Monday, December 15, 2014

አየር መንገድ የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራርን ከስራ አባረረ


• ‹‹በፖለቲካ አመለካከቴ ምክንያት ሁልጊዜም እኔን ማባረር ይፈልጋሉ›› አቶ ወሮታው ዋሴ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰማያዊ ፓርቲ የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑትን አቶ ወሮታው ዋሴን ከስራ አባረረ፡፡ አቶ ወሮታው ከስራ የተባረሩት ጥፋት ያጠፋን ሰራተኛ አልቀጣህም በሚል ሲሆን በእሳቸው ስር የነበረውና አጠፋ የተባለው ሰራተኛ ጉዳይ ተመርምሮ ወደ ስራ መመለሱ ታውቋል፡፡
አቶ ወሮታው ከእሳቸውም በላይ ጉዳዩ የሚያገባው የማኔጅመንት አባል በተመሳሳይ ጉዳይ የአምስት ቀን ደመወዝ ብቻ ሲቀጣ እሳቸው ከስራ መባረራቸው በፖለቲካ አመለካከታቸው ላይ የተመሰረተና ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል፡፡ ከስራቸው ይሰራ የነበረው ሰራተኛ ጥፋተኛ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ወሮታው ‹‹በፖለቲካ አመለካከቴ ምክንያት ሁልጊዜም እኔን ማባረር ይፈልጋሉ›› ሲሉ የተባረሩት በፖለቲካ አመለካከታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ወሮታው ዋሴ ከሁለት አመት በፊት በኢሜል ለህዳሴው ግድብ ገንዘብ እንዲያዋጡ በተጠየቁበት ወቅት ለተላከው የኢሜል መልዕክት አልከፍልም ብለው በመመለሳቸው ‹‹ሰራተኛ በማሳመጽ፣ የኢንዱስትሪ ሰላም በማናጋት›› በሚል ተከሰው ተባርረው ከሁለት አመት በኋላ በፍርድ ቤት ወደ ስራ መመለሳቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ አየር መንገድ አቶ ወሮታው ዋሴ ካሳ ተከፍሏቸው እንዲለቁ ይግባኝ ጠይቆ የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለሁለት አመት ካራዘመ በኋላ ወደ ስራ እንዲመለሱ አዝዞ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ጥፋተኛ ነው ብሎ ያባረራቸው አየር መንገድ ወደ ስራ በተመለሱ በ15 ቀናት ውስጥ ሰርተውበት ወደማያውቁት ክፍል በማዘዋወር እድገት አግኝተው የማኔጅመንት አባል እንደሆኑ እንደገለጸላቸው የሚናገሩት አቶ ወሮታው እድገቱ ሰራተኛ ሲባረር የመክሰስ መብት ስላለው፣ በተቃራኒው ግን ሳይፈልጉት በእድገት የማኔጅመንት አባል እንዲሆኑ የተደረገው የማኔጅመንት አባል የሆነ ግለሰብ ቢባረርም የመክሰስ መብት የሌለው በመሆኑ ሆን ተብሎ ለማባረር የተደረገ ስልት ነው ብለዋል፡፡ አቶ ወሮታው በወቅቱ ይህን እድገት አልቀበልም ብለው እንደነበርም ገልጸውልናል፡፡
አቶ ወሮታው ዋሴ አሁን ከስራ ባባረራቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለ14 ዓመታት ያህል ማገልገላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
source Negere Ethiopia

No comments:

Post a Comment