Friday, June 28, 2013

ይድረስ ለኢትዮጵያው ሥውር መንግሥት

ይነጋል በላቸው

ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ኢትዮጵያን ማን እየገዛ እንደሆነ ከግምት ያለፈ ዕውቀት የለኝም፡፡ በመለስ ጊዜም ቢሆን ሀገሪቱ በዕውር ድንብርና በነሲብ ነበር የየሚገርም አጋጣሚ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንና በዚያ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ኃላፊዎች ጸሎት በቶሎ እንዲድኑ ሲጸልዩላቸው የሀገሪቱ የሃይማኖት ታዋቂ አባትና ተከታይ ምዕመኖቻቸው ግን በሰላም እንዲያርፉ ነው ጸሎት እየተደረገ ያለው – ለኔልሰን ማንዴላ፡፡ ይህ ነገር የሥልጣኔ ልዩነት ይሁን የባህል አልገባኝም፡፡ ይህን የዜና ሽፋን ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ በሚሰራጭ አንድ የተቃውሞው ጎራ ቴሌቪዥን አማካይነት እየተከታተልኩ ነኝ – ልክ አሁን፡፡ በመሠረቱ ከ94 ዓመታት ምድራዊ የሥጋ ለባሽ ሕይወት በኋላ አንድ ብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ ያሳለፈና በእሥርም ብዙ የተሰቃዬ ሰው ዕድሜ እንዲረዝም መመኘት ከፍቅር ብዛት የሚመነጭ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ በጀመርኩት ሃሳብ ትንሽ ልቆይና ወረድ ብዬ በዚህ ላይ እንደመጠቅለያነት እመለስበታለሁ፡፡
… በመለስ ጊዜም ቢሆን ሀገሪቱ በዕውር ድንበርና በነሲብ ነበር እስትንፋሷ ውሎ እሚያድረው፡፡ ሰውዬው የሚፈልገው ሁሉ እዛው ባለበት እየቀረበለትና እንደአንበሣ በብረት አጥር ውስጥ እየኖረ በስልክና በደብዳቤ ሲገዛንና ሲሸጠን ኖረ፤ ፈጣሪ በወደደው ሰዓት ያን የእፉኝት ልጅ ወሰደ፡፡ ጦስ ጥንቡሱ ግን አሁንም እንደገነነ አለ፤ መቃብር ውስጥ ሆኖ በመግዛት መለስ አንደኛ ሣይሆን አይቀርም፡፡ ይቺ ራዕይ የሚሏት ሀገርን የማጥፋት ተልእኮ በየወያኔው ጭንቅላት ውስጥ ሠርፃ ገብታ እነሱንም እኛንም ዕረፍት ነስታለች፡፡ አዳሜ እየተነሣ “ከመለስ ራዕይ ጋር ወደፊት!” ይላል፡፡ “ራዕያቸው ምን ነበር?”ተብሎ ሲጠየቅ በቅጡ የሚመልስ የለም፡፡ የፈረደበት የአባይ የሚሌኒየም ይሁን የሕዳሴ ግድብ አለ፡፡ እሱው መሰለኝ ትልቁ ራዕይ፡፡ በሌሎች ሀገሮች እዚህና እዚያ የተትረፈረፈ የወንዝና የኩሬ ግድብ እኛ ሀገር ሲደርስ ብርቅ ሆኖ ሰውን በመዋጮና በተስፋ ቁንጣን እየገደለ ነው፡፡ ራዕዩ ይሄው ነው፡፡ በተረፈ በሚሊዮኖች ላብና ደም ጥቂት ቅንጡ ሀብታሞችን የመፍጠር ራዕይ ካልሆነ በስተቀር፣ ለብዙ አሠርት ዓመታት ተከፍሎ በማያልቅ ብድር መንገድና ሕንጻ መሥራት ራዕይ ካልሆነ በስተቀር፣ ይበልጡን ለፖለቲካ ፍጆታ በሚመስል መልኩ የሀገርን ሀብት ለተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በማዋል በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችና በኮብል ስቶን ሥራ አደራጅቶ ዜጎችን በጥቅም መከፋፈል ራዕይ ካልሆነ በስተቀር፣ ለዕይታ ሳይቀር የሚዘገንን የኔቢጤ (ለማኝ)፣ ወፈፌና ሰካራም፣ ብስጩና ግልፍተኛ፣ በረንዳ አዳሪና የዐዋቂና ሕጻናት ሴተኛ አዳሪዎችን በየዋና ዋና ከተሞች በብዛትና በስፋት ማምረት በልዩ ራዕይነት ካልተመዘገበ በስተቀር የመለስ ራዕይ ብሎ ነገር የሚጨበጥ ነገር አላየሁም – በዋና ራዕይነት እንዲመዘገብለት ከተፈለገ ዋናው የመለስ ራዕይ የተከፋፈለችና የደከመች፣ ለኤርትራ በምንም መንገድ የማታሰጋ ጥንጥዬ ኢትዮጵያን በሂደት መፍጠር ነው – ይሄ የሚታየው ብልጭልጭ ነገርና የዕድገት እመርታ የሚመስል የፎቅና የአስፋልት ወይም ሌላ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሁሉ መለስ ሳይወድ በግዱ በሥሩ ባሉ ጥቂት ሀገር ወዳድ ወያኔዎች አማካይነት የተከሠተ – ‹ከሬዲቱ› ለርሱ ብቻ የሚሄድ ሳይሆን ለማለት ነው- በመለስ የጥፋት ራዕይና በአፈጻጸሙ መካከል እንደሳይድ ኢፌክ ሊቆጠር የሚችል አጋጣሚ ነው፡፡ ምን ማለቴ ነው – መለስ ኢትዮጵያን በማጥፋት ሂደት ተጠምዶ ሳለ ያን ሂደት ተዓማኒነት እንዲኖረው ለማድረግ ኢትዮጵያዊ መስሎ መታየት ወይም ማታለል ስላለበት ለዚያም ሲባል አንዳንድ የሚታዩና የሚጨበጡ ነገሮችን ማድረግ ስለነበረበት በኢትዮጵያዊ ስብዕና ዓለም አቀፍ አመኔታን ለማግኘት ሲል ባልጠበቀው ሁኔታ ከእጁ ሾልከው ክፉ ገጽታውን በጥሩ ቅባት ያዋዙለት አጋጣሚዎች ነበሩ ወይም ናቸው(ለዚህም ይመስላል ብዙ ኢትዮጵያውያን በዚህ ሰው ‹ምትሃት› ተወናብደው የወያኔን ትክክለኛ ተፈጥሮ እንዳያውቁ የተደረገውና ዐይናቸው በወያኔ ጥፋት ላይ እንዳያማትር እንዲያውም በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም የርሱ ነገረ ፈጅ እስከመሆን እንዲደርሱ የተሞከረውና አሁን አሁን ደግሞ እየቆጫቸው መምጣቱን እየተገነዘብን ያለነው…) ፡- በሕክምና አነጋገር ለጉበት የወሰድከው መድሓኒት ኩላሊትህን ሊጎዳ ይችላል – ኔጌቲቭ ሳይድ ኢፌክት፡፡ ለራስ ምታት የወሰድከው መድሓኒት ከጨጓራ ህመምህ ሊፈውስህ ይችላል – ፖዚቲቭ ሳይድኢፌክት፡፡ የመለስም የአባይ ግድብና ሌላው ግርግር ሁሉ ከዚህ መሠረታዊ እውነት ያለፈ አይደለም፡፡ እውነተኛ የሕዝብ ፍቅርና የሀገር መውደድ ስሜት ቢኖረው ኖሮ… ታውቁት የለ – ምን ወደዚያ ውስጥ ከተተኝ … ፡፡ ይቅርታ – በዋናው የሃሳብ መስመሬ ላይ እንደአረብ ጣቢያ ጣልቃ እየገባ ኳርት የሚለዋውጥብኝና እንድዘባርቅ የሚያደርገኝ ዘርፈ ብዙው የሀገራችን ችግር በመሆኑ ታገሱኝ፡፡
ኢትዮጵያን በአሁኑ ወቅት እያስተዳደረ ያለው ማን ነው? የት ተቀምጦ? በስምና በአካል ይታወቃል ወይ? ብለን እንጠይቅ፡፡
እኔ በግል እንደምታዘበው ኢትዮጵያን በአሁኑ ወቅት እያስተዳደራት የሚገኘው ሰው አይመስለኝም፤ መንፈስ ነው፡፡ ይህ መንፈስ ግማሹ ቅዱስ ነው፤ ግማሹ ደግሞ እርኩስ ነው – አሁንም በኔ ዕይታ፤ ዕይታየ ትክክል ነው ትክክል አይደለም የኔ ጉዳይና የናንተ የኅሊና ፍርድ ነው፡፡
ቅዱስ ያልኩት በተከመሩብን ሁለንተናዊ የፖለቲካና ማኅረሰብአዊ ችግሮች የተነሣ እርስ በርስ ተበላልተን እንዳናልቅ እየረዳን ያለ አንዳች ኃይል መኖሩን ከመገመት ባለፈ ስለማምን ነው፡፡ ይህ ኃይል ባይኖር ኖሮ በሀገሪቱ እንደሚታየው ጭቆናና የኑሮ ውድነት አንድም ሰው በአንጻራዊ ሰላም ከቤት ወጥቶ ወደቤት በሰላም ባልገባ ነበር – እውነቴን ነው የምለው ይህን ዓይነት ደግ መንፈስ ባይጠብቀን ኖሮ ተበላልተን ለማለቅ የሚፈጅብን ጊዜ ሰዓታትን ብቻ በወሰደ ነበር(ሦርያንና ሊቢያን… ያዬ ይፍረድ – ሊያውም ከኛ በእጅጉ ያነሰ ጭቆናና እንግልት ደርሶባቸው!) ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠረው በረንዳ አዳሪ፣ ሥራ አጥና ቤት አልባውም በ”ሰላም” ካደረበት ከየቱቦውና ከየላስቲክ ቤቱ ወጥቶ በቀጣዩ ቀን በየአደባባዩ ባላየነው ነበር፡፡ ካለአንዳች አለሁህ ባይ የመንግሥት መዋቅር በራሱ ኃይልና እንዲሁ በኪነ ጥበቡ ርሀብና ችግሩን ችሎ የሚኖር ሕዝብ ማየት የሚገርምም የሚሰቀጥጥም በድንቃ ድንቅ መዝገብ ሊመዘገብ የሚገባውም የሚሌኒየሙ ተዓምር ነው፡፡ አንድም ሥራና አንድም ደመወዝ የሌለው በሚሊየን የሚገመት ዜጋ ቀኑን አለበቂ ምክንያት እዚህና እዚያ ሲንከራተትና ሲንገላወድ ውሎ አሁንም ልድገመውና በየሥርቻውና በየሥርጓጉጡ በ”ሰላም” አድሮ የቀጣይዋን ዕለት ጀምበር ለማየት እባቡር መንገዱ ላይ ተሰጥቶ መታየቱ የትንግርትን እንጂ የመንግሥትን ኅልውና አያመላክትም፡፡ በዚህ ምክንያት የሀገራችንን በትረ ሥልጣን ከያዙ ሥውር ኃይሎች ውስጥ የተወሰነውን ‹የፓርላማ ወንበር› የተቆናጠጠው አንዳች የተቀደሰ ነገር መሆን አለበት ብዬ አምለሁ፡፡ እንዲያ ባይሆንማ ማን እየተዘባነነ ማንስ በችግር አለንጋ እየተገረፈ በርሀብና በጥም እየተሰቃዬ ይኖር ነበር? ሀሰት ነው?
