Wednesday, October 15, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን ተካሔደብኝ ባለው የስም ማጥፋት ዘመቻ ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጠው ጠየቀ

·ኑፋቄአቸውና ሕገ ወጥ ጥቅማቸው እንዳይጋለጥ የሚሰጉ አካላት ያስተባበሩት ነው
· የብፁዓን አባቶች ስም እየተጠቀሰ የወረደው የስድብ ናዳ በእጅጉ አሳዝኖናል
· በፈቃዳችን በነፃ የምንፈጽመውን የአገልግሎት መብታችንን የሚፃረር ነው
· ግለሰቦቹ በስም ማጥፋት ዘመቻቸው ከቀጠሉ ማኅበሩ በሕግ ይጠይቃቸዋል
(በሰንደቅ ጋዜጣ ሪፖርተር)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር አገልግሎቱን የሚፈጽመው ማኅበረ ቅዱሳን፣ ፓትርያርኩ በተገኙባቸው ስብሰባዎችና ስለ ስብሰባዎቹ በሚዘግቡ ሚዲያዎች ላይ የማኅበሩ ስም እየተጠቀሰ የሚካሔድበትን የስም ማጥፋት ዘመቻ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥበት መጠየቁ ተገለጸ፡፡
Mhbere Kidusan
ማኅበሩ ጥያቄውን ያቀረበው ‹‹በሚዲያና በተለያዩ ስብሰባዎች የተከፈተው የስም ማጥፋት ዘመቻ አግባብ አለመኾኑን ስለመጠየቅ›› በሚል ርእስ ጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በአድራሻ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በግልባጭ ደግሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለኾኑት ለኹሉም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሰራጨው ደብዳቤ ነው፡፡
ላለፉት 23 ዓመታት በቅዱስ ሲኖዶስ በወጣለትና በተፈቀደለት ሕግና ደንብ መሠረት በቤተ ክርስቲያን ሥር ተዋቅሮ ኹለንተናዊ አገልግሎቷን ለመደገፍና ለማጠናከር የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ የገለጸው ማኅበሩ÷ በማያውቀው፣ ጥፋትም ካለ ተጠርቶ ባልተጠየቀበትና መልስ ባልሰጠበት ኹኔታ ፓትርያርኩ ባሉባቸውና በተለያዩ ጊዜያት በተጠሩ ስብሰባዎች የተፈጸምበት የስም ማጥፋት ዘመቻ መደጋገም ደብዳቤውን ለመጻፍ እንዳስገደደው ገልጧል፡፡
ማኅበሩ በደብዳቤው፣ በየስብሰባዎቹ የሕዝብ መገናኛ አውታሮች እየተጠሩ በማኅበሩ አገልግሎት ምክንያት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የኾኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በስም እየተጠቀሱ ተራ የስድብ ናዳ እንደወረደባቸው ገልጦ፣ ‹‹የስም ማጥፋት ዘመቻው እኛንም ኾነ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አባቶችንና ምእመናንን በእጅጉ አሳዝኖናል፤›› ብሏል፡፡ ስብሰባው የተቀረፀበትንና ‹‹አስነዋሪ›› ሲል የገለጸውን ቪዲዮ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሕጋዊ ድረ ገጽ ላይ በኢንተርኔት መለቀቁ፣ የቤተ ክርስቲያን አካላት ነን ከሚሉ ሰዎች የማይጠበቅና ‹‹ቤተ ክርስቲያንን ለጠላት መሳለቂያ ለማድረግ›› በጥፋት መልእክተኞች የተቀናበረ እንደኾነ አመልክቷል፡፡
ትውልዱ በእምነትና በዕውቀት ታንፆ በሞያው፣ በገንዘቡና በጉልበቱ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያገልግልና ሐዋርያዊ ተልእኮዋ እንዲፋጠን ማኅበሩ ያበረከተው አገልግሎትና ስኬት አኹን ላለበት ደረጃ የደረሰው በብፁዓን አባቶችና በሊቃውንት ምክርና ጸሎት ተደግፎ እንደኾነ ደብዳቤው አስታውሷል፡፡ የቤተ ክርስቲያን እምነቷና ሥርዓቷ ሳይበረዝና ሳይከለስ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ጥብቅና በመቆሙ፣ ከዚኽም አንጻር ‹‹አፅራረ ቤተ ክርስቲያን›› ናቸው ካላቸው አካላት የሚሰነዘሩ ‹‹የተሐድሶ ሽምቅ ደባዎች››ን ለቅ/ሲኖዶስ በማስረጃ አስደግፎ በማጋለጡና ማስረጃው ተጠንቶና ተረጋግጦ በመወገዛቸው ምክንያት በአገልግሎቱ ላይ ግልጽና ስውር ፈተናዎች እየተፈጠሩ መቆየታቸውን አስረድቷል፡፡
ማኅበሩ ‹‹አስነዋሪ›› ያለውና በተጠቀሰው መምሪያ ሕጋዊ ድረ ገጽ ላይ የተለቀቀው ቪዲዮ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ ‹‹የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልጸግ›› በሚል ርእስ የተካሔደውን የግማሽ ቀን ስብሰባ የሚያሳይ መኾኑ ታውቋል፡፡ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በጽሑፍ የተደገፈ ገለጻ የሰጡበትና በልዩ ጸሐፊያቸው የተመራው ይኸው ስብሰባ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች የተካፈሉበት ሲኾን የማኅበረ ቅዱሳንን ስም በመጥቀስ ማኅበሩ ‹‹ለአባቶች አይታዘዝም፤ መዋቅር ጠብቆ አይሠራም፤ ሒሳቡን አያስመረምርም፤ ዐሥራት ይሰበስባል፤ የፖሊቲካ ዓላማ አለው፤ አክራሪና አሸባሪ ነው…ወዘተ›› በሚሉ ሐሳቦች ዙሪያ ያተኮሩ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተፈጸመበት ደብዳቤው ዘርዝሯል፡፡
mahibere-kidusan
ማኅበሩ በስብሰባው ላይ ‹‹ስም ማጥፋት›› የተባለውን ድርጊት የፈጸሙበት ግለሰቦች ማንነት እንደየ ምክንያታቸው ሊለያይ እንደሚችል በተለያዩ ጊዜያት ያካሔዳቸውን ጥናቶች መነሻ በማድረግ አመልክቷል፡፡ እኒኽም ራሳቸውን ደብቀው የምንፍቅና ዓላማን ያነገቡና ማኅበሩ ለዓላማቸው መሳካት ዕንቅፋት እንደኾነባቸው የሚያምኑ፤ የቤተ ክርስቲያንን ንብረት በመጠቀም የግል ሀብት የሚያካብቱና ማኅበሩ ሊያጋልጠን አልያም ምቹ ኹኔታ ፈጥሮልን የኖረውን የሒሳብና ሌሎች አሠራሮች ክፍተት ሊደፍንብን ይችላል በሚል የሚፈሩ፤ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር በተማረ ኃይል በመሙላት ቦታ ያሳጣናል በሚል የሚሰጉ፤ ማኅበሩን በመቃወም ማኅበሩን ከሚጠሉ አካላት ጥቅም ለማግኘት ወይም በተሳሳተ መረጃ የማኅበሩን አገልግሎት ጥቅም ባለመረዳት የሚቃወሙ እንደኾኑ ነው ያስረዳው፡፡
የማኅበሩ አገልግሎት ችግር ይኖርበታል ተብሎ ቢታሰብ እንኳ ትክክለኛው አካሔድ ማኅበሩ በጉዳዩ ተጠርቶ፣ ተጠይቆና ችግሩ ተረጋግጦ እንዲያርም ማድረግ ነው ያለው ማኅበረ ቅዱሳን፣ የስብሰባው አካሔድ ‹‹ድብቅ ዓላማ አንግቦ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማደናቀፍ የተቀናጀ ሤራ ነው›› የሚያሰኝ ጥያቄ ሊያሥነሳ እንደሚችል ገልጧል፡፡ ‹‹ቅዱስነትዎም ይህ ኹሉ ሲኾን የማኅበሩን አመራር አካላት አንድም ቀን ጠርተው አለመጠየቅዎ እንደ ልጅነታችን አሳዝኖናል›› በማለትም ከስብሰባው ቀደም ሲል ከፓትርያርኩ ጋራ የውይይት መርሐ ግብር እንዲያዝለት በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባላገኘበት ኹኔታ መሠረት በሌላቸውና ከእውነትነት በራቁ የሐሰት ክሦች ‹‹የስም ማጥፋት ዘመቻ›› እንዲከፈትበት በመደረጉ ቅር መሰኘቱን አስታውቋል፡፡
