Monday, June 30, 2014

ዞን ዘጠኞችን የእምነት ክህደት ቃል በኃይል አስፈርመዋቸዋል (ጽዮን ግርማ)

መዝገቦቹ መልሰው ተቀራረቡ
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በስድስቱ ጦማሪያንና በሦስቱን ጋዜጠኞች ላይ የፌደራል ፖሊስ የተለያየ ምክንያት እየሰጠ ቀጠሮ የሚያራዝመውን ሁለት መዝገብ አንዴ ሲያቀራርበው መልሶ ደግሞ ሲያራርቀው ቆይቶ አሁን ደግሞ መዝገቦቹን መልሶ አቀራርቧቸዋል፡፡እስረኞቹ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ኹኔታ ፖሊስ ያረቀቀውን የእምነት ክህድት ቃል ተገደው እንዲፈርሙ አድርጓቸዋል፡፡
የሦስቱ ብሎገሮች አቤል ዋበላ፣በፍቃዱ ኃይሉና ማኅሌት ፋንታሁን ቀጠሮ ለዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲቀርቡ የሚል የነበረ ሲኾን ከጠዋት ጀምሮ ችሎቱን ለመታደም የመጣውን ቤተሰብ፣ጓደኞቻቸው፣ጋዜጠኞች፣ዲፕሎማቶችና የወጣቶች ደጋፊዎች በአጠቃላይ ወደ ሦስት መቶ የሚጠጋ ሰው ከችሎት ውስጥ የሚሰማውን አዲስ ነገር ለመጠበቅ በግቢው ውስጥ ቆመው ነበር፡፡ ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ የእስረኞቹ ጠበቃ አቶ አመኃ መኮንን ተጠርተው የመዝግብ ቤት ጸሐፊዋ ስለሌለች ችሎቱ ለከሰዓት በኋላ እንደተዛወረ ይነገራቸዋል፡፡ እርሳቸውም ችሎቱን ለመከታተል ለቆመው ሰው መልዕክቱን ያስተላልፋሉ፡፡ ጥቂት ሰዎችም ይህን መልዕክት ሰምተው ግቢውን ለቀው ይወጣሉ ብዙኃኑ ግን እዛው እንደቆሙ መጨረሻውን ለማየት መጠባበቅ ይጀምራሉ፡፡
ሠላሳ ደቂቃ ያህል እንደተቆጠረ የእስረኞቹ መምጣት በጉምጉምታ መወራት ጀመረ፡፡ሁሉም ሰው ወደ ጓሮው በር ዐይኑን ተክሎ ቀረ፡፡ አቤል ዋበላ፣በፍቃዱ ኃይሉ እጃቸውን በሰንሰለት እንደታሰሩ ማኅሌት ፋንታሁ ከካቴና ውጪ ኾና እንደተለመደው በከፍተኛ የፖሊስ ጥበቃ ታጅበው ወደ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ዘለቁ፡፡ ወጣቶቹ ወደ ግቢው ፊታቸው ላይ የጥንካሬ መንፈስ የነበረ ሲኾን ተሰበሰበውም ሕዝብ በጭብጨባ ነበር የተቀበላቸው፡፡በዚህ መካከል እስረኞቹን አጅበው የመጡት ፖሊሶች ወደተሰበሰበው ሰው ዘለው በመግባት ፎቶ ስታነሳ ነበር ያሏትን ምኞት መኮንንን (የሰማያዊው ፓርቲ አባል) የተባለች ወጣት የያዘችውን ስልክ ቀምተው እየጎተቱ ወሰዷት፡፡ፖሊሶች በወጣቷ ላይ የሚፈጽሙት ማንገላት ያስቆጣው ዮናታን ተስፋዬ የተባለ ሌላ ወጣት ድርጊቱን በማውገዝ ለመገላገል ሲጠጋ እርሱንም ጨምረው ወስደውታል፡፡
ፍርድ ቤቱ ይህን ችሎት ማየት ከጀመረ ወዲህ እስረኞቹን አጅበው የሚመጡት ፖሊሶች ቀጠሮ ባለ ቀን ሁሉ ችሎት ለመከታተል የሚመጣውን ሰው ሲያንገላቱ፣ሲሰድቡና ሲዘልፉ ልክ እንደ መብታቸው የሚቆጥሩት ሲኾን እዛ ግቢው ውስጥ የተገኘው ሰው ችሎት ውስጥ ገብቶ በሚገባ መቀመጫ ቦታ ተሰጥቶት ችሎት የመከታተል መብት እንዳለው ቅንጣት ታክል አስበውት የሚያውቁ አይመስል፡፡ እንዲኹም ከችሎቱ ውጪ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥም ቢኾን ‹‹ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው›› የሚል ማስጠንቀቂያ እስካልተለጠፈ ድረስ ከሁለት ሰው በላይ የኾነ ማንም ሰው የተሰበሰበበት ቦታ ላይ ፎቶ የማንሳት ሙሉ መብት እንዳለ የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ በአጠቃላይ በዛ ቦታ ላይ ከእነርሱ ውጪ ሌላ ሰው የመቆም መብት ጭምር እንደሌለው ጠንቅቀው ስሚያውቁ ወደ ተሰበሰበው ሰው ተመልሰው፤‹‹ሁላችሁም ግቢውን ለቃችሁ ውጡ›› ሲሉ ትእዛዝ ሰጡ፡፡
ከፊት ለፊት ቆመው የነበሩት ሰዎች ከግቢው ላለመውጣት እንቢተኝነታቸውን አሳዩ፡፡በተለይ በእስር ላይ የምትገኛው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እህት እስከዳር ዓለሙ፣አባቷ አቶ ዓለሙ እና ሌሎች ወጣቶች አንድ ላይ ኾነው ግቢ ውስጥ መቆም መብት እንዳላቸው በመግለጽ ለመውጣት ፍቃደኛ ሳይኾኑ ቀሩ፡፡ የፖሊሶቹ ማስፈራሪያና ዘለፋ ግን ቀጠለ ሕዝቡ ግቢውን ለቆ የማይወጣ ከኾነ አድማ በታኝ ፖሊስ እንደሚጠሩ ጭምር በመግለጽ ማስፈራራት ቀጠሉ፡፡ፎቶ ማንሳት የተከለከለ እንደኾነ እና እንኳን ሰውን መሬቱንም ጭምር ማንሳት እንደማይቻል በማስፈራራት ጭምር በመግለጽ ሰውን ከግቢው ውስጥ ገፍተው ወደ ውጭ አስወጡት፡፡

ግንቦት ዘጠኝ ቀን 2006 ዓ.ም ውሎ በነበረውና ከዚያም ቀጥሎ በነበረው ችሎት ላይ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ የወከለው ቤተሰብ አባል ወደ ችሎት እዲገባለት ተደርጎ የነበረ ሲኾን አሁን ግን ይህም መብት ተከልክሎ ችሎት ውስጥ በእስረኞቹ በኩል ከጠበቃቸው ከአቶ አመሐ መኮንን በስተቀር ማንም ችሎት ሳይገባ ቀርቷል፡፡ ችሎት ከገቡም በኋላ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጠማሪ ሃያ ስምንት ቀን እንዲፈቀድለት የጠየቀ ሲኾን ፍርድ ቤቱ፤‹‹ከዚህ በኋላ የሚሰጣችሁ ሃያ ስምንት ቀን የለም ዐሥራ አራት ቀን ይበቃችኋል፡፡ ችሎቱም ከዚህ በኋላ እሁድ ስለማይሰየም ቀኑ አንድ ቀን ተቀይሮ ሰኞ ሐምሎ 7 ቀን 2006 ዓ.ም›› ሲል ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የጊዜ ቀጠሮው መዝገብ ሲከፈት የአቤል ዋበላ፣ በፍቃዱ ኃይሉና የማኅሌት ፋንታሁንን ጉዳይ የያዘው መዝገብ ከሌሎቹ ከስድስቱ አስረኞች ጋራ በአንድ ቀን ይለያይ የነበረ ሲኾን በመካከሉ አንዲት ዳኛ የሃያ ስምንት ቀን ጥያቄውን ባለመቀበላቸው ጉዳዩ በዐሥራ አምስት ቀን ተለያይቶ እንደነበር ይታወሳል አሁን ደግሞ መዝገቦቹ መልሰው ተቀራርበዋል፡፡ የስድስቱ ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን ይታያል የሦስቱ ደግሞ ሰኞ ሐምሌ ሰባት ቀን፡፡
በዛሬው ቀጠሮ በፍቃዱ ኃይሉ ያላመነበትን የእምነት ክህደት በኃይል እንዲፈርም መገደዱን ተናግሯል፡፡ እንደምንጮች ገለጻ ከኾነ አብዛኞቹን እስረኞች በከፍተኛ ጫናና በድብደባ በመርማሪ ፖሊሶች የተረቀቀውንና በእነርሱ ሐሳብ የተዘጋጀ የእምነት ክህደት ቃል ላይ ‹‹የሰጠሁት ቃል የኔ ነው ጥፋተኛ ነኝ›› ብለው እንዲፈርሙ ተደርጓል፡፡
የፍርድ ቤቱ መዝገቡን ማጠጋጋትና የእምነት ክህደት ቃሉ ፊርማ እስረኞቹን ለመክሰስ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ማሳያዎች በሚል በሕግ ባለሞያዎች ተገምቷል፡፡
(ፎቶዎቹ ከታምሩ ጽጌ ገጽ ላይ የተገኙ ናቸው)
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ

Sunday, June 29, 2014

እያበበ የመጣዉ ህዝባዊ ትግል

ኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ዘመናት እንወድሀለን በሚሉት ነገስታት ተረግጧል፤ ህብረተሰብዓዊነት አመጣንልህ ባሉት ወታደራዊ አምባገነኖችም ለ17 አመት እጅና እግሩን ታስሮ ተገዝቷል። እነዚህ ሁለት ለህዝብ ደንታ የሌላቸዉ መንግስታት ተራ በተራ በህዝብ ትግል ተንኮታኩተዉ የታሪክ ቅርጫት ዉስጥ ገብተዋል፤ ሆኖም ሁለቱንም መንግስታት በመራራ ትግል አሸንፎ የጣለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የትግሉን ዉጤት ማስጠበቅ ባለመቻሉ ይህ ኃያልና የረጂም ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነ ህዝብ ዛሬም ነፃ አወጣንህ በሚሉት ዘረኛ አምባገነኖች እየተረገጠ ነዉ። አዎ! የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም እየተረገጠ ነዉ። ዛሬም አየታሰረ ነዉ። ዛሬም እየተገደለ ነዉ። ዛሬም ይህንን ሁሉ በደል የሚያደርሱበትን የአንድ ወንዝና የአንድ መንደር ምርት የሆኑ ዘረኛ አምባገነን ገዢዎችን ከጭንቅላቱ ላይ ለማዉረድ እየታገለ ነዉ። በእርግጥም የኢትዮጵያ ህዝብ ከምን ግዜም በተለየ መልኩ የወያኔን ዘረኛ አገዛዝ አምርሮ እየታገለ ነዉ፤ በተለይ በዚህ በያዝነዉ አመት ወያኔንና ሃያ ሁለት አመት ሙሉ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐቱን ለመደምሰስና ኢትዮጵያ ዉስጥ በፍትህና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ስርዐት ለመገንባት የሚደረገዉ የሞት የሽረት ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ወያኔ እግሩ አዲስ አበባን ከረገጠበት ግዜ ጀምሮ የጭቆና ተቋሞቹን በየቦታዉ ተክሎና ተደላድሎ ህዝብን እንዳሰኘዉ መርገጥ እስከጀመረበት ግዜ ድረስ አንዴ ሰዉ በላዉን የደርግ ስርዐት አስወገድኩላችሁ እያለ ሌላ ግዜ ደግሞ ፌዴራል ስርዐት መስርቼ ብሄር ብሄረሰቦችን ነፃ አወጣሁ እያለ ለተወስነ ግዜም ቢሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ መሳብ ችሎ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ያ በፌዴራሊዝም፤ በዲሞክራሲና በይስሙላ ምርጫ የተሸፈነዉ የወያኔ አስቀያሚ ገበና ይፋ እየሆነ መጥቶ ወያኔ አርግጫዉንና ግድያዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ትግሉን፤ እስሩንና ስደቱን ተያያዙት።
የወያኔን መሰሪ አላማ ገና ከጧቱ የተረዱ ኢትዮጵያዉያን ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት ይህንን መሰሪ አገዛዝ በተደራጀ፤ ባልተደራጀ፤ በተባበረና በተበታተነ መልኩ ሲታገሉ ቆይተዋል። ሆኖም የአገራችንን የፖለቲካና የኤኮኖሚ መዋቅሮች ሙሉ ለሙሉ ከሚቆጣጠረዉ ወያኔ ጋር በቁጥር፤ በአይነትና በይዘት የሚመጥን ትግል ማካሄድ ባለመቻላቸዉና እንዲሁም ብትራቸዉን ወያኔ ላይ ብቻ ከመሰንዘር ይልቅ እርስ በርስ ስለሚላተሙበት ምንም አይነት ህዝባዊ ድጋፍ በሌለዉ ወያኔ ላይ የትግል የበላይነት ማግኘት አልቻሉም፡፡ ወያኔም እኛዉ ዉስጥ ከመካከላችን የበቀለ እሾክ በመሆኑና ደካማ ጎናችንን በሚገባ ስለሚያዉቀዉ በዚሁ ደካማ ጎናችን እየገባና እርስ በርስ እያባላን የስልጣን ዘመኑን እስከዛሬ ማራዘም ችሏል።
ወያኔ የአንድን አካባቢ ህዝብ ከሌላዉ አካባቢ ህዝብ፤ አንዱን የህብረተሰብ ክፍል ከሌላ የህብረተሰብ ክፍል ጋር በሆነዉ ባልሆነዉ ምክንያት እየፈጠረ ማጋጨቱን አሁንም አላቆመም፤ እንዲያዉም ይበልላችሁ ብሎ በስፋት እንደቀጠለበት ነዉ። ዘንድሮ ግን ህዝብ፤ የተቃዋሚ ኃይሎችና በወያኔ ተንኮል ተታልለዉ የእርስ በርስ ሽኩቻ ዉስጥ ገብተዉ የነበሩ የህዝብ ወገኖች ሁሉ የወያኔን የከፋፍለህ ግዛዉ ደባና ሴራ በሚገባ ያወቁ ይመስላል። ለምሳሌ በቅርቡ አምቦና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ ከፍተኛ ፀረ ወያኔ የተቃዉሞ ሰልፍ በተካሄደ ግዜ የወያኔ ካድሬዎች የኦሮሞ ህዝብ ቁጣና መነሳሳት አቅጣጫዉን ቀይሮ በትግል አጋሩ በአማራ ህዝብ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ያልፈነቀሉት ዲንጋይ አልነበረም። ሆኖም ወያኔን ከስልጣን ለማባረርና የአገራቸንን ወደፊት በህዝብ እጅ ላይ ለማስቀመጥ ቁልፉ መተባባርና አንድ ላይ መቆም መሆኑን የተረዳዉ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ቁጣ ይበልጥ በወያኔ ላይ ነደደ እንጂ አንደቀድሞዉ ለወያኔ የተንኮል ሴራ እጁን አልሰጠም።
ወየኔን በተለያዩ የትግል ስልቶች የሚፋለሙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች በፀረ ወያኔ አቋማቸዉና በአላማቸዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ድጋፍ ከጎናቸዉ እንዳለ እንኳን እኛ ወያኔም በሚገባ ያዉቃል። ህዝብን የመሰለ እንደ ዉኃ ማጥለቅለቅ የሚችል ኃይል ከጎናቸዉ ያሰለፉ ድርጅቶች ደግሞ ወያኔን የመሰለ ምንም ህዝባዊ መሰረት የሌለዉን ኃይል ቀርቶ ፊታቸዉ ላይ የቆመን ምንም አይነት ኃይል ከማሸነፍ የሚገታቸዉ ምንም ነገር የለም።
ሆኖም ዉኃም ቢሆን ምን ያክል ኃይለኛ መሆኑ የሚታወቀዉ ተገድቦ ወደ ተፈለገበት አቅጣጫ እንዲሄድ ሲደረግ ነዉና የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎችም ከጎናቸዉ የቆመዉን ህዝብ አስተባብረዉ አገራችንን ወደ ድል መምራት የሚችሉት መጀመሪያ እነሱ ተባብረዉ ህዝብን በአንድ አላማና በአንድ አመራር ስር ማሰለፍ ሲችሉ ብቻ ነዉ። ዛሬ በሁሉም አካባቢዎች ባይሆንም አገር ዉስጥና ካገር ዉጭ በተለያዩ አካባቢዎቸ ይቅናችሁ በሚያሰኝ መልኩ ጎልተዉ የሚታዩ ብዙ የትብብርና የትግል ቅንጅት ጅምሮች አሉ። በገበሬዉና በሰራተኛዉ፤በወጣቱና በወታደሩ በተለይ ደግሞ በተለያዩ ብሄረሰቦችና በተለያዪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከመለያየት ይልቅ የመቀራረብ፤ ከመወቃቀስ ይልቅ የመወያየት ከመጠላለፍ ይልቅ የመተቃቀፍ አዝማሚያዎች በብዛት እየታዩ ነዉ።
ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ጀምሮ እስከቅርብ ግዜ ድረስ የተቃዋሚዉን ጎራ በተለይም አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚገኙትን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልህቃን ለሁለት ከፍሎ ሲያጨቃጭቅ የከረመዉ ወያኔን በህዝባዊ አመጽ ወይስ በህዝባዊ እምቢተኝነት ታግለን እናዉርደዉ የሚለዉ ጥያቄ ዛሬም ድረስ አዎንታዊ እልባት ባያገኝም ዛሬ ሌላ ቢቀር እንደቀድሞዉ የተቃዋሚዉን ጎራ ለሁለት ከፍሎ የወያኔ መጠቀሚያ ማድረግ አይችልም። የኢትዮጵያ ህዝብም እኔ ያለሁት ጉድጓድ ዉስጥ ነዉና ወይ ተደጋግፋችሁ አዉጡኝ አለዚያም በቻላችሁትና በሚታያችሁ መንገድ አዉጡኝ ነዉ የሚለን እንጂ በኛ መጨቃጨቅ የሱ የጉድጓድ ዉስጥ ቆይታ ዬትየለሌ እንዲሆን አይፈልግም። ዛሬ ይህንን ተደጋግፋችሁ ነጻ አዉጡኝ የሚለዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ ሰምተዉ በየጫካዉና በየበረሃዉ ከወያኔ ጋር የሞት የሽረት ትግል ለማድረግ የቆረጡ ኃይሎች የሚያደርጉት መሰባሰብና በተባበር ወገንን እጅግ የሚያበረታታ ጠላትን ደግሞ ያንኑ ያክል የሚያንቀጠቅጥ መልካም ጅምር ነዉ።
ከተለያዩ የአገራችን ኣካባቢዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተዉጣጥተዉ ወያኔን በሚገባዉ ብቸኛ ቋንቋ ለማነጋገር ቆርጠዉ የተነሱት የኢትዮጵያ ልጆች ወያኔን አንከባልለዉ የሚጥሉት ባነገቡት ጠመንጃ ብቻ ሳይሆን በህብረታቸዉና በአላማ ጽናታቸዉ እንደሆነ በሚገባ ያዉቃሉ። ለዚህም ነዉ ዛሬ እነዚህ ጀግኖች ባሉበት ጫካና በረሃ ሁሉ የሚሰማዉ መዝሙር . . . . ላንቺ ነዉ ኢትዮጵያ . . . ላንቺ ነዉ… ላንቺ ነዉ ኢትዮጵያ ላንቺ ነዉ… ላንቺ ነዉ ኢትዮጵያ ደሜን የማፈሰዉ የሆነዉ።
ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያን ከዘረኞችና እነሱ ከገነቡት ዘረኛ ስርዐት ለማላቀቅ ዉስብስብነት ገብቷቸዉ ይህንን ዉስብስብ ትግል ከመታግል ዉጭ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለ ተረድተዉ የትግል ህብረትና አንድነት የጀመሩ ብዙ ወገኖች አሉ። ይህ የሚያበረታታና ተስፋዉ የለመለመ ጅምር የሁላችንም ድጋፍና ተሳትፎ የሚያስፈልገዉና አለንልህ ሊባል የሚገባዉ አገራዊ ጅምር ነዉ። በዚህ ጅምር ዉስጥ ትንቅንቅ አለ፤ በዚህ ጅምር ዉስጥ መስዋዕትነት አለ፤ በዚህ ጅምር ዉስጥ ድል አለ። በህዝባዊ እምቢተኝነቱ ጎራ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በብዙ የኢትዮጵያ ከተማዎች ዉስጥ ህዝቡ የወያኔን ግልምጫ፤ እስርና ድብደባና ግድያ ከምንም ባለመቁጠር በየአደባባዩ ወያኔን ፊት ለፊት መጋፈት ጀምሯል። ወያኔን በብዕራቸዉ የሚታገሉ ወጣቶችም ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት ይሻለናል ብለዉ በሰላ ብዕራቸዉ ህዝብን እንዳስተማሩ ቃሊቲ ወርደዋል። በህዝባዊ አመጹ ጎራ ደግሞ የአባቶቹን ታሪክ ለመድገም ቆርጦ የተነሳዉ የኢትዮጵያ ወጣት አዲሱን የኢትዮጵያ የፍትህ፤ የነጻነትና የእኩልነት ታሪክ በደሙ ለመጻፍ የከተማ ኑሮ በቃኝ ብሎ የጫካና የበረሃ ኑሮዉን ተያይዞታል።
ዛሬ ይህንን እንዳባቶቹ ዱር ቤቴ ብሎና ጠመንጃቸዉን አንግቦ ከወያኔ ጋር ትንቅንቅ የጀመረዉን ህዝባዊ አርበኛ የብሄረሰብ ስብጥር የተመከለተ ማንም ሰዉ የአገራችን ኢትዮጵያ ዳግማይ ትንሳኤ ደጃፍ ላይ መሆኑን በሙሉ አፉ ደፍሮ መናገር ይችላል። ወያኔ በነጋ በጠባ ከሚያስረዉና የወደፊቱን ካጨለመበት ወጣት ጀምሮ ገዳማቸዉን ካፈረሰባቸዉ መነኮሳትና ቤ/ክርስቲያናቸዉን አስካረከሰባቸዉ ካህናት ድረስ የትግሉ ጎራ ሁሉንም አይነት ኢትዮጵያዉያን በብዛት አካትቶ ይዟል።
ወያኔ ስልጣን እንደያዘ በሚቆይባት በእያንዳንዷ ቀን ተጨማሪ ወጣቶች እንደሚታሰሩ፤ተጨማሪ ሰላማዊ ሰልፈኞች እንደሚገደሉ፤ተጨማሪ ጋዜጠኞች ሽብርተኞች ተብለዉ እንደሚታሰሩ፤ ተጨማሪ ምሁራን አገራቸዉን ለቅቀዉ እንደሚሰደዱና የአገራችን የኢትዮጵያም አንድነት የበለጠ እየላላ እንደሚሄድ ሁላችንም በሚገባ እናዉቃለን። በሌላ አነጋገር ወያኔ ስልጣን እንደያዘ የመቆየት አንድ ተጨማሪ ቀን በሰጠነዉ ቁጥር የኛም ሆነ የአገራችን ህልዉና በቀላሉ የማናበጀዉ እጥፍ ድርብ ችግር ዉስጥ ይወድቃል። ይህ እናት አገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነዉ ችግርና መከራ ገና ከጧቱ የታያቸዉ ኢትዮጵያዉያን ባለፉት ሃያ አመታት የየራሳቸዉን እርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል። በዚህ ሂደት ዉስጥ አንዳንዶች ዉድ ህይወታቸዉን ገብረዋል፤ ሌሎች ደግሞ ታስረዋል፤ ተደብድበዋል፤ አገር ለቅዉ ተሰድደዋል። እዚህ ላይ አንድ ሁላችንም በትክክል ልንገነዘበዉ የሚገባን ሀቅ አለ፤ እሱም የኢትዮጵያ ችግር የአንድና የሁለት ሰዉ ችግር አይደለም፤ በአንድና በሁለት ሰዎች የሚፈታ ችግርም አይደለም። ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት፤ ችግሩም የሁላችንም ነዉ፤ ወያኔን በቆራጥነት ታግለን አገራችንን ከመበታተን ህዝባችንን ደግሞ ከዘረኝነትና ከድህነት ማላቀቅ ያለብንም እኛዉ ነን። ወያኔ ስለጠላነዉ፤ ስለሰደብነዉ ወይም ስለጮህንበት ብቻ በህዝብና በአገር ላይ በደል መፈጸሙን አያቆምም:፡ እነዚህ በደሎችና ችግሮች የሚቆሙትና የኢትዮጳያ ህዝብ የሰላም አየር መተንፈስ የሚችለዉ ወያኔ ከስልጣን ሲወገድና በምትኩ ኢትዮጵያዉያንን በእኩልነት የሚያስተናግድ መንግስት በኢትዮጵያዉያን ተመርጦ ስልጣን ሲይዝ ብቻ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰብዓዊ መብቱ፤ ለነጻነቱና ለእናት አገሩ አንድነት መከበር ትናንት ካደረገዉ ትገል የዛሬዉ እጅጉን የሚያበረታታ ቢሆንም አሁንም ይህንን ህዝባዊ አደራ ከተሸከሙ ኃይሎች የሚጠበቅ ብዙ ስራ አለ። ከላይ ከፍ ሲል ደጋግመን እንደጠቀስነዉ ከወያኔ ጋር በሚደረገዉ የትግል ሂደት ዉስጥ የህዝብ ኃይሎች የሚመኩበት ትልቁ ኃይል ህብረታቸዉና ከጎናቸዉ የተሰለፈዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ። የተቃዋሚ ኃይሎች አለመተባበርና አለመግባባት ከጎናቸዉ በተሰለፈዉ ህዝብ ዉስጥም አለመግባባትና አለመተባበር ይፈጥራል:፡ ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ እየተቃወምነዉና እየታገልነዉ ዛሬ ድረስ የደረሰዉ እኛ ዉስጥ የነገሰዉ አለመተባበርና አለመግባባት እየረዳዉ ነዉ። ስለዚህ ዛሬ ወያኔን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን ወያኔ ከተወገደ በኋላም የሚገጥሙንን ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን የመገንባትና ህዝባዊ ስርዐትን የመፍጠር አደራ ጭምር ለመወጣት በህብረትና በአንድነት መቆም አለብን። አንድነታችንና ህብረታችን አንድ ስራ ሰርቶ ወያም አንድ ነጣላ አላማ ከግብ አድርሶ የሚቆም ሳይሆን የእኛን ሀላፊነት ተወጥተን ለልጅ ልጆቻችን የምናስተላልፈዉ ብሄራዊ ቅርስ መሆን አለበት።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
source www.ginbot7.org

Monday, June 23, 2014

ከሕገ-መንግሥቱ በፊት … (በጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)

ትናንት ሰኔ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹ያገባኛል ባይነት እና ጋዜጠኝነት በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ›› በሚል ርዕስ እኔን ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ እና ዳዊት ሰለሞንን የውይይት መነሻ እንድናቀርብ በጋበዘን መሰረት በእኔ በኩል ለውይይት መነሻ ሀሰብ ይሆናሉ ብዬ ያቀረብኋቸውን ሶስት ነጥቦች እንዲህ አቅርቤያዋለሁ፡፡
በመጀመሪያ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ጉዳይ ‹‹ያገባኛል ባይነት እና ጋዜጠኝነት በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ›› በሚል ርዕሥ የውይይት መነሻ ሀሳብ ከሙያ አጋሮ ቼ ጋር እንዳቀርብ ስለጋበዘኝ በቅድሚያ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ አናንያ ሶሪ እና ዳዊት ሰለሞን
ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ አናንያ ሶሪ እና ዳዊት ሰለሞን

የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 29
ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት ሲጸድቅ የፈረሙበት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ፡፡ ይህ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 29 (1) እና (2) ላይ ሃሳብን በነጻነት የመገለጽ መብትን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ማናኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት መያዝ ይችላል፡፡ ፣ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በአገር ውስጥም ሆነ ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ-ጥበብ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ በማንኛውም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል፡፡››
ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ከጓደኛዬ አቤል ዓለማየሁ ጋር ‹‹ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?›› በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃነው መጽሐፍ ውስጥ ይህን ሕገ-መንግሥት አስመልክቶ ዶ/ር ነጋሶን ቃለ መጠይቅ በማድረግ አነጋግረናቸው ነበር፡፡ ከላይ በመግቢያዬ የጠቀስኩት አንቀጽ 29 መከበር አለመከበሩ ከጥያቄዎቼ መካከል አንዱ ነበር፡፡ ዶ/ር ነጋሶም እሳቸው በምላሻቸው እንዲህ አሉ፡-
‹‹እንደ ጥሩ ምሳሌ የጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን እና የእስክንድር ነጋን ጉዳይ መውሰድ እንችላለን፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት፣ ርዕዮት እንደጋዜጠኛ የፈለገችውን ሐሳብ ጽፋ ለየትኛውም ሚዲያ የማቀበል መብት አላት፡፡ ይህ ተጥሶ ‹‹ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላት›› ተብሎ ተፈረደባት፡፡ እስክንድር ነጋ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤታችን ድረስ በሕዝብ ግንኙነት ክፍል ተጋብዞ በመምጣት የቀረበውን ሐሳብ ከተሰብሳቢዎች ጋር ተቀምጬ አዳምጫለሁ፡፡ ሐሳቡን በመግለጹ ‹‹ሽብርተኛ ነው›› ተብሎ ተፈረደበት፡፡ እነ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ኦልባና ሌሊሳ ‹‹ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰዎች ጋር ለምን ተነጋገራችሁ?›› ተብለው ነበር የታሰሩት፡፡ በተጨማሪም በአንድነት ፓርቲ ስር ትታተም የነበረችው የ‹‹ፍኖተ ነጻነት›› ጋዜጣ ያለመታተም ጉዳይ፣ የ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ መታገድ፣ የ‹‹አዲስ ነገር›› እና የ‹‹አውራምባ ታይምስ›› ጋዜጦች የደረሰባቸውን ችግር እናውቃለን፡፡ አንቀጽ 29 እስከአሁን አልተከበረም፡፡››
እንግዲህ የተከበራችሁ የዚህ ውይይት ተሳታፊዎች፣ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ፈርመው ያጸደቁት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሕገ-መንግሥቱ አለመከበሩን ጥቂት ምሳሌዎችን በማቅረብ ተናገርው ነበር፡፡ ይህ የሥርዓቱን ህገ ወጥነት እና አደገኝነት የሚያሳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የጊዜው መንግሥታችን ‹‹ሀገርን የማስተዳድርበት ወርቃማ ሕግ አለ፡፡ ይህ ትልቅ ስኬታችን ነው›› በማለት ዘወትር ሲናገር እንዳደምጠዋለን፡፡ የኢህአዴግ መንግሥት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 29 በተለያዩ በርካታ ጊዜያትና በተለያዩ መንገዶች ሲንድ፣ ሲሸራርፍና ሲደፍር፤ ናድኩት፣ ሸራረፍኩና ደፈርኩት አይለንም፡፡ ይልቅ ጥቂት የማይባሉ ጋዜጠኞችን ‹‹ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ሲንቀሳቀሱ … ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር በመተባበር የሀገርን መሰረተ ልማቶች በሽብር ለማውደም ሲያሴሩ …ወዘተ በሚሉ ምክንያቶች ጠርጠሮ በመያዝ በፍርድ ሂደትም በተለያዩ ዓመታት የጽኑ እስራት ቅጣት በይኖባቸዋል፡፡ አሁንም በመሰል አካሄዶች ፖሊስ (በሽብርተኝነት ወንጀል) ሶስት ጋዜጠኞች እና ስድስት ጦማሪያን (ብሎገሮች)ን ‹‹ጠጥሬያቸዋለሁ›› በሚል በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ጣቢያ ከታሰሩ ከ56 ቀናት በላይ አልፏቸዋል፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ሕገ-መንግሥቱን አክብረው የሚንቀሳቀሱ ነበሩ ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡ ዛሬም ሕገ-መንግሥቱን እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሃሳቦችን አንስተን በጋራ ብንወያይ ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ መንግሥት ሕገ-መንግሥቱ በመናድ ብሎ ጋዜጠኞችን ፖለቲከኞችንና ዜጎችን በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ሁሉ እሱም የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች ሲንድ፣ ሲሸራርፍና ሲደፍር በሕግ እንዴት ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል? በሚለው ላይ እንነጋገር እና የመፍትሔ ሀሳቦች ይንሸራሸሩ፡፡

