በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወርሃ ግንቦት የተለየ ሥፍራ አላት።ከወርሃ ግንቦት ግንቦት ሰባትንና ግንቦት ሃያን በተለይ አንረሳቸውም። ግንቦት ሃያ ጎጠኝነት፤ እኔ ብቻ ባይነት፤ አስመሳይነት ፤ስግብግብነት እና ሌብነት ተደምረው የወለዱት ቡድን ብሶት ወለደኝ ብሎ በትረ ስልጣኑን የተቆጣጠረበት ቀን። ብሶት ወለደኝ ብሎ ግንቦት 20 ዕለት በትረ ስልጣኑን የጨበጠው ቡድን ግንቦት ሰባት ዕለት ብዙ ህፃናትን፤ ብዙ ወጣት ሴትና ወንዶችን፤ ብዙ አረጋዊያንን ገድሎና በደም ሰክሮ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ለማዳፈን የሞከረበት ቀን። አዎን ግንቦት ሃያ የኢትዮጵያ ጠላት መሆንን የመረጠ ጉጅሌ ለስልጣን የበቃበት ታሪካዊ ቀን።
ህወሃትን ስልጣን ይዞ አገርን ሊመራ እንደሚችል የፖለቲካ ተቀናቃኝ ድርጅት አድርጎ ማየት ከስህተት ይጥላል። ስህተቱ ደግሞ ለነፃነት፤ ለእኩልነት እና ለፍትህ የሚደረገውን የትግል አቅጣጫ ያዛባል። የትግሉ አቅጣጫ እንዳይዛባ ህወሃት የህዝብ ጠላት መሆንን የመረጠ ጉጅሌ መሆኑን አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል። ህወሃትን ከህዝብ ጠላትነት ዝቅ አድርጎ ማየት በማንኛውም መለኪያ ስህተት ነው።
በዚህ ወቅት ጉጅሌው ህወሃት የህዝብ ጠላት መሆኑን የሚጠራጠር ኢትዮጵያዊ እውነቱን ለመቀበል የማይፈልግ፤ ለነፃነት የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል የማይፈልግ ሰነፍ አልባሌ ሰው ነው። እንዲህ ዓይነት ሰነፍ ሰዎች ጉጅሌዎቹ ሠላም ያመጣነው እኛ ነን ሲሉ ያምኗቸዋል። ልማትም ከመቼውም ግዜ በላይ ለኢትዮጵያ ያመጣንላት እኛ ነን ሲሉ እውነት ነው ይላሉ። እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትበታተናለች ብለው ሲደነፉም ይደነግጣሉ።እንዲያውም ህወሃቶች ከሌሉ ማን አገሪቷን ሊመራት ይችላል ብለው ለመከራከር ይዳዳቸዋል።
ህወሃቶች በማንኛውም መስፈርት አገር ለመምራት ብቃት ያላቸው ቡድኖች አይደሉም። አገር የሚመራ ኃይል ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነትን ለማጥፋት ሳይታክት አይሠራም። ጉጅሌዎቹ ከተመሸጉባቸው የጎሳ ፖለቲካ ክበብ ውስጥ ሁነው ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነትን ለማጥፋት ያልፈነቀሉት ድንጋይ፤ያልቧጠጡት ዳገት የለም። ጉጅሌዎቹ የማያውቁት አንድ እውነት ግን ኢትዮጵያዊ ማንነት በፀና መሠረት ላይ የቆመ ተሸርሽሮ የማያልቅ ፅኑ ዓለት መሆኑን ነው። ግንቦት ሃያ ዕለት ስልጣኑን የጨበጠው ጎጠኛው ነፃ አውጪ ቡድን ከሃያ ዓመት በኋላም ሥሙን እንኳን ሳይቀይር “እኔ ካልገዛኋችሁ ኢትዮጵያ ትበታተናለች” እያለ ያሟርታል። ህወሃትን የህዝብና የአገር ጠላት የሚያሰኘው አንዱ አንጓም ይሄው ነው።”እኔ ያልኩት ካልሆነ አገሪቷን አፈርሳታለሁ፤ የጎሳ ግጭት ተነስቶ ህዝቡ እርስ በርሱ እንዲተላለቅ አደርጋለሁ” እያለ መዛቱ። እንግዲህ “እኔ ከሌለው አገሪቷን አፈርሳታለሁ” የሚል ቡድን በምን መሥፈርት አገርንና ህዝብን መርቶ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያደርሳት እንደሚችል “ህወሃቶች ከሌሉ አገሪቷን ማን ይመራታል” ብለው የሚጨነቁ ሰዎች መልሰው መልሰው ራሳቸውን እንዲጠይቁ እንመክራቸዋለን። ለማንኛውም ከግንቦት ሃያ መራራ ፍሬዎች መካከል አንዱ “እኔ ያልኩት ካልሆነ አገሪቷን እበትናታለሁ” የሚል ክፉና ጎጠኛ ጉጅሌ በአገራችን ጫንቃ ላይ መጫኑ ነው።