በደብዳቤው እንደተብራራው፣ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱን ኹለንተናዊ አገልግሎት የሚያበረክተው፣ ከዋናው ማእከል አንሥቶ በሀገር ውስጥና በውጭ አህጉረ ስብከት በተዘረጋው መዋቅሩ ሲኾን ይኸውም ከየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ በመመካከርና መመሪያ በመቀበል የሚከናወን ነው፡፡ በየጊዜው ዕቅዱን በማሳወቅ በየስድስት ወሩ የዕቅድ አፈጻጸምና የሒሳብ ሪፖርት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያቀርባል፡፡ ሒሳቡን በየጊዜው በውስጥ ኦዲተር የሚያስመረምር ሲኾን በየዓመቱ ደግሞ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው ሕጋዊ የውጭ ኦዲተር አስመርምሮ ለሚመለከታቸው የቤተ ክህነቱ አካላት እያቀረበ ይገኛል፡፡ በዚኽም ከየትኛውም አካል ጥያቄ፣ ነቀፌታ ይኹን እርማት ቀርቦበት ባያውቅም ባቀረባቸው ሪፖርቶች የሚሰጠውን መመሪያ ተከትሎ አገልግሎቱን እያከናወነ ኻያ ሦስተኛ ዓመቱን ማስቆጠሩን በደብዳቤው ተመልክቷል፡፡
ማኅበሩ ‹‹እንኳን የራሱን የሒሳብ አያያዝ የቤተ ክርስቲያንዋ የሒሳብ አሠራር በሙሉ ዘመናዊና ለኦዲት የሚመች እንዲኾን የሚያግዝ ነው፤›› ያለው ደብዳቤው፣ ማኅበረ ቅዱሳን ዘመናዊና የኹለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት (double entry accounting system) የሚከተል በመኾኑ የቤተ ክህነቱን የነጠላ የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት ለመከተል እንደተቸገረ አልሸሸገም፡፡ ይኹንና የቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት ባስፈለገው ጊዜ ማኅበሩ በውስጥ ይኹን በውጭ ኦዲተር ያስመረመረውን ሒሳብ ማየት፣ በአካልም ተገኝቶ ማረጋገጥ እንደሚችል ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ማስታወቁን አውስቷል፡፡ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ወዶ ፈቅዶ አባቶችን ለማገልገል፣ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በፈቃደኝነት ለመደገፍ የተቋቋመ በመኾኑ የመታዘዝ ይኹን በሞያ የተደገፍ የሒሳብ አያያዝ የመተግበር ችግር የለበትም፤›› በማለት ለመዋቅሩ ያለውን ታማኝነት አጽንቷል፡፡
ማኅበሩ ‹‹ከምእመናን የዐሥራት በኵራት ገቢ ይሰበስባል›› በሚል በስብሰባው ላይ የተሰነዘረበትን ‹‹ስም ማጥፋት›› ፍጹም ሐሰት በማለት አጣጥሎታል፡፡ በሰጠው ምላሽም ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን የሚያከናውነው ከአባላቱ ገቢ በሚሰበስበው የኹለት በመቶ ወርኃዊ አስተዋፅኦ እንደኾነ፣ ለቅዱሳት መካናትና ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራሞች ደግሞ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ከገባሬ ሠናይ ምእመናን ድጋፍ እንደሚያፈላልግ ገልጧል፡፡ አገልግሎቱ የበጎ ፈቃድና የትሩፋት መኾኑን በተደጋጋሚ የገለጸው ማኅበሩ ከአባላቱ የሚሰበሰበው የኹለት በመቶ ወርኃዊ አስተዋፅኦ፣ እያንዳንዳቸው ለየሰበካቸው የሚጠበቅባቸውን ዐሥራት ወይም የሰበካ ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ የሚያበረክቱት እንደኾነ አረጋግጧል፡፡
