ህወሃቶች ኢትዮጵያን “ለመምራት” ያላቸው አቅም ተሟጦ አልቋል። ፍርሃት አቅላቸውን አስቷቸዋል። ፍርሃታቸው ጭካኔን ወልዷል። ይህ ጭካኔያቸው ወሰን አጥቷል። ልጥ ባዩ ግዜ እባብ እየመሰላቸው ልጡን በቆመጥ ሲደበድቡ ውለው ያድራሉ። ፍርሃት ያ ደካማ ማሰቢያቸውን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶታል። የፈሪ ዓይን ማየት እንደማይችል፤ ጆሮውም መስማት እንደተሳነው ከህወሃቶች ተርድተናል።
እኛ ግን እንዲህ እንላለን ህወሃቶች ዓይናችው እያየ፤ ጆሮዋቸውም እየሰማ የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነቱን ይቀዳጃል። እውነት እውነት እንላችኋለን የነፃነቱ ግዜ እሩቅ አይደለም። ህወሃቶች ከነፍርሃታቸው ወደ መረጡት መቃብራቸው መውረዳቸው እንደማይቀር ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የለንም።
የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ ነፃነት ነው።ይህን ነፃነት ከህወሃቶች እጅ ለምነን የምናገኘው አይደለም። ነፃነታችንን ታግለንና አሸነፈን የምንቀዳጀው ንፁህ ሃብታችን ነው። ይህን ንፁህ ሃብታችንን በቀማኞች አስነጥቀን ዝም ብንል እርግማን ይሁንብን ያሉ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉ ያሉት ትግል ተስፋ ሰጪ ነው። በተለይም ወጣቶች እምቢ ለክብሬ፤ እምቢ ለነፃነቴ እምቢ ለማያውቁን ህወሃቶች ማለታቸውን ስናይ ተስፋችን ከመቸውም ግዜ በላይ ለምልሟል።
ህወሃቶች ኃላፊነት የሚሰማቸው ቢሆኑ ኑሮ “በሃሳባችሁ ባንስማም ልዩነታችሁን መግለፅ የምትችሉበትን መብት ለማስከበር እሰከ ሞት ድረስ እንቆማለን” ይሉ ነበር። አለመታደል ሁኖ ህወሃቶች አገር፤ ህዝብ፤ ወገን የሚባል ቋንቋ በውስጣቸው የለም። ኢትዮጵያም አገራቸው አትመስላቸውም፤ ህዝቡም ወገናቸው እንደሆነ አይሰማቸውም። ህወሃቶች በወንድምና እህቶቻቸው አጥንት ላይ ቁመው ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ጠላት መሆንን መርጠዋል። ለነፃነት ብለው በትግል ሜዳ የተሰው ጓዶቻቸውን ሞትም ከንቱ ሞት አድርገው አስቀርተውታል። ይሄ እርግማን ነው።ይሄ እርግማን ደግሞ አሁን ባሉት ህወሃቶች ብቻ የሚቆም ሳይሆን ወደ ልጅ ልጆቻቸው እንደሚሸጋገር ህወሃቶች ለማሰብ አቅቷቸዋል።
ህወሃት የስለጠነ ፖለቲካ አያውቅም። የነፃነትንም ትርጉም ሳያውቅ ነፃ አውጪ ነኝ ይላል። በአገሪቷ ጫንቃ ላይ መቆየት ብቻ የህልውናየ መሠረት ነው ብሎ ካመነም ቆይቷል። ይህን የህልውናየን መሠረት የሚነካ ሁኔታ ከተፈጠረም ጠመንጃየ መመኪያ ጉልበቴ ነው የሚል የማይናወፅ አቋምም ይዟል። ይህ አቋሙ አገሪቷ ከተጋረጡባት አደጋዎች መካከል አንዱ ሁኖ ይታየናል። የዚህ አቋም መዘዙ አሁን ባለው ትውልድ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ወደ ቀጣዩ ትውልድ ተሸጋግሮ የአገሪቷ ዜጎች በሠላም አብረው የሚኖሩበትን እድል እንደሚያበላሸው ህወሃቶች አያውቁም ማለት አይቻልም። ተደጋግሞ እንደተነገረው በህወሃቶች ዘንድ ትውልድ የሚባል ቋንቋ እንዲጠፋ በመደረጉ ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ቂም ትተው ለማለፍ ሳያቅማሙ እየሰሩ ይገኛሉ።
የኢኮኖሚ መዋቅሩ በእነርሱ ብቻ መያዙ ነገ ለእነርሱ ልጆች የደም እንጀራን እንደሚያተርፍላቸው እንዲገነዘቡ ማድረግ ተገቢ ይመስለናል።በህወሃቶች አስተሳሰብ ሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ድሃ አድርገን ከያዝነው ከዕለት ጉርሱ አልፎ ሂዶ ነፃነትን ይጠይቀናል ለነፃነት የሚከፍለውንም ዋጋ ለመክፈል አቅም አይኖረውም የሚል ሙት ፍልስፍና መመሪያቸው ሁኗል። እኛ ብቻ በኢኮኖሚ ጎልበትን ሌሎቹን የእኛ ጥገኛ ካደረግን ለዘላለም ከነ ልጅ ልጆቻችን ነግሰን እንኖራለን የሚል ቅዥት ውስጥ ሁነው አገሪቷን ወደ ትርምስ እየወሰዷት እንደሆነ እያየነው ነው።ህወሃቶች ከእህል ውሃ የዘለለ ራዕይ እንደሌላቸው የሚታወቅ ነው። ራዕይ አልባዎች ተደራጅተው አገር መምራት ሲጀምሩ አገሪቷና ህዝቧ በሙሉ ራዕይ አልባ ይሆናሉ። መፅሃፍ እንደሚነግረን ደግሞ “ራዕይ አልባ አገር ይጠፋል” ይላል። የህወሃቶች ምኞት ይሄው ነው። እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ አትኖርም የሚል ክፉ ምኞት።
ኢትዮጵያዊያን ሆይ !
