የኢትዮጵያ መንግሥት ከሦስት ወራት በፊት አውሮፕላን በመጥለፍ ጄኔቭ ያሳረፈው ኃይለመድህን አበራ ተላልፎ እንዲሰጠው ያቀረበውን ጥያቄ የሲዊዘርላንድ መንግሥት እንዳልተቀበለው ተጠቆመ።
ቪኦኤ የስዊዘርላንድ የፍትህ ሚኒስቴር ቃል አቀባይን ጠቅሶ ሰሞኑን እንደዘገበው የኃይለመድህን ጉዳይ በሕግ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሶ ረዳት አብራሪውን ለኢትዮጵያ አሳልፎ ለመስጠት የቀረበለትን ጥያቄ የስዊዝ መንግሥት አልተቀበለውም። ቃልአቀባዩ ለዚህ የሰጡት መልስ ስዊዘርላንድ እና ኢትዮጵያ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት አለማድረጋቸውን ነው።
በየካቲት ወር 2006 ዓ.ም አጋማሽ የበረራ ቁጥር ET702 የተመዘገበና ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 767 አውሮፕላን በ31 ዓመት ወጣት ረዳት አብራሪው ኃይለመድህን አበራ ተጠልፎ የጉዞ መስመሩን በመቀየር ጄኔቭ ኤርፖርት ካረፈ በኋላ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ስለሁኔታው መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ ለኢትዮጵያ ተላልፎ እንዲሰጥ የሲዊዘርላንድ መንግሥትን ለመጠየቅ መንግሥታቸው ማቀዱን መጥቀሳቸው የሚታወስ ነው።
ረዳት ፓይለት ኃይለመድህን አበራ በሌለበት በአገር ውስጥ ክስ የተመሠረተበት መሆኑም አይዘነጋም።
Source sodere.com
No comments:
Post a Comment