ ማስተባበያ መስጠትዎ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ከዜናው ጋር በተያያዘ ለምን ማስተባበል ፈለጉ?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- “የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናና የአስፈፃሚው ተቋማት ኃላፊነት” በሚል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያዘጋጀውን ፕሮግራም የቀረጽኩት እኔ በመሆኔ ነበር። በሰንደቅ ጋዜጣም የተሰራው ዜና “የባለስልጣናት ድምጽ ታፈነ” የሚል በመሆኑም ጭምር ነው። ከዚህ አንፃር እንደአንድ ጋዜጠኛ ውይይቱን አፈነ ተብሎ መወንጀል በጣም አደገኛ ነው። እንዲሁም ማንስ አፈነው? እንዴት ታፈነ? ለሚሉት ጥያቄዎችም ምላሽ የሚፈልጉ መሆናቸው ግልፅ የሆነ ነገር ነው። በተለይ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩትን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ኃላፊነት ታሳቢ ስታደርግ በእኔ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን ድንጋጤ መገመት ከባድ አይደለም። የእነዚህን ከፍተኛ ባለስልጣናት አንደበትን ለማፈን በእኔ በተራ ረዳት አዘጋጅ ቀርቶ በሌላው የተቋሙ ከፍተኛ አመራር የሚሞከር ተግባር ተደርጎ የሚወስድ አካል ያለ አይመስለኝም።
ይህ ችግር ከተፈጠረ በኋላም ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ተወያይቻለሁ። እንዲሁም አንድ የተቋሙ ከፍተኛ አመራር ለማግኘት ጥረት ባደርግም አልተሳካልኝም። የሆኖ ሆኖ ከባልደረቦቼ ጋር ከመከርኩ በኋላ ፕሮግራሙ ታፍኗል ብሎ ለዘገበው ጋዜጣ ማስተባበያ በመስጠት እራሴን ከጉዳዩ ነፃ ማድረግ እንዳለብኝ ተማምነናል። የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናቱም እኔ አለማድረጌን ሊገነዘቡ የሚችሉት ፕሮግራሙ ታፍኗል የሚለውን ዜና ባሰራጫው ሚዲያ መሆኑ አሻሚ አይደለም። ስለዚህም በዚህ ጉዳይ ላይ ንፁህ መሆኔን ለማረጋገጥ ለሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በጉዳዩ ላይ ያለኝን መረጃ ለመስጠት ተገድጃለሁ።
ሰንደቅ፡-እርሶ እንደዚህ ቢሉም፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ታህሳስ 01 ቀን 2005 ዓ.ም. በተፃፈ ደብዳቤ የዲስፕሊን ኮሚቴው “አቶ አዲሱ መሸሻ በየነ በፕሮግራሙ ኢ.ሬ.ቴ.ድ የባለስልጣኖች ድምጽ አፍኗል። ፕሮግራሙ ቆራርጧል የሚል የተሳሳተና ከኃላፊነት የራቀ እና በሀሰት የተሞላ መግለጫ ለሰንደቅ ጋዜጣ” ሰጥቷል ሲል ይከሳል። በዚህ ላይ የእርሷ አስተያየት ምንድን ነው?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት የኢ.ሬ.ቴ.ድ “የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ውይይት በማፈን ተወቀሰ” ያለው ሰንደቅ ጋዜጣ እንጂ እኔ አዲሱ አይደለሁም። በወቅቱም በሰጠሁት ማስተባበያ ተቋሙን በተመለከተ ያልኩት አንዳች ነገር የለም። የማፈን ነገር ተፈጽሟል ከተባለም ግለሰቡ እንጂ ተቋሙ ሊሆን አይገባም በማለት ነበር ተቋሙን የተከላከልኩት። በሌሎችም ተቋማት ግለሰቦች ከተቋሙ ዓላማ በመውጣት የሚፈጽሙት ስህተት በእኛም ተቋም በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጽሟል። ይህ ማለት ግን ግለሰቦች ከተቋም በላይ ናቸው ማለት አይደለም። ስለዚህም ግለሰቦች በሰሩት ጥፋት በግል መጠየቅ አለባቸው እንጂ በተቋም ደረጃ ስህተቱ ሊታይ አይገባም። ስለዚህም አንድ ሰው በራሱ መነሻ በፈጸመው ተግባር የተቋም አድርጎ መውሰድ ከሕግም ከሞራልም አንፃር የሚያስኬድ አይመስለኝም።
ሰንደቅ፡- የተከሰስክበት የደብዳቤ ይዘት ሚስጥር በማውጣት የሚል ነው። የሰጠኸው ማስተባበያ ከሚስጥር መጠበቅ ጋር እንዴት ትገልፀዋለህ?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ሚስጥር ማባከን ከመጥፎ ፍላጎት (intention) የሚመነጭ ነው። ሚስጥር የሚባክነው ተቋምን ወይም ግለሰብን ለማጥቃት ከመፈለግ የሚመጣ ክፉ መንፈስ ነው። ከዚህ አንፃር ስትወስደው፣ እኔ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ የሰራሁትን ፕሮግራም የሚመለከት ዜና በመሰራቱ ብቻ ማስተባበያ ሰጠው እንጂ ምን አጠፈሁ። ከእኔ ጋር ተያያዥነት ያለው ዜና ባይወጣ እኔም ባልተናገርኩ፤ እነሱም ክስ ያሉት ክስ ባልመሰረቱብኝ ነበር። ስለዚህም የጋዜጠኝነት ሙያዬን (integrity) በሚያጠፉ “አፋኝ” ተብሎ በተሰየመ ሁኔታ ስሜ ጠፍቶ፣ ስሜን ለመመለስ መከላከሌ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ከሚስጥር ማባከን ከመጠበቅ ጋር ምን ያገናኘዋል?
