ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
(ክፍል አንድ) 2014 የኢትዮጵያ የአቦ -ጉማሬው ትውልድ የሚነሳሳበት ዓመት፣
እ.ኤ.አ በ2013 በመጀመሪያው ሳምንት ባቀረብኩት ሳምንታዊው ትችቴ ዓመቱ “የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው (የወጣቱ ትውልድ) ዓመት ይሆናል “የሚል ትንበያ ሰጥቼ ነበር፡፡ እንደትንበያውም ዓመቱ የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው (ወጣቱ) ትውልድ ታላቅ የስኬት ዓመት ሆኖ ተጠናቅቋል፡፡
2014 ደግሞ “የኢትዮጵያ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ዓመት ይሆናል” የሚል ትንበያ እሰጣለሁ፡፡ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ በአፈጣጠሩ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) አባል ሲሆን በተግባራዊ እንቅስቃሴው ግን እንደ አቦሸማኔው (ወጣቱ ትውልድ) የሚያስብ፣ አቦሸማኔውን የሚመስል እና እንደ አቦሸማኔው ሁሉ የክንውን ድርጊቶችን የሚፈጽም የማህበረሰብ ክፍል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ለፍትህ እና ለነጻነት በሚደረገው የትግል ሂደት ላይ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) የሚያንጸባርቃቸውን ድክመቶች በሚገባ የተገነዘበ እና እነዚህን ግድፈቶች በማስወገድ የወጣቱን የትግል መንፈስ እና ወኔ ወደ ላቀ የእድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር በአንድ ዓላማ ለአንድ ዓላማ ከአቦሸማኔው (የወጣቱ) ትውልድ ጎን በመሰለፍ የሚሰራ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡
የኢትዮጵያ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ በአፈጣጠሩ ልዩ የሆነ የትውልድ ዝርያ ነው፡፡ ይህ ትውልድ በተፈጥሮው ድልድይ ቀያሽ እና በኃይል አሰላለፍ ላይ ያለውን ወቅታዊ እና ነባራዊ ሁኔታ በተገቢው መንገድ እያጠና ወጣቱን ትውልድ ለድል የሚያበቁ የኃይል ምንጮችን ቀጣይነት ባለው መልክ የሚፈበርክ የህብረተሰብ አካል ነው፡፡ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ወጣቱን ከቀዳሚው ትውልድ የሚያገናኙ ጠንካራ ትውልድ አገናኝ የትውልድ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ ደኃውን ከሀብታም የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ ህዝቦችን ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋግሩ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ በጎሳ የተለያዩ ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ “ክልላዊ ደሴቶች (የጎሳ መንደሮች ወይም ባንቱስታንስ)” ተብለው ተነጣጥለው የሚኖሩ ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ በቋንቋ፣ በኃይማኖት እና በክልል ተነጣጥለው የተቀመጡ ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው:: ባለመተማመን ሸለቆዎች፣ በእምነት ማጣት ጥልቅ ገደሎችና እና በጥርጣሬ ጎርፍ ወንዞች ላይ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ ብሄራዊ ዕርቅ ለማውረድ እና የብሄራዊ አንድነትን ለማምጣት ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚነገነቡ ናቸው፡፡ በአገር ቤት ውስጥ ያሉትን ወጣቶች በውጭ አገር ከሚኖሩት የዲያስፖራ ወጣቶች ጋር የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ለመሻገር አስቸጋሪ በሆኑ የውኃ አካላት ላይ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የአቦ-ሸማኔው ትውልድ አባላት ኃይል አባዥዎችም ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ዘለቄታ ያለው መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እንዲቻል የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት ከእራሳቸው እውቀት፣ ዘዴ እና ልምድ አኳያ በመቀመር የወጣቱን ኃይል፣ ፍቅር እና ጽኑ ዓላማ በአግባቡ ያለምንም ብክነት በስራ ላይ እንዲውል ያደርጋሉ፡፡ በግትር የአምባገነኖች ተለዋዋጭ ባህሪያት ላይ የእራሳቸውን ፈጠራ በመጠቀም በወሳኝ ጉዳዮች ላይ የወጣቶች የለውጥ አራማጅነት የትግል መንፈስ ውጤታማ እና ስኬታማ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡
የአቦ -ጉማሬው ትውልድ አባል በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል!
የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ በአስፈሪ ዕጣ ፈንታ ውስጥ፣
በእኔ አስተያየት የኢትዮጵያ 21ኛው ክፍለ ዘመን ግንባርቀደም ችግር ሆኖ የሚቀርበው የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር ነው፡፡ በአሜሪካ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ ትንበያ መሰረት ከ37 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር አሁን ካለበት ደረጃ በሶስት እጥፍ በማደግ 278 ሚሊዮን በመሆን ኢትዮጵያን ከዓለም በህዝብ ብዛት ከአንድ እስከ አስር ደረጃ ከሚይዙ አገሮች ተርታ ውስጥ ምድብተኛ ያደርጋታል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ዕድገት ላለፉት አስርት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ እ.ኤ.አ በ1967 የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 23.5 ሚሊዮን ነበር፡፡ በ1990 ወደ 51 ሚሊዮን ያደገ ሲሆን በ2003 ደግሞ ቁጥሩ እየጨመረ በመምጣት 68 ሚሊዮን ደረሰ፡፡ በ2008 ይህ ቁጥር እየጨመረ በመምጣት ወደ 80 ሚሊዮን ከፍ አለ፡፡ በ2013 የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ከ94 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 70 በመቶ (66 ሚሊዮን) የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከ35 ዓመት በታች እንደሆነ ይገመታል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1995 ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ዓመታዊ አማካይ የዕድገት መጣኔ ከ3 በመቶ በላይ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
ኔልሰን ማንዴላ እንዲህ በማለት አመላክተዋል፣ “ልጆቻችን ታላቅ ኃብቶቻችን ናቸው፡፡ ልጆቻችን የወደፊት ተስፋዎቻችን ናቸው፡፡ የልጆቻችንን መብት የሚጥስ ማንም ቢሆን የህዝባችንን የትስስር ክር የሚበጥስ እና አገራችንን የሚያዳክም ነው፡፡“ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች የአገሪቱ ታላቅ ኃብቶች ናቸው ብለን ካሰብን እና በአሁኑ ጊዜ በታላቅ አደጋ ውስጥ ይገኛሉ ከተባለ የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታም በአደጋ ላይ መሆኑን በግልጽ ያመላክታል፡፡ የኢትዮጵያ ታላቅ ኃብቶች ተረስተዋል፣ መብቶቻቸው ተደፍጥጠዋል፣ ወርቃማው ጊዚያቸው፣ ዕውቀታቸው፣ ጉልበታቸው እና ብሩህ አዕምሯቸው ለሀገር ጥቅም ሳይውል ቀርቷል፣ እንዲሁም ባክኗል፡፡ “ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሆነ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት የቅበላ መጣኔ (Enrollment Rate) ከሚያስመዘግቡ በዓለም ላይ ከሚገኙ አገሮች አንዷ ናት፡፡…የአፍሪካ የህዝብ እና የጤና ምርምር ማዕከል ባቀረበው ዘገባ መሰረት በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እያሽቆለቆለ እና የክፍል ደጋሚ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት፣ እንዲሁም በጾታ፣ በገጠር እና በከተማ መካከል የሚታየው ሰፊ ልዩነት የአገሪቱ ከባድ ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል፡፡“ የከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመግባት፣ ወይም ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ስራ የማግኘት ዕድላቸው የመነመነ ሆኗል፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 ዩኤስኤይድ/USAID በኢትዮጵያ ላይ ባደረገው ጥናት መሰረት “ኢትዮጵያ 50 በመቶ የከተማ ወጣቶች ስራ አጥ መጣኔ/Unemployment Rate በማስመዝገብ ከፍተኛ ደረጃ የያዘች መሆኗን እና 85 በመቶ ገደማ የሚሆነው ህዝብ በሚኖርበት የገጠር አካባቢ ያለው ወጣት ከፍተኛ በሆነ ስውር ስራ አጥነት/underemployment/disguised unemployment ውስጥ ተተብትቦ ይገኛል፡፡“ በማለት የጥናት ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በ2012 በዓለም አቀፍ የዕድገት ማዕከል/International Growth Center በተባለ ድርጅት በተደረገ የወጣት ስራ አጥነት ሌላ የጥናት ዘገባ መሰረት “የአሁኑ የኢትዮጵያ የ5 ዓመት የልማት ዕቅድ ማለትም እ.ኤ.አ ከ2010/11–2014/15 ድረስ በሚዘልቀው ገዥው አካል የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ/Growth and Transformation Plan እያለ በሚጠራው ዕቅድ ውስጥ የወጣቶች የስራአጥነት ጉዳይ አልተካተተም…“ ያ ጥናት “እ.ኤ.አ በ2011 38 በመቶ የሚሆነው ወጣት መደበኛ ባልሆነው የስራ ዘርፍ ተቀጥሮ የሚገኝ“ ሲሆን “ዝቅተኛ ተከፋይነት ያላቸው እና የምርት ጥራታቸውም ዝቅተኛ የሆኑ“ እንደነበሩ የጥናቱ ግኝት አመላክቷል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ስራ አጥ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን ስራአጥ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ተቀጣሪ የመሆን ዕድል የላቸውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ወጣቶች ከትምህርት አደረጃጀቱ እና አሰጣጡ አንጻር የጥራት ጉድለት የሚንጸባረቅበት በመሆኑ መሰረታዊ የሙያ ክህሎት ያልጨበጡ በመሆናቸው ነው፡፡ ወጣቶቹ በስራ ላይ ለመቀጠር የሚችሉት በሰለጠኑባቸው እና ክህሎት በጨበጡባቸው የሙያ ዘርፎች በመንግስት ስር ያሉ ቀጣሪ መስሪያ ቤቶች ተቀጣሪዎችን በብቃታቸው እና በተወዳዳሪነታቸው መዝነው ሳይሆን አብዛኛውን ጊዜ ከገዥው አካል ጋር ካላቸው የፖለቲካ እና የማህበራዊ ግንኙነት ቅርርብ አንጻር የፓርቲ አባል በመሆን ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም ወጣት ኢትዮጵያዊ በትክክል የእራሱን ጥረት አድርጎ የዩኒቨርስቲ ዲግሪ ከመያዝ ይልቅ የገዥውን ፓርቲ የአባልነት ካርድ መያዝ የበለጠ ዋጋ እንዳለው ይገነዘባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መሬት የሌላቸው የገጠር ወጣቶች ወደ ከተማ ስራ ፍለጋ በገፍ በሚመጡበት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት፣ ስራ አጥነት እና ተስፋ የማጣት ቀውስ የበለጠ እያወሳሰበው ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች አጠቃላይ የአገሪቱን የማህበራዊ ችግር ቀውሶች ቀንበር የመሸከም ኃላፊነት ወድቆባቸዋል፡፡ እንደሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ጎል/GOAL ዘገባ ከሆነ በመንገዶች ላይ በመንከላወስ የሚኖሩ 150,000 ህጻናት ሲኖሩ ከእዚህ ውስጥ 60,000 የሚሆኑት የአገሪቱ ዋና ማዕከል በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ናቸው፡፡ ህጻናት ቤትአልባ የሚሆኑባቸው እና ወደ መንገድ የሚወጡባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በአማካይ 10 እና 11 ዓመት ዕድሜ ሲያስቆጥሩ ነው፡፡ ወጣቶች በኤችአይቪ ኤድስ እና በሌሎች በግብረስጋ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች የመጠቃት ዕድላቸው እየጨመረ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ የተሻለ ዕድል ማግኘት ያልቻሉት በርካታዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች በአደንዛዥ ዕጽ እና አልኮል እንዲሁም በዘሙት አዳሪነት እና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ተዘፍቀው ይገኛሉ፡፡ ምንም ዓይነት የትምህርት ዕድል እና ስራ ያላገኙ የከተማ ወጣቶች ዕጣፈንታቸው ስራየለሽ፣ ቤትየለሽ፣ እረዳትየለሽ እና ተስፋየለሽ መሆን ብቻ ሆኗል፡፡
ከአስርት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል “የብሄራዊ ወጣቶች ፖሊሲ” ሰነድ አዘጋጀ እና “44 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከፍጹም የድህነት ወለል በታች ነው“ በማለት መግለጫ ሰጠ፡፡ በዚህ ዓይነት የድህነት ሁኔታ ውስጥ ወጣቱ በከፍተኛ ሁኔታ ለጥቃቱ ተጋላጭ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ነው… ከስራ አጥ ወጣቱ አብዛኛውን የሚሸፍኑት ሴት ወጣቶች የመሆናቸው ሀቅ በአብዛኛው በሚባል መልኩ የችግሩ ሰለባ ወጣት ሴቶች መሆናቸውን ያመላክታል፡፡” በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ “የብሄራዊ ወጣቶች ፖሊሲ” ተብሎ የሚጠራው የድርጊት መርሀግብር ለገዥው አካል እና ለፓርቲው ደጋፊነት መመልመያ ሰነድነት ከማገልገል በዘለለ የፈየደው ነገር የለም፡፡ የዚህን ፖሊሲ የማስፈጸም ብቃት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ “መንግስት የመምራት፣ የማስተባበር፣ የማዋሀድ እና የመገንባት ኃላፊነት ተጥሎበታል” በማለት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ ሆኖም ግን የዓለም አቀፉ የዕድገት ማዕከል የጥናት ውጤት በግልጽ እንደሚያመለክተው ከ2010/11-2014/15 ድረስ ለአምስት ዓመታት በሚዘልቀው የአሁኑ የኢትዮጵያ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ቀጥታ የወጣቱን የስራ አጥነት የሚመለከት ጉዳይ አልተካተተም፡፡ “ብሄራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ሰነድ” በተግባር ላይ ያልዋሉ የብሄራዊ ወጣት ፖሊሲዎች ዓለም ዓቀፋዊ የመረጃ ቋት በመሆን ላለፉት አስርት ዓመታት በመደርደሪያ ላይ ተቀምጦ አቧራ በመጠጣት ላይ ይገኛል፡፡
የሁለት ትውልዶች ትረካ፣ በኢትዮጵያ የጉማሬው እና የአቦሸማኔው ትውልዶች ተቀራርቦ የመነጋገር አስፈላጊነት፣
አሁን በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር መሰረት ስንት ሰዓት ነው? በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የአቦ-ገማሬው ትውልድ ሰዓት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአቦሸማኔው እና የጉማሬው ትውልዶች ተቀራርበው ለመነጋገር እና ብሄራዊ ዕርቅ ለማውረድ ጥረት የሚያደርጉበት የመጨረሻው ሰዓት ነው፡፡ ጊዜው የኢትዮጵያ እረፍትየለሾቹ የአቦሸማኔው ትውልዶች እና ተራማጁ፣ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው እና አርቆ አሳቢነት የተላበሱት የጉማሬው ትውልዶች በአንድ መድረክ በአንድነት ተቀራርበው የሚያስቡበት እና በአንድነት ወሳኝ እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ ነው፡፡ አሁን ጊዜው 2014 ነው፡፡
