አገራችን ኢትዮጵያ ከድህነት የተላቀቀች፣ ያደገችና የበለፀገች፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ የነገሠባት አገር ሆና ለማየት የማይፈልግ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ሁሉም ዜጋ ትፈልጋለህ ወይ ቢባል አዎን ይላል፡፡ ማልልኝ ቢባልም ‹‹ሙት!›› ይላል፡፡
በተለይ ባለሥልጣናት ይፈልጋሉ ወይ? እነሱም ይምላሉ ወይ? ቢባል አዎን ይፈልጋሉ አዎን ይምላሉ ተብሎ ብቻ የሚመለስ ሳይሆን፣ በፓርላማ ሕዝብ ፊት በአደባባይ አዎን ብለው ቃል ገብተዋል፤ ምለዋል፡፡
ጥያቄው የቃልና የመሀላ ብቻ ሳይሆን የተግባር ነው፡፡ በቃልማ ሕገ መንግሥቱም ያስገድዳል፡፡ እስቲ ለፍትሕ፣ ለሰብዓዊ መብት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለልማት፣ ለአገር፣ ለሕዝብ በሀቅ፣ ከልብ፣ በእምነት፣ በትጋትና በተግባር እየሠራን ነን የምትሉ ባለሥልጣናት እጃችሁን አውጡ፡፡
በአንድ በኩል የአገር ሀብት የሚዳብርበት፣ አገር የሚለማበትና ድህነት የሚጠፋበት ሁኔታ ቢያጋጥም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጉቦ፣ የቪላና የተሽከርካሪ ጥቅማ ጥቅም የምታገኙበት ሁኔታ ቢኖርና ለመምረጥ መስቀለኛ መንገድ ቢያጋጥማችሁ የትኛውን ትመርጣላችሁ? የአገርና የሕዝብ ልማትን ወደ ጎን ገፍቶ የግል ጥቅምን ማካበት? ወይስ የግል ጥቅምን በመግፋት የአገርንና የሕዝብ ጥቅም ማስቀደም? እስቲ ከልብ የአገርና የሕዝብ ልማት የምታስቀድሙ እጃችሁን አውጡ፡፡ በተግባር ነው እያልን ያለነው፡፡
ሕዝብ ፍትሕ እያጣ መሆኑን ብታውቁና ማስረጃ ቢቀርብላችሁ፣ ሕግ የሚጣሰውና ፍትሕ እየታጣ ያለው ኔትወርክ በዘረጉ ወንጀለኞችና በባለገንዘቦች መሆኑን ብታውቁ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ብላችሁ ከሕዝብና ጎን ትቆማላችሁ? ወይስ ከአደገኞች፣ ከወንጀለኞች፣ ከባለገንዘቦችና ከባለኔትወርኮች ጋር ከምንጣላና ከምንጠቃ ብላችሁ ፍትሕና ዴሞክራሲን ትረግጣላችሁ? እስቲ እጃችሁን አውጡ፡፡
ይህንን አጀንዳ ያነሳነው በአጋጣሚ ወይም የተሻለ በማጣታችን አይደለም፡፡ አንገብጋቢ አጀንዳ ስለሆነብን ነው፡፡
ጠረጴዛው ላይ ትክክለኛ ማስረጃ ተደርድሮለት ማየት፣ ማወቅና መወሰን የማይፈልግ ባለሥልጣን እየታዘብን ነን፡፡ በሕገ መንግሥቱና በሕጎች መሠረት አገርንና ሕዝብን ከመምራት ይልቅ፣ ግለሰቦችን በመፍራትና ለእነሱ ተገዥ በመሆን የሚርበተበት ኃላፊ እየታዘብን ነን፡፡
በመገናኛ ብዙኃን ስለሚሰጥ መግለጫ አይደለም እያወራን ያለነው፡፡ ሙሰኛንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የማያወግዝ ባለሥልጣን የለም፡፡ ስለአገርና ስለሕዝብ የማይናገር ሹም የለም፡፡ ሌት ተቀን ስለመሥራት የማይናገር ኃላፊ የለም፡፡ ስለ ሕገ መንግሥት የበላይነት የማይደሰኩር አለቃ የለም፡፡