ሁለተኛው፣ “የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናና የአስፈፃሚው ተቋማት ኃላፊነት” በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተካሄደው ውይይት ዋናው ዓላማው፣ ውይይቱ ለሕዝብ እንዲቀርብ ነበር። ተደራሽነቱም ለሕዝቡ ነው። ለሕዝቡም ግልፅ መረጃ ለማቅረብ የተዘጋጀ ውይይት ነበር። ከሁሉ በላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነበረው የስብሰባ ይዘት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ በዚህች ሀገር ውስጥ የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ ለሕዝብ ማሳየት ነበር። ሕዝቡም አደጋውን በመረዳት ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ግንዛቤ ለማስጨበት ያለመ ስብሰባ ነበር። ይህ ታዲያ ምን ሚስጥር አለው? ሚስጥር ከሆነ መጀመሪያውኑ ሚዲያውን አይጋብዙም ነበር። በወቅቱም ፕሮግራሙ ሲቀረጽም ሚስጥር ነው ያለ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን አልነበረም።
ሌላው በዚህ ተቋም ውስጥ በቆየሁበት የስራ ዘርፎች ሚስጥር ተብለው የሚቀረፁ ስራዎችን ጠንቅቄ አውቃለሁ። በሚስጥር ደረጃ የተቀረፁ ስራዎችንም ሰርቼ አውቃለሁ። በዚህ ደረጃ የሰራኋቸውን ስራዎች እንኳን ለሶስተኛ ወገን፣ በተቋሙ ውስጥ ማወቅ ከሚገባቸው ሰዎች ውጪ ዉይይት አድርጌም አላውቅም። አለቆቼም ይህን ጠንቅቀው ያውቁታል።
ሰንደቅ፡- የዲሲፕሊን ኮሚቴው እንደሚለው ከሆነ “በስሜት ያደረኩት ነው” ሲሉ አቶ አዲሱ በኢዲቶሪያል ስብሰባ ላይ ገልጸዋል ይላል። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- በነገራችን ላይ የነበረው ኢዲቶሪያል ስብሰባ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን ብዙ ርቆ የሄደ ነው። ግልፅ የፖሊስ ምርመራ ነበር የተደረገብኝ። አስራ አራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ባሉበት የተደረገ ስብሰባ ሲሆን አውጣ፣ አታውጣ የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ። እኔ ለማስፈራራት፣ ለማሸማቀቅ የተደረገ ኢዲቶሪያል ስብሰባ ነበር። የቀረበብኝ ውንጀላ እስከሀገር ክህደት የሚደርስ መሆኑ ነበር የተነገረኝ። የፖለቲካ ይዘት ፈጥረውለት እኔ አንገት ለማስደፋት በአደባባይ ውጣና ማስተባበያ ስጥ ብለውኛል። የሚገርመው እኔ ነኝ ፕሮግራሙን የቆረጥኩት ያለው አመራር በዚህ ስብሰባ ውስጥ አንዱ ወቃሽ ሆኖ የተገኘበት ነበር።
ሰንደቅ፡-በዚህ ስብሳባ ደረሰብኝ የሚሉት ጉዳት አለ?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- አለ እንጂ። ከዚህ በፊት የኢዲቶሪያል ስብሳባ የምናደርገው አየር ላይ የዋሉ ፕሮግራሞችን ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን ለመገምገም ነው። ከዚህ ዜና ጋር በተያያዘ የተደረገው ኢዲቶሪያል ግን መንፈሱን የተለየ ነው። የአንድ ተቋም ኃላፊዎች ተሰብስበው የፖሊስን ስራ በመተካት ያን ሁሉ ወከባ ማስፈራራት ሲፈጥሩ መመልከት በጣም አሳዛኝ ተግባር ነው። በእኔ ውስጥ የፈጠረው ስሜት ለረጅም ጊዜ ውስጤን ጎድቶታል። በተለይ የኢ.ሬ.ቴ.ድ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ይታወቃል። የምክር ቤቱን ውይይት መቁረጡን በግልፅ መናገሩን ሳይፈራ፣ ለምን እኔን ውይይቱ ተቆርጧል ብልሃል ብሎ ከስራ ሊያሰናብተኝ እንደፈለገ አልገባኝም።
