ኅዳር 27፣ 2007 (ዲሴምበር 06፣ 2014)
በሀገራችን ውስጥ በአሁኑ ወቅት ምን እየተካሄደ ነው? ብለን ስናጤን በአንድ በኩል ነፃነት የጠማው ሕዝብ የትግል ኃያልነትና በሌላ በኩል ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያና
ሕዝቧ በምን ዓይነት ጨካኝና ዘረኛ ሥርዓት ሥር ወድቀው እንደሚገኙ የሚያሳይ ጉልህ ክስተትን እንገነዘባለን።
ምርጫ 97ትን ተከትሎ ህወሓት/ኢህአዴግ በደረሰበት ሽንፈት ተደናግጦ በጥቅምት ወር እጅግ አሳዛኝ ጭፍጨፋ፣ እሥራትና ሽብር በሕዝባችን ላይ ፈጸመ። የሕዝብ
ድምፅ መቆጠር ሲጀምር ገና ከጅምሩ ተቃዋሚዎች እንዳሸነፉ የተገነዘበው መለስ ዜናዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ኮሮጆ ግልበጣውን ተያያዘው። በዚህም የድምፅ
ስርቆት ከሕዝብ ድምፅ ገልብጦ በተቃራኒው ኢህአዴግ አሸናፊ ነኝ ብሎ አወጀ።
ይህን ዓይን ያወጣ ስርቆት ሕዝብ እሽኝ ብሎ እንደማይቀበለው የተረዳው ህወሓት/ኢህአዴግ በመሪው በመለስ ዜናዊ አማካኝነት ባወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
“የፀጥታ ኃይሎች ጥብቅ እርምጃ እንዲወስዱ መመሪያ ተሰጥቷል” በማለት የፀጥታ ኃይሎች የግፍ በትራቸውን ያለምንም ርህራሄ በሕዝብ ላይ እንዲያሳርፉ ግልጽ
መመሪያ ሰጠ። የተሰረቀ ድምፃቸውን ለማስከበር፣ በድምፃቸው የመረጧቸው ድርጅቶች ሀገሪቱን የማስተዳደር መብታቸው እንዲከበር ለማሳሰብ “ድምፃችን ይከበር“
በማለት አደባባይ የወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እጅግ ዘግናኝ በሆነ መልክ ልዩ ሥልጠና በተሰጣቸው የፀጥታ ኃይሎች በተኩስ እሩምታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉ
በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆሰሉ። እስከ መቶ ሺህ የሚቆጠሩት ደግሞ ከየመንገዱ፣ ከመኖሪያና ከሥራ ቦታቸው ታፍሰው በየእሥር ቤቶች ተወረወሩ፤ በድብደባ
ተሰቃዩ። የዚህ ጭካኔ የተሞላበት አሳዛኝ የኃይል እርምጃ ሰለባ ከሆኑትና በጥይት ግንባር ግንባራቸውን ተመትተው ከተገደሉት ውስጥ የ16 ዓመት ወጣት
የነበረችውን ሽብሬ ደሳለኝን፣ እንዲሁም የ14 ዓመት ሕፃኑን ነቢዩ ዓለማየሁን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። ይህን የግፍ ጭፍጨፋም ተከትሎ ህወሓት/ኢህአዴግ
የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተለይም የቅንጅትን መሪዎች ሙሉ በሙሉ ሰብስቦ ወደ እሥር ወረወራቸው።
በምርጫ 97 ህወሓት/ኢህአዴግ በሕዝባችን ላይ ያካሄደውን ግፍ ስናስብ በዚያኑ ጊዜ ደግሞ የሕዝቡን ትግል አስተባብረው፣ በምርጫ እንዲሳተፍና ከማንም የባዕድ
ኃይል ነፃ ሆኖ የወደፊት ዕጣውን ራሱ እንዲወስን ያደራጁትንና ያስተባበሩትን የፖለቲካ ድርጅቶችና ስብስቦች በተለይም ቅንጅትንና ኅብረትን ማስታወስ ይገባል።
ሁለቱም ስብሰቦች በጊዜው በተገኘው ጠባብ ቀዳዳ በመጠቀም፣ ኃይላቸውን፣ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን በማስተባበር፣ ከማንም ባዕድ ተጽዕኖ ነፃ ሆነው፣
በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ በመተማመን ሕዝባችን የራሱን ጥቅም እዲያስጠብቅ፣ ለራሱ መብት እንዲቆም ከፍተኛ ሥራ በመስራት ምሳሌነት ያለው ተግባር
አከናውነዋል።
ይህ ከ1997 ምርጫ ጋር የተያያዘ የሕዝብ እንቅስቃሴና የፖለቲካ ፓርቲዎች የማስተባበር ተግባር ከሚያሰተምረን እጅግ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የኅብረት ትግል፣
ለተቃዋሚዎች ድርጅታዊ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ መነሳሳት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ነው። 1997 ከተጠናቀቀ ከአሥር ዓመት በኋላ ዛሬ በሌላ ምርጫ