ጉጅሌዎቹ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ልማት አመጣንም እያሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይጮኻሉ።የህወሃቶች ድንቁርና ልማትን ከሰው ልጅ ሠላምና ደስታ ይልቅ ዛሬ ታይቶ ነገ በሚጠፋ ግዑዝ ቁስ መለካታቸው ነው። ይህ ግዑዙ ቁስ ለሠው ልጆች ሠላም፤ ደስታና እፎይታ ካላስገኘ ልማት ሊባል አይቻልም። ጉጅሌዎቹ ልማትን የሚለኩት ከህዝቡ ደስታ፤ ሠላም እና የእለት ጉርሳቸውን ያለጭንቀት አግኝተው ማደር ከመቻላቸው አንፃር ሳይሆን ራሳቸው ዘርፈው ካካበቱት ሃብት አንፃር ነው። እነርሱ ዘርፈው ብዙ ሃብት ስላከማቹና ስም አጠራሩን እንኳ የማያውቁትን መጠጥ በብዙ ሺህ ብር ገዝተው መጠጣት ስለቻሉ አገሪቷ ያደገች ይመስላቸዋል። ጉጅሌዎቹ እንደሚሉት አገሪቷ በልማት ጎዳና ላይ እየተጓዘች ቢሆን ኑሮ ወጣቱ ትውልድ በአገሩ ተስፋ ቆርጦ የባእድ አሸከርና ገረድ ለመሆን ስደትን የሚመርጥ ባልሆነ ነበር።ጉጅሌዎቹ አገሪቷን ከተቆጣጠሩ ከግንቦት ሃያ 1983 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ መሰደድን የማይመኝ ዜጋ አይገኝም። መንኩሴ፤ ሼኽ፤ ፓስተር፤ ገበሬ፤ ምሁር፤ ተማሪ ሁሉም የሚሰደድባት አገር ኢትዮጵያ ነች። ግንቦት ሃያ ካተረፈልን ፍሬዎች መካከል ሊጠቀስ የሚችለው የዜጎች ያለገደብ መሰደድ ነው። ልማታዊ ነን ብለው ራሳቸውን የሚጠሩት ጉጅሌዎቹ ዜጎች እጅግ አደገኛ በሆነ በርሃና ባህር ውስጥ አልፈው ከቀናቸው አሽከርና ገረድ መሆንን ለምን እንደሚመርጡ መልስ የላቸውም።
“የኢኮኖሚ ልማት … በሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት፣ በዋና ዋና መሠረተ ልማት አቅርቦቶች፣ በአካባቢው ገበያ በሚኖር ተወዳዳሪነት፣ በምቹ የተፈጥሮ አካባቢ (ኢንቫይሮመንት)፣ በማኅበራዊ መስተጋብር፣ በጤና፣ በደህንነት፣ በትምህርት እና በመሳሰሉ ነገሮች እድገት ማምጣትን ያካትታል።ብለው ልማትን የሚተረጉሙ ሊሂቃን አሉ።”
የጉጅሌዎቹ ልማት በእነዚህ መሥፈርቶች ቢለካ ተስፋ በሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ዜጎች ብዛትና ዓይነት ደህና ምስክር ነው። የጉጅሌዎችን የህዝብ ጠላትነት ከሚያሳዩ እውነታዎች መካከል ሌላው ገፅ ይሄው ዜጎችን በሙሉ ተስፋ አስቆርጦ ለስደት የሚዳርግ ሥርዓት በአገሪቷ ውስጥ እንዲዘረጋ ማድረጋቸው ነው።
ህወሃቶች የህዝብ ጠላት መሆንን የመረጡ ጉጅሌዎች ናቸው ስንል ሌላው መገለጫቸው ህዝቡን ሠላም ማሳጣታቸው ነው። ጉጅሌዎቹ እኛ ከመጣን በኋላ አገሪቷ ሠላም ወረደላት፤ የህዝቡም አንድነት ከመቸውም ግዜ በላይ ተጠናከረ እያሉ ያላዝናሉ።
በእውኑ ኢትዮጵያችን ውስጥ ሠላም አለን? ህዝቦቿስ ከመቸውም ግዜ በላይ በኢትዮጵያዊነት ስሜት አብሮ የመኖር ዝንባሌ እያሳዩ ነውን ? መልሱ ግልፅ ነው። ሠላም የለም፤ ኢትዮጵያም የዜጎቿ አገር አልሆነችም።
ከግንቦት ሃያ መራራ ፍሬዎች መካከልም ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት እና እትብታቸው ከተቀበረበት መንደር ውጡና ወደ አገራችሁ ሂዱ ተብለው ከነ ቤተሰቦቻቸው ሜዳ ላይ ተበትነው ማየታችን ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ቁም ነገር ነው። ጉራፋርዳ አማራ ተብሎ ለሚጠራው ዘውጌ ማህበረሰብ አገሩ ካልሆነ የአማራ አገሩ የት ነው? ከቤንሻንጉል አማሮች ውጡ ሲባሉ ኢትዮጵያዊነት ከወደየት አለ? በአዲስ አበባ አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞ ገበሬዎች ተፈናቅለው የትም ተጥለው የጉጅሌው አባላት እና ደጋፊዎች መሬታቸውን ሲቀራመቱ ህግ የት ደረሰ? እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች የግንቦት ሃያ ፍሬዎች መሆናቸውን መርሳት አይገባም።
