Tuesday october 21,2014
ተሻለ መንግሥቱ (ከአዲስ አበባ)
ኢትዮጵያ እጅግ ድሃና ኋላ ቀር ከሚባሉ የዓለም ሀገሮች ተርታ የምትሰለፍ መሆንዋን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ያረዳሉ – እኛም በዘግናኙ ኑሯችን ይህንኑ መራራ እውነት እያረጋገጥነው እንገኛለን፡፡ በሰብኣዊ መብት አያያዝ፣ በኢኮኖሚ፣ በሥልጣኔና በመሳሰሉ የሀገርና የሕዝብ ጤናማ ዕድገት መለኪያዎች ከሁሉም ሀገሮች ግርጌ ሆኖ መገኘት ለገዢዎቻችን ምን ያህል የደስታ ስሜት እንደሚፈጥርላቸው ማወቅ ባንችልም እኛ ዜጎቿ ግን በየምንሄድባቸው ሀገራት ሁሉ በዚህ የ“ፊተኞች ኋለኞች ይሆናሉ” እውናዊ ክስተት በግልጽ የሚንጸባረቅበት ውራነታችን እያፈርንና እየተሳቀቅን በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ ሆኖ መፈጠር የሚያሸክመው ቀምበር ምን ያህል ከባድ እንደሆነም ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተረዳን መጥተናል፡፡ በልማድ “ሳታጣ ያጣች” እያልን የምናንቆለጳጵሳት ሀገራችን በወያኔ ትግሬ የራሷ መዥገሮች ተወርራ ላሚቷ በመክሳቷ ለጥቂቶች ታልባ የማትነጥፍ ጥገት ስትሆን ለሚሊዮኖች ግን ድርቅ መትቷት ይሄውና ብዙዎቻችን የምንልሰውንና የምንቀምሰውን እያጣን በርሀብ አለንጋ እየተገረፍን እንገኛለን፡፡ ብልጭልጩ የአስፋልት መንገድና እዚያና እዚህ ሕይወት አልባ ሆነው የተገተሩት የሙሰኛ ዜጎች ቤቶችና ሕንፃዎች እንዲሁም ኢንዱስትሪና ፋብሪካዎች በሚሰጡን የተንሻፈፈ ምስል ሕዝቡ እንዳለፈለት በተለይ በገዢው የትግሬ ዘረኛ መንግሥት ሚዲያዎች ነጋ ጠባ ቢለፈፍም እውነቱ ግን በእጅጉ ተቃራኒና ለመግለጽም አስቸጋሪ ሆኗል፤ ብናነገር የማንታመን መሆናችን በራሱ የሚያስከትለው ጭንቀት ደግሞ ከበደሎች ሁሉ የከፋ በደል ሆኖብናል፡፡ የፍትህ ዕጦት የሚያሰቃየውን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደተምበሸበሸ፣ የራበውን በልቶ እንደጠገበ፣ የተጠማውን ጠጥቶ እንደረካ፣ የታረዘውን ሡፍና ሀር ለብሶ እንዳማረበትና እንደሞቀው … ተደርጎ እንዲታይ በተለይ በዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የውሸት ምስል ለመፍጠር የሚጥር መንግሥታዊ የፕሮፓጋንዳ ማሽን በመኖሩ የምሥኪኖች ዋይታና ልቅሶ እስካሁን ሰሚ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ሰውና እግዜር ተባብረው የጨከኑባት ሀገር – ኢትዮጵያ!
ድህነታችን አጥንትን ዘልቆ የገባና ሀገሪቱንና ሕዝቧን ጥልቅ ገደል ውስጥ የከተተ ሆኖ ሳለ የመንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠሩት ወያኔዎች እየዘረፉት ያለው የሀገሪቱ ውሱን ሀብት እንዲህ በቀላሉ ሊገለጽ የማይችል መሆኑን አንድ አብነት ጠቅሰን በዚች ጽሑፍ ውስጥ ወረድ ብለን እንመለከታለን፡፡ እንዲህ የምናደርገው ለታሪክ መዝገብ ፍጆታ እንዲሆን እንጂ በአሁኑ ወቅት አድማጭ ተገኝቶ መፍትሔ ይኖራል ብለን እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል – ያን ያህል ሞኝነት በአሁኑ ወቅት የለም፡፡ እንናገራለን – ሰሚ ቢጠፋ የኢትዮጵያ ዐፈርና ዛፍ ቅጠል ሰምቶ በታሪካዊ መዝገብነት ቀረፆ ያኖረዋል፤ መጪው ትውልድም ይፋረዳል፤ ይማርበታልም፡፡ እንጂ አፄ ቴዎድሮስ ካህናት አናደውት ሲገስጽ “አንድሽ አንባቢ አንድሽ ተርጓሚ” እንዳለው እነዚህ በሙስና የበከቱ ወያኔዎች አንዳቸው ሌላኛቸውን አደብ ለማስገዛትና ሥርዓት ለማስያዝ የሚያስችል የሞራል ብቃት አላቸው ተብሎ አይታሰብምና ከነሱ ምንም አንጠብቅም – በዚያ ላይ “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ” ወይም “የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ” እንዲሉ በመሆናቸውና ለሀገርም ሆነ ለወገን የሚቆረቆር አንዳችም ስሜት የሌላቸው ግዑዝ ፍጡሮች በመሆናቸው ከነሱ አንዲት ቅንጣት በጎ ነገር መጠበቅ በሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ራስን ማቂያቂያል ይመስለኛል፡፡ በሙስና ስም ሲካሰሱና ሲተሳሰሩ የምናያቸው ለሽፋን እንጂ እውነተኛ ምክንያቱ የሥልጣን ሽኩቻ ወይም ከጥቅም ጋር የተያያዘ የግል ጠብ ነው፡፡ በሙስና የተዘፈቀ ሰው በሙስና የተዘፈቀን ሰው እንዴት በፍትህ አደባባይ ሊያቆም ይችላል? ብዔል ዘቡል ብዔል ዘቡልን ሊያወጣስ ይቻለዋልን? ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡
ባለታሪካችን የወያኔ ጎምቱ ካድሬ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የዕድሜ ይፍታህ ፕሬዚደንት የሆነው ዶክተር ኃይለ ሚካኤል ማንትስ ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ በዘመነ መሣፍንት የአገዛዝ ቅኝት ሥር እንደምትገኝ አንዱ ተጨባጭ ማስረጃ የሚሆነን የዚህ ሰውዬ ሃይ ባይ የሌለው ጋጠወጥ አድራጎት ሲታይና በእግረ መንገድም ሀገራችን የገባችበት አዘቅት ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው ስንረዳ ነው፡፡ በዚህ ላይ መማር አለመማር በወያኔ መንደር ምንም ማለት እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ አንድ ሰው ዶክተርም ሆነ ማስተርስም ኖረው ዘረኝነቱና ሆዱ ከዕውቀት እንደሚበልጥበት በነዚህ ዶክተር ተብዬ የወያኔ አንጋፋ ካድሬዎች አስነዋሪ ተግባራት እንረዳለን፡፡ እነዶክተር ቴዎድሮስ፣ እነዶክተር ገ/አብ ባርናባስ፣ እነ“ፕሮፌሰር” ክንፈ፣ እነዶክተር ሶሎሞን ዕንቋይ፣ እነዶክተር ሐጎስ፣ እነዶክተር አርከበ ዕቁባይ፣ እነዶክተር አብረኸት፣ እነዶክተር አምለሰት፣ እነዶክተር ፍትዊ፣ እነዶክተር ዘርዑ፣ እነዶክተር መዓሾ፣ ያሉትም የሞቱትም … የሚሠሩትን የዘረኝነትና የምዝበራ ወንጀል ሁሉ ተመልክተን “መማር ባፍንጫችን ይውጣ!” ብንል ሊፈረድብን አይገባም፡፡ አዲዮስ ትምህርት! (በአንድ ሆቴል ውስጥ አንዱ ጣሊያን አንዱ ሀበሻ የቀረበለትን ፓስታ በግሩም ሁኔታ በሹካ እየጠቀለለ ሲያወራርደው ባጠገቡ ተቀምጦ ይመለከታል አሉ፡፡ አበላሉ ሥልጡንና አንዲትም የፓስታ ክር ወደጠረጴዛው ወይም ደረቱ ላይ ወዳንጠለጠላት የገበታ ናፕኪን ጠብ ሳትልበት ጥንቅቅ አድርጎ ስለጨረሰ ፈረንጁ ታዛቢ ደስ ይለዋል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው – ያ ሀበሻ ሲያቀብጠው አንድ አቦሬ ውኃ አንስቶ ግጥም አድርጎ ይጠጣና ፓስታውን ያወራርድበታል፡፡ ያኔ ነው “አዲዮስ ፓስታ!” በማለት ጣሊያኑ የፓስታዋን በጎርፍ መወሰድ በጩኸት የገለጸው – እነሱ ወይን ነዋ የሚጠጡት፡፡ የኛም “ምሁራን” ዶክትሬታቸውን በዕውቀት ሣይሆን በዘረኝነት ለወሱት፤ በሙስና አጨቀዩት፤ ብኩርናቸውንም ለግል ጥቅምና ብልጽግና ሲሉ በርካሹ ሸጡት፡፡)
እያንዳንዱን የመንግሥት መሥሪያ ቤት ስናይ የሙስናው ነገር ያስደነግጣል፡፡ የወያኔ ነገረ ሥራ ሁሉ ሱቅ ውስጥ የገባ ሕጻን ነው፡፡ ሕጻኑ ሕጻን ስለሆነ ያንንም ይህንንም ግዙልኝ ቢልና ዐይን ዐዋጅ ቢሆንበት ሕጻን ስለሆነ አንፈርድበትም፡፡ ወያኔዎች ግን ሀፍረታቸውን ባወጣ ሸጠው የሀገሪቱን ሀብት በግላጭና ካለንዳች ይሉኝታ እየተቃረጡት ናቸው፡፡ የሌላውን ነገድ ባይተዋር አባላት በመጠኑ ስኳር እያስላሱ እነሱ ዋናውን ማር በአካፋና በጎላ ይዝቁታል፡፡ እነሱ ባለመብቶች ሌሎች መፃተኛ እንደሆኑ ስለሚቆጥሩም ከነሱ ፈቃድና ይሁንታ ውጪ የተፈጸመች ማንኛዋም የሌሎች ዜጎች ደቂቅ የሙስና ተግባር በሙስና ወደ እስር የምታስግዝ ናት፤ በዚያ ላይ ትንሽ ፖለቲካዊ ጣጣ ካለችባት ክሱ ወደሽርተኝነትም ሊለወጥ ይችላል፡፡ እንደነሱ በሙስና ለመብከትም ቅድመ ሁኔታ ያለው መሆኑን እንግዲህ ልብ ይሏል፡፡ እነሱ ለመብከት ያላቸው ሙስናዊ መብት ሌላው የለውም – በገዛ ሀገሩ ባይተዋርና የበይ ተመልካች ነዋ! እንደዜጋ አይቆጠርማ! ሌላው ዜጋ ቀበጥ አድርጎት ከነሱ እጅግ ባነሰ ሁኔታ እንኳን ሲሞስን ቢገኝ “ድምበር ዘለልክ! ቀስ ብለህ እደግ! ያደረችዋ ባቄላ… እናንተ ፊት ሲያሳዩዋችሁ፣ የዱሮው ይበቃችኋል …” በሚል አደብ እንዲገዛ ያደርጉታል፤ ትግሬ ወያኔ ግን ወያኔ ያልሆነን ሺህ ዜጋ ቢገድል፣ በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ ቢዘርፍ ጠያቂ የለውም – የድርሻውን እንደገደለና የድርሻውን የደም ካሣ እንደወሰደ ይቆጠርለትና እንዲያውም የሚመሰገን ይመስለኛል (በኤርምያስ ለገሠ መጽሐፍ የተገለጸችውንና የሚጣል የበግ ቆዳ ለአንዲት ምሥኪን ጠላ ሻጭ በመስጠቷ ምክንያት ከሥራ የተባረረችውን ሴት እዚህ ላይ ያስታውሷል፤ ያቺ ሴት ትግሬ ብትሆን ኖሮ – በግልጽ እንነጋገርና – አይደለም አንድ ወይ ሁለት የበግ ቆዳ መቶ ሺህ ለዕርድ የተዘጋጁ በጎችን ለፈለገቺው ሰው ብትሰጥ ግፋ ቢል “ምን ነካሽ አንች ልጅ? ዕረፊ እንጂ!” ተብላ በ‹ድርጅቱ› ትገሰጽ እንደሆነ እንጂ ዝምቧን እሽ የሚለው አይኖርም – ምክንያት፡- የአብዮቱ ዋና አንቀሳቃሽ ከሆነው የጠራ ዘር – ምናልባትም ከ“እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ” ምርጥ የዐድዋ ዘር የተገኘች ናታ!)፡፡ እዚህ ላይ የሚታየውን ዐይን ያወጣ ልዩነት ለመግለጽ ያህል እንጂ ለሙሰኞች አቦካቶ መሆን ቃጥቶኝ እንዳልሆነ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ሙሰኛ ሙሰኛ ነው፡፡ የየትኛውም ጎሣ አባል ይሁን፣ በትንሹም ይሞስን በብዙው፣ ሙስና ያው ሙስና (ጥፋት) በመሆኑ በፍጹም ወገንተኝነት ሊያሳዩበት አይገባም፤ ነውርም፣ ኃጢኣትም፣ ወንጀልም ነው፡፡ በፍትህ ሚዛን ጥፋት ሁሉ እኩል የሚለካና እንደየጥፋቱ ቅለትና ክብደት ተገቢውን አንቀጻዊና ኅሊናዊ ፍርድ ማግኘት የሚገባው እንጂ በዘርና በነገድ፣ በትውውቅና በዘመድ አዝማድ እንዲሁም በጉቦና በመማለጃ ገጸ በረከት(በዓይነትም ይሁን በገንዘብ) ፍርድ የሚያዛቡበት ሊሆን አይገባም፡፡ ግን ግን ትግሬ ወያኔ ብቻ የፈለገውን ይዝረፍ ሌላው ግን የተንጠባጠበችዋን እንኳን ሳትቀር መሬት ላይ አግኝቶ ቢልስ ዘብጥያ ይውረድ የሚል ጭፍን ያለ “ፍትህ” ሲበየን እንደ አንድ ሀገር የጋራ ዜግነት ክፉኛ ያማል – የህመሙ ቃንዛ አጥንትን ሰርስሮ መቅኒ ውስጥ እስኪገባ ድረስ፡፡ ለፍርድና ለንግግር ያስቸገረ ሁኔታ እኮ ነው የገጠመን፡፡ ምን ይሻለን ይሆን አሁንስ? ወደፊትስ ይህን ጉዳችንን እንዴት ነው ለሰው የምናወራው? በጣም እኮ ነው የሚያሣፍር! በዚህ የ21ኛው መቶ የ‹IT› ዘመን እንዲህ ያለ ሀገራዊ ውርደት ይግጠመን? እግዜሩን እግዜር ይይለት! ኃጢያታችን ምን ከሰው ቢከፋ እንዴት በዚህ ዓይነት ለወሬ እንኳን በማይመች አሸማቃቂ ቅጣት ይቀጣናል?