ከሕገ-መንግሥቱ በፊት
ኢህአዴግ 1983 ዓ.ም ላይ የደርግ ሥርዓትን ከገረሰ በኋላ ነጻ ፕሬስ ማወጁ ብዙዎቻችንን የሚያስማማ እና ሊመሰገንበት የሚገባ ትልቅ እርምጃ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን፣ ሥርዓቱ ይህንን በማድረጉ ከሰማይ መና እንዳወረደ ተደርጎ መቆጠር አለበት አልልም፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለይ እራሱ ጠቅልሎ በያዛቸው እና እንደፈለገ በሚዘውራቸው ሚዲያዎች ነጻ ፕሬስ ማወጅ መቻሉን ከሚጠበቀው በላይ በማጋነን ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታነት ሲጠቀምበት ተመልክተናል፡፡ ኢህአዴግ በትረ-ሥልጣን ባይይዝ ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ ፕሬስ ፈጽሞ አይታወጅም ብሎ መደምደምም ከባድ ነው፡፡ (እንዲህ ብለው የሚያስቡ ስላሉ ነው) በዚያን ጊዜ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለመሄድ ኢህአዴግ ነጻ ፕሬስን ማወጁ የውዴታ ግዴታውም ነበር – ከልቡ ቢያምንበትም ባያምንበትም፡፡
ከነጻ ፕሬሱ እወጃ በኋላ ባሉት ዓመታትም፣ እስከአሁን ድረስ የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ በምን አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲዳክር መጓዙን መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ስለሚሆን አልፈዋለሁ፡፡
ተሰብሳቢው
አንድ ጉዳይ ግን በውስጤ ብዙ ጊዜ ይብሰለሰላል፡፡ እራሴንም ደጋግሜ ጠይቄ ለራሴ መልስ አግኝቼለታለሁ፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕገ መንግሥቱ ብቻ መሆኑን ደጋግሞ ነግሮናል፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሕገ-መንግሥቱ በፊት ቀዳሚ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ይህንን የምለው፣ ተፈጥሮ የሰውን ልጅ በነጻነት እንዲያስብ፣ ሐሳቡን ሐላፊነት በተሞላው መልኩ እንዲናገር፣ እንዲጽፍ፣ በተለያዩ ጥበባቶችና የመግባቢያ መንገዶች እንዲያስተላልፍ እና እንዲቀበል ቀድማ ለግሳዋለች፡፡ ይህንን የላቀ የተፈጥሮ ሕግ ከሕገ-መንግሥት ጋር ተሰናስሎ በሕግ ማዕቀፍ መደገፉ ጥቅሙ የላቀ መሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አምባገነን ሥርዓቶችን ያየች ሀገር ቀላል የማይባሉ ዜጎች ተፈጥሯዊውንም ሆነ ሕገ-መንግሥታዊ የማሰብ፣ የመናገር፣ የመጻፍ …ወዘተ መብቶቻቸው ተሸብቦ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ መውደቃቸውን አምናለሁ፡፡ ይህም ሥርዓታቱ (ደርግ የለየለት፣ ኢህአዴግ ደግሞ ዴሚክራሲያዊ ካባ የደረበ አንባገነን ነው) ለሥልጣናቸው ማቆያ እና ማራዘሚያ ሲሉ ከእነሱ ሃሳብ በተቃራኒው በሚያስቡ እና በድፍረት በሚናገሩ፣ በሚጽፉ …ዜጎቻቸው ላይ በሚወስዷቸው ኢ-ፍትሃዊ የግድያ፣ የድብደባ፣ የእስር፣ የእንግልት፣ የስደት …እርምጃዎች በዋነኝነት የሚመጣ ነው፡፡ አፋኝ የሆነው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁም ኢትዮጵያኖችን ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን የማሰብ፣ የመጻፍ፣ የመናገር …መብቶች በእጅጉ የሚጨቁን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በመሆኑም ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ አስገብቶ የማክበር እና የማስከበር ግዴታን እንዴት እንወጣው? በሚለው ላይ ብንወያይበት መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

የእስረኞች አያያዝ እና ሰብዓዊ መብቶች
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 18 (1) ላይ ‹‹ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው›› ይላል፡፡ ይህ ግን በተለያዩ ጊዜያት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በግልጽ እየተጣሰ እንደሚገኝ እየደመጥን ያለነው፡፡ በዚያ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ይፈጸማል፡፡ ‹‹እመኑ›› ወይም ‹‹በሌላ ሰው ላይ መስክሩ›› ተብሎ ቶርች ይደረጋል፡፡ ዜጎች ይደበደባሉ፣ ውስጥ እግራቸው ይገረፋል፣ ቀዝቃዛ ውሃ ይደፋባቸዋል፡፡ ‹‹ወፌ ላላ›› የተባለ አውጫጭኝ ግርፍ ሰዎች እንደሚገረፉ ይነገራል፡፡ ይሄንን ጋዜጠኛ አና ጦማሪ በፍቃዱ ሐይሉ፣ ጦማሪያኑ አቤል ዋበላ እና አጥናፍ ድብደባ እና ጥፊ የመብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡ እኔም ለጥቂት ቀናት ማዕከላዊ ታሰሬ በነበረበት ጊዜ ከብዙ ታሳሪዎች ድርጊቱ እንደሚፈጸም አረጋግጫለሁ፡፡ እኔ ታስሬበት በነበረበት ‹‹8›› ቁጥር ውስጥ ከጎንደር የመጣ ብርሃኑ የተባለ ሰው በድብደባ ብዛት እያነከሰ ነበር የሚሄደው፡፡ ከደቡብ ሱዳን በሽብር ጉዳይ ተጠርጥረው ከተያዙት መካከል ከአንዱ የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት (አቶ ኦኬሎ) በስተቀር መደብደባቸውን አረጋግጠውልኛል፡፡ የተደበበደቡትን የአካላቸውን ክፍል አሳይተውኛል፡፡ ለአራት ቀናት ያህል እንዲቆም የተቀጣ ወጣትም የደረሰበትን በመረረ መልኩ ነግሮኛል፡፡ በማንኛውም መንገድ ተጠርጥረው የተያዙ ዜጎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሲጣስ ‹‹ያገባናል፣ ድርጊቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን የሚፈጽሙ ግለሰቦች እና አካላት በሕግ መጠየቅ አለባቸው›› ብለን በድፍረት መናገር፣ የሚመለከተውን አካል መጠየቅና ድምጻችንን በተለያየ መንገድ ማሰማት ይገባናል፣ ለተግባራዊነቱም መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል፡፡
በመጨረሻም በጣም በማከብራቸው ምሁር ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም ሰኔ 13 ቀን 2006 ዓ.ም በነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ‹‹ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንን ማን ይፈራቸዋል?›› በሚል ርዕስ ለንባብ ካቀረቡት ጽሁፍ ውስጥ የማረከኝን ሀሳብ በመውሰድ የውይይት መነሻ ሃሳቤን እቋጫለሁ፡፡
‹‹ …ለእኔም ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የሌሉበት ገዥ አካል ከሚኖር ወይም ደግሞ ገዥ አካል በሌለበት ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ብቻ ከሚኖሩ የትኛው የተሻለ የሚል ምርጫ ቢቀርብልኝ የኋለኛውን ለመምረጥ ለሰከንድ እንኳ ጥርጣሬ አይኖረኝም፡፡ ከሁሉም በላይ ለዓላማ በጽናት የቆምኩ፣ ለምሰራው ትክክለኛ ሥራ ሁሉ ኩራት የሚሰማኝ፣ ላመንኩበት ዓላማ ከልብ እና በወኔ የቆምኩ፣ ዓላማዬን ለማስፈጸም በከባድ እርምጃ ወደፊት የምገሰግስ፣ ላልሰራሁት ወንጀል ይቅርታን የማልጠይቅ፣ በምሰራው ሥራ ሁሉ የማላፍር፣ ቆራጥ እና የማያወላውል ባህሪን የተላበስኩ የኢትዮጵያ ጦማሪ ነኝ፡፡››
ኃይል ለነጻ ጋዜጠኞችና የኢትዮጵያ ጦማሪያን!
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ 

