/ዜና ጎልጉል/ ኢህአዴግ ላይ ቀደም ሲል ሲቀርቡበት ከነበሩት ሪፖርቶች በተለየ ጥቅሞቹ ላይ ያነጣጠሩ አስደንጋጭ መረጃዎች እንደወጡበት ተሰማ። መረጃው የኢህአዴግን አንገት የማነቅ ያህል እንደሚቆጠርና ለተግባራዊነቱ የተንቀሳቀሱትን አካላት “የአስተዋይነት” ትግል ውጤት እንደሆነ ተጠቁሟል።
ኢህአዴግ በህዝብ ስም በብድርና በርዳታ የሚያገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለፖለቲካ ስራ እንደሚያውለውና ለአፈና ተቋማቱ ማጠናከሪያ እንደሚጠቀምበት የተከሰሰበት ሪፖርት መጠናቀቁን የገለጹት የጎልጉል ታማኝ ምንጮች ናቸው። ምንጮቹ እንዳሉት ሪፖርቱ የቀረበለት የዓለም ባንክ በቅርቡ መረጃውን ተቀብሎ ርምጃ ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል። ኢህአዴግ ርምጃው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ለማክሸፍ የተለመደውን ሩጫ መጀመሩ ተሰምቷል።
በኢህአዴግ ላይ የቀረበው ሪፖርት የመፍትሄ ሃሳብም ያካተተ እንደሆነ የተናገሩት የጎልጉል ምንጮች፣ የዓለም ባንክ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሪፖርቱን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበለውና ይፋ እንደሚያደርገው አስረድተዋል። የምርመራ ዘገባውን ስላጠናውና ስላቀረበው የኢንስፔክሽን ተቋምና የስራ ተሞክሮ በቂ ግንዛቤ ያላቸው እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት የዓለም ባንክ ቦርድ ይህ ተቋም ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ያቀረባቸውን ሪፖርቶች ላለመቀበል አንገራግሮ እንደማያውቅ ያስረዳሉ።
በሚመሩት ህዝብ ላይ ግፍ የሚፈጽሙ መንግስታትና በልማት ስም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያካሂዱ አገራት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በስፍራው በመገኘትና መረጃዎችን ከመሠረታቸው ዘልቆ በመመርመር አጥንቶ ተጠያቂ የሚያደርገው ኢንክሉሲቭ ዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል Inclusive Development International (IDI) የሚባለው ተቋም ከኢትዮጵያውያኑ ሰለባዎች ውክልና በመውሰድ ስራውን ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩን ጎልጉል ምንጮቹን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል። ተቋሙም በውክልናው መሰረት ለኢንስፔክሽን ፓናል በዝርዝር የሰለባዎቹን በደል በማተት አሳውቆ ነበር።
ኢህአዴግ በርዳታና በብድር የሚያገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለፖለቲካ ስራ፣ ለአፈና፣ ለወታደራዊ አቅም ግንባታ፣ ለተለያዩ የአፈና ተቋም ሰራተኞቹ ደሞዝና ህዝብን በመርገጥ ስርዓቱን ለሚንከባከቡ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን በመክፈል ገንዘቡን ለመጠቀም ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንደሚያውለው በበርካታ መረጃዎች ያረጋገጠው የኢንስፔክሽን ቡድን ለዚሁ ስራው ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ በቅርቡ አቅንቶ ነበር።
ምርመራው ያስደነገጠው ኢህአዴግ በተለያየ መልኩ ሰለባዎች በደላቸውን እንዳይናገሩ፣ በጥቅም የተደለሉ ሰዎችን በየቦታዎቹ በማዘጋጀትና በማስፈራራት አፈና ማካሄዱን የጎልጉል የመረጃ ምንጮች በወቅቱ ቢያስታውቁም ጎልጉል መረጃውን ለስራው መሳካት ሲባል ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
ከቀናት በፊት ሪፖርቱን አጠናቆ ለዓለም ባንክ ቦርድ ያቀረበው የኢንስፔክሽን ቡድን (ፓናል) በማያወላዳ መንገድ ተጽኖ ፈጣሪ ተቋም መሆኑንን ያስረዱት ለስራውና ለተቋሙ ቅርበት ያላቸው ክፍሎች፣ ሪፖርቱን ከቦርዱ አባላት አንዱ እንኳ አልቀበልም ቢሉ ምን ሊከሰት እንደሚችልም አብራርተዋል።
“አንድ ወይም ከአንድ በላይ የቦርድ አባላት የፓናሉን ሪፖርት ውይይት እንዲደረግበት እስካልጠየቁ ድረስ ፓናሉ ባቀረበው መሠረት እንዳለ ይጸድቃል። ከጸደቀም በኋላ ሪፖርቱ በዓለም ባንክ ስም ይፋ ይሆናል። ሪፖርቱ ታምኖበት ይፋ ከሆነ በሪፖርቱ የቀረቡት የመፍትሄ ጭብጦች ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። እስካሁን ባለው አሰራር የፓናሉ ሪፖርት ተቃውሞ አጋጥሞት አያውቅም” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
“ይህ ታላቅ ውጤት የተገኘው በእቅድና አስተውሎ በመራመድ ነው። ወደፊትም በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራቶች አሉ። የአገዛዙን ትምክህትና ማን አለብኝነት የሚያረግቡ፣ ብሎም የሚያተኑ ስራዎች ለመስራት ለተጀመረው ስራ ይህ ውጤት ከፍተኛ መነቃቃት ይሆናል” ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል እዚህ ያበቁት ክፍሎች አስረድተዋል።
ምንጭ(www.goolgule.com)
No comments:
Post a Comment