እዚህ ላይ አንድ ቁጭት እናንሳ፡፡ የዚህች ሀገር ሀብት በሙስና እንዲህ እየተዛቀ ባይዘረፍ ኖሮ ስንትና ስንት የልማት ሥራ ይሠራ ነበር? ስደትና ሥራ አጥነት በስንት ደረጃ ይቀንስልን ነበር? ከላይ እስከታች ያለው የወያኔ ባለሥልጣን በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ፣ ራሱም አጋጣሚውን እየፈጠረ የጋራ ሀብታችንን እንዲህ ከቋት ከቋቱ ባይሞጨልፍብን ኖሮ አንድ የአባይ ግድብ አይደለም መቶና ሁለት መቶ ትላልቅ የልማት ዕቅድ አይጠናቀቅም ነበር ወይ? ቁርሱን እንደነገሩ ቀምሶ የምሣና የእራቱ ነገር ህልም ከሚሆንበት ሲቪል ሰርቫንት (የመንግሥትና የግል ተቀጣሪ ሠራተኛ?) ለአባይ ግድብ ደመወዙን በግዳጅ ከሚቆረጥ በሰፊ ቧምቧ ወደ ግለሰብ ኪስ የሚንዶለዶለው የሀገር ሀብት ቢገደብ የአንድ የአምስት ስድስት ባለሥልጣናት ገንዘብ ብቻ ግደቡን አያሠራም ነበር ወይ? መከላከያን ወደቢዝነስ በመለወጥ በንግድ ስም የሚካሄደው ስርቆት፣ በባለሥልጣናትና ዘመዶቻቸው እንዲሁም በጥገኛ መዥገሮች በሙስና እየተወሰደ የሚቸበቸበው መሬታችንና ሀብታችን፣ በጦርና በፖሊስ ከፍተኛና መካከለኛ መኮንኖች የሚካሄደው ለከት ያጣ ዘረፋ፣ በመሣሪያ ግዢ ሰበብ፣ በስንቅና ትጥቅ፣ ለወንበር ጥበቃ ለተሠለፈው የመከላከያ፣ የደኅንነትና ፀጥታ ተቋማትና አባላት በከንቱ የሚፈሰው የሀገር ሀብት፣ በወያኔው የኢንዳውመንት ተብዬዎቹ የንግድ ድርጅቶች፣ ወዘተ. የሚመዘበረው ከግምት በላይ የሆነ የሀገር ገንዘብ ድህነትን ከኢትዮጵያ በስንት ማይል ያባርር ነበር? በመለስ ስም – ሊያውም ሳይበላው ለሞተው – ስንት ቢሊዮን ዶላር አለ? ባለሥልጣናት ስንትና ስንት ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ሀብት በሀገር ውስጥና በውጪ አካብተዋል? በመለስ ልጅ በሰምሃል ስም ተቀምጧል የተባለው ከአምስት ቢሊዮን የሚበልጥ ዶላር ስንት ግድብና ስንት ዘመናዊ ሆስፒታል ያሠራ ነበር? በየምሽት ክበቡ ለምታስታውክበትና ጎረምሣ ለምትቀልብበት ለዚህች አሳዳጊ ለበደላት የመርገምት ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ እንደቅቤ በከንቱ የሚቀልጠው የምን ፍርጃ ይሆን? ስንቶቻችን ነን በቀላ ሊድኑ በሚችሉ ጥቃቅን በሽታዎች በየቀኑ እንደቅጠል የምንረግፍ? ስንቶቻችን ነን በርሀብ አለንጋ የምንገረፍ? ለመሆኑ በዚያች ማሕጸን ውስጥ ውኃ ብትሆን በሚሻላት አዜብ በሚሏት መበለት ስም ስንት ዶላር አለ? በእያንዳንዱ ባለሥልጣንና ዘመድ አዝማዶቹ ስም ስንት ገንዘብ በየባንኩ አለምንም ሥራ ታጉሯል? በግለሰቦች እንደተመዘበረ ከተደረሰበትና ውጪ እንደኮበለለ ወይም ወዳገር ሳይገባ በዚያው እንደቀረ ከተነገረው የ8.5 ቢሊዮን ዶላር የአንድ ወቅት ሪፖርት በተጨማሪ በየጊዜው በድብቅ እየወጣ የሚጠፋው ዶላርና ወርቅ ስንት ይሆን? ያ ጋጠወጥ ቀልበ-ቢስ ቱጃርና መሰሎቹ ልበ-ሥውራን ሀብታሞች አለመላው የሚጫወቱበት የሀገር አንጡራ ሀብት በስንት ቢሊዮን ይገመታል? ታዲያ ኢትዮጵያና ሕዝቧ በአጥንታቸው መሄድ ይነሳቸው? የግፋቸው ግፍ ደግሞ ከዚችው ከልደታ እስከባታ እንኳን መድረስ ከማትችለው ደሞዝ ተብዬ አነስተኛ ምንዳ ላይ ከዓለም ሀገሮች በከፍተኛነቱ እጅግ በሚለየው የሥራ ግብርን(income tax) ጨምሮ በፈለጉት ሰበብ መዝረፋቸው ነው( ይገርማችኋል- በዓመት አምስት መቶ ሺህ የተጣራ ገቢ ሊያገኝ የሚችል ነጋዴ አጭበርብሮና ከግብር አስከፋይ ኃላፊዎች ጋር በጥቅም ተሞዳምዶ በዓመት ከአምስት ሺህ ያልበለጠ የገቢ ግብር ሲከፍል እንደኔ ዓይነቱ ደመወዙ ላይ አንድም ድምፅ የሌለው ምሥኪን ሠራተኛ ቫትን ጨምሮ ከደመወዙ 50 በመቶ አካባቢ ይቆረጥበታል፤ ፍትህ የት አለች? ሰሚም ባይኖር አብረን እንጠይቅ፡፡) ዳሩ እነሱ ደሞዛቸውን አያውቁት፤ ዳሩ እነሱ ምን ገደዳቸው በደሞዛቸው አይኖሩ፤ እነሱ ደሞዝን ለስም እንጂ መች ሲጠቀሙበት ፡፡ ይብላኝ ለኛ እንጂ፡፡ እግዜሩ፣ ጨካኙን መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ወስዶ እነዚህን አረመኔ ገዢዎች የሰጠን ምን ያህል ክፉ ብንሆንበት ይሆን? ለመልስ ዳተኛ ቢሆንም እሱንም እንጠይቀው፡፡
ሁሉን ቢያወሩት ራስን ከማሳመም ውጪ ትርፍ የለውምና ስለዶክተር ተብዬው የወያኔ አንዱ መሥፍን ትንሽ እናውጋ፡፡ ነገር እየተጎተተብኝ አንዱን ጀምሬ በቅጡ ሳልቋጭ ሌላውን ማንሳቴን አውቃለሁና ይቅርታችሁን – ወድጄ እንዳይመስላችሁ፡፡