ተቀራርቦ መነጋገር ስል በአቦሸማኔው እና በጉማሬው ትውልድ መካከል በግልጽ እና ግልጽ ባልሆኑ መድረኮች ሁሉ… ማለትም ከእራት ግብዣ አዳራሾች እስከ አካዳሚክ የጥናት ማዕከሎች፣ ከቤተክርስቲያኖች እና መስጊዶች እስከ ሲቪክ ድርጅቶች እና ማህበራት ድረስ የሚያካትት የንግግር እና የውይይት መድረኮችን ማለቴ ነው፡፡ የመነጋገሪያ አጀንዳዎቹ ያልተወሰኑ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን ዓላማዎች አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ በአሮጌዎቹ ሀሳቦች ላይ ጥያቄዎችን ለማንሳት እና ጥሩዎችን ለማካተት አስፈላጊ ያልሆኑትን ደግሞ ለማስወገድ የንግግር መድረኮች ሊኖሩን ይገባል፡፡ አሮጌዎችን፣ ጠባብ አስተሳሰቦችን እና ለሰላም እና እድገት እንቅፋት የሚሆኑ አሉታዊ እንቅስቃሴዎችን ለመለወጥ የንግግር መድረኮች አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ስለፖለቲካ፣ መንግስት እና ህዝብ አዳዲስ ሀሳቦችን ለማመንጨት የንግግር መድረኮች አስፈፈላጊዎቻችን ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቀፍድደው ከያዙን የማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች በድል አድራጊነት ለመውጣት የንግግር መድረኮችን በማመቻቸት ገንቢ እና አዳዲስ የመፍተሄ ሀሳቦችን በማመንጨት የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ላለመስማማትም ቢሆን በሰለጠነ እና በመከባበር ላይ በተመሰረተ አቀራረብ የንግግር መድረኮችን በማዘጋጀት ስምምነት ማድረግ ይቻላል፡፡ ስህተቶችን በማረም ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመምጣት እንዲቻል ተቀራርቦ መወያየት አስፈላጊ እንደሆነ እርስ በእራሳችን መተማመን አለብን፡፡ ይህንን ከባድ ኃላፊነት ለመሸከም እና ለማስተባበር የሚችለው “አዲሱ ትውልድ” ያስፈልገናል፡፡ ሀሳበ ሰፊዎቹ የአቦሸማኔው እና ተራማጅ የጉማሬው ትውልዶች የውይይቱን ሂደት ሊያፍጥኑልን ይችላሉ፡፡
የውይይቱ ዓላማ ያልሆነው የቱ ነው? እንዲካሄድ የሚፈለገው ውይይት አንዱ ሌላውን ጥላሸት ለመቀባት፣ ለመካሰስ እና አንዱ በሌላው ላይ ጣቶቹን ለመቀሰር አይደለም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ቀደም ሲል በተከናወኑ እና ባልተከናወኑ ድርጊቶች ላይ የሆድ ቁርጠት፣ የልብ ስብራት፣ ወይም ጥርስ መንከስ ድርጊቶችን ለማበረታታት አይደለም፡፡ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ኃላፊነት የያዘባቸው የንግግር መድረኮች ሁለት ዓላማዎችን ያካተቱ ናቸው፡፡ እነሱም 1ኛ) ዓለም አቀፋዊ ዕርቅ በማውረድ የንግግር ስራውን መጀመር እና 2ኛ) በአቦሸማኔው እና በጉማሬው ትውልዶች መካከል ባለው የስራ ክፍፍል እና ሚና መግባባት ላይ መድረስ ናቸው፡፡
“የቋንቋ” መግባባት ችግር ባለበት ሁኔታ ዓለም አቀፋዊ መግባባት ሊኖር አይችልም፡፡ በጸጥታ በሚናገሩት የኢትዮጵያ የጉማሬው ትውልድ አባላት እና በዚያ በማይሰማው ንግግር ከኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ ጋር የመግባባት ችግር አለ የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ጥቂት ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት፡፡ ብዙዎቻችን የጉማሬው ትውልድ አባላት ስለለውጥ ስናነሳ የሚታየን ነገር በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኘውን ገዥ አካል ከስልጣን መንበር ላይ በማስወገድ እራሳችንን ከስልጣን ወንበር ላይ ፊጥ ማድረግ ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች መጥፎዎች ናቸው፣ እኛ ግን ጥሩዎች ነን፡፡ አይደለም እኛ የተሻልን ነን፣ በእርግጥም እኛ እጅግ የተሻልን ነን፡፡ በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያሉት የጉማሬው ትውልድ አባላት እራሳቸውን ብቸኛ የለውጥ ሀዋርያ አድርገው ያስባሉ፡፡ እኛ የጉማሬው (የቀድሞው) ትውልድ አባላት ስለአመራር ጉዳይ ስናነሳ የአዲሱ ትውልድ አባላት የእኛን ትዕዛዞች ብቻ እንዲከተሉ እንፈልጋለን፣ ምክንያቱም እኛ ኃይል፣ ልምድ፣ ዘዴዎች እና/ወይም እውቀት ያለን አድርገን እንቆጥራለን፡፡ የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ የበግ መንጋ ሆነው እኛን የሚከተሉ ብቻ እንጅ እነርሱ መልካም ነገሮችን በውል የሚያጤኑ እና ወሳኝ ድርጊቶችን ሊፈጽሙ የሚችሉ ልዩ ችሎታ እና የአመራር ብቃት ያላቸው ወጣቾች እንዳሉ ለመቀበል በጣም እንቸገራለን፡፡ ወጣቶቹ ከእኛ በተለየ መልኩ የእራሳቸው ልዩ የሆነ እና የእራሳቸው ነጻነት እንዲኖራቸው እንፈልግም፡፡ በአጠቃላይ ወጣቱን አሳንሶ የማየት ባህል ተጠናውቶናል፡፡ ወጣቱ ኃይል ዝቅ ያለ ዳኝነት የመስጠት ወይም ነገሮችን በጥልቀት የመረዳት ችሎታ ስለሚያንሰው የእኛን የበግ ጠባቂነት ሚና ማግኘት እና እኛ የምንነግራቸውን ብቻ መከተል አለባቸው እያልን አስተያየት እንሰጣለን፡፡ “ልጆችመታየት አንጂ መደመጥ የለባቸውም”፣የሚሉ ጊዜ ባለፈባቸው የአረጁ እና የአፈጁ አባባሎች ወጣቶቹን ዝቅ አድርገን እንመለከታለን፣ እንዲህ እያልንም እንተርትባቸዋለን፣ “ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም“፡፡ የወጣቶቹን ሀሳቦች አናከብርም፣ ወይም ደግሞ ለየት ያለ ነገር ሲያቀርቡ እና የተሻሉ ነገሮችን ሲሰሩ እየተመለከትን አድናቆት አንቸራቸውም፣ ነገር ግን እነሱን ለመተቸት እና ለማውገዝ የሚቀድመን የለም፡፡
እኛ የጉማሬው ትውልድ አባላት ስለስልጣን ስንነጋገር ምንም ዓይነት ተጠያቂነት እና ግልጽነት በሌለው መልኩ ስልጣንን እንድንይዝ እንገልጋለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው የጉማሬ ትውልድ ስልጣኑን የሚጠቀምበት ለመከፋፈል እና ለመግዛት ነው፣ ስልጣናቸውን በስልጣን ላይ ለመቆየት ከህግ አግባብ ውጭ ይጠቀሙበታል፣ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀም ላይ ይገኛሉ ምክንያቱም ማድረግ ይችላሉና፡፡ ከስልጣን ውጭ ያሉ የጉማሬው ትውልድ አባላት ስልጣን ማግኘትን ይፈልጋሉ ምክንያቱም የላቸውምና፣ ምክንያቱም ስልጣን በእራሱ ሁሉንም ነገር ነውና፡፡ የጉማሬው ትውልድ አባላት ስልጣን ያጡትን ወይም ስልጣን የሌላቸውን ስልጣን እንዲያገኙ አያደርጉም፡፡ በኢትዮጵያ ያሉት ወጣቶች ምንም ዓይነት ስልጣን የሌላቸው እና ስልጣን አልባ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ይህም ማለት 70 በመቶ (66 ሚሊዮን) ያህሉን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚይዘው የህብረተሰብ ክፍል ስልጣን የለውም፡፡
የኢትዮጵያ የአቦሸማሜው ትውልድ በአቦ-ጉማሬው ትውልድ ላይ እምነት አጥቷል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ያ እምነት ወደ መተማመን ሊመለስ የሚችለው በጋራ በመከባበር እና በመግባባት እንዲሁም በመተማመን እና በመቀራረብ ብቻ ነው፡፡ ወጣቶቹ ከእኛ ጋር እኩል እንደሆኑ እና እነሱን በአግባቡ በማስተናገድ መተማመን እና እርቀሰላምን ማውረድ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሀገራቸው ያሏቸው ሀሳቦች እና ራዕዮች ጠቀሜታቸው ከእኛ ሀሳቦች እና ራዕዮች ያላነሱ መሆናቸውን ሙሉ በሙሉ መቀበል አለብን፡፡ ከወጣቶቹ ጋር በእኩልነት በመከባበር እና ተቀራርቦ በመወያየት የጋራ ችግሮቻችንን መፍታት አለብን፡፡