ሰንደቅ፡-በታህሳስ 01 ቀን 2005 ከዲሲፕሊን ኮሚቴው ወጪ በሆነው ደብዳቤ ላይ “ፕሮግራሙን ያዘጋጁት ባልደረባችን አቶ አዲሱ መሸሻ” የሚል ሲሆን፣ በጥር 20 ቀን 2005 ከዲሲፕሊን ኮሚቴው የወጣው ደብዳቤ በበኩሉ “ፕሮግራሙን ከ90 በመቶ በላይ የሰራው አቶ ሳሙኤል ከበደ” ናቸው ይላል። ከዲሲፕሊን ኮሚቴው በዚህ መልኩ ደብዳቤዎቹ ሊዘጋጁ ቻሉ? ፕሮግራሙን የሰራው ማነው ሊባል ይችላል?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- ዲሲፕሊን ኮሚቴው ያወጣው ደብዳቤ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነው። ለክሱ እንዲረዳቸው አንድ ደብዳቤ በእኔ አዘጋጁ። ለመከላከል እንዲረዳቸው ደግሞ ፕሮግራሙን ከ90 በመቶ በላይ የሰራው አቶ ሳሙኤል ከበደ ናቸው የሚል ደብዳቤ አዘጋጅ። ይህ በራሱ የሚነግርህ ነገር አለ። በማኛውም ዋጋ እኔ መክሰስ እና ከስራ ማፈናቀል ለዲሲፕሊን ኮሚቴው የተሰጠው ተልዕኮ ነው። አቶ ሳሙኤል በወቅቱ ትምህርት ላይ ነበሩ። እንዴትም እንደመጡ አላውቅም።
እውነቱ ግን ጥቅምት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ቅዳሜ ፕሮግራሙን ሰርቼ ሙሉ ዝግጅቱ እሁድ ጥቅምት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ዜና በኋላ የሚቀርብ መሆኑ ነው። በዚህ ዕለት የሚተላለፍ መሆኑን የሚገልፅ ከውይይቱ የተወሰዱ አጫጭር ንግግሮች የሚያሳይ ማስታወቂውን /ስፖት/ የሰራሁትም እኔው እራሴ ነኝ።
ሰንደቅ፡- አሁን በዚህ መልስ በእርሶ ላይ የተወሰደው እርምጃ በሌላው ሰራተኛ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምንድን ነው?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- ይህ ጥያቄ ከነሳህልኝ በውይይቱ ላይ አንድ የተሰነዘረ ነጥብ ልንገርህ። በዚህ ውይይት ከተሳተፉት ተሳታፊዎች መካከል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ዓሊ ሱሌማን አንዱ ናቸው። እሳቸው ከገጠማቸው አስቸጋሪ የፀረ-ሙስና ትግል ሲገልፁ፤ “የመልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚታገሉ እና የሙስና ተግባራትን የጠቆሙና ያጋለጡ ሰዎች በአለቆቻቸው የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱባቸው ቤሰቦቻቸው ተበትነዋል። በዚህም የተነሳ እነዚህ ግለሰቦች ምነው ይህን ባልተናገርኩ እያሉ አንገታቸውን ደፍተው ተሸማቀው እየሄዱ ነው። እነዚህ ሃይሎች ገነው ወጥተው ለፀረ-ሙስና ትግል የተሰለፉ ኃይሎች ግን አንገታቸውን ደፍተው ይገኛሉ” ነበር ያሉት።
ሰንደቅ፡- አሁን እርሶ ላይ የደረሰውን ነገር ከዚህ ከአቶ አሊ ሱሌይማን አባባል ጋር እንዴት ያስታርቁታል?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- የኮሚሽነሩን አስተያየት በእኔ ላይ መፈጸሙን ስመለከት በጣም አስገርሞኛል። ምክንያቱም በውይይቱ ላይ ተገኝቼ የቀረጽኩት ውይይቱን ለሕዝብ ለማቅረብ እንጂ፣ በዚህ የውይይት ፕሮግራም መቆራርጥ መነሻ እና በመልካም አስተዳደር ዕጦት ሰለባ ለመሆን አልነበረም። የሆነው ግን በእውነት አስገራሚ ነው። ከስራ ተፈናቅያለሁ። ልጆቼን ለጊዜው ለወላጆቼ ሰጥቻለሁ። ባለቤቴን ከፍዬ ነው፤ የማስተምረው። የፓርላማውን ውይይት በፈለጉት መንገድ የቆረጡት ግን ደረታቸውን ነፍተው ለእኔ የስንብት ደብዳቤ ፅፈው ሰጥተውኛል። ኮሚሽነሩም ያሉት ከላይ የዘረዘርኳቸውን ሂደቶች ነበር። ለእሳቸው አስተያየት ከእኔ በላይ ማረጋገጫ ማን ሊያቀርብ ይችላል?