እንግዲህ ጉጅሌዎቹ ነጋ ጠባ “ሰላማችን፤ ሰላማችን” እያሉ የሚያላዝኑት፤
- ዘረኝነት የፓለቲካ ሥርዓቱ መታወቂያ ሆኖ እያለ፤
- ኢፍትሃዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እና ሙስና የሥርዓቱ መለያ ሆነው እያሉ፤
- ፍትህ ተዋርዳ ፍርድ ቤቶች ገዢዎች የሰጡት ቅጣት ማሳወቂያ በሆኑበት፤
- በዘርና በፓለቲካ ወገንተኝነት የተዋቀሩት የጦር ሠራዊት፣ የፓሊስና የስለላ ተቋማት ኢትዮጵያዊያንን ማጥቂያ ሆነው እያሉ፤
- በፓለቲካ እምነታቸውና በሀይማኖቻቸው ምክንያት ታስረው ሰቆቃ እየተፈፀማቸው ያሉ ወገኖቻችን ብዛት በአስደጋጭ ፍጥነት እየጨመረ ባለበት ሁኔታ፤
- ሚሊዮኖች ድሀ ገበሬዎች ከይዞታቸው እየተፈናቀሉ በገዛ አገራቸው ስደተኛ የሆኑበት ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን እያየን፤
- ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች ቤተሰቦቻቸውን የሚመግቡት ቁራጭ መሬት አጥተው እያለ ሰፋፊ ለም መሬቶች ለውጭ ባለሀብቶች በገፍ እየተሸጠ ባለበት ሁኔታ፤
- የወያኔ ሹማምንት በሀብት ላይ ሀብት እየጨመሩ ከተሞችን በሕንፃዎች ሲያሽቆጠቆጡ ዛንጋባ እንኳን አጥተው በረንዳ ላይ የሚያድሩ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን በገዛ ዓይኖቻችን እያየን፤
- ከፍተኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች ለሚጠብቃቸው የሥራ እድል ባይማሩ ኖሮ ይበልጥ ተመራጭ ይሆኑ የነበረበት የመሆኑ አሳዛኝ ሐቅ እያየን፤
- ወጣቶች በተስፋ እጦት ከአገር ሲሰደዱ በባህር ሰጥመው አሊያም በበረሃ ንዳድ ተቃጥለው እያለቁ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት፤
- አብዛኛው ሰው ቁርስ፣ ምሳና ራቱን ደርቦ “ቁምራ” እየበላ ስለ ተከታታይ ዓመታት 11.6 % ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት መስማት ግዴታ የሆነበት የጉድ አገር ሆኖ እያለ፤
- የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃና የአረብ አገራት እስር ቤቶች በኢትዮጵያዊያን ወንዶችና ሴቶች ተሞልተው እያለ፤ እና
- ወያኔ የሚያደርሰው ግፍ ፅዋውን ሞልቶ በፈሰሰበት በአሁኑ ወቅት ነው “ሰላማችን፣ ሰላማችን” እያሉ የሚያደነቁሩን።
ይኸ ሁሉ ኢ-ፍትሃዊነት ባለበት ሊኖር የሚችለው ሰላም አሉታዊ ሰላም ያውም ተቃውሞን በጉልበት በመደፍጠጥ የሚገኘው አደገኛ አሉታዊ ሰላም ብቻ ነው።በጉልበት የሚመጣ አሉታዊ ሰላም ለአገራችን አይበጃትምና የወያኔን ሰላም መቃወም ተገቢ ነው። ከብዙ አገሮች ልምድ እንዳየነው አደገኛው አሉታዊ ሰላም ከመኖሩ አለመኖሩ ይሻላል። የወያኔ ሰላምም ለኢትዮጵያችን የሚበጅ አይደለም።
የግንቦት ሃያ መራራ ፍሬዎች ብዙ ናቸው።ግንቦት ሃያ የህዝብ ጠላት መሆንን የመረጠ ጉጅሌ የአገሪቷን ስልጣን የተቆጣጠረበት ቀን ነው።ከዚህ ቡድን የሚጠበቅ መልካም ፍሬ የለም። ግንቦት ሰባት የፍትህ፤ የነፃነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ግንቦት ሃያ ቀን የአገሪቷን ስልጣን የተቆጣጠረው የጉጅሌው ቡድን ከህግ በታች እንዲውል ለማድረግ ትግላችንን አጠናክረን እየቀጠልን ነው። የትግላችን መዳራሻም የህዝብ ጠላት መሆንን የመረጠ ቡድን መሪዎች እጅ ተይዞ ለፍርድ እስከሚቀርብ ድረስ ይዘልቃል። ይሄም ያለምንም ጥርጥር ይሆናል።
እናሸንፋለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
ምንጭ www.ginbot.org
No comments:
Post a Comment