ህወሃት የጭለማን መንገድ መርጧል። ይሄ መንገዱም አገሪቷንና ህዝቧን ወደ መቀመቅ እየጨመራት ነው። አገሪቷን አስይዞ ከግል ኩባንያዎች ብድር እስከ መለመን ደርሷል። ቀጣዩ ትውልድ ከሚወርሰው ቂምና በቀል በተጨማሪ በእዳ የተያዘ ትውልድ ይሆናል። በቀላል አነጋገር ትውልዱ የባዕድ ተገዢ እንዲሆን ተፈርዶበታል። ህወሃቶች ለመጪው ትውልድ የሚሰጡት ስጦታ ባርነትን እንዲሁም ቂምና በቀልን እንጂ ነፃነትንና አብሮ መኖርን አይደለም።
እንግዲህ ህወሃቶችን አደብ ማስያዝ የዚህ ትውልዱ ግዴታ ይሆናል። ህወሃት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት ካልተወገደ በቀር በኢትዮጵያ መረጋጋት አይኖርም። ችጋርም አይጠፋም። የንፁህ ሰው ደም ከመፍሰስ አይቆምም። አገሪቷም በእዳ ላይ እዳ ከመጨመር አትመለስም።
ይህ ሁኔታ መቆም እንደሚኖርበት አሁን ሁሉም ተገንዝቧል። ይህ ሁኔታ ግን እንዲሁ በከንቱ የሚቆም አይሆንም። ለዚህ የሚከፈል የደም መሥዋዕትነት የግድ ሁኖብናል። ፍትህ፤ እኩልነት እና ነፃነት የደም ውጤቶች ናቸው። ያለ መሠዋዕትነት የሚመሠረት ፍትህ አይኖርም፤እኩልነትም ቢሆን የብዙዎችን መስዋዕትነት ይጠይቃል፤ የነፃነት ቀንዲል የሚለኮሰው በደም አቀጣጣይነት ነው። ህወሃቶች መሽቶ በነጋ ቁጥር የንፁህ ደም ያፈሳሉ። ዝም ያሉትም ሞት አልቀረላቸውም፤ የተናገሩትም የውርደት የሞት ፅዋቸውን እየተጎነጩ ነው፤ ሌሎቹም ከሞት በባሰ ሁኔታ በየማጎሪያ ቤቱ የመከራ ፅዋቸውን እየተጋቱ ነው። ይሄ የውርደት ታሪክ መቀየር ይኖርበታል።
የሠማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ጥበቃ ሠራተኛ የ72 ዓመቱ አቶ ቀኖ አባጆቢርን ለእስር የዳረገ አገዛዝ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው።የ72 ዓመት ኢትዮጵያዊ ሽማግሌን አንኳ የሚፈራ ቡድን ነው አገሪቷን የተቆጣጠራት። አቶ ቀኖ የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ደመወዝ ተቆርጦላቸው የጥበቃ ሥራ የሚሰሩ እንጂ የፓሪት አባል አልነበሩም ሆኖም ግን ታፍነው ለእስር ተዳርገዋል። የህወሃቶች ግፍ ማብቂያ እና ወሰን አጥቷል።እነዚህ ቡድኖች እየፈፀሙ ያሉት ግፍ ጥላቻን እየወለደ፤ ቂምን እየተከለ ቀጥሏል። የህዝቡ ቂም እንደ ተዳፈነ እሳት የሚቀጣጠልበትን ግዜ እየጠበቀ ነው።ይህ ግዜ የመጣ ቀን ህወሃቶች እና አሸከሮቻቸው ወየውላቸው።ያ ግዜ ደግሞ ያለ ጥርጥር በእርግጠኝነት ይመጣል።ፈጥኖ እንዲመጣ በእኛ በኩል የሚቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው።
