(ጉዳያችን)
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥቅምት 11/2007 ዓም ከቀትር በኃላ በምህላ እና በፀሎት መጀመሩ ይታወቃል።በማግስቱ ጥቅምት 12/2007 ዓም ፓትራርኩ አቡነ ማትያስ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ምእመናንን እና የቤተክርስቲያን አባቶችን ያሳዘኑ ንግግሮችን ተናግረዋል።ፓትራርኩ በንግግራቸው አብዛኛውን ክፍል የያዘው የገዢውን ምድራዊ መንግስት ያስደስታል፣ በአጠገባቸው በሙስና እና የቤተ ክርስቲያንን አይን የወጉ ሙሰኞች፣እበላ ባይ አድር ባዮች እና ”የጨለማው ቡድን” ተብለው የሚታወቁትን ታጣቂ ካድሬዎች ያስደስትልኛል ያሉትን ቃላት እየመረጡ ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ጣታቸውን መቀሰር መርጠዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ የአስተዳደር ችግሮች እና የእምነቷ ቀሳጮች ከመቼውም ጊዜ በላይ በከበቧት በእዚህ ፈታኝ ወቅት ማኅበረ ቅዱሳንን የሚያህል ለቤተ ክርስቲያን እና ለአብቶች የሚታዘዙ፣በእውቀታቸው፣በጉልበታቸው እና በገንዘባቸው ቤተ ክርስቲያንን በነፃ የሚያገለግሉ አባላት ማኅበርን ማፍረስ እንደትልቅ የቅዱስ ሲኖዶሱ ቀዳሚ ተግባር አድርገው ማቅረባቸው በቀጥታ የምያስፈፅሙት አካል ተልኮ እንዳላቸው አመላካች ነው የሚሉ ወገኖች ተበራክተዋል።
ፓትራርኩ በዛሬው ንግግራቸው ”እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ሐዋርያት ሥራ 20፣28 የሚለው ቃል እና ”ለሁሉም እኩል አባት እሆናለሁ” ያሉትን እረስተው ለቤተክርስቲያን ልጆች ከለላ መሆኑ ቀርቶ ”ሽብርተኞች” እያሉ የምነቅፉትን አይዟችሁ ባይ ብቻ ሳይሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ማኅበረ ቅዱሳንን ”በቤተ ክርስቲያን የማይታወቅ ሀብት የሚሰበስብ እና ቤተክርስቲያን ወደ ሁለት የመክፈል አዝማምያ ያለው እና የቤተ ክርስቲያንን መመርያ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነ” የሚል ስም ለጥፈውበታል።
እርሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ የማኅበሩ ሥራ አመራር እና ሥራ አስፈፃሚ አባላት ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ስር ያለ ማኅበር እንደመሆኑ እና መተዳደርያ ደንቡንም እራሱ ያፀደቀው ሳይሆን ከቅዱስ ሲኖዶስ ተረቆ፣ተሰፍሮ፣ ተቆጥሮ እና በራሱ በቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ፀድቆ እና ተፈርሞ በተሰጠው ሕግ መሰረት የሚተዳደር መሆኑ ይታወቃል።
ይህም በመሆኑ የማኅበሩ ሥራ አመራር እና ሥራ አስፈፃሚ በተደጋጋሚ ከርሳቸው የስራ መመርያ ለመቀበልም ሆነ በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ለመመካከር በፅሁፍም ሆነ በቃል በተደጋጋሚ እንዲያናግሯቸው ጠይቀው አንድ ጊዜም ሳያናግሯቸው በአደባባይ ለዋልጌ አባት ነን ባይ ካድሬዎች ተቀምጠው ሲያሰድቡ እና እርሳቸውም ሲወቅሱ መሰንበታቸው ከፍተኛ ትዝብት ላይ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር በእዚህ ደረጃ ማውረዳቸው ብዙ ምዕመናንን አሳዝኗል ።በወጣቶች ዘንድ ደግሞ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።
አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ፓትራርኩ ጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ ለቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ ሳይነግሩ በጠሩት ህገ ወጥ ስብሰባ ላይ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ደፋ ቀና የሚሉ፣በእዚህም አገልግሎት አገልጋዮቹ በጎርፍ አደጋ፣በመኪና አደጋ እና ለብዙ ጤና መታወክ የተዳረጉ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ያሉበትን ማኅበረ ቅዱሳንን ”አልሸባብ፣አሸባሪ፣የቤተ ክርስቲያን ንብረት የሰበሰቡ፣ ወዘተ” እያሉ የግፍ ምላሳቸውን ያስረዘሙባትን ግፉአን ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ ”በሕይወቴ በእዚህን አይነት ደረጃ ሐሰት ነግሳ ስትፎክር፣ ሰው የሚባል ፍጡርም ሕዝብ የሚያውቀውን እውነት በአደባባይ በድፍረት በሐሰት ምላሱ ሲለበልባት አልተመለከትኩም ወደፊትም የምመለከት አይመስለኝም ” ሲል ተሰምቷል።
ሐሰት ማረፍያ ምላስ አገኘች።ሀገር ያወቃቸው ቀማኞች ”አባታችን” በሚል የማቆላመጫ ቃል ፓትራርኩ ፊት ንፁሃንን ባልሰሩት ወንጀል ከሰሷቸው።ፓትራርኩም ቅንድባቸውን አንድ ጊዜ ወደላይ ሌላ ጊዜ ወደታች እያደረጉ አዳነቁላቸው።በእዚህ ብቻ አላበቁም ጠርተው በአንድነት መመካከር፣ቤታቸንን እንዴት እናስተካክል ብለው መምከር ቅሬታቸውንም በግልፅ ጠርተው መግለፅ ያልፈለጉት ፓትራሪክ ከውስጥ ያሉትን እየገፉ ስለውጭው የተጨነቁ መስለው መናገራቸው ሚዛን አልደፋ ያለበት ምዕመን በቀጣዩ ጊዜ ስለሚወስደው የእራሱ እርምጃ የማሰላሰያ ጊዜው መሆኑን ያመነበት ይመስላል።
ከውስጥ ያሉትን የቤተክርስቲያን ነገር ያንገበገባቸውን ”አተላ እና ዘኬ ጋር የሚውሉ” ተብለው ሲሰደቡ ”ተዉ እንዲህ አይባልም” ብለው ከመምከር ይልቅ እንደ ተራ የመንደር ሙግተኛ ስድቡን ለማድነቃቸው ከፊታቸው ላይ መደበቅ አልቻሉም።”እድምያችንን’ ሸውደን’ እንድኖራለን” የሚሉ ‘የዶሮ ማነቅያ’ ሰፈር ቃላትን እንጂ የቤተ ክህነቱ ሽታ የሌላቸው ቀሚስ ለባሾች የተከበረውን የቅዱሳን መታሰብያ ”ዝክርን” ”ዘኬ” በሚል ፀያፍ ቃል ሲጠቀሙም አሁንም ፓትርያሪኩ ቅር አላላቸውም።
ይህንን የሰሙ ሌላ የጉባኤው ተሳታፊ አባት ከግፉአኑ ጉባኤ ከወጡ በኃላ እንባ ባቀረረ ፊታቸው ”በዓለማዊው ትምህርት መግፋታቸው፣ሱፍ መልበሳቸው የማኅበሩን አባላት ከዝክር ማራቅ ነበረበት? ሱፋቸውን አቧራ እንዳይነካው ”እፍ እፍ” እያሉ እንዲኖሩ ነበር ምኞታቸው? አልጋቸውን ትተው የማኅበረ ቅዱሳን ቢሮ መሬቱ ላይ ሰሌን አንጥፈው ተኝተው መስራታቸው ነው አሸባሪ ያስባላቸው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ለማጠቃለል አቡነ ማትያስ ከሰማያዊው አምላክ ይልቅ ለምድራውያኑ ገዢዎች ማድላታቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል።በአንድ ወቅት ”ይህ ማኅበር የሚሰራውን አውቃለሁ ወጣቶች ናችሁ በርቱ” ባሉበት አንደበት መንበረ ፕትርክናውን ሲይዙ እነ አባይ ፀሐዬ እና መሰሎቻቸው ለሚሏቸው የሚታዘዙ፣ ሐሰት ሲነገር የማያርሙ አባት መሆናቸውን አስመስክረዋል።በውስጥ ያሉትን ልጆቻቸውን እንዳይወጡ መጠበቅ ሲገባቸው ለመግፋት እና ለማስገፋት አለ የተባለውን የምድራችንን ያሰቅልልኛል ያሉትን ክስ አንጠፍጥፈው ያርከፈከፉትን በማድነቅ በልጆቻቸው ደረት ላይ በጭካኔ ሰክተውባቸዋል፣ አሰክተውባቸዋል።
እግዚአብሔር እረኞች ጳጳሳትን፣ካህናትን እና አገልጋዮችን ከውጭ ያሉትን በጎች በፍቅር እና በትምህርት ወደ ቤቴ አላመጣችሁም ብሎ የሚወቅስ እና የሚቀጣ ከሆነ ከውስጥ ያሉትን በጎች በሐሰት ፍርድ ወደውጭ እንዲወጡ (አይወጡም እንጂ ) የሚገፉትንማ በምን አይነት ፍርድ ይቀጣቸው? ለነገሩ ስንዝር ያክል ከቤተ ክርስቲያን የምያፈገፍግ የለም።ይልቁን ክንድ ያህል የበለጠ እንቀርባለን።የበለጠ የቤተ ክርስቲያንን ንብረት መተዳደርያቸው ያደረጉትን በግድም በውድም ይነቀሳሉ።በፊውዳል አስተሳሰብ ውስጥ እየዳከሩ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ መኖርን እና ለምድራውያን ገዢዎች እየሰገዱ መኖርን ቤተ ክርስቲያን አላስተማረችንም።
”እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ሐዋርያት ሥራ 20፣28
ጉዳያችን
ጥቅምት 13/2007 ዓም (ኦክቶበር 23/2014)
ምንጭ ዘ-ሐበሻ
No comments:
Post a Comment