ስለማህበረ ቅዱሳን ታሪክ ዝርዝር መረጃ የጠየቃችሁን የተዋህዶ ልጆች እንደሚከተለው እናቀርባለን::
የተዛባ አመለካከት የማይጋርደው ገሐድ እውነታ
ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? ምንስ እየሠራ ነው? ክፍል አንድ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ብራና ዳምጠው፤ ቀለም በጥብጠው፣ ብዕር ቀርጸው በየአብያተ ክርስቲያናቱ የመቃብር ቤቶች ውስጥ በማስተማር ትውልዱ የሀገር መሪ፣ የቤተክርስቲያን አለኝታ፣ የእግዚአብሔር ቅን አገልጋይ እንዲሆን ያበረከቱት አገልግሎት ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ ለትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገራችን ሥልጣኔ በር ከፋች ሆና የኖረች ከመሆኗም በላይ ዛሬ ላለው ዘመናዊ ሥልጣኔም መሠረት የጣለች ባለውለታ ናት፡፡ ቀደምት የቤተክርስቲያን አበው ደከመን፣ ሰለቸን ሳይሉ ዐረፍተ ዘመን እስከገታቸው ድረስ ሲያገለግሉ ኖረው ቤተክርስቲያኒቱ አሁን ከምትገኝበት የዕድገት ደረጃ አድርሰዋታል፡፡
በዚህ ዘመንም የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ሁሉ ይህን ከአበው የተማሩትን ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀውና አስጠብቀው ለሚመጣው ትውልድ የማቆየት ሓላፊነት ያለባቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
በመሆኑም ይሔንን አባቶች ወዛቸውን አንጠፍጥፈው፣ ዐይናቸውን አፍዘው፣ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው በሰማዕትነትና በተጋድሎ ያቆዩትን ሃይማኖት ለማስጠበቅና ለቀጣዩም ትውልድ በተመቻቸ ሁኔታ ለማስተላለፍ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ድጋፍና ዕውቅና የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳን በውጪ በአጽራረ ቤተክርስቲያንና በአሕዛብ፣ በውስጥ ዓላማውን ባልተረዱ፣ ዓላማውን ተረድተው የኑፋቄ ትምህርታቸውን እንደልብ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ለማስረግ ሌት ተቀን በሚተጉ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እየተከሰሰ እየተወቀሰና ያለ ስሙ ስም እየተሰጠው ይገኛል፡፡
እነዚህ በውስጥና በውጭ የሚገኙት የቤተክርስቲያን ጠላቶች ቤተክርስቲያን ላይ በየዘመኑ በሚነሳው ፈተና እየተጠቀሙና በምክንያት እየተሳቡ ለቤተክርስቲያን ወዳጅ መስለው እየቀረቡና እያስቀረቡ ማኅበረ ቅዱሳንን ቢቻላቸው እንዲፈርስ፣ ባይቻላቸው ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓት ለማፍረስ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ የሚያስታጥቋቸው መናፍቃን ሴራና ዓላማ እንዳይጋለጥ እና በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እንደፈለጋቸው እንዲሆኑ ማኅበሩ አገልግሎቱ ተገድቦ እንዲዋቀር ለማስደረግና ለማድረግ የጥፋት ዘመቻዎችን በመክፈት ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ የቤተክርስቲያን ጠላት ወዳጆች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ጊዜ በሰጣቸው ጊዜ ሁሉ በመጠቀም ማኅበሩን ለማሳጣትና ለማጥላላት የሚጠቀሙባቸው ስልቶች በርካቶች ናቸው፡፡
ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል «ማኅበረ ቅዱሳን ሲኖዶስ ከሰጠው ደንብና መመሪያ ውጪ እየሠራ የሚገኝ፣ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለውና ገቢና ወጪው የማይታወቅ ማኅብረ» እንደሆነ አድርገው» ሚያናፍሱት አሉባልታ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀስ ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ግን ባለፉት 17 ዓመታት እነዚህ የውስጥና የውጪ የቤተክርስቲያን ጠላቶች በየጊዜው ማኅበሩ ላይ የሚያናፍሱትን ወሬ ችላ በማለት ከወሬ ሥራ ይቀድማል በማለት ከቅዱስ ሲኖዶስ የተቀበለውን ዓላማ በዓይን በሚታይ፣ በእጅ በሚዳሰስ መልኩ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን «ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል» እንዲሉ ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ? ዓላማውስ ምንድን ነው? ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ሓላፊነት እንዴት እየተወጣ ነው? ለ17 ዓመታትስ ምን ሠራ? የሚሉትን ጥያቄዎት በስፋት ማቅረቡ አስፈላጊ መሆኑን ለምእመናን መግለጽ ግድ ብሎናል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ?
ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት አጽራረ ቤተክርስቲያንና ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱት ተላላኪዎቻቸው የውስጥ ዐርበኞች ማኅበረ ቅዱሳንን በሰው ውስጥ የጥላቻ መንፈስ እንዲያድር ከሚጣጣሩበት መንገድ አንዱ ማኅበሩ የሚጠራበትን ስያሜውን በማዛባት ነው የሚጀምሩት፡፡ ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለውን ነገር ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ስያሜው ላይ አጭር ትንታኔ በመስጠት ወደ ማንነቱና አመሠራረቱ እንለፍ፡፡
የማኅበሩ ስያሜ
አንዳንድ ሰዎች ስያሜውም ግራ ያጋባቸዋል፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው አባላቱ ለራሳቸው ያወጡት አስመስለው የሚነግሯቸው ሰዎች አሉና የዋሀኑ ግራ ቢጋቡ አያስደንቅም፡፡ ነገር ግን የማኅበሩ ስያሜ እኩያኑ ማኅበሩን ለማጥላላት ከሚጠቀሙት ፕሮጋንዳ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ማኅበረ ሚካኤል «የሚካኤሎች ስብስብ»፣ ማኅበረ ማርያምም «የማርያሞች ስብስብ» ካልሆነ /እንዳልሆነ/ ማኅበረ ቅዱሳንም «የቅዱሳን ሰብስብ» አይደለም፣ ሊሆን አይችልም፤ ወይም ማኅበረ ጊዮርጊስን የመሠረቱ ሰዎች ራሳቸውን «ጊዮርጊሶች»ነን እንደማይሉት፤ እንዳልሆኑትም፣ ማኅበረ ቅዱሳንም ቅዱሳን ነን የሚሉ ሰዎች ስብስብ አይደለም፡፡ ይልቁንም ማኅበረ ማካኤል የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት፣ ተራዳኢነት የሚታሰብበት ማኅበር እንደሆነው ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዐት ከመጠበቅና ከማስተማር በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርተ ሃይማኖት መሠረት የቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት እንዲሁም የቅዱሳን መላእክት ክብ ራቸው፤ ገድላቸውና ትሩፋታቸው፣ አማላጅነታቸውና በረከታቸው፤ በሰፊው እንዲታወቅና ትውልዱም የዚህ ተጠቃሚ እንዲሆን ትምህርት የሚሰጡበት ማኅበር ነው፡፡ ምእመናን በነዚህ ቅዱሳን አማላጅነትና ረድኤት እየታገዙ ለመንግሥተ ሰማያት እንዲበቁ ማድረግም ቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡
ከዚህ የተነሣ የእነዚያ ብዙ ማኅበራት ኅብረት የሆነው ማኅበር የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ ጻድቃን ሰማዕታትና የቅዱሳን መላእከት ሁሉ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ተባለ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን እንዴትስ ተመሠረተ?
ዘመኑ የኮምዩኒዝም ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ የሰፈነበት፤ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት አስቸጋሪ የሆነበትና ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሔድ እንደ ኋላቀርነት የሚቆጠርበት ዘመን ነበር 1977 ዓ.ም፡፡
በተለይም በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ /ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች/ በሚገኙ ተማሪዎች ዘንድ ቃለ እግዚአብሔርን በግልጽ መነጋገርም ሆነ መሰማት የማይታሰብበት ወቅት ነው፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች እንዲያስተምሩ ከምዕራባውያኑ ሀገሮች መጥተው የነበሩ ሚሲዮናውያን የኑፋቄ ትምህርታቸውን ያሠራጩ የነበረውም በእነዚሁ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ ትውልዱ በየአቅጣጫው በሚሲዮናውያኑ የኑፋቄ ትምህርት እንዲሁም በኮምዩኒዝም ርዕተ ዓለምና አስተሳሰብ እየተነጠቀ ከኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ እምነት የኮበለለበት ከቤተክርስቲያን የራቀበት ዘመን ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ነው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ዋናው ግቢ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ አምስ
ምንጭ ድምጻችን ይሰማ ዘኦርቶዶክስ
No comments:
Post a Comment