በሌላ በኩል የሚታየውን መቋጫ የሌለው የግፍ አገዛዝና የዘረኝነት ቱማታ ስንቃኝ ከነዚህም ጋር የሚቆራኘውን አጠቃላይ የድቀት ሕይወት ስንታዘብ በተለይ በፖለቲካውና በሃይማኖቱ አመራር ረገድ የእርኩሱ መንፈስ ምን ያህል የበረታ እንደሆነ መረዳት አይቸግርም፡፡ ስለዚያም ምክንያት ይመስለኛል ይህ በመለስ የሙት መንፈስ የሚነዳ የአጋንንት መንጋ አንዳች ሥፍራ ተደብቆ ደህና ሰው ወደ አመራር ዝር እንዳይል እነአዜብንና በረከትን እየተመሰለ በላያችን ላይ የሚያንዣብብብን፡፡ እንደሚወራው አዜብ ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሆና አይደለም ጽዳትና ዘበኛም ሆና ብትመጣ እንኳን ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት፡፡ በሌላ ቦታ እያለች የማዘጋጃ ቤት ሹሞችን በስልክ እያስፈራራችና በአካል እያስጠራች ስንትና ስንት ግፍና በደል መፈጸሟ እየታወቀ አንድያውን በዚያ ቢሮ ስትገኝማ ከተማዋን ብቻ ሣይሆን እኛን ነዋሪዎቹን በጅምላና በችርቻሮ ባወጣንበት ዋጋ ቸብችባ በጥቂት ወራት ውስጥ ትጨርሰናለች፡፡ አዜብ – ዮዲት ጉዲት – እንኳንስ ማዘጋጃ ቤት ገብታ በሩቅ እያለችም – ለብልግናየ ይቅርታና – ለውሽማዋም ይሁን ለምትፈልገው ማንኛውም ሰው ቦታ ለማሰጠት፣ መብራት ለማሰጠት፣ የንግድ ፈቃድ ለማሰጠት፣ (እንዳስፈላጊነቱ ተመላሽ ሊደረግ ወይ ላይደረግ የሚችል) የባንክ ብድር ለማሰጠት፣ በመንግሥት ወጪ ረጃጅም የስልክና የውኃ መስመር ለማዘርጋት፣ የፈለገችውን ለማሾም ወይም ለማሻር፣ ንጹሕን ሰው ካለበደልና ጥፋቱ ዘብጥያ ለማስወረድ፣ በጥፋቱ የታሠረን በቅጽበታዊ ጣልቃ ገብነት ለማስለቀቅ፣ የዜጎችን ሀብትና ንብረት በሕግ ሽፋን ለማዘረፍና ለራሷ ካምፓኒዎች ወይም ለመሰላት ለማሰጠት፣ በነባርና አዳዲስ የአክሲዮን ካምፓኒዎች ራሷን በአባልነትና በቦርድ ሰብሳቢነት ለማስገባት፣ ወዘተ. ታደርገው የነበረውና አሁንም ከማድረግ የማትመለሰው አቅል ያጣ ሩጫ በሕዝብ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ሴትዮዋ ለገንዘብና ለእንትን ሲሏት ገደል እንደምትገባ የሚያውቋት ይመሰክራሉ – አጉል ተፈጥሮ፤ ከምን ዓይነት ሥጋና ደም ተፈጥራ ይሆን ወገኖቼ? በዚህ ዓይነቱ ለከት የሌለው የገንዘብና የሀብት ፍቅሯ ነው እንግዲህ ሰውዬውን ቤተ መንግሥት ውስጥ እንደውሻ አሥራ በርሱ ስምና በርሷ ድፍረት ባጠራቀመችው ንዋይ ከዓለም መሪዎች መለስን በሀብት የሚበልጠው እንዳይገኝ ከፍተኛ ጥረት ላይ የነበረችው – በየባንኩ ብዙ ገንዘብ ታቁር የነበረችው፣ በየዓለም ማዕዘናት ብዙ ቤቶችንና የንግድ ተቋማትን ትመሠርት የነበረችው፣ በፍቅረ ንዋይ መታወሯ እንዳንዳች እያደረጋት እንዲያ ዐይን ባወጣ መንገድ ትዝብት ላይ ወድቃ የነበረችው፡፡ ይህች በገንዘብና በእንትን ፍቅር ያበደች የድብቁ ቢግ ብራዘር ተወዳዳሪ ሴት አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ብትገባ ምን ተዓምር ልትሠራ እንደምትችል ገምቱ – የምን መገመት ነው – ፍንትው ብሎ እየታዬ! የስንቱን ቤት እንደምታፈናቅልና ባወጣ እንደምትሸጥ፣ ስንቱን የኪስ ቦታ እንደምትቸበችብ፣ እንደ አንደኛው ባሏ ‹የዐይናችሁ ቀለም አስጠላኝ› እያለች ስንቱን ምሥኪን ሰው ከሥራና ከደመወዝ እንደምታግድ፣ እንደምታሳስርና ደብዛ እንደምታስጠፋ፣ ስንትና ስንት የሀገር ማፈሪያ ወንጀልና የቁጭ በሉ አሣፋሪ ድርጊቶችን እንደምትሠራ፣ ስንቱን ኮበሌ ካልተኛኸኝ እያለች ከትዳሩና ከጤናማ ኑሮው እንደምታፈናቅል (“አሮጊት ለምኔ! ገንዘብና ሥልጣን ባፍንጫየ ይውጣ!” ብሎ አሻፈረኝ የሚልን መቀመቅ እንደምታወርድ)፣ … በበኩሌ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል – እባካችሁን ‹ህልም እልም› ብለን ሁላችን እናማትብበት፡፡ አዜብ ብሎ ከንቲባ? ወያኔ ይህን ካደረገ በርግጥም ራሱን ለማጥፋት ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ አቋም ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ይህችን የአጋንንት ውላጅ የባንዳ ልጅ ማሳረፍ ይገባል – በሰላም፡፡ በቃ – በመለስ ቀብር እንዳለችው ልጆቿን በማሳደግ ፈተና ላይ ብቻ ታተኩርና በዚያው ትታይ፡፡
አዜብ በሌብነቷ አይደለም ሹም አትሁን እያልኩ የምከራከረው፤ በሌብነቷ ከሆነ መብቷ ነው፡፡ ዓለማችን በሌቦችና አጭበርባሪዎች የተሞላች በመሆኗ የርሷ ሌባ መሆን እንግዳ ነገር አይደለም – በአመራርም ሆነ በተራ ዜጋነት ሌባና አጭበርባሪ ሀገር ምድሩን ሞልቶታል፡፡ አዜብ በተፈጥሯዊ ደመ ሞቃትነቷና ያንንም ተከትሎ በጉልህ ስለሚንጸባረቅባት የሴሰኝነት ጠባይዋ አይደለም ሹም እንዳትሆን የምመኘው፡፡ ያም መብቷ ነው – ካልሰለቻት እንኳንስ ነባር ታጋዮችን አዳዲሶቹንና እምቦቀቅላ ታጋዮችንም ታነባብራቸው፡፡ አዜብም ሆነች ቤቲ በተፈጥሮ የተሰጣቸውን መብት እስከፑንት (ላንድ) ቢጠቀሙበት የነሱ ጉዳይ እንጂ የማንም ራስ ምታት ሊሆን አይገባም፡፡ እኔን ክፉኛ የሚያሳስበኝ ድንበር የማያውቀው ውሸቷ ነው፡፡ በተራ ቃል ‹ውሸታም› መባል በፍጹም አይመጥናትም፡፡
በባህር ዳሩ የወያኔ ስብሰባ የተናገረችው ውሸት ስለሷ ባሰብኩ ቁጥር ስለእውነት በጣም ያመኛል፡፡ በዚያ ስብሰባ ‹መለስ ከዓለም መሪዎች በደመወዙ ብቻ ቤተሰቡን እያሰቃየ የኖረ ብቸኛው መሪ ነው፤ ከስድስት ሺ ብር ደመወዝ ለኢሕአዲግ ተቆርጣ በምትደርሰው አራት ሺህ ምናምን ብር ወርን ከወር እየጣጣፍን በመከራ ሲያኖረን የነበረና አእምሮውን ብቻ ይዞ የተወለደ… ይህ ሊሠመርበት ይገባል ፤ ሰው የሚለው አይደለም – እርሱ በዚያች ትንሽ ደመወዝ ብቻ ኖሮ ያለፈ የተለዬ መሪ ነው…› እያለች የቀላመደች ዕለት ስለርሷ ጨረስኩ፡፡ ስለርሷ ብቻም አይደለም፡- ስለወያኔ/ኢሕአዴግም ያኔውን ጨረስኩ፡፡ አንድ አንጋፋ ድርጅት ያን የመሰለ በሬ ወለደ ዓይነት ነጭ ውሸት ሰምቶ እርምጃ አለመውሰዱ ገርሞኛል – የዚያን ድርጅት የለዬለት ባዶነትም አረጋግጫለሁ፤ የሴትዮዋ ንግግር እውነትነት ቢኖረውም እንኳን የሀገርንና የድርጅትን ምስል በማጠየም ረገድ ቀልማዲት ያደረገችው ነገር እጅግ ሰቅጣጭ በመሆኑ በሕይወት የመኖርን መብት ሳይጨምር ከብዙ ነገር ልትታገድ በተገባት ነበር፡፡ ሕዝብ በሆነ ምክንያት በይሁንታ አፉን ቢለጉም እውነት እንዳይመስላቸው፡፡ ሕዝቡ በዕውቀት ከነሱ ስለሚበልጥ በዚያን ሰሞን ይህን የአዜብን የድህነት ወሬ የቡና ማጣጣሚያ ነው ያደረገው – ሳይጠማን እየጠጣን ብዙ ቡና ፈጅተንበታል – ጊዜው ሲደርስ ይህንን ኪሣራችንንም ታወራርዳለች፡፡ የዚህች ቀልማዳ ሴት ንግግር በአሣፋሪነቱና አጸያፊነቱ በሺዎች ዓመታት አንዴ እንደሚያጋጥም እጅግ ነውረኛ አነጋገር ሊወሰድ ይችላል፡፡ የርሷ ስህተት እንደግለሰባዊ ስህተት ተቆጥሮ በዝምታ ሊታለፍ ይችላል፡፡ የወያኔው ድርጅት በፍርሀት ይሁን በሌለው ይሉኝታ እርሷን በዝምታ ማለፉ ግን ይቅር የማይባል ታሪካዊ ህፀፅ ነው፡፡ ለነገሩ አሁንም ብዙም አልረፈደምና የሴትዮዋን ተፈጥሮ የምታውቁ ወያኔዎች እባካችሁን አንድ ነገር አድርጉ – ለናንተው ስትሉ፡፡ እኛ ሁሉንም ለምደነዋልና ስለኛ ብላችሁ እንደማትጨነቁ እናውቃለን፡፡ ሀፍረቱ ይበልጡን ለእናንተው ስለሆነ አዜብን ግዴላችሁም ተዋት፡፡
ቁጭ ብዬ በእርጋታ ሳስበው ሕዝብንና የታሪክ ፍርድን ንቆ ይህችን ሴት ባለሥልጣን ማድረግ የኋላ ኋላ ኢሕአዴግን ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍለው ይመስለኛል፡፡ እናም ኢሕአዴግ ለክብሩ ሲል – ክብር ካለው ነው ለዚያውም – አለበለዚያም ውርደቱን ቅጥየለሽ ላለማድረግ ሲል ይህችን ሴት ከማዘጋጃ ቤት ሹምነት የዕጩ መዝገብ ይፋቃት፡፡ እኔ ውርድ ከራስ ብያለሁ፡፡ ሰውን መናቅ ፈጣሪን መናቅ እንደሆነ ለሃይማኖት የለሹ ወያኔ መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ እርግጥ ነው – በአምባገነኖች ዘንድ ማይምንና እንደጤናማ ሰው ማሰብ የማይችልን አጋሰስ መሾም የተለመደ ነው፡፡ ሲበዛ ግን ያንገሸግሻል፡፡ ሕዝብ ስቆ ቢያልፈው የውሻን ደም መና የማያስቀረው ፈጣሪ፣ አይደለም ይህችን በሰው ቋንቋ ከመናገሯ ውጪ ከውሻ ብዙም የማትለየው ሴት ትቅርና ሂትለርንና ሙሶሊንን የመሰሉ ለሰማይ ለምድር የከበዱ አምባገነኖችን አይቀጡ ቅጣት አከናንቦ በጭቁኖች መሃል አዋርዷቸዋል፡፡ ይህች መናኛ ሴትም ከወያኔ ጋር የምትዋረድበት ዘመን እየመጣ ቢሆንም ማምሻም ዕድሜ ነውና ማሰብ ያልተሳናችሁ በጣት የምትቆጠሩ ወያኔዎች ካላችሁ የዛሬን ማሩን፤ ቀድሜ እንደገለጽኩት ውርደቱ የጋራችን ነው፡፡ ይበልጡን ግን – ልድገምላችሁ – የእናንተው ነው፡፡ ሴትዮዋን መሾማችሁ የግድ ከሆነ ብትፈልጉ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጓት፡፡ ያ ቦታ ከሕዝብ የራቀ በመሆኑ አንገናኝምና እንደፍጥርጥራችሁ፡፡ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ግን ሺዎችን በየቀኑ የሚያስተናግድ የሕዝብ መናኸሪያ በመሆኑ ባለሥልጣናቱ የሕዝብን ቀልብ እንደነገሩም ቢሆን የሚስቡ መሆን አለባቸው፡፡ ይህች ሴት እኮ አርከበ ዕቁባይ ለሕዝብ ጥሩ ሠራ በመባሉና ሕዝብም በተወሰነ ደረጃና በግል አበርክቶው ስለወደደው በዚያ ቀንታበት ኤች አይ ቪ ሲመረመር የሚያሳየውን ቢልቦርድ በተሰቀለ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንዲወገድና ከዕይታ እንዲሠወር አድርጋለች፡፡ የባል ተብዬው የመለስና የሚስት ተብዬዋ የአዜብ የክፋት ደረጃ እንግዲህ እስከዚህ የወረደና ከአንድ ተራ ዜጋ እንኳን የማይጠበቅ ነው – ለቅጣት መምጣታቸውን በበኩሌ አምናለሁ፡፡ ተራ ዜጋ ምቀኛና ቀናተኛ ቢሆን ምንም አይደለም፡፡ የአንድን ሀገር በትረ ሥልጣን የጨበጠ ቁንጮ ያገር መሪና ሚስቱ ግን እንዲህ ያለ በራሱ በመለስ ወራዳ የቋንቋ አጠቃቀም ለመግለጽ እንዲህ ያለ ወራዳና ልክስክስ ጠባይ ሲያሳዩ የሀገርን አጠቃላይ ውድቀት ነው በጉልህ የሚያስረዳን፡፡ ያልዘሩት መቼም አይበቅልም፡፡ የዘራነውን እያጨድን ነን፡፡
ለማንኛውም አዜብን በከንቲባነት መሾም – ምክትልም ሆነች ዋና ለውጥ የለውም – የሚያስከትለው አደጋና ውርደት ታስቦበት በጊዜ አንድ ነገር እንዲደረግ የዜግነት ጥሪየን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡
በሌላም በኩል ይሄ ለይምሰል ያህል በብሔረሰብ ተዋጽዖ አንጻር የሚደረገው ሹመት ይቁም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ማንም አያምንም – ይህን ያረጀ ያፈጀ ሥልት አንቀልባ ውስጥ ያለ ጡት ያልጣለ ሕጻንም ያውቀዋልና፡፡ እኔ ለምሳሌ በደመቀ መኮንን መሾም ምክንያት አልተደሰትኩም፡፡ አንደኛውና ትልቁ ነገር እንደውሻ አጥንትና ደም አላነፈንፍም፡፡ በብቃትና በችሎታ ከሆነ ሁሉም የሚኒስትር ካቢኔ ከኮንሶና ከሙርሲ ቢሆን ሃሳቡ አይበላኝም፤ ወያኔንም የጠላሁት በመጥፎ ድርጊቱ እንጂ በተሹዋሚዎች የዘር ሐረግ አይደለም – በጭራሽ፡፡ ሁለተኛ የደመቀ መሾም ስሜትን በማይነካ የቃላት አጠቃቀም ለየዋሃን አማሮች ካልሆነ በስተቀር መሬት ላይ የፈጠጠውን ኢትዮጵያዊ እውነት ለሚረዳ ሰው ‹አማራ ተሾመልኝ!› በሚል የሚያስፈነጥዝ አይደለም፡፡ ራሱን ከጥቃት የማያድን አማራ፣ የራሱ ናቸው የተባሉ ወገኖችን ጥቃትና እንግልት ለማስቆም አንዳችም ተሰሚነት የሌለው በድንና ገልቱ ሰውዬ ተሾመልኝ ብዬ ጮቤ የምረግጥ ሞኝና ተላላ መስዬ ከታየኋቸው – አዝናለሁ – ሞኞቹ እነሱ እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡ ደመቀን መሣይ ከረፈፍ ሆዳሞች በሥርዓቱ ውስጥ ወይነው ገብተው ሀገሪቱን ምን ያህል እየጎዱ እንደሆነ ማስታወስም ተገቢ ነው፡፡ በጣም የምወደው ኦባንግ ሜቶ ቅድም ሲናገር እንደሰማሁት ሁልጊዜም እኔ ራሴ እንደምለው ወያኔ ማለት በዘርና በቋንቋ ተወስኖ ወይም ተቀንብቦ የተቀመጠ አለመሆኑንም መረዳት ይገባል፡፡ መነሻውና አስኳል አመራሩ ከትግራይ ይሁን እንጂ ለዚህ የወያኔ ሥርዓት ማበብና ማፍራት ዋና ተባባሪዎቹ ትግሬ ያልሆኑ የተጋቦት ወያኔዎች መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ ግን ግን “የምታሸንፈውን ምታ ቢሉት ወደ ሚስቱ ዞረ” እንዲሉ ሆኖብን አንዴ የፈረደበትን የትግራይ ሕዝብ ብዙዎቻችን እንወርድበታለን፡፡ በበኩሌ አሁን እየሆነ ባለው ነገር ሁሉ የእያንዳንዳችን ልብ ሳይሰበር ነገ ይቅርታ እንደምንባባልና አብሮነታችን ካለሣንካ እንደሚቀጥል በሙሉ ልብ አምናለሁ፡፡ ንዴትና ብስጭት የማይፈጥረው አእምሮኣዊ ምስል ባለመኖሩ ደመናው ሲጠራና እውነት ስታሸንፍ አሁን ችግር የሚመስሉን ብዙ ነገሮች ከላያችን ላይ ተገፍፈው ይጠፋሉ፤ ያለ ነገር ነው – በዚህን መሰሉ ጊዜ የሚያጋጥም ብዙ ነገር አለ፡፡ መምሰልና መሆን ስለሚለያዩ የደፈረሰው ሲጠራና የሰላም አየር በሀገራችን ሰማይ ሲያረብብ የግጭትና የሁከት እርኩሳን መናፍስት ተጠራርገው ይወገዳሉና ስለነገው ከመጠን በላይ አንጨነቅ፡፡ የወቅት ንፋስ የሚፈጥራቸው ብዙ አላፊ ክስተቶች አሉ – በኛ ብቻ ሳይሆን በየሀገሩ፡፡ ሁሉም እንደሚያልፍ መረዳትና ለዚያ በርትቶ መታገል እንደሚገባ ተረድተን በወንድማማችነትና በእህትማማችነት ተባብረን ይህን የለያየንን ቆሻሻ ሥርዓት ለማስወገድ አብረን መታል ብቻ ነው የሚያዋታን፡፡ አለጥርጥር ሥርዓቱ ይወድቃል – ችግሩ በጣም ብዙ ምናልባትም ከእስካሁኑ የከፋ ቨስጠሊታ የታሪክ ጠባሳ ሳይተው የሚወድቀው እንዴት ነው? የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉም ምክክር፣ ትብብርና ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ እውነት ምን ጊዜም ከእውነት መንገድ ለማትወጣው ነገር በመለያየት አዲስ ግን በወያኔያዊ ትልምና ዐቅድ የተለወሰና በፀረ-ኢትዮጵያነት የተመረዘ ታሪክ ለማስመዝገብ የምንቻኮል ሰዎች ካለን ቆም ብለን እንድናስብ በእገረ መንገድ ጠቆም ባደርግ ደስ ይለኛል – ከወያኔ ብዙ ነገሮችን መማር እንችላለን፡፡ የሕዝቡ ችግረና ፍላጎት ይግባን፡፡ ‹ሕዝቡ ምን ይላል? ምንስ ይፈልጋል ?› ብለን እንራመድ እንጂ በየግል ፍላጎታችን የተጓዝን ተሳስተን አናሳስት፤ ታሪክም ይቅር አይለንም፡፡ መደማመጥ ለመልካም የጋራ ስኬት ጠቃሚ መሆኑን እየዘነጋን ለየህልማችን እውን መሆን በተናጠል ስንሮጥ የዓለም ፍጻሜ ተቃረበ፡፡
ማንዴላ እጅ ሆነዋል፡፡ ምናልባትም ይህች ጽሑፍ በአንዱ ድረ ገፅ ከመለጠፏ በፊት አንዳች ነገር ሊከሰት ይችላል፤ ወይም በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ዜና ዕረፍታቸውን እንሰማ ይሆናል – ለነገሩ ‹እግረ ቀጭን እያለ እግረ ወፍራም ይሞታል› እንዲሉ ከማንዴላ በፊት ለምሳሌ እኔ ራሴ ልቀድም እችላለሁ፡፡ የወደፊቱን ያለማወቃችን ምሥጢር ነው ሕይወትን ትርጉም ያላት እንድትሆን ያደረጋት፡፡ ተስፋ ባትኖር ሁሉም በቁም እንደሞተ ያህል ነው – ጧት ከቤቱ በሰላም የወጣ ሰው ማታ ሬሣው ወደቤቱ ሊመለስ እንደሚችል ቢያውቅ ማንም የመኖር ጉጉት አያድርበትም – የእግዜሩም እንበለው የተፈጥሮ ጥበብ መገለጫም ይሄው ነው – ስለወደፊቱ አለማወቅ፡፡ በዚህም አለ በዚያ በማንዴላ ሁኔታ ዓለም በጭንቀት ላይ የምትገኝ ትመስላለች፡፡ ጭንቀቷ ግን ለማንዴላ ለራሱ እንዳይመስላችሁ፡፡ ምሥጢሩ ወዲህ ነው፡፡(በነገራችን ላይ ‹ድኅረ ገፅ› የምንል ሰዎች ‹ድረ ገፅ› ማለትን ብንለምድ ደስ ይለኛል፡፡ ‹ድኅረ› ማለት ‹በኋላ›(post) ማለት እንደሆነና ‹ድረ› የሚለው ቃል ግን ‹ድር› ከሚለው የአማርኛ ቃል ተወስዶና ከ‹ገፅ› ጋር ተጋምዶ ‹website› የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል እንዲተካ መደረጉን ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ ዕውቀት አይናቅምና በተለይ ድረ-ገፆች እባካችሁን ይቺን ነጥብ አትናቋት፡፡ መናደድ ሲያምረኝ ከምናደድባቸው ነገሮች አንደኛዋ ይህች ነች፡፡ )
የዓለም ሕዝብ አንድ አባሉ ከ94 ዓመታት በላይ በመሬት ላይ እየኖረ እንዲሰቃይ የሚፈልግ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰዎች እስከዘላለሙ እንዲኖሩ የሚፈለግበት ምኞት – ከልብ ስለመሆኑ ማወቅ ቢያስቸግርም – በብዛት የሚታየው በኛይቷ ሀገር በኢትዮጵያ ነው፡፡ የመቶ ሃያ ዓመት ሽማግሌ ሲሞት ፊት የሚነጨው በሌላ ሀገር አይደለም – በኢትዮጵያ ነው – ሊያውም ይበልጡን በአማራው አካባቢ፡፡ ባህላችን ከኛ ወቅታዊ ግንዛቤ በልጦ የሚገኝበትን ሁኔታዎች አንዳንዴ እንታዘባለን፤ ከአንዳንዴም በላይ እንዲያውም፡፡ ለዚህም ነው በዛሬዋ ውሎየ እንኳ ሁለት ተቃራኒ ጸሎቶችን የታዘብኩት – አንድ ከኢትዮጵያውያን፣ አንድ ከደቡብ አፍሪካውያን፡፡ መቼም እኛ ከነሱ በልጠን እግዜሩ ለማንዴላ የማቱሳላን ዕድሜ እንዲሰጥልን ልንጸልይ እንደማንችል ቢያንስ ኅሊናችን ያውቃል – እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፡፡ ይህ ምን ያሳያል? ፊት ለፊት የሚታየው ባህላችን ለሰው መጥፎ የማይመኝ መሆኑንና በብዙ ነገር ከሌሎች የምንለይ ሕዝብ መሆናችንን ነው ለዓለም እያስመሰከርን የምንገኘው – ምነው እውነተኛና በምንም ዓይነት ማዕበል የማይናወጥ አቋም ባደረገልን!
ማንዴላ እንዳይሞት የምንፈልግበት ምክንያት ግልጥ ነው፡፡ ዓለማችን በሰው እጦት ምች ስለተመታች ጥሩ ሰው ስናገኝ እንደብርቅ እናየዋለን፤ ሞት እንዳይነጥቀንም እንሳሳለታለን፤ እስከወዲያውም አብሮን እንዲኖር እንመኛለን – ትውልድ ቢያልፍም ከቀጣዩ ትውልድ ጋር፡፡ ብዙ ደጋግ ሰዎች ቢኖሩን ኖሮ የዓለም ሕዝቦች ትኩረት በአሁኑ ሰዓት ያለቪዛና የትራንስፖርት ወጪ ደቡብ አፍሪካ ሄዶ ፕሪቶሪያ ሆስፒታል ዙሪያ ባልከተመ ነበር፡፡ ጥሩ ሰው ብርቅ በሆነበት ዘመን መፈጠር እንዴት መታደል ነው! መለስም እንዲያ የተንጫጫንለት እኮ የርሱን አእምሮ ይዞ የሚወለድ – እንደአዜብ አነጋገር በዓለም የአንጎል ገበያ ተመራጭ ጭንቅላት ይዞ በሺዎች ዓመታት አንዴ የሚወለድ ዐዋቂና ታዋቂ በመሆኑ ነው፡፡ እኔ ለመለስ የነጨሁት ፊት እስካሁን አላገገመም፤ የምለብሰውም ማቅ ከላየ ላይ አልወረደም፡፡ እርግጥ ነው – ይበልጡን ለክፋት ቢጠቀምበትም መለስን በዕውቀቱ መቀጣጠብ አይቻልም፤ ሰይጣን ለዘዴው ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል እንደሚባል መለስም የነበረው ሁለገብ ዕውቀትና ብልጣብልጥ ተፈጥሮ ከብዙዎች መሪዎች ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ የኔነህ ሳይለኝ ቢሞትም የኔነው ማለት ወጪ የለውምና ሳልወድ በግዴ የኔነው ብዬ ብቀበለው ከሚኮሰኩሰው ኢትዮጵያዊነቱ አንጻር ብቻም ሳይሆን ከአጠቃላይ ስብዕናው የሚፈልቁ ብዙ የሚደነቁ ሰብኣዊ ተሰጥዖዎች እንደነበሩት አልክድም – አጭበርባሪው፣ አስመሳዩና መልቲው መለስ ዜናዊ፡፡ ግን ተሰጥዖዎቹን ለተንኮልና እንደሥራየ ቤት ነገርን በመጠምዘዝ ሕይወቱን ጨርሶ ዕውቀቱን ሳይጠቀምበት ሞተና ዐርፎ ዐሣረፈን፡፡ በሚስቱ ሲንገበገብ የነበረ አንድ ፈላስፋ መቃብሯ ላይ እንዲህ የሚል ጽሑፍ አስፍሯል አሉ፡- My wife lies here; let her rest in peace, so do I.
አትታዘቡኝ፡፡ በበኩሌ ማንዴላ እንዲያርፍ እጸልያለሁ – በሰላም ማረፍ ለኔ አይገባኝም – ሰው እየሞተ ምን ሰላም አለና፤ ማንዴላ በ‹ሰላም› እንዲያርፍም በ‹ሰላም› እንዲድንም ከጸሎት ጀምሮ ሁሉም ነገር ቢደረግም እስከዚች ሰዓት ድረስ አልዳነም ወይም አላረፈም፤ የዚህን ደብዳቤ የመጀመሪያ ረቂቅ ስጽፍ – አሁን ሰዓቱ ከሌሊቱ ስምንት ገደማ መሆኑን ልብ ይሏል – የማንዴላ የጤና ሁኔታ እንደሰሞኑ ሁሉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው የሚገኝ፤ ከአሳሳቢነቱም የተነሣ ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ ሊያደርጉት የነበረውን የሀገር ውጪ ጉዞ እስከመሠረዝ ደርሰዋል፡፡ ዕንቁ ልጃችን – ብርቅዬ የአፍሪካ ብቻ ሣይሆን የዓለማችን ልጅ ማዲባ ሲያርፍ ደግሞ ነፍሱ በማኅተመ ጋንዲና በእማሆይ ተሬዛ፣ በአብርሃምና በያዕቆብ ነፍሳት አጠገብ እንድትቀመጥ የቸሩ እግዚአብሔር ፈቃድ ይሆን ዘንድ የሁላችንንም ጸሎት እኔም በበኩሌ እጸልያለሁ፡፡ ይቅርታችሁን – ቀደም ብዬ ማዲባን በአንቱታ የጠራሁት ብዙ ሰው ያለው እኔስ ለምን ይቅርብኝ ብዬ ከሰው ለመመሳሰል ነው፤ ስጨርስ በአንተ የጠራሁት የሕዝብ ሰው አንቱ እንደማይባል ስለምረዳ የአንጀቴን ነው – የሕዝብ ሰው ማለት ደግሞ የሚፈቀርና የሚወደድ ማለት ነው፡፡ አብንና ወልድን ማን አንቱ ይላል? ቅድስት ማርያምንስ? ኧረ መለስ ዜናዊንስ ማን በአንቱታ ጠርቶት ያውቃል? የሕዝብ ሰው ማለት እንዲህ ነው – ቺንዋ አቼቤ A man of the people የሚል ርዕስ ለአንድኛው መጽሐፉ የሰጠው እኮ ለነማንዴላ ዓይነቱ መላ ሕይወታቸውን ለራሳቸው ጥቅም መስዋዕት ላደረጉ ሣይሆን ለነመለስ ዜናዊ ዓይነቱ ለቤት ቀጋዎች ለውጭ አልጋዎች ነው፡፡ ዓለም ግን ምን ዓይነት የዕንቆቅልሽ ምድር ናት ጎበዝ?!
ውድ ማንዴላ ሆይ! ሁልጊዜ ከኅሊናችን አትጠፋም – በአካል ብትለየን በመንፈስ ምንጊዜም አብረኸን አለህ – ከአሁኑም ከወደፊቱም ትውልዶች ጋር፤ ፈጣሪ አንተን እንደወሰደ በምትክህ ለዓለም ሰላም የሚተጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቅን አሳቢ ዜጎችን እንዲልክልን ስትሄድ አሳስብልን፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግልህ፡፡ የሁለት ወር ሀገርህን ኢትዮጵያንም በፈጣሪ ፊት አስባት፡፡ ስቃይና ጣር ሳይበዛብህ በቶሎ ሂድልን፡፡ በዚህች አንተን ሳይቀር ለ27 ዓመታት በእሥር ባንላታች የእርጉማን ምድር ከአሁን በኋላ ለሴከንድም መቆየቱ መከራና ስቃይ መጨመር እንጂ ጤናውም ጤና አይሆንህም፡፡ ሰዎች ስንባል ራስ ወዳዶች ነን፤ ‹ቆይልን› የምንልህ በአንተ ስቃይ የኛን ‹ኢጎ› ለማስደሰት እንጂ አንተ አልጋ ላይ ውለህ የመከራ ቀናትንና ሌሊቶችን በእዬዬ ማሳለፍህ፣ በድጋፍ ሰጪ የሕክምና ቴክኖሎጂ እየታገዝክ ካለ እንቅልፍ መቆየትህ አንዳችም ነገር አይፈይድልንም – ለአንተም ለእኛም፡፡ በሀገሬ ሰው ይሙት ተብሎ እንደማይጸለይ አውቃለሁ ማዲባየ – ግን ‹ይህን አለ› ተብዬ ኩነኔ መግባቱን እመርጣለሁ እንጂ ስትሰቃይ ለማየት ከእንግዲህ ቆይልን አልልህም፡፡ በቃ፡፡ በሰላም ሂድልን፡፡ ስትመጣ እንደምትሄድ ይታወቅ ነበር፡፡ እኛም በሕይወት አለን የምንል ወገኖችህም ወረፋችንን ጠብቀን እንከተልሃለን፡፡ ዱሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው መባሉም ለዚህ ነው፡፡ ይብላኝ ለኛ ግና፡፡ በጅቦችና በእሪያዎች መካከል እንደተጣልን ተለይተኸን ለምትሄደው ለኛ ይብላኝ እንጂ አንተማ ከፋም ለማም 95 የሚጠጉ ክረምቶችን ለሕዝብህ ስትል ከአፓርታይድና ከመጥፎ ግላዊ ገጠመኞችህ ጋር ስትፋለም ኖረህ አሁን በመጨረሻው ሥጋዊ ሽንፈትህ ደረጃ ላይ ደርሰሃል፡፡ በዚያች በደቡብ አፍሪካዊቷ አዜብ እንኳን ያየኸውን አበሳ ማን ይረሳዋል? ብቻ ሆድ ይፍጀው ማዲባየ፡፡ እዚያው እስክንገናኝ ደህና ሰንብትልኝ፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያና ሕዝቧ፤ በዚህ ዓለም አቀፍ ሀዘን መጽናናት ለሚያስፈልገው ሁሉ ፈጣሪ እንዲያጽናናው እመኝለታለሁ፡፡
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=4791

No comments:

Post a Comment