Saturday, October 12, 2013

አደባበዬቻችን እና መንገዶቻችን መሉሱልን? ይድነቃቸው ከበደ (የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ሃላፊ)

‹‹ ዲሞክራሲ የሚመሠረተው መንግስት ሕዝቡን ሊያገለግል የቆመ ነው በሚል መሠረት ሃሳብ ላይ ነው፡፡ ይህም ማለት
ሕዝብ መንግሥትን ለማገልገል የተፈጠረ አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ህዝብ የአንድ ዲሞክራሳዊ አገር ዜጋ እንጂ ተገዥ
አይደለም፡፡ መንግስት የህዝብን መብት በሚያስጠብቅበት ወቅት ህዝብ ደግሞ በልዋጩ ለመንግስት ታማኝነቱን
ይገልፃል፤በጨቋኝ ሥርዓት ግን መንግስት ራሱን ከህዝብ በማግለል ታማኝነትን ከህዝብ ይሻል ፤መንግስት ውሳኔ
የሚወስነው ተገቢውን የህዝብ ድጋፍና ተሳትፎ ሳያገኝ ከሆነ የህዝብ ታማኝነት መመኘት ከንቱ ቅዠት ይሆናል፡፡ ›› (what
is democracy) ከሚለው መፃፍ የተወሰደ ነው፡፡
ጥላቻ ሁለተኛ ከባዱ የሰው ልጅ ስሜት ነው፤ፍቅር የመጀመሪያ ነው፡፡ ጥላቻ በፍራቻ በእውቀት ማነስና በተጠራጣሪነት
የሚመጣ ነው፡፡ ጥላቻ ይቅር ባይነትና መግባባትን ያሣጣል፡፡ ጥላቻ በቡድን፤ጥላቻ በግለሰብ እና ጥላቻ በማህበረሰብ
ውስጥ ሊከሰት ይችላል ውጤቱ ግን ከባድ ቀውስን ያስከትላል፤ለዚህም ይመስላል በሰማያዊ እና በአንድነት ፓርቲ
አማካኝነት በተካሄዱ የተቃውሞ ሠልፈኞቹ ላይ ሁሌም ፍቅር የሚሰበከው ፡፡በመሆኑም በተቃውሞ ሠልፎች ላይ
ፍቅርን፣ሠላምን፣አንድነትን እና ተስፋን ለሰበኩ ለሠላማዊ ታጋዬች ያለኝ አክብሮቴ የባዛ ነው፡፡
በአገራችን ለታየው ብልሹ የመንግስት አስተዳደር በተቃዋሚ ፓርቲዎች እየታየ ያለው እንቅስቃሴ አንድ ሰው ከእንቅልፉ
ተነስቶ ሁለት እጁን ከፍ አድርጎ ከመንጠራራት ጋር የሚዛመድ ነው፤ ይህን መንጠራራት ያልወደደዉ ሽብሩ መንግስታችን
እንቅስቃሴዎችን ለመግታትና ለማፈን የሚያደርገው ጥረት የፖለቲካው እንቅስቃሴ ውጥረት የበዛበት እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በመሆኑም በማንቀላፋት ላይ ይገኝ የነበረው የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ በእድሜ ለጋ የሆነው ሰማያዊ ፓርቲ አደባባይ
በመውጣት ህዝብን በማስተባበር ተቃውሞ ማሰማት መጀመሩን ተከትሎ በሌሎች ፓርቲዎች እየታየ ያለው መነቃቃትና
ተገቢ የሆነው ሥራ ለጨቋኙ መንግስታችን ፈታና ለህዝብ ደግሞ ተስፋ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ በዚህም መሠረት
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንጠራራት ባለፈ እራሳቸውን በጠንካራ መዋቅር በማደራጀት እና አባል በማብዛት፤ እንዲሁም
አማራጭ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሠነዶችን በማዘጋጀት የህዝብ ሙሉ እምነትን እና ተሳትፎ ማዳበር
ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪ የተለያዩ ሠላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን በማስተባበር መንግስትን ማስጨነቅ እና
ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ በማድረግ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን የሚጠበቅ ተግብር
ነው፡፡
ስለ ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን እንስቃሴ ጅማሮ በበጎ ጎን የሚታይ እና የሚበረታታ መሆኑ ቅድሚያ የሚሰጠው ሲሆን፤
በተቃዋሚ ፓርቲዎች እየተደረጉ ያሉና ወደፊት የሚደረጉ የተቃዋሚ እንቅስቃሴዎችን ለመግታትና ለማፈን የሚወጡ
መመሪያዎችና ደንቦች እንዲሁም አዋጆች የህዝብን ድምፅ ለማፈን የተለመደው የገዥው ስርዓት የፈሪ ብትር መሆናቸው
የሚታወቅ ነው፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሠልፍና የአደባባይ ስብሰባ መሳወቂያ ክፍል አዲስ
መመሪያ ማውጣቱን በተለያየ የዜና ማሰራጨዎች ተሰምቷል፡፡መመሪያውን መስተዳደሩ በስራ ላያ እንደዋለውና ሰማያዊ እና
አንድነት ፓርቲ በዚህ መመሪያ መሠረት መስተናገዳቸውን አቶ ማርቆስ ብዙነህ የሰላማዊ ሠልፍና የአደባባይ ስብሰባ
መሳወቂያ ክፍል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣና ለኢሳት በሰጡት አጭር መብራሪያ ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ የተባበሩት መግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጉባሄ ባፀደቀው መግለጫ ኢትዮጵያም
በፈረመችው ስለ መሰብሰብ እና መደራጀት መብቶች የሚከተሉትን ብሏል ‹‹ የዜጎች የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች
ተግባራዊ ሂደት ገደብ በማይጣልበት ሁኔታ መከበር ሲኖርበት ነገር ግን ገደብ ቢደረግ እንኳን ገደቡ የዓለም ዓቀፍ ህግና
ሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ እና የእነዚህን መብቶች ሁለንተናዊ ጥበቃ እዉን የሚያደርግ መሆን አለበት፤በተለይም
ዜጎች የፖለቲካ እና የአይማኖት ለማስከበር የሚያደርጓቸው ተቃውሞዎች መደገፍ አለባቸው፡፡ ››የሚል ሲሆን ፡፡
የኢፌዴሪ ህገ መንስት አንቀፅ 30 ንዑስ አንቀፅ 1 ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዞ በሰላም የመሰብሰብ
፣ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነት እና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሠልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሔድ ላይ ያለ
ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምን፣ዴሞክራሳዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ
ያላቸው ስርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡ በማለት ለህገ መንግስቱ አፈፃፀም ይረዳ ዘንድ ደንብና መመሪያ ሊወጣ እንደሚችል
የሚያመለክት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ህገ መንግስቱ ከመፅደቁ በፊት በኢትዩጵያ ሽግግር መንገስት የተወካዮች ምክር ቤት ተጠባባቂነት የወጣ አዋጅ
ቁጥር 3/1983 ያለ ሲሆን ፤በወስጡ ተደንግገው የሚገኙ የህግ ማቀፎች ህገ መንግስቱን በግልፅ የሚቃረን ያለመሆኑ እንደ
በጎ ጎን ይታያል፡፡ ሆኖም ግን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እና የዲሞክራሲ መብቶችን እንዲሁም የኢፌዴሪ ህገ መንስት
ያስቀመጣቸው የዲሞክራሲ መብቶችን ከግምት ያስገባ አዋጅ አለመሆኑ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው የሚያመላክት ነው፡፡
ከላይ የተገለፁት የህግ ቅደም ተከተሎች ማለትም ዓለም አቀፍ ስምምነት ፣ የኢፌዴሪ ህገ መንስት እና አዋጅ ቁጥር 3/1983
በመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ መብት ላይ ተዘርዝረው የሚገኙ የህግ ድንጋጌዎች እጅግ በጣም ተቀባይነት
ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ለዚህ አፈፃፀም ይረዳ ዘንድ ወጣ ስለተባው እና የአ/አ መስተዳደርም እየሰራውበት እገኛለው
ስለሚለው መመሪያ ህጋዊነቱ አጠራጣሪ ነው፤ በመሆኑም እነዚህን ማሳያዎች መመልከት በቂ ነው፡፡
1ኛ.የመመሪያው ድብቅነትና ህጋዊነት ፡- ‹‹ ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም ›› ተብሎ በደማቁ ተፅፎ የሚገኝው የህግ
ድንጋጌ አመላካችነቱ ማንም ሰው ህግን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ላጠፋው ጥፋት ተጠያቂ እንደሚሆን ነው፡፡ ስለዚህም
ተጠያቂነት የሚመነጨው ከህግ ነው ፤አንድ ህግ ደግሞ ህግ ነው ሊያስብለው የሚያስችለው የህግ አወጣጥ ስነ-ስርአቱን
ተከትሎ ሲሄድ ነው፡፡ በመሆኑም የአገራችን የህግ አወጣጥ ስነ-ስርአት ስንመለከት በቅድሚያ የሚፈለገው ህግ በህዝብ
ተወካዬች ምክር ቤት ወይንም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ሲፀድቅ እና በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ሲወጣ ነው፡፡ ታትሞ
የወጣውን ህግ ማወቅ የሁሉም ሰው ግዴታ ነው ፤ ለዚህም ነው ‹‹ ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም ›› የተባለው፡፡
ስለዚህም የአ/አ ከተማ አስተዳደር ስለ ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የወጣ መመሪያ አለኝ የሚለው ለህዝብ
ግልፅ አይደለም፡፡በመሆኑም አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ የተስተናገዱት በመመሪያው መሠረት ነው ይባል እንጂ ፓርቲዎች
መመሪያውን ከየትኘውም ቦታ መግዛትም ሆነ መግኘት አልተቻላቸውም፡፡በተጨማሪ የሰላማዊ ሠልፍና የአደባባይ ስብሰባ
መሳወቂያ ክፍል አለኝ የሚለው መመሪያ ለፓርቲዎቹ ለማሳየትም ሆነ ለመግለፅ ፍቃደኛ አይደለም፡፡ ነገር ግን በቃል ብቻ
የማይታይ እና የማይነበብ መመሪያ አለኝ ከማለት ያለፈ መመሪያው የት እንዳለ የማይታወቅ ነው፡፡ ስለዚህም የመመሪያው
ድብቅነትን መነሻ በማድረግ በአገራችን የህግ አወጣት ስነ-ስርአት መሠረት መመሪያው ህግ ነው ብሎ ለመቀበል ይቸግራል፡፡
2ኛ. መመሪያዊ ከይት እንደመጣ አይታወቅም፡- የህግ ቅደም ተከተሎችን ስነመለከት አዋጅ፣ደንብ እና መመሪያ
ናቸው፡፡በመሆኑም በአወጅ ባልተሰጠ ስልጣን ደንብ ሊወጣ አይችልም እንደዚሁም በደንብ ላይ ባልተሰጠ ስልጣን መመሪያ
ሊወጣ አይችልም፡፡ በዚህም መሠረት በአዋጅ ቁጥር 3/1983 ታትሞ በወጣ ስለ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ
ስነ-ስርአት አዋጅ ላይ ለአዋጁ ማስፈፀሚያ የሚረዳ ደንብና መመሪያ ማውጣት እንደሚቻል እና ማን ሊያወጣ እንደሚችል
የሚያመላክት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም የአ/አ ከተማ አስተዳደር ስለ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ስነ-ስርአት
የወጣ መመሪያ አለኝ የሚለው በየትኛውም መመዘኛ የህግ አግባብነት የሌለው ነው፡፡ምክንያቱ ደግሞ በስራ ላይ ዋለ
የተባለው መመሪያ በህግ በተሰጠ ስልጣን መሠረት የወጣ መመሪያ አይደለም ስለዚህም መመሪያው ህጋዊነቱ አጠራጣሪ
ነው፡፡
3ኛ. መመሪያ ከህገ መንግስቱ በላይ አይደለም፡- ይህ ማለት መመሪያ በህግ ተደንግገው ለሚገኙ መብት እና ግዴታዎች
ማስፈፀሚያ የሚረዳ የአሰራር ስልት አመላካች ነው፡፡ በመሆኑም ከአዋጅ ቁጥር 3/1983 እንዲሁም ከህገ-መንግስቱ በላይ
መመሪያን መሠረት በማድረግ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የማድረግ መብት በመመሪያ ለመገደብ የሚስችል
ህጋዊ መሠረት የለም፡፡በህገ መንግስቱ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ1 ማንኛውም ህግ፣ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት
ባለስልጣን ወይም አካል ውሳኔ ከህገ መንግስቱ የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም ሲል እንዲ አይነቱን በህግ ሰይሆን
በጉልበት እና በማንአለብኝነት የሚወጡ መመሪያዎችን ለመከላከል ወይም ውድቅ ለማድረግ ነው፡፡
በመሆኑም በህገ መንግስቱ የተቀመጡት ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቶች ለዜጎች ዋስትና የሚሆኑት በህግ አስፈፃሚው እና
በህግ ተርጓሚው በወረቀት ከመፃፍ በላፈ ተግባራዊ ሲደረግ ነው፡፡ በይበልጥ ደግሞ ህገ መንግስቱን መሠረት አድርገው ዜጎች ድጋፋቸውን እና ተቃውሟቸውን እንዲሁም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዬቻቸውን በገዛ አገራቸው ዋስትና አግኝተው
በነፃነት በመረጡት መንገድ ሃሳባቸውን ሲገልፁ ህገ መንግስቱ ተቀባይነቱ በዛው ልክ ይጨምራል፡፡
ይሁን እንጂ በአገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ህገ መንግስት እና ህዝብ ፊትና ጀርባ ሆኗዋል ለዚህም እንደማሳያ ብዙ
ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል፤የሚቀርብ ምክንያቶች የአደባባይ ሚስጥር ከሆኑ ሰንብተዋል፡፡የነገሩ ሁኔታ በዚህ የሚቀጥል
ከሆነ ለህግ እና ለህጋዊ ሥርአት የሚኖረው አመለካከት ከመበላሸቱ በላፈ ያልተረጋጋ ምህበረሰብን ለመፍጠር ዋንኛ
ምክንያት ይሆናል፤ የዚህን ውጤት ደግሞ መገመት ቀላል ነው፡፡
ስለዚህም ከላይ የተገለፁትን መጠነኛ የህግ አመላካቾችን በመዳሰስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሠልፍና
የአደባባይ ስብሰባ መሳወቂያ ክፍል አለኝ የሚለው መመሪያ ምንም አይነት ህጋዊነት መሠረት እንደሌለው የሚያመላክት
ነው፡፡ በመሆኑም ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን የሚያሰማበት መንገዶችን እና አደባባዬችን በህግ ወጥ መመሪያ እና በፖሊስ
ጉልበት መከልከል ይቻል ይሆናል ግን እስከመቼ …………. ??????፡፡
source ethiopian media forum .

No comments:

Post a Comment