Monday, May 19, 2014

በአባይ ጉዳይ ኃያላኑ በግብጽ ላይ ጫና እየፈጠሩ ነው የጫናው መነሻ አነጋገሪ ሆኗል

ምዕራባውያን ሃያላን አገሮች ግብጽ በአባይ ዙሪያ የድርድር ጠረጴዛ ላይ እንድትቀመጥ ጫና እያደረጉ መሆኑ ተሰማ፡፡ ዜናውን የዘገበው አልአህራም ቃል በቃል ግብጽ ላይ ጫና ተፈጠረ ብሎ ባይጽፍም ከዜናው ለመረዳት እንደተቻለው ግብጽ ላይ ጫና እየተደረገባት ነው፡፡ ሃያላኑ ግብጽ ላይ እያሳደሩት ያለው ጫና መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
እንደ ጋዜጣው ዘገባ ያለፈው ቅዳሜ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ከኢትዮጵያ ጋር በአባይ ጉዳይ ለመደራደር አገራቸው ፈቃደኛ መሆኗን ማሳወቃቸውን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ይህንን መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት የውሃ ሃብት ልዩ አስተባባሪ ከሆኑት አሮን ሳልዝበርግ እንዲሁም ከአውሮጳ ኅብረት ልዩ ልዑክ አልክሳንደር ሮንዶስ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በተለይ የአሜሪካው ተወካይ ሳልዝበርግ ወደ ግብጽ ከመሄዳቸው በፊት አዲስ አበባ ላይ ቆይታ አድርገው ከኢህአዴግ ባለሥልጣናት ጋር ግድቡን በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸው አብሮ ተዘግቧል፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ በምን ነጥቦች ላይ እንደተደራደረ የተገለጸ ነገር ባይኖርም የአሜሪካው ባለሥልጣን ወዲያው ወደ ግብጽ እንደበረሩ ግብጽ ድርድር መፈለጓ መገለጹ የበርካታዎችን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል፡፡
idan ofer
ኢዳን ኦፈር – ፎቶ ሪፖርተር
በተያያዘ ዜና ሪፖርተር እሁድ ባስነበበው ጋዜጣ ላይ እስራኤል በኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ሥራ የመሰማራት ዕቅድ እንዳላት ዘግቧል፡፡ እስካሁን ድረስ እስራኤል በኃይል ማመንጨት ሥራ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለት ሲጠቀስ የቆየ ቢሆንም ከዚሁ ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም እንደ ሪፖርተር ዘገባ ከሆነ በኢትዮጵያ የፖታሽ ፕሮጀክት 30በመቶ ባለድርሻ የሆኑትን የሚስተር ኢዳን ኦፈር ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ የመሰማራት ዕቅድ እንዳላቸው ጠቅሷል፡፡
እንደ ዜናው ከሆነ እስራኤል የምትሰማራበት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ “የውኃ፣ የጂኦተርማል ወይም የንፋስ መሆኑን” በግልጽ እንዳላሳወቀች ነገር ግን ጥናቱ በኩባንያው ቴክኒክ ቡድን በኩል እንደሚካሄድ የኩባንያው ባለቤት መናገራቸውን ጨምሮ ዘግቧል፡፡ ሚስተር ኦፈር የሚመሩት ኢዝራኤሊ ኬሚካልስ የተባለው ኩባንያ በማዳበሪያና መሰል ምርቶች ላይ የተሠማራ ሲሆን የማዕድን ማውጣት ተግባሩን በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በአውሮጳና ቻይን ያካሂዳል፡፡ ከኩባንያው አክሲዮን ሁለተኛው ከፍተኛ ባለድርሻ የካናዳው የፖታሽ ኮርፖሬሽን እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የእስራኤል በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተግባር የመሰማራቷ ዜና ምናልባትም ከአባይ ግድብ ጀርባ የሃያላኑ አገራት ድጋፍና ጥበቃ እንዲሁም ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ የሆነ ጥቅም የማስከበር ፍላጎት እንዳለ የሚሰነዘረውን ሃሳብ ያጠነክረዋል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት የጫናው መነሻ ይህ የጡንቸኞቹ የጥቅም ጉዳይ እንደሆነ ያስረግጣል ይላሉ፡፡