ማኅበሩ ረብ የለሽ ሲል ውድቅ ካደረጋቸው የአንዳንድ ተሰብሳቢዎች ክሦች ውስጥ ግንባታውን የተጠናቀቀውንና የሚገለገልበትን የጽ/ቤት ሕንፃ የሚመለከት ይገኝበታል፡፡ ሕንፃው ያረፈበት ቦታ የተገዛው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የወቅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በሰጡት ውክልና መኾኑን ማኅበሩ በደብዳቤው ገልጦ፣ አባላቱ የወር ደመወዛቸውን በተደጋጋሚ በማዋጣት የገነቡትና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ስም በሕግ ተመዝግቦ የሚገኘውንና በማኅበሩ የሒሳብ ሪፖርትም በቋሚ ንብረትነት ተይዞ በየወቅቱ የሚገለጸውን ሕንፃ አመራሩ ይኹን አባላቱ የመጠበቅና የመገልገል እንጂ ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ የመስጠት ይኹን የመሸጥ ፍላጎት እንደሌላቸው አስታውቋል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀውና እየተመራበት በሚገኘው መተዳደርያ ደንቡ መሠረት ማኅበሩ በማንኛውም የፖሊቲካ አመለካከት ጣልቃ እንደማይገባና አገልግሎቱ ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳልኾነ ያረጋገጠው ማኅበሩ፣ የፖሊቲካ ዓላማ እንዳለው ለተሰነዘረው ውንጀላ መረጃው ቀርቦ በሚመለከተው አካል ሊታይና ሊጣራ እየቻለ የማይመለከታቸው አካላት ከሜዳ ተነሥተው ስም ለማጥፋት ሊጠቀሙበት እንደማይገባ አሳስቧል፡፡ ማኅበሩ ‹‹አክራሪ ነው፤ አሸባሪ ነው›› ማለትም ‹‹ውንጀላን ከማዳመቅ›› ያላለፈ ፋይዳ የሌለው መሠረተ ቢስ ክሥ ነው ብሏል፡፡
ማንም ግለሰብ ይኹን ኅብረተሰብ የፈለገውን እምነት ሊከተል እንደሚችል እምነቱ እንዳለውና የማንንም ሰብአዊና ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደማይነካ በአጽንዖት የገለጸው ማኅበሩ፣ ማንም የራሱን እምነት ከማራመድ አልፎ በሌላው እምነት ጣልቃ መግባት ስለሌለበት፣ ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ጣልቃ ገብተው የሚያውኩትን የተሐድሶ መናፍቃን የመከላከልና ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ ተልእኮዬን አጠናክሬ እቀጥላለኹ፤›› ብሏል፤ ‹‹እናቱን አውሬ ሲበላት ቆሞ የሚሥቅ ልጅ የለም›› ሲልም አቋሙን አስረግጧል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተጣለባቸው ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊነትና አባትነት በማኅበሩ ላይ የሚካሔደውን የስም ማጥፋት ዘመቻውን በአጽንዖትና በተረጋጋ መንፈስ እንዲመለከቱ ማኅበረ ቅዱሳን በአቤቱታው ተማፅኗል፡፡ ግለሰቦቹን በሕግ ለመጠየቅ ሊገደድ እንደሚችል ያስታወቀው ማኅበሩ ‹‹አስነዋሪና የቤተ ክርስቲያን ነን ከሚሉ አካላት የማይጠበቅ ነው›› ያለው ድርጊት ‹‹በቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን በፈቃዳችን ገንዘባችንን፣ ጉልበታችንንና ጊዜአችንን አስተባብረን የምናደርገውን ነፃና የፈቃድ አገልግሎት መብታችንን የሚፃረር ነው፤›› ሲል አስገንዝቧል፡፡ ኹኔታው በተመሳሳይ መልኩ ከቀጠለ ቤተ ክርስቲያንን እርስ በርሷ የማትናበብ፣ ማእከላዊ አሠራር የሌላት የሚያስመስልና ለአገልግሎቷ ዕንቅፋት የሚፈጥር በመኾኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዪን በጥንቃቄ መርምሮና አጣርቶ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቋል፡፡
ምንጭ ዘ-ሐበሻ 

1 comment:

  1. የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.

    ReplyDelete