እዚህ ላይ ማወቅ ያለብህ በጋዜጣችሁ ዝግጅት ክፍል ይህን እድል አግኝቼ ለመናገር ቻልኩ እንጂ ስንቶቹ የሆዳቸውን ይዘው የቢሮክራቶች ሰለባ ሆነው ቁጭ ማለታቸውን መዘንጋት የለብንም።
ሰንደቅ፡- ተጠሪነታችሁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። አሁን ደርሶብኛል የምትለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በአካል ሄደህ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ የቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያመለከትከው ነገር የለም?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- በመጀመሪያ የወሰድኩት እርምጃ እራሴን ማረጋጋት ነበር። በዚህ ጉዳይ አንተ ሶስተኛ ወገን ስለሆንክ እንጂ የተፈጠረው ሁኔታ እጅግ ድፍረት የተሞላበት ነው። መዋሸት የማልፈልገው ከስራ ተሰናብተሃል የሚለውን ውሳኔ ስሰማ ደንግጫለሁ።
ሰንደቅ፡- ለምን?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- ምክንያቱም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጠራው ስብሳባ ታማኝ ባለመሆኑ ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት ኢ.ቴ.ሬ.ድ ነው። ይህን የምለው የእኛ ተቋም አስፈፃሚ መስሪያቤት በመሆኑ ተጠሪ ለሆነበት ተቋም በሰራው ስህተት ይቅርታ መጠየቅ ይገባዋል የሚል እምነት ስለነበረኝ ነው። የሆነው ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት በአግባቡ አልተስተናገደም የሚል መከራከሪያ ባነሳሁት ግለሰብ ላይ፣ የስራ ስንብት ደብዳቤ ሲሰጥ ምን ሊሰማህ ይችላል። እንደዚህ ዓይነት ድፍረት የተሞላበት እርምጃ እንዴት ይወስዳሉ ብለህ ትገምታለህ። ስለዚህም ግራና ቀኙን ለመመልከትና የተፈጠረብኝን ጫና ለመርሳት ወደ ሆነ ቦታ ዞር ማለትን ነበር የመረጥኩት።
ሰንደቅ፡- ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ምን ትጠብቃለህ?
ጋዜጠኛ አዲሱ፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ከእኔ ስራ መፈናቀል በላይ አጀንዳ ያለው ይመስለኛል። ምክንያቱም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ ተቋም፣ በምን ምክንያት ውይይቱን ሊቆርጠው ይችላል? ውይይቱ መቆረጡንም ምክር ቤቱ ያውቃል። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ምክር ቤቱ ውይይቱ እየተቆራረጠ መቅረቡን እንደሚያውቅ እየታወቀ፣ ለምን የሃሰት መረጃ እንዳቀረብኩ ተቆጥሮ ከስራ ገበታዬ እስናበታለሁ? የፓርላማው ውይይት በትክክል አለመዘገቡን በመቃወም ምላሽ መስጠቴ ዋጋው ከስራ መሰናበት ከሆነ፣ ከእኔ የስራ ዋስትና በላይ ፓርላማው ሊመለከተው የሚገባ ጉዳይ ነው። ይህን መሰል ብልሹ የመልካም አስተዳደር ከተለመደ ተቋሙም ወዴት እየሄደ እንደሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል።¾
(ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 411 ሀምሌ 17/2005)

Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=5617

No comments:

Post a Comment