Sunday, June 8, 2014

ሱዳን እና አወዛጋቢው የሞት ቅጣት አፍሪቃ /DW.DE/07.06.2014

«የፍትሁ አውታር የሞት ቅጣት ለተበየነባት የማርያም ያህያ ኢብራሂም ይስሀግ ጉዳይ ፣ የሚመለከታቸውን ወገኖች ሁሉ የሚያረካ መፍትሔ እንደሚያስገኝለት እናምናለን። » ነው የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ አህመድ ካርቲ ያሉት።
በሱዳን የሀገሪቱ ዜጋ የሆነችው የ27 ዓመቷ ሐኪም ማርያም ያህያ ኢብራሂም ይስሀግ በሀይማኖት ክህደት ተከሳ ከተያዘችበት ካለፈው ግንቦት ወር ወዲህ በወህኒ ትገኛለች። በሱዳን ሀይማኖትዋን አልቀይርም በማለቷ በካርቱም የሚገኘው የአል ሀጅ ዩሱፍ ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በስቅላት እንድትቀጣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፈረደባት እና በታሰረችበት ጊዜ ነፍሰ ጡር የነበረችው ማርያም በእስር ቤት አንድ ሴት ልጅን ተገላግላለች።
ጥፋቷ በፈርድ ቤቱ ብይን መሠረት። ጥፋቷ አንድ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነ ግለሰብ ማግባቷ ነው። በሸሪዓ በምትተዳደረው ሱዳን ውስጥ ይህ በሕግ የሚያስቀጣ ጥፋት ነው።
ማርያም ያደገችው ከኢትዮጵያዊ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን እናቷ ጋ ሲሆን፣ የምትከተለው የክርስትናን እምነት ነው። በዚህ እና ክርስትያን በማግባቷ የተነሳ ፍርድ ቤቱ መጀመሪያ ላይ 100 ጊዜ በጅራፍ እንድትገረፍ በይነ። ይሁንና፣ ወላጅ አባቷ ሙሥሊም መሆኑ በታወቀበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ ብይኑን በማጠናከር በስቅላትም እንድትቀጣ ወሰነ፦ ምክንያቱም፣ አባቷ ሙሥሊም በመሆኑ ማርያም በሱዳን ሕግ መሠረት እንደ ሙሥሊም ነው የምትቆጠረው። ብይኑን ያስተላለፉት የአል ሀጅ ዩሱፍ ፍርድ ቤት ዳኛ ማርያም ሀይማኖትዋን በመቀየር ሙሥሊም ከሆነች የግርፋቱ እና የሞቱ ቅጣት ሊሻርላት እንደሚችል አስታውቃለች። ማርያም ጥፋተኛ አለመሆንዋን በተደጋጋሚ በጠበቃዋ ኤሊ ሻሪፍ አማካኝነት ለፍርድ ቤቱ በማስታወቅ ይህንን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነችም።
በሸሪዓ ሕግ መሠረት፣ ማርያም ሕፃኑን ልጇን ለማሳደግ የሁለት ዓመት ጊዜ ከተሰጣት በኋላ ነው የሞቱ ቅጣት ተፈፃሚ የሚሆነው። አንድ ዓመት ከስምንት ወር የሆነው የመጀመሪያው ወንድ ልጇም ጉዳዩን የሚከታተሉት ዳኛ ልጁ የክርስትና እምነት ከሚከተለው አባቱ፣ ዳንየል ዋኒ ጋ ማደግ የለበትም ብለው በመከልከላቸው፣ በዚያው በወህኒ ቤት ውስጥ አብሯት ይኖራል።
Amnesty International
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የአብያተ ክርስትያን ተወካዮች እና በርካታ የሀገራት መሪዎች የሱዳን ፍርድ ቤት በማርያም ላይ ያሰለፈው ኢሰብዓዊ ያሉትን ብይን በጥብቅ አውግዘዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ብይኑን በሴቶች ላይ የተፈፀመ የአድልዎ አሰራር በሚል ነቅፎታል።
ብይኑ ከተላለፈበት ጊዜ አንስቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቃውሞ የተፈራረቀ ሲሆን፣ በሱዳን መዲና ካርቱም የሚገኙ የምዕራባውያት ሀገራት አምባሳደሮች ማርያም ያህያ ኢብራሂም ይስሀግ እንድትፈታ ለሱዳን መንግሥት ጥያቄ አቅርበዋል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ከጥቂት ቀናት በፊትበበርሊን ከሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ ካርቲ ጋ ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት የጋራ ግንኙነት ላይ ሀሳብ በተለዋወጡበት ጊዜ የሚርያምን ጉዳይ በማንሳት በወጣቷ እናት ላይ የተላለፈውን ብይን በጥብቅ በመንቀፍ የሱዳን መንግሥት ማርያምን እንዲፈታት ጠይቀዋል።
« የጀርመን ሕዝብ የሚርያም ጉዳይ ዘግናኝ እንደሆነበት እና ይኸው ብይን በሱዳን አኳያ በጀርመን ባለው አመለካከት ላይ ጥላ ማሳረፉ እንደማይቀር ግልጽ አድርጌአለሁ። ይኸው በሚርያም ኢብራሂም ላይ የተበየነው ኢሰብዓዊ የሞት ቅጣት እንዲሻር የምንጠብቅ መሆናችንን ግልጽ እንዳደረግሁ ተስፋ አለኝ። ወጣቷ ከባለቤቷ እና ከሁለት ልጆችዋ ጋ መደበኛ ኑሮ መምራት የምትችልበት ሁኔታ እንደሚፈጠርላትም ተስፋ አደርጋለሁ። »
Deutschland Deutsche Welle Review 2014 DW-Interview mit Frank Walter Steinmeier
