በነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ የወጣ
እንደ ህዳሴው ግድብ በብርቅ ለምመለከትሽ፤እንደ መለስ ራዕይ ሰርክ ከአፌ ለማትጠፊው፤እንደትራንስፎርሜሽን እቅዱ ዘወትር ስምሽን ለማነሳሳሽ፤እንደ ቀለበት መንገዳችን ሁሌም በአይኔ ውል ለምትይው፤እንደ ሞባይሌ ኔት-ወርክ ፍቅርሽ የሚያንገላታኝ፤እንደ ቧንቧችን ውሃ ሄድ መጠት የሚለው ናፍቆትሽ፤እንደ ከተማችን መብራት ብልጭ ድርግም የሚለው ምትሃታዊ ውበትሽ፤እንደ ቦሌው መንገድ የተንጣለለው ደረትሽ፤እንደ አዋሽ ባንክ ህንጻዎች በትይዩ የተገተሩት ጡቶችሽ፤እንደ ቤተ መንግስት ፓውዛዎች የሚያበሩት አይኖችሽ፤እንደ ባቡሩ ሀዲድ የተጥበዘመዘው ወገብሽ፤እንደ ኮንዶሚኒየም ህንጸዎች በረድፍ የተደረደሩት ጥርሶችሽ፤እንደ ኪራይ ሰብሳቢ ቦርጭ ወጣ ያለው ዳሌሽ፤እንደ ሀገራችን ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባው ተረከዝሽ፤ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ እመርታ ያስመዘገበው ውበትሽ በህልሜም በውኔም እየመጣ ሲረብሸን ይህቺን ደብዳቤ ሰደድኩልሽ፡፡
ውዴ ሰላምታየ ካለሁበት ቦታ እንደ ትራንስፎርሜሽኑ ባቡር ፈጥኖ እንደሚደርስሽ ተስፋ አደርጋለው፡፡ መቸም አውሮጵላናችን ጠልፎ ጀኔቭ ላይ እንዳሳረፈው ጸረ-ልማት ወፈፌ ፓይለት ደብዳቤየን የሚጠልፍ እረዳት ፖስተኛ እንዳማይኖር እተማመናለው፡፡ለዚህ ደግሞ አሁን ያለው የደህንነታችን ጥበቃ እጅግ አመርቂ በመሆኑ የደብዳቤው መጠለፍ አያስጨንቀኝም፡፡ደህንነትሽ እንዴት ነው? ጤንነትሽስ? ለነገሩ እንደው ለመጠየቅ ያክል ነው እንጂ ጤንነትሽ እንኳን ረጅም እድሜ ለልማታዊ መንግስታችን ይስጥልን እንጅ በየ አምስት መቶ ሜትሩ ጤና ጣቢያ ስለገነባልን ምንም አይነት የጤና እክል እንደማይገጥምሽ ሳላውቅ ቀርቸ አይደለም፡፡
ውዴ ከዚህ ስልጠና ከገባው ቀን አንስቶ የምማረው የአመራርነት ስልጠና ሀገራችን በአንዴ ከድህነት ሊያላቅቅ የሚችልና በሚቀጥሉት አስር አመታት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ዘንድ ሊያሰልፍ የሚችል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የሚገርምሽ አሰልጣኞቻችን ከታዋቂው የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የመጡ ምጡቅ አዕምሮ ያላቸው በመሆኑ የሚሰጡን ትምህርት አጃይብ የሚያስብል ነው፡፡ እውቀታቸው ሞልቶ አለመፍሰሱ የተፈጥሮን ስራ እንድናደንቅ ያደርገናል፡፡ ፍቅሬ ስልጠናው እየተገባደደ ስለሆነ በቅርብ እመጣለው ብየ አስባለው፡፡
የእኔ እና ያንቺ ፍቅር በየ አመቱ የሚያስመዘግበው እድገት ከጎረቤት ሀገራት ፍቅረኛሞች ጋር ሲነጻጸር 11.2 ብልጫ እንዳለው ይገመታል፡፡ ይህ ተሞክሯችን በደንብ ከተቀመረ የጎረቤት ሀገራት ፍቅረኛሞች የልምድ ልውውጥ የሚያገኙበትን አሰራር ሊያስዘረጋ የሚችል ነው፡፡ ፍቅራችንም ለተከታታይ አስር አመት ከፍተኛ የሆነ የማይዋዥቅ እድገት አስመዝግቧል፡፡ በቅርቡም ሞዴል ፍቅረኛሞች የሚል በአይነቱ ልዩ የሆነ ሽልማት ጸሀዩ መንግስታችን ሊያበረከትልን እንደሚችል ወሬ ደርሶኛል፡፡ በዚህ ደግሞ ኩራት ሊሰማሽ ይገባል፡፡ምንም እንኳን እንደ ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ህብተተሰቡ ገንዘቡን አዋጥቶ አይገንባው እንጂ የፍቅራችን ሌጋሲ ለትውልድ የሚተላለፍ ነው ብየ መናገር እችላለው፡፡ ይህ ደግሞ ባለ ራዕይ መሪያችን ሲያስተምሩን የነበረው የፍቅር ሌጋሲ ሳይሸራረፍ መቀጠሉን አማላካች ነው ፡፡
አብዮታዊ መራሹ ፍቅራችን በደንብ አድርጎ ፍሬ ያፈራ ዘንድ ቀጣይ አርባ እና ሀምሳ አመት ሊያስፈልገን እንደሚችል ትዘነጊዋለሽ ብየ አላስብም፡፡ አንዳንድ የኒዮሊበራል ተላላኪዎች በእኔና በአንቺ መካከል ያለውን የፍቅር እድገት ለማደናቀፍ ሲታትሩ መመልከት የተለመደ ነው፡፡እነዚህን የፍቅር እንቅፋቶች በቅርቡ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለፍርድ እንደምናቀርባቸው በዚህ አጋጣሚ ቃል እገባልሻለው፡፡ በዚህ ሀሳብ አይግባሽ !! አይደለም ምድር ላይ መንግስተ ሰማያት እንኳን ቢገቡ ሊያመልጡን አይችሉም፡፡የእኛን ፍቅር ለመበጥበጥ፤ ለማደናቀፍና ብሎም ለመናድ የተንቀሳቀሱትን ፤ አደናቃፊዎችን የደገፉትን እንዲሁም ለመንቀሳቀስ ያሰቡትንም ሁሉ በጸረ-ፍቅር አዋጁ መሰረት እስከ ሞትና የእድሜ ልክ እስራት ሊያስፈርድ የሚችል ደርዘን ሙሉ መረጃ አግኝተንባቸዋል፡፡ እነዚህ ጸረ-ፍቅር ሰዎች የእኛን ፍቅር ተጠቅመው አላግባብ የሆነ ድብቅ አጀንዳቸውን ሊያስፈጽሙ ሲሉ በህብረተሰቡ ጥቆማና በደህንነታችን ክትትል ሊደረስባቸው ተችሏል፡፡የእነዚህን የከሰሩ ስብስቦች ሴራም በቅርቡ ፍቅራዊ-ሀረካት በሚል አርዕስት ዶክመንተሪ ሰርተን በቴሌቪዥን እናጋልጣቸዋለን፡፡
ውዴ እኔና አንቺ እኮ በሀገራችን የሰፈነውን የብሄር ብሄረሰቦች የወንድማማችነት ፍቅር የሚያስንቅ የአብሮነት ትስስር አለን፡፡ ፍቅራችን ሰንደቅ አላማው መሃል ላይ ያለው ኮከብ እንደሚያስተምረው ተከባብሮ የመኖርን አላማ ያነገበ ነው፡፡ ውዴ እንደምታውቂው በሚቀጥለው ወር የፍቅራችን 10ኛ አመት በዓት በታላቅ ዝግጅት ሞቅ ደመቅ ባለ ሁኔታ ይከበራል፡፡ የሚገርምሽ የአሁኑን የፍቅር በዓላችን ለየት የሚያደርገው የሕዳሴው ግድብ በተጀመረበት ሶስተኛ አመት በመሆኑ፤ባለራዕዩ ፤አርቆ አሳቢው፤ አባይን የደፈረው መሪያችን የተሰውበት ሁለት አመት ሊሆነው ሁለት ወር ሲቀረው መሆኑ፤ጀግናው አብዮታዊው ሰራዊታችን የደርግን ሰራዊት ድል ባደረገበት 23ኛ አመት መሆኑ፤እንዲሁም ብዙ ልማታዊ ስራዎችን ልንሰራ ባሰብንበት ሰዓት መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡
ውዴ ስልጠናየኝ ጨርሸ እንደመጣሁ የአንድ ቀበሌ ሊቀመንበር ሆኘ ስለምመደብ ከእኔና አንቺ በተጨማሪ ለዘመዶቻችን ሁሉ የቀበሌ ቤት እናድላቸዋለን፡፡ በመሆኑም ለቤተሰቦችሽ ባለ ሁለት ክፍል የቀበሌ ቤት ስለምንሰጣቸው እኔን እንዳታገቢ ሲዶልቱት የነበረውን ሴራቸውን ያከሽፍልናል፡፡ ይገርምሻል አሰልጣኞቻችን ስለ ታማኝነት ባስረዱበት ወቅት ስንቱ አስመሳይ ራሱን ሲጠራጠር እኔ የአንቺ ባል ግን በኩራት ደረቴን ነፍቸ ዘና ብየ ነበር አዳምጥ የነበረው፡፡መቸም ለድርጅቴ ያለኝን ታማኝነት አንቺም ታውቂዋለሽ ብየ እገምታለሁ፡፡ እንደ እኔ አይነት ታማኝ የድርጅታችን አገልጋይ በማግባትሽም ኩራት ሊሰማሽ ይገባል፡፡ ውዴ ነገ ከፍተኛ የሆነ የውይይት መርሃ ግብር አለብኝ፤ስለሆነም ለውይይቱ ተወዳጇን አዲስ ራዕይ መጽሄትን ማንበብ ስለሚጠበቅብኝ ደብዳቤየን በዚህ ለማጠናቀቅ እገደዳለው፡፡ ያንቺና የድርጅቴ ታማኝ ሆኘ እስከመጨረሻው እንደምዘልቅ እገልጽልሻለሁ፡፡ ቻው……………
አባይ ይገደባል!! የመለስ ሌጋሲም ሳይሸራረፍ ይቀጥላል!!!
ኢህአዲጋዊ የፍቅር ደብዳቤ!!!
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ
No comments:
Post a Comment