በዚህና በተለያዩ ምክንያቶች በአባይ ግድብ ዙሪያ የሚነሱት መላምቶች ወይም መከራከሪያዎች ከሃያላኑ ጫና ጋር ተዳምረው መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል፡፡ግብጽ ጫናውን አስመልክቶ በይፋ የገለጸችው ተቃውሞ ወይም ቅሬታ የለም፡፡ ይሁን እንጂ በግብጽ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ላይ ያሉትና የምዕራባውያን ቀጥተኛ ድጋፍ ያላቸው ፊልድ ማርሻል አል-ሲሲ “የውሃ ነገር” ለግብጽ “የህይወትና የሞት ጉዳይ” መሆኑን መግለጻቸውንና  ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን መፍትሔ መፈለጉ “የግድ” እንደሆነ ማስታወቃቸውን ጎልጉል ዘግቦ ነበር፡፡
በዜናው መሠረት አል-ሲሲ “የሌሎችን ፍላጎትና ጥቅም የምንረዳ መሆናችንን ማሳየት ይገባናል፤ (የዚያኑ ያህልም) የራሳችንን ጥቅም ለማስጠበቅ ጽኑ መሆን አለብን፤ (ምክንያቱም) ውሃ ማለት ለእኛ የህይወትና የሞት ጉዳይ ነው” ማለታቸውን ጎልጉል ጨምሮ በማስታወቅ እጩው ፕሬዚዳንት ከዚህ በፊት ያልታየ መለሳለስ በማሳየት “ለኢትዮጵያና ለሌሎች አፍሪካ ወንድሞቻችን ተገቢውን ጥረት አለማድረጋችንን ማመን አለብን፤ በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ለመተባበርና መፍትሔ ለማግኘት ድርድርና የጋራ መግባባት ቁልፍ ናቸው” ማለታቸውን ጭምሮ ዘግቦ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡
የአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያንና ግብጽን ለዘመናት በተለያዩ እሰጥ አገባ ውስጥ የከተታቸው ነው፡፡ በአባይ ከሚፈሰው 90በመቶ የሚሆነው ውሃ የሚመነጨው እንዲሁም በአባይ ተጠርጎ ከሚወሰደው ለም አፈር 96በመቶ የሚሆነው የሚሄደው ከኢትዮጵያ ደጋማ ክፍል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የአባይ ወንዝን አጠቃቀም በተመለከተ የሚያስተዳድሩት ሕጎች እኤአ በ1929 እና በ1959 በግብጽና በሱዳን እንዲሁም በግብጽና በብሪታኒያ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረሙ ውሎች ሲሆን በውሉ መሠረት ግብጽና ሱዳን ከአባይ ወንዝ ኃብት በድምሩ 90በመቶ የሚሆነውን የመጠቀም መብት አላቸው (ይህም በየዓመቱ 55.5 ሜትር ኩብ የሚሆነው ለግብጽ 18.5 የሚሆነው ደግሞ ለሱዳን ማለት ነው)፡፡
ይህ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ውልና አሠራር እንዳለ ሆኖ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ በታህሳስ ወር አቶ መለስ ይህንኑ የቅኝ ግዛት ዘመን ውል እንደገና በመቀበል ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ የተፈቀደላትን የድርሻ ኮታ ማግኘት ይገባታል በማለት ስምምነት መፈረማቸውን አልአህራም በወቅቱ ዘግቦ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ ኢነርጂ ቢዝነስ ሪቪውን በመጥቀስ ሪፖርተር ለንባብ ባበቃው ዜና ላይ “በምሥራቃዊ ሱዳን በኩል ከከሰላ ግዛት ተነስቶ ወደ ኤርትራ በሚዘረጋ የ45 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር” በኩል ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትገዛውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለኤርትራ ለመሸጥ እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ዘግቧል፡፡ ሱዳን ከዚሁ የአባይ ግድብ በርካሽ የምትገዛውን የኤሌክትሪክ ኃይል ምን ያህሉን በምን ያህል ትርፍ ለኤርትራ ለመሸጥ እንዳሰበች እስካሁን አለመታወቁን ጋዜጣው ጭምሮ አስታውቋል፡፡
አቶ መለስ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዓመታት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ያለቀረጥ ክፍያ በነጻ ያህል ከኢትዮጵያ የምትወስደውን ቡና በዓለም ገበያ ላይ በመሸጥ ከቡና አምራችና ሻጭ አገራት ውስጥ ተመዝግባ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ልምድ በመነሳት አሁንም ኤርትራ ከሱዳን የምትገዛውን ከአባይ ግድብ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል በአቅራቢያዋ ለሚገኘው አጎራባቿ የሰሜን ኢትዮጵያ ክልል መልሳ በትርፍ ትሸጥ ይሆናል የሚለው አስተያየት ስላቃዊ ቢሆንም አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡
ምንጭ www.goolgule.com

No comments:

Post a Comment