ባለፈው ቅዳሜ አንድ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚንስትር ማርያም እንደምትለቀቅ ካስታወቀ ከሁለት ቀናት በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ፍርድ ቤት የሚቀርብለትን ይግባኝ ተመልክቶ እንደሚወስን በመግለጽ ማስተባበሉ ይታወሳል። የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ ካሩቲም በበርሊን ለጀርመናዊው አቻቸው እንዳስታወቁት፣ በሀገራቸው የሀይማኖት ነፃነት መኖሩን እና የሱዳን የፍትሕ ሥርዓት ለሚርያም ጉዳይ ትክክለኛውን መልስ ይሰጣል።
« የወጣቷ ወይዘሮ ጉዳይ ከሱዳን መንግሥት ጋ የሚያገናኘው ነገር የለም። በወይዘሮዋ ቤተሰብ ውስጥ ጥል ከተፈጠረ በኋላ፣ የባል ቤተዘመዶች ጉዳዩን ለፍርድ ቤት አቅረቡት፣ እዚህ ላይ መዳረሳቸው ያሳዝናል። የወጣቷ ወይዘሮ ጠበቆችን በብይኑ አንፃር የሱዳን ሕግ ስለሚፈቅድ የይግባኝ ማመልከቻ እንዲያስገቡ የሀገሬ መንግሥት ምክር ሰጥቶዋል። የሀገራችንን የፍትሕ ሥርዓት እናከብራለን። እና ሕግ አስፈፃሚው አካል በፍትሑ ሥርዓት ላይ ጣልቃ ሊገባ አይችልም። የፍትሑ አውታር ለዚህ ጉዳይ ፣ የሚመለከታቸውን ወገኖች ሁሉ የሚያረካ መፍትሔ ራሱ እንደሚያስገኝለት እናምናለን። የፍትሑ አካል የይግባኝ መመልከቻውን እንደሚቀበል ተስፋ አለን። በሱዳን የሚሰራበት ሕገ መንግሥት የሀይማኖት ነፃነትን እንደሚፈቅድ ላረጋግጥ እፈልጋለሁ። ይህ ገሀድ ደግሞ የሞት ቅጣት ለተፈረደባት ወጣት ወይዘሮ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
Ali Ahmed Karti Außenminister Sudan
ማርያም በነፃ ትለቀቃለች አትለቀቅም በሚል ሰሞኑን የተሰማው ተፃራሪ ዜና በዚሁ ብይን ሰበብ ዓለም አቀፍ ቁጣ የተፈራረቀበት የሱዳን መንግሥት የሚገኝበትን ግራ መጋባት የሚያንፀባርቅ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ገለጹ። ሱዳናዊው ተንታኝ ኻሊድ አል ቲጃኒ አል ኑር እንዳስረዱት፣ የካርቱም መንግሥት የሞቱ ቅጣት በሚደግፉት እና በነፃ ትለቀቅ በሚል ከውጭ ባረፈበት ግፊት በአሁኑ ጊዜ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። ለዚሁ ተፃራሪ ዜና ትኩረት ያልሰጡት አንዱ የሚርያም ጠበቃ፣ አሊ ኤልሻሬፍ ደንበኛቸው ጥፋተኛ እንዳልሆኑ በድጋሚ በማስታወቅ ወይዘሮዋን ለማስፈታት ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ነው ያመለከቱት።
« ማየት የምንፈልገው ማርያም ከእስር ቤት ተፈታለች የሚል የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው። ምክንያቱም አንድም ጥፋት አልፈፀመችም፣ በትዳሯ ላይ አልማገጠችም፣ ሀይማኖትዋንም አልካደችም። ትዳሯ ሕጋዊ ነው። እና የሱዳን መንግሥት በፈረመችው አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረትም፣ በዚች ሀገር ውስጥ ማንም በሚከተለው ሀይማኖት የተነሳ ክትትል ሊያርፍበት አይገባም። »
Symbolbild Justitia Justizia
በጀርመን ለውሁዳን ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና አድልዎ ያረፈባቸው ቡድኖች የሚሟገተው ድርጅት መሪ የሆኑት ኡልሪኽ ዴልዩስ ግምት፣ ሚርያም በነፃ ትለቀቃለች በሚል የተሰማው ዜና የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሊ ካርቲ ሰሞኑን በአውሮጳ ያደረጉትን ጉብኝት ለማመቻቸት ተብሎ ሆን ተብሎ የተደረገ ሳይሆን አልቀረም። በሚርያም ላይ የተበየነው የሞት ቅጣት የሱዳንን ገፅታ ስለሚያበላሽ ተግባራዊ መሆኑን ያጠያየቁት ኡልሪኽ ዴልዩስ ሸሪዓን በምትከተል ሱዳን ውስጥ ነፃ የፍትሕ አውታር አለመኖሩን አመልክተዋል።
« ሱዳን የሕግ የበላይነት የሚከበርባት ሀገር አይደለችም። በዚችው ሀገር ነፃ የፍትሕ አውታር የለም። የፍትሑ አውታር ካለፉት ዓመታት፣ እንዲያውም ፣ ካለፉት 25 ዓመታት በላይ ወዲህ፣ በተለይም፣ ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን አል በሺር በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የአጥባቂ ሙሥሊሞች ተፅዕኖ ይታይበታል። »
አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ
 
---------------------------------

AUDIOS AND VIDEOS ON THE TOPIC

  • ቀን 07.06.2014
  • source www.dw.de DW(Amharic)

No comments:

Post a Comment