ዋዜማ ላይ እንገኛለን። እንደ 1997 ሁሉ ይህን ሁኔታም ለሕዝብ ነፃነት ትግል መጠቀም ከተቃዋሚዎች የሚጠበቅ ነው። ምንም እንኳ ህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ
ምህዳሩን ከምን ጊዜውም በላይ አጥብቦ ሁሉንም የፖለቲካ መብቶች አፍኖ ፍጹም አምባገነን መሆኑን ያረጋገጠበት ጊዜ ቢሆንም፣ አሁንም ይህን ወቅት ለሕዝብ
ትግል ማጠናከሪያ፣ ለማንቃትና ትግሉም አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲሄድ ለማድረግ ልንጠቀምበት ይገባል።
የህን ለማድረግ ደግሞ የተቃዋሚ ድርጅቶች ቢቻል በሙሉ ኅብረት ባይቻል ግን ሊያግባቡዋቸው በሚችሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሕዝብን ተስፋ
ሊያበረታታ፣ ስሜቱንም ይበልጥ በጠነከረ ሁኔታ ሊያዳብር የሚችል የተቀናጀ እንቅስቃሴ ሳይውል ሳያድር መጀመርን ይጠይቃል። በመሆኑም ባለፈው ወር በሃገር
ውስጥ የሚገኙ 9 የተላያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግና ስምምነት ላይ በመድረስ በጋራ ለመታገል
መወሰናቸውና በተለይም ያለነጻነት ነጻ ምርጫ ሊኖር አይችልም የሚል መርሃ ግብር በማውጣት የጀመሩት የትግል አንቅስቃሴ ወቅታዊ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ
እንደግፈዋለን። በተጨማሪም በአንድነት ፓርቲ በኩል የሚካሄደውን የሚሊዮኖች ድምፅ እንቅስቃሴና መድረክም የሚያደርገውን የትግል እንቅስቃሴ እንደግፋለን።
የዚህ መርሃ ግብር አካል በሆነው በዛሬው እለት በተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተሳታፊ በሆኑ ሰላማዊ ህዝብና የፖለቲካ መሪዎች ላይ የተደረገውን ጭካኔ የተሞላበት
እንግልት፤ ድብደባ አፈናና እስር በጽኑ ስናወግዝ፤ ፍራቻን በመስበርና እምቢኝ ለነጻነቴ በማለት በሰልፉ ላይ ለተሳተፉ ጀግኖቻችን ያለንን አክብሮትና አድናቆት በዚህ
አጋጣሚ መግለጽ እንወዳለን።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምሥራች ለህወሓት/ኢህአዴግም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች የሚፈሩት ከነሱ ተጽእኖ ነፃ የሆነ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ኅብረት ወይም
ትብብርን ነው። በሀገራችን ውስጥ የሰፈነውን ዘረኛና ጨካኝ የአገዛዝ ሥርዓት በማስወገድና በሁሉ አቀፍ የሽግግር መንግስት በመተካት ዘላቂ ዴሞክራሲ የሰፈነበት፣
የሕግ የበላይነት የተጠበቀበትና አንድነቷ የታፈረበትና የተከበረባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችለው አንዱ አውራ ሌላው ተከታይ፤ አንዱ የበላይ ሌላው
የበታች፤ አንዱ ትልቅ ሌላው ትንሽ፤ አንዱ ነባር ሌላው አዲስ...ወዘተ የማይባልበት ከላይ የተዘረዘሩትን መሰረት ያደረገ በኢትዮጵያ ህዝብና በአለም አቀፉ ህብረተሰብ
ተቀባይነት ያለው የአማራጭ ሃይል በማውጣት ትግሉንም ሆነ ድሉን የጋራ ማድረግ ወቅታዊ ነው።
ይህን እውነታ በመገንዘብ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት (ENTC) ከላይ የተዘረዘሩትን ጭብጦች
ለመተግበርና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ የጋራ እንቅስቃሴዎችን ያካሂዳሉ። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኘው ነጻነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊና
የዲሞክራሲ ሃይሎች ሁሉ የዚህ እንቅስቃሴ አካል እንዲሆኑና በሀገር ቤት የሚካሄደውን ትግል በሁሉም መልኩ እንዲያግዙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የተባበረ የሕዝብ ትግል ምንጊዜም አሸናፊ ነው!
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት (ENTC)
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
ምንጭ ዘ-ሐበሻ
No comments:
Post a Comment