ሴቶችን በተለይም ታዳጊዎችን ጠልፎና አግቶ የሚፈልጉትን ለማግኘት በመደራደሪያነት መያዝ የተለመደ አይደለም፡፡ ዓለምም እንደዚህ ዓይነቱን ክስተት እምብዛም አስተናግዳ አታውቅም፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በቀውስ ውስጥ የሚገኙ አገሮችን ቀድሞ የሚረዳው ሴቶችና ሕፃናትን ነው፡፡ ከየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታም ለመውጣት ትኩረት የሚያገኙት ቀድመው ነው፡፡
ናይጄሪያ ግን ሰሞኑን ዓለምን ያነጋገረ ክስተት አስተናግዳለች፡፡ ላለፉት 12 ዓመታት የናይጄሪያ መንግሥትን ለመጣል ሲዋጉ የከረሙት የጽንፈኛው የቦኮ ሐራም ታጣቂዎች ከወር በፊት ያገቷቸውን ከ300 የማያንሱ ሴት ተማሪዎችን በመንግሥት ለታሰሩባቸው አባላቶቻቸው ልዋጭ ድርድር አቅርበዋቸዋል፡፡
በክርስትናም ይሆን በእስልምና አስተምርሆ ሴትን ማሰቃየትም ሆነ ማጉላላት የተከለከለ ነው፡፡ እስልምናን በናይጄሪያ አስፋፋለሁ፣ እስላማዊ መንግሥትም እመሠርታለሁ ለሚለው ቦኮ ሐራም ግን ይህ በተግባር አልታየም፡፡ ይልቁንም ሴት ተማሪዎችንና እናቶችን እየጠለፈ ለእስረኛ ልዋጭ እየተደራደረባቸው መገኘቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና ኃያላን መንግሥታትን አስቆጥቷል፡፡
ቦኮ ሐራም ከዚህ ቀደም በሽምቅ ውጊያ የናይጄሪያን መንግሥት ሲፈታተን ቢቆይም፣ አሁን ሥልቱን በመቀየር ሴቶችን ማደን ተያይዞታል፡፡ ከአንድ ወር በፊት ከአዳሪ ትምህርት ቤት የጠለፋቸውን 276 ሴት ተማሪዎች ‹‹ለባርነት እሸጣቸዋለሁ›› ብሎ ዓለምን ያስደመመው ቦኮ ሐራም፣ በያዝነው ሳምንት ባሰራጨው የቪዲዮ መልዕክት ‹‹ተማሪዎቹን አስልሜያቸዋለሁ›› ብሏል፡፡ አብዛኞቹ ክርስቲያን ተማሪዎች እንደነበሩ፣ ከተጠለፉ በኋላ በተሰጣቸው የእስልምና ትምህርትም ወደ እስልምና እንደተቀየሩም የቦኮ ሐራም መሪ አቡበከር ሽካው ተናግሯል፡፡
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ባሰራጨው የቦኮ ሐራም የቪዲዮ መልዕክት ተማሪዎቹ ሥፍራው በግልጽ በማይታወቅ አረንጓዴ ቦታ ላይ በሂጃብ ተሸፋፍነው ታይተዋል፡፡ አምላካቸውን በዓረብኛ ቋንቋ ሲያመሠግኑም ተሰምተዋል፡፡ 17 ደቂቃዎች በሚፈጀውና በሐውሳና በዓረብኛ ቋንቋዎች የቪዲዮ መልዕክት የቦኮ ሐራም መሪ ላለፉት አምስት ዓመታት በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙት አባላቶቹ ከተለቀቁ ሴቶቹን እንደሚለቅ አስታውቋል፡፡
የሴቶችን መማርና የምዕራባውያንን ትምህርት የማይቀበለው ቦኮ ሐራም በትምህርት ቤት የሚገኙ ሴቶችን ከመጥለፍ ባለፈም፣ በገጠር የሚገኙ እናቶችንም እየጠለፈ መሆኑ ተነግሯል፡፡ 276 ሴት ተማሪዎችን ከወር በፊት ከጠለፈ በኋላ በቡርኖ ከተማ የሚገኙ 11 ሴቶችን በድጋሚ ጠልፏል፡፡ አሁንም ሴቶችን የሚጠልፍ መሆኑንም በይፋ አሳውቋል፡፡
ቦኮ ሐራም ትምህርት ቤት የሚሄዱ ሴቶችን እንደሚጠልፍ ካስጠነቀቀ በኋላ፣ የዋራብ ነዋሪ የሆኑት አብዱላሂ ሳኒ መሣሪያ የታጠቁ የቦኮ ሐራም ሸማቂዎች ሴቶችን ፍለጋ ቤት ለቤት እንደሚያስሱ ተናግረዋል፡፡
‹‹በአካባቢያችን ምንም ጥበቃ የለም፡፡ መሣርያ የታጠቁት ሸማቂዎች ሴቶቻችንን ሊወስዱ ሲመጡ መስጠት ነው፡፡ የሚያስቆማቸው የለም፤›› ብለዋል፡፡
በ12 እና በ15 ዓመት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን ከአካባቢው የጠለፉ ሲሆን በጠለፋው ወቅት ግን እንዳልተኮሱና ማንንም እንዳልገደሉም እማኞች ተናግረዋል፡፡ ዓላማቸውም ሴቶችን ጠልፈው መሄድ ብቻ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በናይጄሪያ ጦር ከይዞታቸው ያፈገፈጉት የቦኮ ሐራም አባላት ሌሎችን ሳይጎዱ ሴቶችን ብቻ እየጠለፉ መሄዳቸው ሥልት በመቀየር ትኩረት ለመሳብ መሆኑም ተነግሯል፡፡