ይህ ሰው ሲቪል ሰርቪስን እንዲመራ ከተመደበ 20 ዓመት ሊሞላው ጥቂት ጊዜ ነው የሚቀረው፡፡ ያን ግቢ እንደፈለገው ያሽከረክረዋል፤ አስፈሪና አስጨናቂ ንጉሥ ነው፡፡ የእናት አባቱ ርስተ ጉልት ይመስል በወያኔ ካድሬነቱ በመኮፈስና ከማንጠልጠያዎቹ ጋር ባለው የጥቅም ትስስር ምክንያት ማንም ምንም ሊያደርገው እንደማይችል በመረዳት መምህራንና ሠራተኞችን ሲያንገላታ አንድም ጠያቂ የለውም፡፡ በድንጋይ ማምረቻነት የሚታወቀውን ይህን ዩኒቨርስቲ ልክ እንደ አንድ ኪንደር ጋርተን (ሙኣለ ሕጻናት) በመቁጠር እንደፈለገው ይዘባነንበታል፡፡ በሰሞኑ የወያኔ የዩንቨርስቲ መምህራን ሥልጠና ግና በስብሰባው መጨረሻ ላይ በተከፈተች አንዲት ጠባብ “የተቋማችሁን ችግሮች አስረዱ” የምትል መድረክ ምክንያት የዚህ ሰውዬ ገመና ተፍረጥርጦ ሊነገር ችሏል፡፡ ደፋር አይጥፋ፡፡ እስከዶቃ ማሰሪያው ነው የነገሩት፡፡ ከሰማሁት በጥቂቱ ላካፍላችሁ እችላለሁ፡፡ የሰውዬው ገመና በተለይ ይህን ተቋም ለሚያውቅ የአደባባይ ምሥጢር ስለሆነ አዲስ ነገር አልናገርም፡፡ (በነገራችን ላይ ዩኒቨርስቲው ካባ (ድንጋይ ማምረቻ) እየተባለ የሚጠራው በመምህራኑ ዕውቀትና ችሎታ ማነስ ሣይሆን በፖለቲካው ቅኝት ተመርጠው የሚገቡት ተማሪዎች “ሀ” ቢሏቸው “ሁ” የማይሉ ደናቁርት በመሆናቸው ነው፡፡ በወያኔ ቡድን ከወረቀትና ከታማኝነት ባለፈ የትምህርት ጥራትና ብቁ የዲግሪ ትምህርት አያስፈልግም፡፡ ስለሆነም እምነት የሚጣልበት ቅን ታዛዥ ይሁን እንጂ ከስምንተኛ ክፍልም ቢሆን ተመልምሎ የሚላክ ካድሬ የላከው ድርጅት የፈለገው ድግሪ በተቋሙ እንዲሰጠው የወያኔ ያልተጻፈ ህግ ያስገድዳል – ዐይኑን ሳያሽ የታዘዘውን የሚፈጽም ሙሰኛ አለቃም ስላለ ድንጋይ ለማምረት አደናቃፊ ነገር አይኖርም፡፡ የድንጋዮች መጨረሻ አምሮ እንደማያውቅ ብጠቁም ግን ደስ ይለኛል፡፡)
- ሰውዬው ፍጹም አምባገነን ነው፡፡ በግቢው ውስጥ ያሉ ትላልቅና ንዑሳን የሥራ ክፍል ኃላፊዎች በፕሬዝደንቱ በኩል ሳያልፍ ከማንም ጋር ምንም ዓይነት መደበኛም ይሁን ኢ-መደበኛ ግንኙነት እንዲያደርጉ አይፈቀድላቸውም፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ምንም ደብዳቤ መጻፍና መላላክ እንዳይችሉ አንዳቸውም ቢሮ የሥራ ክፍሉ ማኅተምና የኃላፊው ቲተር እንዳይኖር የተደረገው፡፡ እንኳንስ በአንድ ትልቅ ዩኒቨርስቲ በአንዲት ትንሽ ተቋም እንኳን፣ ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች እዚህ የተጠቀሱት የመደበኛ ደብዳቤ መላኪያ ማኅተምና ቲተር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ አፄ መለስ ዳግማዊ ግን ይህን አልፈቀደም፡፡ ሁሉንም በርሱ ሥር ማሳለፍና መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ተቋሙ የግሉ ንብረት እንደሆነ ያህል ስለሚሰማው በንብረቱም ሆነ በገንዘቡ ያሻውን ያደርጋል፤ እንደብዙዎቹ ወያኔዊ የመንግሥት ተቋማት ሁሉ በዚህ ግቢም ቁጥጥር ብሎ ነገር የለም፡፡ ሠራተኞችንና መምህራንንም አባቱ የቀጠሩለት የዱሮ ዘመን ባሪያዎች የሆኑ ያህል ሳይቆጥራቸው አልቀረም፡፡ የሚገርም ‹ዶክተር› ነው እባካችሁ!
- ሠራተኞችንና መምህራንን ደስ ባለው ጊዜ እየተነሣ ከሥራ ያባርራል – ይህም ጠባይ ሀገሪቱን እንደግል ርስት የያዙ የሚመስላቸው የብዙ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች የሚጋሩት ነው፤ ወያኔን አይንኩ እንጂ በሌላው ጎሣና ነገድ ላይ እንደዐይጥ እንዲጫወቱበት ዘረኛ ሥርዓቱ ይፈቅድላቸዋል – በትግሬ ላይ ቢያደርጉት ግን የአለቃ ገ/ሃናን “እዚያም ቤ እሳት አለ!” የሚለውን ብሂል ሊያስታውሱ የግድ ነው (መለስ ስለሚስቱ ሲናገር እሳት የሚተፋ ምን ነበር አላት ያለው?) ፡፡ ሰውዬው – ዶፍተሩ – ከመጠን በላይ አሉቧልታና ሀሜት እንደሚወድ ይነገርለታል፤ በትንሹም በትልቁም እያኮረፈ ታዲያን ሠራተኞችን ከሕግ ውጪ ከሥራ ያግዳል፤ ያባርራል፡፡ ባለፈ አንድ ወቅት አንዳችም መሠረታዊ አሳማኝ ምክንያት ሳይኖረው ስምንት መምህራንን አባርሮ እንደነበርና ኋላ ላይ ግን ብዙዎቹ በፍርድ ቤት ተከራክረው መመለሳቸው ታውቋል፤ ይህም በስብሰባው ላይ ተገልጾኣል፡፡ አምባገነን ግለሰብ ከአምባገነን የመንግሥት ሥርዓት ጋር ሲጎዳኝ የዜጎች የመኖር ዋስትና እንዴት እንደሚጨፈለቅ ከዚህ ሰውዬ ነውረኛ ድርጊት መገንዘብ ይቻላል – ተምሮ ያልተማረ ማይም፡፡ በአንድ የምረቃ መጽሔት የመጨረሻ ቃል ማስፈሪያ የፎቶዋ ግርጌ ላይ አንዲት ተመራቂ “ሣይማሩ ላስተማሩኝ መምህሮቼ ምሥጋና ይድረሳቸው” የሚል አስደንጋጭ ሐረግ ማስቀመጧን አሁን ሳስበው የዚህ ‹ዶክተር› ትምህርትም ውኃ እንደበላው ገባኝ፡፡ ግን ግን ሞኝ አትበሉኝና መማር ለመደደብ በር ከፋች ዘበኛ(doorman) ይሆን እንዴ?