ከህወቶች በተጨማሪ በዚያች አገር ታሪክ ውስጥ ፌዴራል ፖሊስ ተብለው የተደራጁት እና ከሰው መፈጠራቸውን የረሱ ቡድኖች መኖር በብርቱ ያሳስበናል። የፌዴራል ፖሊስ አባላት እየፈፀሙ ያሉት ጭካኔ አስገራሚ ነው። የዝህ ጦር አባላት ሰው ሁነው መፈጠራቸውን እስክንጠራጠር ድረስ አስገርመውናል። እንግዲህ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ብዙ ግዜ ማሳሰቢያ ልከንላችኋል። አሁንም በተጨማሪ እንነግራችኋለን። ነገራችንንም ለታሪክ ይቆይ ዘንድ በመዝገብ እናኖረዋለን። አሁን የጭካኔ ሰይፋቸሁን መዛችሁ እንደ ፈለጋችሁ የምትገሏቸው ዜጎች ወገኖቻችሁ መሆናችሁን አትርሱ። ነገ ቢርባችሁ የሚያበሏችሁ፤ ብትወድቁ የሚያንሷችሁ፤ ብትጠሙ የሚያጠጧችሁ ዛሬ በያዛችሁት ጠመንጃ የምትገድሏችው ወገኖች ናቸው። እናንተ ግን ይሄን እውነት ለማየት አዚም የተደረገባችሁ ይመስላል።
ፌዴራል ፖሊሶች ታዝዤ ገደልኩ በማለት የምታመልጡ እንዳይመስላችሁ። ታዝዤ ገደልኩ ማለት ሥራየ መግደል ነው ማለት ነው። ሥራው መግደል የሆነ ማንም ይሁን ማን ወንጀለኛ ነው። ወንጀለኛ ደግሞ ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት መቀጣቱ አይቀርም። ስለሆነም የፌዴራል ፖሊስ አባላት በሰላማዊ መንገድ ኑሮ ተወወደብኝ የሚለውን ወንድማችሁን በቆመጥ ደብድቡ ስትባሉ አይ ሠላማዊ ሰውን እጠበቅ ዘንድ እንጂ እደበድብ ዘንድ ህግ አይፈቅድልኝም ማለት ስትችሉ ያገኛችሁትን ሁሉ እየሰበራችሁ መኖራችሁን እያየነው ነው። ይሄ በምንም መሥፈርት ትክክል አይደለም። አንዱ ታዝዤ ወንድምህን ወይም ልጅህን ወይም ደግሞ አባትህን ገደልኩ ቢልህ ምንድ ነው የሚሰማህ? መቸስ ታዘህ ነው እንግዲህ ምን ይደረጋል እንደማትል እርግጠኞች ነን። እኛ ሁላችን አንተ የፌዴራል ፖሊስ አባል በምትፈፅመው ጭካኔ በእጅጉ ተጎድተናል።የያዘከው ጠመንጃ የሸንበቆ ምርኩዝ የሚሆንበት ግዜ ወደ አንተ ፈጥኖ እየመጣ ነው። አሁን የያዝከው ቆመጥ ተሰብሮ ይወጋሃል በተወጋህ ግዜ ግን ዞር መግቢያ እንዳታጣ ለራስህ ተጠንቀቅ። አዛዦችህ እንደሆነ የአገሪቷን ንብረት ዘርፈው ወደ ውጭ አገር አሽሽተዋል፤ የቀረውንም በዘመድ አዝማዶቻቸው ሥም ብዙ ህንፃዎችን አሰርተው እየተዘባነኑበት ነው። አንተ ግን ከቀሪው ወገንህ ጋር ደም ትቃባለህ። ነገ ሌላ የተለየ አዲስ ቀን ነው። አዲስ ቀን በሆነ ግዜ መግቢያ እንዳታጣ አሁኑኑ ራስህን ከዘረኞች፤ ከዘራፊዎችና ከግፈኞች ጎን አግልለህ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንድትሰለፍ ደግመን ደጋግመን እንመክርሃለን። ይሄን ምክር አልስማ ካልክ ግን የሚመክርህ መከራ በደጅህ ፈጥኖ ይመጣል።
በመጨረሻም ህወሃቶችን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ተፈፍሞ መቀጠል የኖርበታል። ሁሉም በሚችለውና በሚያምነበት መንገድ ሳያቅማማ ይታገል። በሁሉም መንገድ የሚደረገው ትግል ፍሬ አፍርቶ በነፃነት እንደሚቋጭ ባለ ሙሉ ተስፋ ነን። እኛ የጀመርነውን ሁለ-ገብ ትግል አጠናክረን ተያይዘነዋል። ዕለት ዕለት እየጎለበትን እየሄድን ነው። አደረጃጀታችንም መሠረት ይዟል። ካሁን ወዲያ ትግላችንን የሚያቆም ምድራዊ ኃይል የለም። ነፃነታችንን ሳንቀዳጀ የጀመርነውን ትግል አናቆምም።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
Source www.ginbot7.org
No comments:
Post a Comment