በሐረር ከተማ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን በቤቱ ደብቆ የተገኘ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋለ ተገለፀ፡፡ የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የመንግስት ሠራተኛ በሆነው ግለሰብ ቤት ውስጥ 2 ቦንቦች፣ 250 የመትረየስና 168 የስናይፐር ጥይቶች፣ 2 ጠብመንጃ፣ 2 የተለያዩ ሽጉጦች፣ 21 የልዩ ልዩ የጦር መሣሪያ ካርታዎች እንዲሁም 1 ሣንጃ ደብቆ ተገኝቷል፡፡
ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በግለሰቡ ቤት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ፤ የጦር መሣሪያዎቹ ቤት ውስጥ፣ ቦንቦቹና ጥይቶቹ ደግሞ በዘይት ጀሪካን ውስጥ ተደብቀው እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ግለሰቡ በግምት ከ50 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለውና በከተማው የረዥም ጊዜ ነዋሪ እንደሆነ ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በቅርቡም በሐረር ከተማ ቀበሌ 08 ነዋሪ በነበረ ግለሰብ ቤት ውስጥ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች ተደብቀው መገኘታቸውን የጠቆሙት ኮማንደሩ፤ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ፣ በግለሰቡ ላይ ክስ እንደተመሰረተበት ተናግረዋል፡፡ ምንጭ አዲስ አድማስ
No comments:
Post a Comment