- አምስት መቶ ሺህ ብር እንኳን በማትፈጅ ትንሽዬ ድልድይ ስምንት ሚሊዮን ብር እንደፈጀ አድርጎ ማወራረዱ ተሰብሳቢን በሣቅ ባፈነዳ ሁኔታ ጉባኤው ላይ በግልጽ ተነግሯል፡፡ በዚህ ትንሽ ሰው ይህን ያህል የሀገር ሀብት ከተዘረፈ እሱን መሰሎች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የወያኔ ካድሬዎች ምን ያህል የሀገር ሀብት ሊመዘብሩ እንደሚችሉ ይታያችሁ፡፡ አሁንም ከፍ ሲል የጠቀስኩትን እዚህ ልድገመው – እናም እኛ ኢትዮጵያውያን በችጋርና በችግር ያላከክን ማን ሊያክ ኖሯል? ድልድይቱን እኔም በዐይኔ በብረቱ አይቻታለሁ፡፡ ዩኒቨርስቲውን በስተጀርባ በኩል ካለው መንገድ የምታገናኝ በጣም ትንሽ ድልድይ ናት፡፡ የሚገርመው “ስምንት ሚሊዮን”ም ፈጅታ ከተሠራች ስድስት ወር ሳይሆናት ተሰነጣጥቃለች፡፡ ምን ይታወቃል – ለማሳደስ በሚል ሰበብ ደግሞ አንድ አሥር ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረግባት ይሆናል፡፡ የተዓምራት መገለጫ በሆነች ሀገራችን ምን የማንሰማው ድንቅ ነገር አለ?
- ይቺኛዋ ታሪክ ደግሞ ትንሽ ቆየት ያለች እውነተኛ ዘገባ ናት፡፡ አንድ ጊዜ ነው – ብዙ የሕዝብ ማመላለሻ የቻይና ሃይገር አውቶቡሶች ወደዩኒቨርስቲው ይመጣሉ፡፡ ሹፌሮቹም አቶ ማንን ነው እቴ – ዶክተር እንጂ፣ ዶክተር ኃይሌን ጥሩልን ይላሉ፡፡ ዶክተሩ ተጠርቶ ሲመጣ ሾፌሮቹንና መኪኖቹን ባዬ ጊዜ በድንጋጤ ተውጦ “ለምን እዚህ መጣችሁ? ለምን በስልክ አታናግሩኝም?” በማለት ይጮህባቸዋል፡፡ እነሱ ደግሞ የገጠማቸውን ችግር ያስረዳሉ – የመጡት ከመኪና መሳደሪያ ሒሳብ ጋር በተያያዘ በገጠማቸው እሰጥ አገባ ምክንያት የደረሰባቸውን ጊዜ የማይሰጥ ችግር ለማስረዳትና በወቅቱ መፍትሔ ለማግኘት ነበር፡፡ ለካንስ እነዚያ መኪኖች የዶክተሩ የግል ንብረቶች ናቸው! አንድ የዩንቨርስቲ ፕሬዚደንት ይህን ያህል ሀብትና ንብረት ማፍራት እንዴት ይችላል? አዎ፣ የኛ ሀገር የወያኔ ካድሬዎች የሆኑ “ምሁራን” ሙስና እንደማይዘወተርበት በሚታመነው የትምህርቱ መስክ ሣይቀር ይህን የመሰለ ዘረፋ ያካሂዳሉ – በሌሎች መስኮች የሚገኙትማ እንዴቱን ያህል አይዝቁት፤ የየባለሥልጣኑ ሆድ እንዴት ነው እንዲህ እንደፊኛ እየተለጠጠ የሀገርን ሀብት የሚያግበሰብሰው ጃል! ታዲያ እኛ ያልከሳን ያልጠቆርን ማን ይክሳ፣ ማንስ ይክሰል? አክስቴ ማንጠግቦሽ አሥሯን አሥራ አምስት አደርጋለሁ ብላ በየጉሊቱ የሃምሣ ብር ቃሪያና ሽንኩርት በአንድ ብርና በሁለት ብር ትቸረችራለች – እነወያኔ ደግሞ በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ከድሃዋ ኢትዮጵያ በሰበብ አስባቡ ይዘርፋሉ፤ እነሱ እየዛቁ ወደግል ካዝናቸው ሲከቱ ሀገሪቱ ለደሞዝ መክፈያ እንኳን እጅ እያጠራት ከቀን ወደ ቀን እየደኸየች ትሄዳለች፤ የነዚህን ወያኔዎች ቀዳዳ ሆድ ለመሙላትም ብሔራዊ ባንክ በየቀኑ የወረቀት ግፋፎ እያተመ ገበያውን ያጨናንቀዋል፡፡ ሠራተኛው በዚህ መሀል ጭዳ ይሆናል – ግራሟ(ክብደቷ) የአንድ ጆሮ ጌጥ ለምታህል አንዲት ጉርሻ ፎርኖ አንድ ብር ከሠላሣ ሣንቲም እየገዛን ልጆቻችንን ቁርስ ማቅመስ አቅቶን ባዶ ሆዳቸውን ትምህርት ቤት የምንልክ ብዙ ነን – ሊያውም ለዚህም የታደልን እንጂ ዩኒፎርምና ደብተር መግዛት እያቃተው ስንቱ ወላጅ መሰላችሁ ልጆቹ በረንዳ ሲያሞቁ ውለው ማታ ሲገቡ ወይም በየጎዳናው ሲርመሰመሱ እያዬ አንጀቱ የሚቃጠለው፡፡ በዓይነቱ የተለዬ ዕንቆቅልሽ ገጥሞናል፡፡ ፈጣሪ ይሁነን እንጂ በዚህ ከቀጠልን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ስሊያችንን አንቀው እንደተራበ ነብር ደማችንን በጠራራ ፀሐይ ሳይመጡት አይቀሩም፡፡ እነዚህ መዥገሮች ቀላል እንዳይመስሏችሁ፡፡
- አንድ መምህር ለትምህርት ወደ ውጭ ሀገር ይሄዳል፡፡ ባለቤቱና ሕጻን ልጁ በግቢው በተሰጣቸው ቤት ይኖራሉ፡፡ ይህ ዶክተር ሕጻን ይመስል ከመምህሩ ጋር በተጋባው እልህ ምክንያት ሴትዮዋን ከቤቱ ውጪ ይላታል፡፡ ቤት አፈላልጋ ልትወጣ ወደግቢው ስትገባ ዘበኞቹ አትገቢም ይሏታል፡፡ የሚገርመው በፊት ስትወጣም አትወጪም ተብላ በመከራ ነው የወጣችው፤ አትወጪም – አትገቢም፡፡ የወያኔ ነገር “ያውጡብሽ እምቢ፣ ያግቡብሽ እምቢ” መሆኑ አይገርምም? ምን ዓይነት ትዕዛዝ ነው? ከዛም የምታደርገውን ስታጣ ፖሊስ ይዛ መጣችና የምታጠባው ሕጻን ልጅ ስለነበረ እንድትገባ ተደረገ፡፡ ሰውዬው – ዶክተሩ – ግራ የሚያጋባ ስብዕና ባለቤት ነው – እንደብዙዎቹ ወያኔዎች፡፡ ወያኔዎች ሥራቸው ሲታይ የሕጻንነት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ይመስለኛል ትልቅ የሚሆኑት፡፡ እልሃቸው ይገርማል፤ ቂም በቀልን የሚወጡበት ሥልት ይገርማል፤ የሚጠሉትን ለማጥቃት የሚሄዱበት አስቂኝ መንገድ ሁሉ ይገርማል፡፡ አሁን እስኪ ይታያችሁ “ከስምንት ዓመት በፊት የገዛሃት መኪና የቀረጥ ችግር ነበረባት” ብሎ ከተሸጠችና ከተረሳች ዘመን ያለፋትን መኪና ታሪክ – ችግሩ እውነት ነው ብለን ብናምንላቸውም እንኳን – ከመቃብር አውጥቶ ሰውን መክሰስ ሕጻንነት እንበለው ወይንስ መጃጃል? በርግጥም ለሀገር የሚቆረቆሩ ከሆነ እስኪ የዶክተር ኃይሌን ድልድይ ወጪ ያጣሩና ከዚያች መኪና የበለጠ ገንዘብ ለ“መንግሥት” ለማስገባት ይሞክሩ፡፡ እንዴ! ምንድናቸው እነዚህ “ሰዎች”?