የጉማሬዎቹ አስተምህሮ ለአቦሸማኔው ትውልድ፣
የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት ከእኛ ከጉማሬው ትውልድ አባላት ጋር ተቀራርበው መነጋገር ለእነሱ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ፡፡ ምሳሌ በማቅረብ የጉማሬው ትውልድ ትምህርት ማስተማር ይችላሉ፡፡ ከታላላቆቻቸው ስህተቶች ሊማሩ የማይችሉ ወጣቶች ተመሳሳዮቹን ስህተቶች ይደግማሉ፡፡ እኛ የጉማሬው ትውልድ አባላት ብዙ ስህተቶችን ሰርተናል፡፡ ሁለተኛው ትምህርት የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት የጉማሬውን ትውልድ አባላት ድክመቶች ማሸነፍ እና የእራሳቸውን አዲስ ጅምሮች መተግበር ነው፡፡ የጉማሬው ትውልድ ለአቦሸማኔው ትውልድ ሊያስተምሯቸው የሚችሏቸው ነገሮች የድፍረት ወኔን፣ መተማመንን፣ ለበጎ ነገር መስዕዋትነት መክፈልን፣ ታማኝነትን፣ መንፈሰ ጠንካራነትን፣ ችግሮችን በጽናት የመቋቋም ችሎታ የማዳበርን፣ ለውሳኔ ተገዥነትን፣ እና ችግሮችን በድል አድራጊነት እንዴት መውጣት እንደሚቻል ማስተማር ከብዙዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ “ክብር እና ሞገስ አጥተን” በታላቅ ችግር ላይ ነን፡፡ እነዚህን ክብር እና ሞገሶች ለመመለስ ግን በጋራ ሆነን መሞከር እና ለመተግበር መሞከር ነው፡፡ የአቦሸማኔ ትውልዶችን ከግትርነት፣ ከቁጣ፣ ከጥርጣሬ፣ ከታጋሽየለሽነት፣ ከሙስና፣ ካለመቻቻል፣ ስልጡን ያልሆነ አካሄድን ካለመከተል፣ ከፍርሀት፣ መጥፎ ነገር ከማድረግ፣ ከበቀልተኝነት እና እራስን ከማድነቅ በማለት በእርግጠኘነት የአቦሸማኔውን ትውልድ ለማስተማር ይቻላል፡፡ የአቦሸማኔውን ትውልድ ግልጽ የሆኑ ውይይቶችን በማድረግ በግል እና በህዝብ ህይወት ላይ የተጠያቂነት እና ግልጽኘነት የማስተማር ዘዴን በማሳየት የአቦሸማኔውን ትውልድ ማገዝ እንችላለን፡፡
የአቦሸማኔው አስተምህሮ ለጉማሬው ትውልድ፣
የአቦሸማኔው ትውልድ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ችግሮችን በሰላማዊ እና ኃይልን ባልተጠቀመ መልኩ ሰላማዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ለጉማሬው ትውልድ ማስተማር ይችላሉ፡፡ ወጣቶቹ የሚማሩት እና የሚሰለጥኑት የጦር ተዋጊዎች እንዲሆኑ ብቻ ለማድረግ ብቻ አይደለም ነገር ግን የሰላም ጠበቃዎች እንዲሆኑ ጭምር እንጅ፡፡ ወጣቶቹ ጤናማ የህብረተሰብ ግንኙነቶችን የመፍጠር እና የጎሳ፣ የኃይማኖት ጽንፈኝነትን እና የዘር ጥላቻን የማስወገድ ችሎታ አላቸው፡፡ ወጣቶቹ የህብረተሰብ ትብብሮችን፣ ፍቅርን፣ መግባባትን፣ ሰላምን፣ አንድነትን እና ተስፋን የሚፈጥሩ አስፈላጊ ጉዳዮች ሁሉ ለጉማሬው ትውልድ ማስተማር ይችላሉ፡፡ ሁላችንም በሰላም፣ በእኩልነት እና ፍትህ በነገሰበት መልኩ የምንኖርባት “አዲሲቷን ኢትዮጵያ” ለመገንባት የሚያስችል ችሎታ እንዳላቸው ለጉማሬው ትውልድ ማስተማር ይችላሉ፡፡ የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት ከተፈቀደላቸው እና በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እውነተኛ ተባባሪ እና አጋር እንዲሆኑ ከተደረጉ ለውጥን የሚያመጡ የለውጥ ዘዋሪነት ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ መሆናቸውን ለጉማሬው ትውልድ ማስተማር ይችላሉ፡፡ ወጣቶቹን በጥሞና የምናዳምጣቸው ከሆነ እራሳችንን ከእራሳችን እንድንጠብቅ ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡ ይኸንን ጉዳይ እናስብ! ወጣቶቹ ከጎሳ እስር ቤቶች ግድግዳዎች ሰብረን እንድንወጣ፣ ከምናባዊ ፍርሀቶች እንድንላቀቅ እና የሌሎቸን ሀሳቦች ያለመቀበል እና መጥፎ ሀሳቦች ዓይናችንን እንዳያይ ሸፍነው “አዲሲቷን ኢትዮጵያ” ከአድማሱ ባሻገር እንዳናይ አድርገውን የነበሩትን እንድናስወግድ ሊረዱን ይችላሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን እንደ አገር እና እንደ ህዝብ ህልውናቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ከተፈለገ ያ ህልውና የሚወሰነው በፈጣሪነት፣ በአዕምሯዊ ሃይል እና ጥንካሬ፣ መንፈሰ ጽናት፣ መልካም አመለካከት እና በወጣቶቹ መንፈሰ ጠንካራነት እና በሚከፍሉት መስዋዕትነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ያ ሁኔታ በወጣቶች ላይ ከባድ ሸክምን ይጥላል፡፡ ወጣቶቹ ያንን ከባድ ሸክም፣ ከባድ ስራ እና ታላቅ መስዋዕትነት በመክፈል የአንበሳውን ድርሻ መያዝ አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር እና እንደ ህዝብ ህልውናቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ከተፈለገ ያ የመቆየት ህልውና የሚወሰነው የቀድሞው ትውልድ አባላት ለአዲሱ ትውልድ አባላት ቀልጣፋ እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ ስንችል ነው፡፡ እኛ የጉማሬው ትውልድ አባላት የምንችለውን ነገር ሁሉ በማድረግ የአቦሸማኔዎቹ (ወጣት) ትውልድ እምነት እንዳያጡ እና ውድቀት እንዳይደርስባቸው ተጋድሎ ማደረግ ይጠበቅብናል፡፡ ወጣቶቹ ይህንን ሲያደርጉ ማበረታታት፣ ማገዝ እና ደጋግመው እንዲሰሩት ድጋፍ መስጠት ይኖርብናል፡፡ ትግሉ የፈለገውን ያህል ረዥም ጊዜ ቢወስድም ምንጊዜም ቢሆን ከወጣቶቹ ጎን መሰለፍ አለብን፡፡ ከወጣቶቹ ጋር መወያየት እና መነጋገር አለብን፡፡ ወጣቶቹን መደገፍ እና መውደድ ይኖርብናል፣ ወጣቶቹ በአዲሲቱ ኢትዮጵያ የፕሮጀክት የግንባታ መስክ ላይ ሆነው በጽናት እየሰሩ አስከቆዩ ድረስ ለእነሱ ውኃ ማቀበል እና ሌሎችንም ድጋፎች በደስታ በማድረግ መደገፍ ይኖርብናል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣት ኃይል ምንም ማንም ሊያቆመው የማይችል ኃይል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ተወርዋሪ የአቦሸማኔ ትውልድ ሊያቆመው የሚችል ምድራዊ ኃይል፣ እስካፍንጫው የታጠቀ አምባገነን ኃይል ሊያሸንፈው የሚችል ኃይል የለም፡፡ እኛ የቀድሞው ትውልድ አባላት ምንጊዜም ቢሆን የሚከተለውን የድሮ አባባል ልንከተል ይገባል፣ “ልታሸንፋቸው አለመቻልህን ካረጋገጥህ ተቀላቀላቸው፡፡“ የአቦሸማኔውን (የወጣቱን) ትውልድ በውይይት እንቀላቀል፡፡ ከእነርሱ ጋር ቀረብ በማለት እንወያይ፣ ምን ፍላጎት እንዳላቸውም እንጠይቃቸው፡፡ የእኛን ምክር የሚወዱ እና የሚፈልጉ ከሆነ ይህንን በለጋሽነት እና በነጸነት እንችራቸው፡፡ የእኛን ቴክኒካዊ እገዛ የሚፈልጉ ከሆነ ዕገዛውን እናድርግላቸው፡፡ የሞራል ድጋፋችንን የሚፈልጉ ከሆነ ለእነሱ እናደርግላቸው፡፡ የማቴሪያል ድጋፍ የሚፈልጉ ከሆነ ለእነርሱ የገንዘብ መዋጮ በማሰባሰብ ድጋፍ እናድርግ፡፡ ወጣቶቹ ታላቅ ሸክሞችን ከጫንቃቸው ላይ ለማውረድ፣ ድልድይ በሚገነቡበት ጊዜ፣ የመንገድ ጥገና በሚያካሄዱበት ጊዜ እና ተራሮችን በሚወጡበት ጊዜ በትህትና የተሞላን ውኃ አቀባያቸው ሆነን መቅረብ አለብን፡፡ ለወጣቶቻችን የኃይል ምንጮች መሆን አለብን!
(ክፍል ሁለት ይቀጥላል፡፡)
ታህሳስ 29 ቀን 2006 ዓ.ም
ምንጭ የኢትዮጵያ ሜዲያ መድረክ
No comments:
Post a Comment