በተግባር ግን አቶ እከሌን በመፍራት፣ የእከሊትን በመስማት፣ በግል ግንኙነት በመገዛት የአገርንና የሕዝብ ጥቅምና ክብር የሚረግጥ ባለሥልጣን እየታዘብን ነው፡፡ ከበስተጀርባ የሚሠራውና በአደባባይ የሚናገረው የሚጋጭበት ባለሥልጣን አለ፡፡ በአደባባይ ሙስናን ለማጥፋት አንገቴን እሰጣለሁ ብሎ እየፎከረ በተግባር ግን ሙሰኛውን እንዳትነኩት ብሎ ከለላ የሚሰጥ ሹም አለ፡፡
ከእከሌ ጋር ከሚጣሉና ከሚቀየሙ፣ ለምን ይህን አደረግክ ተብለው ከሚጠየቁ ይልቅ ሳይወስኑ፣ ሳይፈርሙና አቋም ሳይዙ የሚሽከረከሩ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ የሕዝብ አደራ ተቀብለው፣ የሕገ መንግሥት አደራ ተሸክመው በስንትና ስንት ዜጎች መስዋዕትነት ተሸጋግረው ለሹመት የበቁ ባለሥልጣናት ሕዝብንም፣ መስዋዕትነትንም፣ ትግልንም በመርሳትና በመርገጥ ለጥቅማ ጥቅም ሲሉ አሽከርና ተላላኪ ሆነው ሲሽመደመዱም እያየን ነው፡፡ አገርንና ሕዝብን ለሽያጭና ለጥቅማ ጥቅም የሚያቀርቡ አሉ፡፡
ከመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል በደካማነታቸው የሚገለጹ አሉ ስንል ጥሩዎች፣ ሀቀኞችና የሕዝብ አገልጋዮች የሉም ማለታችን አይደለም፡፡ ለአገር ልማት፣ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ በተግባር እንቆማለን ብለው እጃቸውን ቢያወጡ የማይገርሙን አሉ፡፡ መጥፎዎች እንዳሉ ሁሉ ሀቀኞችም አሉ፡፡
ሥጋታችን ሞላጫው እየበዛ መምጣቱ ነው፡፡ ሥጋታችን ሞላጫው ድምፁ በከፍተኛ መጠን ሲሰማና ሲስተጋባ የሀቀኛው ድምፅ በሹክሹክታና በለሆሳስ መሆኑ ነው፡፡ ጠላት በአገር ላይ አደጋ የሚያደርሰው በሞላጮቹ፣ በስግበግቦቹና በሙሰኞቹ አማካይነት ነው፡፡ ለጥቅማ ጥቅም ብለው አገርን አሳልፈው የሚሸጡ እነሱ ናቸውና፡፡
መንግሥት ራሱን ያፅዳ እንላለን፡፡ መንግሥት ራሱን በማፅዳት ያጠናክር እንላለን፡፡ መንግሥት የራሱን ጋንግሪን ቆራርጦ ይጣል እንላለን፡፡ መንግሥት ከሚቦረቡር ካንሰር በሽታ ራሱን ይከላከል ይጠብቅ እንላለን፡፡
መንግሥት ሀቀኛ፣ ኩሩና ታማኝ ባለሥልጣናት ሊኖሩት ይገባል፡፡ ከመጀመሪያውም ንፁኃንና ሀቀኞችን ይሹም፡፡ ከሾመ በኋላም መዝቀጥና መንሸራተት እንዳይኖር ይከታተል፡፡ ከታየም የሚታከመውን ያክም፡፡ ታክሞ የማይድነውን ቆርጦ ይጣል እንላለን፡፡
በሀቀኛ ባለሥልጣናት የምንኮራውን ያህል በደካማ፣ በሙሰኛ፣ በተላላኪ ባለሥልጣናት ተግባር እያፈርን፣ እየሰጋና እየተሸማቀቅን እንገኛለን፡፡ አገርንና ሕዝብን ለአደጋ የሚዳርጉ ናቸውና፡፡
ስለዚህ መንግሥት ሆይ! ባለሥልጣናት ሆይ! አገርንና ሕዝብን ከአደጋ ለመጠበቅ በድፍረት ውስጣችሁን ገምግሙ፣ አፅዱ፣ ተጠናከሩ፡፡ ደካሞችና አስመሳዮች ይወገዱ፡፡ ሀቀኞችና የሕዝብ አገልጋዮች በኩራት አዎን ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለልማት፣ ለአገር፣ ለሕዝብ፣ በሀቅ፣ ከልብ፣ በእምነት፣ በትጋትና በተግባር እየሠራን ነን ብላችሁ እጃችሁን አውጡ፡፡
ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