- አንድ ወቅት ለሰባት መምህራን ቤት ሊሰጥ ከሃያ መምህራን መካከል በተቀመጡ መሥፈርት አማካይነት የማጣራት ሥራ ይካሄዳል፡፡ ከሃያዎቹ መካከልም ሰባቱ ነጥረው ይወጡና ከአንድ እስከ ሰባት በደረጃ ይቀመጣሉ፡፡ ሰውዬው ይህን ሲመለከት ከሰባቱ ውስጥ በተለይ አንደኛና ሁለተኛ የወጡትን ሁለት ግለሰቦች አይወዳቸውም ነበርና ውጤቱን ለመገለባበጥ አዲስ መስፈርት ይጨምራል፡፡ ያም መመሪያ የአስተዳደር ግምገማ ከ20 በመቶ እንዲያዝ የሚል አዲስ ትዕዛዝ ነው፡፡ በአዲሱ “መመዘኛ” መሠረት ሰውዬው የሚፈልጋቸው በፊተኛው የማጣራት ሂደት የወደቁ ሁለቱ ግለሰቦች አንደኛና ሁለተኛ እንዲወጡ ሆኖ የፊተኞቹ አንደኛና ሁለተኛ የወጡ መምህራን ፎሪ ይደረጋሉ፡፡ የሚገርመው ዝርዝሩ ብዙ ስለሆነ እዚህ ላይ መጥቀሱ ይከብደኛል እንጂ በአዲሱ መመዘኛም እነዚያ ቤት እንዳገኙ የተደረጉ ሁለት መምህራን እነዚህኞቹን በውጤት በልጠዋቸዋል፤ ግን ሞኝ እንዴት ያሸንፋል ቢሉ እምቢ ብሎ እንዲሉ ሆኖ በድርቅና ብቻ እንዲያሸንፉ ተደረገ፡፡ ይህን ዐይን ያወጣ የመድሎ ሥራ ሁሉም የግቢው ሰው ያውቀዋል፡፡ ነገር ግን ዘረኝነት ያሳወረውን ሰው መጋፈጥ ለበለጠ ጥቃት ማጋለጥ በመሆኑ ገፍቶ የሄደበት ሰው የለም፡፡ በቀደም ዕለት ግን ይህ አስነዋሪ ተግባር በአደባባይ በስብሰባው ወቅት ተጋለጠና ሰውዬው የሀፍረት ጃኖ ለበሰ፤ ግን ማፈርስ ሲያውቅበት አይደል?
- በዚህች የመጨረሻ ድሃ ሀገር ይህ ሰውዬ ለመሥሪያ ቤት ሥራ የሚጠቀምባቸው መኪኖች ቁጥር አራት ናቸው፡፡ “ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት” እንደምንለው ወያኔዎች ካሉባቸው መጥፎ ጠባዮች አንዱ ሁሉንም ነገር የመቆጣጠር አባዜ ነው፡፡ በአንዲት ድሃ ሀገር የአንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ኃላፊ አንድ ዐይን የማይገባ መኪና ቢጠቀም የትኛው ክብሩ ይቀነስበታል? የዚህ ሰውዬ መኪኖች ዋጋ ደግሞ ሰማይ ነው፡፡ እንደሚባለው ድምር ዋጋቸው ከአምስት ሚሊዮን አያንስም፡፡ የመኪኖቹ ዋጋ ራሱ በአንድ መንደር አንድ አነስተኛ ክሊኒክ ሊያሠራ ይችላል፡፡ የአንድ ሀገር ባለሥልጣን የሚያስተዳድረውን ሀገር ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ አቅምና የአገሩን የዕድገት ደረጃ ካላወቀ ዓለም እስክትታዘበው ድረስ ትልቅ ችግር ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ በሚከፈለው ደሞዝ የወር ቀለቡን መሸፈን ሳይችል በርሀብ የሚንጠራወዝ የመንግሥት ሠራተኛን በሥሩ ያቀፈ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ለፕሮቶኮሉ ሣይሆን ለደኅንነቱ ሲባል በእግሩ እንዲመላለስ ባይጠበቅበትም በአምስትና ስድስት ሚሊዮን ብር በሚገዛ ተሸከርካሪ እንዲጓዝ ኅሊናው ሊፈቅድለት አይገባም፡፡ አእምሮ የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነውና የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ ኑሮና አጠቃላይ ሁኔታ ወረድ ብሎ ማየትና ባጭር ታጥቆ የሕዝብን ችግር ለመጋፈጥ መነሣት ከአንድ ሀገር ወዳድ ባለሥልጣን የሚጠበቅ ነው – እንደወያኔ የድሆችን ገንዘብ እየመዘመዙ በድሃ ላይ መንቀባረር ሳይሆን “እንዲህ ከምቀናጣ ለሕዝቤ ስል ይህን ይህን ነገር ልተው” ማለት ይገባል – “ሆድ” ደግሞ “እንዳሳዩት ነው” ይባላል፡፡ በመሠረቱ ሀገርን ለማስተዳደር በቅድሚያ ሀገራዊና ብሔራዊ ስሜት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የምንጮኸው ጅብንና ዓሣማን እንደሰው አስቡ የማለት ያህል ነው፡፡ ከንቱ የቁራ ጩኸት፡፡ ምን ይሻለን ይሆን ግን?
