ክቡራን የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ክቡራን የደቡብ ወሎ ዞን የአንድነት ፓርቲ አመራሮች፣አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ጥሪያችንን አክብራችሁ የተገኛችሁ ክቡራን የኃይማኖት አባቶች ፣ የደሴ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ ፡-
በቅድሚያ ለዚህ ታሪካዊ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በመገኘታችሁ በፓርቲውና በራሴ ስም ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ክቡራን የዚህ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ታዳሚዎች፤ ፓርቲያችን አንድነት ገዥው የኢህአዴግ መንግስት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈፅማቸው ህገ መንግስቱን የጣሱ በርካታ ተግባራት በመኖራቸው ፓርቲያችን ከተግባሩ እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ በደብዳቤና በጋዜጣዊ መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ሁላችንም እንደምናውቀው የኢህአዴግ መራሹ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈፅመው ህገወጥ ተግባር ተጠናክሮ በመቀጠሉ በደብደቤና በጋዜጣዊ መግለጫ ብቻ መጠየቁ መፍትሄ ባለማስገኘቱ በሀገራችን ህገ መንግስት አንቀፅ 30 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት የዛሬውን ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እንድናደርግ ተገደናል፡፡
በዚህ ተቃውሞም በዋናነት ፓርቲያችን 4 አበይት ነጥቦችን በማንሳት የኢህአዴግ መንግስት ጥያቄያችንን ተቀብሎ በአስቸኳይ ስህተቶቹን እንዲያርም የምንጠይቅ ሲሆን፤ እነኚህም፡
1.የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ህገ መንግስቱን የሚጥሱና የዜጎችን ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ የአመለካከትና የኃይማኖት ነፃነትን በነፃነትና በራስ ፈቃድ ለመከተል የሚያስችለውን ተፈጥሯዊ ሰብዓዊ እና ህገ መንግስታዊ መብቶችን የሚጥሱ በርካታ አንቀፆች በመያዙ እንዲሰረዝ እና በምትኩ የሀገሪቱን ዜጎች ሁሉ በእኩልነት ሊጠብቅና ሊጠቅም የሚችል ህግ እንዲወጣ፣በዚህ ህግ ሰበብ የታሰሩ የህሊና እስረኞች በተለይም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ጋዜጠኞች እና የኃይማኖት ነፃነት መብት ጠያቂዎች በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣
2. የኑሮ ውድነቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ በመሄዱ እና ለራሳቸው፣ለቤተሰቦቻቸውና ለሀገራቸው እንዲሁም ለዓለማችን በጎ አስተዋፅዖ ያላቸው ወጣቶች ላይ በሰፊው እየታየ ያለው ስራ አጥነት የገዥው ፓርቲ ስርዓት የተሳሳተ ፖሊሲ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲታረም፣
3. ዜጎችን በሚናገሩት ቋንቋንና ዘርን ብቻ መሰረት በማድረግ የሚደረግ ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የድርጊቱ ፈፃሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ እና ከሚኖሩበት አካባቢ በግፍ ለተፈናቀሉ ዜጎችም ተገቢው ካሳ እንዲፈፀም፣
4.መንግስት በኃይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚለው ህገ መንግስት እንዲከበርና መንግስት ከኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እጁን እንዲያወጣ እንጠይቃለን፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አምብገነኑ ኢህአዴግ ዜጎችን ማፈኑን ሳያቆም አንድነት ፓርቲ የዓባይ ግድብን አይደግፍም የሚለው ፕሮፖጋንዳ ሐሰት መሆኑን እያረጋገጥኩ አባላቱ ለግድቡ ከሰጡት የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ባካበቱት እውቀትና ሙያ ማገልገል ቢፈልጉም እስካሁን ቀን ምላሽ እንዳልተገኘ በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እወዳለሁ፡፡
የአባይ ግድብ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ የሁልጊዜም የህልውና ጥያቄ በመሆኑ ዛሬም ድጋፋችንን እንቀጥላለን፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ለርካሽ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ የሚጠቀምበትን አካሄድ እንቃወማለን፡፡ከዚህ በተጨማሪ ሙስና ኢህአዴግ ከከፍተኛ አመራሩ እስከ ዝቅተኛ ካድሬው ድረስ የሚፈፀም መለያ ባህሪው በመሆኑ ይህንንም አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ በንግዱ ማኀበረሰብ ላይም የሚጣለውን ኢ-ፍትሐዊና ህገወጥ ከፍተኛ ግብርንም እንቃወማለን፡፡
ክቡራትና ክቡራን ፡- በአሁን ወቅት ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በዜጎች መካከል ገዥው መንግስት ልዩነትና አድሎዓዊነትን በመፈፀም የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም አንድነት እያናጋ በመሆኑ ይህም በአስቸኳይ እንዲቆም አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
በመጨረሻም ፡-እኛ ይህንን ህጋዊና ሰላማዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የማንንም መብት ሳንነካ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ በመደረጉ እና ጥያቄያችንንም በአደባባይ በማቅረባችን ከሚመለከተው የመንግስት አካል ተገቢውን መልስ እንደምናገኝ፤ ጥያቄያችን ከሚመለከተው አካል ተገቢውን መልስ ካላገኘ ህጋዊና ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን እንደምንቀጥል እንገልፃለን፡፡
ለፈጣሪውና ለህሊናው የሚኖሩ እንጂ ለሆዱ የሚገዛ ትውልድ ኢትዮጵያ አትሻም!!
ለዚህ ሰላማዊ ሰልፍ መሳካት አስተዋፅዖ ላበረከቱ የደሴ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች፣ የአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም የደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ አስተዳደር እና የፀጥታ ኃይሎች ላደረጋችሁልን ቀና ትብብር በደቡብ ወሎ ዞን የአንድነት ፓርቲ አባላትና አመራሮች እንዲሁም በራሴ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment