ወጣቱ የነፃነት ሰላማዊ ታጋይ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ ዋለ የፃፈው ‹‹ያልተሄደበት መንገድ›› ገበያ ላይ ዋለ፡፡ አንዷለም አርአያ ክብር ነው፡፡ ምሳሌና አርአያ ብናደርገው የምንጠቀምበት ምርጥ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በቅርበት ስለማውቀው ብቻ እራሴን እንደ ዕድለኛ እቆጥራለሁ፡፡ ማርቲን ሉተር ኪነግንና ማህተመ ጋንዲን አንስቶ አይጠግብም፡፡ ስለፍቅር ሲል ሁሉን አሳልፎ መስጠት የሚችል፤ ስለ ኢትዮጵያ የሚሰስተው የሌለው ውድ ወጣት ነው፡፡ ለአላማው በፅናት መቆምን ተክኖበታል፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ ጨለማው ሳይበግረው ያልተሄደበት መንገድን ሊያሳየን በመፅሐፍ መጣ፡፡ የማይበገር ራዕይ ያላቸው ሰዎች እንደዚህ ናቸው፡፡ እድለኛ ካልሆኑ በስተቀር እንደዚህ መሆን ከባድ ነው፡፡
ለቅምሻ ያህልም ከመግቢያው እነሆ ብያለሁ፡-
‹‹….መታሰር ነገሮችን በጽሞና ለማየት እድል ይሰጣል፡፡ በስራ የተጠመደ ሰው ነገሮችን በአንክሮ ለማሰብ የሚፈልገውን ያህል ጊዜ አያገኝም፡፡ ድንገት የሚከሰቱ ነገሮች ማእበል ከአንዱ ጉዳ ወደ ሌላው ያላጋዋል፡፡ እኔ አሁን ከእንዲህ አይነት ሁኔታ ነፃ ነኝ፡፡ስለዚህ ፍፁም አስቸጋሪ በሚባል ሁነታም ቢሆን በግፍ ከተለየሁት የኢትጵያ ህዝብ ጋር በሃሳብ ለመገናኘት መሞከር እንደሚገባኝ ወደንኩ፡፡ ጥረቴ የሚገትመው ፈተና በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ግልፅ ነበር፡፡ በመሆኑም የሃገራችን አንዳንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነገሮችን አንስቼ ለመወያየት በማሰብ ‹‹ከዚህ ወዴት እንሄዳለን? ትላንት ዛሬና ነገ›› የሚል ርእስ መዘገብኩ እንደሃገር ካለፈው ይልቅ ስለሚመታው አብዝትን ልንጨነቅ እንደሚገባን ባምንም ያለፈውና አሁን ያለንበት ደግሞ ወደሚመጣው ዘመን የምንደርስበት ሜዳ በመሆኑ መዳሰስ ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ያለሁባት ክፍል እጅግ ጠባብ ከመሆኗ የተነሳ ስድስት ሆነን እግርና ጭንቅላታችንን ገጥመን ከዳር እስከዳር ሞልተናታል፡፡ መኝታውም መቀመጫውም ፍራሽ ነው፡፡ እጅና እግር ሲጠጋጉ የጠረጴዛና ወንበር ሚና ይጫወታሉ፤ እጅም የመፃፍ ስራውን ይሰራል፡፡ ለመቀመጥ አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ግን የጀርባ ህመም ማስከተሉ አልቀረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ለመፃፍ ሌሊቱን መጠቀም ነበረብኝ፡፡ ለምን ቢሉ እኔ ምን እንደምሰራ እንዲከታተሉ የተመደቡ ወንደሞች በመኖራቸው እነርሱም በማዳከም እንቅልፍ ባለውለታዬ ነው፡፡ ከጎኔ ተኝተው እንቅልፋቸውን ሲያጣጥሙ እኔ ደግሞ በሃሳብ ፈረስ ጋልቤ የምወዳት ሃገሬን የእስር ቤት አጥር ሳይገድበኝ እዞራታለሁ፡፡ በሃሳብ ዶሴዎቿን ከመሳቢያ እያወጣሁ አገላብጣለሁ፤ የሚመስሉኝን ሃሳቦች እሰነዝራለሁ፤ እፅፋለሁ፡፡
በዚህ ሁኔታ ሆኜ ወረቀትና ብእርን ማገናኘት ቀላል ባይሆንም ከሁሉ የሚያስቸግረው ግን ዋቢ መፅሃፍትን ሰብስቦ እያጣቀሱ በጥሩ ሁኔታ የተጠና መፅሃፍ ማዘጋጀት ነበር፡፡ መፅሃፍትን ማስገባት በጣም ከባድ ነው፡፡ ማስገባት ቢቻል እንኳን መፅሃፍቱን በሚገባ አመሳክሮና ጊዜ ወስዶ አንድ መፅሃፍ ማበርከት በጣም ከባድ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ሞልቷል፡፡ ነገርግን የሚፃፉ ፅሁፎች በየጊዜው በሚደረግ ፍተሻ ይወሰዳሉ፡፡ የዶ/ር ኪንግን መፅሃፍ ትርጉምን አጥቻለሁ፡፡ ሌላ ተመሳሳይ ችግር ደግሞ ማስተናገድ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ከጊዜ ጋር የሚደረገው ግብግብም ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ በተለያዩ ምክንያቶች ዋቢ መፅሃፍትን ማመሳከር አለመቻሌን እንዳለመታደል እቆጥረዋለሁ፡፡ አንባቢም ይኸንን ውሱንነት እንዲረዳልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ በእርግጥ ያም ሆኖ እጄ ላይ ያሉ ውሱን መፃህፍትን ማገላበጥ ችለሁ፡፡
በመሆኑም ለመፃፍ እቅድ ማውጣት በንፅፅር ሲታይ ቀለል ቢልም በተለይ አሁን ባለሁበት ሁኔታ ሃሳብን አደራጅቶ ለመከራከር ብሎም ለመፃፍ መሞከር በጣም ከባድ ነበር፡፡ ፈጣሪ ፀጋውን አብዝቶልኝ ግን ለመፃፍ ሞክሬያለሁ፡፡ ለእኔ ትልቁ ቁምነገር በዚህ አይነት ሁኔታም ሆኜ ለሃገሬ ይበጃል የምለውን ነገር ሃሳቤን የመግለፅ ተጠቅሜ መፃፍ መቻሌ ነው፡፡እንደመሸበብ ክፉ ነገር ይኖር ይሆን?
በእኛ ሃገር የፖለቲካ ባህል ውስጥ ላደገ ሰው በግፍ ከሚስቱ፣ ከልጆቹና በዙርያው ካሉ ወዳጅ ዘመዶቹ ተለይቶ በወህኒ ቤት ሆኖ የጭቆናን ገፈት የሚጎነጭ ሰው ስሜታዊ እንደሚሆንና የመጠቃት ስሜትም ሊታይበት እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ከደረሰብኝ ነገር ሁሉ አንዳች ያልጠበኩት ነገር ባይኖርም አንዳንድ ጊዜ ስሜቴ መጎዳቱ አልቀረም፡፡ ስሜቴ በምፅፍበት ወቅትም ሚዛናዊ እንዳልሆን ይልቅስ ስሜቴን ብቻ እንደወረደ እንዳስተናግድ በተደጋጋሚ ቢፈትነኝም በተቻለኝ መጠን ፈተናውን ለማለፍ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በግል በደል ወይንም ጥቅም ላይ ተመርኩዞ ከመፃፍ ይልቅ ለሁላችን የሚጠቅመውን በተለይም ከዛሬ ይልቅ ለነገ ይበጀናል የምለውን ሃሳብ ለማመላከት ሞክሬያለሁ፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሞት ለሁላችንም ማይቀር እዳ ነው፡፡ ከሞት በኋላም ግን ዛሬ ያላነሳነው አጀንዳና ያነገብነው እውነት በልጆቻችን ፊት መቅረቡ አይቀርም፡፡ ዛሬ የያዝነው ሃሳብ የጊዜን ፈተና አልፎ በትውልድ ፊት ሞገስ ቢያገኝ ፍሬም ቢያፈራ ትልቅ መታደል ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለኝ መጠን ሚዛናዊ ለመሆን አቅሜ የፈቀደውን ጥረት አድርጌያለሁ፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ ሌላም የሃሳብ ውጣ ውረድ ለማስተናገድ ተገድጃለሁ፡፡ እንደሚታወቀው የሃገራችን ፖለቲካ በብዙ መልኩ ጠርዝ የያዘ ነው፡፡ ሚዛናዊ ለመሆን ስሞክር በኢህአዴግ በኩል‹‹ ክንዳችንን አቀመስነው፣ አስተነፈስነው›› የሚል ስሌት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ በመገመቴ ይኼን አይነት ስሜት በማይፈጥር መልኩ ለመፃፍ መታገል ነበረብኝ፡፡ ይኼን ሳደርግ ደግሞ እኔም ደግሞ በቃራኒው ከእምነቴ ውጪ የሆነ ነገር እንዳላራምድ መጠንቀቅ ከባድ ኃላፊነት ነበር፡፡ በሌላ ወገን አንባቢ የተሳሳተ ግምት እንዳያድርበትም እንዲሁ መጠንቀቅ ነበረብኝ፡፡ በተቀውሞው ጎራ ያለው ወገን ደግሞ ‹‹ተሸጠ፣ተለወጠ፣ ከኢህአዴግ ጋር ተሞዳሞደና እጅመንሻ የውዳሴ መፅሃፍ ፃፈ›› የሚል የተሳሳተ ሃሳብ ውስጥ እንዳይገባ ለመጠንቀቅ ሞክሬያለሁ፡፡በእነዚህ ሁለት ፅንፎች ውስጥ ለማለፍ ስሞክር ማስተላለፍ የፈለኩትን መሰረታዊ ሃሳብና ልከተል የፈለኩትን የሃሳብ መስመር ላለመልቀቅ ተፍጨርጭሬያለሁ፡፡ እንዲህ አይነት የሃሳብ ማእበል ሲኖር ምንም ያህል ቢደከምም የሚፈለገውን ያህል ሌላውን ቀርቶ እራስንም ለማስደሰት ይከብዳል፡፡ ኃላፊነት ከባድ ነው፡፡ ሁላችንም ከልዩነቶቻችን ይልቅ ወደአንድነታችንና በጎ ነገሮቻችንን እንደናይ የሚያስችል ፅሁፍ ለመፃፍ ሞክሬያለሁ፡፡ ስሜቴ አሸንፎኝ ልዩነቶቻችንን የሚያሰፋ ጎዳና ተከትዬ ከሆነ አንባቢ እኔ ያልሄድኩበትን መንገድ እንዲሄድበት እጋብዛለሁ፡፡ ምናልባት በለስ ቀንቶኝ አንድነታችንን የሚያጠናክርና እራሳችንን እንድናርም፤ ያለመቆጠብ ወደ ውስጣችን እንድናይ፣ ልዩነቶቻችንም በሰከነ መንገድ ለመፍታት እንድንችል ሃሳብ ሰንዝሬ ከሆነ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ከተዘጋጀ መፅሃፍ ክፍተት አይጠፋምና አንባቢ ክፍተቶችን ለመሙላት ይሞክር፡፡ ውይይቱንም በማስፋት የተሸለና የተሞረደ ሃሳብ እንዲወለድ ሃገራችንም ከምትገኝበት አዘእቅት ውስጥ እንድትወጣ የበኩሉን አስተዋፅዎ ያድርግ ቢለዋ ከቢለዋ ሲፋጭ ስለት ይወጣዋልና፡፡››
ምንጭ ዘ-ሐበሻ
No comments:
Post a Comment