ወያኔ ጋር ለመሥራት ኅሊና ስለማያስፈልግ እነሱን ተጠግቶ ሀገሪቱን ባለ በሌለ አቅሙ የሚግጠው የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ዜጋ ብዙ ነው – ያ የእግር ኳስ አሰልጣኝ እንኳ ግብ በገፍ የሚያስተናግድ ልፍስፍስ ቡድናችንን ለ“ማሠልጠን” የስንትና ስንት ሠራተኛ ደመወዝ ጭማሪ ቢሆን የብዙ ሕጻናትን ወስፋት ይሸነግል የነበረ 500,000.00 ሺህ ብር አይደል በየወሩ የሚከፈለው? በሞኝ ደጃፍ ሞፈር እንደተቆረጠ በኢትዮጵያ ግዛት ፀሐይ ሳትወጣ እስከመቼ እንደምንዘልቅ ሳስበው ግርም ይለኛል – ለዚህ ለዚህማ ሰውነት ቢሻው እንደለመዳቸው እያሰለጠናቸው ደህና ደሞዝ ቢከፈለው ምን ነበረበት? ለምን በቆዳ ይታመናል? ራስን እየናቁና የራስን እያጣጣሉ የት ይደረሳል? ይህን የምለው በሁሉም ዘርፍ ስላለው የጭቡ ሥራ ሁሉ እንጂ የስፖርቱን ብቻ አይደለም፡፡ ለአብነት በትምህርቱ ዘርፍ ዶክትሬት ይኑረው አይኑረው፣ ዶክትሬቱ ሊያስተምር በተቀጠረበት የትምህርት ዓይነት ይሁን አይሁን ሳይታወቅ እንዲሁ በቀለምና በዘር የማምለክ ጠባያችንና ምናልባትም በሙስናዋ ደንዝዘን ለአንድ የሕንድ ዶክተር ተብዬ መምህር ብዙ ሺህ ብር ስንከፍል እሱን ለሚበልጠው ኢትዮጵያዊ ምሁር ግን አንድ አሥረኛውን እንኳን አንከፍለውም፤ ለምንከፍለው አነስተኛ ገንዘብም እንቆጫለን – ወጉ አይቀርምና ሲሉም ተሰምቷልና በሚዲያችን ላይ “brain drain” እያልን እናላዝናለን – የውሸታችንን፡፡ ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት ስለሀገር የሚጨነቅ አንድ ባለሥልጣን አለ? ለተማራና ለሠለጠነ የሀገር ልጅ ቅድሚያስ የሚሰጥ ተቋም አለ? የለም፣ ምክንያቱም ብዙዎቻችን የምቀኝነትና የማይምነት ልክፍት ሰለባዎች ነና፤ ፈረንጁ ሲልጠን ደስ ይለናል፤ የኛው ሲያገኝ ግን ይከፋናል፤ ብዙዎቻችንን የተጠናወተንን ጠማማ አስተሳሰብና አመለካከት በአወንታዊ የቀናነት ቅባት ካላሸነው ከዚህ በበለጠ ገና እንጠፋለን፤ ምቀኝነትና ቅናት ፈዋሽ ጠበል ካልፈለቀላቸው ሀገርን የሚያጠፉ አደገኛ መርዞ ናቸው፡፡ እንዲያው ባጭሩ ግን ብዙዎቻችን ፈረንጅ አምላኪዎች ነን – የማንረባ! ስንቱ ጉዳችን ተነግሮ ይዘለቃል እባካችሁ(በተማሪ መግቢያና መውጫ ሰዓት ነጭ ገዋን አልብሰው ባገሩ አትክልተኛ የነበረ ማይም ፈረንጅ በግቢያቸው የሚገትሩ የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች እንዳሉ ሰምታችኋል? ወላጅ ልጁ በፈረንጅ ሲማርለት እየታየው የተጠየቀውን ገንዘብ ይከፍላላ! መቼ ይሆን ሰው የምንሆነው?)፡፡ እውነቱን ያ ብላቴና “ባለቤት የሌላት ከተማ” ያላት አዲስ አበባን፡፡ ሀገሪቱም ሕዝቧም እንደጠፍ አህያ ማንም እንደፈለው የሚጭነን ባለቤት አልባዎች ሆነናል፡፡(እዚች ላይ ባጭሩ ሳልጠቅሳት ማለፍ የማልፈልጋት የምቀኝነትን ባህላዊ ትክልነት የምትጠቁም ነገር አለችኝ፡፡ በወቅቱ አንድ መጣጥፍ ልጽፍባት አስቤ እየዘነጋሁትና ንዴቴ እየበረደ ሄዶ ተውኩት፤ ቆይቶ ደግሞ ያናደደኝ አንድ በጣም የምወደው ጋዜጠኛ ወገኔ ወደእስር ስለወረደ መጻፌን በገምቢነት አላየሁትም፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- በስም የማልጠቅሰው ጋዜጠኛ በኤርምያስ ለገሠ መጽሐፍ ላይ ትችት ሲያቀርብ ኤርምያስ እያገኘ ያለውን ዝናና ታዋቂነት መሠረት ያደረገ በሚመስል የምቀኝነት ሊለቀን ያልቻለ አባዜ የወጣቱን ልጅ ሀገራዊ አስተዋፅዖ – ምናልባትም ሳይታወቀው – አንኳስሶ ሲጽፍበት በውነቱ አፍሬያለሁ፤ እንደዚያ ያለ ለጠላት በር የሚከፍት ነገር በወዳጅ ጋዜጠኛ ብዕር ተጽፎ ሳነብ የተሰማኝ የመከፋት ስሜት ወደር አልነበረውም፡፡ … አንድ ሰው የሚኖረው ዝና የኛን ስብዕናና ታዋቂነት የሚሻማብን እየመሰለን አንዳንዶቻችን የምናሳየው ያልተለመደ የመቅበጥበጥና የመወራጨት ባሕርይ ትዝብት ውስጥ ይጥለናልና ጠንቀቅ ማለቱ ደግ ነው፡፡ የጻፍነውን ነገርም ደግመን ማየቱና ‹ኤዲት› ማድረጉ ብዙዎችን ከማስከፋት ያድነናል፡፡ በዚህ ብቻ ልለፈው፡፡ እሱም በአሁኑ ሰዓት እየተሰቃዬ ስለሆነ ፈጣሪ ከርሱና ከመሰሎቹ ጋር ይሁን፡፡)
ወደጀመርኩት አለፍኩ፡፡ በነዳጅ ስም፣ በአበል ስም፣ በወንበር ስም፣ በቤት አበል፣ በትምህርት አበል፣ በግልጽ በሚታወቅም በማይታወቅም ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅም ስም በየቢሮው የሚዘረፈውን ገንዘብ ታሪክ ያስላው ከማለት ውጪ የምናውቀውና የምንለውም የለም፡፡ የሚገርመው ሌላ ነገር በርዕሳችን የተገለጠውን ዶክተር ተብዬ ጨምሮ እነዚህ የወያኔ ባለሥልጣናት አለን የምንለውን ትንሽ ሀብት እንዲህ ሲዘባነኑበት ሕዝቡ ግን መንገድ የለው፣ መብራት የለው፣ ውኃ የለው፣ ስልክ የለው፣ ህክምና የለው፣ ዴሞክራሲ የለው፣ ትምህርት (ቤት) የለው፣ የመኖሪያ ቤት የለው፣ ሠራተኛው ከወር ወር ቀርቶ ለሦስት ቀናት የሚበቃ ደሞዝ እንኳን አይከፈለው…. ኧረ ምን ይሻለናል ገበዝ? በአንድ በኩል የባለሥልጣናቱንና አጃቢዎቻቸው የሆኑ የነጋዴዎችን ኑሮ ስታዩት፣ በሌላ በኩል የአብዛኛውን ሕዝብ የከፋ የድህነት ኑሮና ጉስቁልና እንዲሁም የታህታይና ላዕላይ መዋቅሮች በበቂና ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ አለመዘርጋት ስታዩ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ግራ በመጋባት ሁሉም ነገር ጨልሞባችሁ ጭንቅላታችሁ ይዞርባችኋል፡፡( የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ብፃይ ቴዎድሮስ አንደሆም አንድ የሐኪሞች ስብሰባ ላይ ለተጠየቀ የጥራት ጥያቄ ምን አለ አሉ – “እኛ የምናሰለጥናችሁ ለዚህ ሀገር ሕዝብ የሚበቃችሁን ያህል መጠነኛ ዕውቀት እንጂ ለዓለም አቀፍ ገበያ የምትሸጡት ከፍ ያለ የሕክምና ዕውቀት አይደለም”፡፡ አሃ! ኢትዮጵያውያንን ለማከም አስፕሪንና ፓናዶል ማዘዝ ብቻ የሚችል ዶክተር ነዋ የሚያስፈልገን! ለዚች ለዚችማ ዳማከሴና አርማጉሳ፣ ሐረግሬሣና ጤናዳም የት ሄደው? ለነገሩ “ራቁቱን ለተወለደ እርቦ ምን አነሰው” ይባል የለም? ጊዜያቸው ነውና ግዴለም እነብፃይ ይጫወቱብን፡፡ “ይደልዎሙ” ይላል ግዕዙ “ይገባቸዋል” ሊል ሲፈልግ፤ እኛም “ይደልዎነ” እንበላ “We deserve!” ለማለት፡፡ አዎ፣ ከችግራችን ለመውጣት የምንጓደድ ከሆነ ችግራችን ድሎታችን እንደሆነ በመቁጠር ተስማምተን ተቀብለናል ማለት ነውና ቢረግጡን ሊከፋን አይገባም፡፡…)
እኛና ፖለቲከኞቻችን እንግዲህ እንዲህ ነን፡፡ ሙስናና ንቅዘት የሌለበት ሀገራዊ ተቋም በፍጹም አይገኝም፡፡ ለአንድ ፕሮጀክት ከሚመደብ በጀት ውስጥ በግምት ከሃምሣና ስልሣ በመቶ በላይ በባለሥልጣናት ይመነተፋል፡፡ በቀሪዋ በጀት ሥራውን እናስጨርሳለን ብለው ሲሞክሩ ደግሞ የሥራው ጥራት ይበላሽና ለምሳሌ ቤት ከሆነ ገና ሥራ ሳይጀምር በባህር ዛፍና በጥድ አጣና የሚደገፍ ወይም ስብርብሩ ወጥቶ ከናካቴው የሚገነደስ ይሆናል፤ መንገድም ከሆነ አንድ ክረምት ሳያልፍ ምናልባትም ርክክቡ ሳይፈጸምና በወጉ ሳይመረቅ ፍርክስክሱ ወጥቶ ወይ አስፋልት ወይ የጠጠር የገጠር መንገድ ሳይሆን የሸማኔ ጉድጓድ እንደሆነ መኪኖችን ሲያረትም ይገኛል – ባለመኪኖችን ለተወደደ የተሸከርካሪ መለዋወጫ ሊያጋፍጥ፡፡ በመጨረሻም…
በመጨረሻም ፈገግ ልታሰኛችሁ ብትችል አንዲት ሙስና ቀመስ ቀልድ ልንገራችሁና እንሰነባበት – ዛሬ መቼስ አሰለቸኋችሁ፡፡ ከአንድ ከፍተኛ ተቋም በምህንድስና ሙያ የተመረቁ ሁለት ጓደኛሞች ዘወትር እየተገናኙ ይጨዋወታሉ፡፡ ከሁለቱ አንደኛው በአጭር ጊዜ ውስጥ እያለፈለት ሲሄድ ሌላኛው ግን እግረኛና የሚቀይረውም ልብስ የሌለው ናቸው፡፡ በኑሮው ያለፈለት መሃንዲስ መኪና እንደሸሚዝ ይቀያይራል፤ አለባበሱና አመጋገቡ እንዲሁም ቆነጃጅትን አለዋወጡም ሌልኛ ነው፡፡ ይህን የታዘበው ጓደኛው “ደሞዛችን ተመሳሳይ ነው፤ አንተ ግን በኑሮህ በጣም እየተለወጥክ ነው፤ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ እንዴት እንዳለፈልኝ ልንገርህ? ይለውና አዎንታውን ሲያገኝ እንዲህ ያጫውተዋል፡፡ በተውኔት መልክ እናቅርበው መሰለኝ፡፡ ስማቸውንም ወደሌላ ቅኔ ውስጥ ሳንገባ እንዲሁ በዘፈቀዳዊ አሰያየም ያለፈለትን መሃንዲስ አበበ፣ ያላለፈለትን ደግሞ ደበበ እንበላቸው፤
አበበ፤ ያን ድልድይ ታየዋለህ?
ደበበ፤ እዚያ ወዲያ ያለው?
አበበ፤ አዎ፣ እሱ፡፡ እሱን ሳሠራ ለርሱ ከተመደበው በጀት 30 በመቶውን ለራሴ ውስድ፡፡
ደበበ፤ እሺ …
አበበ፤ ያ እዚያ ጋ የተገተረው ሕንፃስ ይታይሃል?
ደበበ፤ በሁለቱ ቪላ ቤቶች መሃል ያለው?
አበበ፤ እህሳ! ከርሱ በጀት ደግሞ 35 በመቶውን ቅርጥፍ!
(ከጥቂት ወራት በኋላ ደቤ ጀግናው ፕራዶ ሚካናውን ይዞ ሱፉን ከነሚያምር ክራቫቱ ገጭ አድርጎ ሲሄድ መብራት ያቆመውና አቤን ያገኘዋል፡፡ መብራ ተለቅቆ ዳር ይዘው ከቆሙ በኋላ …)
አበበ፤ እንዴ! በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ምን አግኝተህ እንዲህ ተለወጥክ?
ደበበ፤ ዕድሜ ላንተ፡፡
አበበ፤ እኔ ደግሞ ምን አደረግሁልህ?
ደበበ፤ ይልቁናስ እንዴት እንዳለፈለኝ እንዳሳይህ ና ተከተለኝ፡፡ (ምንም ቤትና መንገድ እንዲሁም ሕንፃና ድልድይ ወደሌለበት ገላጣ የከተማ ዳርቻ ሥፍራ ይወስደዋል – ደበበ አበበን፡፡)
ደበበ፤ ያ ድልድይ ይታይሃል ?
አበበ፤ የትኛው ድልድይ? ( ምንም ነገር ወደሌለበት ባዶ ጫካ እየተመለከተ)
ደበበ፤ ባይታይህ አይፈረድብህም፤ ብቻ ለሱ ሥራ የተመደበውን በጀት 100 ፐርሰን ልቅሙጭ!
አበበ፤ እሺ…
ደበበ፤ ያ እዚያ ታች ከዛፎቹ መሃል የተገተረው ሕንፃ ይታይሃል?
አበበ፤ የቱ ሕንፃ? (አሁንም ከዛፍና ቁጥቋጦ ውጭ አንዳችም የቤት ዘር ወደሌለበት ደን እየተመለከተ)
ደበበ፤ ባይታይህ አይፈርድብህም፤ ብቻ የርሱንም በጀት መቶ ፐርሰነት ልቅሙጭ!
ማብራሪያ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ትምህርት ማለት እንዲህ ነው፡፡ ከራሱ የሚበልጥ ተማሪ የማያፈራ አስተማሪ እንዳስተማረ አይቆጠርም ይሉ ነበር ግሪካውያን የጥንት ፈላስማዎች በዘመነ አሪስጣጣሊስ ወአፍላጦን፡፡ ግሩም ሀገር ገምቢ ወጣትና ጎልማሣ በብዛት እያፈራን ነው፡፡ ለሀገርና ለወገን ተቆርቋሪ ቴክኖራት በገፍ እያመረትን መላ የወያኔ ኢትዮጵያን እያጥለቀለቅናት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ በጥራትም በብዛትም እጅግ የላቁ የተማሩ ልጆች ሕዝብሽን ወደታላቅ የሥልጣኔ ማማ ሊያደርሱት ቀን ከሌት እየተጉልሽ ናቸው፡፡ አዲዮስ ፓስታ ነበር ያለው ያ ጣሊያን? አዲዮስ ሀገር! አዲዮስ ሕዝብ! አዲዮስ ዕውቀት! አዲዮስ ትምህርት! አዲዮስ ኅሊና!… ራስ ብቻ ጤና፡፡
ምንጭ ዘ-ሐበሻ
No comments:
Post a Comment