Wednesday, December 10, 2014

የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ውሳኔዎችን አስተላለፈ

• ‹‹አገዛዙ የወሰደውና ወደፊት የሚወስደው ከእስካሁኑ የባሰ አረመኔነት እርምጃ ይበልጡን ያጠናክረናል››
የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ትናንት ህዳር 30/2007 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ትግሉን ያጠናክራሉ ያላቸውን ውሳኔዎችን አስተላለፈ፡፡ ብሄራዊ ምክር ቤቱ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ‹‹ህወሓት/ኢህአዴግ በፈፀመው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ እና እስር ምክንያት ክፍተት ሳይፈጠር የፓርቲው እንቅስቃሴ እንዲቀጥልና ትግሉም እንዲጠናከር የሚያስችሉ ናቸው›› ሲሉ የብሄራዊ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰይድ ኢብራሊም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ብሄራዊ ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ህወሓት/ኢህአዴግ በአመራሩ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ ላይ የፈጸመው ጭካኔ ለሰላማዊ ታጋዮች ባለው ጥልቅ ጥላቻና ጭካኔ በተሞላበት እርምጃው ከትግሉ ያፈገፍጋሉ ከሚል ስሌት እንደሆነ በመግለጽ ‹‹አገዛዙ የወሰደውና ወደፊትም ሊወስደው የሚችለው ከእስካሁኑ የባሰም አረመኔነት የተሞላበት እርምጃ ይበልጡን ያጠናክረናል እንጅ ከትግላችን ቅንጣት ያህል ወደኋላ እንደማናፈገፍግ›› ብሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በአንድ በኩል ‹‹ምንም ችግር ሳይፈጥሩ በቁጥጥር አዋልናቸው›› ያላቸውን ሰላማዊ ታጋዮች በሌላ በኩል ፍርድ ቤት አቅርቦ ‹‹መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት አውደመዋል›› ሲል መክሰሱም በገዥው ፓርቲ የሚዘወሩ ተቋማት በጉዳዪ ላይ አንድ አይነት አቋም እንደሌላቸውና ይህም የተጀመረው ሰላማዊ ትግል ስርዓቱን መያዣ መጨበጫ እንዳሳጣው ያሳያል ብሏል፡፡
ከህወሓት/ኢህአዴግ ከዚህ የባሰ ጭካኔን እንጠብቃለን ያለው ምክር ቤቱ ‹‹በምናደርገው ትግል ሁሉ የሚጠበቅብንን መስዋእትነት ለመክፈልና ሀገራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችን እየገለጽን መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀንለትና የምናከብረው ህዝብ ከጎናችን እንዲቆም›› ሲል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ምክር ቤቱ እሁድ ታህሳስ 5/2007 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባ የጠራ ሲሆን የተላለፉት ውሳኔዎች በምን መልኩ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተወያይቶ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
source Negere Ethiopia 


No comments:

Post a Comment