• በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተያዙ ሌሎች 10 ያህል ዜጎችም ቀርበዋል
በሽብርተኝነት ተከሰው ማዕከላዊ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ የጋሞጎፋ ዞን አመራሮች ዛሬ መስከረም 23/2007 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ 8፡00 አራዳ ችሎት ቀርበው 28 ቀን ተቀጠረባቸው፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የጋሞጎፋ ዞን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ፍቃዱ አበበ እንዲሁም የዞኑ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ኢንጅነር ጌታሁን አርባምንጭ ውስጥ ወር ከ15 ቀን ያህል ታስረው የነበር ሲሆን ወደ ማዕከላዊ ከተዛወሩ 24 ቀናት በላይ እንደሆናቸው ታውቋል፡፡ አመራሮቹ ጥቅምት 21 ከሰዓት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ታሳዎቹ በቤተሰብ፣ በኃይማኖት አባትና በጠበቃ እንዳይጎበኙ የተከለከሉ ሲሆን ለመጎብኘት ፈቃድ አግኝተው የነበሩትም እንደገና እንደተገለከሉ ተገልጾአል፡፡ ለአብነትም የሰማያዊ ፓርቲ የጋሞጎፋ ዞን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ፍቃዱ አበበ አባት ከሳምንት በፊት ልጃቸውን እንዲጠይቁ ተፈቅዶላቸው ቢጠይቁም ከሳምንት በኋላ ዳግመኛ ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት ‹‹ከሳምንት በፊት ጠይቀሃል፡፡ ይበቃሃል!›› ተብለው መመለሳቸውን የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ ተገልጾአል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዛሬው ችሎት ቤተሰብ፣ የኃይማኖት አባት፣ ጠበቃና ሌሎችም ዜጎች እንዳይገቡ የተከለከሉ ሲሆን የህግ ጉዳይ ኃላፊው ድርጊቱ በታሳሪዎቹ ላይ እየጠፈጸመ ያለውን ህገ ወጥነት ያሳያል ብለዋል፡፡ ኃላፊው ጨምረውም ‹‹ችሎት በዝግ የሚታየው ታሳሪዎቹ ላይ ችግር ይደርሳል ተብሎ ሲታሰብ ነው፡፡ በአሁኑ ሁኔታ በችሎት ሊገባ የሚችለው ህዝብ በታሳሪዎቹ ላይ ችግር እንዳይደርስባቸው መንግስትን የሚጠይቅ እንጅ ችግር ሊያደርስ የሚችል አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ግን ታሳሪዎቹ ይህ ነው ተብሎ ባልተነገረ ምክንያት ጉዳያቸው በዝግ ችሎት እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ይህ ህገ ወጥነት ነው፡፡›› ሲሉ ሁኔታውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል አዲስ አበባ ውስጥ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተያዙና ለ4ኛ ጊዜ 28 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር ችሎት የቀረቡ 10 ያህል ግለሰቦች መኖራቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች አለብን ባሉት ስጋት ስለ ታሳዎቹ አያያዝና ሌሎች ጉዳዮች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነገረ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ማቅረብ አልቻለችም፡፡
ባለፈው ሳምንት ወደማዕከላዊ እየታፈኑ የሚወሰዱት ዜጎች ቁጥር መበራከቱንና 12 ያህል ዜጎች ከኦሮሚያ ታፍነው በማዕከላዊ እንደሚገኙ ከእነ ስም ዝርዝራቸው ማቅረባችን ይታወሳል፡፡
source Negre Ethiopia
No comments:
Post a Comment