Tuesday, June 17, 2014

ኮካ ኮላ የተባለው መጠጥ አጠገቤ አይደርስም! – ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ኮካ ኮላ ትክክለኛ ነገር አይደለም!
የኮካኮላ ኩባንያ በታዋቂው የኢትዮጵያ ኮከብ ድምጻዊ ሙዚቀኛ በሆነው በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ላይ ያደረገውን ስነምግባርን የጣሰ፣ የዘፈቀደ እና ፍትሀዊ ያልሆነ ድርጊት በማስመልከት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ በማህበራዊ እና በመገናኛ ድረ ገጾች ተቃውሞውን በመግለጽ የኮካ ኮላ ምርት እንዳይጠጣ ጥሪውን በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡ የዲያስፖፈራው ማህበረሰብ በማያያዝም የኮካ ኮላ ኩባንያ ተንኮልን ባዘለ መልኩ ቴዲን ነጥሎ በማውጣት የአድልኦ ሰለባ እንዲሆን አድርጓበታል በማለት ላይ ነው፡፡ የኮካ ኮላ ኩባንያ 32 የልዩ ልዩ አገሮች ሙዚቃ የቡድን አቀንቃኞችን ለብራዚል የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን/FIFA ዋንጫ የመክፈቻ ስነስርዓት ማድመቂያ ሙዚቃ አንድያቀነባበሩ አድርጎ ነበር፡፡ የኮካ ኮላ ኩባንያ በቴዲ አፍሮ ከተቀነባበረው የኢትዮጵያ ሙዚቃ በስተቀር የሁሉንም ዓይነት መሰል ሙዚቃዎች ለቅቋል!
አሁን የኮካ ኮላ ምርት እንዳይጠጣ የሚለውን መርህ እቀላቀላለሁ፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት ሳቀርባቸው የነበሩትን ትችቶቸን ስትከታተሉ ለቆያችሁ በሚሊዮኖች ለምትቆጠሩ አንባቢዎቸ አሁን የኮካ ኮላ ምርት እንዳይጠጣ የሚለውን ቡድን እንድትቀላቀሉልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
የኮካ ኮላ ኩባንያ እና ተወካዮች በቴዲ ላይ ስህተት የፈጸሙ መሆናቸውን ከጥርጣሬ በላይ ተገንዝቢያለሁ፡፡ ስሙን አጥፍተዋል፣ ስብእናውን ዝቅ አድርገዋል እናም በአደባባይ በህዝብ ፊት አዋርደውታል፡፡ ይዞት የቆየውን ዝና እና ክብር ነፍገዋል፣ ስሙን ጥላሸት ቀብተዋል፣ እናም በስራው እና በጥሩ ስነምግበሩ ተጎናጽፎት የቆየውን ጥሩ ስሙን አጉድፈዋል፡፡ ፍትሀዊ ያልሆነ፣ ጨካኝነት የተሞላበት እና የሞራል ስብዕናን ባልተላበሰ ሁኔታ አስተናግደውታል፡፡
እ.ኤ.አ ጁን 7/2014 የኮካ ኮላ ኩባንያ ተወካይ የሆኑ ባለስልጣን የተናገሩትን ዘገባ በመጥቀስ እንደሚከተለው ቀርቧል፣ “ለፊፋ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ‘ዓለም የእኛ ናት‘ የሚለውን የኢትዮጵያ ልዩ ሙዚቃ ለማቅረብ ዓላማ በማድረግ ዜማውን እንዲያቀርብ እና እንዲቀረጽ እዚህ እኛ የኮካ እስቱዲዮ ድረስ ወደ አፍሪካ እንዲመጣ ተደርጎ ነበር፡፡ ከቴዲ አፍሮ ጋር የተደረገው የኮንትራት ስምምነት ‘ማንዳላ የተወሰነ’ በተባለ መቀመጫውን በናይሮቢ ያደረገ በሌላ ሶስተኛ አምራች ወገን የተፈጸመ ሲሆን ቴዲ አፍሮም ላደረገው ጥረት ሙሉ ክፍያ ተሰጥቶታል፡፡“ የባለስልጣኑ መግለጫ በመቀጠልም እንዲህ ይላል፣ “የድምጽ ቀረጻው ከተጠናቀቀ በኋላ ኮካ ኮላ ሴዋ የተባለ ኩባንያ የሚያዝዝበት የግል መጠቀሚያ ንብረት ነው፣ ሆኖም ግን ሙዚቃው እስከ አሁን ድረስ አልተለቀቀም፣ እናም በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሙዚቃው ይለቀቃል የሚል ዕቅድ የለም፡“ በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡
እ.ኤ.አ ጁን 10/2014 በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የቴዲ አፍሮ ተወካይ ባለስልጣን የኮካ ኮላን አስደንጋጭ አዋጅ በማወጅ እና ቴዲ አፍሮ ሙያዊ ያልሆነ ባህሪ አሳይቷል በማለት በኮንትራት ስምምነቱ በግልጽ በተቀመጠው አንቀጽ መሰረት እምነትን የሚያጎድል ድርጊት ሲፈጸም ለህዝብ እንዳይለቀቅ የሚከለክል እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡ መግለጫው በማያያዝም የኢትዮጵያን የዓለም ዋንጫ ልዩ ሙዚቃ ላይ ኮካ ኮላ ያልተገደበ ክልከላ ያደረገበትን ምክንያት ለማወቅ እኛ ጉዳዩን በድረ ገጽ ይፋ ከማድረጋችን በፊት ለእነርሱ ብናቀርበውም እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ ያለመስጠቱ እንቆቅልሽ ግራ እንዳጋባው ገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት የኮካ ኮላ ኩባንያ መጥፎ እምነትን በማራመድ፣ እና “የእራሱን የኮኩባንያ የጽናት፣ የታማዕኒነት፣የህዝብ እምነት እና በእራስ የመተማመን መርሆዎች” በይፋ በመደፍጠጥ “በኩባንያ እብሪት” ተዘፍቆ ይገኛል በማለት ክስ አቅርቦበታል፡፡ የኮካ ኮላ ኩባንያ “የሚያዋርድ፣ የአድናቂዎቻችንን ስሜት እና የኮካ ኮላን ደንበኞች የሚጎዳ መግለጫ በመስጠቱ የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡
የቴዲ አፍሮ ተወካይ የኮካ ኮላን ፍረጃ ሙሉ በሙሉ እንዲህ በማለት ውድቅ አድርጎታል፣ “ከቴዲ አፍሮ ጋር የተፈጸመው የኮንትራት ስምምነት ማንዳላ የተወሰነ/Manadala Limited በተባለው በናይሮቢ የሚገኝ የምርት ተቋም ሶስተኛ ወገንተኝነት አማካይነት ነው፡፡“ አቶ ምስክር ሙሉጌታ [የኢትዮጵያ እና የኤርትራ እንዲሁም የማናዳላ ቲቪ ብራንድ ማናጀር] የተባሉ የኮካ ኮላ ተወካይ ባለስልጣን እኛን ከቀረቡን በኋላ ተነሳሽነቱን በመውሰድ የኮካ ፕሮጀክትን ምርጫ እና በቀጣይነትም እኛን ወደ ኮካ ስቱዲዮ በማምጣት የኮካኮላ ማዕከላዊ፣ የምስራቅ እና የምዕራብ አፍሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ከማንዳላ ቲቪ ጋር የኮንትራት ስምምነት እንድንዋዋል አድርገዋል…” አቶ ምስክር እንደ ሰራተኛ እና ማንዳላ ቲቪ ደግሞ እንደ በርካታ የሙዚቃ ንብረት አገልግሎቶች ኃላፊ ለኮካ ኮላ ማዕከላዊ፣ የምስራቅ እና ምዕራብ አፍሪካ ተወካይ በመሆን በአንድ ዓይነት የህግ ማዕቀፍ እና በኮካ ኮላ ኩባንያ ላይ ለሚያስከትለው እንደምታ ዋና መስሪያ ቤቱን በአትላንታ ያደረገውን ተቋም በመወከል የተደረገ የኮንትራት ስምምነት ነው፡፡”
እንደዚሁም ደግሞ በኮካ ኮላ መግለጫ ላይ ጉልህ የሆኑ መጣረሶች የተስተዋሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የኮካ ኮላ ኩባንያ ከቴዲ አፍሮ ጋር ምንም ዓይነት የኮንትራት ስምምነት ግንኙነት ባይኖረው ኖሮ በእርሱ ላይ ያነጣጠረ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ለምን አስፈለገው? በሌላም በኩል ኮካ ኮላ ቴዲ አፍሮ “ላደረገው ጥረት ሙሉ ክፍያ ተፈጽሞለታል” ብሏል፣ እንዲሁም የኮካ ኮላ ኩባንያ ከቴዲ አፍሮ ጋር የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማድመቂያ ሙዚቃን ለማሰቀረጽ የኮንትራት ስምምነት ባይኖረው ኖሮ “የተቀረጸው ሙዚቃ የኮካ ኮላ ሴዋ/Coc-Cola CEWA ንብረት ነው ማለት ለምን አስፈለገው?”
ኮካኮላን የዓለም እግር ኳስ የዋንጫ ጨዋታ ማድመቂያ የሆነውን ልዩ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በይፋ እንዳይለቅቀው ያስገደደው ተቃውሞ ምንድን ነው?
ለዓለም የእግር ኳስ የዋንጫ ጨዋታ ማድመቂያ በወጣው የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ግጥም እና ቅላጼ ላይ ምንም ዓይነት የፖለቲካም ወይም ሌላ አወዛጋቢ ጉዳይ የለበትም፡፡ በእርግጥ ቴዲ ኮካ ኮላ ዴቪድ ኮሬይ አንዲገጥም ባደረገው ግጥሞች ውስጥ ቃላትን በቀጥታ ወስዶ “ዓለም የእኛ ናት” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተርጉሞ ነበር ያቀርበው፡፡ ሌላ የጨመረውም ሆነ የቀነሰው ነገር የለም፡፡
ቴዲ አፍሮ ከ32 የዓለም የሙዚቃ ጥበብ ባለሙያዎች ለምንድን ነው እንዲነጠል የተደረገው እና የኮካ ኮላ የማዋረድ እና የዘለፋ ኢላማ እንዲሆን የተዳረገው? ኮካ ኮላ ለምንድን ነው የኢትዮጵያን ልዩ የቴዲ ሙዚቃ በአደባባይ ለመልቀቅ ያገደበትን ምክንያት? ለቴዲ ለግሉ ለመገለጽ ፈቃደኛ ያልሆነውስ? ኮካ ኮላ ለምንድን ነው ጉዳዩን ግልጽ በማድረግ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት የቴዲ አድናቂዎች የኢትዮጵያ ልዩ ሙዚቃ እንዳይወጣ የተደረገበትን ምክንያት ለመናገር ያልፈለገው?
ኮካኮላን ለምን እደምማስወግደው፣
የኮካ ኮላ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የኢትዮጵያን ልዩ ሙዚቃ ላለመልቀቅ ያወጣው ይፋ የተቃውሞ መግለጫ ለቴዲ አፍሮ ጠላቶች የደስታ እና የደረት ድለቃ ምንጭ ሆኗል፡፡ በድል አድራጊነት እንዲህ በማለት ድሰታቸውን ገልጸዋል፣ “ኮካ ኮላ ቴዲን አሽቀንጥሮ ጣለው!“
ኢንዱስትሪዎች መርዛማ ኬሚካሎችን ወደ ቆሻሻ መጣያ ቦታ እደሚጥሉ ሁሉ እኔም እንደዚሁ ኮካ ኮላን ወደ መርዛማ የኬሚካሎች ቆሻሻ መጣያ ቦታ ጥየዋለሁ፡፡ ይህንን ተመሳስሎ አነጋገር በቀላሉ የምጠቀምበት አይደለም፡፡ “የኮካ ኮላ ኩባንያ ካንሰር አምጭ በሆኑት ፋንታ ፒንአፕል እና ቫውልት ዜሮ ቤንዚን (በሁለት ምርቶቹ ላይ) ያለውን መጠጦች በህግ ተከሶ በስምምነት ጉዳይዩን እልባት ሰጥቷል፡፡“ ኮካ ኮላ 114 የምርት ዓይነቶችን በእንግሊዝኛ ቋንቋ አኳፑሬ ከሚለው ጀምሮ ዚኮ እስከሚለው ድረስ ድረ ገጹ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡
አሁን 114 ምርቶቹን ላለመጠቀም የማይለወጥ ዉሳኔ አድርጌአለሁ፡፡ አኳፑሬን፣ ባርቅን፣ ኮካ ኮላን፣ ዳሳኒን፣ ኢቪያንን፣ ፉዝን፣ ጋላሴኡን፣ ቪታሚን ዋተርን፣ ሐይ-ሲንን፣ ኢንካኮላን፣ ጀሪኮንን፣ ኪንሌይንን፣ ሊፍትን፣ ሚኑት ሜይድን፣ ኖርዘርን ኔክን፣ ኦዱዋላን፣ ፓዎሬድን፣ ሬድ ፍላሽን፣ ስፕራይትን፣ ታብን፣ ቫውልትን፣ ወርክስ ኢነርጅን፣ ዚኮን… አነዚህን መጠጦች በምንም ዓይነት ሁኔታ አልገዛም ወይም በምንም ዓይነት መንገድ አልጠቀምም፡፡ ማንም ቢሆን እነዚህን ምርቶች እንዲገዛ ወይም እንዲጠቀም አላደፋፍርም ወይም ደግሞ ሀሳብ አላቀርብም፡፡ በዚህም እውነታ መሰረት በዓለም ላይ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎቼ እነዚህን ምርቶች እንዳይገዙ ወይም ደግሞ እንዳይጠቀሙ በአክብሮት እጠይቃለሁ!
ሁላችንም አንድ በመሆን እንተባበር እና ኮካ ኮላን እና 114 የሚሆኑ ምርቶቹን ባለመጠቀም ከገበያ ውጭ እናድርጋቸው፡፡
ለአስርት ዓመታት የኮ ካላ ኩባንያ ምርቶቹን በደስታ እና የደስታ ስሜት በተቀላቀለበት ዓይነት ሁኔታ እና መፈክሮችን ሊረሱ በማይችሉ ቃላት በማሽሞንሞን የኮርፖሬት ንግዱን ሲካሄድ ቆይቷል፣ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እና አጠቃላይ የንግድ እሴቶቹን ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፡፡ ባለም የተሰራጩት መፈክሮቹ እንዲህ ይላሉ፣ “ኮካ፡ እውነተኛ ነገር ነው“፣ “ከኮካ ጋር ነገሮቸ ሁሉ የተሻሉ ይሆናሉ“፣ “በአሁኑ ጊዜ ዓለም የሚፈልገው ኮካን ነው”፣ “ኮካ ይህ ነው“፡፡ ኮካ ኮላ እንዲህ ብሎ የሚጀምር የቴሌቪዥን የንግድ ሙዚቃ አለው፣ “የተሟላ ደስታ ባለበት ሁኔታ በመዘመር ዓለምን ለማስተማር እወዳለሁ“፣
ኮካ እንደ እስፕራይት እውነት ሳይሆን ዉሸት
በኢትዮጵያ ነገሮች ኮካ መራራ ያደርጋል፣
ኮካ ኮላ በኢትዮጵያ ጥላቻ እንጅ በኢትዮጵያ ፍቅርን የሚያመጣ አይደለም፣
ኮካ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እድሜ ሳይሆን ጥላቻ ነው የጨመረው፣
ኮካ ኢትዮጵያውያንን ፈገግ የሚያደርግ ሳይሆን በጥላቻ እንዲሞሉ ያደረገ ነው፣
ብዙ የስኳርነት ባህሪው ስለሚያፍነኝ ኮካን አልጠጣም፣
የዓለም ህዝብ ኮካን ወይም ደግሞ ማንኛውንም 113ቱን የኮካ ምርቶች እንዳይገዛ እፈልጋለሁ፣
በአሁኑ ጊዜ የመጨረሻው እና የዓለም ህዝብ የማይፈልገው ነገር ቢኖር ኮካ ነው፣
ኮካ ዘበት ነው!
የኢትዮጵያ ታዋቂ ሙዚቃ በኩሩው የኢትዮጵያ ወፍ ሲዘመር እንዳይሰማ የተደረገበት ምክንያት ለምን እንደሆነ አውቃለሁ፣
ቴዲ አፍሮ የእራሱን ህዝብ እና አገር ይወዳል፣ ለዚህ ዓላማው አየተቀጣ ይገኛል፡፡
ውርደት ቀለቡ የሆነው እና የትንሽ ጭንቅላት ባለቤት የሆነው በኢትዮጵያ ህዝቦች ጫንቃ ላይ ከፍላጎታቸው ውጭ ተቆናጥጦ የሚገኘው ገዥው አካል ኮካ ኮላ የቴዲን ሙዚቃ እንዳይለቅቀው ተጽዕኖ ያደረገበት ለመሆኑ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ በበቀል እና በጥላቻ የተሞሉት ገዥ ጽንፈኛ የወሮበላ ስብስብ ቡድን የቴዲ አፍሮ ትክክለኛ ጌታው ማን እንደሆነ ለማሳየት ያደረጉት ከንቱ ምግባር ነው፡፡ እነዚህ የበቀል እና የጥላቻ ቋቶች እንዴት ባለ የማታል ዘዴ እና የተለሳለሰ በሚመስል ማደናገሪያ እየተጠቀሙ በቴዲ እና በደጋፊዎቹ ላይ እየወሰዷቸው ያሏቸውን ዕኩይ ተግባራት ለማሳየት ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከኮካ ኮላ ጋር የተደረገውን አጠቃላይ ስምምነት ብልግና በተቀላቀለበት መልኩ እየሳቁ ሲመለከቱት ቆይተዋል፡፡ እንዲቀጥልም ፈቅደዋል፡፡ እንዲህም ብለው ነበር፣ “ቴዲ ከልቡ ጥረት ያድርግ እና ቆንጆ የሙዚቃ ስራ ይዞ ይቅረብ“፣ መዳፎቻቸውን በማፋተግ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ጥሩ አድርገን በመበቀል ሊረሳው በማይችል መልኩ አርአያ የሚሆን ትምህርት እንሰጠዋለን“፡፡ በእነዚህ የእኩይ ምግባር አራማጆች የደም ስሮች ውስጥ ጥላቻ እና በቀልተኝነት ተዋህደዋል፡፡
በመጨረሻዋ ደቂቃ በኮካ ኮላ በኩል የበቀል እርምጃቸውን ወስደዋል፡፡ (ኮካ ኮላ እ.ኤ.አ በ2013 ሶስተኛውን የጠርሙስ ፋብሪካ በድሬ ዳዋ ከተማ ያጠናቀቀ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) ኮካ ኮላ ገበያውን በኢትዮጵያ ለማስፋት ከፈለገ የቴዲ አፍሮን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማድመቂያ ሙዚቃ መልቀቅ የለበትም፡፡ ምስኪኑ ኮካ ኮላ በሰይጣኖች እና በቴዲ አፍሮ መካከል በተያዘው ጉዳይ ላይ መሳሪያ በመሆን የይስሙላ መወዛወዝን ይዞ ቀትረ ቀላል ሆኖ ይገኛል፡፡
በእርግጥ ያ ሁሉ በገዥው አካል እየተደረገ ያለው በሸፍጥ የተሞላ እርባና የለሽ ድርጊት በቴዲ አፍሮ ስብዕና ላይ የሚያመጣው ነገር አይኖርም፡፡ ቴዲ በሚመስጠው ቅላጼው “ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል” የሚል ሙዚቃውን ማሰማቱን ይቀጥላል፡፡ “ሙሉ ይቅርታን ከማድረግ በላይ በቀል የለም” የሚለውን መርህ ነው የሚከተለው፡፡ እሱን ጥፋተኛ ያደረጉትን ይቅርታ ያደርግላቸዋል (ጃህ ያስተሰርያል!)
በኢትዮጵያ ላለው ወሮበላ ዘራፊ ቡድን ማንኛውም ተመልካች የቴዲ አፍሮን ስም ጥላሸት ለመቀባት፣ ለማበሳጨት እና የአገሪቱ ብሄራዊ የአንድነት እና የክብር መገለጫ ምልክት የሆነውን ጀግና ታዋቂ የኢትዮጵያ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ስሜት ለመጉዳት በሚያደርጉት እርባና የለሽ የስነ ልቦና ጦርነት ላይ እንግዳ ሊሆንበት አይችልም፡፡ ለበርካታ ዓመታት እነዚህን ቆሻሻ የማታለል ድርጊቶቻቸውን በተቀናቃኞቻቸው ላይ ሲፈጽሙ ቆይተዋል፣ አሁንም ይህንን እኩይ ምግባራቸውን በተጠናከረ መልኩ ይቀጥሉበታል፡፡
እውነታው ግን የቴዲ አፍሮ የኪነ ጥበብ ሙያ ለኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት የማይሞተውን ጠንካራ ፍቅር አሳይቷል፡፡ በሁሉም ሙዚቃዎቹ እና ግጥሞቹ ቴዲ የኢትዮጵያን ክብር ከፍ አድርጎ አሳይቷል፣ እንዲሁም ለወሮበላ ዘራፊዎች እና ለከሀዲዎች እውነታውን ነግሯቸዋል፡፡ የእርሱ ሙዚቃ፣ መዝሙሮች እና ግጥሞች የአውዳሚነት ጥረቶችን በማዳከም በኩል የኢትዮጵያን ህዝብ እምነት እና ሞራል ከፍ በማድረግ ውጤታማ ክስተቶችን ፈጥረዋል፡፡ ቴዲ በግጥሞቹ እንዲህ በማለት አውጇል፣ “ያዙት፣ ጠበቅ አድርጋችሁ ያዙት! እርስ በእርሳችን ይቅርታ ካደረግን እና ከተፋቀርን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቅርብ ነው፡፡“
ቴዲ ተያስተሰርያል በሚለው አልበሙ በቡድን የወሮበላ ስብስብ ወንጀለኞች የተያዘውን ዙፋን አጋልጧል፡፡ መዝሙሩን በመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም የጎሳ መሰረት ያላቸው ህዝቦች በስምምነት፣ በሰላም እና በፍቅር በአንድ ኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በህብረት እንዲኖሩ አዚሟል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን የሙዚቃ ክህሎት በመጠቀም የክርስቲያን እና የእስልምና እምነት ተከታዮች እጆቻቸውን በማጣመር በአንድነት በሰላም እና በፍቅር እንዲኖሩ አስተምሯል፡፡ ቴዲ የታደለውን የዓላማ ጽናት ለእኩይ ምግባር እንዲሸጥ ለማድረግ ለመቁጠር ከሚያዳግተው በላይ በርካታ ሀብት እና ሽልማት ቀርቦለት ነበር፡፡ ሆኖም ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ነብሱን ለወሮበላ ዘራፊዎች ለመሸጥ እንደማያስብ ጽኑ ተቃውሞ አሳይቷል፡፡
ቴዲ አፍሮ በእርሱ የትውልድ ዘመን ካሉ የጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ የበለጠ እና የላቀ ተነሳሽነት ያለው ወጣት ከያኒ ነው፡፡ ቴዲ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት ወጣቶችን ቀልብ በመሳብ ዴሞክራሲ፣ ነጻነት እና ሰብአዊ መብቶች በአንዲት ኢትዮጵያ እንዲጠበቁ እና እንዲከበሩ አነቃንቋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የእኩይ ምግባር አራማጆቹ በሙዚቃው ያሳየውን አርበኝነት ለመበቀል አሁን ያዘጋጀው ሙዚቃ እንዳይለቀቅ በመከልከል “ዋጋ” እንዲከፍል እያደረጉ ነው፡፡ የእውነትን መዝሙርን በምንም ዓይነት መልኩ ማገድ እና ጸጥ ማድረግ አይቻልም፡፡
ቴዲ የሚሸጥ ዕቃ አይደለም! ቴዲ በኮካ ኮላ ወይም በወሮበላ ዘራፊ ቡድን ባለብዙ ቢሊዮን ገንዘብ ባለቤት ቱጃሮች የሚገዛ ሸቀጥ አይደለም፡፡ እርሱን ለማዋረድ እና ለመዘለፍ መሞከር ይችላሉ፡፡ ቀላሉ እውነታ ግን ቴዲ በእራሱ እና በሀገሩ ላይ የራስ ደጀን ተራራን የሚያህል ኩራት እና ክብር ያለው ትንታግ ወጣት መሆኑን ያለመገንዘባቸው ነው፡፡ ወሮበላ ዘራፊዎች ከህዝብ በሰረቁት እና በዘረፉት ኃብት ምንም ያህል ኃብት ቢያከማቹ ማጅራት መችዎች ለዘላለም የሚኖሩ ወሮበላ ዘራፊዎች፣ በጥባጮች እና ማጅራት መችዎች ሆነው ይቀራሉ፡፡ ይህም የሚያዋርድ የቋንቋ ቃላትን መደርደር አይደለም፡፡ ይህ እንደ ቀትር ጸሐይ የበራ ኃቅ ነው!
እባካችሁ ቴዲ አፍሮ በእራሱ እና በእናት ሀገሩ ላይ ኩራት እና ፍቅር ያለው ትንታግ ወጣት በመሆኑ ምክንያት ብቻ አትጥሉት! እርሱን አትጥሉት፣ ምክንያቱም የሀገር ምልክት ነው፡፡ እርሱን አትጥሉት፣ ምክንያቱም የሀገር አርበኛ ነው፡፡ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ እንደዚያ ሆኖ ነው የተወለደው!
በኢትዮጵያ ያለው እውነተኛው ቴዲ አፍሮ እንጂ የኮካ ሸቀጥ አይደለም!
ዓለም እና አብዛኛው የዓለም ህብረተሰብ እንዲሁም የዓለም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴዲ አፍሮን ይፈልገዋል፡፡ ቴዲ የአፍሪካ የሙዚቃ ሊቅ ነው፡፡ የእርሱ የሙዚቃ ግጥም “ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል” በሚል መርህ ላይ የተዋቀረ ነው! አፍሪካውያን/ት ግጥሞቻቸውን እና የሙዚቃ ፍቅሮቻቸውን ወደ አንድነት መድረክ እንዲያመጡ እያደረገ ነው፡፡
ቴዲ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ታዋቂው የጥበብ ባለሙያ ነው ምክንያቱም የእርሱ ሙዚቃ ህዝቡን ወደ አንድነት እያመጣ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያውያን/ት እና አፍሪካውያን/ት ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አብሮነትን እና መልካም ነገርን ሁሉ ይዘምራል፡፡ የእምቢተኝነት መዝሙሮችን ይዘምራል፡፡ ስለእርቅ አስፈላጊነት፣ መግባባት እና ይቅርባይነት ይዘምራል፡፡ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት አጠንክረው ለሚሰሩ ሀገር ወዳዶች ሁሉ የስራ መዝሙሮችን ይዘምራል፡፡ ስለኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ማራኪነት እና ስለህዝቧ ደግነት ይዘምራል፡፡ ቴዲ አፍሮ በአፍሪካ ላይ ስላለው ፍቅር ይዘምራል፡፡
የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ህይወትን የበለጠ አስደሳች አድርጎታል፡፡ የዓለም ህዝብ ቴዲ አፍሮ ሰለፍቅር ሲዘምር እንዲያዳምጠው ማየት እፈልጋሁ፡፡ በማያቋርጥ አምባገነንነት መዳፍ ስር ወድቃ ህይወት አልባ እና ደስታ ከራቃት አገር ይልቅ የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ህይወትን እና ደስታን ይጨምራል
ቴዲ አፍሮ እውነተኛ ነገር ነው! ቴዲ አፍሮ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ነው!
ቴዲ አፍሮ በቅርብ ጊዜ ያሳተመው “ጥቁር ሰው” የተባለው አልበሙ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1896 በኢጣሊያ ቅኝ ገዥ ወራሪ ኃይል ላይ የተቀዳጀችውን ድል የሚዘክር ነው፡፡ ያ አንጸባራቂ ድል በአፍሪካ እና በዓለም ታሪክ ላይ ጉልህ ምዕራፍን ይዞ ይገኛል፡፡ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ለመከፋፈል እና የአፍሪካን ህዝቦች በባርነት በመያዝ ጥሬ ሀብቷን ለመዝረፍ በማቀድ በበርሊን ከተማ ከተደረገው ጉባኤ ሁለት ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በኢጣሊያን እና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገው የመጀመሪያው ጦርነት የኢትዮጵያው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የኢጣሊያንን ወራሪ ወታደሮች በአድዋ ጦርነት ላይ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የሞቱት ሞተው የተረፉት እግሬ አውጭኝ በማለት ወደመጡበት እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ የአድዋ ጦርነት የአውሮፓ ኃያል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ወታደሮች ጉልበት ስር እንዲንበረከክ የተገደደበት ጊዜን ያስታውሳል፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያ እንደገና እ.ኤ.አ በ1935 ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ ሁለተኛውን የኢጣሊያን እና የኢትዮጵያን ጦርነት ለኮሰች፡፡ በዚህም ጦርነት ለዘላለም ሊረሱት የማይችሉት የሽምቅ ውጊያን ሽንፈት ተከናንበው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ (በአፍሪካ ከሌላዋ ላይቤሪያ በስተቀር) ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች ከቅኝ ግዛትነት ነጻ የሆነች አገር ሆና እንድትቆይ አድርጓታል፡፡ ቴዲ አፍሮ ስለፍርኃት የለሽ መሪዎቿ እና ነጻነታቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን ላለማስደፈር በቀስት እና በደጋን እንዲሁም ኋቀር በሆኑ ጠብመንጃዎች በመታገዝ ብቻ ሳይሆን በነበራቸው ኩራት እና ወኔ በጀግንነት ተዋግተው የሀገራቸውን ነጻነት እና ህልውና ላስከበሩት ተራ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም ዘምሯል፡፡
በቴዲ እና ልዩ በሆኑት የኪነ ጥበብ ስራዎቹ ኮርቻለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ልዩ ባህል እርሱ ላበረከታቸው እጅግ መጠነ ሰፊ በሆኑ አበርክቶዎቹ ሁሉ በጣም ኮርቻለሁ፡፡ በሙዚቃ ስራዎቹ አማካይነት ፍቅር፣ አንድነት እና በህዝቦች መካከል ብሄራዊ ዕርቅ እንዲወርድ ባደረጋቸው እልህ አስጨራሽ ጥረቶች ላይ እጅግ ኮርቻለሁ፡፡ ቴዲ ልዩ የመንፈስ ጽናት ያለው እና የውርደትን ትጥቅ ያስፈታ ትንታግ ከያኒ ወጣት ነው፡፡ የእርሱን ዝና እና ክብር ለማንቋሸሽ በተከታታይነት ዘመቻ ሲያደርጉበት ምንም ዓይነት ምላሽ አይሰጣቸውም፡፡ በእርግጠኝነት እንዲህ ብቻ ይላል፣ “ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል፡፡“ በጥላቻ የተሞሉ የእኩይ ምግባር አራማጆች ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል ብሎ የተነሳን ሰው በምንም ዓይነት መልኩ ሊያሸንፉ አይችሉም፡፡
አሁን በህይወት የሌለው መለስ እ.ኤ.አ በ2008 በሰው ላይ የመኪና አደጋ አድርሶ አምልጧል በሚል በውሸት የተቀነባበረ የሸፍጥ ክስ ሳቢያ ቴዲ አፍሮን ወደ እስር ቤት በወረወረው ጊዜ በቴዲ ጎን ቆሜ በዓለም ህዝብ የሕሊና ፍርድ ቤት ስከራከር ነበር፡፡ እንደዚሁም ቴዲ አፍሮ ፈጽሟቸዋል በሚል የፍብረካ ወንጀሎች በቁጥጥር ስር ውሎ ክስ እንዲመሰረትበት መለስ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ የተቀነባበሩ 10 አገር ከመውደድ ጋር ተያይዞ የሰራዉን የ “ወንጀል ክሶች” ዝርዝር መዝግቤ ይዣለሁ፡፡ የመለስ እኩይ የሙት መንፈስ በቴዲ ግጥሞች በተገለጹ እውነቶች እና እምነቶች ሲወጋ እና ሲባንን ይኖራል፡፡
ቴዲ እ.ኤ.አ በ2010 ወደ ሎስ አንጀለስ በመጣበት ወቅት የእርሱን የሙዚቃ ትርኢት ተመልክቸ ነበር፡፡ የሙዚቃ ትርኢቱ አስደናቂ ነበር፡፡ የቴዲ የሙዚቃ ትርኢት ወጣት በነበርኩበት ጊዜ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በመጀመሪያው እረድፍ ላይ ቆሜ ያየሁትን የታላቁን ቦብ ማርሌይን ካያ እና የህይወት ግብግብ ጎዞ/Kaya and Survival tour በሚል ርዕስ የቀረበውን ሙዚቃዊ ትርኢት እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡ ቦብ ማርሌይ በአፍሪካ ነጻነት እና በፓን አፍሪካኒዝም ላይ እንደነበረው ፍቅር ሁሉ ቴዲ አፍሮም በተመሳሳሳይ መልኩ በነጻነት፣ በአንድነት፣ ዕርቀ ሰላም በማውረድ እና በአትዮጵያ ህዝቦች ላይ ፍቅር እንዲሰፍን ይፈልጋል፡፡ እንደ ማርሌይ ሁሉ የቴዲ ሙዚቃም ቀስቃሽ፣ አስደማሚ እና ልብ አንጠልጣይም ነው፡፡ እንደ ማርሌይ ሁሉ ቴዲም ስለፍቅር፣ ሰላም፣ ተስፋ፣ እምነት፣ ለጋሽነት፣ ፍትህ፣ ዕርቅ፣ መግባባት እና ይቅርታ አድራጊነት ይዘምራል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ነገሮች ናቸው የቴዲ አፍሮን የሙዚቃ የቅላጼ ኃይል በኢትዮጵያውያን/ት ልብ እና ልቦና ውስጥ ዘልቀው በመግባት የተስፋ ማጣት ቁስልን፣ ማለቂያ የሌለውን ጭቆና እና ኢትዮጵያን ከአምባገነንነት መቃብር ለማዳን ለቀዶ ጥገናው ስራ በመስፊያ ክርነት እያገለገሉ ያሉት፡፡ ቴዲን በኢትዮጵያ ውስጥ ስለፍቅር፣ ሰላም እና ፍትህ ከመስበክ እና ከመዘመር የሚያግደው ምንም ምድራዊ ኃይል የለም፡፡
ቴዲን የኢትዮጵያ ጅግና የስነ ጥበብ ባለሙያ እና የእራሴም ግላዊ ጀግና አድርጌ እቆጥረዋለሁ!
ዓለም የእኛ ናት የኮካ አይደለችም፡፡ አንድ ኮካ ኮላን በአንድ ሰው ማስወገድ፣ አንድ ኮካ ጠርሙስ በአንድ ጊዜ ማስወገድ አለብን!
የእኔን ሳምንታዊ ትችቶች ለበርካታ ዓመታት በመከታተል ላይ ለሚገኙት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎቼ እኔን እዲቀላቀሉኝ እና “ኮካን ከመጠቀም እንዲያስወግዱ” የአክብሮት ጥሪየን አቀርባለሁ!
ኮካ ኮላ በጨለማ እንደሚካሄድ የኃይማኖት ክብረ በዓል የሻማ ብርሀን ይዘን ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ብንወጣ ጉዳዩ አይደለም፡፡ ኮካ ኮላ ስለእኛ ሞራል ዝቅጠት ጉዳይ ደንታ የለውም፡፡ የኮካ ኮላ ዋና ጉዳይ ከሁሉም በላይ ስለትርፍ እና ኪሳራ ማሰላሰል ብቻ ነው፡፡ ኮካ ኮላ ከ200 በላይ በሚሆኑ አገሮች ከ30 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ሽያጮችን ያካሂዳል፡፡ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለገበያ ማስተዋወቂያ ዘመቻ ወጭ ያደርጋል፡፡ ኮካ ኮላ በውል ሊገነዘበው የሚችለው ብቸኛው ቋንቋ የትርፍ እና ኪሳራ ቋንቋ ነው፡፡
በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ኮካ ኮላን መግዛት እና መጠቀምን ቢያቆም እና የ114 የኮካ ኮላ ምርት ውጤቶችን መግዛት እና መጠቀምን ብናቆም ዓለማችንን ከኮካ ኮላ መዳፍ ስር በ114 ቀናት ውስጥ ማላቀቅ እንችላለን፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ አንባቢዎቼ ኮካ ኮላ መጠጣትን እንዲያቆሙ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ የእራሳቸው “የኮካ መጠቀም ማስወገጃ ቀን” እንዲኖራቸው እጠይቃለሁ፡፡ ሁልጊዜ ኮካ ሲቀርብ አሻፈረኝ አልፈለግም አንዲሉ !!!
ይህ የማስወገድ ስልት በኮካ ኮላ ላይ ብቻ የተወሰነ መሆን የለበትም፡፡ ስለኢትዮጵያ ብሄራዊ ኩራት ጭምር ነው፡፡ አገራችንን ከሶዳ ቸርቻሪ እና ከወሮበላ ዘራፊዎች ማላቀቅ አስፈላጊ ነው፡፡
አንድ የካካ ኮላ ጠርሙስን ባንድ ሰው እንዋጋ እላለሁ፣ አንድ ሰው ኮካ ኮላ በአንድ ጊዜ ማስወገድ ይቻላል! እምቢ ኮካ አልፈልግም
ኮካ ኮላ እንዲህ በማለት ጉራዉን ይነዛል ፣ “ዓለም የእኛ ናት!“ አኛ ደግሞ ለ ኮካ ኮላ ኢትዮጵያ የእኛ መሆኗን ማሳየት አለብን!
በመጨረሻም የእኔ ኮካ ኮላን መጠጣት የማስወገድ ዓላማ ቴዲን ነጻ እንዲያደርገው በኮካ ኮላ ላይ ውጥረት ለመፍጠር አይደለም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ከጀርባ መጋረጃ ሆኖ የኮካ ኮላን እጅ ለሚጠመዝዘው ለአንደበተ ድሁሩ የገዥ አካል እውነተኛውን ነገር እስከ አፍንጫው ለመንገርም አይደለም፡፡ ይህንን የማደርገው ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ስለሚሰማኝ ክብርና ሞገስ ስለማስብ ብቻ ነው፡፡
ተባበሩኝ እባካቸሁ ለክብራችሁ
ተባበሩኝ ለክብራችን
ውርደት እስከመቼ ተሸክምን እንችላለን?
ባንደበታችን መናገር ባንችል
ባንደበታችን የሚገባዉን ማስቆም አንችላለን ::
ተባበሩኝ ወገኖች ጀግኖች ለክብራችን !
ኮካ ኮላ ነው በሉ የሚያስጠላ፥ የሚያጣላ::
በግሌ የምለው አንዲህ ነው፥
ኮካ ኮላ ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ካዘዛቸው 32 አገራዊ ልዩ ሙዚቃዎች መካከል 31ዱን ከለቀቀ እና የታላቂቱ የኢትዮጵያን ልዩ ሙዚቃ አሽቀንጠሮ ከጣለ በበኩሌ ኮካ ኮላን የምለው “ተምዘግዝጋችሁ ገሀነም ግቡ” ነው!!!”
ኮካ ኮላ፥ የሚያስጠላ የሚያጣላ!!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሰኔ 10 ቀን 2006 ዓ.ም
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ

Sunday, June 15, 2014

ጄኔራል ሰዓረና ጋዜጠኛ እስክንድር (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

ሰኔ 1 ቀን 1997ዓ.ም፤ በአዲስ ከተማ ት/ቤት የተጀመረው ተማሪዎችንና ንጹሃን ዜጐችን በግፍ የመግደል እርምጃ ተከትሎ አብዛኛው ባለስልጣናት ልጆቻቸውን ከየት/ቤቱ በአጃቢ ያስወጡ ነበር። ወደ ካቴድራል ት/ቤት በሁለት ኮብራ ተጭነው የተላኩ 20 ልዩ የፌዴራል ፖሊሶች የጄ/ል ሰአረና የጄ/ል ብርሃነ (ወዲ መድህን) ሴት ልጆችን አጅበው ሄዱ።
ሁለቱ ሴት ልጆች በማግስቱ አሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ ተመቶላቸው ዓርብ ሰኔ 3 ቀን በረሩ። የብዙ ባለስልጣናት ልጆች በተመሳሳይ እንዲወጡ ተደረገ። ..29ሺህ የአሜሪካ ዶላር በተርም እየተከፈለላቸው መማር ቀጠሉ። የአዜብ ልጅና የእህቷ ልጅ፣ (በነገራችን ላይ አርአያ መኮንን ይባላል፤ በ1995ዓ.ም ቦሌ ከሩዋንዳ ፊት ለፊት ጥቂት ገባ ብሎ አዜብ ለዚህ ወጣት በ7 ሚሊዮን ብር ቪላ ቤት ገዝታ በስጦታ አበርክታለች። የቪላው ኪራይ ሂሳብ በስሙ ባንክ ይገባለታል) ..የአርከበና ስብሃት ልጆች በቨርጂኒያ፣ የሽፈራው ጃርሶ ልጆች በካሊፎርኒያ፣ የፖሊስ ኮሚሽነር የነበረው ወንጀለኛውና 5ሚሊዮን ዶላር ሰርቆ የወጣው ተስፋዬ መረሳ ልጆች በኒዮዎርክ….ወዘተ በተቀማጠለ ኑሮና በውድ ክፍያ መማር ያዙ።ባለፈው አመት በነርስ የተመረቀችው የጄ/ል ሰአረ ልጅ ሐመልማል ሰዓረ የምርቃት ፕሮግራም ላይ ጄኔራሉ ተገኝተው ነበር።…ወደ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንለፍ። እስክንድር በላባቸው ሰርተው ሃብት ካፈሩ ጥሩ ቤተሰቦች የተገኘ ልጅ ሲሆን የተማረው በሳንፎርድ ት/ቤት ነው። ከዚያም አሜሪካ መጥቶ ትምህርትና ህይወቱን ቀጠለ። “አገር አማን” ብሎ በዘመነ ኢህአዴግ አገር ቤት ገባ። ተደጋጋሚ እስርና ድብደባዎችን አሳለፈ። እነሆ “አሸባሪ” ተብሎ ከሌሎች ንፁሃን ጋር በእስር እየማቀቀ ይገኛል።
seareእነ ጄ/ል ሰአረና መሰሎቻቸው በመቶ ሺህ በሚቆጠር ዶላር ልጆቻቸውን በአሜሪካና አውሮፓ ሲያስተምሩና ሲያንደላቅቁ፣ እንዲሁም ልጆቻቸውን ለማስመረቅ ሲገኙና ሲደሰቱ በአንፃሩ በመፃፉና ሃሳቡን በመግለፁ ብቻ እስር ቤት የተወረወረውና ናፍቆት ልጁን እንዳያሳድግ የተደረገው እስክንድር ነጋ ጭራሽ ቤተሰቡ ያወረሱትን ቤት በግፍ እንዲነጠቅ ተደረገ። በጄኔራሎቹና ባለስልጣናቱ ሰፈር ግን በሚሊዮን ብር የተገነባ ቪላ፣ ልጆቻቸው የሚንደላቀቁበት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ዶላር…ወዘተ አለ። ይህ ከህዝብ የተዘረፈ የአገር ሃብት ነው!! የጄ/ል ሰዓረ ባለቤት ኰ/ል ፅጌ በስማቸው በገርጂ የተገነባውና ሰባት ሚሊዮን ብር የፈጀው ቪላ ሲገኝ የሚገርመው የቅጥር ግቢው ወለል በእምነበረድ መሸፈኑ ነው።ሌላው በሙስና የታሰሩት የደህንነት ሹሞቹ ወ/ስላሴና ገ/ዋህድ..መኖሪያ ቤት ውስጥ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ቦንቦች እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና የቤት ካርታ ወዘተ መገኘቱን ገዢው ፓርቲ ይፋ አድርጓል። ዛሬ ጠያቂ ባይኖርም ቅሉ ነገር ግን ጄኔራሎቹና ባለስልጣናቱ እንደነ ወ/ስላሴ ዘርፈው ያካበቱት ለመሆኑ አያጠያይቅም። የሚገርመው መፅሐፍትና ጋዜጣ የተገኘበት የእስክንድር ቤት ሲወረስ በአንፃሩ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና ሚሊዮኖች ተገኘበት ያሉትን የዘራፊዎቹን የሙስና ቤት አልነኩም።… እንደ እስክንድር ሁሉ አቶ አንዱአለም፣ አቶ በቀለ፣ ውብሸት፣ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ተወካዮች እነ አቡበከር.. በሙሉ ልጆቻቸውን እንዳያሳድጉ የተደረጉ የህሊና እስረኞች ናቸው!! እንዲሁም ጄ/ል ሰአረ በምሳሌነት ተጠቀሱ እንጂ የአብዛኛው ባለስልጣን ከዘረፋ የተገኘ ህይወት ተመሳሳይ ነው። የአንዳንዶቹ ባለስልጣናትና ልጆች የአሜሪካ ውሎና ኑሮ የሚያሳይ በፎቶ የተደገፈ ማስረጃ እንዳለ ሳልጠቁም አላልፍም።…
(በፎቶው ጄ/ል ሰዓረ ሴት ልጃቸውን አቅፈው ሲያስመርቁና ሲደሰቱ- በአንፃሩ እስር ቤት ከጋዜጠኛ ሰርካለም የተወለደው ሕፃን ናፍቆት እስክንድር በጨቅላነቱ በስደት ያለ አባት እንዲያድግ ተፈርዶበት ይታያል..)
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ

Saturday, June 14, 2014

የዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል የትምህርት ማስረጃዎች ሐሰተኛ ናቸው ተባለ

 by  ናፍቆት ዮሴፍ
በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ሲቪል መሀንዲስ እንደሆኑና ከአውስትራሊያና ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መመረቃቸውን ሲገልፁ የቆዩት የዶ/ር ኢንጂነር ሳሙኤል ዘሚካኤል የትምህርት ማስረጃዎች ሀሰተኛ እንደሆኑ ሬድዮ ፋና ትላንት ዘገበ፡፡
ኢ/ር ሳሙኤል በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ቃለ-ምልልስ ከሰጡ በኋላ እንግዳ አድርገዋቸው እንደነበር የገለፁት የ“አዲስ ጣዕም” አዘጋጆች፤ ኢ/ር ሳሙኤል በ1996 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ድግሪያቸውን ሲቀበሉ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ እንደነበሩ፣ ከአውስትራሊያና ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መመረቃቸውንና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንዳገኙ መናገራቸውን አስታውሰዋል፡፡ አዘጋጆቹ የመረጃዎቹን ትክክለኛነት ሲያጣሩ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1991 ጀምሮ ሳሙኤል ዘሚካኤል በሚባል ስም የተመዘገበና የተመረቀ ለማወቅ እንደሌለ ገልፀዋል፡፡
ከአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪ እንዳገኙ ቢገልፁም ዩኒቨርሲቲው በተባለው ዘርፍ ስልጠና እንደማይሰጥ አረጋግጧል ያሉት አዘጋጆቹ፤ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተምሬያለሁ በሚሉት ጉዳይ ላይ አንዴ በተልዕኮ ተምሬ ተመርቄያለሁ ቢሉም ማስረጃ አላቀረቡም ብለዋል፡፡ “በእርግጥ ኢ/ር ሳሙኤል አነቃቂ ንግግሮችን በተለያዩ መድረኮች ላይ ያደርጋሉ” ያሉት አዘጋጆቹ፤ የታዋቂ የግለሰቦችን ስም እየጠሩ የተጋነነ ነገር እንደሚናገሩና የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ያለ ምንም ማስረጃና ለፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሚያበቃ መስፈርት ማዕረጉን እንደሰጣቸው ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የተማሪዎችን ቀን ምክንያት በማድረግ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ለተማሪዎች የማነቃቂያ ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲም ቀጠሮ ተይዞላቸው እንደነበር የገለፁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዲላ ዩኒቨርስቲ መምህር፤ ሰሞኑን ከተናፈሰው ወሬ ጋር በተያያዘ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተያዘላቸው ፕሮግራም መሰረዙን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን ለአቶ ሳሙኤል በተደጋጋሚ ብንደውል ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ

Thursday, June 12, 2014

ድምጻችን ይሰማ መግለጫ አወጣ፦ “በህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ላይ በማረሚያ ቤት እየተደረገ ያለው ወከባ በአስቸኳይ ይቁም!”

ረቡዕ ሰኔ 4/2006
የታሰሩት ኮሚቴዎች
የታሰሩት ኮሚቴዎች
በሐሰት የሽብር ክስ ህገ መንግስታዊ መብቶችን በጣሰ ሁኔታ መሪዎቻችንን እያጉላላ የሚገኘው መንግስት በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚያደርገውን ወከባ ቀጥሎበታል፡፡ ገና ወደማረሚያ ቤት ከተዛወሩበት ጊዜ አንስቶ ጠያቂዎችን በማጉላላት፣ የጥየቃ ሰአትን ከሌሎች በተለየ መልኩ በመገደብ፣ እንዲሁም በጠያቂዎች ቁጥር ላይ ገደብ በማድረግ በተለያዩ ወቅቶች መብታቸውን ሲነግፍ የቆየው መንግስት ዛሬ ደግሞ በታሪካዊው የካንጋሮ ፍርድ ቤት የችሎት ሂደት ምስክሮቻቸውን እያቀረቡና ትክክለኛው የህዝበ ሙስሊሙ ትግል ገጽታ በችሎት እየተመሰከረ ባለበት በዚህ ቅትት በፍርድ ቤት እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት ለመቋቋም ወኪሎቻችን ላይ የተለያዩ ወከባዎችን እየፈጸመ ይገኛል፡፡ እስካሁን ድረስ በእስር ቤቱ ታሪክ በምንም መልኩ የማያስጠይቅን፣ ይልቁንም በማረሚያ ቤቱ ደንብ ጥበቃ የተደነገገለትን ገንዘብ የመያዝ መብት እንደወንጀል በመቁጠር በኮሚቴው ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እና በሸኽ መከተ ሙሄ ላይ፣ እንዲሁም በሌሎች ታሳሪዎች ላይ ሲያደርስ የነበረውና በቅርቡ የተረጋጋው ወከባ መሪዎቻችንን የማጥቂያ ሰበብ ፍለጋ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ግልጽ ነበር፡፡
አሁንም ይህንኑ ህገወጥ ድርጊቱን የቀጠለበት የእስር ቤቱ አስተዳደር በዞን አንድ በሚገኙ ጀግኖቻችን፣ (ማለትም በሸኽ መከተ ሙሄ፣ በኡስታዝ አቡበከር፣ በኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፣ በኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ፣ በጋዜጠኛ አቡበከር ዓለሙ፣ በወንድም አብዱረዛቅ አክመል እና በወጣት ሙባረክ አደም) ላይ በዞን አንድ በሚገኙት 8 ክፍሎች እንዲበታተኑና እንዲለያዩ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡ ጓዞቻቸውንም ወደየተመደቡበት ክፍሎች እንዲቀይሩ እንደተነገራቸው ታውቋል፡፡ ባለበት የጤና ችግር ምክንያት ልዩ ትኩረትና ረዳት ጓደኛ የሚያስፈልገውን ወንድም አብዱረዛቅን ድጋፍ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆንበት እያወቁ ብቻውን መድበውታል፡፡ ኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋንም እንዲሁ ጊዜያዊ ማቆያ ተብሎ በሚታወቀውና በእስረኞች ቶሎ ቶሎ ተለዋዋጭነት ምክንያት ማህበራዊ ትስስር መመስረት አስቸጋሪ በሆነበት ክፍል ሆን ተብሎ እንዲመደብ ተደርጓል፡፡
የማረሚያ ቤቱ ደንብ በአንድ የክስ መዝገብ ችሎት የሚከታተሉ ታራሚዎች በችሎታቸው ዙሪያ በየጊዜው መነጋገርና መወያየት እንዲችሉ በአንድ ዞን የመታሰር መብት የሚሰጥ ቢሆንም አስተዳደሩ ግን ይህንን የሚያደርገው ሆን ብሎ የችሎታቸውን ፍሰት ለማስጓጎል እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ ሆነ ተብሎ እነሱን ብቻ የለየ ጥቃትና የመብት ጥሰት የሚፈጸምባቸውም በእስር ቤት ውስጥ ባለቻቸው ውስን ነጻነት የገነቧትን ማህበራዊ ትስስር ለማፍረስና የመጪውን ረመዳን ጾምም ተረጋግተው መጾም እንዳይችሉ ጫና ለማሳደር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አወዛጋቢው የፍርድ ሂደት ቀጥሎ የሰው ምስክርነት እየተደመጠ ባለበት ሁኔታ የመጨረሻ ውሳኔ የማስለወጥ ሃይል ባይኖረውም እየተደመጠ ያለው ምስክርነት እጅግ እንዳደናገጣቸውና በዚህም ይህንን እርምጃ ለመውሰድ እንደተገደዱም የሚያሳብቅ ሆኗል፡፡ መንግስት በሃሰት የሽብር ክስ ማንገላታቱ ሳያንሰው በእስር ቤት ውስጥ እንኳን ታራሚዎች ላይ የሚያደርሰው በደል በእርግጥም የአገሪቱ የፍትህ ስርአት የቁልቁለት ጉዞውን እያፋጠነ ለመሆኑ ከበቂ በላይ ምስክር ነው፡፡
የእስር ቤቱ አስተዳደር ውስጥ ያሉት አንዳንድ ሀላፊዎች በግፍ እስር ላይ ለሚገኙት የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ያላቸውን ጥላቻ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያሳዩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ካሁን ቀደም የደሴ ወጣት ታሳሪዎች ወደጨለማ ክፍል እንዲገቡ መወሰኑን ተከትሎ ሌሎች እስረኞች ተቃውሟቸውን ለማሰማት በተሰበሰቡበት ወቅት በቅጽል ስሙ ሻእቢያ ተብሎ የሚጠራው የማረሚያ ቤቱ የጸጥታ ሀላፊ ‹‹እኒህን አሸባሪዎች ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ መረሸን ነበር!›› ብሎ ቁጭቱን ሲገልጽ በግላጭ የተሰማ ሲሆን በተለያዩ አጋጣሚዎችም ጥቃት ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይሉ መታዘብ ተችሏል፡፡ በማረሚያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ካሁን ቀደምም በሌሎች በርካታ ታሳሪዎች ላይ አሰቃቂ የጅምላ ድብደባ ሲፈጸም የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ይህን መሰል የህገ መንግስቱን የእስረኛ አያያዝ ደንብ በግላጭ የሚጥሱ ወከባዎችና በደሎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ይጠይቃል! ህዝበ ሙስሊሙ ላይ ያወጁትን ጦርነት ሲያስፈጽሙ የቆዩት ደህንነቶችና የመዋቅራቸው አካላት ከህግ በላይ የሆነ አካሄዳቸውን በአስቸኳይ እንዲያቆሙም ያሳስባል! በህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ወንጀል በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡ እነርሱ ላይ የሚደርስ በደል ፈርሞ ወደመንግስት በላካቸው ሰፊው ህዝበ ሙስሊም ላይ የሚደርስ በደል ነው፡፡ በመሆኑም በወኪሎቻችን ላይ አንዳች ነገር ቢደርስ ሃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ የሚወስደው መንግስት መሆኑን እያስታወቅን ሰላማዊው ህዝበ ሙስሊምም ይህን መሰሉን ድንበር ያለፈ ጥቃት እስከመጨረሻው የሚፋረደው መሆኑን በጥብቅ እናሳውቃለን!
በህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ላይ በማረሚያ ቤት ውስጥ እየተደረገ ያለው ወከባ በአስቸኳይ ይቁም!
የእስር ቤቱ አስተዳደር ከህግ በላይ መሆኑን በአስቸኳይ ያቁም!
የህዝብ ወኪሎችን ማጉላላት ይብቃ!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

Wednesday, June 11, 2014

ኢህአዲጋዊ የፍቅር ደብዳቤ!!! (ለፈገግታ ያህል)

በነገረ‬-ኢትዮጵያ ጋዜጣ የወጣ
እንደ ህዳሴው ግድብ በብርቅ ለምመለከትሽ፤እንደ መለስ ራዕይ ሰርክ ከአፌ ለማትጠፊው፤እንደትራንስፎርሜሽን እቅዱ ዘወትር ስምሽን ለማነሳሳሽ፤እንደ ቀለበት መንገዳችን ሁሌም በአይኔ ውል ለምትይው፤እንደ ሞባይሌ ኔት-ወርክ ፍቅርሽ የሚያንገላታኝ፤እንደ ቧንቧችን ውሃ ሄድ መጠት የሚለው ናፍቆትሽ፤እንደ ከተማችን መብራት ብልጭ ድርግም የሚለው ምትሃታዊ ውበትሽ፤እንደ ቦሌው መንገድ የተንጣለለው ደረትሽ፤እንደ አዋሽ ባንክ ህንጻዎች በትይዩ የተገተሩት ጡቶችሽ፤እንደ ቤተ መንግስት ፓውዛዎች የሚያበሩት አይኖችሽ፤እንደ ባቡሩ ሀዲድ የተጥበዘመዘው ወገብሽ፤እንደ ኮንዶሚኒየም ህንጸዎች በረድፍ የተደረደሩት ጥርሶችሽ፤እንደ ኪራይ ሰብሳቢ ቦርጭ ወጣ ያለው ዳሌሽ፤እንደ ሀገራችን ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባው ተረከዝሽ፤ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ እመርታ ያስመዘገበው ውበትሽ በህልሜም በውኔም እየመጣ ሲረብሸን ይህቺን ደብዳቤ ሰደድኩልሽ፡፡
ውዴ ሰላምታየ ካለሁበት ቦታ እንደ ትራንስፎርሜሽኑ ባቡር ፈጥኖ እንደሚደርስሽ ተስፋ አደርጋለው፡፡ መቸም አውሮጵላናችን ጠልፎ ጀኔቭ ላይ እንዳሳረፈው ጸረ-ልማት ወፈፌ ፓይለት ደብዳቤየን የሚጠልፍ እረዳት ፖስተኛ እንዳማይኖር እተማመናለው፡፡ለዚህ ደግሞ አሁን ያለው የደህንነታችን ጥበቃ እጅግ አመርቂ በመሆኑ የደብዳቤው መጠለፍ አያስጨንቀኝም፡፡ደህንነትሽ እንዴት ነው? ጤንነትሽስ? ለነገሩ እንደው ለመጠየቅ ያክል ነው እንጂ ጤንነትሽ እንኳን ረጅም እድሜ ለልማታዊ መንግስታችን ይስጥልን እንጅ በየ አምስት መቶ ሜትሩ ጤና ጣቢያ ስለገነባልን ምንም አይነት የጤና እክል እንደማይገጥምሽ ሳላውቅ ቀርቸ አይደለም፡፡
ውዴ ከዚህ ስልጠና ከገባው ቀን አንስቶ የምማረው የአመራርነት ስልጠና ሀገራችን በአንዴ ከድህነት ሊያላቅቅ የሚችልና በሚቀጥሉት አስር አመታት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ዘንድ ሊያሰልፍ የሚችል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የሚገርምሽ አሰልጣኞቻችን ከታዋቂው የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የመጡ ምጡቅ አዕምሮ ያላቸው በመሆኑ የሚሰጡን ትምህርት አጃይብ የሚያስብል ነው፡፡ እውቀታቸው ሞልቶ አለመፍሰሱ የተፈጥሮን ስራ እንድናደንቅ ያደርገናል፡፡ ፍቅሬ ስልጠናው እየተገባደደ ስለሆነ በቅርብ እመጣለው ብየ አስባለው፡፡
የእኔ እና ያንቺ ፍቅር በየ አመቱ የሚያስመዘግበው እድገት ከጎረቤት ሀገራት ፍቅረኛሞች ጋር ሲነጻጸር 11.2 ብልጫ እንዳለው ይገመታል፡፡ ይህ ተሞክሯችን በደንብ ከተቀመረ የጎረቤት ሀገራት ፍቅረኛሞች የልምድ ልውውጥ የሚያገኙበትን አሰራር ሊያስዘረጋ የሚችል ነው፡፡ ፍቅራችንም ለተከታታይ አስር አመት ከፍተኛ የሆነ የማይዋዥቅ እድገት አስመዝግቧል፡፡ በቅርቡም ሞዴል ፍቅረኛሞች የሚል በአይነቱ ልዩ የሆነ ሽልማት ጸሀዩ መንግስታችን ሊያበረከትልን እንደሚችል ወሬ ደርሶኛል፡፡ በዚህ ደግሞ ኩራት ሊሰማሽ ይገባል፡፡ምንም እንኳን እንደ ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ህብተተሰቡ ገንዘቡን አዋጥቶ አይገንባው እንጂ የፍቅራችን ሌጋሲ ለትውልድ የሚተላለፍ ነው ብየ መናገር እችላለው፡፡ ይህ ደግሞ ባለ ራዕይ መሪያችን ሲያስተምሩን የነበረው የፍቅር ሌጋሲ ሳይሸራረፍ መቀጠሉን አማላካች ነው ፡፡
አብዮታዊ መራሹ ፍቅራችን በደንብ አድርጎ ፍሬ ያፈራ ዘንድ ቀጣይ አርባ እና ሀምሳ አመት ሊያስፈልገን እንደሚችል ትዘነጊዋለሽ ብየ አላስብም፡፡ አንዳንድ የኒዮሊበራል ተላላኪዎች በእኔና በአንቺ መካከል ያለውን የፍቅር እድገት ለማደናቀፍ ሲታትሩ መመልከት የተለመደ ነው፡፡እነዚህን የፍቅር እንቅፋቶች በቅርቡ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለፍርድ እንደምናቀርባቸው በዚህ አጋጣሚ ቃል እገባልሻለው፡፡ በዚህ ሀሳብ አይግባሽ !! አይደለም ምድር ላይ መንግስተ ሰማያት እንኳን ቢገቡ ሊያመልጡን አይችሉም፡፡የእኛን ፍቅር ለመበጥበጥ፤ ለማደናቀፍና ብሎም ለመናድ የተንቀሳቀሱትን ፤ አደናቃፊዎችን የደገፉትን እንዲሁም ለመንቀሳቀስ ያሰቡትንም ሁሉ በጸረ-ፍቅር አዋጁ መሰረት እስከ ሞትና የእድሜ ልክ እስራት ሊያስፈርድ የሚችል ደርዘን ሙሉ መረጃ አግኝተንባቸዋል፡፡ እነዚህ ጸረ-ፍቅር ሰዎች የእኛን ፍቅር ተጠቅመው አላግባብ የሆነ ድብቅ አጀንዳቸውን ሊያስፈጽሙ ሲሉ በህብረተሰቡ ጥቆማና በደህንነታችን ክትትል ሊደረስባቸው ተችሏል፡፡የእነዚህን የከሰሩ ስብስቦች ሴራም በቅርቡ ፍቅራዊ-ሀረካት በሚል አርዕስት ዶክመንተሪ ሰርተን በቴሌቪዥን እናጋልጣቸዋለን፡፡
ውዴ እኔና አንቺ እኮ በሀገራችን የሰፈነውን የብሄር ብሄረሰቦች የወንድማማችነት ፍቅር የሚያስንቅ የአብሮነት ትስስር አለን፡፡ ፍቅራችን ሰንደቅ አላማው መሃል ላይ ያለው ኮከብ እንደሚያስተምረው ተከባብሮ የመኖርን አላማ ያነገበ ነው፡፡ ውዴ እንደምታውቂው በሚቀጥለው ወር የፍቅራችን 10ኛ አመት በዓት በታላቅ ዝግጅት ሞቅ ደመቅ ባለ ሁኔታ ይከበራል፡፡ የሚገርምሽ የአሁኑን የፍቅር በዓላችን ለየት የሚያደርገው የሕዳሴው ግድብ በተጀመረበት ሶስተኛ አመት በመሆኑ፤ባለራዕዩ ፤አርቆ አሳቢው፤ አባይን የደፈረው መሪያችን የተሰውበት ሁለት አመት ሊሆነው ሁለት ወር ሲቀረው መሆኑ፤ጀግናው አብዮታዊው ሰራዊታችን የደርግን ሰራዊት ድል ባደረገበት 23ኛ አመት መሆኑ፤እንዲሁም ብዙ ልማታዊ ስራዎችን ልንሰራ ባሰብንበት ሰዓት መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡
ውዴ ስልጠናየኝ ጨርሸ እንደመጣሁ የአንድ ቀበሌ ሊቀመንበር ሆኘ ስለምመደብ ከእኔና አንቺ በተጨማሪ ለዘመዶቻችን ሁሉ የቀበሌ ቤት እናድላቸዋለን፡፡ በመሆኑም ለቤተሰቦችሽ ባለ ሁለት ክፍል የቀበሌ ቤት ስለምንሰጣቸው እኔን እንዳታገቢ ሲዶልቱት የነበረውን ሴራቸውን ያከሽፍልናል፡፡ ይገርምሻል አሰልጣኞቻችን ስለ ታማኝነት ባስረዱበት ወቅት ስንቱ አስመሳይ ራሱን ሲጠራጠር እኔ የአንቺ ባል ግን በኩራት ደረቴን ነፍቸ ዘና ብየ ነበር አዳምጥ የነበረው፡፡መቸም ለድርጅቴ ያለኝን ታማኝነት አንቺም ታውቂዋለሽ ብየ እገምታለሁ፡፡ እንደ እኔ አይነት ታማኝ የድርጅታችን አገልጋይ በማግባትሽም ኩራት ሊሰማሽ ይገባል፡፡ ውዴ ነገ ከፍተኛ የሆነ የውይይት መርሃ ግብር አለብኝ፤ስለሆነም ለውይይቱ ተወዳጇን አዲስ ራዕይ መጽሄትን ማንበብ ስለሚጠበቅብኝ ደብዳቤየን በዚህ ለማጠናቀቅ እገደዳለው፡፡ ያንቺና የድርጅቴ ታማኝ ሆኘ እስከመጨረሻው እንደምዘልቅ እገልጽልሻለሁ፡፡ ቻው……………
አባይ ይገደባል!! የመለስ ሌጋሲም ሳይሸራረፍ ይቀጥላል!!!
ኢህአዲጋዊ የፍቅር ደብዳቤ!!!
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ

Tuesday, June 10, 2014

ኦባንግ “ከምርጫው” በፊት ለተቃዋሚዎች “ምርጫ” አቀረቡ

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በአገር ውስጥ ለሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና አግባብ አላቸው ለሚሏቸው አካላት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተቀምጠው እንዲመክሩ ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ ኢህአዴግ በውስጥ ችግሩ፣ በውጭ ተጽዕኖ ወይም በፖለቲካው የተፈጥሮ ባህርይ የሚከስምበት ደረጃ መድረሱን ያሳሰበው በ”ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ስምና ፊርማ የተበተነው የአኢጋን ደብዳቤ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አጥብበው እንዲሠሩ ጠይቋል፡፡ ይህንን ለኢትዮጵያና ለሕዝባቸው ሲሉ መሥራት የማይችሉ ከሆነ ከኢህአዴግ በላይ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
የፖለቲካ ዕርቅ በመጀመሪያ በተቃዋሚዎች ደጅ ሊተገበር እንደሚገባው ያሳሰበው አኢጋን፤ ይህንኑ ዕርቅ መሠረት በማድረግ ወደ ኅብረት እንዲመጡ በደብዳቤው ገልጾዋል፡፡ ወደ ኅብረት ሲመጡ የፖለቲካ ሥልጣን የመጨበጥ ዓላማቸውን ወደ ጎን መተው እንዳለባቸውና ኢትዮጵያን በማዳን ተግባር ላይ እንዲያተኩሩ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
መግለጫው ሲቀጥልም “የጋራ ንቅናቄያችን ከበርካታ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ካለው ግንኙነት አኳያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መረጃ ይሰበስባል፡፡ በቅርቡ አንድ ታዋቂ የምዕራቡ ዓለም የፖሊሲ አውጪ ሲናገሩ ኢትዮጵያውያን የምዕራቡ ዓለም ነጻ ያወጣናል ብለውበጭራሽ ማመን የለባቸውም፡፡ ከውጭ የሚላከውን ዕርዳታና ድጋፍ ብናቆም እንኳን ይህ የሚሆን አይደለም፡፡ የለውጥ አራማጅና መሪመሆን ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ናቸው እንጂ ለጋሽ መንግሥታት አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሊረዱ ይገባል፡፡ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ከህወሃት/ኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ በሚፈጥሩበት ጊዜ እኛ የግድ እንድንደግፋቸው ያደርጉናል በማለት ለጋራ ንቅናቄያችን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል” በማለት በመረጃ ላይ የተደገፈ ጭብጥ አቅርቧል፡፡
ሰሞኑን የዚህ ዓመት የSEED ተሸላሚ የሆኑት ይህ የአቶ ኦባንግ የምርጫ አማራጭ ግልጽ ደብዳቤ መጪውን ሁኔታ በሚከተለው ሁኔታ ገልጾታል፤ “አገራችንበበርካታድሎችያንጸባረቀታሪክያላት ነች፡፡ ከሁሉ በበላይ የሚጠቀሰው የዓድዋ ድል በድጋሚ የሚፈጸምበት ጊዜቢኖር አሁን ነው፡፡ የዓድዋን የጦር ድል በፖለቲካው መድረክ እንድገመው፡፡ መጪውን ምርጫ ፖለቲካዊ የዓድዋ ድልየምንጎናጸፍበት እናድርገው፡፡ ነጻነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛው ራሳችን እንደአድዋ ድል አንድ ሕዝብ ሆነን በመውጣት የራሳችን የምናደርገበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ቅንነት ካለ የጦር ሜዳውን አድዋ በፖለቲካውሜዳ ላይ መድገም ይቻላል፡፡ አንድ ሊያደርጉንና ሊያስተባብሩን የሚችሉ “ምኒልኮችን” ለመጠቀም ፈቃደኛና ቅን እንሁን፡፡
በአኢጋን አድራሻና በዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ ስምና ፊርማ የተሰራጨው ይህ የማሳሰቢያ ግልጽ ደብዳቤ አኢጋን በተለይ በዕርቅ ዙሪያ የሚጠየቀውን ማንኛውንም ጥያቄ ድጋፍ እንደሚሰጥ ያረጋገጠ ነው፡፡ የደብዳቤው ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

“ነጻነትነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም!”
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች ያስተላለፈው ግልጽ መልዕክት
የተወደዳችሁ በኢትዮጵያ የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤
በቅድሚያ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የአክብሮት ሰላምታ በማቅረብ በትግሉ መስክ የምትከፍሉትን መስዋዕትነት የሚያደንቅ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ ጠብቦ የለም የሚባልበት ደረጃ በደረሰበት ወቅት በምታገኙት ስንጥቅ ሁሉ እየተጠቀማችሁ ለህዝባችሁ የብርሃን ጭላንጭል ስለምትፈነጥቁ አኢጋን ሥራችሁን ያደንቃል፤ ያከብራል፡፡ እኛ በሥራችሁ ስኬት የምንመኘው ለቆማችሁለት የፖለቲካ ዓላማ ብቻ ሳይሆን ከህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት አቅቷቸው መፈናፈኛ ላጡትም የመወሰን ኃይል እንደምትሰጧቸው በማመን ነው፡፡
አገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የበርካታዎች ጥያቄ “ህወሃት/ኢህአዴግን በምን ዓይነት የተሻለ አስተዳደር እንዴት መለወጥ ይቻላል የሚለው ነው?” ይህ ጥያቄ “እኛ ኢትዮጵያውያን የዘርና የጎሣ ትንንሽ አጥሮቻንን አፍርሰን ሁሉን አቀፍ ትግል ለማድረግ ተዘጋጅተናል ወይ?” ብለን ራሳችንን መልሰን አንድንጠይቅ የሚያደርገን ነው፡፡ እንዲሁም ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠትሁሉም ነጻ ሳይወጣ ራሳችንን ነጻ ለማውጣት እንችላለን ወይ? ብለንም እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ነው፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው እንዲሁም ለመላው አፍሪካ “የሚተርፍ” እኩይ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ በማስፋፋት አገራችንን እንደዚህ ባለ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በጣለበት በአሁኑ ወቅት የብዙዎች ጭንቀት አገራችን ወደ ምን ዓይነት አዘቀት ውስጥ እየገባች ይሆን የሚለው ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ፍርሃት ወደ ተስፋ የሚቀይር አማራጭ እስካሁን ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ አማራጭ የጠፋ ይመስል ህወሃት/ኢህአዴግም “እኔ ከሌለሁ …” እያለ ያስፈራራል፤ ተቃዋሚዎችም በእርስበርስ ሽኩቻ የህዝብ አመኔታ በማጣት ወደ አለመታመን ከመሄዳቸው የተነሳ መልሶ ተዓማኒነትን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ገና ብዙ የሚቀር አለ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለኢትዮጵያ ሕጋዊ አማራጭ በመሆን ለሕዝባችን መፍትሔ የምታመጡበት ወሳኝ ጊዜ አሁን መሆኑን የጋራ ንቅናቄያችን ያምናል፡፡
እንደምታውቁት የዛሬ ዓመት ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ ነው፡፡ ምርጫውንና አመራረጡን ከሥሩ ጀምሮ የተቆጣጠረው ህወሃት/ኢህአዴግ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል ብለን አናምንም፡፡ ሆኖም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የሚፈለገው ተግባር ከተከናወነ በአገራችን እውነተኛ ለውጥ ይመጣል ብለን እናምናለን፡፡ ዓመኔታ የሚጣልበት አማራጭ ከተገኘ ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ህወሃት/ኢህአዴግን አንቅሮ ለመትፋት ከምንጊዜውም ይልቅ ዝግጁ ነው፡፡ ይህንንም የምንለው ከምንም ተነስተን ሳይሆን ድርጅታችን በአውሮጳ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ባለው የግንኙነት መስመር ከሚያገኘው ተጨባጭና ተዓማኒ መረጃ በመነሳት ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ዘንድ ህወሃት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያራምደው የዘር ፖለቲካ፣ የሚከተለው እጅግ ጭቋኝ ፖሊሲ፣ በየጊዜው በሚያወጣቸው አረመኔያዊ ህግጋት፣ ወዘተ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ አደጋ የጣለና ለአህጉሩ መጥፎ ምሳሌ እየሆነ በመምጣቱ በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ የመከሰቱ ጉዳይ ከምንጊዜውም በላይ አሳማኝ የሆነበት ጊዜ ላይ ይገኛሉ፡፡ አሁንም ጥያቄው “ህወሃት/ኢህአዴግን ማን ይተካዋል?” የሚለው ነው፡፡ይህንን የመመለሱ ኃላፊነት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ የወደቀ ቢሆንም በተለይ አገር ውስጥ ያላችሁት የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድሚያ ልትመልሱት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ አመኔታ የሚጣልበት አማራጭ ሆናችሁ የመቅረባችሁ ሁኔታ ስለምርጫው ነጻና ፍትሃዊነት ከመጠየቅ ባልተናነሰ መልኩ ተጠይቆ መልስ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡
አገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለእናንተ ማስረዳት የሚያስፈልግ አይመስለንም፡፡ በየቀኑ የሚፈጸመውን በደልና ግፍ መከታተል ብቻ ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንደሆነ በበቂ ሁኔታ የሚያመላክት ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ተቀጣጣይ (ክላስተር) ቦምብ በየቦታው የበተነው የጎሣ ፖለቲካ ፈንጂ ከፋፍሎ በመግዛት ለራሱ የሥልጣን ማቆያ ቢጠቀምበትም በአሁኑ ጊዜ አገራችንን ከላይና ከታች እያነደዳት ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ በአገራችን ላይ ሊፈነዳ የሚችለው ነገር ሁሉንም የሚያሳስብ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ራሱ በፈጠረው ችግርና በበተነው መርዝ ራሱን በራሱ ሊያጠፋው እንደሚችል ከድርጅቱ ውስጥ የሚታዩት የሥልጣን ሽኩቻዎች ሁሉም “ሳይቀድሙኝ ልቅደም” በሚል አስተሳሰብ እንደተወጠረ የሚያመለክት ነው፡፡ አገራችን ነጻነቷን ከመጎናጸፏ በፊት ይህንን ዓይነቱ የህወሃት/ኢህአዴግ እርስበርስ መበላላት የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን እጅግ በርካቶች ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ እናንተ ባላችሁ ኃላፊነት ይህንን በውል የምታጤኑት እንደሆነ የጋራ ንቅናቄያችን ያምናል፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ ከውስጥ በሚነሳበት ግፊትና የመበላላት ስጋት፤ ከውጪ በሚመጣበት ተጽዕኖ ወይም በሁለቱ ጥምረት ከሥልጣን መወገዱ የማይቀር ነው፡፡ ይህንን የሚቀበል ካልሆነም ሥርነቀል ተሃድሶ ማድረጉ እየጎመዘዘው የሚጠጣው ሐቅ ነው፡፡ በየትኛውም መልኩ የሚከሰተው ለውጥ አገራችንን መልሶ መልኩን ለቀየረ በዘር ላይ ለተመሠረተ አገዛዝ አሳልፎ የሚሰጣት መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም የሚመጣው ለውጥ ሕዝባችንን እውነተኛ ነጻነት የሚያጎናጽፍ፣ ፍትሕ የሚሰጥና ወደ ዕርቅ የሚመራ መሆን ይገባዋል፡፡ አገራችን በዚህ ጎዳና ላይ እንድትጓዝ የማድረጉ ኃላፊነት የእናንተ እንደሆነ የጋራ ንቅናቄያችን ያሳስባል፡፡
ይህ ደግሞ ሥልጣን ከመጨበጥ ባለፈ ምኞት ላይ የተመሠረተና እያንዳንዱ ነጠላ ፓርቲ ከሌሎች ጋር በኅብረት በመሥራት ተግባራዊ ሊያደርግ የሚገባው መሠረታዊ ዓላማ ነው፡፡ አገራችን ካለችበት ታላቅ ችግር አኳያ የፓርቲዎች መተባበርና ከተቻለም መዋሃድ ወደ መፍትሔ በሚወስደው መንገድ ላይ የመጀመሪያው ስኬት ነው፡፡ ይህ ግን በቀላሉ አይገኝም፤ ሆደ ሰፊ መሆንን፣ ከራስ ይልቅ ለአገርና ለሕዝብ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ማሰብን፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከፍተኛ የመንፈስ ልዕልናን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሥልጣንን፣ የራስን ክብር፣ የበላይነትን፣ “እኔ ከሌላው የተሻልኩ ነኝ” ማለትን፣ ወዘተ እያውጠነጠኑ ለአገር አስባለሁ ማለት በእጅጉ አስቸጋሪ ነው፡፡ “ከጠላት” የላቀ የመንፈስ ልዕልና ከሁሉም ይጠበቃል፡፡
በመጪው ምርጫ ከምንጊዜውም በበለጠ በመጽናት ለለውጥና ለነጻነታችን የምንታገልበት ሊሆን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የናፈቀውን ነጻነት ሊጎናጸፍ የሚችልበት አማራጭ ሊፈጠር እንደሚችል አኢጋን ያምናል፡፡ ይህ ሊከሰት የሚችለው በአገር ውስጥ ያላችሁት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥቃቅን ልዩነታችሁን አስወግዳችሁ አጀንዳችሁን ሕዝባዊ በማድረግ በኅብረት ለመሥራት ስትወስኑ ነው፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን ባደረገው ጥናት አብዛኞቻችሁ ያላችሁ ልዩነት መሠረታዊ እንዳልሆነ ለመረዳት ችሏል፡፡ ይህም የሚያሳየው እርስበርስ ከሚያለያያችሁ ነገሮች ይልቅ ሊያስማሟችሁ የሚችሉት በርካታዎች እንደሆኑ ነው፡፡ በተለይ በአመራር ላይ ያላችሁ በተለያየ ጊዜ ከሌሎች ጋር የተከሰቱ ልዩነቶችና ግጭቶች እንዲሰፉ ምክንያት ከመሆን ይልቅ ለአገርና ሕዝብ በማሰብ ኢትዮጵያን የመታደግ ኃላፊነት ወድቆባችኋል፡፡ አገር ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም፤ እንደ ትልቅ የያዛችሁት ልዩነትና ችግርም ከንቱ ይሆናል፤ አብሮ ይከስማል፡፡
በተደጋጋሚ የሚሰማው ነጠላ ዜማ “በኢትዮጵያዊ ውስጥ ተስፋ የሚጣልበት ተቃዋሚ ፓርቲ የለም” የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ለዚህ ጥያቄ ዋንኛ ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው፡፡ ምክንያቱም በአስመሳይ ዲሞክራሲና ተግባራዊ ባልሆነ ሕገመንግሥት ሕዝባችንን ከመጠርነፍ አልፎ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ሸብቧቸዋል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚከተለው ፕሮግራም በኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖር ያደረገ ለመሆኑ ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በኢህአዴግ ብቻ እያመካኙ መኖር ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው፡፡እያንዳንዱ የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲ ዓላማው የኢህአዴግን መሰሪነትና አፋኝነት ለመስበክ ሳይሆን ሕዝብን ለነጻነት ማብቃት ነው፡፡ እታገለዋለሁ ከሚለው አካል መላቅ ካልቻለ ለትግል ብቁ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡
ሽንፈት ላይ እያተኮሩና የጠላትን ኃይለኛነት እየሰበኩ ድል አይገኝም፡፡ ልዩነትን እያራመዱ ኅብረትና አንድነት ተግባራዊ መሆን አይችልም፡፡ለአገራዊ ዕርቅ እንሰራለን እያሉ በፓርቲ መካከል ከዚያም በታች በግለሰብ ደረጃ መተራረቅ ካልተቻለ ብሔራዊ ዕርቅ ከቀን ቅዠት አያልፍም፡፡ እያንዳንዳችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ፣ መኢአድ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ፣ ኦህኮ፣ አረና፣ እና ሌሎች እጅግ በርካታ ፓርቲዎች የተቋቋማችሁትና ዓላማ ያደረጋችሁት ኢህአዴግን እየተቃወማችሁ ለመኖር እንዳልሆነ የፓርቲ ፕሮግራማችሁ ይመሰክራል፡፡ ወይም ዓላማችሁ የራሳችሁን የፓርቲ ምርጫ የማድረግና ፕሬዚዳንት (ሊቀመንበር)፣ ምክትል፣ ሥራ አስፈጻሚ፣ … በመምረጥ አዙሪት ውስጥ ራሳችሁን ላለማሽከርከር እንደሆነ ከማንም በላይ ራሳችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ ከዚህ አንጻር በጥንቃቄና በብዙ ጥናት የተቀመጠው የፓርቲያችሁ ፕሮግራምና ዓላማ ለአገራችን አንዳች ለውጥ ሳያመጣ እንደዚሁ እንዳማረበት ቢቀመጥ ለሕዝብ የሚያመጣው ትርፍ ምንድርነው? እናንተንስ ለመቃወም ብቻ የምትሰሩ አያደርጋችሁምን? ለኢህአዴግና ወዳጆቹስ ጣት የሚጠቁሙበትን ዕድል እየሰጣችሁ እስከመቼ ትኖራላችሁ? ስለዚህ የእስካሁኑ በነጠላ የመጓዙ ጉዳይ ካልሰራ በኅብረት የመሥራቱ ጉዳይ የግድ ይሆናል፡፡ ይህ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አኢጋን ያምናል፡፡
የጋራ ንቅናቄያችን ከበርካታ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ካለው ግንኙነት አኳያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መረጃ ይሰበስባል፡፡ በቅርቡ አንድ ታዋቂ የምዕራቡ ዓለም የፖሊሲ አውጪ ሲናገሩ “ኢትዮጵያውያን የምዕራቡ ዓለም ነጻ ያወጣናል ብለው በጭራሽ ማመን የለባቸውም፡፡ ከውጭ የሚላከውን ዕርዳታና ድጋፍ ብናቆም እንኳን ይህ የሚሆን አይደለም፡፡ የለውጥ አራማጅና መሪ መሆን ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ናቸው እንጂ ለጋሽ መንግሥታት አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሊረዱ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ከህወሃት/ኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ በሚፈጥሩበት ጊዜ እኛ የግድ እንድንደግፋቸው ያደርጉናል” በማለት ለጋራ ንቅናቄያችን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ይህ ንግግር በአገር ውስጥ ለምትገኙት ብቻ ሳይሆን በዳያስፖራ ለምንገኘውም ልንገነዘብ የሚገባው ሐቅ ነው፡፡ ነጻነት ከምዕራቡ ዓለም ብቻ ሳይሆን በዳያስፖራ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያንም ሊመጣ አይችልም፡፡ የነጻነታችንን ጥያቄ ተግባራዊ የሚሆነው እናንተ በአገር ውስጥ የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኅብረት በመሥራት ሕዝባችንን ለለውጥ ስታስተባብሩት ብቻ ነው፡፡ እኛ ይህንን ከራሳችን ትከሻ ላይ ለማውረድና እናንተን በኃላፊነት ለመጠየቅ የምንጭነው ሳይሆን አገር ውስጥና ውጭ መሆናችን በታሪክም ይሁን በሌላ ምክንያት የተከሰተ በመሆኑ በቅንነትና በሐቅ የምንናገረው እውነታ ነው፡፡ እኛም ከአገር ውጭ ነን በማለት እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥ ሳይሆን በአገር ውስጥ የሚካሄደውን ትግል የመደገፍ፣ የማገዝ፣ የምዕራባውያንን አመለካከት የማስቀየር፣ በአገር ውስጥ የሚካሄደውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የማሳወቅ፣ … ኃላፊነት እንዳለብን በመገንዘብ ነው፡፡ አኢጋን ይህንን ዓይነቱን ተግባር ሲያካሂድ የቆየ አሁንም ከአገር ውስጥ የሚመጣውን ጥያቄ ለመመለስና በሚችለው ሁሉ ለማገዝ ሙሉ ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡
ከዚህ በፊት በተካሄዱት ምርጫዎች እንደታየውና በፓርቲያችሁ ፕሮግራም ላይ እንደሰፈረው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ተወዳድራችሁ ሥልጣን የመያዝ ዓላማ እንዳላችሁ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ግን ማናችሁም ብትሆኑ በነጠላ ፓርቲነት ተወዳድራችሁ ሥልጣን በመያዝ ለውጥ እንደማታመጡ በግልጽ ልንነግራችሁ እንወዳለን፡፡ በምርጫ አሸነፋችሁ ቢባል እንኳን ሥልጣን የሌለው ቢሮ ከመያዝና የህወሃት/ኢህአዴግ አሻንጉሊት ከመሆን እንደማታመልጡ እሙን ነው፡፡ ይልቁንም ይህ ዓይነቱ አካሄድ ህወሃት/ኢህአዴግ በተለይም ለምዕራቡ ዓለም ለሚደሰኩረው የይስሙላ ዴሞክራሲ ማረጋገጫ ሆኖ በማቅረብ የኢህአዴግ ዕድሜ መቀጠያ መድሃኒት ነው የምትሆኑለት፡፡ ስለዚህ ከመጪው ምርጫ አኳያ ትግሉ የተናጠል ሳይሆን ፓርቲዎች በኅብረት በመሆን ኢህአዴግን በእርግጠኝነት ሊተኩ የሚችሉበት አማራጭ ሊሆን ይገባዋል፡፡
በበርካታ አገሮች እንደሚታየው እናንተም በኅብረት በመሆን ኃይላችሁን አስተባብራችሁ ለሕዝባችሁ ስትሉ እርስ በርስ መጠላለፍ፣ መነቋቆር፣ መካሰስ፣ ወዘተ አሁኑኑ ማቆም ይገባችኋል፡፡ በእስራኤል፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ … በተለያዩ ጊዜያት እንደታየው ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት በመመሥረት ሕዝባቸውን ታድገዋል፣ አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያስ ይህ ሊሆን የማይቻልበት ምክንያት ምንድርነው? መልሱን መመለስ የሚገባችሁ እያንዳንዳችሁ የፓርቲ አመራሮች ናችሁ፡፡
ይህ ሳይሆን የሚቀር ከሆነ በቅርቡ የፖለቲካ ታሪካችን እንደታየው በዚህም ዘመን በተመሳሳይ መልኩ ይደገማል፡፡ በዘመነ አጼ ኃይለሥላሴ የተነሳው የህዝብ ብሶት ዳር ሳይደርስ ደርግ ለራሱ አስቀረው፡፡ በደርግ ዘመን መከራውንና ስቃዩን ያየው ሕዝብ ህወሃት/ኢህአዴግ “የሕዝብ ብሶት” የወለደኝ ነው ብሎ ሲመጣ የመከራው ዘመን ማብቂያው የደረሰ መስሎት ተስፋ አደረገ፡፡ “ብሶት” ወለደኝ ያለው ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ታይቶ በማይታወቅ የዘር “ድንበር” ከፋፍሎ የሕዝባችንን ብሶት ለ23ዓመታት በየቀኑ እያበዛው ይገኛል፡፡ አሁንም ጥንቃቄ ወስዳችሁ ሁላችሁም ለሕዝባችን የሚሆን መፍትሔ የማታመጡ ከሆነ የሕዝባችን ብሶት እንዲቀጥል የምታደርጉ ብቻ ሳይሆን በመጪው ትውልድም ከመጠየቅ አታመልጡም፡፡
በቅንጅት ጊዜ ሕዝብ እጅግ ተስፋ አድርጎ ውጤት ሲጠብቅ ቅንጅቶች “መቀናጀት” አቅቷቸው ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረው የሕዝባችን ድል ገደል ገባ፤ በራሱ ተቀናጅቶ የነበረው ሕዝብ የህወሃት/ኢህአዴግ የበቀል እርምጃ ሰለባ ሆነ፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን ከበርካታ ወገኖች ጋር ባለው ግንኙነት አሁንም ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል እያሉ ስጋታቸውን የሚገልጹልን ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ በአገራችን ላይ በርካታ ችግሮች የተጋፈጥን ቢሆንም ከፈጣሪ በኩል ግን ሁልጊዜ መፍትሔና የተበላሸውን የማስተካከል ዕድል አለ፡፡ ይህም ዕድል አሁን እንደሆነ አኢጋን ያምናል፡፡ ከዚህ አንጻር ጥቂት ሃሳቦችን ለማካፈል እንወዳለን፤
  1. በምንም መልኩ በኢትዮጵያ አማራጭ ፓርቲ የለም የሚለውን ተስፋ አስቆራጭ ንግግር አትቀበሉ፡፡
  2. ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብራችሁ ልትሰሩ የሚያስችላችሁን ነጥቦች ዘርዝሮ በማውጣት በሚያስማማችሁ ጉዳዮች ላይ የጋራ አስተሳሰብ ልትወስዱ የምትችሉበትን መንገድ አመቻቹ፡፡
  3. በዕቅዳችሁና ከሌሎች ጋር በጥምረት በመሆን ምንም እንኳን አስቸጋሪ ቢሆን በዋንኛነት በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር የሚሰፋበትንና ዕርቅ የሚመጣበትን መንገድ ከመቀየስ ተስፋ አትቁረጡ፡፡
  4. የፓርቲ ፕሮግራምና ማኒፌስቶ ከሰማይ የወረደ፣ የማይገሰስ፣ የማይሻርና የማይለወጥ የፈጣሪ ቃል አይደለም፡፡ ስለዚህ ወደ ውኅደት በሚደረገው ጉዞ መሻሻል፣ መለወጥ፣ መስተካከል፣ የሚገባው የፕሮግራም አንቀጽ የፓርቲያችሁን ኅልውና አደጋ ላይ እስካልጣለ ድረስ ተፈጻሚ ለማድረግ ሆደሰፊ ሁኑ፡፡
  5. ከመሪዎች ጀምሮ በፓርቲያችሁ ውስጥ ውህደትን፣ ጥምረትን፣ … ተግባራዊ ለማድረግና በጋራ ለመሥራት ዕንቅፋት የሚሆኑ ግለሰቦችን በግልጽ መውቀስና እንዲታረሙ ወዲያውኑ ማድረግ ወሳኝነት ያለው ተግባር ነው፡፡ “እገሌን እንዴት እወቅሰዋለሁ” ወይም “አቶ እገሌ የፓርቲያችን የጀርባ አጥንት ነው እንዴት ተሳስተሃል እላልሁ” በሚሉ የይሉኝታ አስተሳሰቦች ለአንድ ሰው ሲባል አገርና ሕዝብ መከራና ስቃይ እንዲቀጥል መደረግ የለበትም፡፡ አገር ለመምራት ፓርቲ መሥርታችሁ ሕዝብን በይሉኝታ መንግሥት ማስተዳደር ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ለይሉኝታ በራችሁን ዝግ ይሁን፡፡
  6. ሁልጊዜ ለመምራት ሳይሆን ለመመራት ተዘጋጁ፡፡ የሰላማዊ ትግል መሪ መመሪያ ይኸው ነው፡፡ ለመመራት የተዘጋጀ መሪ ለመሆን ምንም አይቸግረውም፡፡ ከሥልጣንህም ተነሳ ሲባል ፓርቲውን አይገነጥልም ወይም “እኔ ከሞትኩ …” በሚል ጭፍን አስተሳሰብ በሕዝብ ላይ የውድመት ተግባር አይፈጽምም፡፡ ይህ ምንም የምንደባበቅበት ነገር አይደለም በተግባር ሲፈጸም የኖረ ነው፤ መስተካከልና መሻሻል የሚያስፈልገው ነው፡፡ ከመገልገል ይልቅ ለማገልገል ትሁት ሁኑ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ትክክለኛ አስተዳደር ነው እንጂ ህወሃት/ኢህአዴግን በሌላ መተካት አይደለም፡፡ ሕዝባችን ይህ ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም፡፡ ስለሆነም “ኢህአዴግ ይነሳ እንጂ” የሚለው ጠባብና ሰንካላ ሃሳብ የእውነተኛ ለውጥ መርህ ስላልሆነ በጭራሽ ለሕዝባችን አትመኙለት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንግዲህ ወዲህ የሚያስፈልገው “ከጎሣና ዘረኝነት ይልቅ ሰብዓዊነት”የሚያብብባትና “አንዱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነጻ የወጣባትን”፤ ፍትህ፣ ሰላምና ዕርቅ የሰፈነባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያን ነው፡፡ ከዚህ ያነሰ ለውጥ በለውጥ ደረጃ ሊታሰብም ሆነ ሊታቀድ አይገባውም፡፡
እናንተ አገር ውስጥ ሆናችሁ በየጊዜው በምታደርጉት የመስዋዕትነት ተግባር የጋራ ንቅናቄያችን ከጎናችሁ ይቆማል፡፡ ሥራችሁንም በታላቅ አክብሮት ይከታተላል፡፡ የመስዋዕትነታችሁ ውጤት ፍሬ እንዲያፈራ የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ በውጭ ከበርካታ ወገኖች ጋር ባለን ግንኙነት ለምትፈልጉን ሥራ በምንችለው ሁሉ ለመተባበር ፈቃደኛ መሆናችን እንገልጻለን፡፡ በተለይ በዕርቅ መንገድ ላይ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የሚጠየቀውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኝነቱን ይገልጻል፡፡ ይህ ጉዳይ በዚህ ደብዳቤ ላይ ለፕሮቶኮል ብለን የምንናገረው እንዳልሆነ እንድትረዱልን እንፈልጋለን፡፡
አገራችን በበርካታ ድሎች ያንጸባረቀ ታሪክ ያላት ነች፡፡ ከሁሉ በበላይ የሚጠቀሰው የዓድዋ ድል በድጋሚ የሚፈጸምበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ የዓድዋን የጦር ድል በፖለቲካው መድረክ እንድገመው፡፡ መጪውን ምርጫ ፖለቲካዊ የዓድዋ ድል የምንጎናጸፍበት እናድርገው፡፡ ነጻነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛው ራሳችን እንደ አድዋ ድል አንድ ሕዝብ ሆነን በመውጣት የራሳችን የምናደርገበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ቅንነት ካለ የጦር ሜዳውን አድዋ በፖለቲካው ሜዳ ላይ መድገም ይቻላል፡፡ አንድ ሊያደርጉንና ሊያስተባብሩን የሚችሉ “ምኒልኮችን” ለመጠቀም ፈቃደኛና ቅን እንሁን፡፡
እርስበርሳችን እንደ ወንድምና እህት ለመተያየትና ለመግባባት ፈጣሪ ቅን ልብ ይስጠን፡፡ እናንተንም ለፍትሕ፣ ለነጻነት፣ ለሰብዓዊነት፣ ለፍቅርና ዕርቅ ስትታገሉ ማስተዋልንና ጥበብን ይስጣችሁ፡፡
ከአክብሮት ጋር ለአገራችን ፈውስ እንዲመጣ የትግል አጋራችሁ፤
ኦባንግ ሜቶ
ዋና ዳይሬክተር፤
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
source www.goolgule.com