ቦኮ ሐራም በሴት ተማሪዎችና በእናቶች ላይ የሚያደርገው ጠለፋና በደል በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እየተወገዘ ነው፡፡ ኃያላን መንግሥታትም ናይጄሪያ የቦኮ ሐራምን ድርጊት እንድትገታ ድጋፍ መስጠት ጀምረዋል፡፡
የሴት ተማሪዎችን መጠለፍ ‹‹ልብ የሚሰብር›› በማለት ለኤቢሲ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ጊዜው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተባብሮ ተማሪዎቹንና ናይጄሪያን ከችግር የሚያላቅቅበት ነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት የተጠለፉትን ናይጄሪያውያት ለመታደግ ባለሙያዎቹን ከመላኩ በላይ፣ ከናይጄሪያ መንግሥት ባገኘው ፈቃድ መሠረት ቦኮ ሐራም ሴቶቹን ያግትባቸዋል የሚባሉ ሥፍራዎችን በሙሉ በሳተላይት በመታገዝ ቅኝት እያደረገ ይገኛል፡፡
አሜሪካ ከጦር ኃይሏ፣ ከሕግ አስከባሪዎችና ከተለያዩ ኤጀንሲዎች የተውጣጣውን ቡድን ወደ ናይጄሪያ የላከች ሲሆን፣ የቡድኑ አባላት ሴቶቹን ለማግኘትና ዕርዳታ ለመስጠት ሁኔታዎችን ያመቻቻሉም ተብሏል፡፡
በአስፀያፊ ድርጊቱ የዓለም አቀፍ ሚዲያ መነጋገሪያ የሆነው ቦኮ ሐራም በሰው ልጆች ላይ አስፀያፊ ወንጀል ሠርቷል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞችም በሴቶች ላይ የተቃጣ ከባድ በደል ብለውታል፡፡
ከ300 ያላነሱ ሴቶችን የጠለፈው ቦኮ ሐራም ባሰራጨው የቪዲዮ መልዕክት ሴቶቹ ተረጋግተው የሚታዩ እንዲመስሉ ተደርጓል፡፡ እንዲያውም አንዷ በሸማቂዎቹ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ተናግራለች፡፡ ባለፈው ሳምንት የወጡ ሪፖርቶች የሚያሳዩት ግን የተወሰኑት ታጋቾች ጠላፊዎቻቸውን እንዲያገቡ መገደዳቸውን ነው፡፡
የናይጄሪያ መንግሥት ሴቶቹ ከትምህርት ቤት ሲጠለፉ አፋጣኝ ዕርምጃ ባለመውሰዱ እየተወቀሰ ነው፡፡ ትንሽ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረውም የቦኮ ሐራም የመጀመርያው የቪዲዮ መልዕክት ከተለቀቀና ሸማቂዎቹ ‹‹ሴቶቹን በገበያ ቦታ እሸጣለሁ›› ካለ በኋላ ነው፡፡
ይህንን ተከትሎ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይናና እስራኤል የፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታንን መንግሥት ለመርዳትና ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል፡፡
አገሮቹ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ታጋቾቹ የሚገኙበትን ለማወቅ እያሰሱ ናቸው፡፡ ቦኮ ሐራም በበኩሉ፣ ‹‹ሴቶቹን የምታገኙት የናይጄሪያ መንግሥት ያሰረብንን አባላት በሙሉ ሲለቅ ነው፤›› ብሏል፡፡ የናይጄሪያ መንግሥት ደግሞ የቦኮ ሐራምን ጥያቄ ሲያጣጥለው፣ አሜሪካም ‹‹ወንጀለኞች ለሚፈጽሙት ድርጊት ማካካሻ የለም›› ስትል ተደምጣለች፡፡ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ግን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጫናው በርትቶባቸዋል፡፡ ቦኮ ሐራም እንዴት ሊንሰራፋ ቻለ በማለት፡፡
ምንጭ www.ethiopianreporter.com
No comments:
Post a Comment